ምዕራፍ 22
ይህን ያህል መመሪያ የሚበዛብኝ ለምንድን ነው?
ወላጆችህ ያወጧቸውን አንዳንድ መመሪያዎች ጥቀስ። ․․․․․
ወላጆችህ የሚያወጧቸው መመሪያዎች ሁልጊዜ ምክንያታዊ እንደሆኑ ይሰማሃል?
□ አዎ □ አይ
ለመታዘዝ በጣም የሚከብድህ የትኛው መመሪያ ነው? ․․․․․
ወላጆችህ ወይም አሳዳጊዎችህ፣ ምን ማድረግ እንዳለብህና እንደሌለብህ ነግረውህ መሆን አለበት። ይህም የትምህርት ቤት ሥራህን፣ የቤት ውስጥ ሥራዎችንና ቤት የምትገባበትን ሰዓት የሚመለከቱ መመሪያዎችን እንዲሁም ከስልክ፣ ከቴሌቪዥን ወይም ከኮምፒውተር አጠቃቀምህ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ገደቦችን ሊጨምር ይችላል። አንዳንዶቹ መመሪያዎች ከቤት ውጭ ያለህን ሕይወት ማለትም በትምህርት ቤት የምታሳየውን ባሕርይና የጓደኛ ምርጫህንም የሚመለከቱ ሊሆኑ ይችላሉ።
ወላጆችህ ያወጧቸው መመሪያዎች መፈናፈኛ እንዳሳጡህ ይሰማሃል? ምናልባት አንተም ከዚህ በታች እንደተጠቀሱት ወጣቶች ይሰማህ ይሆናል፦
“በተወሰነ ሰዓት ቤት እንድገባ የሚጠበቅብኝ መሆኑ በጣም ያበሳጨኝ ነበር! ሌሎች ልጆች አምሽተው እንዲገቡ እየተፈቀደላቸው እኔ መከልከሌ ያናድደኝ ነበር።”—አለን
“በሞባይል ስልክህ ከማን ጋር እንደምታወራ ቁጥጥር ሲደረግብህ በጣም ይደብራል። እንደ ሕፃን ልጅ የምታይ ይመስለኛል!”—ኤሊዛቤት
“ወላጆቼ ከማንም ጋር እንዳልገናኝ ለማድረግ እየሞከሩ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር፤ ሁኔታው ጓደኛ የሚባል ነገር እንዳይኖረኝ የሚፈልጉ ይመስል ነበር!”—ኒሳን
ወጣቶች ብዙውን ጊዜ ወላጆቻቸው ያወጡላቸውን መመሪያዎች ሲጥሱ ይስተዋላል፤ ያም ሆኖ አብዛኞቹ ወጣቶች በቤት ውስጥ ሥርዓት እንዲኖር አንዳንድ መመሪያዎች መውጣታቸው አስፈላጊ እንደሆነ ይስማማሉ። ታዲያ ወላጆች የሚያወጧቸው መመሪያዎች ይህን ያህል አስፈላጊ ከሆኑ አንዳንዶቹ መመሪያዎች ልጆችን የሚያበሳጯቸው ለምንድን ነው?
“እኔኮ ሕፃን ልጅ አይደለሁም!”
ወላጆችህ የሚያወጧቸው መመሪያዎች የሚያበሳጩህ እንደ ልጅ እንደምትታይ ስለሚሰማህ ሊሆን ይችላል። “እኔኮ ሕፃን ልጅ አይደለሁም!” በማለት ተቃውሞህን ትገልጽ ይሆናል። ወላጆችህ ደግሞ አንተን ከጉዳት ለመጠበቅም ሆነ ስታድግ ኃላፊነት የሚሰማህ ሰው መሆን እንድትችል ከወዲሁ ለማዘጋጀት አሁን የሚያወጡልህ መመሪያዎች ወሳኝ እንደሆኑ ይሰማቸው ይሆናል።
እርግጥ ነው፣ በዕድሜ ከፍ እያልክ ብትሄድም ወላጆችህ ልጅ ሳለህ ያወጡልህ መመሪያዎች ምንም እንዳልተሻሻሉ ይሰማህ ይሆናል። አንተም ብሌን እንደተባለችው ወጣት ገደብ እንደበዛብህ ሊሰማህ ይችላል፤ ብሌን ስለ ወላጆቿ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “በእኔ ዕድሜ ያለፉ አይመስሉም። አመለካከቴን እንድገልጽ፣ የራሴን ምርጫ እንዳደርግ ወይም ትልቅ ሰው እንድሆን አይፈልጉም።” አሊሰን የተባለች ወጣትም እንደዚህ ይሰማታል። “ወላጆቼ 18 ዓመት እንደሞላኝ የዘነጉ ይመስላል፤ ዛሬም የሚያዩኝ እንደ 10 ዓመት ልጅ ነው። የበለጠ ሊተማመኑብኝ ይገባል!” ብላለች።
በተለይ ደግሞ ወላጆችህ በወንድሞችህና በእህቶችህ ላይ ያን ያህል ጥብቅ ካልሆኑ የሚያወጧቸውን መመሪያዎች መታዘዝ ይበልጥ አስቸጋሪ ሊሆንብህ ይችላል። ለምሳሌ ማቲው የተባለው ወጣት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በነበረበት ጊዜ ወላጆቹ ታናሽ እህቱንና የአክስቱን ልጆች እንዴት እንደሚይዟቸው ሲያስታውስ “እነሱ የፈለጉትን ቢያደርጉ ምንም አይባሉም ነበር!” ብሏል።
ጨርሶ መመሪያ ባይኖርስ?
ከወላጆችህ ቁጥጥር ነፃ የምትወጣበትን ጊዜ ትናፍቅ ይሆናል። ሆኖም ከእነሱ ቁጥጥር ነፃ መውጣትህ የሚያዋጣህ ይመስልሃል? እስከፈለጉበት ሰዓት አምሽተው ቤታቸው የሚገቡ፣ ያሻቸውን የሚለብሱ ብሎም ከጓደኞቻቸው ጋር ወደፈለጉበት ቦታ ባሰኛቸው ሰዓት የሚሄዱ እኩዮችህን ታውቅ ይሆናል። ምናልባት ወላጆቻቸው በሥራ ከመጠመዳቸው የተነሳ ልጆቻቸው ምን እንደሚያደርጉ ሳያስተውሉ ቀርተው ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ፣ እንዲህ ዓይነቱ የልጅ አስተዳደግ የተሳካ ውጤት እንደማያስገኝ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ምሳሌ 29:15) ዛሬ በዓለም ላይ ለሚታየው የፍቅር መጥፋት ዋነኛው መንስኤ ሰዎች ራስ ወዳድ መሆናቸው ሲሆን ከእነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ ቁጥጥር በማይደረግበት ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ናቸው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
ደስ ያላቸውን ነገር ሁሉ እንዲያደርጉ የሚፈቀድላቸውን ወጣቶች በማየት ከመቅናት ይልቅ ወላጆችህ መመሪያዎች የሚያወጡልህ ስለሚወዱህና ስለሚያስቡልህ እንደሆነ ለመረዳት ሞክር። እንዲያውም ወላጆችህ ምክንያታዊ የሆኑ ገደቦች ማውጣታቸው የይሖዋ አምላክን ምሳሌ እንደሚከተሉ የሚያሳይ ነው፤ ይሖዋ ለሕዝቡ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ።”—መዝሙር 32:8
አንዳንድ ጊዜ ግን ወላጆችህ የሚያወጧቸው መመሪያዎች የማያፈናፍኑ እንደሆኑ ይሰማህ ይሆናል። ታዲያ በተወሰነ መጠን ነፃነት ለማግኘት ምን ማድረግ ትችላለህ?
ውጤታማ የሆነ ውይይት ማድረግ
የበለጠ ነፃነት ለማግኘትም ይሁን አሁን ያሉት ገደቦች የሚፈጥሩብህን መጥፎ ስሜት ለማስወገድ እንድትችል ቁልፉ ጥሩ ውይይት ማድረግ ነው። አንዳንዶች ‘ወላጆቼን ለማነጋገር ሞክሬያለሁ፤ ግን ምንም ለውጥ አልመጣም!’ ይሉ ይሆናል። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ‘አነጋገሬን ማሻሻል ያስፈልገኝ ይሆን?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። ከወላጆችህ ጋር መነጋገር በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም (1) ሌሎች የአንተን ስሜት ይበልጥ እንዲረዱ ለማድረግ ወይም (2) የፈለግኸውን እንዳታደርግ የተከለከልከው ለምን እንደሆነ ለማወቅ ያስችልሃል። በእርግጥም፣ እንደ አዋቂ መታየት ከፈለግህ ንግግርህም እንደ አዋቂ ሊሆን ይገባል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
ስሜትህን መቆጣጠር ተማር። ጥሩ ውይይት ለማድረግ ራስህን መግዛት ያስፈልግሃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ተላላ ሰው ቍጣውን ያለ ገደብ ይለቀዋል፤ ጠቢብ ሰው ግን ራሱን ይቈጣጠራል” ይላል። (ምሳሌ 29:11) ስለዚህ ከወላጆችህ ጋር በምትነጋገሩበት ጊዜ አትነጫነጭ፣ አታኩርፍ እንዲሁም ሕፃን ይመስል ለምን ተነካሁ አትበል። ወላጆችህ አንድ ነገር ሲከለክሉህ በር የምታላትም ወይም እየተመናጨቅክ የምትሄድ ከሆነ ይህ ዓይነቱ ባሕርይ ይበልጥ ነፃነት እንድታገኝ ከማድረግ ይልቅ ተጨማሪ ገደቦች እንዲጣሉብህ ሊያደርግ ይችላል።
የወላጆችህን አመለካከት ለመረዳት ሞክር። በነጠላ ወላጅ ያደገች ትሬሲ የተባለች ክርስቲያን ወጣት እንዲህ ትላለች፦ “‘እናቴ መመሪያውን ያወጣችበት ምክንያት ምንድን ነው?’ በማለት ራሴን እጠይቃለሁ።” ትሬሲ የደረሰችበትን መደምደሚያ ስትገልጽ “እናቴ ይህን የምታደርገው የተሻልኩ ሰው መሆን እንድችል ለመርዳት ነው” ብላለች። (ምሳሌ 3:1, 2) አንተም የወላጆችህን ስሜት ለመረዳት መሞከርህ ውጤታማ የሆነ ውይይት ለማድረግ ያስችላችኋል።
ለምሳሌ ያህል፣ ወላጆችህ ወደ አንድ ግብዣ እንድትሄድ አልፈቀዱልህም እንበል። ከመከራከር ይልቅ “አንድ የጎለመሰና እምነት የሚጣልበት ሰው ከእኔ ጋር ቢሄድስ?” ብለህ ልትጠይቃቸው ትችላለህ። እርግጥ እንዲህ ብትልም ወላጆችህ የጠየቅከውን ነገር ላይፈቅዱልህ ይችላሉ። ሆኖም ያሳሰባቸውን ነገር መረዳትህ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችል ሐሳብ ለማቅረብ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥርልሃል።
ወላጆችህ የሚተማመኑብህ ልጅ ለመሆን ጥረት አድርግ። አንድ ሰው ከባንክ ገንዘብ ተበድሯል እንበል። ይህ ሰው ዕዳውን በጊዜው የሚከፍል ከሆነ የባንኩን አመኔታ ስለሚያተርፍ ባንኩ ወደፊት ተጨማሪ ብድር ሊሰጠው ይችላል። ከወላጆችህ ጋር ባለህ ግንኙነትም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ወላጆችህን የመታዘዝ “ዕዳ” አለብህ። በትናንሽ ነገሮችም እንኳ እምነት የሚጣልብህ መሆንህን ካስመሠከርክ በወላጆችህ ዘንድ የበለጠ አመኔታ ታተርፋለህ። በሌላ በኩል ግን ዕዳህን በጊዜው ካልከፈልክ ባንኩ ለአንተ የሚሰጠውን ብድር ሊቀንስ አሊያም ከናካቴው ሊያቆም እንደሚችል ሁሉ በተደጋጋሚ ጊዜ የወላጆችህን ትእዛዝ የምትጥስ ከሆነም ወላጆችህ በአንተ ላይ ያላቸው እምነት ቢቀንስ ወይም እስከነጭራሹ ቢጠፋ ልትገረም አይገባም።
የወላጆችህን መመሪያ ስትጥስ
የወላጆችህን መመሪያ ብትጥስ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ለምሳሌ የታዘዝከውን ሥራ አልሠራህም ወይም በተወሰነልህ ሰዓት ቤት አልገባህም አሊያም ደግሞ ከተፈቀደልህ ሰዓት በላይ ስልክ አውርተሃል እንበል። (መዝሙር 130:3) በዚህ ጊዜ ምክንያትህን ለወላጆችህ መናገር ይኖርብሃል! ታዲያ ችግሩ እንዳይባባስ ምን ልታደርግ ትችላለህ?
እውነቱን ተናገር። የማይመስል ነገር አታውራ። አለዚያ ወላጆችህ በአንተ ላይ ያላቸው እምነት ጨርሶ ሊጠፋ ይችላል። ስለዚህ ሐቀኛ ሁን፤ እንዲሁም ጉዳዩን አድበስብሰህ ለማለፍ አትሞክር። (ምሳሌ 28:13) ድርጊትህ ትክክል እንደሆነ ለማሳመን ከመጣር ወይም ጥፋትህን ቀለል አድርገህ ከመናገር ተቆጠብ። እንዲሁም ‘የለዘበ መልስ ቍጣን እንደሚያበርድ’ ምንጊዜም አስታውስ።—ምሳሌ 15:1
ይቅርታ ጠይቅ። ወላጆችህን በማስጨነቅህ፣ በማበሳጨትህ ወይም በእነሱ ላይ ጫና በመፍጠርህ በጣም እንዳዘንክ መግለጽህ ተገቢ ከመሆኑም በላይ የሚደርስብህን ቅጣት ሊያቀልልህ ይችላል። ሆኖም የተጸጸትከው ከልብህ መሆን አለበት።
ጥፋትህ የሚያስከትለውን ቅጣት ለመቀበል ፈቃደኛ ሁን። (ገላትያ 6:7) በተለይ መቀጣትህ ተገቢ እንዳልሆነ ከተሰማህ መጀመሪያ ላይ የሚቀናህ ቅጣቱን ላለመቀበል ሙግት መግጠም ሊሆን ይችላል። ሆኖም ድርጊትህ ያስከተለውን ውጤት መቀበል የጉልምስና ምልክት ነው። ከሁሉ የተሻለው አማራጭ የወላጆችህን አመኔታ መልሰህ ለማግኘት መጣር ሊሆን ይችላል።
ከላይ ከተዘረዘሩት ሦስት ነጥቦች መካከል ይበልጥ ልትሠራበት እንደሚገባ የሚሰማህን በክፍት ቦታው ላይ ጻፍ። ․․․․
ወላጆችህ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ አንተን የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለባቸው ማስታወስ ይገባሃል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ስለ አባትህ ትእዛዝ’ እና ‘ስለ እናትህ ትምህርት’ ወይም ሕግ የሚናገረው ለዚህ ነው። (ምሳሌ 6:20) ያም ቢሆን ወላጆችህ የሚያወጡልህ መመሪያ ሕይወትህን መራራ እንደሚያደርገው ሊሰማህ አይገባም። ከዚህ በተቃራኒ ለወላጆችህ ሥልጣን የምትገዛ ከሆነ ‘መልካም እንደሚሆንልህ’ ይሖዋ ቃል ገብቷል!—ኤፌሶን 6:1-3
ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 3 ተመልከት
አባትህ ወይም እናትህ የዕፅ ወይም የአልኮል ሱሰኞች ናቸው? እንዲህ ያለውን ችግር መቋቋም የምትችለው እንዴት እንደሆነ ትምህርት ታገኛለህ።
ቁልፍ ጥቅስ
‘አባትህንና እናትህን አክብር፤ ይህም መልካም እንዲሆንልህ ያደርጋል።’—ኤፌሶን 6:2, 3
ጠቃሚ ምክር
ወላጆችህ ተጨማሪ ነፃነት እንዲሰጡህ ከፈለግህ ያወጧቸውን መመሪያዎች በመታዘዝ የእነሱን አመኔታ አትርፍ። ታዛዥ ልጅ በመሆን ጥሩ ስም ካተረፍክ የምትጠይቃቸውን ነገር የመፍቀዳቸው አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል።
ይህን ታውቅ ነበር?
ያወጧቸውን መመሪያዎች ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ የሚያስፈጽሙ ወላጆች ያሳደጓቸው ወጣቶች፣ በአብዛኛው በትምህርት የላቀ ውጤት እንደሚያመጡ፣ ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንደሚኖራቸውና ደስተኞች እንደሚሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ።
ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች
የወላጆቼን መመሪያ ከጣስኩ እንዲህ እላቸዋለሁ፦ ․․․․․
የወላጆቼን አመኔታ ለማትረፍ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․
ምን ይመስልሃል?
● አንዳንድ ጊዜ ወላጆችህ ቁጥጥር እንደሚያበዙብህ የሚሰማህ ከሆነ እንዲህ የሚያደርጉት ለምን ይመስልሃል?
● ወላጆችህ የሚጥሉብህ ገደቦች አንዳንድ ጊዜ የሚያበሳጩህ ለምን ሊሆን ይችላል?
● ከወላጆችህ ጋር በምትነጋገርበት መንገድ ላይ ማሻሻያ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 183 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ወጣት እያለህ ሁሉን ነገር የምታውቅ ይመስልሃል። በመሆኑም ወላጆችህ ገደብ ሲያወጡብህ በቀላሉ ትበሳጫለህ። እውነቱን ለመናገር ግን መመሪያዎቹን የሚያወጡት ለአንተው ጥቅም ነው።”—ሜገን
[በገጽ 186 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ማዳላት ሊባል ይችላል?
‘ወላጆች ሁሉንም ልጆች በእኩል ዓይን የማያዩት ለምንድን ነው?’ በማለት ጠይቀህ ታውቃለህ? ከሆነ ልብ ልትለው የሚገባ አንድ ሐቅ አለ፦ ወላጆችህ ሁሉንም ልጆቻቸውን በእኩል ዓይን መመልከታቸው ሁልጊዜ ትክክል ይሆናል ማለት አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ እዚህ ላይ መነሳት የሚገባው ጥያቄ ‘ወላጆችህ የሚያስፈልጉህን ነገሮች አያሟሉልህም?’ የሚለው ነው። ለምሳሌ የወላጆችህ ምክር፣ እርዳታ ወይም ድጋፍ በሚያስፈልግህ ጊዜ ከእነሱ የሚጠበቀውን ነገር ያደርጉልሃል? ከሆነ አድሎ እንደተደረገብህ ብትናገር እውነት ይሆናል? የአንተም ሆነ የወንድሞችህና የእህቶችህ ባሕርይ ወይም የሚያስፈልጋችሁ ነገር የተለያየ በመሆኑ ወላጆቻችሁ ሁላችሁንም ሁልጊዜ በእኩል መንገድ መያዝ አይችሉም። ቤዛ የተባለችው ወጣት ከጊዜ በኋላ ይህንን ተገንዝባለች። ቤዛ አሁን 18 ዓመት የሆናት ሲሆን እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ወንድሜ ሁለት የተለያየን ሰዎች በመሆናችን ወላጆቻችን እኩል ሊይዙን አይችሉም። ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስበው ልጅ እያለሁ ይህንን መረዳት አለመቻሌ ይገርመኛል።”
[በገጽ 189 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የመልመጃ ሣጥን
ወላጆችህን አነጋግራቸው!
ከዚህ በፊት ባሉት ሁለት ምዕራፎች ላይ ወላጆችህ ከሚሰነዝሩብህ ነቀፋ እንዲሁም ከሚያወጧቸው መመሪያዎች ጋር በተያያዘ ምን ማድረግ እንደምትችል የሚጠቁም ሐሳብ ቀርቧል። ታዲያ ወላጆችህ ከሚገባው በላይ እንደሚነቅፉህ ወይም መመሪያዎቻቸው በጣም ጥብቅ እንደሆኑ ቢሰማህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ይህን ጉዳይ አንስተህ ልታነጋግራቸው የምትችለው እንዴት ነው?
● ወላጆችህን በሥራ ባልተወጠሩበትና አንተም በተረጋጋህበት ሰዓት አነጋግራቸው።
● ስሜታዊ ሳትሆን ከልብህ የሚሰማህን ለወላጆችህ ንገራቸው። እንዲሁም ተገቢውን አክብሮት አሳያቸው።
ወላጆችህ ከሚገባው በላይ እንደሚነቅፉህ የሚሰማህ ከሆነ እንዲህ ልትላቸው ትችላለህ፦ “ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የቻልኩትን ያህል እየጣርኩ ነው፤ ሁልጊዜ ስነቀፍ ግን ይህን ማድረግ ይከብደኛል። ስለዚህ ጉዳይ መነጋገር እንችላለን?”
ስለዚህ ጉዳይ አንተ ራስህ ከወላጆችህ ጋር ውይይት ለመጀመር ምን ማለት እንደምትችል ከዚህ በታች ጻፍ።
․․․․․
✔ጠቃሚ ምክር፦ ለውይይቱ መንደርደሪያ እንዲሆንህ በምዕራፍ 21 ላይ የቀረቡትን ነጥቦች አንሳላቸው። ምናልባትም ወላጆችህ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ በቀረቡት ትምህርቶች ላይ ከአንተ ጋር ለመወያየት ሊነሳሱ ይችላሉ።
ወላጆችህ ተገቢውን ነፃነት እንዳልሰጡህ የሚሰማህ ከሆነ እንዲህ ልትላቸው ትችላለህ፦ “ከጊዜ በኋላ የበለጠ ነፃነት ማግኘት እንድችል ይበልጥ ኃላፊነት የሚሰማኝ ሰው ለመሆን ጥረት ማድረግ እፈልጋለሁ። በዚህ ረገድ ምን ማሻሻል እንደሚገባኝ ልትነግሩኝ ትችላላችሁ?”
ስለዚህ ጉዳይ አንተ ራስህ ከወላጆችህ ጋር ውይይት ለመጀመር ምን ማለት እንደምትችል ከዚህ በታች ጻፍ።
․․․․․
✔ጠቃሚ ምክር፦ የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 3 ተመልከት። ከዚያም ባነበብከው ላይ ተመሥርተህ ከወላጆችህ ጋር ልትወያይባቸው የምትፈልጋቸውን ጥያቄዎች ጻፍ።
[በገጽ 184 እና 185 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የወላጆችን መመሪያ መታዘዝ ለባንክ ዕዳን ከመክፈል ጋር ይመሳሰላል፤ እምነት የሚጣልባችሁ በሆናችሁ መጠን ተጨማሪ ብድር ታገኛላችሁ በሌላ አባባል የበለጠ አመኔታ ታተርፋላችሁ