ምዕራፍ 13
“የይሖዋ ሕግ ፍጹም ነው”
1, 2. ብዙ ሰዎች ለሕግ ያላቸው አክብሮት እየቀነሰ የመጣው ለምንድን ነው? ይሁን እንጂ እኛ ስለ አምላክ ሕግ ምን ሊሰማን ይችላል?
“ሕግ ምን ቢከቱበት የማይሞላ ጉድጓድ ነው። . . . ያገኘውን ሁሉ ይውጣል።” ይህ በ1712 ከታተመ አንድ መጽሐፍ የተወሰደ አባባል ነው። የመጽሐፉ ደራሲ የፍርድ ቤት ሙግቶች ለረጅም ጊዜ እንዲጓተቱ የሚያደርገውንና ፍትሕ የሚሹ ሰዎችን ለኪሳራ የሚዳርገውን የሕግ አሠራር አውግዟል። በበርካታ አገሮች ያለው የሕግ አሠራርና የፍትሕ ሥርዓት በጣም የተወሳሰበ፣ የተዛባ፣ አድሏዊነት የሚንጸባረቅበትና ተለዋዋጭ በመሆኑ ብዙ ሰዎች ለሕግ ያላቸው አክብሮት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል።
2 በአንጻሩ ደግሞ ከ2,700 ዓመታት ገደማ በፊት የተጻፉትን “ሕግህን ምንኛ ወደድኩ!” የሚሉትን ቃላት ልብ በል። (መዝሙር 119:97) መዝሙራዊው እንዲህ ሊሰማው የቻለው ለምንድን ነው? እሱ የጠቀሰው ሕግ አንድ ሰብዓዊ መንግሥት ሳይሆን ይሖዋ አምላክ ያወጣው በመሆኑ ነው። ስለ ይሖዋ ሕግ እያወቅህ በሄድክ መጠን አንተም እንደ መዝሙራዊው ለማለት ልትገፋፋ ትችላለህ። የይሖዋን ሕግ መመርመርህ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀው ሕግ አውጪ ምን አመለካከት እንዳለው እንድትገነዘብ ይረዳሃል።
ከሁሉ የላቀው ሕግ አውጪ
3, 4. ይሖዋ ሕግ አውጪ መሆኑን ያሳየው በምን መንገዶች ነው?
3 መጽሐፍ ቅዱስ “ሕግ የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ብቻ ነው” ይላል። (ያዕቆብ 4:12) በእርግጥም ትክክለኛው ሕግ አውጪ ይሖዋ ብቻ ነው። ሌላው ቀርቶ የሰማይ አካላት እንኳ የሚንቀሳቀሱት እሱ ባወጣላቸው “ሕጎች” መሠረት ነው። (ኢዮብ 38:33) እልፍ አእላፋት የሆኑት የይሖዋ ቅዱሳን መላእክትም በተለያየ ሥልጣንና ደረጃ ተከፋፍለው ይሖዋ በሚሰጣቸው ትእዛዝ መሠረት የሚያገለግሉ በመሆናቸው በመለኮታዊ ሕግ የሚመሩ ናቸው።—መዝሙር 104:4፤ ዕብራውያን 1:7, 14
4 ይሖዋ ለሰው ልጆችም ሕግ ሰጥቷል። እያንዳንዳችን የይሖዋን የፍትሕ ባሕርይ የሚያንጸባርቅ ሕሊና ተሰጥቶናል። ሕሊና ጥሩና መጥፎ የሆነውን ነገር ለይተን ማወቅ እንድንችል የሚረዳ በውስጣችን የተቀመጠ ራሱን የቻለ ሕግ ነው ሊባል ይችላል። (ሮም 2:14) የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ፍጹም የሆነ ሕሊና ተሰጥቷቸው ስለነበር ብዙ ሕግ አላስፈለጋቸውም። (ዘፍጥረት 2:15-17) ይሁን እንጂ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች የአምላክን ፈቃድ መፈጸም እንዲችሉ ተጨማሪ ሕግ ያስፈልጋቸዋል። ይሖዋ አምላክ እንደ ኖኅ፣ አብርሃምና ያዕቆብ ላሉት የጥንት አባቶች ሕግ የሰጣቸው ሲሆን እነሱም የተሰጣቸውን ሕግ ለቤተሰቦቻቸው አስተላልፈዋል። (ዘፍጥረት 6:22፤ 9:3-6፤ 18:19፤ 26:4, 5) በኋላም ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤል ሕዝብ ሕግ በመስጠት ቀደም ካሉት ጊዜያት ለየት ባለ መንገድ ሕግ አውጪ መሆኑን አሳይቷል። ይህ ሕግ ስለ ይሖዋ የፍትሕ ባሕርይ ጠለቅ ያለ ግንዛቤ እንዲኖረን ይረዳናል።
የሙሴ ሕግ ጠቅለል ያለ ገጽታ
5. የሙሴ ሕግ አስቸጋሪና ውስብስብ የሆኑ ደንቦችን የያዘ ነው? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?
5 ብዙዎች የሙሴ ሕግ አስቸጋሪና ውስብስብ የሆኑ ደንቦች የያዘ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው። በሙሴ ሕግ ውስጥ በአጠቃላይ ከ600 የሚበልጡ ሕግጋት ተካትተው ይገኛሉ። ይህ በጣም ብዙ ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ በ20ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ የፌዴራል ሕግ መጻሕፍት በድምሩ ከ150,000 በላይ ገጾች ነበሯቸው። በየሁለት ዓመቱ ደግሞ ከ600 የሚበልጡ ሕጎች ይጨመራሉ! ስለዚህ ስፍር ቁጥር ከሌላቸው ሰብዓዊ ሕጎች አንጻር ሲታይ የሙሴ ሕግ በጣም አነስተኛ ነው። ሆኖም አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ ዛሬ ያሉት ሕጎች የማይዳስሷቸውን የሕይወት ዘርፎች ሁሉ የሚዳስስ ነው። እስቲ የሙሴን ሕግ ጠቅለል ያለ ገጽታ እንመልከት።
6, 7. (ሀ) የሙሴን ሕግ ከሌሎች ሕጎች ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው? በዚህ ሕግ ውስጥ ከሰፈሩት ሕግጋት ሁሉ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው የትኛው ነው? (ለ) እስራኤላውያን የይሖዋን ሉዓላዊነት እንደተቀበሉ የሚያሳዩት እንዴት ነበር?
6 ሕጉ የይሖዋን ሉዓላዊነት የሚያጎላ ነበር። በመሆኑም የሙሴ ሕግ ከሌላ ከማንኛውም ሕግ የላቀ ነው። በሙሴ ሕግ ውስጥ ከሰፈሩት ሕግጋት ሁሉ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው “እስራኤል ሆይ ስማ፣ አምላካችን ይሖዋ አንድ ይሖዋ ነው። አንተም አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ” የሚለው ሕግ ነው። የአምላክ ሕዝቦች ለእሱ ያላቸውን ፍቅር የሚገልጹት እንዴት ነው? ለሉዓላዊነቱ በመገዛትና እሱን በማገልገል ነው።—ዘዳግም 6:4, 5፤ 11:13
7 እያንዳንዱ እስራኤላዊ ኃላፊነት ለተሰጣቸው ሰዎች በመገዛት የይሖዋን ሉዓላዊነት እንደተቀበለ ያሳይ ነበር። ወላጆች፣ የነገድ አለቆች፣ ፈራጆች፣ ካህናትና ንጉሡ መለኮታዊ ሥልጣንን የሚወክሉ ናቸው። ይሖዋ በእነዚህ ሰዎች ላይ የሚያምፁ ግለሰቦችን በእሱ ላይ እንዳመፁ አድርጎ ይመለከታቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ሕዝቡን የሚጨቁኑ ወይም የሚያንገላቱ ከሆነ የይሖዋ ቁጣ ይወርድባቸዋል። (ዘፀአት 20:12፤ 22:28፤ ዘዳግም 1:16, 17፤ 17:8-20፤ 19:16, 17) በመሆኑም ሥልጣን የተሰጣቸው ሰዎችም ሆኑ በእነሱ ሥር ያሉት ተገዢዎች የአምላክን ሉዓላዊነት የመደገፍ ኃላፊነት ነበረባቸው።
8. ሕጉ ለይሖዋ ቅድስና የቆመ ነበር የምንለው ለምንድን ነው?
8 ሕጉ ለይሖዋ ቅድስና የቆመ ነበር። “ቅዱስ” እና “ቅድስና” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥ ቃላት በሙሴ ሕግ ውስጥ ከ280 ጊዜ በላይ ተጠቅሰው ይገኛሉ። ሕጉ አንድን እስራኤላዊ ሊያረክሱ የሚችሉ ወደ 70 የሚጠጉ የተለያዩ ነገሮችን በመዘርዘር የአምላክ ሕዝቦች ንጹሕና ርኩስ የሆነውን ነገር እንዲለዩ ረድቷቸዋል። ሕጉ አካላዊ ንጽሕናን፣ አመጋገብን አልፎ ተርፎም ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድን የሚመለከቱ ደንቦችን የያዘ ነበር። እንዲህ ያሉት ደንቦች ለጤንነት እጅግ ጠቃሚ ናቸው።a ይሁን እንጂ እነዚህ ደንቦች የተሰጡበት ዋና ዓላማ ሕዝቡ፣ በአካባቢው ያሉት ወራዳ ሥነ ምግባር ያላቸው ብሔራት ከሚፈጽሟቸው መጥፎ ድርጊቶች በመራቅ የይሖዋን ሞገስ እንዲያገኝ ማድረግ ነበር። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።
9, 10. የሕጉ ቃል ኪዳን የፆታ ግንኙነትንና ልጅ መውለድን በተመለከተ ምን ደንቦችን ይዟል? እነዚህ ደንቦችስ ምን ጥቅሞች አስገኝተዋል?
9 በሕጉ ቃል ኪዳን ውስጥ የተካተቱት ደንቦች በተጋቡ ሰዎች መካከልም እንኳ የሚደረግ የፆታ ግንኙነት ለተወሰነ ጊዜ እንደሚያረክስ ይገልጻሉ፤ ከዚህም በተጨማሪ አንዲት ሴት ልጅ በምትወልድበት ጊዜ ለተወሰነ ጊዜ ትረክሳለች። (ዘሌዋውያን 12:2-4፤ 15:16-18) እንዲህ ያሉት ደንቦች እነዚህን ንጹሕ የሆኑ የአምላክ ስጦታዎች የሚያንቋሽሹ አይደሉም። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:18-25) ከዚህ ይልቅ እነዚህ ደንቦች ሕዝቡን ከብክለት በመጠበቅ የይሖዋ ቅድስና ትልቅ ቦታ እንዲሰጠው የሚያደርጉ ናቸው። የእስራኤላውያን አጎራባች ብሔራት፣ የፆታ ግንኙነትና የመራባት ሥርዓት የአምልኳቸው ክፍል የነበረ መሆኑ ልብ ሊባል የሚገባው ነው። የከነአናውያን የአምልኮ ሥርዓት የወንድና የሴት ዝሙት አዳሪነትንም የሚያካትት ነበር። በዚህም ሳቢያ እጅግ ወራዳ የሆኑ ድርጊቶችና ልማዶች ተስፋፍተው ነበር። በአንጻሩ ግን የሙሴ ሕግ የይሖዋ አምልኮ ከማንኛውም የፆታ ርኩሰት ሙሉ በሙሉ የጠራ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።b ይሁንና ሌሎች ጥቅሞችም ነበሩት።
10 እነዚህ ሕጎች አንድ የሚያስተምሩት እውነታም አለ።c ለመሆኑ የአዳም ኃጢአት ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ የሚተላለፈው እንዴት ነው? በፆታ ግንኙነትና በመዋለድ አይደለም? (ሮም 5:12) አዎን፣ ለእስራኤላውያን የተሰጠው ሕግ ኃጢአት ከሰው ልጅ ጋር አብሮ የሚኖር ነገር እንደሆነ እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል። እንዲያውም ሁላችንም ስንወለድ ጀምሮ ኃጢአተኞች ነን። (መዝሙር 51:5) በመሆኑም ቅዱስ ወደሆነው አምላካችን ለመቅረብ ምሕረት ማግኘትና ከኃጢአታችን መቤዠት ያስፈልገናል።
11, 12. (ሀ) ሕጉ ምን ዓይነት ፍርድ እንዲሰጥ ያዝዝ ነበር? (ለ) ሕጉ ፍትሕ እንዳይዛባ ይከላከል የነበረው እንዴት ነው?
11 ሕጉ ፍጹም የሆነውን የይሖዋን ፍትሕ የሚያንጸባርቅ ነበር። የሙሴ ሕግ ከፍትሕ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ተመጣጣኝና ሚዛናዊ የሆነ ፍርድ እንዲሰጥ ያደርግ ነበር። በመሆኑም ሕጉ “ሕይወት ስለ ሕይወት፣ ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ፣ እጅ ስለ እጅ እንዲሁም እግር ስለ እግር ይሁን” ሲል ይገልጻል። (ዘዳግም 19:21) ወንጀል በሚፈጸምበት ጊዜ የሚበየነው ቅጣት ከወንጀሉ ጋር የሚመጣጠን መሆን ነበረበት። ይህ መለኮታዊ ፍትሕ በሕጉ ላይ ጎልቶ የተንጸባረቀ ከመሆኑም በላይ በምዕራፍ 14 ላይ እንደምንመለከተው የኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት በተመለከተ ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘት እንድንችል ይረዳናል።—1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6
12 ከዚህም በተጨማሪ ሕጉ ፍትሕ እንዳይዛባ ይከላከላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ክስ ተቀባይነት እንዲኖረው ቢያንስ ሁለት ምሥክሮች ያስፈልጉ ነበር። በሐሰት መመሥከር ከፍተኛ ቅጣት ያስከትል ነበር። (ዘዳግም 19:15, 18, 19) በተጨማሪም ሙስናና ጉቦ በእጅጉ የተወገዙ ድርጊቶች ነበሩ። (ዘፀአት 23:8፤ ዘዳግም 27:25) የአምላክ ሕዝቦች በንግድ ጉዳዮችም እንኳ ሳይቀር የይሖዋን የፍትሕ መሥፈርት መጠበቅ ነበረባቸው። (ዘሌዋውያን 19:35, 36፤ ዘዳግም 23:19, 20) ይህ የላቀና ፍትሐዊ የሆነ ሕግ እስራኤላውያንን በእጅጉ ጠቅሟቸዋል!
ምሕረት የተንጸባረቀባቸውና ከአድልዎ ነፃ የሆኑ ሕጎች
13, 14. ሕጉ ለሌባም ሆነ ንብረቱ ለተሰረቀበት ሰው ፍትሐዊ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
13 የሙሴ ሕግ ድርቅ ያሉ ምሕረት የለሽ ደንቦችን የያዘ ነው? በፍጹም! ንጉሥ ዳዊት በአምላክ መንፈስ ተገፋፍቶ “የይሖዋ ሕግ ፍጹም ነው” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 19:7) ሕጉ ምሕረት የተንጸባረቀበትና ምንም ዓይነት አድልዎ የማያደርግ እንደሆነ በሚገባ ያውቅ ነበር። ሕጉ ምሕረትና ፍትሕ የተንጸባረቀበት ነበር የምንለው ለምንድን ነው?
14 በዛሬው ጊዜ በአንዳንድ አገሮች ያለው ሕግ ልል ከመሆኑም ሌላ የወንጀል ተጠቂ ከሆኑት ሰዎች ይልቅ ወንጀለኞቹን የሚጠቅም ይመስላል። ለምሳሌ ያህል፣ ሌቦች ሊታሰሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የወንጀሉ ተጠቂዎች የተዘረፈባቸው ንብረት ላይመለስላቸው ይችላል፤ በዚያ ላይ ደግሞ ለመንግሥት የሚከፍሉት ግብር እነዚህን ወንጀለኞች ለመቀለብ ይውላል። በጥንት እስራኤል እንደ አሁኑ እስር ቤቶች አልነበሩም። ከዚህም በተጨማሪ የሚበየነው ቅጣት ጥብቅ ገደብ ነበረው። (ዘዳግም 25:1-3) አንድ ሌባ የሰረቀውን ነገር መልሶ መተካት ይጠበቅበት የነበረ ከመሆኑም በላይ ተጨማሪ ክፍያ ይበየንበት ነበር። የክፍያው መጠን እንደ ሁኔታው ይለያያል። ፈራጆቹ የኃጢአተኛውን የንስሐ ዝንባሌ ጨምሮ የተለያዩ ነገሮችን በመመዘን መፍረድ ይጠበቅባቸው ነበር። በዘሌዋውያን 6:1-7 ላይ የተገለጸው ካሳ በዘፀአት 22:7 ላይ ከተጠቀሰው ካሳ ያነሰ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው።
15. በሙሴ ሕግ መሠረት ሳያውቅ ሕይወት ያጠፋ ሰው ምሕረት የሚያገኘውና ፍትሐዊ ውሳኔ የሚበየንበት እንዴት ነው?
15 ሕጉ ባለማወቅ ጥፋት የፈጸሙ ሰዎች ምሕረት የሚያገኙበትንም ሁኔታ አመቻችቷል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ሳያውቅ ሕይወት በሚያጠፋበት ጊዜ በቅርብ ወዳለ መማጸኛ ከተማ በመሸሽ ተገቢውን እርምጃ ከወሰደ ሕይወት ስለ ሕይወት መክፈል አይጠበቅበትም። ብቃት ያላቸው ፈራጆች ጉዳዩን ከመረመሩ በኋላ ግለሰቡ ሊቀ ካህናቱ እስኪሞት ድረስ በመማጸኛ ከተማው ውስጥ ይቆያል። ከዚያ በኋላ ወደፈለገው ቦታ ሄዶ መኖር ይችላል። በዚህ መንገድ አምላክ ባደረገው የምሕረት ዝግጅት መጠቀም ይችላል። ይህ ሕግ እግረ መንገዱንም የሰው ሕይወት ምን ያህል ውድ እንደሆነ የሚጠቁም ነው።—ዘኁልቁ 15:30, 31፤ 35:12-25
16. ሕጉ አንዳንድ ሰብዓዊ መብቶችን የሚያስከብረው እንዴት ነው?
16 ሕጉ ሰብዓዊ መብቶችንም የሚያስከብር ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ለተበደሩ ሰዎች እንዴት ከለላ እንደሚሆን ተመልከት። ሕጉ ተበዳሪው ቤት ውስጥ ገብቶ መያዣ መውሰድን ይከለክላል። ከዚህ ይልቅ አበዳሪው ውጭ ቆሞ ተበዳሪው ለመያዣነት የሚሰጠውን ዕቃ እስኪያመጣለት መጠበቅ ይኖርበታል። ይህም የግለሰቡ ቤት እንዳይደፈር ይረዳል። አበዳሪው የተበዳሪውን ልብስ በመያዣነት ወስዶ ከነበረ ተበዳሪው ሌሊት ለብሶት የሚተኛው ልብስ ሊሆን ስለሚችል አመሻሹ ላይ ሊመልስለት ይገባ ነበር።—ዘዳግም 24:10-14
17, 18. እስራኤላውያን ከጦርነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ከሌሎች ብሔራት የተለዩ የነበሩት እንዴት ነው? ለምንስ?
17 በሕጉ ውስጥ ጦርነትን የሚመለከቱ ደንቦችም እንኳ ሳይቀሩ ተካትተዋል። የአምላክ ሕዝቦች ከሌሎች ብሔራት ጋር ይዋጉ ነበር። ይህን ያደርጉ የነበረው ግን ‘በይሖዋ ጦርነት’ የአምላክ ወኪሎች ሆነው ለማገልገል እንጂ የበላይ ወይም ኃያል መሆናቸውን ለማስመሥከር ብለው አልነበረም። (ዘኁልቁ 21:14) ብዙውን ጊዜ እስራኤላውያን በቅድሚያ ጠላቶቻቸው በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ ይጠይቁ ነበር። አንዲት ከተማ ይህን ግብዣ ለመቀበል አሻፈረኝ በምትልበት ጊዜ እስራኤላውያን አምላክ የሰጣቸውን መመሪያ በመከተል ከተማዋን ይከብቡ ነበር። በታሪክ ዘመናት እንደታዩት እንደ ብዙዎቹ ወታደሮች የእስራኤል ሠራዊት አባላት ሴቶችን አስገድደው አይደፍሩም ወይም ያገኙትን ሰው ሁሉ በጅምላ አይጨፈጭፉም። ሌላው ቀርቶ ሕጉ ጠላቶቻቸው የተከሏቸውን የፍራፍሬ ዛፎች በመጨፍጨፍ በአካባቢው ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ይከለክል ነበር።d የሌሎች ብሔራት ሠራዊት ግን እንዲህ እንዳያደርጉ የሚከለክል ሕግ አልነበራቸውም።—ዘዳግም 20:10-15, 19, 20፤ 21:10-13
18 በአንዳንድ አገሮች ገና በለጋ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ለውትድርና እንደሚሠለጥኑ ስትሰማ አይዘገንንህም? በጥንት እስራኤል ከ20 ዓመት በታች የሆነ ማንም ሰው ለውትድርና አይመለመልም ነበር። (ዘኁልቁ 1:2, 3) ሌላው ቀርቶ ትልቅ ሰውም እንኳ ቢሆን በጣም የሚፈራ ከሆነ ከወታደራዊ ግዳጅ ነፃ ይሆን ነበር። አዲስ ሙሽራ የሆነ ሰው ደግሞ ሕይወትን ሊያሳጣ በሚችለው የውትድርና አገልግሎት ከመሰማራቱ በፊት ወራሽ የሚሆን ልጅ ወልዶ መሳም እንዲችል ለአንድ ዓመት ከግዳጅ ነፃ ይሆን ነበር። በዚህ መንገድ አዲሱ ሙሽራ ‘በቤቱ ተቀምጦ ሚስቱን ሊያስደስታት’ እንደሚችል ሕጉ ይገልጻል።—ዘዳግም 20:5, 6, 8፤ 24:5
19. ሕጉ ለሴቶች፣ ለልጆች፣ ለቤተሰቦች፣ ለመበለቶችና ወላጅ ለሌላቸው ልጆች ጥበቃ የሚያደርገው እንዴት ነበር?
19 በተጨማሪም ሕጉ ሴቶች፣ ልጆችና ቤተሰቦች ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያገኙ የሚረዱ ደንቦችን ያካተተ ነበር። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ዘወትር ጊዜ እንዲያሳልፉና መንፈሳዊ ነገሮችን እንዲያስተምሯቸው ያዝዝ ነበር። (ዘዳግም 6:6, 7) በሥጋ ዘመዳሞች መካከል የሚፈጸምን የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጽሞ የሚከለክል ሲሆን እንዲህ የሚያደርግ ሰው በሞት ይቀጣ ነበር። (ዘሌዋውያን ምዕራፍ 18) ከዚህም በተጨማሪ ብዙውን ጊዜ የቤተሰብን አንድነትና ሰላማዊ ሕይወት የሚያናጋውንና ክብር የሚያሳጣውን ምንዝርን ያወግዛል። ሕጉ ለመበለቶችና ወላጅ ለሌላቸው ልጆች ጥበቃ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ በደል እንዳይፈጸምባቸው አጥብቆ ያስጠነቅቃል።—ዘፀአት 20:14፤ 22:22-24
20, 21. (ሀ) የሙሴ ሕግ እስራኤላውያን ከአንድ በላይ እንዳያገቡ ያልከለከለው ለምንድን ነው? (ለ) ፍቺን በተመለከተ በሕጉ ላይ የሰፈረው ደንብ ኢየሱስ ከጊዜ በኋላ ካስተማረው ሥርዓት የሚለየው ለምንድን ነው?
20 ይሁን እንጂ ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዳንዶች ‘ሕጉ ከአንድ በላይ ማግባት የሚፈቅደው ለምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። (ዘዳግም 21:15-17) እንዲህ ያሉትን ሕጎች በዚያ ዘመን ከነበረው ሁኔታ አንጻር መመርመር ይኖርብናል። የሙሴን ሕግ በአሁኑ ጊዜ ካለው ሁኔታና ልማድ አንጻር የሚመለከቱ ሰዎች ሕጉን በተሳሳተ መንገድ ሊረዱት ይችላሉ። (ምሳሌ 18:13) ይሖዋ በኤደን ያቋቋመው ሥርዓት አንድ ወንድና አንዲት ሴት ለዘላለም በጋብቻ ተሳስረው እንዲኖሩ የሚያደርግ ነበር። (ዘፍጥረት 2:18, 20-24) ይሁን እንጂ ይሖዋ ሕጉን ለእስራኤላውያን በሰጠበት ወቅት ከአንድ በላይ ማግባት ለበርካታ መቶ ዘመናት የቆየ ልማድ ሆኖ ነበር። ይሖዋ “ግትር” የሆኑት ሕዝቦቹ ከጣዖት አምልኮ እንዲርቁ የሚያዘውን ሕግ ጨምሮ በጣም መሠረታዊ የሆኑትን ትእዛዛት እንኳ ሳይቀር በተደጋጋሚ ጊዜያት እንደሚጥሱ በሚገባ ያውቃል። (ዘፀአት 32:9) በመሆኑም ይሖዋ በዚያ ወቅት የጋብቻ ልማዳቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲለውጡ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ አልታየውም። ያም ሆነ ይህ ከአንድ በላይ ማግባት ይሖዋ ያቋቋመው ሥርዓት እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ይሁንና ይሖዋ ይህን ልማድ አላግባብ እንዳይጠቀሙበት ለማድረግ በሙሴ ሕግ አማካኝነት አንዳንድ ገደቦችን አበጅቷል።
21 በተጨማሪም የሙሴ ሕግ አንድ ሰው ሚስቱን ሊፈታ የሚችልባቸውን የተለያዩ ከበድ ያሉ ጉዳዮች ይጠቅሳል። (ዘዳግም 24:1-4) አምላክ ለአይሁድ ሕዝብ ይህን የፈቀደው “[የልባቸውን] ደንዳናነት አይቶ” እንደሆነ ኢየሱስ ገልጿል። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንዲህ ያሉትን ነገሮች የፈቀደው ለጊዜው ብቻ ነበር። ኢየሱስ ተከታዮቹ ይሖዋ መጀመሪያ ላይ ያወጣውን የጋብቻ ሥርዓት እንዲከተሉ አስተምሯል።—ማቴዎስ 19:8
ሕጉ ፍቅር እንዲያሳዩ የሚያበረታታ ነበር
22. የሙሴ ሕግ ፍቅር ማሳየትን የሚያበረታታው በምን መንገዶች ነው? ለእነማንስ?
22 በዛሬው ጊዜ ሰዎች ፍቅር እንዲያሳዩ የሚያበረታታ ሕግ ይኖራል ብለህ ታስባለህ? የሙሴ ሕግ ለፍቅር የላቀ ቦታ የሚሰጥ ነበር። እንዲያውም በዘዳግም መጽሐፍ ውስጥ ብቻ እንኳ “ፍቅር” የሚለው ቃል በተለያየ መንገድ ከ20 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል። “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው ትእዛዝ በሕጉ ውስጥ ከሰፈሩት ታላላቅ ትእዛዛት ሁለተኛውን ደረጃ የያዘ ነው። (ዘሌዋውያን 19:18፤ ማቴዎስ 22:37-40) የአምላክ ሕዝቦች የራሳቸው ወገን ለሆኑት ብቻ ሳይሆን በመካከላቸው ለሚኖሩት የባዕድ አገር ሰዎችም እንዲህ ዓይነት ፍቅር ማሳየት ነበረባቸው፤ በአንድ ወቅት እነሱም የባዕድ አገር ሰው እንደነበሩ እንዲያስታውሱ ተነግሯቸዋል። ድሆችንና የተለያዩ ችግሮች ያሉባቸውን ሰዎች በቁሳዊ ነገር በመርዳት እንዲሁም በእነዚህ ሰዎች ላይ አግባብ ያልሆነ ድርጊት ከመፈጸም በመታቀብ ለእነሱ ያላቸውን ፍቅር ማሳየት ነበረባቸው። ሌላው ቀርቶ ለእንስሳት እንኳ ደግነትና አሳቢነት ማሳየት ይጠበቅባቸው ነበር።—ዘፀአት 23:6፤ ዘሌዋውያን 19:14, 33, 34፤ ዘዳግም 22:4, 10፤ 24:17, 18
23. የመዝሙር 119 ጸሐፊ ምን ለማድረግ ተገፋፍቷል? እኛስ ምን ለማድረግ መነሳሳት ይኖርብናል?
23 እንዲህ ያለ አስደናቂ ሕግ የተሰጠው ሌላ ሕዝብ አለ? መዝሙራዊው “ሕግህን ምንኛ ወደድኩ!” ሲል መጻፉ ምንም አያስደንቅም! ይሁን እንጂ መዝሙራዊው እንዲሁ በማድነቅ ብቻ አልተወሰነም። ከዚህ ይልቅ ይህን ሕግ ከልብ ለመታዘዝና በሕይወቱ ተግባራዊ ለማድረግ ጥሯል። “ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ” ሲል አክሎ ተናግሯል። (መዝሙር 119:11, 97) አዎን፣ የይሖዋን ሕግ ዘወትር ያጠና ነበር። ይህም ለሕጉ ያለው ፍቅር ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ እንዲሄድ እንደረዳው ምንም ጥርጥር የለውም። ይህን ሕግ ላወጣው ለይሖዋ አምላክ ያለው ፍቅርም የዚያኑ ያህል ጨምሯል። አንተም መለኮታዊውን ሕግ በመመርመር የፍትሕ አምላክና ከሁሉ የላቀ ሕግ አውጪ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ ምኞታችን ነው።
a ለምሳሌ ያህል እዳሪ እንዲቀበር፣ የታመመ ሰው እስኪድን ድረስ ከሌሎች ሰዎች ተገልሎ እንዲቀመጥና አስከሬን የነካ ሰው እንዲታጠብ የሚያዙት ሕጎች በዘመኑ ከነበረው አስተሳሰብ እጅግ የመጠቁ ነበሩ።—ዘሌዋውያን 13:4-8፤ ዘኁልቁ 19:11-13, 17-19፤ ዘዳግም 23:13, 14
b የከነአናውያን ቤተ መቅደሶች የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም የሚያገለግሉ ክፍሎች የነበሯቸው ሲሆን በሙሴ ሕግ ግን የረከሱ ሰዎች ወደ ቤተ መቅደሱ መግባት እንኳ አይፈቀድላቸውም ነበር። የፆታ ግንኙነት በራሱ ለተወሰነ ጊዜ የሚያረክስ ስለሆነ በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚከናወነው የአምልኮ ሥርዓት ክፍል ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይመስል ነገር ነው።
c ሕጉ የተሰጠበት ዋነኛ ዓላማ የአምላክን ሕዝብ ለማስተማር ነበር። እንዲያውም ኢንሳይክሎፒዲያ ጁዳይካ “ሕግ” ተብሎ የተተረጎመው ቶራህ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “ትምህርት” ማለት እንደሆነ ይገልጻል።
d ሕጉ “ሰው ይመስል የሜዳን ዛፍ ከበህ ማጥፋት አለብህ?” ሲል በግልጽ ይጠይቃል። (ዘዳግም 20:19) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው አይሁዳዊው ምሁር ፊሎ ይህን ሕግ በመጥቀስ አምላክ “ሰዎች በጠላቶቻቸው ሳቢያ ያደረባቸውን ቁጣ ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው ነገሮች ላይ መወጣታቸው አግባብ አይደለም” የሚል አመለካከት እንዳለው ገልጿል።