ምዕራፍ 3
እውነተኛው አምላክ ማን ነው?
1. ብዙዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ቃላት ጋር የሚስማሙት ለምንድን ነው?
በጠራ ሌሊት ሰማዩን አሻቅበህ ስትመለከት በምታያቸው ከዋክብት ብዛት አትደነቅም? እነዚህ ሁሉ ከዋክብት እንዴት ሊገኙ ቻሉ? ደማቅ ቀለም ያላቸው አበቦች፣ አስደሳች ዝማሬ የሚያሰሙ አእዋፍ፣ በውቅያኖስ ላይ የሚቦርቁ ዓሣ ነባሪዎች፣ በጠቅላላው በምድር ላይ የምናያቸው ሕያዋን ፍጥረታትስ? አስደናቂ የሆኑትን ፍጥረታት ዘርዝረን ለመጨረስ አንችልም። ይህ ሁሉ በአጋጣሚ ሊገኝ አይችልም። ብዙ ሰዎች “በመጀመሪያም እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” በሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ የመክፈቻ ቃላት የሚስማሙ መሆናቸው አያስደንቅም!— ዘፍጥረት 1:1
2. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ምን ይላል? ምን እንድናደርግስ ያበረታታናል?
2 የሰው ልጅ ስለ አምላክ በሚነሱ ጥያቄዎች ረገድ በእጅጉ የተከፋፈለ ነው። አንዳንዶች እግዚአብሔር የተወሰነ አካል የሌለው አንድ ኃይል ነው ይላሉ። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክ በጣም ሩቅና ሊቀረብ የማይቻል ነው ብለው በማሰብ የሞቱ የቀድሞ አባቶቻቸውን ያመልካሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን እውነተኛው አምላክ የተወሰነ አካል ያለው እንደሆነና ስለ እያንዳንዳችንም አጥብቆ እንደሚያስብ ያመለክታል። “ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም” በማለት ‘አምላክን እንድንፈልግ’ የሚያበረታታንም በዚህ ምክንያት ነው።— ሥራ 17:27
3. አምላክ ይህን ይመስላል ብሎ ምስል መሥራት የማይቻለው ለምንድን ነው?
3 አምላክ ምን ይመስላል? አንዳንድ አገልጋዮቹ በዙሪያው ያለውን ታላቅ ግርማ በራእይ ተመልክተዋል። በእነዚህ ራእዮች እርሱ በዙፋን እንደተቀመጠና ከእርሱም በጣም ብሩሕ የሆነ ብርሃን እንደሚፈነጥቅ ሆኖ ታይቷል። ይሁን እንጂ እንደነዚህ ያሉትን ራእዮች ከተመለከቱት ሰዎች አንዳቸውም ቢሆኑ የፊቱ መልክ ይህን ይመስላል ብለው አልገለጹም። (ዳንኤል 7:9, 10፤ ራእይ 4:2, 3) ይህ የሆነው ‘አምላክ መንፈስ ስለሆነና’ ሥጋዊ አካል ስለ ሌለው ነው። (ዮሐንስ 4:24) እንዲያውም “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ” ስለ ሌለ ፈጣሪያችን ይህን ይመስላል ብለን ትክክለኛ መልክ ልንሰጠው አንችልም። (ዮሐንስ 1:18፤ ዘጸአት 33:20) ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ብዙ የሚያስተምረን ነገር አለ።
እውነተኛው አምላክ ስም አለው
4. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለአምላክ ከተሰጡት ትርጉም አዘል የማዕረግ ስሞች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
4 እውነተኛው አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ኤልሻዳይ” ወይም ሁሉን የሚችል አምላክ፣ “ልዑል”፣ “ታላቅ ፈጣሪ”፣ “ታላቅ አስተማሪ”፣ “ልዑል ጌታ” እና “የዘላለም ንጉሥ” በሚሉ ቃላት ተጠርቷል። (ዘፍጥረት 17:1፤ መዝሙር 50:14፤ መክብብ 12:1፤ ኢሳይያስ 30:20፤ ሥራ 4:24፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:17 አዓት) እንደነዚህ ስላሉት የማዕረግ ስሞች ቆም ብለን ብናሰላስል ስለ አምላክ ያለን እውቀት ያድጋል።
5. የአምላክ ስም ማን ነው? በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችስ ምን ያህል ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል?
5 ይሁን እንጂ አምላክ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ብቻ 7,000 ጊዜ ያህል የተጠቀሰ ልዩ ስም አለው። ይህ ስም ቀደም ብለን ከተመለከትናቸው የማዕረግ ስሞች ሁሉ ይበልጥ ብዙ ጊዜ ተጠቅሷል። አይሁዳውያን ከ1,900 ዓመታት በፊት በአጉል አስተሳሰብ ምክንያት መለኮታዊውን ስም መጥራት አቆሙ። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት የዕብራይስጥ ቋንቋ አናባቢ ፊደላት አልነበሩትም። በዚህም ምክንያት ሙሴ፣ ዳዊት፣ ወይም ሌሎቹ የጥንት ሰዎች መለኮታዊውን ስም ይወክሉ የነበሩትን አራት ተነባቢ ፊደላት (יהוה) እንዴት ያነቡ እንደነበረ ለማወቅ አልተቻለም። አንዳንድ ምሁራን የአምላክ ስም “ያህዌህ” ተብሎ ይጠራ ነበር ቢሉም ለዚህ አባባላቸው እርግጠኛ ሊሆኑ አልቻሉም። በአማርኛ ስሙ “ይሖዋ” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በብዙ ሌሎች ቋንቋዎችም ከዚህ አጠራር ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው አጠራሮች ሰፊ ተቀባይነት ለማግኘት ችለዋል።— ዘጸአት 6:3ን በ1879 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ እትም ተመልከት።
በአምላክ ስም መጠቀም የሚኖርብህ ለምንድን ነው?
6. በይሖዋ ስም መጠቀም የሚኖርብን ለምንድን ነው?
6 ይሖዋ የተባለው ስም አምላክ ብቻ የሚጠራበት ሲሆን እርሱን ከሌሎች አማልክት ለመለየት ያገለግላል። በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ በተለይም በዕብራይስጡ ክፍል ይህን ያህል ብዙ ጊዜ ተጠቅሶ የምናገኘው በዚህ ምክንያት ነው። ብዙ ተርጓሚዎች መለኮታዊውን ስም ባይጠቀሙበትም በአንዳንድ የአማርኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መሠረት “እግዚአብሔር” የሚለው መጠሪያ “ይሖዋ” የሚለውን የዕብራይስጥ ስም ያመለክታል። ስለዚህ ስለ አምላክ በምንናገርበት ጊዜ በስሙ መጠቀም ይገባናል።
7. ይሖዋ የሚለው ስም ትርጉም ስለ አምላክ ምን ያስተምረናል?
7 ይሖዋ የሚለው ስም “መሆን” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ግሥ የተገኘ ነው። ስለዚህ የአምላክ ስም “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም አለው። ይሖዋ በዚህ ስሙ ታላቅ ዓላማ ያለው አምላክ መሆኑን አሳውቋል። ምን ጊዜም ቢሆን ዓላማዎቹ እውን እንዲሆኑ ያደርጋል። የሰው ልጆች ስለ እቅዶቻቸው መሳካት እርግጠኛ ሊሆኑ ስለማይችሉ ይህን ስም ሊሸከም የሚችለው እውነተኛው አምላክ ብቻ ነው። (ያዕቆብ 4:13, 14) “ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ . . . የላክሁትንም ይፈጽማል” ሊል የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው።— ኢሳይያስ 55:11
8. ይሖዋ በሙሴ በኩል ምን ዓላማ እንዳለው አስታውቋል?
8 ዕብራውያን አባቶች የነበሩት አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ‘የይሖዋን ስም የጠሩ’ ቢሆንም የመለኮታዊውን ስም ሙሉ ትርጉም አላወቁም። (ዘፍጥረት 21:33፤ 26:25፤ 32:9፤ ዘጸአት 6:3) ይሖዋ ቆየት ብሎ የእነዚህን አባቶች ዝርያዎች ከግብፅ ባርነት አውጥቶ “ወተትና ማር” የምታፈስስ ምድር ሊሰጣቸው ዓላማ እንዳለው በተናገረ ጊዜ ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነገር መስሎ ታይቷቸው ሊሆን ይችላል። (ዘጸአት 3:17) ይሁን እንጂ አምላክ ለነቢዩ ሙሴ እንደሚከተለው ብሎ በመናገር ስሙ ያዘለውን ዘላለማዊ ትርጉም ገልጿል:- “የአባቶቻችሁ አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] ወደ እናንተ ላከኝ፤ ይህ ለዘላለሙ ስሜ ነው፣ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ይህ ነው።”— ዘጸአት 3:15
9. ፈርዖን ለይሖዋ ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው?
9 ሙሴ የግብፁን ንጉሥ ፈርዖንን እስራኤላውያን ወደ ምድረ በዳ ሄደው ይሖዋን እንዲያመልኩ እንዲለቃቸው ጠየቀው። ራሱ እንደ አምላክ ይታይ የነበረውና ሌሎችን የግብፃውያን አማልክት ያመልክ የነበረው ፈርዖን ግን “ቃሉን እሰማ ዘንድ እስራኤልንስ እለቅቅ ዘንድ እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] ማን ነው? እግዚአብሔርን [“ይሖዋን” አዓት] አላውቅም፣ እስራኤልንም ደግሞ ልለቅቅም” ሲል መለሰ።— ዘጸአት 5:1, 2
10. ይሖዋ ለእስራኤላውያን የነበረውን ዓላማ ለማስፈጸም በጥንትዋ ግብፅ ላይ ምን እርምጃ ወሰደ?
10 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ዓላማውን ለመፈጸም ሲል ሁኔታው የሚጠይቀውን እርምጃ በመውሰድ ከስሙ ትርጉም ጋር የሚስማማ ነገር አድርጓል። በጥንቶቹ ግብፃውያን ላይ አሥር መቅሠፍት አወረደባቸው። የመጨረሻው መቅሠፍት የእብሪተኛውን ፈርዖን ወንድ ልጅ ጨምሮ የግብፅን በኩራት በሙሉ ገደለ። በዚህ ጊዜ ግብፃውያን እስራኤላውያን ቶሎ እንዲወጡላቸው ፈለጉ። አንዳንድ ግብፃውያን ግን ልባቸው በይሖዋ ኃያልነት በጣም ስለተነካ ከእስራኤላውያን ጋር ሆነው ከግብፅ ወጡ።— ዘጸአት 12:35–38
11. ይሖዋ በቀይ ባሕር ምን ተአምር አደረገ? ጠላቶቹስ ምን ነገር ለመቀበል ተገደዋል?
11 እልከኞቹ ፈርዖንና ሠራዊቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር ሠረገሎች ይዘው ባሮቹን እስራኤላውያን አንቀው ለመመለስ ተነሱ። ግብፃውያኑ ወደ እስራኤላውያን ሊደርሱ በተቃረቡ ጊዜ አምላክ በተአምር ቀይ ባሕርን ስለከፈለ አስራኤላውያን በደረቅ ምድር ሊሻገሩ ቻሉ። ያባርሯቸው የነበሩት ጭፍሮች ወደ ደረቀው መሬት በገቡ ጊዜ ይሖዋ ‘የሠረገሎቻቸውን መንኮራኩር ስላሰረባቸው’ ወደፊት መጓዝ በጣም አስቸጋሪ ሆነባቸው። “ግብፃውያንም:- እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] በግብፃውያን ላይ ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ አሉ።” ይሁን እንጂ ሊሸሹ የሚችሉበት ጊዜ አልፎባቸው ስለነበረ ወደ ኋላቸው ለመመለስ አልቻሉም። እንደ ግድግዳ ቆሞ የነበረው ውኃ ተደረመሰና “ሰረገሎችን፣ ፈረሰኞችንም የፈርዖንንም ሠራዊት ሁሉ ከደነ፤ ከእነርሱም አንድ ስንኳ አልቀረም።” (ዘጸአት 14:22–25, 28) በዚህ መንገድ ይሖዋ ለራሱ ታላቅ ስም ለማትረፍ ችሏል። ይህ ክንውን እስከ ዛሬ ድረስ አልተረሳም።— ኢያሱ 2:9–11
12, 13. (ሀ) ዛሬስ የአምላክ ስም ለእኛ ምን ትርጉም አለው? (ለ) ሰዎች በአስቸኳይ ምን ነገር ማወቅ ያስፈልጋቸዋል? ለምንስ?
12 አምላክ በዚያ ጊዜ ለራሱ ያተረፈው ስም በዛሬው ጊዜ ለምንኖረውም ታላቅ ትርጉም አለው። ይሖዋ የተባለው ስሙ ዓላማውን እንደሚፈጽምና እውን እንደሚያደርግ ዋስትና ይሆነናል። ዓላማው ደግሞ ምድራችን ገነት እንድትሆን ያወጣውን የመጀመሪያ ዓላማ መፈጸምን ይጨምራል። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:8) አምላክ ይህን ዓላማውን ለማስፈጸም ሉዓላዊነቱን የሚቃወሙትን በሙሉ ያስወግዳል። “እኔም እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] እንደ ሆንሁ ያውቃሉ” ብሏል። (ሕዝቅኤል 38:23) ከዚያ በኋላ አምላክ የሚያመልኩትን ሰዎች ከዚህ ዓለም መከራ ለማዳንና ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለማኖር የገባውን ቃል ይፈጽማል።— 2 ጴጥሮስ 3:13
13 የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ስሙን አውቀው በእምነት ሊጠሩት ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ “የጌታን [“የይሖዋን” አዓት] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” የሚል ተስፋ ይሰጣል። (ሮሜ 10:13) አዎን፣ ይሖዋ የተባለው ስም ብዙ ትርጉም ያዘለ ስም ነው። ይሖዋን አምላክህና አዳኝህ አድርገህ በመመልከት ስሙን መጥራትህ ፍጻሜ የሌለው ደስታ ያመጣልሃል።
የእውነተኛው አምላክ ባሕርያት
14. መጽሐፍ ቅዱስ የትኞቹን የአምላክ መሠረታዊ ባሕርያት ያጎላል?
14 ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፅ ጭቆና ያዳነበትን ሁኔታ ስናጠና አምላክ ፍጹም በሆነ ሚዛናዊነት የሚያንጸባርቃቸው አራት መሠረታዊ ባሕርያቱ ጎላ ብለው ይታዩናል። በጣም ታላቅ የሆነው ኃይሉ በፈርዖን ላይ ባደረጋቸው ነገሮች ተገልጧል። (ዘጸአት 9:16) አምላክ ይህን ውስብስብ የሆነ ሁኔታ ለማስተካከል የተጠቀመባቸው የረቀቁ ዘዴዎች ተወዳዳሪ የማይገኝለት ጥበብ ያለው አምላክ መሆኑን አሳይተዋል። (ሮሜ 11:33) ሕዝቦቹን በእልከኝነት ይጨቁኑና ይቃወሙ የነበሩትን ሰዎች በመቅጣቱ የፍትሕ አምላክ መሆኑን አሳይቷል። (ዘዳግም 32:4 አዓት) ከእነዚህ ሁሉ የሚበልጠው የአምላክ ባሕርይ ፍቅር ነው። ይሖዋ ለአብርሃም ዘሮች የገባውን ቃል በመፈጸም በጣም ታላቅ የሆነውን ፍቅሩን ገልጧል። (ዘዳግም 7:8) በተጨማሪም አንዳንድ ግብፃውያን የሐሰት አማልክትን ትተው ከእውነተኛው አምላክ ጎን እንዲቆሙ በመፍቀድና ብዙ እንዲጠቀሙ በማስቻል ፍቅር አሳይቷቸዋል።
15, 16. አምላክ ፍቅር ያሳየው በምን መንገዶች ነው?
15 መጽሐፍ ቅዱስን በምታነብበት ጊዜ ፍቅር ዋነኛው የአምላክ ባሕርይ እንደሆነና ይህንንም ባሕርይ በብዙ መንገዶች እንዳሳየ ታስተውላለህ። ለምሳሌ ያህል ፈጣሪ የሆነውና የሕይወትን ደስታ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመንፈሳዊ ፍጥረታት ጋር የተጋራው በፍቅር ተነሳስቶ ነው። እነኚህ በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ መላእክት በሙሉ አምላክን ይወዱታል፣ ያወድሱታልም። (ኢዮብ 38:4, 7፤ ዳንኤል 7:10) በተጨማሪም አምላክ ምድርን በመፍጠርና የሰው ልጅ በደስታ የሚኖርባት ሥፍራ እንድትሆን አድርጎ በማዘጋጀት ፍቅሩን አሳይቷል።— ዘፍጥረት 1:1, 26–28፤ መዝሙር 115:16
16 ከአምላክ ፍቅር የምንጠቀምባቸውን የተለያዩ መንገዶች ዘርዝረን ለመጨረስ አንችልም። በመጀመሪያ ደረጃ አምላክ በሕይወት ለመደሰት እንድንችል የሰውነታችንን ክፍሎች ግሩም አድርጎ በመሥራት ፍቅሩን አሳይቷል። (መዝሙር 139:14) “ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፣ ልባችንንም በመብልና በደስታ” በመሙላት ፍቅሩን አሳይቶናል። (ሥራ 14:17) እንዲያውም አምላክ “በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፣ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባል።” (ማቴዎስ 5:45) በተጨማሪም ፈጣሪያችን በፍቅር ተገፋፍቶ ስለ እርሱ እውነተኛ እውቀት እንድናገኝና አምላኪዎቹ በመሆን በደስታ እንድናገለግለው ይረዳናል። በእርግጥም “እግዚአብሔር ፍቅር ነው።” (1 ዮሐንስ 4:8) ይሁን እንጂ ባሕርያቱ እነዚህ ብቻ አይደሉም።
‘መሐሪና ሞገስ ያለው አምላክ’
17. በዘጸአት 34:6, 7 ላይ ስለ አምላክ ምን ነገር እንማራለን?
17 እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን ከተሻገሩ በኋላም ቢሆን አምላክን በይበልጥ ማወቅ አስፈልጓቸው ነበር። ሙሴም ይህን ተገንዝቦ ስለነበረ “አሁንም በፊትህ ሞገስን አግኝቴ እንደ ሆነ፣ አውቅህ ዘንድ በፊትህም ሞገስን አገኝ ዘንድ መንገድህን እባክህ አሳየኝ” ሲል ጸልዮአል። (ዘጸአት 33:13) አምላክ ራሱ “እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፣ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፣ አበሳንና መተላለፍን ይቅር የሚል፣ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ [“ሳይቀጣ የማያልፍ” አዓት]” ብሎ ሲያውጅ ሙሴ በመስማቱ አምላክን ይበልጥ ለማወቅ ችሏል። (ዘጸአት 34:6, 7) አምላክ ፍቅሩንና ፍትሑን ጎን ለጎን እንዲሄዱ በማድረግ የነገሮችን ሚዛን ስለሚጠብቅ ሆን ብለው ኃጢአት የሚሠሩ ሰዎች የጥፋታቸውን ውጤት እንዳያገኙ ከለላ አይሆንላቸውም።
18. ይሖዋ መሐሪ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
18 ይሖዋ ምሕረት የሚያሳይ መሆኑን ሙሴ ተገንዝቧል። መሐሪ የሆነ ሰው ችግር ለደረሰባቸው ሰዎች ስለሚያዝን ከችግራቸው የሚወጡበትን መንገድ እንዲያገኙ ለመርዳት ይሞክራል። አምላክም የሰው ልጆች ከመከራ፣ ከበሽታና ከሞት ለዘለቄታው የሚገላገሉበትን ዝግጅት በማድረግ መሐሪነቱን አሳይቷል። (ራእይ 21:3–5) የእግዚአብሔር አምላኪዎች በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ በሚያጋጥሟቸው ሁኔታዎች ምክንያት ችግር ሊደርስባቸው ወይም ጥበብ የጎደለው ድርጊት በመፈጸም መከራ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ። ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ወደ አምላክ ከቀረቡና ይሖዋ እንዲረዳቸው ከጠየቁ ግን ያጽናናቸዋል፣ ይረዳቸዋል። ለምን? ለአምላኪዎቹ ስለሚራራና በምሕረት ዓይንም ስለሚያያቸው ነው።— መዝሙር 86:15፤ 1 ጴጥሮስ 5:6, 7
19. አምላክ ሞገስ አለው ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?
19 በሥልጣን ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ሌሎችን ያንገላታሉ። ይሖዋ ግን ትሑታን ለሆኑ አገልጋዮቹ ሞገስ ያሳያል። በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ ከእርሱ ጋር የሚተካከል ባለ ሥልጣን ባይኖርም ለመላው የሰው ልጆች አጠቃላይ በሆነ መንገድ ልዩ ደግነት ያሳያል። (መዝሙር 8:3, 4፤ ሉቃስ 6:35) በተጨማሪም ይሖዋ ግለሰቦች የሚያቀርቡትን ልመና በመስማት ብዙ ሞገስ ያሳያቸዋል። (ዘጸአት 22:26, 27፤ ሉቃስ 18:13, 14) እርግጥ፣ አምላክ ለማንም ቢሆን ሞገስ ወይም ምሕረት የማሳየት ግዴታ የለበትም። (ዘጸአት 33:19) ስለዚህ ለአምላክ ምሕረትና ሞገስ የጠለቀ አድናቆት ማሳየት ያስፈልገናል።— መዝሙር 145:1, 8
ለቁጣ የዘገየ፣ የማያዳላና ጻድቅ
20. ይሖዋ ለቁጣ የዘገየና የማያዳላ መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?
20 ይሖዋ ለቁጣ የዘገየ አምላክ ነው። ይህ ማለት ግን ምንም ዓይነት እርምጃ አይወስድም ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም እልከኛውን ፈርዖንና ሠራዊቱን በቀይ ባሕር ደምስሷል። በተጨማሪም ይሖዋ የማያዳላ አምላክ ነው። በዚህም ምክንያት ልዩ ሞገስ አግኝተው የነበሩት ሕዝቦቹ እስራኤላውያን ደጋግመው ጥፋት በሠሩ ጊዜ ሞገሱን አጥተዋል። ይሖዋ ከሁሉም ብሔራት የመጡ ሰዎች አምላኪዎቹ እንዲሆኑ የሚቀበል ቢሆንም የሚቀበለው ከጽድቅ መንገዶቹ ጋር የሚስማሙትን ብቻ ነው።— ሥራ 10:34, 35
21. (ሀ) ራእይ 15:2–4 ስለ አምላክ ምን ነገር ያስተምረናል? (ለ) አምላክ ትክክል ናቸው የሚላቸውን ነገሮች ለማድረግ ቀላል የሚሆንልን ምን ብናደርግ ነው?
21 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ ስለ አምላክ ‘የጽድቅ ፍርዶች’ ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን አጠንክሮ ይገልጻል። የሰማይ ፍጥረታት እንደሚከተለው በማለት እንደሚዘምሩ ይነግረናል:- “ሁሉን የምትችል ጌታ አምላክ ሆይ! ሥራህ ታላቅና አስደናቂ ነው፤ የሕዝቦች ንጉሥ ሆይ! መንገድህ ትክክልና እውነት ነው፤ ጌታ ሆይ! አንተን የማይፈራና ስምህንም የማያከብር ማን ነው? ምክንያቱም ቅዱስ አንተ ብቻ ነህ፤ የእውነት ፍርድህ ስለተገለጠ፣ ሕዝቦች ሁሉ መጥተው በፊትህ ይሰግዳሉ።” (ራእይ 15:2–4 የ1980 ትርጉም) ይሖዋ ትክክል ናቸው ከሚላቸው ነገሮች ጋር የሚስማማ ነገር በማድረግ ለእርሱ ጤናማ ፍርሃት እንዳለን ወይም እርሱን ቅዱስ አድርገን እንደምንመለከት እናሳያለን። ሁልጊዜ የአምላክን ጥበብና ፍቅር ብናስታውስ ይህን ማድረግ ቀላል ይሆንልናል። ትእዛዞቹ ሁሉ እኛን የሚጠቅሙ ናቸው።— ኢሳይያስ 48:17, 18
“አምላካችን ይሖዋ አንድ ነው”
22. መጽሐፍ ቅዱስን የሚቀበሉ ሁሉ ሥላሴን የማያመልኩት ለምንድን ነው?
22 የጥንቶቹ ግብፃውያን ብዙ አማልክት ያመልኩ ነበር። ይሖዋ ግን ‘እርሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ አምላክ ነው።’ (ዘጸአት 20:5) ሙሴ “አምላካችን ይሖዋ አንድ ይሖዋ ነው” በማለት እስራኤላውያንን አስገንዝቦ ነበር። (ዘዳግም 6:4 አዓት) ኢየሱስ ክርስቶስም እነዚህኑ ቃላት በድጋሚ ተናግሯል። (ማርቆስ 12:28, 29) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚቀበሉ ሁሉ ሥላሴን ወይም ሦስትነት በአንድነት ያለውን አምላክ አያመልኩም። እንዲያውም “ሥላሴ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። እውነተኛው አምላክ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተለየ አንድ አካል ነው። (ዮሐንስ 14:28፤ 1 ቆሮንቶስ 15:28) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የራሱ የተወሰነ አካል ወይም ሕልውና ያለው ነገር አይደለም። ሁሉን የሚችለው አምላክ ይሖዋ ዓላማዎቹን ለማከናወን የሚጠቀምበት አንቀሳቃሽ ኃይሉ ነው።— ዘፍጥረት 1:2፤ ሥራ 2:1–4, 32, 33፤ 2 ጴጥሮስ 1:20, 21
23. (ሀ) ለአምላክ ያለህ ፍቅር እያደገ የሚሄደው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ አምላክን ስለመውደድ ምን ብሏል? ስለ ክርስቶስስ ምን ማወቅ ያስፈልገናል?
23 ይሖዋ ምን ያህል አስደናቂ አምላክ እንደሆነ ስትመለከት በእርግጥ ሊመለክ የሚገባው አምላክ ነው ቢባል አትስማማም? የይሖዋ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ ባጠናህ መጠን ይሖዋን በይበልጥ ልታውቀውና ዘላለማዊ የሆነ ደኅንነትና ደስታ ለማግኘት ከአንተ ምን እንደሚፈልግ ልትረዳ ትችላለህ። (ማቴዎስ 5:3, 6) በተጨማሪም ለአምላክ ያለህ ፍቅር እያደገ ይሄዳል። ይህም ተገቢ ነገር ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ” ብሏል። (ማርቆስ 12:30) ኢየሱስ ለአምላክ ይህን የመሰለ ፍቅር እንደነበረው ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ይገልጻል? በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ያለውስ ሚና ምንድን ነው?
እውቀትህን ፈትሽ
የአምላክ ስም ማን ነው? በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችስ ምን ያህል ጊዜ ተጠቅሷል?
በአምላክ ስም መጠቀም የሚኖርብህ ለምንድን ነው?
አንተን በተለይ የሚማርኩህ የትኞቹ የአምላክ ባሕርያት ናቸው?
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሁሉንም ነገሮች ፈጣሪ ምን ያህል ታውቀዋለህ?