የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 47—2 ቆሮንቶስ
ጸሐፊው:- ጳውሎስ
የተጻፈበት ቦታ:- መቄዶንያ
ተጽፎ ያለቀው:- በ55 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
ጊዜው 55 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ የበጋው ወራት ማብቂያ ወይም የመከር መግቢያ ላይ ሳይሆን አይቀርም። አሁንም በቆሮንቶስ በሚገኘው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስን የሚያሳስቡት አንዳንድ ጉዳዮች ነበሩ። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የመጀመሪያውን ደብዳቤ የጻፈው ከጥቂት ወራት በፊት ነበር። ከዚያ በኋላ፣ ቲቶ በይሁዳ ለሚኖሩ ቅዱሳን መዋጮ የማሰባሰቡን ሥራ ለማገዝና ምናልባትም የቆሮንቶስ ሰዎች ለመጀመሪያው ደብዳቤ የሰጡትን ምላሽ ለመመልከት ሳይሆን አይቀርም ወደ ቆሮንቶስ ተልኳል። (2 ቆሮ. 8:1-6፤ 2:13) በቆሮንቶስ የሚኖሩት ክርስቲያኖች ምን ምላሽ ሰጥተው ነበር? ጳውሎስ ደብዳቤው እንዲጸጸቱና ንስሐ እንዲገቡ እንደገፋፋቸው ሲሰማ ምንኛ ተጽናንቶ ይሆን! ቲቶ በመቄዶንያ ወዳለው ወደ ጳውሎስ ይህን የመሰለ አስደሳች ሪፖርት ይዞ ሲመለስ የሐዋርያው ልብ በቆሮንቶስ ለነበሩት የተወደዱ የእምነት አጋሮቹ ባለው ፍቅር መሞላቱ አይቀርም።—7:5-7፤ 6:11
2 ስለሆነም ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ዳግመኛ ደብዳቤ ጻፈላቸው። ይህ ልብ የሚነካና ጠንካራ መልእክት ያዘለ ደብዳቤ የተጻፈው በመቄዶንያ ሲሆን ደብዳቤውንም ያደረሰው ቲቶ ሳይሆን አይቀርም። (9:2, 4፤ 8:16-18, 22-24) ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ እንዲጽፍ ካነሳሱት አሳሳቢ ነገሮች መካከል አንዱ በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መካከል “ታላላቅ ሐዋርያት” የመገኘታቸው ጉዳይ ነበር። ጳውሎስ እነዚህን ሰዎች “ሐሰተኞች ሐዋርያትና አታላዮች ሠራተኞች” ሲል ጠርቷቸዋል። (11:5, 13, 14) በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አዲስ የሆነው የዚህ ጉባኤ መንፈሳዊ ደህንነት በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኝ የነበረ ሲሆን በጳውሎስ የሐዋርያነት ሥልጣን ላይም ጥያቄ ተነስቶ ነበር። በመሆኑም ለቆሮንቶስ ሰዎች ሁለተኛ ደብዳቤ መጻፉ እጅግ አስፈላጊ ነበር።
3 ጳውሎስ “ወደ እናንተ ለመምጣት ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛዬ ነው” እንዳለ ልብ ማለት ይገባል። (2 ቆሮ. 12:14፤ 13:1) ጳውሎስ የመጀመሪያውን ደብዳቤ ሲጽፍላቸው “ለሁለተኛ ጊዜ” ሊጎበኛቸው አቅዶ የነበረ ቢሆንም ይህ ሳይሳካለት ቀርቷል። (1 ቆሮ. 16:5፤ 2 ቆሮ. 1:15 NW) እርግጥ ጳውሎስ ከዚህ በፊት ወደ ቆሮንቶስ የሄደው አንዴ ብቻ ነበር፤ ይህም ከ50-52 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የቆሮንቶስ ጉባኤ ሲመሠረት ሲሆን በዚያም ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ቆይቷል። (ሥራ 18:1-18) ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ ቆሮንቶስን በድጋሚ ለመጎብኘት የነበረው ምኞት ተሳክቶለታል። በ56 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ በግሪክ በቆየባቸው ሦስት ወራት ቢያንስ የተወሰነውን ጊዜ ያሳለፈው በቆሮንቶስ ሲሆን ለሮሜ ሰዎች ደብዳቤ የጻፈላቸውም በዚያ ሳለ ነው።—ሮሜ 16:1, 23፤ 1 ቆሮ. 1:14
4 ሁለተኛ ቆሮንቶስ እንደ አንደኛ ቆሮንቶስና እንደ ሌሎቹ የሐዋርያው መልእክቶች ትክክለኛ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ተደርጎ ሲታይ ቆይቷል። አሁንም በቆሮንቶስ የነበረውን ጉባኤ ሁኔታ መመልከትና ጳውሎስ እነሱንም ሆነ እኛን ለመምከር ሲል በመንፈስ አነሳሽነት ከጻፋቸው ቃላት ጥቅም ማግኘት እንችላለን።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
18 በሁለተኛ ቆሮንቶስ ውስጥ ተገልጾ የምናገኘው ጳውሎስ ለክርስቲያናዊ አገልግሎት የነበረው አድናቆት እጅግ የሚያነቃቃና የሚያበረታታ ነው! እኛም ጳውሎስ ለአገልግሎቱ የነበረው ዓይነት አመለካከት ይኑረን። በአምላክ ፊት የተሟላ ብቃት ያለው አንድ ክርስቲያን ቃሉን አይሸቃቅጥም፤ ከዚህ ይልቅ በቅንነት ያገለግላል። ብቃት ያለው የአምላክ አገልጋይ መሆኑን የሚያረጋግጥለት አንድ የተጻፈ ሰነድ ሳይሆን በአገልግሎቱ የሚያፈራው ፍሬ ነው። የሚያከናውነው አገልግሎት ታላቅ ክብር ያለው መሆኑ ባይካድም ይህ ግን እንዲታበይ አያደርገውም። የአምላክ አገልጋዮች ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች እንደመሆናቸው መጠን ይህ የከበረ አገልግሎት በተሰባሪ የሸክላ ዕቃ ውስጥ አላቸው። ይህም የሆነው ያገኙት ኃይል ከአምላክ እንደሆነ በግልጽ እንዲታይ ነው። ስለዚህ የአምላክ አገልጋዮች የመሆንን ታላቅ መብት መቀበል ትሕትናን ይጠይቃል። እንዲሁም “የክርስቶስ እንደራሴዎች” ወይም አምባሳደሮች ሆነን ለማገልገል መቻላችን የአምላክ ጸጋ ታላቅ መግለጫ ነው! ጳውሎስ “[የአምላክን] ጸጋ ከንቱ እንዳታደርጉ” ሲል ማሳሰቢያ መስጠቱ ምንኛ ተገቢ ነው!—2:14-17፤ 3:1-5፤ 4:7፤ 5:18-20፤ 6:1
19 ጳውሎስ ክርስቲያን አገልጋዮች ሊኮርጁት የሚገባ ግሩም ምሳሌ መተዉ ምንም አያጠያይቅም። በመጀመሪያ ደረጃ ጳውሎስ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በተደጋጋሚ ጠቅሶ በመናገር፣ በተዘዋዋሪ በማውሳት እንዲሁም ተግባራዊ የሚሆኑበትን መንገድ በማብራራት እነዚህን መጻሕፍት ከፍ አድርጎ ይመለከታቸውና ያጠናቸው እንደነበር አሳይቷል። (2 ቆሮ. 6:2, 16-18፤ 7:1፤ 8:15፤ 9:9፤ 13:1፤ ኢሳ. 49:8፤ ዘሌ. 26:12፤ ኢሳ. 52:11፤ ሕዝ. 20:41፤ 2 ሳሙ. 7:14፤ ሆሴዕ 1:10) ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ የበላይ ተመልካች እንደመሆኑ መጠን ለመንጋው በጥልቅ እንደሚያስብ ሲያሳይ “እኔ ግን ስለ እናንተ ያለኝን ሁሉ ራሴንም ጭምር ብሰጥ ደስ ይለኛል” ብሏል። ዘገባው በግልጽ እንደሚያሳየው ራሱን ሙሉ በሙሉ ለወንድሞቹ ሰጥቷል። (2 ቆሮ. 12:15፤ 6:3-10) የቆሮንቶስ ጉባኤን ለማስተማር፣ ለመምከርና ነገሮችን ለማቅናት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ጥሯል። “ከማያምኑ ሰዎች ጋር አግባብ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ” በማለት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ከጨለማ ጋር እንዳይወዳጁ በግልጽ አስጠንቅቋቸዋል። ጳውሎስ ለእነዚህ ክርስቲያኖች ካለው ፍቅራዊ አሳቢነት የተነሳ “እባብ ሔዋንን በተንኰል እንዳሳታት” ሁሉ የእነሱም አእምሮ እንዲበላሽ አልፈለገም። በመሆኑም “በእምነት መሆናችሁን ለማወቅ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ” በማለት ልባዊ ምክር ሰጥቷቸዋል። ክርስቲያናዊ ለጋስነት እንዲያሳዩ ሲያበረታታቸው “[አምላክ] በደስታ የሚሰጠውን ሰው ይወዳል” ብሏቸዋል። ከዚህም ባሻገር እሱ ራሱ በአድናቆት ተሞልቶ በቃላት ሊገለጽ ስለማይቻል ስጦታው አምላክን አመስግኖታል። በቆሮንቶስ የሚገኙ ወንድሞቹ በጳውሎስ የልብ ጽላት ላይ ተጽፈው የነበሩ ሲሆን እነሱን ለመጥቀም ሲል ራሱን ሳይቆጥብ ማገልገሉ ቀናተኛና ንቁ የበላይ ተመልካች መሆኑን የሚያሳይ ነበር። ጳውሎስ ዛሬ ለምንገኘው እንዴት ያለ ግሩም አርዓያ ነው!—6:14፤ 11:3፤ 13:5፤ 9:7, 15፤ 3:2
20 ሐዋርያው ጳውሎስ ፈተና ሲደርስብን እውነተኛ የብርታት ምንጭ የሚሆነን “የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” መሆኑን በመግለጽ አእምሯችን በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ እንዲያተኩር አድርጓል። አምላክ ደኅንነታችን ተጠብቆ ወዳዘጋጀልን አዲስ ዓለም እንድንገባ “በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።” በተጨማሪም ጳውሎስ ‘በሰማይ ስለሚገኘውና በሰው እጅ የተሠራ ሳይሆን ከአምላክ ስለሆነው ዘላለማዊ ቤት’ የሚገልጸውን ታላቅ ተስፋ ከተናገረ በኋላ “ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፣ አዲስ ሆኖአል” ብሏል። ሁለተኛ ቆሮንቶስ እንደ ጳውሎስ ሰማያዊውን መንግሥት የመውረስ ተስፋ ላላቸው ሰዎች በእርግጥም አስደናቂ ማረጋገጫ ይዟል።—1:3, 4፤ 5:1, 17