ምዕራፍ 5
ዮሐንስ ክብር የተቀዳጀውን ኢየሱስን ተመለከተ
ራእይ 1—ራእይ 1:10 እስከ 3:22
ርዕሰ ጉዳይ:- ኢየሱስ በምድር ላይ የመንፈሳዊ እሥራኤልን ሁኔታ ከመረመረ በኋላ ሞቅ ያለ ማበረታቻ ሰጠ
ራእዩ የሚፈጸምበት ጊዜ:- ይኸኛው የጌታ ቀን ክፍል የሚቆየው ከ1914 ጀምሮ የመጨረሻው ታማኝ ቅቡዕ ሞቶ ትንሣኤ እስኪያገኝ ድረስ ነው
1. የመጀመሪያው ራእይ የቀረበው እንዴት ነው? ራእዩ የሚፈጸምበትን ጊዜ ዮሐንስ ያመለከተው እንዴት ነው?
የመጀመሪያው የራእይ መጽሐፍ ራእይ የሚጀምረው ምዕራፍ 1 ቁጥር 10 ላይ ነው። ይህ ራእይ እንደሌሎቹ ራእዮች ዮሐንስ በጣም አስደናቂ ነገር ሊያይ ወይም ሊሰማ እንደሆነ በመግለጽ ይከፈታል። (ራእይ 1:10, 12፤ 4:1፤ 6:1) የዚህ የመጀመሪያው ራእይ ይዘት በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ሲሆን በዮሐንስ ዘመን ለነበሩት ሰባት ጉባኤዎች የተለያዩ መልእክቶች ተልከዋል። ይሁን እንጂ ዮሐንስ “በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ” በማለት ራእዩ መቼ እንደሚፈጸም አመልክቶአል። (ራእይ 1:10ሀ) ታዲያ ይህ “ቀን” መቼ ነው? በዚህ ተነዋዋጭ ሁኔታዎች በበዙበት ዘመን የተፈጸሙ ነገሮች ከዚህ ቀን ጋር ግንኙነት ይኖራቸው ይሆንን? ግንኙነት ካላቸው ትንቢቱ የየግል ሕይወታችንን እንዲያውም ከመጥፋት መዳናችንን የሚመለከት ስለሚሆን በትኩረት ልንከታተለው ይገባል።—1 ተሰሎንቄ 5:20, 21
በጌታ ቀን
2. የጌታ ቀን የጀመረው መቼ ነው? የሚያልቀውስ መቼ ነው?
2 ታዲያ በዚህ መሠረት የራእይ ትንቢት የሚፈጸመው በየትኛው ጊዜ ይሆናል ማለት ነው? የጌታ ቀን ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው ፍርድና መለኮታዊ ተስፋዎች የሚፈጸሙበት ጊዜ ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:8፤ 2 ቆሮንቶስ 1:14፤ ፊልጵስዩስ 1:6, 10፤ 2:16) ይህ “ቀን” እየቀረበ ሲመጣ የይሖዋ ታላላቅ ዓላማዎች በድል አድራጊነት ወደ መጨረሻው ታላቅ ፍጻሜአቸው ይገሰግሳሉ። ይህ “ቀን” የሚጀምረው ኢየሱስ ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ ዘውድ ሲደፋ ነው። ኢየሱስ የቅጣት ፍርዱን በሰይጣን ዓለም ላይ ከፈጸመ በኋላ እንኳን ይህ የጌታ ቀን ምድር ገነት እስክትሆን፣ የሰው ልጅ ወደ ፍጽምና ደረጃ እስኪደርስና በመጨረሻም ኢየሱስ ‘መንግሥቱን ለአምላኩና ለአባቱ መልሶ’ እስከሚያስረክብበት ጊዜ ድረስ ይቀጥላል።—1 ቆሮንቶስ 15:24-26፤ ራእይ 6:1, 2
3. (ሀ) ዳንኤል ስለ “ሰባቱ ዘመናት” የተናገረው ትንቢት የጌታ ቀን የሚጀምርበትን ጊዜ እንድናስተውል የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) የጌታ ቀን የጀመረው በ1914 መሆኑን የሚያረጋግጡልን በምድር ላይ የተፈጸሙ ምን ሁኔታዎች ናቸው?
3 የሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ የጌታ ቀን መቼ እንደሚጀምር እንድናስተውል ይረዱናል። ለምሳሌ ያህል ዳንኤል የንጉሥ ዳዊት ሥርወ መንግሥት አገዛዝ እንደሚቆረጥ ተናግሮ ነበር። “ከሰባት ዘመን” በኋላ “ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሰለጥን ለሚወድደውም እንደሚሰጠው” ይታወቃል። (ዳንኤል 4:23, 24, 31, 32) የዚህ ትንቢት ዋነኛ ፍጻሜ የጀመረው የይሁዳ መንግሥት በጠፋ ጊዜ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ እንደሚያሳየው ይህ የተፈጸመው በጥቅምት ወር በ607 ከዘአበ ነው። ራእይ 12:6, 14 ላይ 3 1/2 ዘመናት 1, 260 ቀን እንደሆኑ ተመልክቶአል። ስለዚህ ሰባት ዘመናት (የዚህ እጥፍ ስለሆኑ) 2, 520 ቀን መሆን ይኖርባቸዋል ማለት ነው። ‘አንዱን ቀን በአንድ ዓመት’ ስንመነዝር “ሰባት ዘመናት” የ2, 520 ዓመት ርዝመት ያለው ጊዜ እንደሆነ እንረዳለን። (ሕዝቅኤል 4:6) ስለዚህ ክርስቶስ ኢየሱስ ሰማያዊ ግዛቱን የጀመረው በ1914 ማለቂያ አካባቢ ላይ ነው። በዚህ ዓመት አንደኛው የዓለም ጦርነት መፈንዳቱ “የምጥ ጣር መጀመሪያ” ሲሆን ይኸው ጣር እስከ አሁን ድረስ የሰው ልጆችን ሲያሰቃይ ቆይቶአል። ከ1914 ወዲህ በዚህች በደም በተጨማለቀችው ምድር ላይ የተፈጸሙት ሁኔታዎች ኢየሱስ የሚገኝበት “ቀን” በዚህ ዓመት የጀመረ መሆኑን አረጋግጠዋል።—ማቴዎስ 24 :3-14a
4. (ሀ) የመጀመሪያው ራእይ ስለተፈጸመበት ጊዜ የራእይ መጽሐፍ ምን ያመለክታል? (ለ) የመጀመሪያው ራእይ ተፈጻሚነት የሚያልቀው መቼ ነው?
4 ስለዚህ ይህ የመጀመሪያው ራእይና በራእዩ ውስጥ የተጠቃለሉት ምክሮች ከ1914 ወዲህ ላለው የጌታ ቀን የሚያገለግሉ ናቸው። ይህንን የጊዜ ምደባ የአምላክ እውነተኛና ጻድቅ ፍርድ እንደሚፈጸም የሚገልጸው የኋለኛው የራእይ መጽሐፍ ክፍል ይደግፈዋል። በዚህም የነገሮች አፈጻጸም ላይ ጌታ ኢየሱስ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። (ራእይ 11:18፤ 16:15፤ 17:1፤ 19:2, 11) የመጀመሪያው ራእይ መፈጸም የጀመረው በ1914 ከሆነ የሚያበቃው መቼ ነው? መልእክቶቹ ራሳቸው እንደሚያመለክቱት ራእዩ የተላከለት ድርጅት በምድር ላይ የሚኖሩት የአምላክ ቅቡዓን ጉባኤ ነው። ስለዚህ የመጀመሪያው ራእይ ፍጻሜ የሚያበቃው የዚህ የቅቡዓን ጉባኤ የመጨረሻ አባል ሞቶ የሰማያዊ ሕይወት ትንሣኤ ሲያገኝ ነው። ቢሆንም ለምድራዊዎቹ ሌሎች በጎች በረከት የሚያመጣው የጌታ ቀን የኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት እስከሚፈጸምበት ጊዜ ድረስ ይቀጥላል።—ዮሐንስ 10:16፤ ራእይ 20:4, 5
5. (ሀ) አንድ ድምፅ ዮሐንስን ምን እንዲያደርግ ጠየቀው? (ለ) የሰባቱ ጉባኤዎች አቀማመጥ የመጽሐፍ ጥቅልል ለመላክ አመቺ የነበረው ለምንድን ነው?
5 በዚህ የመጀመሪያ ራእይ ዮሐንስ ምንም ነገር ከማየቱ በፊት አንድ ነገር ይሰማል። “በኋላዬም የመለከትን ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ፣ እንዲሁም:- የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ወደ ኤፌሶንና ወደ ሰምርኔስ ወደ ጴርጋሞንም ወደ ትያጥሮንም ወደ ሰርዴስም ወደ ፊልድልፍያም ወደ ሎዶቅያም በእስያ ወዳሉት ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላክ አለኝ።” (ራእይ 1:10ለ, 11) እንደ መለከት ጩኸት ያለ ኃይልና የማዘዝ ሥልጣን የነበረው ድምፅ ዮሐንስን ለሰባቱ ጉባኤዎች እንዲጽፍ አዘዘው። ዮሐንስ ተከታታይ መልእክቶችን መቀበልና የሚያየውንና የሚሰማውን ለሌሎች ማስተላለፍ ነበረበት። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ጉባኤዎች በዮሐንስ ዘመን በትክክል የነበሩ ጉባኤዎች እንደሆኑ እናስተውል። ሁሉም ከጳጥሞስ በስተማዶ ከባሕር ባሻገር በታናሽቱ እስያ የሚገኙ ጉባኤዎች ነበሩ። በአካባቢው በነበረው ግሩም የሆነ የሮማውያን አውራ ጎዳና አማካኝነት ከአንዱ ጉባኤ ወደሌላው ጉባኤ በቀላሉ መጓዝ ይቻል ነበር። አንድ መልእክተኛ የመጽሐፉን ጥቅልል ተሸክሞ ከአንድ ጉባኤ ወደሌላው ለማድረስ ምንም አይቸገርም። እነዚህ ሰባት ጉባኤዎች በዘመናችን በአንድ የይሖዋ ምስክሮች ክልል ውስጥ በሚገኝ አንድ አካባቢ ሊመሰሉ ይችላሉ።
6. (ሀ) ‘አሁን ያለውን’ የሚለው አነጋገር ምን ትርጉም አለው? (ለ) በአሁኑ ጊዜ በቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ውስጥ ያለው ሁኔታ በዮሐንስ ዘመን ከነበረው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆን እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
6 አብዛኞቹ የራእይ መጽሐፍ ትንቢቶች ከዮሐንስ ዘመን በኋላ የሚፈጸሙ ናቸው። “ከዚህ በኋላ ይሆን ዘንድ ያለው” ጊዜን የሚያመለክቱ ናቸው። ለሰባቱ ጉባኤዎች የተሰጠው ምክር ግን “አሁን ያለውን” ማለትም በዚያ ጊዜ በሰባቱ ጉባኤዎች ውስጥ የነበረውን ሁኔታ የሚመለከት ነበር። መልእክቶቹ በእነዚህ ሰባት ጉባኤዎችም ሆነ በዘመኑ በነበሩት በሌሎች የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤዎች ውስጥ ለነበሩ ሽማግሌዎች እጅግ የሚጠቅሙ ነበሩ።b ራእዩ ዋነኛ ተፈጻሚነቱን የሚያገኘው በጌታ ቀን መሆኑ ኢየሱስ የተናገራቸው ሁኔታዎች በዘመናችን ባሉት ጉባኤዎች ውስጥም እንደሚኖሩ ያመለክታል።—ራእይ 1:10, 19
7. ዮሐንስ በዚህ የመጀመሪያ ራእይ ማንን ተመለከተ? ለእኛስ በጣም አስፈላጊና የሚያስደስት የሆነው ለምንድን ነው?
7 ዮሐንስ በዚህ በመጀመሪያ ራእዩ ውስጥ በታላቅ ግርማ ያሸበረቀውን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በሰማያዊ ክብሩ አይቶታል። በሰማይ ስለተሾመው ጌታ ታላቅ ቀን የሚናገረው ይህ የትንቢት መጽሐፍ በዚህ ራእይ መከፈቱ የተገባ ነው። በዚህ ጊዜ ለምንኖረውና ትዕዛዛቱን ሁሉ በጥንቃቄ ለምናከብረው ለእኛም ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር ሊኖር ይችላልን? ከዚህም በላይ መሲሐዊው ዘር የዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ ከሰይጣን የተሰነዘረበትን ያን ሁሉ ፈተናና ስደት ከተቋቋመና ተረከዙ በቆሰለ ጊዜ አሰቃቂ ሞት ከሞተ በኋላ አሁን የአምላክን ታላቅ ዓላማ በድል አድራጊነት ለማስፈጸም ሥልጣን ተሰጥቶት በሰማይ ሕያው ሆኖ መኖሩን ማወቅ የይሖዋን ሉዓላዊነት ለሚደግፉ ሁሉ ምንኛ የሚያስደስት ነው!—ዘፍጥረት 3:15
8. ኢየሱስ አሁን ምን ለማድረግ ዝግጁ ሆኖአል?
8 ኢየሱስ አሁን ዘውድ ስለጫነ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ሆኖ እንደሚጠባበቅ ግልጽ ነው። በዚህ አሮጌና ክፉ ሥርዓት እንዲሁም የዚህ ሥርዓት ዲያብሎሳዊ አምላክ በሆነው በሰይጣን ላይ የይሖዋን የመጨረሻ ፍርድ እንዲያስፈጽም ዋነኛ የይሖዋ ፍርድ አስፈጻሚ ሆኖ ተሹሞአል። በተጨማሪም ለቅቡዓኖቹና ባልንጀሮቻቸው ለሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎች ጉባኤ እንዲሁም ለዓለም ፍርድ ለመስጠት ተዘጋጅቶአል።—ራእይ 7:4, 9፤ ሥራ 17:31
9. (ሀ) ዮሐንስ በሰባቱ የወርቅ መቅረዞች መካከል የቆመውን ኢየሱስ ክርስቶስን የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ቤተ መቅደስ የሚመስለው ትርዒትና ኢየሱስ የለበሰው ልብስ ምን ያመለክታሉ? (ሐ) የወርቅ መታጠቂያው ምን ያመለክታል?
9 ዮሐንስ ወደ ታላቁ ድምፅ ዘወር ብሎ የሚከተለውን ተመለከተ:- “የሚናገረኝንም ድምፅ ለማየት ዘወር አልሁ፣ ዘወርም ብዬ ሰባት የወርቅ መቅረዞች አየሁ።” (ራእይ 1:12) ዮሐንስ ቆየት ብሎ የእነዚህን ሰባት መቅረዞች ትርጉም ተረድቶአል። አሁን ግን ትኩረቱን የሳበው በመቅረዞቹ መካከል የቆመው ነው። “በመቅረዞቹም መካከል የሰው ልጅ የሚመስለውን አየሁ፣ እርሱም እስከ እግሩ ድረስ ልብስ የለበሰ ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር።” (ራእይ 1:13) እዚህ ላይ “የሰው ልጅ” የተባለው ኢየሱስ በተመለከተው ሁሉ በጣም በተደነቀው ታማኝ ምሥክር በዮሐንስ ፊት የታየው ታላቅ ክብርና ግርማ የተቀዳጀ ሆኖ ነው። ኢየሱስ እንደ እሳት በሚያበሩ የወርቅ መቅረዞች መካከል በታላቅ ግርማ የሚያብረቀርቅ ሰው ሆኖ ታየ። ይህ የቤተ መቅደስነት መልክ ያለው ትዕይንት ኢየሱስ የፍርድ ሥልጣን ያለው የይሖዋ ታላቅ ሊቀ ካህናት ሆኖ መቅረቡን ለዮሐንስ አስገንዝቦታል። (ዕብራውያን 4:14፤ 7:21-25) የለበሰው ረዥም መጎናጸፊያ የክህነት ሹመት የተሰጠው መሆኑን ያረጋግጣል። እንደ ጥንቶቹ የአይሁዳውያን ሊቀ ካህናት በደረቱ ላይ ልቡን የሚሸፍንለት የወርቅ መታጠቂያ ለብሶ ነበር። ይህም ከይሖዋ አምላክ የተቀበለውን መለኮታዊ ሥራ በሙሉ ልቡ እንደሚፈጽም ያመለክታል።—ዘጸአት 28:8, 30፤ ዕብራውያን 8:1, 2
10. (ሀ) እንደ በረዶ የነጣው የኢየሱስ ፀጉርና የእሳት ፍም የሚመስለው ዓይኑ ምን ያመለክታሉ? (ለ) የኢየሱስ እግር የጋለ ነሐስ መምሰሉ ምን ትርጉም አለው?
10 ዮሐንስ መግለጫውን እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ራሱና የራሱ ጠጉርም እንደ ነጭ የበግ ጠጉር እንደ በረዶም ነጭ ነበሩ፣ ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ።” (ራእይ 1:14) እንደ በረዶ የነጣው ጠጉሩ በረዥም እድሜው ያካበተውን ጥበብ ያመለክታል። (ከምሳሌ 16:31 ጋር አወዳድር።) ዓይኖቹ እንደ እሳት ነበልባል መሆናቸው በሚመረምርበት፣ በሚፈትንበትና ቁጣውን በሚገልጽበት ጊዜ ንቁ፣ የማያወላውልና ዒላማውን የማይስት መሆኑን ያመለክታል። የኢየሱስ እግር እንኳን የዮሐንስን ትኩረት መሳቡ አልቀረም። “እግሮቹም በእቶን የነጠረ የጋለ ናስ ይመስሉ ነበር፣ ድምፁም እንደ ብዙ ውኃዎች ድምፅ ነበር።” (ራእይ 1:15) በራእዩ ውስጥ የኢየሱስ እግሮች እንደ ነሐስ የሚያብረቀርቁና የጋሉ ሆነው ታይተዋል። ይህም በይሖዋ አምላክ ፊት ጥሩ አቋም ላለውና በቅንዓት ለሚመላለስ እንደ ኢየሱስ ላለ አካል የተገባ ነው። ከዚህም በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የመለኮትነት ባሕርይ ያላቸው ነገሮች በወርቅ ሲመሰሉ የሰብዓዊነት ባሕርይ ያላቸው ነገሮች ደግሞ አንዳንድ ጊዜ በነሐስ ይመሰላሉ።c ስለዚህ የኢየሱስ እግሮች የጋለ ጥሩ ነሐስ መስለው መታየታቸው ምሥራቹን እየሰበከ በምድር ላይ ይመላለስ በነበረ ጊዜ እግሮቹ ምን ያህል ያማሩ እንደነበሩ ያሳስበናል።—ኢሳይያስ 52:7፤ ሮሜ 10:15
11. (ሀ) የኢየሱስ ክቡር እግሮች ምን ነገር ያስታውሱናል? (ለ) የኢየሱስ ድምፅ “እንደ ብዙ ውኆች ድምፅ” መሆኑ ምን ያመለክታል?
11 በእርግጥም ኢየሱስ ፍጹም ሰው ስለነበረ ለመላእክትም ሆነ ለሰዎች ግልጽ ሆኖ የታየ ነፀብራቅ ነበረው። (ዮሐንስ 1:14) በተጨማሪም ባለግርማ እግሮቹ ሊቀካህናት በሆነለት የይሖዋ ድርጅት ውስጥ በቅዱስ ሥፍራ ላይ እንደሚመላለስ ያስገነዝበናል። (ከዘጸአት 3:5 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በተጨማሪ እንደ ትልቅ ፏፏቴ የሚተምም ድምፅ አለው። ይህ ሁሉ የአምላክ ቃል ለተባለውና “ዓለሙን ሁሉ በጽድቅ ሊፈርድ” ለሚመጣው የሚገባ አስፈሪና አስደናቂ ገጽታ ነው።—ሥራ 17:31፤ ዮሐንስ 1:1
12. ‘በሁለት በኩል የተሳለው ረዥም ሠይፍ’ ምን ትርጉም አለው?
12 “በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ነበሩት፣ ከአፉም ከሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ወጣ፣ ፊቱም በኃይል እንደሚበራ እንደ ፀሐይ ነበረ። ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ ከእግሩ በታች ወደቅሁ።” (ራእይ 1:16, 17ሀ) የሰባቱን ከዋክብት ትርጉም ኢየሱስ ራሱ ቆየት ብሎ ይገልጻል። አሁን ግን ከአፉ የሚወጣው ምን እንደሆነ አስተውል። “ከሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ወጣ።” ይህም ለእርሱ በጣም የሚስማማ መግለጫ ነው። ይሖዋ በጠላቶቹ ላይ የሚያመጣውን የመጨረሻ ፍርድ እንዲያስታውቅ ሥልጣን የተሰጠው ኢየሱስ ነው። ከአፉ የሚወጡት ወሳኝ ቃላት ክፉዎችን በሙሉ እንዲደመሰሱ ያደርጋሉ።—ራእይ 19:13, 15
13. (ሀ) ብሩሕ የሆነው የኢየሱስ አንፀባራቂ ፊት ምን ነገር ያስታውሰናል? (ለ) ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ከሰጠው መግለጫ ምን አጠቃላይ ግንዛቤ እናገኛለን?
13 የኢየሱስ ፊት ብሩሕ ሆኖ ማንጸባረቁ ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ከይሖዋ ጋር ከተነጋገረ በኋላ ፊቱ ማብራት የጀመረበትን ጊዜ ያስታውሰናል። (ዘጸአት 34:29, 30) በተጨማሪም ኢየሱስ የዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ በሦስት ሐዋርያቱ ፊት በተለወጠ ጊዜ ‘ፊቱ እንደ ፀሐይ በርቶ፣ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ’ ሆኖ ነበር። (ማቴዎስ 17:2) አሁን ደግሞ ኢየሱስ በጌታ ቀን የሚኖረውን ሁኔታ በሚያሳየው ራእያዊ ትዕይንት ላይ ፊቱ በይሖዋ ፊት የቆየ ማንኛውም ፍጡር የሚኖረውን አንፀባራቂ ግርማ ያሳያል። (2 ቆሮንቶስ 3:18) እንዲያውም ዮሐንስ የተመለከተው ራእይ ታላቅ የግርማ ጨረር ነበር ለማለት ይቻላል። እንደ በረዶ ከነጣው ፀጉር፣ እንደ እሳት ፍም ከሚያበራው ዓይንና ብሩሕ ከሆነው ፊት ጀምሮ እሳት እስከሚመስለው እግር ድረስ የታየው ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ “ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን” የሚኖረውን ኢየሱስን የሚያመለክት ከፍተኛ ራእይ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 6:16) መላው ትዕይንት በጣም እውን ሆኖ የሚታይ ነበር። ባየው ነገር ሁሉ በጣም የተደነቀውና የደነገጠው ዮሐንስ ምን አደረገ? ሐዋርያው “ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ በእግሩ ሥር ወደቅሁ” በማለት ይነግረናል።—ራእይ 1:17
14. ዮሐንስ ክብር ስለተቀዳጀው ኢየሱስ የተመለከተውን ራእይ ስናነብ ምን ሊሰማን ይገባል?
14 በዛሬው ዘመን የአምላክ ሕዝቦች በዝርዝር ተብራርቶ የተገለጸውን ደማቅ ራእይ ሲያነቡ በልባዊ አድናቆት ይሞላሉ። ራእዩ በአስደናቂ ሁኔታ መፈጸም የጀመረበት የጌታ ቀን ከገባ እስከአሁን ድረስ ከ90 ዓመት በላይ አሳልፈናል። የኢየሱስ ንጉሣዊ አገዛዝ ለእኛ ወደፊት የምንጠብቀው ተስፋ ሳይሆን ሕያው የሆነ የአሁኑ ጊዜ እውነታ ሆኖአል። ስለዚህ የመንግሥቱ ታማኝ ደጋፊዎች እንደመሆናችን መጠን ዮሐንስ በመጀመሪያ ራእዩ የሚገልጸውን ለማወቅና ክብር የተቀዳጀው ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገራቸውን ቃላት በታዛዥነት ለማዳመጥ መፈለግ ይኖርብናል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 88-92, 215-218 ተመልከት።
b በመጀመሪያው መቶ ዘመን አንድ ጉባኤ ከአንድ ሐዋርያ መልእክት ሲደርሰው ሁሉም ጉባኤዎች ከተሰጠው ምክር እንዲጠቀሙ መልእክቱን ወደ ተለያዩ ጉባኤዎች የመላክ ልማድ ነበር።—ከቆላስይስ 4:16 ጋር አወዳድር።
c የሰሎሞን ቤተ መቅደስ የውስጥ ዕቃዎችና ጌጦች በወርቅ የተለበጡ ወይም ከወርቅ የተሠሩ ሲሆኑ የውጨኛው አደባባይ ዕቃዎች ግን ከነሐስ የተሠሩ ነበሩ።—1 ነገሥት 6:19-23, 28-35፤ 7:15, 16, 27, 30, 38-50፤ 8:64
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ሰባቱ ጉባኤዎች በነበሩባቸው ከተሞች የተደረገው የመሬት ቁፋሮ ጥናት የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገብ ትክክል መሆኑን አረጋግጦአል። በዛሬው ጊዜ በመላው ዓለም ያሉትን ጉባኤዎች የሚቀሰቅሱትን የኢየሱስ አበረታች መልእክቶች የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የተቀበሉት በእነዚህ ቦታዎች ሆነው ነበር
ጴርጋሞን
ሰምርኔስ
ትያጥሮን
ሰርዴስ
ኤፌሶን
ፊልድልፍያ
ሎዶቂያ