ምዕራፍ 8
“የሰላሙ መስፍን” “ደስታ” ተካፋይ መሆን
1. (ሀ) አንድ ሰው ወደ ሌላ አገር የተጓዘው በምን ምክንያት ነበር? (ለ) በቀጥታ ባይገለጽም እንኳ የኢየሱስ ምሳሌ የሚጠቍመው ምን ነገር አለ?
ኢየሱስ በሰጠው የመክሊት ምሳሌ ውስጥ ከብር የተሠሩ ስምንት መክሊቶች ባለቤት የሆነው ሰው ወደ ሌላ አገር የሄደው እንዲሁ የሽርሽር ጉዞ ለማድረግ አልነበረም። ወደ ሌላ አገር የሄደው ለቍምነገር ነበር። አንድ ውድ የሆነ ነገር ለማግኘት ፈልጎ ነበር። ምሳሌው እንደሚያሳየው ወደ ሌላ አገር የሄደው ከሌሎች “ብዙ ነገሮች” ጋር አንድ ዓይነት “ደስታ” ለማግኘት ነበር። (ማቴዎስ 25:21) ስለዚህም ይህንን የተለየ ደስታ ለሚሰጠው ጥያቄ ለማቅረብ ሰፋ ያለ ጊዜ የሚጠይቅ የረጅም እርቀት ጉዞ ማድረግ ነበረበት።
2. (ሀ) ኢየሱስን በሚመለከት የሃብታሙ ሰው ወደ ሌላ አገር መጓዝ ምንን ያመለከታል? እርሱስ የሄደው ወደ ማን ነበር? (ለ) ጌታው ይዞ የተመለሰው ምንድን ነው?
2 በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሰው ሀብታም ሰው ኢየሱስ ክርስቶስን ስለሚያመለክት ሰውየው ረጅም ጉዞ ለማድረግ ወደ ሌላ አገር መሄዱ ኢየሱስ ከፊቱ የሚጠብቀውን ደስታ ወደሚሰጠው አምላክ መሄዱን ያመለክታል። ታዲያ እርሱ የሄደው ወደ ማን ነበር? ዕብራውያን 12:2 ይነግረናል:- “የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፣ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሶ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧልና።” አዎን በእርግጥም የዚያ ደስታ ምንጭ ይሖዋ አምላክ ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ ላሉት ታማኝ ደቀመዛሙርቱ “መክሊት” በአደራ በመስጠት ትቷቸው የሄደው ወደ እርሱ ነበር። ጌታው ለሦስቱ ባሮች ስምንት መክሊቶችን በሰጠበት ጊዜ ያልነበሩትን ሌሎች “ብዙ ነገሮች” ይዞ ተመለሰ። ቀደም ብሎ ኢየሱስ የሰጠው ምሳሌ ማለትም ‘የአሥሩ ምናን’ ምሳሌ እርሱ ይዞ የተመለሰው ‘ንጉሣዊ ሥልጣንን’ እንደሆነ ይገልጻል።— ሉቃስ 19:12–15 አዓት
3. በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የዘካርያስ 9:9 ትንቢት መፈጸም ሲጀምር ምን ዓይነት ጊዜ ነበር?
3 አዲስ የተሾመ ንጉሥ ደስተኛ የሚሆንበት ምክንያት አለው፤ ታማኝ ተገዥዎቹም እንደዚያው ለመደሰት ምክንያት ይኖራቸዋል። የአምላክ ልጅ በዘካርያስ 9:9 ላይ የሚገኘውን ትንቢት ለመፈጸም እየጋለበ ወደ ኢየሩሳሌም የገባበትን ጊዜ እናስታውሳለን። የዚያን ትንቢት ፍጻሜ በተመለከተ እንደዚህ ተጽፎአል:- “ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፣ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቆረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር። የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም:- ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ [በይሖዋ (አዓት)] ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሳዕና በአርያም እያሉ ይጮሁ ነበር። ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ መላው ከተማ:- ይህ ማን ነው? ብሎ ተናወጠ።”— ማቴዎስ 21:4–10፤ በተጨማሪም ሉቃስ 19:36–38 ተመልከት
4. ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ “ባሮቹን” ወደ አስደሳች ሁኔታ ለመጋበዝ ልዩ ምክንያት የነበረው ለምንድን ነው?
4 እርሱ ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ራሱን በይሖዋ መንፈስ ለንጉሥነት እንደተቀባ ብቻ አድርጎ ያቀረበበት ወቅት የደስታ ጊዜ ከነበረ በአሕዛብ ዘመን ፍጻሜ በ1914 ንጉሥ ሆኖ ሲሾም ምን ያህል የበለጠ ደስታ ሆኖ ነበር? ይህ ለእርሱ በጣም አስደሳች ጊዜ ነበር። በእርግጥም በዚያን ጊዜ ከዚያ በፊት በፍጹም ታይቶ ወደማይታወቅ ደስታ ገብቶ ነበር። ስለዚህ ሂሳቡን ከእነርሱ ጋር በሚተሳሰብበት ጊዜ ‘በጎና ታማኝ’ ብሎ ለጠራቸው ደቀመዛሙርቱ:- “በጥቂቱ ታምነሃል፣ በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” ሊላቸው ችሎ ነበር። (ማቴዎስ 25:21) ተቀባይነት ያገኙት “ባሪያዎቹ” አሁን ሊካፈሉ የሚችሉበት አዲስ ደስታ መጥቶ ነበር። እንዴት ያለ ሽልማት ነው!
5. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቶስ “አምባሳደር” ሲሆን ሁኔታዎቹ እንዴት ያሉ ነበሩ? (ለ) ይሁን እንጂ ዛሬ ቅቡዓን ቀሪዎች የክርስቶስ “አምባሳደሮች” የሆኑት ምን አዲስ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ በኋላ ነው?
5 በመግዛት ላይ ያለው ንጉሥ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅቡዓን ደቀ መዛሙርት በ1919 ተቀባይነት ወደሚያገኙበት ሁኔታ ገብተው ነበር፤ ይህም ከፍተኛ ደስታ አመጣላቸው። ከአሥራ ዘጠኝ መቶ ዘመናት በፊት ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ጓደኞቹ ስላላቸው ከፍተኛ ቦታ ሲነግራቸው “ስለ ክርስቶስ መልዕክተኞች [አምባሳደሮች] ነን” ብሎ ጽፎላቸው ነበር። (2 ቆሮንቶስ 5:20) ይህ የተጻፈው ኢየሱስ ገና “መንግሥተ ሰማያትን” ለመቀበል ሕጋዊ ወራሽ ብቻ ሆኖ በተስፋ በሚጠባበቅበት ጊዜ ነው። (ማቴዎስ 25:1) ስለዚህም በዚያን ጊዜ በአባቱ ቀኝ መቀመጥና የሚሾምበትን ቀን መጠበቅ ያስፈልገው ነበር። ይሁን እንጂ ሞገስ ያገኙት ቀሪዎች አሁን ከ1919 ወዲህ “አምባሰደሮች” በመሆን እየገዛ ባለው ንጉሥ ተልከዋል። (ዕብራውያን 10:12, 13) ይህ እውነታ በ1922 በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ በተደረገው ስብሰባ ላይ ለዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተገልጾላቸው ነበር።
6. “መክሊት” የተሰጣቸው ሰዎች ከጦርነቱ በኋላ ያደረጉአቸው ጥረቶች በመጀመሪያ ወደ ምን ዓይነት ሥራ ያተኩሩ ነበር?
6 ከገዥው ንጉሥ “መክሊቶች” ጋር የሚተካከል ነገር በ1919 ላይ በአደራነት ተረክበው ነበር። ይህም በመግዛት ላይ ባለው ንጉሣቸው ፊት ያለባቸውን ተጠያቂነት ሰፋ አደረገው። ከጦርነቱ በኋላ ያደረጓቸ ጥረቶች ገና ከመጀመሪያው አንስቶ በ“መከሩ” ሥራ ማለትም ‘የስንዴ’ ክፍል የሆኑትን በመሰብሰቡ ላይ ያተኮረ ነበር። (ማቴዎስ 13:24–30) ኢየሱስ መከሩ “የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ነው ስላለ ከጦርነቱ በኋላ ያለው ዓመት ማለትም 1919 ስንዴ መሰል የሆኑት ‘የመንግሥቱን ልጆች’ ማለትም ታማኞቹ ቅቡዓን ቀሪዎች ልክ እንደ መከር መሰብሰብ የሚጀምሩበት ትክክለኛው ጊዜ ነበር።— ማቴዎስ 13:37–39
7. (ሀ) የመከር ሠራተኞቹ ከጌታቸው ጋር ወደ ምን ዓይነት ጊዜ ውስጥ ነበር የገቡት? (ለ) ይሖዋ የመከር ሠራተኞቹን ወደ ምን ዓይነት ሁኔታ አስገብቷቸዋል? የትኛውን ትንቢታዊ አባባልስ በራሳቸው ላይ ያውላሉ?
7 የመከር ጊዜ ለአጫጆች አስደሳች ጊዜ ነው፣ ጌታቸውም በዚህ አጋጣሚ ከእነርሱ ጋር ይደሰታል። (መዝሙር 126:6) ይህ የመከር ጊዜ በኢየሱስ ክርስቶስ የምትመራው የአምላክ መንግሥት በ1914 በሰማይ መቋቋሟንና ይሖዋ በምድር ላሉት ውስን ሕዝቦቹ የጽድቅ አቋምን መስጠቱን በሚያረጋግጠው እያደገ በሚሄደው ማስረጃ መሠረት በከፍተኛ ደረጃ ተባርኳል። እነርሱም እንደ አንድ ቡድን በመሆን በኢሳይያስ 61:10 ላይ የሚገኙትን ቃላት በራሳቸው ላይ ያውላሉ:- “የማዳንን ልብስ አልብሶኛልና፣ የጽድቅንም መጎናጸፊያ ደርቦልኛልና [በይሖዋ] ደስ ይለኛል።”
‘የደስታው’ ተካፋይ የሚሆኑትን “እጅግ ብዙ ሰዎች” መሰብሰብ
8. በመንግሥቱ ወራሾች መሰብሰብ መጨረሻ ላይ ቅቡዓን ቀሪዎች ምን ያልጠበቁት ደስታ አግኝተው ነበር?
8 ወደ ጌታቸው “ደስታ” የገቡት እነዚህ ቅቡዓን ቀሪዎች የመጨረሻዎቹ የሰማያዊ መንግሥት ወራሽ አባላት በሚሰበሰቡበት ጊዜ ደስታ የሚያመጣ ሌላ ያልተጠበቀ ነገር እንደሚኖር ያላሰቡበትና ያልተዘጋጁበት ጉዳይ ነው። ይህም በሺው ዓመት የኢየሱስ ክርስቶስ ግዛት ስር ገነት በምትሆነዋ ምድር ላይ የሚኖረው ምድራዊ ቡድን መሰብሰብ ነው። እነርሱን በሚመለከት ስለሚገለጸው አዲስ እውቀት እንዲሰሙ ግብዣ ቢቀርብላቸው ተገቢ የሚሆኑት ከዚህ ምድራዊ ቡድን ሌላ እነማን መሆን ይችላሉ?
9. በ1935 በዋሽንግተን ዲ ሲ በተደረገው ስብሰባ ላይ እንዲገኙ በተለይ እነማን ተጋብዘው ነበር? ለእነርሱስ ምን ወቅታዊ አዲስ ትምህርት ተገልጾላቸው ነበር?
9 ስለዚህም በመጠበቂያ ግንብa ላይ ለታተመው ጥሪ ምላሽ በመስጠት ከይሖዋና በስሙ ከተጠራው ሕዝብ ጋር ዝምድና የሚፈልጉ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ከግንቦት 30 እስከ ሰኔ 2, 1935 ድረስ በዋሽንግተን ዲ.ሲ በተደረገው አጠቃላይ የይሖዋ ምስክሮች ስብሰባ ላይ ተገኝተዋል። በዚህ ስብሰባ ላይ በራእይ 7:9–17 ላይ የተገለጹት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ምድራዊ ክፍል እንደሚሆኑ በማወቃቸው ከልባቸው ተደስተው ነበር።
10, 11. ይህ ሁኔታ በሰማይ የልዩ ደስታ ጊዜ የሆነው ለእነማን ነው?
10 በዋሽንግተን ዲ ሲ የተደረገው ይህ ስብሰባ የሁሉ የበላይ ገዥ ጌታ ለሆነው አምላክ ለይሖዋ እንዴት ያለ ደስታ አምጥቶለት ይሆን! እንዲሁም አሁን እነዚህን “ሌሎች በጎች” ወደ “አንድ መንጋ” መሰብሰብ ለጀመረው መልካም እረኛ ማለትም ለልጁ ይህ እንዴት ያለ ታላቅ ደስታ የሚያመጣ ነበር!— ዮሐንስ 10:16
11 የቀሪዎቹ አባላትና ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄደው ‘ከሌሎች በጎች’ የሆኑት “ብዙ ሰዎች” በምሳሌያዊ አነጋገር እረኛቸው ሲመራቸውና ሲያሰማራቸው በሰላምና በፍቅር ተቀላቅለዋል። ‘የአንዱ እረኛቸው’ ልብ በዚህ “የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ” መደምደሚያ ላይ ይህንን ያህል ታላቅ “መንጋ” በማግኘቱ በደስታ ፈንድቆ መሆን ይኖርበታል።
“የሰላሙ መስፍን” መልዕክተኞች
12, 13. (ሀ) ጌታው ሲመለስ በመጣው ደስታ ከቅቡዓን ቀሪዎች ጋር እንዲካፈሉ የተጋበዙት እነማን ናቸው? ለዚህስ ምክንያቱ ምንድን ነው? (ለ) የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ‘የሰላሙን መስፍን’ ሥራዎች የሚያከናውኑት በምን ደረጃ ነው?
12 “እጅግ ብዙ ሰዎች” የተባሉት በግ መሰል ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ደስታ በከፍተኛ ሁኔታ ይካፈላሉ። ይህ ሊሆን የቻለው በተለይ በራእይ 7:9 ላይ ቁጥራቸው ያልተወሰነውን “እጅግ ብዙ ሰዎች” ለማሟላት የሚያስፈልጉትን ሰዎች ለማምጣት በሚደረገው ሥራ በንቃት ስለሚሳተፉ ነው።
13 “ሌሎች በጎች” የሚካፈሉበት ይህ የመሰብሰብ ሥራ ቁጥራቸው እየቀነሰ የሚሄደው ቅቡዓን ቀሪዎች ብቻቸውን ሊፈጽሙት ከሚችሉት በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ መጥቋል። በዚህም ምክንያት ቁጥራቸው እየጨመረ ያለው “ሌሎች በጎች” ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ገና የሚመጡ ብዙ “ሌሎች በጎች” ለመሰብሰብ ተሳትፎአቸውን ከፍ ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ሆኖባቸዋል። በዚህም መንገድ “ሌሎች በጎች” ‘የሰላሙ መስፍን’ ታማኝ መልዕክተኞች ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው። ምሳሌ 25:13 ጨምሮ እንዲህ ይላል:- “በመከር ወራት የውርጭ ጠል ደስ እንደሚያሰኝ፣ እንዲሁ የታመነ መልዕክተኛ ለላኩት ነው፤ የጌቶቹን ነፍስ ያሳርፋልና።”
14. (ሀ) በማቴዎስ 25:31–46 ላይ በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሱት ምሳሌያዊ በጎች የሚወርሱት ምንድን ነው? (ለ) “ዓለም ከተፈጠረበት ጀምሮ” መንግሥት የተዘጋጀላቸው እንዴት ነው?
14 በበጎችና በፍየሎች ምሳሌ ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ “እናንተ የአባቴ ብሩካን ኑ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” የሚላቸው ምሳሌያዊዎቹ በጎች ናቸው። (ማቴዎስ 25:31–46) እነርሱ በሺው ዓመት ግዛት ውስጥ መንግሥተ ሰማያት የሚያስተዳድረውን ምድራዊ ግዛት ይወርሳሉ። ከታማኙ ከአቤል ዘመን ጀምሮ ይሖዋ ይህንን ግዛት ለሚዋጀው የሰው ዘር ዓለም ሲያዘጋጅ ቆይቷል።— ሉቃስ 11:50, 51
15, 16. (ሀ) በሰለሞን እንደተገለጸው ጌታው አሁን እየገዛ ያለው በጠላቶቹ መካከል ቢሆንም ያገኘው የንጉሥ “ክብር” ምንድን ነው? (ለ) በመግዛት ላይ ያለው ንጉሥ ዛሬ ይህንን “ክብር” ያገኘው በምን ዓይነት መልክ ነው? (ሐ) ለዚህ “ክብር” ምክንያት የሆኑት ሰዎችስ ምን አድርገዋል?
15 የጥንቷ እስራኤል ጥበበኛ ንጉሥ ሰለሞን:- “የንጉሥ ክብር በሕዝቡ ብዛት ነው” ብሎ ጽፎአል። (ምሳሌ 14:28) ከምድራዊው ንጉሥ ከሰለሞን የሚበልጠው የዛሬው ንጉሣዊ ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስ ‘ብዛት ያላቸውን ሕዝብ’ በተመለከተ እንደዚህ ያለውን “ክብር” አግኝቷል። ይህ ነገር የሺህ ዓመት ግዛቱን ከመጀመሩ በፊት ሰይጣን ዲያብሎስ ከሰው በላይ የሆነ የማይታይ ንጉሣቸው በሆነው ምድራዊ ጠላቶቹ መካከል በሚገዛበት በአሁኑ ጊዜም ቢሆን እውነተኛ ሆኖአል።— ማቴዎስ 4:8, 9፤ ሉቃስ 4:5, 6
16 የዛሬው “ክብር” ቁጥራቸው እያደገ በሚሄደውና “እጅግ ብዙ ሰዎች” በሆኑት የእርሱ “ሌሎች በጎች” ውስጥ ከሚገኘውና በንጉሥነት ደረጃ ላይ ላለ ለአንድ ባለሥልጣን ከሚሰጠው ጋር ይስማማል። እነርሱም በአንድነት ሆነው:- “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው” በማለት በደስታ ይጮሃሉ። (ራእይ 7:9, 10) ሰይጣን ዲያብሎስ “አምላክ” ከሆነለትና የጥፋት ፍርድ ከተፈረደበት የነገሮች ሥርዓት አሁንም እንኳ ድነዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) በምሳሌያዊ አባባልም “ልብሳቸውን አጥበው በበጉ ደም” በማንጻት በፈራጁ በይሖዋ አምላክ ፊት እድፈት የሌለበት ነጭ አድርገውታል።— ራእይ 7:14
17. (ሀ) “እጅግ ብዙ ሰዎች” የትኛውን መዳን በመጠባበቅ ላይ ናቸው? (ለ) ‘በሰላሙ መስፍን’ የሺህ ዓመት ግዛት ውስጥ ምን ዓይነት መብት ያገኛሉ?
17 ይሁን እንጂ “በታላቁ ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ቀን” በአርማጌዶን በሚሆነው በይሖዋ ንጉሣዊ ድል ወቅት የሚያገኙትን በአምላክ የተዘጋጀ ማዳን በናፍቆት ይመለከታሉ። የእርሱም አስደናቂ ድል የአጽናፈ ዓለም የበላይ ገዥነቱን መረጋገጥ የሚያስከትል ይሆናል፣ እነርሱም በዚህ ክፉ ዓለም አስቸጋሪ ፍጻሜ ውስጥ በሕይወት ተጠብቀው ስለሚያልፉ ምድራዊ የዓይን ምስክሮች ይሆናሉ። (ራእይ 16:14፤ 2 ጴጥሮስ 3:12) እንዴት ያለ ውድ መብት ነው! በዚያን ጊዜ የሰላሙ መስፍን ከጥፋቱ ከሚተርፉት የታማኞቹ “ሌሎች በጎች” ክፍል ከሆኑት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ጋር እንዴት ያለ ታላቅ ደስታ ያገኛል!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የሚያዝያ 1 እና 15፤ እንዲሁም የግንቦት 1, እና 15, 1935 የመጠበቂያ ግንብ ዕትሞች
[በገጽ 71 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መልካሙ እረኛ ባሁኑ ጊዜ እጅግ በጣም ብዙ “ሌሎች” በጎች በማግኘቱ ልቡ በደስታ ተሞልቶ መሆን አለበት