ምዕራፍ 13
‘የሰላሙ መስፍን’ ከአዲሱ ቃል ኪዳን ውጭ ወዳሉት ትኵረቱን አዞረ
1. በዛሬው ጊዜ ያሉት አይሁዶች ከአባቶቻቸው ጋር የተደረገው የሙሴ ቃል ኪዳን ወደ ፍጻሜው የሚመጣ መሆኑን ሊክዱ የማይችሉት ለምንድን ነው?
ዛሬ ያሉት የጥንቱ የቤተሰብ ራስ የአብርሃም ሥጋዊ ዝርያዎች የሆኑ አይሁዶች አሮጌው የሙሴ የሕግ ቃል ኪዳን በአዲስና በተሻለ ቃል ኪዳን የሚተካ መሆኑን ሊክዱ አይችሉም። በኤርምያስ 31:31 ላይ የሚገኙትን የሚከተሉትን የአምላክ ቃላት ከዕብራይስጥ የብራና ቅዱሳን ጽሑፎቻቸው ላይ መደምሰስ አይችሉም:- “እነሆ፣ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል።”
2. የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ማን ስለመሆኑ የተነሳው ጥያቄ በመጨረሻ ግልጽ የሆነው እንዴት ነው?
2 የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ማን እንደሚሆን ኤርምያስ አልተነበየም። ይሁን እንጂ በኒሣን 14 ቀን 33 እዘአ ምሽት ኢየሱስ ክርስቶስ የማለፍን ወይን ጠጅ የያዘውን ጽዋ ለደቀመዛሙርቱ ሲሰጥ መካከለኛው እርሱ እንደሚሆን አሳይቷል። (ሉቃስ 22:20) በዕብራውያን 7:22 (አዓት) ላይ ለዚህ አዲስና ‘የተሻለ ቃል ኪዳን’ “መያዣ”፣ ማረጋገጫ፣ ወይም ዋስትና ራሱ እንደሆነ ተነግሮናል።
3. ኢየሱስ ክርስቶስ ከአምላክ ጋር የሚያገናኝ ምን ሌላ ስልጣን ይዟል? ይህስ በትውልድ መስመር የተገኘ ነውን?
3 ኢየሱስ ለአዲሱ ቃል ኪዳን ሲል ባቀረበው መስዋዕት የይሖዋ ሊቀካህን ሆኗል። እርሱ ሊቀ ካህን የሆነው የመጀመሪያው የእስራኤል ሊቀካህን የአሮን ሥጋዊ ዝርያ በመሆን አይደለም። የሊቀካህንነቱ ስልጣን የጸደቀለት ካህን አድራጊ በሆነው በልዑሉ አምላክ በይሖዋ መሐላ ነው። በመዝሙር 110:4 ላይ የሚገኙት “እንደመልከ ጼዴቅ ሥርዓት አንተ ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ [ይሖዋ (አዓት)] ማለ (የፀፀት ስሜት አይሰማውም)” የሚሉት ቃላት ለኢየሱስ ይሠራሉ።— ዕብራውያን 7:20, 21
4. (ሀ) ይሖዋ ተስፋ የተሰጠበትን አዲስ ቃል ኪዳን ያደረገው ከየትኛው “እስራኤል” ጋር ነው? ለምንስ? (ለ) ወደ አዲስ ቃል ኪዳን ውስጥ የገቡት የየትኞቹ ወላጆች ልጆች ይሆናሉ?
4 አነስተኛ ቁጥር ካላቸው ቀሪዎች በስተቀር የሥጋዊ እስራኤላውያን ሕዝብ ኢየሱስ ክርስቶስን የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ አድርገው አልተቀበሉትም። በዚህም ምክንያት አምላክ ስለ አዲሱ ቃል ኪዳን የተነበየለት “የእስራኤል ቤት” “የአምላክ እስራኤል” የተባለው መንፈሳዊ እስራኤል ሆነ። (ገላትያ 6:16) ይህ መንፈሳዊ እስራኤል በ33 እዘአ በዋለው የጴንጠቆስጤ ዕለት ተወለደ። መንፈሳዊ በመሆኑም የሚያምኑትን አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎች ወይም አሕዛብን ዜጋ አድርጎ ሊቀበል ችሏል። (ሥራ 15:14) ጴጥሮስ ይህንን “የተመረጠ ትውልድ ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን” ብሎ ጠርቶታል። (1 ጴጥሮስ 2:9) ይህ “ቅዱስ ሕዝብ” የአብርሃምን ቃል ኪዳን አድራጊና ፈጻሚ በሆነው በታላቁ አብርሃም በይሖዋ መንፈሳዊ ልጆች የተገነባ ነው። ስለዚህም እነርሱ በአብርሃም ሚስት በሣራ የተመሰለችው የይሖዋ ሚስት መሰል ሰማያዊት ድርጅት “ልጆች” ናቸው። የታላቁ አብርሃም አዲስ ቃል ኪዳን ይህችን ሰማያዊ ድርጅት አስቀድሞ በይስሐቅ ለተመሰለው ተስፋ ለተሰጠበት “ዘር” እናት አድርጎ እንደሚቆጥራት አያጠራጥርም።
“ሌሎች በጎች” በአንድ መንጋ ውስጥ ተጨመሩ
5. አዲሱ ቃል ኪዳን በዚህ ምድር ላይ ምን ያስፈልጉታል?
5 ይህ አዲስ ቃል ኪዳን በዚህ ምድር ላይ ንቁ የሆኑ አገልጋዮች አስፈልገውታል፤ የቅቡዓኑ ቀሪዎች አባላት አሮጌውን የሙሴን የሕግ ቃል ኪዳን ለተካው “ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች” በመሆን በብቃት አገልግለዋል። (2 ቆሮንቶስ 3:6) እነርሱ የዘመናዊቷ ታላቂቱ ባቢሎን ዋነኛ ክፍል በሆነችው በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ባሉ በብዙ መቶ በሚቆጠሩ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ውስጥ ያሉት ቀሳውስት አይደሉም። የራእይ 18:4ን ትዕዛዝና ጥሪ አዳምጠው ከዚያች ከዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ወጥተዋል።
6. (ሀ) የአዲሱ ቃል ኪዳን አገልጋዮች ቁጥር በስንት የተወሰነ ነው? (ለ) መልካሙ እረኛ ትኩረቱን ከአዲሱ ቃል ኪዳን ውጭ ወዳሉት እንደሚያዞር እንዴት እናውቃለን?
6 የዚህ የአዲስ ቃል ኪዳን አገልጋዮች ቁጥር በ144, 000 የተወሰነ ነው። (ራእይ 7:1–8፤ 14:1–5) ስለዚህም መልካሙ እረኛ ትኩረቱን ከአዲሱ ቃል ኪዳን አገልጋዮች ውጭ ወደ ሌላ የሚያደርግበት ጊዜ መምጣት ነበረበት። የይሖዋ ዋነኛ አገልጋይ 144, 000 ቁጥር ያላቸው ‘ከታናሹ መንጋ’ ክፍል ያልሆኑ “ሌሎች በጎች” እንዳሉት በዮሐንስ 10:16 ላይ በተናገረ ጊዜ ይህንን አስቀድሞ ተመልክቶትና ጠቅሶት ነበር።— ሉቃስ 12:32
7. (ሀ) ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል አባላት የአዲስ ቃል ኪዳን አገልጋዮች የማይሆኑት ለምንድን ነው? (ለ) በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ያሉት ቀሪዎች አሁንም ቢሆን ለምድር ነገዶችና ሕዝቦች በረከት የሆኑት እንዴት ነው?
7 “ሌሎች በጎች” የተባሉት “ከታናሹ መንጋ” ክፍል ባይሆኑም እነርሱም ጭምር የአምላክ አገልጋዮች ይሆናሉ፤ ይሁን እንጂ የአዲስ ቃል ኪዳን አገልጋዮች አይደሉም። እነዚህ “ሌሎች በጎች” “ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች” ከሆኑት ቀሪዎች ጋር አንድ መንጋ መሆናቸው አንድን ታላቅ ነገር ያመለክታል። ያስ ነገር ምን ይሆን? የሚከተለውን ነው:- ቀሪዎቹ የሰማያዊ መንግሥት ክብር ከማግኘታቸው በፊት በዚሁ ምድር ላይ ‘ከሌሎች በጎች’ ጋር የቅርብ ግንኙነት ይኖራቸዋል። በዚህም መንገድ መንፈሳዊ የአብርሃም ዘር ቀሪዎች በአርማጌዶን ከሚሆነው ‘ሁሉን ከሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ በፊትና የሺው ዓመት ግዛት ከመጀመሩ በፊት ለሁሉም ነገዶችና ሕዝቦች በረከት መሆን ይጀምራሉ።— ገላትያ 3:29፤ ራእይ 16:14, 16
8. መልካሙ እረኛ ትኩረቱን ከአዲሱ ቃል ኪዳን ውጭ ወዳሉት ያደረገው መቼ ነው? እነዚህስ “ሌሎች በጎች” ምን የመጀመሪያ ደረጃ ርምጃ ወስደዋል?
8 በተለይ ከ1935 ወዲህ ሁኔታው እንደዚህ ሆኖአል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ በሚልዮን የሚቆጠሩ “ሌሎች በጎች” በመላው ዓለም ላይ በብዙ ሺህ በሚቆጠሩ የይሖዋ ምስክሮች ጉባኤዎች በመሰብሰብ ከሁሉ በላይ ለሆነው እረኛ ለይሖዋ አምላክ ራሳቸውን ወስነዋል። በዚህም መንገድ ወደ መልካሙ እረኛ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ “አንድ መንጋ” እንዲገቡ ተፈቅዶላቸዋል።
9. የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ትኩረቱን ማስፋቱ በምድር ላይ የአዲሱ ቃል ኪዳን አገልግሎት አብቅቷል ማለት ነበርን?
9 ከዚያን ጊዜ ወዲህ የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ‘ሌሎች በጎችን’ ለመጨመር ትኩረቱን በማስፋፋቱ የአዲሱ ቃል ኪዳን አገልግሎት በ1935 አበቃ ማለት ነውን? አይደለም፤ ምክንያቱም አሁንም የአዲሱ ቃል ኪዳን አገልጋዮች ገና በምድር ላይ አሉ፤ ይህንን አገልግሎትም መፈጸም ይኖርባቸዋል።
10. በዛሬው ጊዜ በስምንቱ የክርስቲያን ግሪክኛ መጻሕፍት ጸሐፊዎች ከተሰጠው የአዲስ ኪዳን አገልግሎት እየተጠቀሙ ያሉት እነማን ናቸው?
10 በዛሬው ጊዜ ‘የታናሽ መንጋ’ ቀሪዎችም ሆኑ ቁጥራቸው እየጨመረ በመሄድ ላይ ያለው “እጅግ ብዙ ሰዎች” የተባሉት የመልካሙ እረኛ “ሌሎች በጎች” ከእነርሱ በፊት አስቀድመው የሄዱት እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ያሉት ከሚሰጡት አገልግሎት እየተጠቀሙ ነው። ኢየሩሳሌም በ70 እዘአ ከመጥፋትዋ ከጥቂት ጊዜ በፊት በሮም እስከሞተበት ድረስ ጳውሎስ የአዲስ ቃል ኪዳን አገልግሎቱን በታማኝነት ሲያከናውን ከ27ቱ ክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ 14ቱን እንዲጽፍ በመንፈስ ተመርቶአል። ቅቡዓን ቀሪዎችና የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑ “እጅግ ብዙ ሰዎች” እንደ ሐዋርያው ጳውሎስና ሌሎች ሰባት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጽሐፍት ጸሐፊዎች ያሉት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ታማኝ ሰዎች የአዲስ ኪዳን አገልግሎታቸውን እስከ ምድራዊ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ በማከናወናቸው ምንኛ አመስጋኞች ሊሆኑ ይችላሉ! በዘመናችንም ቢሆን በሚልዮን የሚቆጠሩት “ሌሎች በጎች” ቀደም ካለው ጊዜ ጀምሮ መካከለኛ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስር ቅቡዓን ቀሪዎቹ በሚሰጡት የአዲስ ኪዳን አገልግሎት እየተጠቀሙ ነው። ‘የሰላሙ መስፍን’ አሁን ትኵረቱን ቁጥራቸው በፍጥነት እያደገ ወዳለው ወደነዚህ ውድ “ሌሎች በጎች” አዙሯል።
11. (ሀ) አዲሱ ቃል ኪዳን በሥራ ላይ ከዋለ ምን ያህል ጊዜ ሆኖታል? ይህስ ምን ያመለክታል? (ለ) የአዲሱ ቃል ኪዳን አገልጋዮች ቀሪዎች በዛሬው ጊዜ ምን በመሆን ያገለግላሉ?
11 ያም ሆነ ይህ ጊዜው አሁን እያለቀ መሆን ይኖርበታል! አዲሱ ቃል ኪዳን ቀደም ብሎ ከተቀየረው ከሙሴ የሕግ ቃል ኪዳን 407 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ማለት ለ1953 ዓመታት በሥራ ላይ ቆይቷል፤ እንዲሁም እያንዳንዱ አባል ከምድር ገጽ በሞት እያለፈ ስለሚሄድ የአዲሱ ቃል ኪዳን አገልጋዮች ቁጥር እየቀነሰ በመሄድ ላይ ነው። ይሁን እንጂ ዛሬ ያሉት የእነዚህ አገልጋዮች ቀሪዎች ጌታው ኢየሱስ ክርስቶስ “ባለው ሁሉ ላይ” የሾመው “ታማኝና ልባም ባሪያ” በመሆን ማገልገላቸውን ይቀጥላሉ።— ማቴዎስ 24:45–47
“ና” የሚለውን ግብዣ ማቅረብ
12. በራእይ 22:17 መሠረት ‘የሙሽራዋ’ ክፍል የሆኑት ምን ግብዣ እያቀረቡ ነው? ለማንስ?
12 በአዲሱ ቃል ኪዳን አገልጋዮች የሚቀርበው አገልግሎት ምንኛ ፍቅራዊ ነው! ለምሳሌ ያህል በራእይ 22:17 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “መንፈሱና ሙሽራይቱም:- ና ይላሉ። የሚሰማም:- ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፣ የወደደም የሕይወትን ውሃ እንዲያው ይውሰድ።” ‘የሙሽራይቱ’ ክፍል ከይሖዋ አንቀሳቃሽ ኃይል ወይም መንፈስ ጋር በመሆን ከአዲሱ ቃል ኪዳን ውጭ ላሉት ያንን ግብዣ በማቅረብ ላይ ናቸው። ግብዣው የቀረበው አሁን ሞተው በመታሰቢያ መቃብር ላሉትና ከሞት በመነሳት ለሚባረኩት ሳይሆን በአርማጌዶን የመጥፋት አደጋ ለተደቀነባቸውና የሚሰማ ጆሮ ላላቸው አሁን በሕይወት ለሚኖሩት ሰዎች ነው።
13. (ሀ) ‘በሙሽራዋ’ ክፍል የቀረበው ግብዣ ከንቱ ሆኖአልን? አብራራ (ለ) ቀደም ሲል ግብዣውን የተቀበሉት ራእይ 22:17ን በመታዘዝ ምን እያደረጉ ነው? (ሐ) ግብዣውን ለማቅረብ የቀረውን ጊዜ በሚመለከት ያለው ሁኔታ ምንድን ነው?
13 ይህ ፍቅራዊ ግብዣ በተለይ ከ1935 ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ መቅረቡ በከንቱ አይደለም። መጥተው እንዲጠጡ ለቀረበላቸው ክብራማ ግብዣ እስከ ዛሬ ድረስ ከሦስት ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች ምላሽ ሰጥተዋል። እነዚህ በአድናቆት የሰሙ ሰዎች በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠሩ ለተጠሙ ሌሎች ሰዎች በገነት ምድር ላይ ዘላለማዊ ሕይወት እንዲያገኙ በታዛዥነት “ኑ” እያሉ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ክብራማ ግብዣ “ሌሎች በጎች” ለሆኑት የሚቀርብበት ጊዜ የተወሰነ ነው። ከግማሽ መቶ ዘመን የሚበልጥ ጊዜ ከተፈቀደ በኋላ አሁን በአርማጌዶን የሚደረገው የአምላክ ጦርነት በዚህ የሰው ዘር “ትውልድ” ላይ በአደገኛ ሁኔታ እያንዣበበ ስለሆነ የሚቀረው ጊዜ በጣም አጭር መሆን ይኖርበታል።— ማቴዎስ 24:34
14. ለይሖዋ ምስጋናና ውዳሴ ማቅረብ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
14 ስለዚህ አሁን ለስሙ የሚሆን 144, 000 ጠንካራ ሕዝብ በመፍጠር አዲሱን ቃል ኪዳን በተሳካ ሁኔታ ለመፈጸም ብቁ የሆነውን መካከለኛ ስላዘጋጀ ይሖዋ የተመሰገነ ይሁን! እንዲሁም የእርሱ መካከለኛ እንደ አንድ መልካም እረኛ በመሆን ቁጥራቸው እየጨመረ ያለውን “ሌሎች በጎች” ቀደም ብሎ ከአዲሱ ቃል ኪዳን የሚገኙት የመጀመሪያ ጥቅሞች እየፈሰሱ ወዳሉበትና እነርሱ አስቀድሞ ወደገቡበት “አንድ መንጋ” በማምጣቱ ለይሖዋ ውዳሴ ይድረሰው!
[በገጽ 111 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሚልዮን የሚቆጠሩ “ሌሎች በጎች” በእነዚህ መጨረሻ ቀኖች ወደሚታየው የይሖዋ ድርጅት መጥተዋል