ምዕራፍ 10
አምላክ ለሰው ልጆች አደርግላቸዋለሁ ብሎ የማለላቸው ነገሮች የሚጨበጡበት ጊዜ ደርሷል!
1, 2. (ሀ) አምላክ የሚምለው በምን መንገድ ነው? ለምንስ? (ለ) በኢሳይያስ 45:23 ላይ አምላክ ምን አለ? (ሐ) ነቢዩ ኢሳይያስ ከተናገራቸው ከየትኞቹ ቃላት ጋር መስማማት ይኖርብናል?
አምላክ ይምላልን? አዎን፣ አምላክ ይምላል፤ ይሁን እንጂ እርሱ በቁጣ በመገንፈልና ከቁጥጥር ውጭ በመሆን በጸያፍ አነጋገር ተጠቅሞ አይምልም። ምን ጊዜም መሐላው ዓላማዬ ይህ ነው ብሎ የገለጸውን ነገር ለማጠናከር ታስቦ የሚደረግ ነው። ይህም በዚህ ለሚነኩት ሁሉ ተጨማሪ ማረጋገጫ ይሰጣል። ስለዚህ ሁሉም የሰው ዘሮች በኢሳይያስ 45:23 ላይ ላሉት “ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፣ አትመለስም:- ጉልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፣ ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል ብዬ ለራሴ ምያለሁ” ለሚሉት እርሱ ለተናገራቸው ቃላት ትኵረታቸውን ቢሰጡ መልካም ያደርጋሉ።
2 እኛ ዛሬ ይህ ትንቢት ከተነገረ ከ2, 700 ዓመታት በኋላ የምንኖረው በኢሳይያስ 45:24 ላይ የሚገኘው “[በይሖዋ (አዓት)] ዘንድ ብቻ ጽድቅና ኃይል አለ፣ ወደ እርሱም ሰዎች ይመጣሉ፣ በእርሱም ላይ የተቆጡ ሁሉ ያፍራሉ” የሚለው አነጋገር እውነት ያለው ማረጋገጫው በጕልህ ይታየናልን? የሚታየን ከሆነ በቁጥር 25 ላይ ከሚገኙት ከሚከተሉት የኢሳይያስ ቃላትም ጋር ጭምር ልንስማማ እንችላለን:- “የእስራኤልም ዘር ሁሉ [በይሖዋ (አዓት)] ይጸድቃሉ፣ ይመካሉም።”
3, 4. (ሀ) ኢሳይያስ 45:25 ስለ እስራኤል ሪፖብሊክ እንድናስብ የማያደርገን ለምንድን ነው? (ለ) ኢሳይያስ 45:23–25 ሳይፈጸም ቀርቷልን? እንደዚያ ብለህ ለምን መለስህ?
3 ኢሳይያስ 45:25ን ስናነብ ትዝ ሊለን የሚገባው የእስራኤል ሪፑብሊክ ነውን? አይደለም! እነዚህ እስራኤላውያን በጦርነት ድል አድርገን ምድራችንን የያዝነው በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች አምላክ እርዳታ ነው ብለው አያምኑም። በተሳሳተ አጉል አክብሮት በመገፋፋትም ስሙን እንኳ ከመጥራት ይቆጠባሉ።
4 እንደዚህ ስንል ኢሳይያስ 45:23–25 እስከዚህ ዓመት ድረስ ሳይፈጸም ቀርቷል ብለን መከራከራችን ነውን? አይደለም! ትንቢቱ ይሖዋ በወሰነው ጊዜ ላይ እንዳይፈጸም ምንም ነገር አላገደውም። በእርሱ ዘንድ ትንቢቱ ሳይፈጸም መቅረቱ የማይቻል ነገር ነው! ቃሉ ራሱ ፍጹም እምነት ሊጣልበት የሚችልና የማይታጠፍ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ የነገሮችን እውነተኝነት ለማረጋገጥ ብሎ መሐላውን ሲጨምርበት ቃሉ የበለጠ አስተማማኝ ይሆናል።
አምላክ በመሐላ በመካከል ገባ
5. ዕብራውያን 6:13–18 አምላክ ለአብርሃም በሰጠው ቃል ኪዳን ላይ በመሐላ እንደገባ የሚገልጸው እንዴት ነው?
5 ይህንን በሚመለከት በዕብራውያን 6:13–18 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ:- በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ እያበዛሁም አበዛሃለሁ፣ ብሎ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ፣ በራሱ ማለ፤ እንዲሁም እርሱ ከታገሠ በኋላ ተስፋውን አገኘ። ሰዎች ከእነርሱ በሚበልጠው ይምላሉና ለማስረዳትም የሆነው መሐላ የሙግት ሁሉ ፍጻሜ ይሆናል፤ ስለዚህም እግዚአብሔር የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደማይለወጥ አብልጦ ሊያሳያቸው ስለፈቀደ፣ እግዚአብሔር ሊዋሽ በማይችል በሁለት በማይለወጥ ነገር፣ በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት ይሆንልን ዘንድ በመሐላ በመካከል ገባ።”
6. (ሀ) አምላክ ለአብርሃም የገባውን ቃል በሚመለከት በራሱ እንዲምል የገፋፋው ምክንያት ምን ነበር? (ለ) ይሖዋ ‘ወዳጁን’ እንዴት አድርጎ ሊጠቀምበት ችሏል?
6 ብዙውን ጊዜ ለመማል፣ የመሐላ ቃል ለመናገር የሚገፋፋ ኃይለኛ የሆነ ምክንያት ይኖራል። ይህም በተለይ መሐላው በአምላክ በራሱ ፈቃድ በሚደረግበት ጊዜ እውነት ነው። ይሖዋ እንደማለ፣ አዎን በራሱ እንደማለ ስለተገለጸ እንደዚህ ያለው የሚገፋፋ ምክንያት ለማግኘት ይቻላል። ይሖዋ ‘ለወዳጁ’ ለአብርሃም የሰጠው በመሐላ የተደገፈ ተስፋ በዛሬው ጊዜ ሁላችንንም ይነካል። አብርሃም መለኮታዊውን ጥሪ ተቀብሎ የትውልድ አገሩን በመልቀቅ ይሖዋ ለአብርሃም ዘሮች እንደ ውርሻ አድርጎ ወደሚሰጣቸው ምድር ለመሄድ እርምጃ ሲወስድ ይሖዋ ተደስቶበት ነበር። ይሖዋ ስለ አብርሃም አስተማማኝነት እርግጠኛ ሆኖ የዚህን “ወዳጅ” ስም ታላቅ ሊያደርገውና ሌሎችን ለመባረክ ሊጠቀምበት ችሏል። ይሖዋም ለእርሱ:- “የሚባርኩህንም እባርካለሁ፣ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶች ሁሉ በአንተ ይባረካሉ” ሊለው ችሏል።— ዘፍጥረት 12:3፤ ኢሳይያስ 41:8
7. (ሀ) ሚስቱ በ90 ዓመት ዕድሜዋ ላይ በነበረችበት ጊዜ አምላክ አብርሃምን የባረከው በምን ተዓምር ነበር? (ለ) አብርሃም እምነቱንና ታዛዥነቱን በልዩ መንገድ ያሳየው እንዴት ነው?
7 የአብርሃም ሚስት ሣራ ልጅ የመውለጃዋ ወቅት በጣም ባለፈበት ጊዜ ማለትም በ90 ዓመትዋ አምላክ ለአብርሃም የሰጠውን አስደናቂ ተስፋ ለማጠናከር ለአብርሃም የተወደደውን ልጃቸውን ይስሐቅን በተአምር እንድትወልድለት በማድረግ ባርኳታል። አብርሃም የአምላኩን የይሖዋን ትእዛዝ ለማክበር ውድ የሆነውን ይህንን ልጅ እንደ ሰብዓዊ መስዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ዝግጁና ፈቃደኛ መሆኑን አስመሰከረ። ይህ ልዩ የሆነ የእምነትና የታዛዥነት መግለጫ ይሖዋ ‘ለወዳጁ’ ለአብርሃም እንደሚከተለው ብሎ እንዲናገር ገፋፍቶት ነበር:-
8, 9. (ሀ) ይሖዋ አብርሃም ላሳየው የእምነትና የታዛዥነት መግለጫ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው? (ለ) አምላክ ራሱን ተጠያቂ ያደረገው ለማን ነበር?
8 “[ይሖዋ (አዓት)]–በራሴ ማልሁ ይላል፤ ይህን ነገር አድርገሃልና፣ አንድ ልጅህንም አልከለከልህምና በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ፣ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላቶችን ደጅ ይወርሳል፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ፣ ቃሌን ሰምተሃልና።”— ዘፍጥረት 22:15–18
9 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ እንደማለ የተገለጸበት የመጀመሪያ ቦታ ይህ ነው። ከእርሱ በሚበልጥ በሌላ በማንም ሊምል ስለማይችል ራሱን ከዚህ ጋር በማስተሳሰር በራሱ ማለ። በዚህ መንገድ ራሱን ለሌላ ለማንም ሳይሆን ለራሱ ተጠያቂ አደረገ። በግልጽ ያሳወቀውን ዓላማ በማስፈጸሙ የሚከበረው እርሱ ራሱ ነው።
እስከ ምን ያህል ድረስ
10. አምላክ ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን ያደረገው ከምን ያህል ጊዜ በፊት ነው? ስለዚህ ምን ጥያቄ ይነሣል?
10 አብርሃም ወደ ተስፋይቱ የከነዓን ምድር የገባው የዛሬ 4, 000 ዓመታት ገደማ ነበር። ታዲያ በ1943 ከዘአበ የተደረገው ያ ቃል ኪዳን አሁን እስከ ምን ያህል ድረስ ተፈጽሟል?
11. (ሀ) የእስራኤል ሪፖብሊክ የተባበሩት መንግሥታት አባል መሆንዋ ምን ያመለክታል? ከምንስ ውጤቶች ጋር? (ለ) የአብርሃም ሥጋዊ ዝርያዎች ተስፋ የተደረገበት “ዘር” ለመሆን ብቁ መሆናቸውን እያሳዩ ነውን?
11 ዛሬ በመካከለኛው ምሥራቅ የእስራኤል ሪፖብሊክ ትገኛለች። ለግል ጥቅሟ ስትል የተባበሩት መንግሥታት አባል ሆናለች። የተባበሩት መንግሥታት ተስፋ በተሰጠበት በአብርሃም “ዘር” አማካኝነት የሚመጣውን የይሖዋ አምላክን መንግሥት አለመቀበልን የሚያመለክት ነው። ስለዚህም አርማጌዶን በሚባለው ‘ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ ቀን በሚሆነው ጦርነት’ ይደመሰሳል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል የሆኑት ሁሉ፣ የእስራኤል ሪፑብሊክም ጭምር ከኅልውና ውጭ ይደረጋሉ። የሚያሳዝነው ነገር በትውልድ የአብርሃም ሥጋዊ ዝርያ የሆኑት እስራኤላውያን ይሖዋ አምላክ ሁሉንም የሰው ዘር የሚባርክበት፣ ተስፋ የተሰጠው መሲሐዊ “ዘር” ለመሆን የሚያስፈልጉትን ብቃቶች አያሟሉም።— ራእይ 16:14–16
12, 13. (ሀ) ከቀድሞ አባቱ ከዳዊት በተለየ መንገድ ‘የሰላሙ መስፍን’ ብቻውን የማይገዛው ለምንድን ነው? (ለ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ቃል የተገባለትን በረከት ለመቀበል መንግሥቱ በ1914 እስከሚቋቋም ድረስ መጠበቅ ነበረባቸውን? እንዴትስ እናውቃለን?
12 ሁሉም ሰው ሊረዳው እንደሚችለው ተስፋ የተደረገበት መሲሕ የአብርሃምን ቃል ኪዳን ለማስፈጸም በመካከለኛው ምሥራቅ በምትገኘው በምድራዊቷ ኢየሩሳሌም ላይ ተቀምጦ አይገዛም። እንደ ቀድሞ አባቱ እንደ ዳዊት መሲሑ ‘የሰላም መስፍን’ ብቻውን የሚገዛ አይሆንም። 12 ታማኝ ሐዋርያቱና በመንፈስ የተዋጁ ሌሎች ደቀመዛሙርቱን በመጨመር በአገዛዙ ከእርሱ ጋር በጠቅላላው 144, 000 እንደሚተባበሩ ቃል ገብቷል። (ራእይ 7:1–8፤ 14:1–4) አሁንም ገና ከእነዚህ ደቀ መዛሙርት ውስጥ ቀሪዎቹ በምድር ላይ ይገኛሉ። አምላክ የማለበት የአብርሃም ቃል ኪዳን ተፈጻሚነት እንዲያገኝ ለእነርሱ ምን ሲደረግላቸው ቆይቷል? በዚያ መንግሥት ውስጥ ለመግባት ቀደምትነት ካላቸው አንዱ የሆነው ሐዋርያው ጳውሎስ በገላትያ 3:8 ላይ “መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ:- በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ” በማለት ጻፈ።
13 ከአሕዛብ መካከል የተመረጡ ክርስቲያኖች ቃል የተገባለትን በረከት ለመቀበል መንግሥቱ በ1914 እስከሚቋቋምበት ጊዜ ድረስ መጠበቅ አላስፈለጋቸውም፣ ምክንያቱም ሐዋርያው ጳውሎስ ቀጥሎ:- “እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ” ብሎአል። (ገላትያ 3:9) ጳውሎስ ክርስቲያን ስለነበረ ተባርኳል፣ እንዲሁም በዘመኑ የነበሩት በመንፈስ የተወለዱ ክርስቲያኖች ሁሉ ተባርከዋል።a ዛሬም በተመሳሳይ መሲሑ ሁሉም የሰው ዘሮች የሚባረኩበት ዋነኛው የአብርሃም “ዘር” እንደሆነ የሚያምኑት በመንፈስ የተዋጁ ክርስቲያኖች ቃል የተገባላቸውን በረከት እያገኙ ነው።
14. (ሀ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች በአብርሃም ቃል ኪዳን መሠረት በተለይ የተባረኩት እንዴት ነው? (ለ) ይህስ ይሖዋን ያስከበረው በምን መንገድ ነው?
14 ራሳቸውን ለይሖዋ በመወሰንና ይህንንም ውሳኔ በጥምቀት በማሳየት በኋላም በአምላክ መንፈስ አማካኝነት ለመንፈሳዊ ርስት በመወለድ እነዚህ ክርስቲያኖች የታላቁ አብርሃም የይሖዋ አምላክ መንፈሳዊ ልጆች ሆነዋል። በተጨማሪም ከታላቁ ይስሐቅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ተባባሪ ወራሾች ሆነዋል። (ሮሜ 8:17) በእርግጥም እነርሱ በአብርሃሙ ቃል ኪዳን መሠረት በልዩ መንገድ ተባርከዋል። ይሖዋ አደርገዋለሁ ብሎ የማለውን ነገር ፈጽሞታል። በዚህ መንገድ እውነት ተናጋሪ መሆኑን፣ ክብደት ሰጥቶ በራሱ ስም የማለለትን ነገር ለመፈጸም ፍጹም ችሎታ እንዳለው አስመስክሮአል።
15. ሐዋርያው ጳውሎስ እያንዳንዱ በመንፈስ የተመረጡ ክርስቲያኖች አባል ምን ይሆናል አለ?
15 በመንፈስ የተመረጡት ቅቡዓን ክርስቲያኖች እያንዳንዱ አባል በመንፈሳዊ ሁኔታ አይሁዳዊ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው:- “በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፣ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤ ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፣ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም።”— ሮሜ 2:28, 29
16. መንፈሳዊ አይሁዶች በዘካርያስ 8:23 ላይ የተተነበየው የትኛው ክፍል ሆነዋል?
16 በዚህ ‘የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ’ ውስጥ ልባቸውን በመገረዝ በስውር አይሁዳዊ የሆኑት በመንፈስ የተመረጡ ክርስቲያኖች በዘካርያስ 8:23 ላይ የተተነበየለት አይሁዳዊ ክፍል ሆነዋል:- “በዚያ ዘመን ከአሕዛብ ቋንቋ ሁሉ አሥር ሰዎች የአንዱን አይሁዳዊ ሰው ልብስ ዘርፍ ይዘው እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ ይላሉ።”
17. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ ካሉት የመንፈሳዊ አይሁዶች ቀሪዎች ጋር ይሖዋን ለማምለክ በሚፈልጉት “አሥር ሰዎች” የተመሰሉት እነማን ናቸው? (ለ) በይሖዋ አምልኮ ከመንፈሳዊ አይሁዶች ጋር በመተባበር ‘የሌሎች በጎች’ አባላት አሁን ምን አስደሳች ነገር አግኝተዋል?
17 እነዚህ “አሥር ሰዎች” ወደ ይሖዋ አምላክ አምልኮ አብረው ለመሄድ የፈለጉት በዚህ ዘመን ካሉትና መንፈሳዊ አይሁዶች ከሆኑት በማቴዎስ 24:45–47 ላይ “ታማኝና ልባም ባሪያ” የተባለው ቡድን ክፍል ከሆኑት ጋር ነው። አሥር ቁጥር የሚያመለክተው በምድራዊ ሁኔታ ሙላትን ስለሆነ “ከአሕዛብ ቋንቋ ሁሉ (የመጡት) አሥር ሰዎች” በማቴዎስ 25:32–46 ትንቢት ላይ የተገለጹትን ምሳሌያዊ በጎች በሙሉ ያመለክታሉ። እነዚህ ኢየሱስ በግ መሰል ከሆኑት ቀሪዎች ጋር ‘በአንድ እረኛ’ ማለትም በእርሱ ሥር “አንድ መንጋ” በመሆን እንደሚተባበር የተናገረለት ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል ናቸው። (ዮሐንስ 10:16) በዚህ መንገድ በታላቁ አብርሃም በይሖዋ አምላክ “ዘር” አማካኝነት የአብርሃም ቃል ኪዳን የሚያስገኛቸውን በረከቶች ቅምሻ ያገኛሉ። ስለዚህ አምላክ ለሰው ዘር ሁሉ ሊያደርገው የማለው ነገር በእርግጥም በቅርቡ ሊጨበጥ ነው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “ክርስቲያኖች” የሚለውን ስም በመጥቀስ ማጣቀሻ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ የግርጌ ማስታወሻ በሥራ 11:26 ላይ “በዕብራይስጥ ሜሺኪይም ማለትም ‘መሲሐውያን’” ይላል።
[በገጽ 89 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሁሉም ብሔራት የመጡ ሰዎች ከመንፈሳዊ እስራኤል ጋር የቅርብ ግንኙነት ያደርጋሉ ሲል መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር