ምዕራፍ 21
ኢየሱስ ባደገባት ከተማ ውስጥ በሚገኝ ምኩራብ
ኢየሱስ ወዳደገባት ወደ ናዝሬት ሲመለስ በከተማይቱ ውስጥ ልዩ ስሜት እንደተቀሰቀሰ ምንም አያጠራጥርም። ኢየሱስ ከአንድ ዓመት ብዙም ከማይበልጥ ጊዜ በፊት በዮሐንስ ለመጠመቅ ከናዝሬት ሲወጣ ይታወቅ የነበረው በአናጢነቱ ነበር። አሁን ግን ተአምር የሚፈጽም ሰው መሆኑ በስፋት ተወርቷል። በከተማዋ የሚኖሩ ሰዎች በመካከላቸው አንዳንድ ተአምራት ሲሠራ ለመመልከት ጓጉተው ነበር።
ኢየሱስ እንደ ልማዱ በከተማዋ ውስጥ ወደሚገኘው ምኩራብ ሲሄድ ጉጉታቸው ይበልጥ ተቀሰቀሰ። የአምልኮ ሥርዓት እየተከናወነ በነበረበት ወቅት ኢየሱስ ለማንበብ ተነሣ፤ የነቢዩን የኢሳይያስን ጥቅልል ሰጡት። በይሖዋ መንፈስ ስለ ተቀባው ሰው የሚናገረውን ቦታ አገኘ፤ ይህ በዛሬው ጊዜ ባለው መጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ምዕራፍ 61 ላይ ይገኛል።
ይህ ሰው በምርኮ ላሉት ነፃነትን፣ ለዓይነ ስውራን ደግሞ ማየትን እንዴት እንደሚሰብክ የሚገልጸውን ሐሳብና ስለ ተወደደችው የእግዚአብሔር ዓመት የሚናገረውን ሐሳብ ካነበበ በኋላ ጥቅልሉን ለአገልጋዩ መልሶ ተቀመጠ። የሁሉም ዓይኖች እሱ ላይ ተተክለዋል። ኢየሱስ በመቀጠል “ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ” ብሎ በመግለጽ ረዘም ላለ ጊዜ ሳይናገር አልቀረም። (ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።)
ሰዎቹ ከአፉ ከሚወጣው “ከጸጋው ቃል” የተነሣ ተገርመው “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” ይባባሉ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ተአምራት ሲፈጽም ለመመልከት እንደፈለጉ በመገንዘብ እንዲህ አለ:- “ያለ ጥርጥር ይህን ምሳሌ:- ባለ መድኃኒት ሆይ፣ ራስህን ፈውስ፤ በቅፍርናሆም እንዳደረግኸው የሰማነውን ሁሉ በዚህ አድርግ ትሉኛላችሁ።” ቀደም ሲል የኢየሱስ ጎረቤቶች የነበሩት እነዚህ ሰዎች ፈውስ መጀመሪያ ለራስ አገር ሰዎች ጥቅም ሲባል ከአገር መጀመር አለበት የሚል ስሜት እንደነበራቸው ከአባባሉ መረዳት ይቻላል። ስለዚህ ኢየሱስ የናቃቸው መሰላቸው።
ኢየሱስ አስተሳሰባቸው ገባውና ከሁኔታው ጋር የሚሄዱ አንዳንድ ታሪኮች ነገራቸው። በኤልያስ ዘመን በእስራኤል ውስጥ ብዙ መበለቶች እንደነበሩ ጠቀሰላቸው፤ ሆኖም ኤልያስ ወደነዚህ መበለቶች አልተላከም። ከዚህ ይልቅ በሲዶና ወደምትኖር አንዲት እስራኤላዊት ያልሆነች መበለት ዘንድ ሄደና ሕይወት አድን የሆነ ተአምር ፈጸመ። በኤልሳዕም ዘመን ብዙ የሥጋ ደዌ የያዛቸው ሰዎች ነበሩ፤ ሆኖም ኤልሳዕ ከዚህ ደዌ ያነጻው የሶርያውን ንዕማንን ብቻ ነው።
በምኩራቡ የነበሩት ሰዎች ራስ ወዳድነታቸውንና እምነተ ቢስነታቸውን በሚያጋልጡት በእነዚህ ወቀሳ አዘል ታሪካዊ ንጽጽሮች በመቆጣት ኢየሱስን ከከተማው አስወጡት። የናዝሬት ከተማ ከተቆረቆረችበት ተራራ ጫፍ ላይ ሊወረውሩት ሞከሩ። ሆኖም ኢየሱስ ከእጃቸው አምልጦ በሰላም ሄደ። ሉቃስ 4:16-30፤ 1 ነገሥት 17:8-16፤ 2 ነገሥት 5:8-14
▪ ናዝሬት ውስጥ ልዩ ስሜት ተቀስቅሶ የነበረው ለምንድን ነው?
▪ ሰዎቹ የኢየሱስን ንግግር ሲሰሙ ምን ስሜት አደረባቸው? ሆኖም በኋላ በጣም እንዲቆጡ ያደረጋቸው ነገር ምንድን ነው?
▪ ሰዎቹ ኢየሱስን ምን ሊያደርጉት ሞክረው ነበር?