ምዕራፍ 6
በሰውነቴ ላይ የማየው ለውጥ ምንድን ነው?
“ቁመቴ በአንድ ጊዜ ተመዘዘ። ሁኔታው ሕመም አስከትሎብኝ ነበር። ማደግ ደስ የሚል ነገር ቢሆንም እግሬ ላይ ሕመም ይሰማኝ ነበር። ይህም ያናድደኝ ነበር!”—ጳውሎስ
“ሰውነትሽ እየተለወጠ መሆኑ ታውቆሻል፤ እናም ‘ምነው ሌሎች ባላወቁብኝ’ ብለሽ ታስቢ ይሆናል። ይሁንና ሰዎች አንቺን ለማሸማቀቅ አስበው ባይሆንም ‘ዳሌ አወጣሽ እኮ’ ይሉሻል፤ በዚህ ጊዜ መሬት ተከፍታ ብትውጥሽ ደስ ይልሻል!”—ሸነል
ያደግክበትን ሰፈር ለቀህ በሌላ አካባቢ ኖረህ ታውቃለህ? መቼም አዲሱን አካባቢ መልመድ አስቸጋሪ ሳይሆንብህ አልቀረም። ቤትህን፣ ትምህርት ቤትህን እንዲሁም ጓደኞችህን ጨምሮ የለመድካቸውን ነገሮች ሁሉ ትተህ መሄድ ከባድ እንደሆነብህ ግልጽ ነው። ከአዲሱ ሁኔታ ጋር ራስህን ለማስማማት ጊዜ ወስዶብህ ይሆናል።
የጉርምስና ዕድሜ ላይ ስትደርስ ማለትም በአካላዊ ሁኔታ መጎልመስ ስትጀምር በሕይወትህ ውስጥ ከሚከናወኑት ጉልህ ለውጦች አንዱን ማየት ትጀምራለህ። ሁኔታው የኖርክበትን ሰፈር ለቀህ ወደ አዲስ “አካባቢ” ከመሄድ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አዲሱን መኖሪያህን ለማየት እንደምትጓጓ ጥርጥር የለውም! ይሁንና ወደ ጉልምስና የምታደርገው ጉዞ የተደበላለቀ ስሜት ይፈጥርብህ ይሆናል፤ አዲሱን ሁኔታ መልመድም ቀላል ላይሆንልህ ይችላል። በአንድ በኩል የሚያስደስት በሌላ በኩል ደግሞ ግራ የሚያጋባ በሆነው በዚህ ወቅት በሕይወትህ ውስጥ የሚከናወኑት ነገሮች ምንድን ናቸው?
ሴቶች ልጆች የሚያጋጥሟቸው ለውጦች
የጉርምስና ዕድሜ ከፍተኛ ለውጥ የሚከናወንበት ወቅት ነው። ከሚያጋጥሙሽ ለውጦች አንዳንዶቹ በግልጽ የሚታዩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ሰውነትሽ የሚያመነጫቸው ሆርሞኖች በፆታ ብልትሽ አካባቢ ፀጉር እንዲያድግ ያደርጋሉ። በተጨማሪም ጡት ማውጣት ትጀምሪያለሽ፣ ዳሌሽ ይሰፋል፤ እንዲሁም ጭንሽና መቀመጫሽ እየተለቀ ይሄዳል። ቀስ በቀስ ልጅነትሽን እየተሰናበትሽ የሴት ቅርጽ እየያዝሽ ትመጫለሽ። ይህ ጤናማ የእድገት ምልክት ስለሆነ ልትጨነቂ አይገባም። ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ለውጦች ሰውነትሽ ልጅ ለምትወልጂበት ጊዜ እየተዘጋጀ መሆኑን የሚጠቁሙ ናቸው።
በጉርምስና ወቅት የሚያጋጥምሽ ሌላው ለውጥ ደግሞ የወር አበባ ማየት መጀመርሽ ነው። አስቀድመሽ አስፈላጊውን ዝግጅት ካላደረግሽ በሕይወትሽ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የምትጀምሪበት ይህ ወቅት የሚያስፈራ ሊሆንብሽ ይችላል። ሰማንታ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች፦ “ፔሬዴ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመጣ ምንም አልተዘጋጀሁበትም ነበር። ቁሽሽ እንዳልኩ ሆኖ ተሰማኝ። ሰውነቴ በጣም ስላስጠላኝ ፍትግ አድርጌ እታጠብ ነበር። ከዚህ በኋላ ለዓመታት በየወሩ ፔሬድ ማየት የሚለውን ነገር ሳስበው በጣም አስፈራኝ!”
የወር አበባ ማየትሽ የመራቢያ አካላትሽ እየዳበሩ መሆናቸውን የሚጠቁም መሆኑን አትዘንጊ። እናት ለመሆን ዝግጁ የምትሆኚው ከዓመታት በኋላ ቢሆንም ወደ ሴትነት የምትሸጋገሪበትን ጉዞ የምትጀምሪው በዚህ ወቅት ነው። ያም ሆኖ የወር አበባሽ መጀመሩ እንድትረበሺ ሊያደርግሽ ይችላል። ኬሊ “ከሁሉ የከፋው ነገር በዚያ ወቅት የሚያጋጥመኝ የስሜት መለዋወጥ ነበር” ብላለች። “ቀኑን ሙሉ ደስ ብሎኝ ውዬ ማታ ላይ ዓይኔ እስኪያብጥ ድረስ አለቅሳለሁ፤ እንዲህ የምሆነው ለምን እንደሆነ አለማወቄ ያበሳጨኝ ነበር።”
አንቺስ በአሁኑ ወቅት እንደዚህ ይሰማሻል? ከሆነ ተስፋ አትቁረጪ። ውሎ አድሮ ለውጡን እየለመድሽው ትመጫለሽ። የ20 ዓመቷ አኔት እንዲህ ስትል ታስታውሳለች፦ “ሴትን ሴት የሚያስብላት የወር አበባ ማየቷ እንደሆነና ይህ ደግሞ ይሖዋ ልጅ የመውለድ ችሎታ እንደሰጠኝ የሚያሳይ ምልክት መሆኑን ከጊዜ በኋላ ተገነዘብኩ። ይህን ለመቀበል ጊዜ የሚወስድ ከመሆኑም በላይ ለአንዳንድ ወጣቶች በጣም ሊከብዳቸው ይችላል። ይሁንና በጊዜ ሂደት ለውጡን መቀበል ትጀምራላችሁ።”
ከላይ ከተጠቀሱት ለውጦች አንዳንዶቹን በሰውነትሽ ላይ መመልከት ጀምረሻል? ካጋጠሙሽ ለውጦች ጋር በተያያዘ የሚፈጠርብሽን ማንኛውንም ጥያቄ በክፍት ቦታው ላይ አስፍሪ።
․․․․․
ወንዶች ልጆች የሚያጋጥሟቸው ለውጦች
ወንድ ልጅ ከሆንክ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ስትደርስ በመልክህና በቁመናህ ላይ ጉልህ ለውጥ መመልከት ትጀምራለህ። ለምሳሌ፣ ቆዳህ አሁንም አሁንም ወዝ ስለሚያወጣ ሰውነትህ ላይ ብጉር ይወጣብህ እንዲሁም ጥቁር ነጠብጣቦች ይታዩብህ ይሆናል።a የ18 ዓመቱ ማት እንዲህ ብሏል፦ “ቆዳህ ብጉር በብጉር ሲሆን በጣም ያበሳጫል። ሁኔታው ጦርነት የተያያዝክ ያህል ነው፤ ብጉሩን ለማጥፋት መታገል ይኖርብሃል። ብጉሩ ከቆዳህ ላይ ጨርሶ ይጥፋ አይጥፋ ወይም ምልክት ይተው አይተው ምንም የምታውቀው ነገር የለም፤ ‘ብጉር ስለወጣብኝ ሰዎች ለእኔ ያላቸው ግምት ይቀንስ ይሆን?’ ብለህም ታስባለህ።”
ይሁን እንጂ በሰውነትህ ላይ የሚታየው ለውጥ መልካም ጎንም አለው፤ ሰውነትህ እያደገና እየጠነከረ መምጣቱን እንዲሁም ትከሻህ እየሰፋ መሆኑን ታስተውል ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ እግርህና ፊትህ ላይ እንዲሁም ደረትህ አካባቢና ብብትህ ሥር ፀጉር መታየት ይጀምር ይሆናል። በነገራችን ላይ በሰውነትህ ላይ ብዙ ፀጉር መኖሩ የወንድነት መለኪያ አይደለም፤ ይህ በዘር የሚወረስ ነገር ነው።
ሁሉም የሰውነትህ ክፍሎች በተመጣጠነ መንገድ ስለማያድጉ በዚህ ወቅት ቅልጥፍ ማለት ያስቸግርህ ይሆናል። ድዌን የተባለ አንድ ወጣት ‘እጆቼና እግሮቼ አእምሮዬ የሚያስተላልፈው መልእክት የሚደርሳቸው አይመስልም ነበር’ ብሏል።
በአሥራዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ ስትሆን ድምፅህ ይጎረንናል፤ ሆኖም ድምፅህ የሚቀየረው ቀስ በቀስ ነው። ጎርነን ባለ ድምፅ እያወራህ ሳለ ሳታስበው ድምፅህ ቀጭንና ስልል ያለ ሊሆንብህና ሽምቅቅ ልትል ትችላለህ። ይሁን እንጂ ይህ መሆኑ ሊያስጨንቅህ አይገባም። ውሎ አድሮ ድምፅህ እየተስተካከለ ይሄዳል። እስከዚያው ድረስ ግን እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥምህ በራስህ መቀለድህ የሚሰማህን የኀፍረት ስሜት በመጠኑም ቢሆን ይቀንስልሃል።
የመራቢያ አካላትህ እየዳበሩ ሲሄዱ የፆታ ብልትህ የሚያድግ ከመሆኑም ሌላ በዙሪያው ፀጉር ይበቅላል። እንዲሁም የመራቢያ አካላትህ የወንድ ዘር ተሸካሚ ፈሳሽ ማምረት ይጀምራሉ። ይህ ፈሳሽ በሚሊዮን የሚቆጠሩ በዓይን የማይታዩ የወንድ ዘሮችን (ስፐርም) የያዘ ሲሆን የፆታ ግንኙነት በሚደረግበት ወቅት እነዚህ ዘሮች ከሰውነትህ ይወጣሉ። አንድ የወንድ ዘር ከሴቷ እንቁላል ጋር በመዋሃድ ፅንስ እንዲፈጠር ማድረግ ይችላል።
በሰውነትህ ውስጥ ያለው የወንድ ዘር ተሸካሚ ፈሳሽ መጠን እየጨመረ ሲሄድ ሰውነትህ የተወሰነውን ይጠቀምበታል፤ ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ሌሊት ተኝተህ እያለ ሊፈስ ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ሁሉም ወንዶች ሊያጋጥማቸው የሚችል ነገር ነው። የዘር መፍሰስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ተጠቅሷል። (ዘሌዋውያን 15:16, 17) ይህ ሁኔታ የመራቢያ አካላትህ በሚገባ እየሠሩ እንደሆነና ወደ ወንድነት የምትሸጋገርበትን ጉዞ እንደጀመርክ የሚጠቁም ነው።
ከላይ ከተጠቀሱት ለውጦች አንዳንዶቹን በሰውነትህ ላይ መመልከት ጀምረሃል? ካጋጠሙህ ለውጦች ጋር በተያያዘ የሚፈጠርብህን ማንኛውንም ጥያቄ በክፍት ቦታው ላይ አስፍር።
․․․․․
አዳዲስ ስሜቶችን መቋቋም
ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆች የመራቢያ አካላታቸው እየዳበሩ ሲመጡ ስለ ተቃራኒ ፆታ ከዚህ በፊት ተሰምቷቸው የማያውቅ ስሜት ይፈጠርባቸዋል። ማት እንዲህ ብሏል፦ “የጉርምስና ዕድሜ ላይ ስደርስ ቆንጆ ቆንጆ የሆኑ ብዙ ሴቶች ልጆች እንዳሉ አስተዋልኩ። በሌላ በኩል ደግሞ እስካድግ ድረስ የፍቅር ጓደኝነት መመሥረት እንደማልችል አውቅ ነበር፤ ይህም በጣም የሚያበሳጭ ነበር።” እያደግህ ስትሄድ የሚፈጠርብህን እንዲህ ያለውን ስሜት በተመለከተ ምዕራፍ 29 ሰፋ ያለ ማብራሪያ ይዟል። እስከዛው ልታውቀው የሚገባው ነገር የፆታ ስሜትህን መቆጣጠርን መልመድህ አስፈላጊ መሆኑን ነው። (ቆላስይስ 3:5) ስሜትህን መቆጣጠር ከባድ ሊመስል ቢችልም እንዲህ ማድረግ ትችላለህ!
በጉርምስና ወቅት የሚታገሉህ ሌሎች ስሜቶችም ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ ለራስህ ጥሩ አመለካከት አይኖርህ ይሆናል። ብዙውን ጊዜ ወጣቶች የብቸኝነት ስሜት የሚያድርባቸው ከመሆኑም ሌላ አልፎ አልፎ በመንፈስ ጭንቀት ይዋጣሉ። በእነዚህ ጊዜያት ወላጆችህን ወይም የምትተማመንበትን አንድ ትልቅ ሰው ማነጋገርህ ጥሩ ነው። በውስጥህ የሚታገሉህን ስሜቶች በተመለከተ ልታወያየው የምትችል ትልቅ ሰው አለ? ስሙን ከታች አስፍር።
․․․․․
ከምንም በላይ አስፈላጊ የሆነው ነገር
ከማደግ ጋር በተያያዘ ከምንም በላይ አስፈላጊ የሆነው ነገር ቁመትህ፣ ተክለ ሰውነትህ ወይም መልክህ ሳይሆን በማንነትህ ይኸውም በአስተሳሰብህና በስሜትህ ከሁሉ በላይ ደግሞ በመንፈሳዊነትህ ረገድ የምታደርገው እድገት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ሕፃን በነበርኩበት ጊዜ እንደ ሕፃን እናገር፣ እንደ ሕፃን አስብ እንዲሁም እንደ ሕፃን አመዛዝን ነበር፤ አሁን ሙሉ ሰው ከሆንኩ በኋላ ግን የሕፃንነትን ጠባይ ትቻለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 13:11) ሊተላለፍ የተፈለገው ነጥብ ግልጽ ነው፤ ትልቅ ሰው መስሎ መታየት ብቻውን በቂ አይደለም። አነጋገርህና አስተሳሰብህ እንዲሁም ነገሮችን የምታከናውንበት መንገድ እንደ ትልቅ ሰው ሊሆን ይገባል። ለውስጣዊ ሰውነትህ ትኩረት የመስጠትን አስፈላጊነት እስክትዘነጋ ድረስ ስለ ውጫዊ ገጽታህ ከሚገባ በላይ መጨነቅህ ተገቢ አይደለም!
ከዚህም በተጨማሪ አምላክ ‘ልብን እንደሚያይ’ አትዘንጋ። (1 ሳሙኤል 16:7) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ንጉሥ ሳኦል ቁመቱ ዘለግ ያለ መልከ ቀና ሰው እንደነበር ይናገራል፤ ይሁንና ከአንድ ትልቅ ሰውም ሆነ ከአንድ ንጉሥ የማይጠበቅ ነገር አድርጓል። (1 ሳሙኤል 9:2) ከዚህ በተቃራኒ፣ ዘኬዎስ “ቁመቱ አጭር” ቢሆንም ውስጣዊ ጥንካሬ ስለነበረው ሕይወቱን አስተካክሎ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ለመሆን ችሏል። (ሉቃስ 19:2-10) በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ውስጣዊ ማንነት ነው።
ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ ሁን፦ ጤንነትህን ሳትጎዳ አካላዊ እድገትህን ማፋጠን ወይም ማዘግየት የምትችልበት ምንም መንገድ የለም። ስለዚህ በሰውነትህ ላይ ለውጦች በመታየታቸው ልትጨነቅ ወይም እነዚህን ለውጦች ልትጠላቸው አይገባም፤ ከዚህ ይልቅ በጸጋ ብትቀበላቸውና በራስህ ላይ መሳቅ ብትለምድ የተሻለ ይሆናል። ጉርምስና በሽታ አይደለም፤ በዚህ ሂደት ለማለፍም አንተ የመጀመሪያው አይደለህም። ጉርምስና ማንንም አልገደለም፤ አንተም ይህን ወቅት እንደምታልፈው እርግጠኛ ሁን። እንደ ማዕበል የሚያንገላታህ የጉርምስና ወቅት ሲያልፍ ሙሉ ሰው ወደ መሆን ትሸጋገራለህ!
ራስሽን በመስተዋት ስታዪ መልክሽ ቢያስጠላሽስ? ስለ መልክሽ ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበር የምትችዪው እንዴት ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሴቶች ልጆችም ብጉር ሊወጣባቸው ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ለቆዳ ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ ችግሩ እንዳይባባስ መከላከል ይቻላል።
ቁልፍ ጥቅስ
“ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ።”—መዝሙር 139:14
ጠቃሚ ምክር
እያደጋችሁ ስትሄዱ የፆታ ስሜት የሚቀሰቅሱ ልብሶችን ላለመልበስ መጠንቀቅ ይኖርባችኋል። ምንጊዜም አለባበሳችሁ ‘ልከኝነትና ማስተዋል’ የሚንጸባረቅበት ሊሆን ይገባል።—1 ጢሞቴዎስ 2:9
ይህን ታውቅ ነበር?
ጉርምስና ገና በስምንት ዓመት ዕድሜ ወይም ከዘገየ ደግሞ በአሥራዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ ሊጀምር ይችላል። በመሆኑም ጉርምስና የሚጀምርበት ዕድሜ ከሰው ሰው ይለያያል።
ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች
ወደ ሙሉ ሰውነት በማደርገው ጉዞ በተለይ ላዳብረው የሚገባው ባሕርይ ․․․․․
በመንፈሳዊ ለማደግ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․
ምን ይመስልሃል?
● በጉርምስና ወቅት የሚያጋጥሙትን አካላዊና ስሜታዊ ለውጦች መቀበል ያን ያህል አስቸጋሪ የሚሆነው ለምንድን ነው?
● በዚህ የሽግግር ወቅት በጣም አስቸጋሪ የሆነብህ ነገር ምንድን ነው?
● በጉርምስና ወቅት ለአምላክ ያለህ ፍቅር ሊቀንስ የሚችለው ለምን ይመስልሃል? ይህ እንዳይሆን ምን ማድረግ ትችላለህ?
[በገጽ 61 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በጉርምስና ወቅት ስጋት እንዲያድርባችሁ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች ያጋጥሟችኋል፤ በሰውነታችሁ ላይ ምን ለውጥ እንደሚካሄድ በእርግጠኝነት ማወቅ አትችሉም። ሆኖም እያደጋችሁ ስትሄዱ እነዚህን ለውጦች የምትለምዷቸው ከመሆኑም በላይ ሁኔታውን ተቀብላችሁ መኖር ትጀምራላችሁ።”—አኔት
[በገጽ 63 እና 64 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከአባባ ወይም ከእማማ ጋር ከፆታ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ማውራት የምችለው እንዴት ነው?
“ከፆታ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ጥያቄ ቢኖረኝ በምንም ዓይነት ወላጆቼን አልጠይቃቸውም።”—ቤዛ
“እንዲህ ያለውን ጉዳይ ለማንሳት ድፍረቱ የለኝም።”—ዳንኤል
አንተም እንደ ቤዛና እንደ ዳንኤል የሚሰማህ ከሆነ በእርግጥም ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ገጥሞሃል። ከፆታ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ማወቅ ትፈልጋለህ፤ ወላጆችህ ስለዚህ ጉዳይ ሊነግሩህ ቢችሉም አንተ ግን ወደ እነሱ መሄድ አትፈልግ ይሆናል። የሚከተሉት ጉዳዮች ያሳስቡሃል፦
ስለ ፆታ ብጠይቃቸው ስለ እኔ ምን ይሰማቸዋል?
“ብጠይቃቸው በጥርጣሬ ዓይን ያዩኛል ብዬ ስለምፈራ ዝም ማለት እመርጣለሁ።”—ጄሲካ
“ወላጆች ምንጊዜም ምንም የማታውቁ ልጆች ሆናችሁ ብትኖሩ ደስ ይላቸዋል፤ ስለ ፆታ ብታዋሯቸው ግን እናንተን እንደ ድሮው ማየት ያቆማሉ።”—ቤዛ
ምን ይሉኝ ይሆን?
“ወላጆቼ፣ ገና ተናግሬ ሳልጨርስ ዘለው አንድ መደምደሚያ ላይ ይደርሱና ማቆሚያ የሌለው ምክር ይሰጡኛል ብዬ እፈራለሁ።”—ግሎሪያ
“ወላጆቼ ስሜታቸውን መደበቅ ስለማይችሉ ብጠይቃቸው እንዳዘኑብኝ የሚጠቁም ነገር ፊታቸው ላይ ባይስ ብዬ እፈራለሁ። እንዲያውም አባቴ፣ እኔ እየተናገርኩ እያለ የሚያስበው ምን ብሎ እንደሚመክረኝ ሊሆን ይችላል።”—ፓም
በተሳሳተ መንገድ ይረዱኝ ይሆን?
“ጉዳዩን አክብደው በመመልከት ‘የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም አሰብሽ እንዴ?’ ወይም ‘እኩዮችሽ ግፊት እያሳደሩብሽ ነው?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎች መጠየቅ ይጀምሩ ይሆናል። እናንተ ግን ጉዳዩን ያነሳችሁት ለማወቅ ስለፈለጋችሁ ብቻ ሊሆን ይችላል።”—ሊሳ
“ስለ ወንድ ባነሳሁ ቁጥር በአባቴ ፊት ላይ የጭንቀት ስሜት አነባለሁ። ከዚያም ወዲያውኑ ስለ ፆታ ጉዳዮች ማውራት ይጀምራል። በዚህ ጊዜ ‘አባባ እኔኮ ልጁ ያምራል ብቻ ነው ያልኩት። ስለ ጋብቻ ወይም ስለ ፆታ ግንኙነት የተናገርኩት ነገር አለ?’ ልለው ይቃጣኛል።”—ስቴሲ
ከፆታ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ከወላጆችህ ጋር ማውራት አንተን እንደሚያሳፍርህ ሁሉ ወላጆችህም ይህን ጉዳይ አንስተው ከአንተ ጋር መወያየት እንደሚያሳፍራቸው ማወቅህ ጭንቀትህን ቀለል ያደርግልህ ይሆናል። አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከፆታ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ከልጆቻቸው ጋር እንደተነጋገሩ የገለጹት ወላጆች 65 በመቶ ሆነው ሳለ እንዲህ ዓይነት ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹት ልጆች ግን 41 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው፤ ይህ ልዩነት የተፈጠረው ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር እንዲህ ዓይነት ውይይት ማድረግ ስለሚያሳፍራቸው ሊሆን ይችላል።
ወላጆችህ ከፆታ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ማውራት ሊከብዳቸው የሚችል መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው። ይህ የሆነው የእነሱም ወላጆች ስለዚህ ጉዳይ በግልጽ ስላላዋሯቸው ሊሆን ይችላል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን አትፍረድባቸው፤ ከዚህ ይልቅ ስሜታቸውን ተረዳላቸው። አንተ ራስህ ደፈር ብለህ ጉዳዩን ብታነሳባቸው ሁለታችሁም ትጠቀማላችሁ። እንዲህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
ውይይቱ እንዴት ይጀመር?
ወላጆችህ ከፆታ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ሰፊ እውቀት ያላቸው ከመሆኑም በላይ ካካበቱት ተሞክሮ ብዙ ጠቃሚ ሐሳብ ሊያካፍሉህ ይችላሉ። ከአንተ የሚፈለገው ነገር ለውይይቱ በር መክፈት ብቻ ነው። እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦
1 ስለ አንድ ጉዳይ ልታነጋግራቸው እንደፈለግክ ሆኖም የሚሰጡህ ምላሽ እንዳስፈራህ በግልጽ ንገራቸው። “ላነጋግራችሁ ያሰብኩት ነገር ነበር፤ ሆኖም . . . ብላችሁ እንዳታስቡ ፈርቻለሁ።”
2 ከዚያም እነሱን ለማነጋገር የመረጥከው ለምን እንደሆነ ንገራቸው። “አንድ ጥያቄ አለኝ፤ መልሱን ከሌላ ሰው ከምሰማው እናንተ ብትነግሩኝ ይሻላል ብዬ ነው።”
3 ከዚያም ጥያቄህን በግልጽ አቅርብላቸው። “ልጠይቃችሁ ያሰብኩት . . .”
4 ውይይታችሁ መደምደሚያ ላይ በሌላም ጊዜ እንደዚሁ ልታነጋግራቸው እንደምትፈልግ ግለጽ። “ሌላ ጥያቄ ከተፈጠረብኝ ስለዚህ ጉዳይ እንደገና ላነጋግራችሁ እችላለሁ?”
ወላጆችህ የሚሰጡህ መልስ ‘አዎ’ እንደሆነ ብታውቅም ይህን ከእነሱ አንደበት መስማትህ ሌላ ጊዜ ልታነጋግራቸው ብታስብ መንገዱ ክፍት እንዲሆንና የበለጠ ነፃነት እንዲሰማህ ያደርጋል። ታዲያ እነዚህን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ለምን አትሞክርም? አንተም እንደ ትሪና ይሰማህ ይሆናል። አሁን 24 ዓመት የሆናት ይህቺ ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ከእማማ ጋር እያወራን እያለ ‘እንዲህ ያለ ነገር ምነው ባይነሳ’ ብዬ ተመኝቼ ነበር። አሁን ሳስበው ግን እናቴ ስለዚህ ጉዳይ ምንም ሳትሸፋፍን በግልጽ ስላነጋገረችኝ በጣም ደስተኛ ነኝ። እንዲህ ማድረጓ ትልቅ ጥበቃ ሆኖልኛል!”
[በገጽ 59 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልጅነትሽን መሰናበት የኖርሽበትን ሰፈር ለቀሽ የመሄድን ያህል ከባድ ሊሆንብሽ ቢችልም አዲሱን ሁኔታ መልመድ ትችያለሽ