“አላስተዋሉም”
ማስጠንቀቂያዎችን አቅልሎ መመልከት ለጥፋት ሊዳርግ ይችላል።
በ1974 ዳርዊን በተባለች አንዲት የአውስትራሊያ ከተማ የሚኖሩ ሰዎች ለበዓል ዝግጅት ሽር ጉድ እያሉ ሳለ ኃይለኛ ዐውሎ ነፋስ እየመጣ መሆኑን የሚያስታውቅ የማስጠንቀቂያ ደወል በከተማይቱ ውስጥ ያስተጋባ ጀመር። ይሁንና ዳርዊን ለ30 ዓመታት ያህል በከባድ ዐውሎ ነፋስ ተመታ አታውቅም። ታዲያ አሁን ምን የተለየ ነገር ተፈጠረ? አብዛኞቹ ነዋሪዎች ዐውሎ ነፋሱ ጣሪያዎችን መገነጣጠልና ቤቶችን ማፈራረስ እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ አደጋውን ብዙም አክብደው አልተመለከቱትም ነበር። በነጋታው ጠዋት ከተማይቱ እንዳልነበረች ሆነች።
በኅዳር ወር 1985 በኮሎምቢያ እሳተ ገሞራ ፈነዳ። የቀለጠ በረዶ የፈጠረው የጭቃ ጎርፍ ከ20,000 በላይ የሚሆኑትን የአርሜሮ ከተማ ነዋሪዎች ቀበራቸው። በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ አልተሰጠም ነበር ማለት ነው? እሳተ ገሞራው የፈነዳበት ተራራ በርከት ላሉ ወራት ሲንቀጠቀጥ ነበር። ሆኖም አብዛኞቹ የአርሜሮ ነዋሪዎች እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ ስለተላመዱት ብዙም ግድ አልሰጣቸውም። ባለ ሥልጣናቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ቢደርሳቸውም ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ ያደረጉት ጥረት አልነበረም። ነዋሪዎቹን ለማረጋጋት በሬዲዮ ማስታወቂያ ይነገር ነበር። እንዲያውም በቤተ ክርስቲያን በሚገኙ የድምፅ ማጉያዎች ሳይቀር በመጠቀም ሕዝቡ እንዳይረበሽ ለማድረግ ተሞክሯል። ይሁንና በዚያው ዕለት ምሽት ሁለት ከባድ ፍንዳታዎች ተከሰቱ። አንተ እዚያ ብትኖር ኖሮ ንብረትህን ጥለህ ትሸሽ ነበር? አደጋው ከመከሰቱ በፊት ይህን እርምጃ ለመውሰድ የሞከሩት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው።
የስነ ምድር ተመራማሪዎች የመሬት መንቀጥቀጥ የሚከሰትባቸውን ቦታዎች በተመለከተ በአብዛኛው ትክክለኛ ትንበያ ይሰጣሉ። የመሬት መንቀጥቀጥ የሚከሰትበትን ጊዜ በትክክል መተንበይ የሚችሉት ግን ከስንት አንዴ ነው። በ1999 በዓለም ዙሪያ 20,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች በመሬት መንቀጥቀጥ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከሞቱት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ይህ አደጋ ይደርስብናል ብለው ፈጽሞ አልጠበቁም።
አምላክ ለሚሰጠው ማስጠንቀቂያ ምን ምላሽ ትሰጣለህ?
መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻውን ዘመን ለይተው የሚያሳውቁ ምልክቶችን ከረጅም ጊዜ በፊት ገልጿል። ስለ መጨረሻው ዘመን የሚናገረው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ “በኖኅ ዘመን” የተፈጸመውን ሁኔታ መለስ ብለን እንድናስብ አጥብቆ ያሳስበናል። “ከጥፋት ውሃ በፊት” የነበሩት ሰዎች በጊዜው ተስፋፍቶ የነበረው ዓመፅ ያስጨንቃቸው የነበረ ቢሆንም በዕለት ተዕለት የኑሮ ጉዳዮች ተጠምደው ነበር። አምላክ በአገልጋዩ በኖኅ በኩል ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም “የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉን ጠራርጎ እስከወሰደ ድረስ አላስተዋሉም።” [NW] (ማቴዎስ 24:37-39) በዚያን ጊዜ ብትኖር ኖሮ ማስጠንቀቂያውን ሰምተህ እርምጃ ትወስድ ነበር? አሁንስ እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ ነህ?
የአብርሃም የወንድም ልጅ የሆነው ሎጥ በኖረበት ዘመን በሙት ባሕር አቅራቢያ በነበረችው በሰዶም ብትኖር ኖሮ ምን እርምጃ ትወስድ ነበር? ምድሪቱ ገነት ትመስል ነበር። ከተማይቱ ደግሞ በጣም የበለጸገች ነበረች። ነዋሪዎቿ ያላንዳች ሐሳብ ተንደላቅቀው ይኖሩ ነበር። በሎጥ ዘመን ሰዎች “ይበሉና ይጠጡ፣ ይገዙና ይሸጡ፣ ተክል ይተክሉና ቤት ይሠሩ ነበር።” ኅብረተሰቡ በጾታ ብልግና የረከሰ ነበር። ሎጥ መጥፎ ድርጊቶችን በማውገዝ ይሰጥ የነበረውን ማስጠንቀቂያ ትሰማ ነበር? አምላክ የሰዶምን ከተማ ለማጥፋት እንደወሰነ ሲነግርህ ትሰማው ነበር? ወይስ ልጆቹን ሊያገቡ የነበሩት ሰዎች እንዳደረጉት ማስጠንቀቂያውን እንደ ቀልድ አድርገህ ትወስደው ነበር? የሎጥ ሚስት እንዳደረገችው ከተማይቱን ጥለህ መውጣት ከጀመርክ በኋላ ወደኋላ ትመለሳለህ? ሌሎች የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ ቢሉም ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን “እሳትና ዲን ከሰማይ ዘንቦ በሙሉ አጠፋቸው።”—ሉቃስ 17:28, 29
በዛሬው ጊዜ ያሉት አብዛኞቹ ሰዎችም ማስጠንቀቂያውን ቸል ይላሉ። ሆኖም እነዚህ ምሳሌዎች በአምላክ ቃል ውስጥ ተመዝግበው እንዲቆዩ የተደረገው ለእኛ ማስጠንቀቂያ እንዲሆኑንና ምንጊዜም ነቅተን እንድንኖር ለማሳሰብ ነው።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ በእርግጥ ተከስቶ ነበር?
ብዙ ተቺዎች አልተከሰተም የሚል መልስ ይሰጣሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የጥፋት ውኃ በእርግጥ ተከስቶ እንደነበረ ይገልጻል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ስለዚህ የጥፋት ውኃ የተናገረ ሲሆን ጥፋቱ በደረሰበት ጊዜም ከሰማይ ሆኖ ተመልክቷል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ሰዶምና ገሞራ በእርግጥ ጠፍተዋል?
የከርሰ ምድር ጥናት ይህን ሐቅ አረጋግጧል።
የዓለም ታሪክ ስለዚህ ጥፋት ይናገራል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ይህ ጥፋት መድረሱን የመሰከረ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ 14 የተለያዩ መጻሕፍት ስለዚህ ጥፋት ጠቅሰዋል።