የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 40—ማቴዎስ
ጸሐፊው:- ማቴዎስ
የተጻፈበት ቦታ:- ፓለስቲና
ተጽፎ ያለቀው:- በ41 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
ታሪኩ የሚሸፍነው ጊዜ:- ከ2 ከክ.ል.በፊት እስከ 33 ከክ.ል.በኋላ
ይሖዋ፣ በኤደን ዓመጽ ከተፈጸመበት ጊዜ አንስቶ ጽድቅ ወዳድ የሆኑ ሰዎችን በሙሉ “በሴቲቱ” ዘር አማካኝነት እንደሚያድናቸው የሚገልጽ አጽናኝ ተስፋ ለሰው ዘሮች ሰጥቷል። የይሖዋ ዓላማ ይህ ዘር ወይም መሲሕ ከእስራኤል ብሔር እንዲወለድ ነበር። ከዚያ በኋላ በነበሩት ዘመናትም አምላክ፣ ዕብራውያን ጸሐፊዎች በመንፈሱ ተነሳስተው በርካታ ትንቢቶችን በጽሑፍ እንዲያሰፍሩ ያደረገ ሲሆን እነዚህ ትንቢቶችም ይህ ዘር የአምላክ መንግሥት ገዥ እንደሚሆንና በይሖዋ ስም ላይ የተከመረውን ነቀፋ በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማስወገድ የአምላክን ስም እንደሚያስቀድስ ጠቁመዋል። እነዚህ ነቢያት የይሖዋን ሉዓላዊነት ስለሚያረጋግጠውና ሰዎችን ከፍርሃት፣ ከጭቆና፣ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ስለሚያወጣው ስለዚህ ዘር በርካታ ዝርዝር ሐሳቦችን አስፍረዋል። የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ተጽፈው መጠናቀቃቸው አይሁዳውያን በመሲሑ ላይ ያላቸው ተስፋ የጸና እንዲሆን አድርጓል።
2 ይህ በእንዲህ እንዳለ በዓለም ላይ ያለው ሁኔታም በመለወጥ ላይ ነበር። አምላክ ለመሲሑ መምጣት አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር በብሔራት የተጠቀመ ሲሆን ይህንን ዜና በስፋት ለማዳረስ ነገሮች ተመቻችተው ነበር። አምስተኛ የዓለም ኃያል መንግሥት የነበረችው ግሪክ በወቅቱ በብሔራት መካከል የጋራ መግባቢያ ሆኖ የሚያገለግል ቋንቋ እንዲኖር አድርጋለች። ስድስተኛዋ የዓለም ኃያል መንግሥት የሆነችው ሮም ደግሞ በሥሯ ያሉትን ብሔራት አንድ የሚያደርግ ዓለም አቀፋዊ ግዛት የመሠረተች ሲሆን ወደ ሁሉም የግዛቷ ክፍሎች በቀላሉ ለመድረስ የሚያስችሉ ጎዳናዎችን ሠርታ ነበር። ብዙ አይሁዳውያን በሮም ግዛት በሙሉ ተበታትነው ስለነበር አይሁዳውያን መሲሕ እንደሚመጣ ይጠባበቁ እንደነበር ሌሎች ሕዝቦችም ያውቁ ነበር። በኤደን ተስፋ ከተሰጠ ከ4,000 ዓመታት በኋላ መሲሑ ተገለጠ! ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው ተስፋ የተደረገበት ዘር መጣ! መሲሑ በዚህች ምድር ላይ የአባቱን ፈቃድ በታማኝነት ባከናወነበት በዚህ ወቅት እስከዚያ ጊዜ ድረስ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከታዩት ሁሉ የላቀ ግምት የሚሰጣቸው ነገሮች ተከስተዋል።
3 በዚህም የተነሳ እነዚህን አስደናቂ ክስተቶች በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት በጽሑፍ የሚያሰፍሩ ሰዎች አስፈለጉ። የይሖዋ መንፈስ አራት ታማኝ ወንዶች፣ ራሳቸውን የቻሉ አራት ዘገባዎችን እንዲጽፉ ያነሳሳቸው ሲሆን እነዚህ ዘገባዎችም ኢየሱስ፣ መሲሕ እንዲሁም ተስፋ የተደረገበት ዘርና ንጉሥ መሆኑን ከአራት አቅጣጫ መሥክረዋል፤ ከዚህም በላይ እነዚህ ሰዎች ስለ ሕይወቱ፣ ስለ አገልግሎቱ እንዲሁም ስለ ሞቱና ትንሣኤው በዝርዝር ጽፈዋል። እነዚህ የታሪክ ዘገባዎች ወንጌሎች ተብለው የሚጠሩ ሲሆን “ወንጌል” የሚለው ቃል “ምሥራች” የሚል ትርጉም አለው። አራቱ የወንጌል ዘገባዎች ተመሳሳይና ብዙውን ጊዜም አንድ ዓይነት ገጠመኞችን የሚተርኩ ቢሆኑም አንዳቸው የሌላው ግልባጭ ግን አይደሉም። የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ ወንጌሎች የኢየሱስን ምድራዊ ሕይወት በተመሳሳይ መንገድ የሚተርኩ በመሆናቸው ሲኖፕቲከ ማለትም “በተመሳሳይ አቅጣጫ ያተኮሩ” ተብለው ይጠራሉ። ይሁን እንጂ አራቱም ጸሐፊዎች ማለትም ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ በየራሳቸው መንገድ ተርከዋል። እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ጭብጥና ለመጻፍ የተነሡበት ዓላማ የነበራቸው ከመሆኑም በላይ በጽሑፎቻቸው ውስጥ የግል ባሕርያቸው ተንጸባርቋል፤ በተጨማሪም ያሰፈሩት ዘገባ በወቅቱ የነበሩትን አንባቢዎቻቸውን ግምት ውስጥ ያስገባ ነው። እነዚህን መጻሕፍት ይበልጥ በመረመርን መጠን የእያንዳንዱን መጽሐፍ ለየት ያለ ገጽታ ይበልጥ እንገነዘባለን፤ ከዚህም በላይ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት እነዚህ አራት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት የያዟቸው ዘገባዎች ራሳቸውን የቻሉ፣ እርስ በርስ የሚደጋገፉና ስምምነት ያላቸው ናቸው።
4 ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች መጀመሪያ በጽሑፍ ያሰፈረው ማቴዎስ ነበር። ማቴዎስ “የይሖዋ ስጦታ” የሚል ትርጉም ያለው “ማቲታያህ” የሚለው የዕብራይስጥ ስም አጭር አጠራር ሳይሆን አይቀርም። ማቴዎስ ኢየሱስ ከመረጣቸው 12 ሐዋርያት መካከል አንዱ ነበር። ጌታ ስለ አምላክ መንግሥት እየሰበከና እያስተማረ በፓለስቲና ምድር በተዘዋወረበት ጊዜ ሁሉ ማቴዎስ ከእሱ ጋር የቀረበና ጥብቅ ግንኙነት ነበረው። ማቴዎስ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ከመሆኑ በፊት ቀረጥ ሰብሳቢ የነበረ ሲሆን ይህ ሥራ አይሁዳውያኑ በሮም ንጉሠ ነገሥት ግዛት ሥር እንደሆኑና ነፃነት እንደሌላቸው ስለሚያስታውሳቸው በጣም የተጠላ ነበር። የእልፍዮስ ልጅ የሆነው ማቴዎስ ሌዊ ተብሎም ይጠራል። ማቴዎስ፣ ኢየሱስ እንዲከተለው ሲጋብዘው ምንም ሳያመነታ ተከትሎታል።— ማቴ. 9:9፤ ማር. 2:14፤ ሉቃስ 5:27-32
5 በማቴዎስ ስም የሚጠራውን ወንጌል የጻፈው ማቴዎስ መሆኑ በመጽሐፉ ውስጥ ባይጠቀስም የጥንቶቹ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች የመጽሐፉ ጸሐፊ እሱ እንደሆነ የሚያረጋግጥ የማያሻማ ምሥክርነት ሰጥተዋል። እንዲያውም የማቴዎስን መጽሐፍ ያህል ስለ ጸሐፊው ማንነት ጥያቄ ያልተነሳበትና በማያሻማ መንገድ የተረጋገጠለት ሌላ የጥንት መጽሐፍ መኖሩ ያጠራጥራል። የሃይራፖሊስ ከተማ ነዋሪ ከሆነው ከፓፒየስ ዘመን (ሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ መጀመሪያ) አንስቶ፣ የዚህ ወንጌል ጸሐፊ ማቴዎስ እንደሆነና መጽሐፉም ትክክለኛ መሆኑን የሚያረጋግጡ በርካታ የጥንት ምሥክሮች እናገኛለን። የማክሊንቶክና ስትሮንግ ሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “ሰማዕቱ ጀስቲን፣ ለዲዮግኒተስ የተላከው ደብዳቤ ጸሐፊ (ሰማዕቱ ጀስቲን የተባለውን የኦቶ መጽሐፍ ጥራዝ 2 ተመልከት)፣ ሄጄሲፐስ፣ ኢራንየስ፣ ታቲያን፣ አቴናጎራስ፣ ቴዎፍሎስ፣ ክሌመንት፣ ተርቱሊያንና ኦሪጀን ከማቴዎስ መጽሐፍ ጠቅሰዋል። በእጃችን ያለው መጽሐፍ አንዳችም ለውጥ እንዳልተደረገበት እርግጠኞች የምንሆነው፣ እነዚህ ሰዎች ከመጽሐፉ ስለጠቀሱ ብቻ ሳይሆን ይህንን ያደረጉበትን መንገድ በመመልከትም ጭምር ነው። በመጽሐፉ ውስጥ ያለውን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ እምነት እንደሚጣልበት አድርገው በመቀበላቸው ማስረጃ ለማቅረብ ጥረት አላደረጉም፤ ከዚህም በላይ እንደሚጠራጠሩት የሚጠቁም ምንም ፍንጭ የለም።”a ማቴዎስ ሐዋርያ ከመሆኑም በላይ የአምላክ መንፈስ የነበረው ሰው መሆኑ እሱ የጻፈው ነገር የታመነ ዘገባ እንደሚሆን ማረጋገጫ ይሆነናል።
6 ማቴዎስ ዘገባውን የጻፈው በፓለስቲና ሆኖ ነው። ወንጌሉ የተጻፈበት ትክክለኛ ዓመት ባይታወቅም በአንዳንድ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች መጨረሻ ላይ የሰፈሩት መግለጫዎች (ሁሉም ከአሥረኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተዘጋጁ ናቸው) የማቴዎስ ወንጌል በ41 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደተጻፈ ይገልጻሉ። ማቴዎስ፣ ወንጌሉን በመጀመሪያ የጻፈው ቀላል በሆነ የዕብራይስጥ ቋንቋ እንደነበረና በኋላ ወደ ግሪክኛ እንደተረጎመው የሚጠቁሙ ማስረጃዎች አሉ። ጄሮም ዴ ቪሪስ ኢላስተሪበስ በተባለው የጽሑፍ ሥራው ሦስተኛ ምዕራፍ ላይ እንዲህ ብሏል:- “ሌዊ በመባል የሚታወቀውና ከቀረጥ ሰብሳቢነት ወደ ሐዋርያነት የተለወጠው ማቴዎስ፣ በይሁዳ ሆኖ የክርስቶስን ወንጌል በዕብራይስጥ ቋንቋና ፊደል በመጀመሪያ የጻፈው ላመኑት የተገረዙ ሰዎች ነበር።”b ጄሮም አክሎም የዚህ መጽሐፍ የዕብራይስጥ ቅጂ በእሱም ዘመን (በአራተኛውና በአምስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ) ፓምፊለስ በቂሣርያ ባደራጀው ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ይገኝ እንደነበር ገልጿል።
7 ኦሪጀን በሦስተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ስለ ወንጌሎች ሲናገር እንደሚከተለው ብሎ እንደነበር ዩሲቢየስ ጽፏል:- “በመጀመሪያ የተጻፈው . . . የማቴዎስ ወንጌል ሲሆን . . . ማቴዎስ ከአይሁድ እምነት ወደ ክርስትና ለተለወጡት ሰዎች ሲል መጽሐፉን ያዘጋጀው በዕብራይስጥ ቋንቋ ነው።”c ማቴዎስ፣ ከአብርሃም አንስቶ የኢየሱስን ሕጋዊ የዘር ሐረግ መዘርዘሩ እንዲሁም ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በተደጋጋሚ በመጥቀስ እነዚህ መጻሕፍት ስለ መሲሑ መምጣት እንደተናገሩ ማሳየቱ መጽሐፉን በዋነኝነት የጻፈው ለአይሁዳውያን እንደነበር ይጠቁማል። ማቴዎስ የአምላክን ስም ከያዙ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ሲጠቅስ ይሖዋ የሚለውን መለኮታዊ ስም ለመጻፍ ቴትራግራማተን በመባል የሚታወቁትን ፊደላት ተጠቅሟል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው። በ19ኛው መቶ ዘመን በመጀመሪያ በኤፍ ዴሊሽ እንደተዘጋጀው የማቴዎስ መጽሐፍ የዕብራይስጥ ትርጉም ሁሉ የአዲስ ዓለም ትርጉምም በማቴዎስ መጽሐፍ ውስጥ የይሖዋን ስም 18 ጊዜ የሚጠቀመው ለዚህ ነው። ማቴዎስ መለኮታዊውን ስም በሚመለከት የኢየሱስ ዓይነት አመለካከት ስለነበረው በዚህ ስም መጠቀምን በተመለከተ በጊዜው ሰፍኖ የነበረው የአይሁዳውያን አጉል እምነት ተጽዕኖ አላሳደረበትም።— ማቴ. 6:9፤ ዮሐ. 17:6, 26 የ1954 ትርጉም
8 ማቴዎስ ቀረጥ ሰብሳቢ ስለነበረ ገንዘብን፣ አኃዞችንና ዋጋዎችን በተመለከተ ግልጽ የሆነ ማብራሪያ መስጠቱ የሚያስገርም አይደለም። (ማቴ. 17:27፤ 26:15፤ 27:3) ቀረጥ ሰብሳቢ እንደመሆኑ መጠን የተናቀ የነበረው ማቴዎስ የወንጌሉ አገልጋይ እንዲሁም የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ የመሆን መብት በማግኘቱ የአምላክን ምሕረት ከልቡ ያደንቅ ነበር። በመሆኑም መሥዋዕት ብቻ ሳይሆን ምሕረትም እንደሚያስፈልግ ኢየሱስ በተደጋጋሚ መግለጹን ከወንጌል ጸሐፊዎች ሁሉ የጠቀሰው ማቴዎስ ብቻ ነው። (9:9-13፤ 12:7፤ 18:21-35) ማቴዎስ በይሖዋ ጸጋ በእጅጉ በመበረታታቱ ኢየሱስ ከተናገራቸው በጣም የሚያጽናኑ ቃላት መካከል አንዳንዶቹን መዝግቦልናል:- “እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና።” (11:28-30) ከአገሩ ሰዎች ከስድብ በቀር ሌላ ነገር አግኝቶ ለማያውቀው ለዚህ የቀድሞ ቀረጥ ሰብሳቢ ይህ ደግነት ያዘለ ንግግር እንዴት የሚያጽናና ነበር!
9 ማቴዎስ የኢየሱስ ትምህርት ጭብጥ “የእግዚአብሔር መንግሥት” መሆኑን ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። (4:17) ኢየሱስን፣ ሰባኪ ንጉሥ እንደሆነ አድርጎ ተመልክቶታል። ይህ ሐዋርያ “መንግሥት” የሚለውን ቃል ደጋግሞ (ከ50 ጊዜ በላይ) ከመጠቀሙ የተነሣ እሱ የጻፈው ወንጌል፣ የመንግሥት ወንጌል ተብሎ ሊጠራ ይችላል። ማቴዎስ ይበልጥ ትኩረት ያደረገው ኢየሱስ ለሕዝብ ያቀረባቸውን ንግግሮችና ስብከቶች በትክክል አቀናብሮ በማቅረቡ እንጂ የጊዜ ቅደም ተከተሉን በመጠበቁ ላይ አልነበረም። ማቴዎስ፣ በመጀመሪያዎቹ 18 ምዕራፎች ውስጥ ጎላ አድርጎ የገለጸው ስለ አምላክ መንግሥት ስለነበር እነዚህን ክፍሎች በጊዜ ቅደም ተከተላቸው መሠረት አላስቀመጣቸውም። የመጨረሻዎቹ አሥር ምዕራፎች ግን (19 እስከ 28) የመንግሥቱን መልእክት ማጉላታቸው ባይቀርም በአጠቃላይ ሲታዩ ቅደም ተከተላቸውን የጠበቁ ናቸው።
10 አርባ ሁለት በመቶ የሚሆነው የማቴዎስ ወንጌል ዘገባ በሌሎቹ ሦስት ወንጌሎች ውስጥ አይገኝም።d በሌሎች ወንጌሎች ውስጥ የማይገኘው ክፍል ቢያንስ አሥር ምሳሌዎችን ያካተተ ሲሆን እነሱም:- በእርሻው መካከል የተዘራው እንክርዳድ (13:24-30)፣ የተደበቀው ሀብት (13:44)፣ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነው ዕንቁ (13:45, 46)፣ የመረቡ (13:47-50)፣ ይቅር ያላለው አገልጋይ (18:23-35)፣ የሠራተኞቹና የዲናሩ (20:1-16)፣ የአባትና የሁለት ልጆቹ (21:28-32)፣ የንጉሡ ልጅ ሠርግ (22:1-14)፣ የአሥሩ ልጃገረዶች (25:1-13) እንዲሁም የታላንቱ (25:14-30) ምሳሌዎች ናቸው። መጽሐፉ ኢየሱስ ከተወለደበት ከ2 ከክርስቶስ ልደት በፊት አንስቶ ወደ ሰማይ ከማረጉ ጥቂት ቀደም ብሎ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እስከተገናኘበት እስከ 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ድረስ ያለውን ዘገባ ይተርካል።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
29 ከአራቱ ወንጌሎች የመጀመሪያ የሆነው የማቴዎስ መጽሐፍ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ወደ ክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት የሚያሸጋግር ግሩም ድልድይ ነው። መሲሕና አምላክ ቃል የገባው መንግሥት ንጉሥ ማን እንደሆነ፣ የእሱ ተከታዮች ለመሆን ምን ብቃቶችን ማሟላት እንደሚያስፈልግና በምድር ላይ የሚኖሩት ተከታዮቹ ምን ሥራ እንደሚጠብቃቸው ምንም በማያሻማ መንገድ ገልጿል። በመጀመሪያ አጥማቂው ዮሐንስ፣ ከዚያም ኢየሱስ በመጨረሻም ደቀ መዛሙርቱ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች” እያሉ ሰብከዋል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት የሰጠው ትእዛዝ እስከዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ድረስ የሚዘልቅ ነው። በእውነትም፣ ጌታችን የተወውን ምሳሌ በመከተል ‘ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት ማድረግን’ ጨምሮ ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩ ሥራ መካፈል በዚያን ጊዜም ሆነ ዛሬ ታላቅና አስደናቂ መብት ነው።— 3:2፤ 4:17፤ 10:7፤ 24:14፤ 28:19
30 በእርግጥም የማቴዎስ ወንጌል “ምሥራች” ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ፣ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የማቴዎስን መልእክት ሰምተው ተግባራዊ ላደረጉት ሰዎች “ምሥራች” ሆኖላቸው ነበር፤ ይሖዋ አምላክ እስከ ዛሬም ድረስ ይህ መልእክት “ምሥራች” ሆኖ እንዲቆይ አድርጓል። ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች እንኳ ይህ ወንጌል ያለውን ኃይል አምነው ለመቀበል ተገደዋል፤ ለምሳሌ ያህል የሂንዱ እምነት መሪ የሆኑት ሞሃንደስ (ማሃትማ) ጋንዲ እንዲህ ብለዋል፦ “እንደምንም ብላችሁ በተራራው ስብከት ከፈሰሰላችሁ ውኃ በደንብ ጠጡ፤ . . . በተራራው ስብከት ላይ የተሰጠው ትምህርት ለእያንዳንዳችን የሚያስፈልግ ነው።”e
31 ይሁን እንጂ ክርስቲያን ነን የሚሉትን ወገኖች ጨምሮ የመላው ዓለም ችግር አልተፈታም። የተራራ ስብከቱንም ሆነ ማቴዎስ በጻፈው ወንጌል ውስጥ የሚገኙትን ሌሎች ግሩም ምክሮች በሙሉ እንደ ውድ ሀብት አድርገው የሚመለከቱት፣ የሚያጠኑትና በሥራ ላይ የሚያውሉት ጥቂት ቁጥር ያላቸው እውነተኛ ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው፤ እነዚህ ሰዎች እንዲህ በማድረጋቸው ይህ ነው የማይባል ጥቅም አግኝተዋል። ኢየሱስ እውነተኛ ደስታ ስለ ማግኘት እንዲሁም ስለ ሥነ ምግባርና ጋብቻ፣ ፍቅር ስላለው ኃይል፣ ተቀባይነት ስላለው ጸሎት፣ በመንፈሳዊና በቁሳዊ ሀብት መካከል ስላለው ልዩነት፣ የአምላክን መንግሥት ስለ ማስቀደም፣ ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች አክብሮት ስለማሳየት እንዲሁም ንቁና ታዛዥ ስለመሆን የሰጣቸውን ግሩም ማሳሰቢያዎች ደግሞ ደጋግሞ ማጥናት በጣም ጠቃሚ ነው። ማቴዎስ ምዕራፍ 10 ኢየሱስ ስለ “መንግሥተ ሰማይ” ምሥራች በመስበኩ ሥራ ለተሠማሩት ሰዎች የሰጠውን የአገልግሎት መመሪያ ይዟል። ኢየሱስ የተናገራቸው በርካታ ምሳሌዎች ‘ሰሚ ጆሮ ላለው’ ሁሉ በጣም አስፈላጊ ትምህርት ይዘዋል። ከዚህም በተጨማሪ ‘ለመምጣቱ ምልክት’ የሚሆኑ ነገሮችን በተመለከተ የተናገረውን ትንቢት የመሳሰሉት የኢየሱስ ትንቢቶች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ጠንካራ ተስፋና ሙሉ እምነት እንዲኖረን ያደርጋሉ።— 5:1 እስከ 7:29፤ 10:5-42፤ 13:1-58፤ 18:1 እስከ 20:16፤ 21:28 እስከ 22:40፤ 24:3 እስከ 25:46
32 የማቴዎስ ወንጌል ፍጻሜያቸውን ባገኙ ትንቢቶች የተሞላ ነው። በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የጠቀሳቸው ብዙዎቹ ሐሳቦች፣ ትንቢቶቹ ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸውን ለማሳየት የገቡ ናቸው። በትንቢቶቹ ላይ ፍጻሜያቸውን ያገኙትን ዝርዝር ሁኔታዎች በሙሉ አስቀድሞ ማዘጋጀት ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር በመሆኑ ትንቢቶቹ መፈጸማቸው ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ማቴዎስ 13:14, 15ን ከኢሳይያስ 6:9, 10፤ ማቴዎስ 21:42ን ከመዝሙር 118:22, 23 እንዲሁም ማቴዎስ 26:31, 56ን ከዘካርያስ 13:7 ጋር አወዳድር። እንደነዚህ ያሉት ትንቢቶች መፈጸማቸው ማቴዎስ የመዘገባቸው የኢየሱስ ትንቢቶች በሙሉ ይሖዋ ‘መንግሥተ ሰማያትን’ በተመለከተ ያለው ክብራማ ዓላማ እውን ሲሆን ጊዜያቸውን ጠብቀው እንደሚፈጸሙ ጠንካራ ማረጋገጫ ይሆንልናል።
33 አምላክ፣ የመንግሥቱ ንጉሥ በምድር ላይ ስለሚኖረው ሕይወት አስቀድሞ የተናገራቸው ጥቃቅን ዝርዝሮች እንኳ ሳይቀሩ በትክክል ተፈጽመዋል! በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈው ማቴዎስም የእነዚህን ትንቢቶች ፍጻሜ በታማኝነት መዝግቧል! ጽድቅ ወዳድ የሆኑ ሰዎች፣ በማቴዎስ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግበው ስለሚገኙት አስቀድመው የተነገሩ ትንቢቶች ፍጻሜዎችና ተስፋዎች ሲያስቡ ይሖዋ ስሙን ስለሚያስቀድስበት “መንግሥተ ሰማያት” በሚያገኙት እውቀትና ተስፋ እጅግ ደስ ይላቸዋል። “በሚመጣው አዲስ ዓለም የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን ላይ በሚቀመጥበት ጊዜ” የዋህ ለሆኑና በመንፈሳዊ ለተራቡ ሰዎች ሥፍር ቁጥር የሌላቸው በረከቶችን የሚያፈስላቸው እንዲሁም ደስታ የሞላበት ሕይወት የሚያጎናጽፋቸው ይህ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራ መንግሥት ነው። (ማቴ. 19:28) ይህ ሁሉ ሐሳብ የሚገኘው አበረታች በሆነው “የማቴዎስ ወንጌል” ውስጥ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በ1981 እንደገና የታተመው ጥራዝ 5 ገጽ 895
b በኢ ሲ ሪቻርድሰን ተዘጋጅቶ “ቴክስቴ ኧንድ አንተርሹንገን ዙር ጌሰሽቺቴ ደር ኦልትክሪስትሊቸን ሊተራቸር” በሚል ርዕስ በተከታታይ ከታተመው የላቲን ጽሑፍ የተተረጎመ፣ ላይፕዚግ 1896 ጥራዝ 14 ገጽ 8, 9
c ዚ ኤክለሲያስቲካል ሂስትሪ፣ VI, xxv, 3-6
d ኢንትሮዳክሽን ቱ ዘ ስተዲ ኦቭ ዘ ጎስፕልስ፣ 1896፣ ቢ ኤፍ ዌስትኮት ገጽ 201
e በሲ ኤፍ አንድሪውስ የተዘጋጀው ማሃትማ ጋንዲስ አይዲያስ 1930 ገጽ 96