ምዕራፍ ስምንት
“የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው”
1-4. (ሀ) ኢየሱስ ሳምራዊቷን ሴት በጥበብ ያስተማራት እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ነበር? (ለ) ሐዋርያቱ ምን ተሰማቸው?
ለሰዓታት ሲጓዙ ቆይተዋል። ኢየሱስና ሐዋርያቱ ከይሁዳ ተነስተው በስተ ሰሜን አቅጣጫ ወደ ገሊላ እየተጓዙ ነው። የመረጡት አቋራጭ መንገድ ሦስት ቀን ገደማ የሚፈጅ ሲሆን ሰማርያን አቋርጦ ያልፋል። ፀሐይዋ አናት ላይ ስትሆን ሲካር ወደተባለች ትንሽ ከተማ ደረሱ፤ በዚያም አረፍ አሉ።
2 ሐዋርያቱ ምግብ ሊገዙ ሲሄዱ ኢየሱስ ከከተማዋ ውጭ ባለ አንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ቁጭ አለ። በዚህ ጊዜ አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስ እንዳላያት ሆኖ ዝም ሊላት ይችል ነበር። ምክንያቱም “ከጉዞው የተነሳ ደክሞት” ነበር። (ዮሐንስ 4:6) በመሆኑም ይህች ሳምራዊት ሴት ውኃ ቀድታ ስትሄድ አይቶ እንዳላየ ቢሆን አይፈረድበትም። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 4 ላይ እንደተመለከትነው ሴትየዋም ብትሆን ማንኛውም አይሁዳዊ በንቀት ቢመለከታት አያስገርማትም። ይሁንና ኢየሱስ ያነጋግራት ጀመር።
3 ኢየሱስ ጭውውቱን የጀመረው ምሳሌ በመጠቀም ነው፤ ምሳሌው ከዕለት ተዕለት ሕይወቷ እንዲያውም በዚያ ወቅት እያከናወነችው ካለችው ነገር ጋር የተያያዘ ነው። ሴትየዋ ወደዚያ የሄደችው ውኃ ለመቅዳት ነበር፤ በመሆኑም ኢየሱስ መንፈሳዊ ጥሟን ሊያረካላት ስለሚችል ሕይወት ሰጪ ውኃ ነገራት። በውይይታቸው መሃል ሴትየዋ ሊያከራክሯቸው የሚችሉ ጉዳዮችን በተደጋጋሚ አነሳች።a ኢየሱስ ግን ለእነዚህ ጉዳዮች መልስ ሳይሰጥ በዘዴ ውይይታቸው እንዲቀጥል አድርጓል። ትኩረት ያደረገው በመንፈሳዊ ጉዳዮች ይኸውም በንጹሑ አምልኮና በይሖዋ አምላክ ላይ ነበር። ደግሞም የነገራት ነገር ብዙዎችን ጠቅሟል፤ ምክንያቱም ሴትየዋ ከኢየሱስ ጋር ስላደረገችው ውይይት በከተማዋ ውስጥ ላሉ ሰዎች በመናገሯ እነሱም ኢየሱስን ለመስማት መጥተዋል።—ዮሐንስ 4:3-42
4 ሐዋርያቱ በተመለሱ ጊዜ ኢየሱስ በዚያ እያከናወነ ያለውን አስደናቂ የስብከት ሥራ ሲመለከቱ ምን ተሰማቸው? በሁኔታው እንደተደሰቱ የሚያሳይ ነገር የለም። እንዲያውም ኢየሱስ ይህችን ሴት ማነጋገሩ ራሱ አስገርሟቸው ነበር፤ እነሱም ያነጋገሯት አይመስልም። ሴትየዋ ከሄደች በኋላ ያመጡትን ምግብ እንዲበላ ኢየሱስን ወተወቱት። ኢየሱስ ግን “እናንተ የማታውቁት የምበላው ምግብ አለኝ” አላቸው። እነሱም ያላቸውን ነገር ቃል በቃል ስለወሰዱት መጀመሪያ ላይ ግራ ተጋብተው ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና እንዳከናውነው የሰጠኝን ሥራ መፈጸም ነው” በማለት አብራራላቸው። (ዮሐንስ 4:32, 34) በዚህ መንገድ በሕይወቱ ውስጥ የሚያከናውነው ዋነኛ ሥራ ከምግብ እንኳ እንደሚበልጥበት አስተማራቸው። እነሱም ይህን ሥራ በተመለከተ እንዲሁ ዓይነት ስሜት እንዲያድርባቸው ፈልጎ ነበር። ይህ ሥራ ምንድን ነው?
5. ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ የሚያከናውነው ዋነኛ ሥራ ምን ነበር? በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
5 በአንድ ወቅት ኢየሱስ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 4:43) አዎ፣ ኢየሱስ የተላከው የአምላክን መንግሥት ምሥራች እንዲሰብክና እንዲያስተምር ነበር።b በዛሬውም ጊዜ የኢየሱስ ተከታዮች ተመሳሳይ ሥራ እንዲያከናውኑ ይጠበቅባቸዋል። በመሆኑም ኢየሱስ የሰበከው ለምን እንደሆነ፣ ስለ ምን እንደሰበከና ስለተሰጠው ሥራ ምን አመለካከት እንደነበረው ማወቃችን አስፈላጊ ነው።
ኢየሱስ የሰበከው ለምንድን ነው?
6, 7. ኢየሱስ “ማንኛውም የሕዝብ አስተማሪ” ምሥራቹን ለሌሎች ስለማካፈል ምን ዓይነት ስሜት እንዲያድርበት ፈልጎ ነበር? በምሳሌ አስረዳ።
6 በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ ለሚያስተምረው እውነት ምን አመለካከት እንደነበረው እንይ፤ ከዚያም ለሚያስተምራቸው ሰዎች የነበረውን አመለካከት እንመረምራለን። ኢየሱስ፣ ይሖዋ ያስተማረውን እውነት ለሌሎች ማካፈል ምን ዓይነት ስሜት እንደሚያሳድርበት ለመግለጽ ሕያው የሆነ ምሳሌ ተጠቅሟል። እንዲህ ብሏል፦ “ስለ መንግሥተ ሰማያት የተማረ ማንኛውም የሕዝብ አስተማሪ ከከበረ ሀብት ማከማቻው አዲስና አሮጌ ዕቃ ከሚያወጣ የቤት ጌታ ጋር ይመሳሰላል።” (ማቴዎስ 13:52) በዚህ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው የቤት ጌታ ከከበረ ሀብት ማከማቻው ዕቃዎችን የሚያወጣው ለምንድን ነው?
7 ይህን ያደረገው በጥንት ዘመን እንደነበረው እንደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ሀብቱን ለማሳየት አይደለም፤ ሕዝቅያስ እንደዚያ ማድረጉ አሳዛኝ ውጤት አስከትሎበታል። (2 ነገሥት 20:13-20) ታዲያ ይህ የቤት ጌታ እንዲህ እንዲያደርግ ያነሳሳው ምንድን ነው? የሚከተለውን ምሳሌ ተመልከት፦ በጣም የምትወደውን አንድ አስተማሪ ለመጠየቅ ወደ ቤቱ ሄድክ እንበል። እሱም ሁለት ደብዳቤዎችን ከጠረጴዛው መሳቢያ ውስጥ አወጣ፤ አንደኛው የቆየ ስለሆነ ወረቀቱ ወይቧል፤ ሌላኛው ግን አዲስ ነው። ደብዳቤዎቹ ከአባቱ የተላኩለት ናቸው፤ አንደኛው ከዓመታት በፊት አስተማሪው ገና ልጅ ሳለ የተላከለት ሲሆን ሌላው ደግሞ በቅርቡ የደረሰው ነው። አስተማሪው እነዚህን ደብዳቤዎች ምን ያህል ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸው ሲገልጽልህ ደስታው ፊቱ ላይ ይነበባል፤ የያዙት ምክር እንዴት ሕይወቱን እንደለወጠው ብሎም አንተን ሊጠቅምህ እንደሚችል ይነግርሃል። ደብዳቤዎቹን እንደ ውድ ሀብት አድርጎ እንደሚመለከታቸውና በልቡ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንደያዙ በግልጽ ማየት ይቻላል። (ሉቃስ 6:45) ደብዳቤዎቹን ለአንተ ያሳየህ ጉራውን ለመንዛት ወይም የሆነ ጥቅም ለማግኘት ፈልጎ ሳይሆን አንተን ለመርዳትና ምን ያህል ዋጋማ እንደሆኑ ሊገልጽልህ ስለፈለገ ነው።
8. ከአምላክ ቃል የተማርናቸውን እውነቶች እንደ ውድ ሀብት አድርገን የምንመለከታቸው ለምንድን ነው?
8 ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስም ስለ አምላክ የሚገልጹትን እውነቶች ለሌሎች እንዲያካፍል የሚያነሳሳው ነገር ተመሳሳይ ነው። እነዚህ እውነቶች ለእሱ በዋጋ ሊተመን እንደማይችል ውድ ሀብት ናቸው። ከልቡ ይወዳቸዋል እንዲሁም ለሌሎች ለማካፈል ይጓጓል። “ማንኛውም የሕዝብ አስተማሪ” ይኸውም ተከታዮቹ በሙሉ እንዲሁ እንዲሰማቸው ይፈልጋል። እኛስ እንዲህ ይሰማናል? ከአምላክ ቃል የተማርናቸውን እውነቶች ሁሉ የምንወድበት በቂ ምክንያት አለን። እንደ ዕንቁ የሚታዩትን እውነቶች ይኸውም ከረጅም ጊዜ በፊት የተማርናቸውንም ይሁን በቅርብ ማስተካከያ የተደረገባቸውን ትምህርቶች እጅግ ከፍ አድርገን እንመለከታቸዋለን። ስለ እነዚህ እውነቶች ከልብ በመነጨ ቅንዓት በመናገርና ይሖዋ ላስተማረን ነገሮች ያለንን ፍቅር ጠብቀን በመኖር ልክ እንደ ኢየሱስ ሌሎችም እነዚህን እውነቶች እንዲወዷቸው መርዳት እንችላለን።
9. (ሀ) ኢየሱስ ለሚያስተምራቸው ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው? (ለ) ኢየሱስ ለሰዎች የነበረውን አመለካከት መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?
9 ኢየሱስ ለሚያስተምራቸው ሰዎችም ፍቅር ነበረው፤ ይህን ወደፊት በክፍል 3 ላይ በስፋት እንመለከተዋለን። በትንቢት እንደተነገረው መሲሑ “ለችግረኛውና ለድሃው ያዝናል።” (መዝሙር 72:13) በእርግጥም ኢየሱስ ለሰዎች ያስብ ነበር። አስተሳሰባቸውንና አመለካከታቸውን ግምት ውስጥ ያስገባ ነበር፤ ከዚህም ሌላ የተጫነባቸው ሸክምና እውነትን እንዳይቀበሉ እንቅፋት የሚሆኑባቸው ነገሮች ያሳስቡት ነበር። (ማቴዎስ 11:28፤ 16:13፤ 23:13, 15) ሳምራዊቷን ሴት እናስታውስ። ኢየሱስ ትኩረት ስለሰጣት እጅግ ተደንቃ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ያለችበትን ሁኔታ በሚገባ የሚያውቅ መሆኑ ነቢይ እንደሆነ እንድታምንና ለሌሎች ስለ እሱ እንድትናገር አነሳስቷታል። (ዮሐንስ 4:16-19, 39) እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ ያሉ የኢየሱስ ተከታዮች የሚሰብኩላቸውን ሰዎች ልብ ማንበብ አይችሉም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ለሰዎች ትኩረት መስጠት፣ እንደምናስብላቸው በተግባር ማሳየት እንዲሁም በምንናገርበት ጊዜ ፍላጎታቸውንና ያሉባቸውን ችግሮች ግምት ውስጥ ማስገባት እንችላለን።
ኢየሱስ የሰበከው ስለ ምን ነበር?
10, 11. (ሀ) ኢየሱስ የሰበከው ስለ ምን ነበር? (ለ) የአምላክ መንግሥት መቋቋም ያስፈለገው ለምንድን ነው?
10 የኢየሱስ ስብከት ያተኮረው በምን ላይ ነበር? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ኢየሱስን እንወክላለን የሚሉትን የብዙዎቹን አብያተ ክርስቲያናት ትምህርት ከመረመርክ፣ ኢየሱስ የሰበከው ማኅበራዊ ለውጥ ስለማምጣት እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ወይም ኢየሱስ የሰበከው የፖለቲካ ለውጥን እንደሆነ አድርገህ ልታስብ ትችላለህ፤ አሊያም ደግሞ ኢየሱስ ‘አንድ ሰው ከሁሉ በላይ ሊያሳስበው የሚገባው የራሱ መዳን ነው’ ብሎ እንዳስተማረ ይሰማህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል እንዳየነው ኢየሱስ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ” ሲል በግልጽ ተናግሯል። ታዲያ ይህ ምን ነገሮችን ይጨምራል?
11 ሰይጣን ለመጀመሪያ ጊዜ የይሖዋን ቅዱስ ስም ባጎደፈበትና በአገዛዙ ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ ባነሳበት ወቅት ኢየሱስ በቦታው እንደነበረ አስታውስ። ኢየሱስ፣ ጻድቅ የሆነው አባቱ ፍጥረታቱን ጥሩ ነገር የሚነፍግ ጨቋኝ ገዢ እንደሆነ ተደርጎ ክስ ሲሰነዘርበት እጅግ አዝኖ መሆን አለበት! የሰው ልጆች ወላጆች የሆኑት አዳምና ሔዋን የሰይጣንን የስም ማጥፋት ዘመቻ አምነው በመቀበላቸው የአምላክ ልጅ ስሜቱ እንደተጎዳ ጥርጥር የለውም! ወልድ፣ በዚህ ዓመፅ ምክንያት የሰው ልጆች ለኃጢአትና ለሞት መዳረጋቸውን አይቷል። (ሮም 5:12) ያም ሆኖ አባቱ በመንግሥቱ አማካኝነት ሁኔታውን ለማስተካከል እርምጃ እንደሚወስድ ማወቁ ምንኛ አስደስቶት ይሆን!
12, 13. የአምላክ መንግሥት ለየትኞቹ ጉዳዮች እልባት ያስገኛል? ኢየሱስ አገልግሎቱ በመንግሥቱ ዙሪያ እንዲያተኩር ያደረገው እንዴት ነበር?
12 ሆኖም እልባት የሚያሻው ዋነኛ ጉዳይ ምንድን ነው? የይሖዋ ስም መቀደስ ማለትም ሰይጣንና ግብረ አበሮቹ ከሰነዘሩበት ከማንኛውም ዓይነት ነቀፋ ነፃ መሆን አለበት። የይሖዋ ስም ሲባል ‘ምን ዓይነት ገዢ ነው?’ የሚለውንም ይጨምራል፤ በመሆኑም ሉዓላዊነቱ ወይም አገዛዙ ከሁሉ የተሻለ መሆኑ መረጋገጥ ይገባዋል። ኢየሱስ ስለ እነዚህ ወሳኝ ጉዳዮች ከማንኛውም ሰው የበለጠ ግንዛቤ አለው። ኢየሱስ በናሙናው ጸሎት ላይ ተከታዮቹ በመጀመሪያ የአባቱ ስም እንዲቀደስ፣ ከዚያም የአባቱ መንግሥት እንዲመጣ ቀጥሎ ደግሞ የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲሆን እንዲለምኑ አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:9, 10) ኢየሱስ ክርስቶስ ገዢ የሆነበት የአምላክ መንግሥት በቅርቡ የሰይጣንን ብልሹ ሥርዓት ከምድር ላይ ጠራርጎ በማስወገድ የአምላክ አገዛዝ ከሁሉ የተሻለ መሆኑን ያረጋግጣል፤ የጽድቅ አገዛዙም ለዘላለም ይቀጥላል።—ዳንኤል 2:44
13 የኢየሱስ አገልግሎት በዋነኝነት ያተኮረው በዚህ መንግሥት ላይ ነበር። ኢየሱስ የሚናገረውና የሚያደርገው ነገር ሁሉ የዚህን መንግሥት ምንነትና ይህ መንግሥት የይሖዋን ዓላማ የሚያስፈጽመው እንዴት እንደሆነ ግልጽ የሚያደርግ ነበር። ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከመስበክ ተልእኮው ምንም ነገር እንዲያዘናጋው አልፈቀደም። እሱ በኖረበት ዘመን አሳሳቢ ማኅበራዊ ጉዳዮች የነበሩ ሲሆን የፍትሕ መዛባትም ተንሰራፍቶ ነበር፤ ያም ሆኖ የኢየሱስ ትኩረት ያረፈው በመልእክቱና በሥራው ላይ ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ማድረጉ ጠባብ አመለካከት እንዳለው ወይም የሌሎች ችግር ደንታ እንደማይሰጠው የሚያሳይ ነው? የሚሰብከው መልእክትስ ተደጋጋሚና አሰልቺ ነበር? በፍጹም!
14, 15. (ሀ) ኢየሱስ “ከሰለሞን የሚበልጥ” የሆነው እንዴት ነው? (ለ) ከምንሰብከው መልእክት ጋር በተያያዘ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
14 በዚህ ክፍል ውስጥ እንደምናየው ኢየሱስ ትምህርቱን ያቀረበው አስደሳችና ማራኪ በሆነ መንገድ ነበር። ኢየሱስ የሰዎችን ልብ ለመንካት ጥረት አድርጓል። ይህም ጠቢቡን ንጉሥ ሰለሞንን ያስታውሰን ይሆናል፤ ሰለሞን ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት እንዲጽፍ የመራውን ሐሳብ ሲያሰፍር ደስ የሚያሰኙ ቃላት ለማግኘትና የእውነትን ቃል በትክክል ለመመዝገብ ጥረት አድርጓል። (መክብብ 12:10) ይሖዋ ፍጽምና ለሚጎድለው ለዚህ ሰው “ሰፊ ልብ” ሰጥቶታል፤ በመሆኑም ስለ አእዋፍ፣ ስለ ዓሣዎች፣ ስለ ዛፎችና ስለ እንስሳት እንዲሁም ስለ ሌሎች ብዙ ነገሮች ተናግሯል። ሰዎች ሰለሞን የሚናገረውን ለመስማት ከሩቅ ይመጡ ነበር። (1 ነገሥት 4:29-34) ያም ሆኖ ኢየሱስ “ከሰለሞን የሚበልጥ” እንደሆነ ተገልጿል። (ማቴዎስ 12:42) ኢየሱስ ከሰለሞን የሚልቅ ጥበብና “ሰፊ ልብ” ነበረው። ስለ አምላክ ቃል፣ ስለ አእዋፍ፣ ስለ እንስሳት፣ ስለ ዓሣዎች፣ ስለ ግብርና፣ ስለ አየር ንብረት፣ በወቅቱ ስለነበሩት ሁኔታዎች፣ ስለ ታሪክና ስለ ማኅበራዊ ጉዳዮች ያለውን ከሁሉ የላቀ እውቀት ሰዎችን ለማስተማር ተጠቅሞበታል። ይሁንና ኢየሱስ በእውቀቱ ሰዎችን ለማስደመም አልሞከረም። መልእክቱ ቀላልና ግልጽ ነበር። በእርግጥም ሰዎች እሱን መስማት ያስደስታቸው የነበረ መሆኑ ምንም አያስገርምም!—ማርቆስ 12:37፤ ሉቃስ 19:48
15 በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል ይጥራሉ። እውነት ነው፣ የኢየሱስን ያህል ጥልቅ ጥበብና እውቀት የለንም፤ ይሁንና ሁላችንም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት ለሰዎች ለማካፈል የሚያስችል የተወሰነ እውቀትና ተሞክሮ አለን። ለምሳሌ ያህል፣ ወላጆች ይሖዋ ለልጆቹ ያለውን ፍቅር ለማስረዳት ልጆቻቸውን በማሳደግ ያገኙትን ተሞክሮ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት ያጋጠማቸውን ነገር አሊያም ስለ ሰዎችና በወቅቱ ስላሉት ሁኔታዎች ያላቸውን እውቀት ምሳሌ አድርገው ሊጠቅሱ ይችላሉ። ያም ሆኖ በዋነኝነት ትኩረት ማድረግ ያለብን በምንናገረው መልእክት ማለትም በአምላክ መንግሥት ምሥራች ላይ መሆኑን መዘንጋት የለብንም።—1 ጢሞቴዎስ 4:16
ኢየሱስ ለአገልግሎቱ ምን አመለካከት ነበረው?
16, 17. (ሀ) ኢየሱስ ለአገልግሎቱ ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው? (ለ) ኢየሱስ ሕይወቱ በዋነኝነት ያተኮረው በአገልግሎቱ ላይ እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው?
16 ኢየሱስ አገልግሎቱን እንደ ውድ ሀብት ይመለከተው ነበር። በሰማይ የሚኖረው አባቱ እውነተኛ ማንነት በሰው ወጎችና ትምህርቶች ሳይሸፈን በግልጽ እንዲታወቅ ማድረግ ያስደስተው ነበር። ሰዎች በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙና የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲኖራቸው መርዳትም ደስ ያሰኘው ነበር። ሰዎች የምሥራቹን መልእክት በመስማት ሲጽናኑና ሲደሰቱ ማየት እርካታ ይሰጠው ነበር። ይህን እንዴት እናውቃለን? የሚከተሉትን ሦስት መንገዶች ተመልከት።
17 በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ በዋነኝነት ትኩረት ያደረገው በአገልግሎቱ ላይ ነበር። በሕይወቱ ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘው ሥራ ስለ መንግሥቱ መናገር ሲሆን ትኩረቱ ሁሉ ያረፈውም በዚሁ ላይ ነው። ምዕራፍ 5 ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ አኗኗሩን ቀላል ያደረገው ለዚህ ነበር። ሌሎችን እንደመከረው ሁሉ የእሱም ዓይን ያተኮረው ይበልጥ አስፈላጊ በሆነው ነገር ላይ ነው። ልቡ እንዲከፋፈል የሚያደርጉ ብሎም ብዙ ወጪ፣ ክትትልና ጥገና የሚጠይቁ ንብረቶች አልነበሩትም። አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ከአገልግሎቱ ወደኋላ እንዳይጎትቱት ሲል አኗኗሩን ቀላል አድርጎ ነበር።—ማቴዎስ 6:22፤ 8:20
18. ኢየሱስ ራሱን ሳይቆጥብ በአገልግሎቱ በትጋት የተካፈለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
18 ሁለተኛ፣ ኢየሱስ ራሱን ሳይቆጥብ በአገልግሎቱ በትጋት ተካፍሏል። ምሥራቹን ለማዳረስ ሲል በመላው ፓለስቲና በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን በእግሩ በመጓዝ ሙሉ ኃይሉን ለዚህ ሥራ አውሏል። ሰዎችን በቤታቸው፣ በአደባባዮች ላይ፣ በገበያ ቦታዎችና በሌሎች ቦታዎች አነጋግሯል። እረፍት፣ ምግብ፣ ውኃ ወይም ከቅርብ ወዳጆቹ ጋር ጥቂት ጊዜ ማሳለፍ በሚያስፈልገው ወቅትም እንኳ ምሥራቹን ከመስበክ ወደኋላ አላለም። ሊሞት በተቃረበበት ጊዜም ቢሆን የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሰዎች መስበኩን አላቆመም።—ሉቃስ 23:39-43
19, 20. ኢየሱስ የስብከቱ ሥራ አጣዳፊ መሆኑን በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው?
19 ሦስተኛ፣ ኢየሱስ አገልግሎቱን በጥድፊያ ስሜት አከናውኗል። በሲካር አቅራቢያ ባለው የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ያደረገውን ውይይት አስታውስ። የኢየሱስ ሐዋርያት በዚያ ወቅት ምሥራቹን ለሌሎች መናገር አጣዳፊ እንደሆነ የተሰማቸው አይመስልም። በመሆኑም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ መከር ሊገባ ገና አራት ወር ይቀረዋል ትሉ የለም? እነሆ እላችኋለሁ፣ ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ።”—ዮሐንስ 4:35
20 ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተናገረው ከነበሩበት ወቅት ጋር አያይዞ ነው። ወሩ ኪስሌው (ኅዳር/ታኅሣሥ) እንደነበር ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። የገብስ መከር የሚጀምረው ከአራት ወር በኋላ ይኸውም የፋሲካ በዓል በሚከበርበት በኒሳን 14 አካባቢ ነው። በመሆኑም በዚህ ወቅት ገበሬዎች አዝመራ ለመሰብሰብ የሚጣደፉበት ምክንያት አልነበራቸውም። ገና ብዙ ጊዜ አላቸው። ስለ ሰዎች አዝመራስ ምን ማለት ይቻላል? ለመሰብሰብ ደርሷል? ብዙዎች ለመስማት፣ ለመማር፣ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆንና ይሖዋ የዘረጋላቸውን ድንቅ ተስፋ ለማግኘት ዝግጁ ነበሩ። ኢየሱስ በምሳሌያዊ ሁኔታ ለመሰብሰብ የደረሰውን ነጣ ያለ አዝመራ ነፋሱ ዘንበል ቀና ሲያደርገው እያየ ያለ ያህል ነው።c መከር ደርሷል፤ ሥራውም አጣዳፊ ነው! በመሆኑም ኢየሱስ የአንድ ከተማ ነዋሪዎች ከእነሱ ጋር እንዲቆይ ለማድረግ በፈለጉ ጊዜ “ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” ብሏቸዋል።—ሉቃስ 4:43
21. የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?
21 የኢየሱስን አርዓያ እስካሁን በተመለከትናቸው ሦስት መንገዶች መከተል እንችላለን። ክርስቲያናዊ አገልግሎታችን በሕይወታችን ውስጥ ዋነኛውን ቦታ እንዲይዝ ማድረግ እንችላለን። ከቤተሰብና ከሰብዓዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ኃላፊነቶች ቢኖሩብንም ኢየሱስ እንዳደረገው አገልግሎታችንን ዘወትር በቅንዓት በማከናወን ለዚህ ሥራ ቅድሚያውን እንደምንሰጥ እናሳያለን። (ማቴዎስ 6:33፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8) ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ጥሪታችንን ምንም ሳንቆጥብ በአገልግሎቱ በትጋት መካፈል እንችላለን። (ሉቃስ 13:24) ሥራችን አጣዳፊ መሆኑን ምንጊዜም መዘንጋት የለብንም። (2 ጢሞቴዎስ 4:2) ለመስበክ የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች ሁሉ መጠቀም አለብን!
22. በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
22 ኢየሱስ ይህ ሥራ እሱ ከሞተም በኋላ እንዲቀጥል በማድረግ ሥራው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አሳይቷል። ተከታዮቹ የመስበኩንና የማስተማሩን ሥራ በቀጣይነት እንዲያከናውኑ ተልእኮ ሰጥቷቸዋል። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይህ ተልእኮ በሰፊው ይብራራል።
a ለምሳሌ ያህል፣ ‘አንድ አይሁዳዊ አንዲትን ሳምራዊት እንዴት ያነጋግራል?’ የሚል ጥያቄ ስታነሳ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለውን ለበርካታ ዘመናት የዘለቀ አለመግባባት መጥቀሷ ነበር። (ዮሐንስ 4:9) በተጨማሪም ሳምራውያን የያዕቆብ ዘሮች መሆናቸውን ገልጻለች፤ ይህ በዘመኑ የነበሩት አይሁዳውያን ፈጽሞ የማይቀበሉት ሐሳብ ነው። (ዮሐንስ 4:12) አይሁዳውያን፣ ሳምራውያን ከባዕድ ሕዝቦች የመጡ መሆናቸውን ለመግለጽ ኩታውያን ብለው ይጠሯቸው ነበር።
b መስበክ ማለት አንድን መልእክት ማወጅ ወይም ማሰራጨት ማለት ነው። ማስተማርም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ትርጉም ያለው ቢሆንም አንድን መልእክት በጥልቀትና በስፋት ማብራራትን ይጨምራል። ጥሩ የማስተማር ችሎታ፣ የተማሪውን ልብ በመንካት ትምህርቱን በሥራ ላይ ለማዋል እንዲነሳሳ ለማድረግ የሚያስችሉ ዘዴዎች መጠቀምን ያካትታል።
c አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ይህን ጥቅስ ሲያብራራ “ሰብል በሚደርስበት ጊዜ ከአረንጓዴነት ወደ ቢጫነት አሊያም ነጣ ወዳለ ቀለም ይለወጣል፤ ይህም ለመሰብሰብ መድረሱን ይጠቁማል” ይላል።