ምዕራፍ 15
የአምላክ መንግሥት ዜጋ መሆን
1, 2. የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለመሆን የሚያስፈልገው ነገር ምንድን ነው?
በአምላክ መንግሥት ስር በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ትፈልጋለህን? ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው ሁሉ ለዚህ ጥያቄ አዎን! የሚል መልስ ይሰጣል። በመንግሥቱ ስር አስደናቂ በረከቶች ይመጣሉ። ይሁን እንጂ እነዚህን ለማግኘት እንዲሁ እጅህን በማውጣት ብቻ ‘የአምላክ መንግሥት ዜጋ መሆን እፈልጋለሁ’ ለማለት አትችልም። ሌላም የሚያስፈልግ ነገር አለ።
2 ለምሳሌ የሌላ አገር ዜጋ ለመሆን ፈለግህ እንበል። ይህን ለማድረግ የዚያ አገር መንግሥት መሪዎች ያወጡአቸውን ግዴታዎች ማሟላት ይኖርብሃል። ይሁን እንጂ ከዚያ በፊት እነዚህ ግዴታዎች ምን እንደሆኑ መማር አለብህ። በተመሳሳይም አምላክ የመንግሥቱ ዜጎች መሆን ከሚፈልጉት ሰዎች ምን ነገር እንደሚጠይቅ መማር ያስፈልግሃል። ከዚያም እነዚህን ግዴታዎች ማሟላት ያስፈልግሃል።
እውቀት ያስፈልጋል
3. የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለመሆን እንድናሟላ የሚፈለግብን አንዱ ነገር ምንድን ነው?
3 የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለመሆን በጣም አስፈላጊ የሆነው አንዱ ግዴታ የመንግሥቱን “ቋንቋ” ማወቅ ነው። በእርግጥ ይህ ምክንያታዊ ነው። አንዳንድ ሰብዓዊ መንግሥታትም ቢሆኑ አዲስ ዜጎቸ የአገራቸውን ቋንቋ መናገር መቻልን ግዴታ ያደርጉባቸዋል። ታዲያ በአምላክ መንግሥት ስር ሕይወት የሚያገኙት ሊማሩት የሚገባቸው “ቋንቋ” ምንድን ነው?
4. የአምላክ ሕዝቦች ሊማሩት የሚገባው “ንጹሕ ቋንቋ” ምንድን ነው?
4 ይሖዋ ስለዚህ ነገር በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተናገረውን ልብ በል:- “በዚያን ጊዜም አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው [ይሖዋን (አዓት)] ያገለግሉት ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሑን ልሳን (ቋንቋ) እመልስላቸዋለሁ።” (ሶፎንያስ 3:9) ይህ “ንጹሕ ልሳን” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የአምላክ እውነት ነው። በተለይም ስለ አምላክ ንጉሣዊ መንግሥት የሚገልጸው እውነት ነው። ስለዚህ የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለመሆን ስለ ይሖዋና ስለ መንግሥቱ አደረጃጀት እውቀት በመውሰድ ይህንን “ቋንቋ” መማር ይኖርብሃል።— ቆላስይስ 1:9, 10፤ ምሳሌ 2:1-5
5. (ሀ) ስለ አምላክ መንግሥት ምን ማወቅ አለብን? (ለ) የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን እውቀት ያስፈልገናል?
5 በዛሬው ጊዜ ሰብዓዊ መንግሥታት የዜግነት መብት የሚሰጧቸውን ሰዎች ስለ መንግሥታቸው ታሪክና አሁን አገሩ እንዴት እንደሚተዳደር እንዲያውቁ ይፈልጉባቸዋል። በተመሳሳይም የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለመሆን ከፈለግህ ስለ አምላክ መንግሥት እንደዚህ ያሉትን ነገሮች ማወቅ ይኖርብሃል። ይህ እውቀት ወደ ዘላለም ሕይወት ሊመራ የሚችል ነው። ወደ አባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ ኢየሱስ:- “የዘላለም ሕይወትም ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስ ማወቅ ነው።”— ዮሐንስ 17:3 የ1980 እትም
6. (ሀ) የአምላክ መንግሥት ዜጎች ሊመልሱአቸው የሚገቡ አንዳንድ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው? (ለ) አንተስ ልትመልሳቸው ትችላለህን?
6 ያለፉትን የዚህ መጽሐፍ ምዕራፎች አጥንተህ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ ይህንን በጣም አስፈላጊ የሆነ እውቀት በብዙው አግኝተህ መሆን ይኖርበታል። ታዲያ አግኝተሃልን? እንደሚከተሉት ያሉትን ጥያቄዎች በመመለስ እውቀቱን ማግኘትህን ልታሳይ ትችላለህን? አምላክ ንጉሣዊ መንግሥት ለማቋቋም ዓላማ እንዳለው ለመጀመሪያ ጊዜ የገለጸው መቼ ነበር? የዚያ መንግሥት ምድራዊ ተገዥዎች ለመሆን ይጠባበቁ የነበሩት አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች እነማን ናቸው? የአምላክ መንግሥት ስንት ገዥዎች ወይም ነገሥታት ይኖሩታል? እነዚህ ነገሥታት የሚገዙት ከየት ሆነው ነው? በአምላክ መንግሥት ውስጥ ነገሥታት እንዲሆኑ በመጀመሪያ የተመረጡት እነማን ነበሩ? ኢየሱስ ጥሩ ንጉሥ እንደሚሆን ያስመሰከረው እንዴት ነው? ሆኖም የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለመሆን ስለ መንግሥቱ እውቀት ማግኘት አይበቃም፤ ሌላም ነገር ይፈለጋል።
የጽድቅ አኗኗር ያስፈልጋል
7. የሰው መንግሥታት ያወጡአቸው የዜግነት ብቃቶች የሚለያዩት እንዴት ነው?
7 ዛሬ መንግሥታት አዲስ ዜጎች አንዳንድ የተግባር መመዘኛዎችን እንዲያሟሉ ይፈልጉባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወንድ ሊያገባ የሚችለው አንዲት ሚስት ብቻ እንደ ሆነ፤ አንዲት ሴትም አንድ ባል ብቻ ልታገባ እንደምትችል ይገልጹ ይሆናል። ሌሎች መንግሥታት ደግሞ የተለዩ ሕጎች አሏቸው። እነዚህም ለዜጎቻቸው ከአንድ በላይ የትዳር ጓደኛ እንዲኖራቸው ይፈቅዱላቸዋል። የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎችስ ምን ዓይነት አኗኗር ይጠበቅባቸዋል? ጋብቻን በሚመለከት አምላክ ትክክለኛ ነው ብሎ የተናገረው ሥርዓት ምንድን ነው?
8. (ሀ) አምላክ ለጋብቻ ያወጣው ሥርዓት ምንድን ነው? (ለ) ምንዝር ምንድን ነው? አምላክስ ስለዚህ ነገር ምን ይላል?
8 በመጀመሪያ ይሖዋ ለአዳም አንዲት ሚስት ብቻ በመስጠት ለጋብቻ ሥርዓት አውጥቶ ነበር። አምላክ እንዲህ አለ:- “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” (ዘፍጥረት 2:21-24) ክርስቲያኖች ሊከተሉት የሚገባ ትክክለኛ ሥርዓት ይህ መሆኑን ኢየሱስ ገልጿል። (ማቴዎስ 19:4-6) የትዳር ጓደኛሞች “አንድ ሥጋ” ስለሆኑ ከሌላ ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት ቢፈጽሙ በጋብቻቸው ላይ ውርደት ያመጣሉ። ይህ ድርጊት ምንዝር ተብሎ ይጠራል። አምላክም አመንዝሮችን እንደሚቀጣ ተናግሯል።— ዕብራውያን 13:4፤ ሚልክያስ 3:5
9. (ሀ) አምላክ ሳይጋቡ የጾታ ግንኙነት ለሚፈጽሙት ሰዎች ያለው አመለካከት ምንድን ነው? (ለ) ዝሙት ምንድን ነው?
9 በሌላም በኩል፣ ብዙ ወንዶችና ሴቶች አብረው እየኖሩ የጾታ ግንኙነት ያደርጋሉ፤ ይሁን እንጂ አይጋቡም። ሆኖም አምላክ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚኖረው በጣም የሚያቀራርብ የትዳር ዝምድና በዚህ ዓይነት የሙከራ ጊዜ እንዲመሠረት ሐሳቡ አልነበረም። ስለዚህ ሳይጋቡ በአንድ ላይ መኖሩ የጋብቻን ሥርዓት ባቋቋመው አምላክ ላይ ኃጢአት መሥራት ማለት ነው። ይህ ዝሙት ተብሎ ይጠራል። ዝሙት ካላገቡት ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸም ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስም “ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ . . . ነውና ከዝሙት እንድትርቁ” ይላል። (1 ተሰሎንቄ 4:3-5) እንግዲያው ነጠላ የሆነ ሰው ከማንም ጋር የጾታ ግንኙነት ማድረጉ ስሕተት ነው።
10. የአምላክን ሕጎች የሚያስጥሱ ሌሎች የጾታ ድርጊቶች ምንድን ናቸው?
10 በዛሬው ጊዜ ብዙ ወንዶችና ሴቶች ከተመሳሳይ ጾታ ጋር ይኸውም ወንዶች ከወንዶች ጋር ሴቶችም ከሴቶች ጋር የጾታ ግንኙነት ይፈጽማሉ። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች (ሆሞ ሴክሹዋልስ) ተብለው ይጠራሉ። አንዳንድ ጊዜም ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ሴቶች ሌዝቢያንስ ተብለው ይጠራሉ። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል እነርሱ የሚያደርጉት ነገር መጥፎ እንዲሁም “አስነዋሪ” እንደሆነ ይናገራል። (ሮሜ 1:26, 27) በተጨማሪም አንድ ሰው ከእንስሳ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረጉ የአምላክን ሕግ የሚቃረን ነው። (ዘሌዋውያን 18:23) በአምላክ መንግሥት ስር ለመኖር የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ከእነዚህ የብልግና ድርጊቶች መራቅ ያስፈልገዋል።
11. (ሀ) አምላክ ስለ አልኮል መጠጦች አጠቃቀም ያለው አመለካከት ምንድን ነው? (ለ) የአምላክ መንግሥት ዜጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ ሰዎች ጤናን ከሚጎዱ ከየትኞቹ ልማዶች መራቅ ይገባቸዋል?
11 ወይን ጠጅ፣ ቢራ ወይም ሌሎች የአልኮል መጠጦችን በልክ መጠጣቱ የአምላክን ሕግ ማፍረስ አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ጥቂት ወይን ለአንድ ሰው ጤንነት ጥሩ ሊሆን እንደሚችል ያሳያል። (መዝሙር 104:15፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:23) ይሁን እንጂ መስከር ወይም ብልግና በሚፈጽሙባቸው መረን የለቀቁ ፓርቲዎች መሳተፍ የአምላክን ሕግ ማፍረስ ነው። (ኤፌሶን 5:18፤ 1 ጴጥሮስ 4:3, 4) በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ለመስከር ወይም ሞቅ እንዲላቸው የሚወስዱት የአልኮል መጠጥን ብቻ አይደለም። ለዚሁ ዓላማ በልዩ ልዩ አደንዛዥ ዕፆችም ይጠቀማሉ። እንዲሁም ደስታ ለማግኘት ማሪዋና ይወስዳሉ ወይም ትምባሆ ያጨሱ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ቢተል ነት የሚባለውን ዕፅ ወይም የጫት ቅጠሎችን ያኝኩ ይሆናል። ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሮች ሰውነታቸውን አርክሰው ጤንነታቸውን ይጎዳሉ። ስለዚህ የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለመሆን የምትፈልግ ከሆነ ከእነዚህ ጎጂ ነገሮች መራቅ ይኖርብሃል።— 2 ቆሮንቶስ 7:1
12. (ሀ) የአምላክን ሕጎች የሚቃረኑ አንዳንድ እምነት የማጉደል ድርጊቶች ምንድን ናቸው? (ለ) በእነዚህ ድርጊቶች የተጠመደ ሰው የአምላክን ሞገስ ሊያገኝ የሚችለው እንዴት ነው?
12 ሰብዓዊ መንግሥታት ወንጀለኞችን አዲስ ዜጎች አድርገው ለመቀበል እንደማይፈልጉ ግልጽ ነው። ይሖዋ የሚፈልገው የአቋም ደረጃ ግን ከእነርሱ ከፍ ያለ ነው። ‘በሁሉም ነገሮች የእውነተኝነት ጠባይ እንድናሳይ’ ይፈለግብናል። (ዕብራውያን 13:18 አዓት) ሰዎች የአምላክን ሕጎች ካልጠበቁ በአምላክ መንግሥት ውስጥ እንዲኖሩ አይፈቀድላቸውም። ዛሬ ሰዎች ብዙውን ጊዜ እውነተኛ መስለው ለመታየት ይሞክራሉ፤ ይሁን እንጂ ብዙ ሕጎች ያፈርሳሉ። አምላክ ግን ሁሉንም ነገር ለማየት ይችላል። ማንም ሊያታልለው አይችልም። (ዕብራውያን 4:13፤ ምሳሌ 15:3፤ ገላትያ 6:7, 8) ስለሆነም ይሖዋ እንደ መዋሸትና መስረቅ የመሳሰሉትን ነገሮች የሚከለክሉ ሕጎቹን የሚያፈርሱት ሰዎች ሁሉ የመንግሥቱ ዜጎች አለመደረጋቸውን ያረጋግጣል። (ኤፌሶን 4:25, 28፤ ራእይ 21:8) እንዲህም ሆኖ አምላክ ታጋሽና ይቅር ባይ ነው። ስለዚህ ኃጢአተኛ ሰው መጥፎ ነገር ማድረጉን ቢተውና መልካም ማድረግ ቢጀምር አምላክ ይቀበለዋል።— ኢሳይያስ 55:7
13. የአምላክ አገልጋዮች ለሰብዓዊ መንግሥታት ሕጎች ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?
13 የሰብዓዊ መንግሥታትን ሕጎች ስለ መጠበቅስ ምን ሊባል ይቻላል? የሰዎች መንግሥታት በምድር ላይ እስካሉ ድረስ አምላክ አገልጋዮቹ ለእነዚህ “የበላይ ባለ ሥልጣኖች” እንዲገዙ ይፈልግባቸዋል። ግብር ሊከፈላቸው ይገባል። ግብሩ በጣም ብዙ ቢሆንም ወይም አንድ ሰው የግብሩን አጠቃቀም ባይስማማበትም እንኳ ለእነርሱ ቀረጥ መክፈል ይገባዋል። በተጨማሪም የመንግሥቱ ሕጎች መከበር ይኖርባቸዋል። (ሮሜ 13:1, 7፤ ቲቶ 3:1) በዚህ ላይ ግን አንድ ሰው የተለየ አቋም የሚወስደው ሕጉን ማክበሩ የአምላክን ሕግ እንዲያፈርስ የሚያደርገው ከሆነ ብቻ ነው። እንደዚህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥም ጴጥሮስና ሐዋርያት እንዳሉት “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል።”— ሥራ 5:29
14. ስለ ሕይወት ዋጋማነት የአምላክን አመለካከት እንደያዝን እንዴት ልናሳይ እንችላለን?
14 አምላክ ለሕይወት ከፍተኛ ዋጋ ይሰጣል። የመንግሥቱ ዜጎች ለመሆን የሚፈልጉት ሁሉ ይህንን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ሰውን መግደል የአምላክን ሕግ ማፍረስ እንደሆነ ግልጽ ነው። ብዙውን ጊዜ ጥላቻ ወደ መግደል ይመራል። አንድ ሰው ባልንጀራውን መጥላቱን ከቀጠለ የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለመሆን አይችልም። (1 ዮሐንስ 3:15) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በኢሳይያስ 2:4 ላይ ባልንጀራችንን ለመግደል መሣሪያ እንዳናነሣ የሰጠውን ትእዛዝ በሥራ ላይ ማዋሉ አስፈላጊ ነው። የአምላክ ቃል ገና በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ያለ ያልተወለደ ሕፃን ሕይወትም እንኳ ሳይቀር በይሖዋ ፊት ውድ እንደ ሆነ ያሳያል። (ዘፀአት 21:22, 23፤ መዝሙር 127:3) ይህም ሆኖ በየዓመቱ በሚልዮን የሚቆጠር ፅንስ የማስወረድ ወንጀል ይፈጸማል። ይህ የሕይወት ማጥፋት ድርጊት የአምላክን ሕግ ማፍረስ ነው፤ ምክንያቱም በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ያለው ሰብዓዊ ፍጡር መገደል የማይገባው ሕያው ሰው ነው።
15. የመንግሥቱ ዜጎች የሆኑት ሁሉ አምላክ የሾመው ንጉሥ የሰጣቸውን የትኞቹን ትእዛዞች ማክበር ይኖርባቸዋል?
15 ሆኖም የአምላክ መንግሥት ዜጎች የሚሆኑት ሰዎች የተሳሳተ ወይም ስነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ከመፈጸም መቆጠባቸው አይበቃም። ከዚያም የበለጠ ነገር ይፈለግባቸዋል። ለሌሎች የደግነትና ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ነገር ለማድረግም ከልብ እንዲጥሩ ይፈለግባቸዋል። ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ:- “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” በማለት የሰጠውን አምላካዊ መመሪያ መከተል ይኖርባቸዋል። (ማቴዎስ 7:12) ለሌሎች ፍቅር በማሳየት በኩል ክርስቶስ ምሳሌ ትቶልናል። እርሱ ሕይወቱን ለሰው ዘር ሰጥቷል፤ ተከታዮቹንም “እኔ እንደወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” ብሎ አዟቸዋል። (ዮሐንስ 13:34፤ 1 ዮሐንስ 3:16) በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ስር መኖርን አስደሳች የሚያደርገው እንደዚህ ያለው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅርና ለሌሎች አሳቢ መሆኑ ነው።— ያዕቆብ 2:8
16, 17. (ሀ) አምላክ የሚፈልግብንን ነገሮች ለማሟላት በሕይወታችን ውስጥ ለውጦችን ለማድረግ ምን ጥሩ ምክንያቶች አሉን? (ለ) አስፈላጊ የሆነ ማንኛውንም ለውጥ ማድረግ እንደምንችል እርግጠኞች ለመሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
16 ሰዎች የአምላክ መንግሥት ዜጎች ለመሆን የሚያስችሏቸውን ብቃቶች ለማሟላት በሕይወታቸው ውስጥ ልዩ ልዩ ለውጦችን ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። (ኤፌሶን 4:20–24) እነዚህን ለውጦች ለማድረግ እየጣርክ ነውን? በእርግጥም ማንኛውም ዓይነት ጥረት ሊደረግለት የሚገባው ነገር ነው! ለምን? በአንድ ዓይነት ሰብዓዊ መንግሥት ስር ለጥቂት ዓመታት የተሻለ ሕይወት ለማግኘት ብለን አይደለም። ከዚህ ይልቅ በአምላክ በሚገዛ መንግሥት ስር ገነት በምትሆነዋ ምድር ላይ ከፍጹም ጤንነት ጋር የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ!
17 አሁንም እንኳ ቢሆን አምላክ የሚፈልግብህን ነገሮች በማሟላትህ ሕይወትህ የበለጠ ደስታ ያለበት ይሆንልሃል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል። ጥላቻ ወይም ስግብግብነት የነበረባቸው በጣም ብዙ ሰዎች ተለውጠዋል። እንዲሁም ዝሙት የሚሠሩ፣ አመንዝሮች፣ ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች፣ ሰካራሞች፣ ነፍሰ ገዳዮች፣ ሌቦች፣ የዕፅ ሱሰኞችና በትምባሆ የሚጠቀሙ ሰዎች የአኗኗር መንገዳቸውን ለውጠዋል። ይህንንም ሊያደርጉ የቻሉት ከፍተኛ ጥረት በማድረግና በአምላክ እርዳታ ነው። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11፤ ቆላስይስ 3:5-9) ስለዚህ አምላክ የሚፈልግብህን ለማሟላት ከበድ ያለ ለውጥ ማድረግ ቢያስፈልግህ ተስፋ ቆርጠህ አታቁም። ለማሸነፍ ትችላለህ።
ለአምላክ መንግሥት በታማኝነት መቆም
18. አምላክ ለመንግሥቱ በምን ልዩ መንገድ የታማኝነት ድጋፍ እንድንሰጥ ይፈልግብናል?
18 ይሖዋ አምላክ ተገዢዎቹ ለንጉሣዊ መንግሥቱ ታማኝ ሆነው እንዲቆሙ መጠየቁ የሚያስደንቅ ሊሆን አይገባውም። የሰዎች መንግሥታትም ከዜጎቻቸው ተመሳሳይ ነገር ይጠይቃሉ። ይሁን እንጂ አምላክ በምን የተለየ መንገድ የታማኝነት ድጋፍ እንዲሰጥ ይፈልጋል? ዜጎቹ የጦር መሣሪያ ይዘው ለመንግሥቱ በመዋጋት ነውን? አይደለም። ከዚህ ይልቅ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስና እንደ መጀመሪያዎቹ ተከታዮቹ የአምላክ መንግሥት ታማኝ አፈ ቀላጤዎች ወይም አዋጅ ነጋሪዎች መሆን ይኖርባቸዋል። (ማቴዎስ 4:17፤ 10:5-7፤ 24:14) መንግሥቱ ምን እንደሆነና የሰውን ዘር ችግሮች እንዴት እንደሚፈታ እያንዳንዱ ሰው እንዲያውቅ የይሖዋ ፈቃድ ነው። ከአምላክ ቃል ውስጥ የተማርካቸውን ነገሮች ለዘመዶችህ፣ ለጓደኞችህና ለሌሎች አካፍለሃልን? ይህንን ማድረግህ የአምላክ ፈቃድ ነው።— ሮሜ 10:10፤ 1 ጴጥሮስ 3:15
19. (ሀ) ለሌሎች ስለ አምላክ መንግሥት ስንናገር ተቃውሞ እንደሚደርስ ልንጠብቅ የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ መስጠት አለብህ?
19 ክርስቶስና የመጀመሪያዎቹ ተከታዮቹ ስለ መንግሥቱ ለሌሎች ለመናገር ድፍረት አስፈልጓቸዋል፤ ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ ተቃውሞ ያጋጥማቸው ነበር። (ሥራ 5:41, 42) ዛሬም ቢሆን ሁኔታው ያው ነው። ይህ በዲያብሎስ የሚገዛ ዓለም የአምላክ መንግሥት የምሥራች እንዲሰበክ አይፈልግም። ስለዚህ አሁን የሚነሡት ጥያቄዎች ‘በየትኛው ወገን ትቆማለህ? ለአምላክ መንግሥት የታማኝነት ድጋፍ ትሰጣለህን?’ የሚሉት ናቸው። የእርሱ ፈቃድ ፍጻሜው ከመምጣቱ በፊት ታላቅ የመንግሥት ምስክርነት እንዲሰጥ ነው። አንተስ ይህንን ምስክርነት በመስጠቱ ላይ ትካፈላለህን?
[በገጽ 128 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ መንግሥት ዜጋ የሚሆኑ ሁሉ ስለ መንግሥቱ ሁኔታ ማወቅ ይኖርባቸዋል
[በገጽ 131 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የአምላክ መንግሥት ዜጎች አምላክ ካወገዛቸው ድርጊቶች መራቅ አለባቸው
[በገጽ 133 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ መንግሥት ዜጎች ለሌሎች ስለ መንግሥቱ መናገር አለባቸው