ምዕራፍ 5
ንጉሡ ስለ መንግሥቱ የሚገልጽ ብርሃን እንዲፈነጥቅ አደረገ
1, 2. ኢየሱስ ከማንም በላይ ጠቢብ አስጎብኚ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
አንድ ልምድ ያለው አስጎብኚ፣ አስደናቂና ውብ የሆነች ከተማ እያስጎበኘህ ነው እንበል። አንተም ሆንክ አብረውህ ያሉት ሰዎች ከተማዋን ስለማታውቋት አስጎብኚው የሚናገረውን እያንዳንዱን ቃል በትኩረት ታዳምጣላችሁ። በጉብኝታችሁ ወቅት ያላያችኋቸውን የከተማዋን አንዳንድ ገጽታዎች በተመለከተ በየመሃሉ አስጎብኚያችሁን ትጠይቁታላችሁ። እሱ ግን ትክክለኛው ጊዜ እስከሚመጣ ምናልባትም የጠየቃችሁን ነገር ማየት የምትችሉበት ቦታ ላይ እስከምትደርሱ ድረስ ማብራሪያ አይሰጣችሁም። በኋላ ግን፣ አስጎብኚያችሁ አስተዋይ እንደሆነ ትገነዘባላችሁ፤ ምክንያቱም ማወቅ የሚያስፈልጋችሁን ነገር የሚነግራችሁ ልክ በትክክለኛው ጊዜ ላይ ነው።
2 እውነተኛ ክርስቲያኖች ያሉበት ሁኔታ ከአገር ጎብኚዎች ጋር ይመሳሰላል። እኛም ከሁሉ በላይ አስደናቂ ስለሆነች አንዲት ከተማ ይኸውም ‘እውነተኛ መሠረት ስላላት ከተማ’ እየተማርን ነው፤ ይህች ከተማ የአምላክን መንግሥት ታመለክታለች። (ዕብ. 11:10) ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ለተከታዮቹ ይህችን ከተማ በማስጎብኘት ስለመንግሥቱ ጥልቀት ያለው እውቀት እንዲያገኙ ረድቷቸው ነበር። ታዲያ ኢየሱስ፣ የተከታዮቹን ጥያቄዎች በሙሉ መልሶላቸዋል? ስለ መንግሥቱስ ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ነግሯቸዋል? እንዲህ አላደረገም። እንዲያውም “ገና ብዙ የምነግራችሁ ነገር አለኝ፤ አሁን ግን ልትሸከሙት አትችሉም” ብሏል። (ዮሐ. 16:12) ከማንም በላይ ጠቢብ አስጎብኚ የሆነው ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ በወቅቱ ሊረዱት ከሚችሉት በላይ ብዙ መረጃ አላዥጎደጎደባቸውም።
3, 4. (ሀ) ኢየሱስ፣ ታማኝ ተከታዮቹን ስለ አምላክ መንግሥት ማስተማሩን የቀጠለው እንዴት ነው? (ለ) በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የትኞቹን ነጥቦች እንመረምራለን?
3 ኢየሱስ በዮሐንስ 16:12 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ የተናገረው በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ነው። ታዲያ ከሞተ በኋላ ታማኝ ተከታዮቹን ስለ አምላክ መንግሥት ማስተማሩን የሚቀጥለው እንዴት ነው? ለሐዋርያቱ “የእውነት መንፈስ . . . ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷቸው ነበር።a (ዮሐ. 16:13) መንፈስ ቅዱስን እንደ አንድ ትዕግሥተኛ አስጎብኚ ልንቆጥረው እንችላለን። ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ስለ አምላክ መንግሥት ማወቅ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ ማወቅ በሚገባቸው ትክክለኛ ጊዜ ለማስተማር በመንፈስ ቅዱስ ይጠቀማል።
4 የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች ስለ አምላክ መንግሥት ይበልጥ እንዲያውቁ ሲመራቸው የቆየው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። በመጀመሪያ፣ የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረበትን ጊዜ እንዴት መረዳት እንደቻሉ እናያለን። ከዚያም የመንግሥቱን ገዥዎችና ተገዥዎች ማንነት እንዲሁም ምን ተስፋ እንዳላቸው እንመረምራለን። በመጨረሻም፣ የክርስቶስ ተከታዮች ለአምላክ መንግሥት ታማኝ መሆን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ግንዛቤ ያገኙት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ዓመት መለየት
5, 6. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ መንግሥቱ የሚቋቋምበትን ጊዜና የመከሩን ወቅት በተመለከተ ምን የተሳሳተ አመለካከት ነበራቸው? (ለ) እንዲህ ያለ የተሳሳተ አመለካከት መያዛቸው ኢየሱስ ተከታዮቹን እየመራ ስለመሆኑ እንድንጠራጠር የማያደርገን ለምንድን ነው?
5 በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ላይ እንደተመለከትነው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ 1914 ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ጋር በተያያዘ ትልቅ ቦታ እንዳለው ለአሥርተ ዓመታት ሲናገሩ ቆይተዋል። ይሁንና የክርስቶስ መገኘት የጀመረው በ1874 እንደሆነ፣ በ1878 ደግሞ በሰማይ መግዛት እንደጀመረና መንግሥቱ ሙሉ በሙሉ የሚቋቋመው ጥቅምት 1914 እንደሆነ ያስቡ ነበር። በተጨማሪም የመከሩ ሥራ ከ1874 እስከ 1914 ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወንና ቅቡዓኑ በሰማይ ሲሰበሰቡ ይህ ሥራ እንደሚያበቃ ያምኑ ነበር። ታዲያ እነዚያ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ እንደዚህ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች የነበሯቸው መሆኑ ኢየሱስ ታማኝ አገልጋዮቹን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እየመራቸው እንደነበር እንድንጠራጠር ያደርገናል?
6 በፍጹም! እስቲ በመግቢያችን ላይ የጠቀስነውን ምሳሌ መለስ ብለን እንመልከት። ጎብኚዎቹ ተገቢው ቦታ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ያቀረቧቸው ሐሳቦች ወይም ያነሷቸው ጥያቄዎች አስጎብኚው እምነት የሚጣልበት መሆኑን እንድንጠራጠር ያደርጉናል? እንደማያደርጉን የታወቀ ነው! በተመሳሳይም የአምላክ ሕዝቦች፣ መንፈስ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ዓላማ ዝርዝር ጉዳዮችን የሚገልጽበት ጊዜ ከመድረሱ በፊት እነዚህን እውነቶች ለመረዳት ጥረት ያደረጉባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ኢየሱስ እየመራቸው እንደነበረ ግልጽ ነው። በመሆኑም የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ለመታረም ዝግጁ ነበሩ፤ እንዲሁም ትሑት በመሆን አመለካከታቸውን አስተካክለዋል።—ያዕ. 4:6
7. የአምላክ ሕዝቦች ስለ የትኞቹ ነገሮች መንፈሳዊ ብርሃን በርቶላቸዋል?
7 ከ1919 በኋላ ባሉት ዓመታት የአምላክ ሕዝቦች ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጨማሪ መንፈሳዊ ብርሃን በራላቸው። (መዝሙር 97:11ን አንብብ።) በ1925 “የብሔሩ መወለድ” የሚል ትኩረት የሚስብ ርዕስ መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጥቶ ነበር። ይህ ርዕስ፣ መሲሐዊው መንግሥት በ1914 እንደተወለደ የሚያሳይ አሳማኝ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አቀረበ፤ ይህ መንግሥት መቋቋሙ በራእይ ምዕራፍ 12 ላይ የሚገኘውና የአምላክ ሰማያዊት ሴት፣ ልጅ እንደምትወልድ የሚገልጸው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርጓል።b ርዕሱ አክሎም ጦርነቱ በተካሄደባቸው ዓመታት በአምላክ ሕዝቦች ላይ የደረሰው ስደትና መከራ፣ ሰይጣን ከሰማይ እንደተወረወረና “ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ በታላቅ ቁጣ [እንደተሞላ]” የሚያሳይ ግልጽ ምልክት እንደሆነ አብራርቷል።—ራእይ 12:12
8, 9. (ሀ) የአምላክ መንግሥት ትልቅ ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ የተገለጸው እንዴት ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
8 የአምላክ መንግሥት ምን ያህል አስፈላጊ ነው? መጠበቂያ ግንብ በቤዛው አማካኝነት እያንዳንዳችን ከምናገኘው መዳን ይበልጥ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ከ1928 አንስቶ ጎላ አድርጎ መግለጽ ጀመረ። በእርግጥም ይሖዋ ስሙን የሚቀድሰው፣ ሉዓላዊነቱን የሚጠቀምበት መንገድ ትክክል መሆኑ እንዲረጋገጥ የሚያደርገውና ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ ያለውን ዓላማ በሙሉ የሚያስፈጽመው በመሲሐዊው መንግሥት አማካኝነት ነው።
9 በዚህ መንግሥት ከክርስቶስ ጋር ሆነው የሚገዙት እነማን ናቸው? የዚህ መንግሥት ምድራዊ ተገዥዎችስ እነማን ናቸው? የክርስቶስ ተከታዮች በየትኛው ሥራ ሊጠመዱ ይገባል?
የመከሩ ሥራ ቅቡዓኑን በመሰብሰብ ላይ ያተኮረ ነው
10. የአምላክ ሕዝቦች ከ144,000ዎቹ ጋር በተያያዘ ቀደም ካሉት ዘመናት ጀምሮ ምን ተገንዝበው ነበር?
10 እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ 144,000 የክርስቶስ ታማኝ ተከታዮች ከኢየሱስ ጋር በሰማይ እንደሚገዙ 1914 ከመድረሱ ከአሥርተ ዓመታት በፊት ተገንዝበው ነበር።c እነዚያ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የ144,000ዎቹ ቁጥር ቃል በቃል እንደሚወሰድና የዚህ ቡድን አባላት መሰብሰብ የጀመሩት ከአንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. አንስቶ እንደሆነ አስተውለው ነበር።
11. የክርስቶስ ሙሽራ የሚሆኑት ቅቡዓን በምድር ላይ ስለሚያከናውኑት ሥራ ያላቸው እውቀት እየጨመረ የመጣው እንዴት ነው?
11 ታዲያ የክርስቶስ ሙሽራ የሚሆኑት እነዚህ ቅቡዓን በምድር ላይ እንዲያከናውኑ የተሰጣቸው ሥራ ምንድን ነው? ኢየሱስ ለስብከቱ ሥራ ትልቅ ትኩረት እንደሰጠና ከመከሩ ወቅት ጋር አያይዞ እንደገለጸው እነዚህ ቅቡዓን ተገንዝበው ነበር። (ማቴ. 9:37፤ ዮሐ. 4:35) በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ላይ እንደተመለከትነው የመከሩ ሥራ ለ40 ዓመታት እንደሚቆይና ቅቡዓኑ ወደ ሰማይ ሲሰበሰቡ እንደሚጠናቀቅ ያስቡ ነበር። ይሁንና 40 ዓመታት ካለፉም በኋላ የመከሩ ሥራ ስለቀጠለ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ያስፈልግ ነበር። አሁን፣ የመከሩ ወቅት ይኸውም ስንዴው ከእንክርዳዱ ማለትም ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከአስመሳይ ክርስቲያኖች የሚለዩበት ጊዜ የጀመረው በ1914 እንደሆነ ተገንዝበናል። ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ ካላቸው መካከል ቀሪዎቹን በመሰብሰቡ ሥራ ላይ ትኩረት የሚደረግበት ጊዜ ደርሶ ነበር!
12, 13. ኢየሱስ ስለ አሥሩ ደናግልና ስለ ታላንቱ የተናገራቸው ምሳሌዎች በመጨረሻዎቹ ቀናት የተፈጸሙት እንዴት ነው?
12 ክርስቶስ፣ ከ1919 ጀምሮ ታማኝና ልባም ባሪያ ትኩረቱን በስብከቱ ሥራ ላይ እንዲያደርግ ሲመራው ቆይቷል። ይህን ተልእኮ የሰጠው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ነበር። (ማቴ. 28:19, 20) በተጨማሪም ቅቡዓን ተከታዮቹ ይህን የስብከት ተልእኮ ለመወጣት የሚያስፈልጓቸው ባሕርያት የትኞቹ እንደሆኑ ጠቁሟል። እንዴት? ኢየሱስ ስለ አሥሩ ደናግል በተናገረው ምሳሌ ላይ ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ ነቅተው መጠበቅ ይኸውም በመንፈሳዊ ንቁ መሆን እንደሚኖርባቸው ጠቁሟል። እንዲህ ካደረጉ ዋነኛ ግባቸው ላይ መድረስ ይችላሉ፤ በሌላ አባባል ክርስቶስ ‘ከሙሽራው’ ይኸውም ከ144,000ዎቹ ጋር በሚጣመርበት በሰማይ በሚካሄደው ታላቅ ሠርግ ላይ መካፈል ይችላሉ። (ራእይ 21:2) ኢየሱስ ቀጥሎ በተናገረው ስለ ታላንት በሚገልጸው ምሳሌ ላይ ደግሞ ቅቡዓን አገልጋዮቹ እሱ በአደራ የሰጣቸውን የስብከት ሥራ በትጋት እንደሚያከናውኑ ተናግሮ ነበር።—ማቴ. 25:1-30
13 ባለፈው መቶ ዓመት ቅቡዓኑ ንቁና ትጉ መሆናቸውን አሳይተዋል። ንቁ መሆናቸው ሽልማት እንደሚያስገኝላቸው ምንም ጥርጥር የለውም! ይሁንና ታላቁ የመከር ሥራ፣ ከክርስቶስ ጋር አብረው ከሚገዙት 144,000ዎች መካከል የቀሩትን ሰዎች በመሰብሰብ ላይ ብቻ ያተኮረ ይሆናል ማለት ነው?
መንግሥቱ በምድር ላይ የሚኖሩ ተገዥዎቹን ይሰበስባል!
14, 15. ያለቀለት ሚስጥር የተባለው መጽሐፍ ስለ የትኞቹ አራት ቡድኖች ያብራራል?
14 የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች በራእይ 7:9-14 ላይ የተጠቀሰውን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ማንነት ለማወቅ ለረጅም ጊዜ ሲጓጉ ቆይተዋል። ክርስቶስ፣ ይህ ታላቅ ቡድን እነማንን ያቀፈ እንደሆነ የሚገልጽበት ጊዜ ከመድረሱ በፊት የአምላክ አገልጋዮች ስለዚህ ቡድን የነበራቸው አመለካከት፣ እኛ ዛሬ ከምናውቀው ብሎም ከፍ አድርገን ከምንመለከተው ግልጽና ለመረዳት ቀላል የሆነ እውነት ፈጽሞ የተለየ ነበር።
15 በ1917 የተዘጋጀው ያለቀለት ሚስጥር (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ፣ “መዳን አግኝተው ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሰዎች ሁለት ዓይነት ደረጃ እንዳላቸውና በምድር ላይ መዳን የሚያገኙት ሰዎችም ሁለት ዓይነት ደረጃ እንደሚኖራቸው” ገልጾ ነበር። እንዲህ ያለ የተለያየ ተስፋ ያላቸው አራት ቡድኖች አባላት እነማን ነበሩ? የመጀመሪያዎቹ፣ ከክርስቶስ ጋር የሚገዙት 144,000ዎች ናቸው። የሁለተኛው ቡድን አባላት፣ እጅግ ብዙ ሕዝብ ናቸው። በዚያ ወቅት፣ እጅግ ብዙ ሕዝብ የሚለው አገላለጽ በሕዝበ ክርስትና የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙ ስመ ክርስቲያኖችን እንደሚያመለክት ይታሰብ ነበር። እነዚህ ሰዎች የተወሰነ እምነት ቢኖራቸውም እምነታቸው የታማኝነት አቋም ለመውሰድ የሚያበቃ አይደለም። በመሆኑም በሰማይ ላይ ሁለተኛ ደረጃ ይሰጣቸዋል። ወደ ምድር ስንመጣ ደግሞ፣ “የጥንቶቹ ጻድቃን” ይኸውም እንደ አብርሃምና ሙሴ የመሳሰሉት ታማኝ ሰዎች በሦስተኛው ቡድን ውስጥ እንደሚካተቱ ይታሰብ ነበር፤ እነዚህ ሰዎች፣ በአራተኛው ቡድን ማለትም በመላው የሰው ዘር ላይ ሥልጣን ይሰጣቸዋል።
16. በ1923 እና በ1932 ምን ዓይነት መንፈሳዊ ብርሃን ፈነጠቀ?
16 ታዲያ የክርስቶስ ተከታዮች፣ ዛሬ ከፍ አድርገን የምናየውን ግንዛቤ እንዲያገኙ መንፈስ ቅዱስ የረዳቸው እንዴት ነው? ይህ የሆነው ቀስ በቀስ ሲሆን በተለያየ ጊዜ የተወሰነ መንፈሳዊ ብርሃን ይፈነጥቅላቸው ነበር። በ1923 በታተመ መጠበቂያ ግንብ ላይ፣ ወደ ሰማይ የመሄድ ፍላጎት የሌላቸውና በክርስቶስ ግዛት ሥር በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች እንዳሉ የሚጠቁም ሐሳብ ወጥቶ ነበር። በ1932 የወጣ መጠበቂያ ግንብ ደግሞ ስለ ኢዮናዳብ የሚናገር ሐሳብ ይዞ ነበር፤ ኢዮናዳብ፣ አምላክ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን ከቀባው ከኢዩ ጋር በመጣበቅ ኢዩ የሐሰት አምልኮን ለማጥፋት ውጊያ ሲያካሄድ አግዞታል። (2 ነገ. 10:15-17) በዚህ መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣው ርዕስ፣ በዘመናችን እንደ ኢዮናዳብ ዓይነት ቡድን እንደሚኖር የሚናገር ሲሆን አክሎም ይሖዋ ይህ ቡድን “አርማጌዶንን በሕይወት እንዲያልፍ” እንደሚያደርግና የዚህ ቡድን አባላት በዚህች ምድር ላይ እንደሚኖሩ ገልጿል።
17. (ሀ) በ1935 የትኛው ደማቅ መንፈሳዊ ብርሃን በራ? (ለ) ታማኝ ክርስቲያኖች ስለ እጅግ ብዙ ሕዝብ አዲስ ግንዛቤ ሲያገኙ ምን ተሰማቸው? (“ትልቅ እፎይታ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
17 በ1935 ደማቅ መንፈሳዊ ብርሃን በራ። በዚህ ዓመት በዋሽንግተን ዲ. ሲ. በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ፣ እጅግ ብዙ ሕዝብ የሚለው አገላለጽ በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያላቸውን ሰዎች እንደሚያመለክት ተገለጸ፤ እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ ስለ በጎችና ፍየሎች በተናገረው ምሳሌ ላይ በበጎች የተመሰሉት ናቸው። (ማቴ. 25:33-40) እጅግ ብዙ ሕዝብ፣ ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል ናቸው፤ ኢየሱስ ስለ እነዚህ በጎች ሲናገር “እነሱንም ማምጣት አለብኝ” ብሏል። (ዮሐ. 10:16) ንግግሩን ያቀረበው ወንድም ጆሴፍ ራዘርፎርድ፣ “በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላችሁ ሁሉ እባካችሁ አንድ ጊዜ ብድግ በሉ” ሲል ጠየቀ፤ በዚህ ጊዜ ከተሰብሳቢዎቹ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ብድግ አሉ! ከዚያም ወንድም ራዘርፎርድ “እነሆ፣ እጅግ ብዙ ሕዝብ!” አለ። ብዙዎቹ ተሰብሳቢዎች ስለ ወደፊት ተስፋቸው መረዳታቸው በጣም አስደስቷቸው ነበር።
18. የክርስቶስ ተከታዮች ከአገልግሎቱ ጋር በተያያዘ ትኩረት ያደረጉት በምን ላይ ነው? ውጤቱስ ምን ሆኗል?
18 ከዚያ ጊዜ ወዲህ ክርስቶስ፣ ታላቁን መከራ በሕይወት የሚያልፉትን የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት በመሰብሰቡ ሥራ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ተከታዮቹን ሲመራቸው ቆይቷል። መጀመሪያ ላይ፣ የሚሰበሰቡት ሰዎች ያን ያህል ብዙ አይመስሉም ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት ወንድም ራዘርፎርድ “‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ ቁጥር ብዙ የሚሆን አይመስልም” ብሎ ነበር። እርግጥ ነው፣ በአሁኑ ጊዜ ያለን ክርስቲያኖች ይሖዋ የመከሩን ሥራ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ምን ያህል እንደባረከው እናውቃለን። ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ “ሌሎች በጎች” የተባሉት አጋሮቻቸው፣ በኢየሱስና በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ ክርስቶስ አስቀድሞ እንደተናገረው ‘በአንድ እረኛ’ ሥር አብረው የሚያገለግሉ “አንድ መንጋ” ሆነዋል።
19. የእጅግ ብዙ ሕዝብ ቁጥር እያደገ እንዲሄድ አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
19 አብዛኞቹ ታማኝ የአምላክ ሕዝቦች፣ በክርስቶስና በ144,000 ተባባሪ ገዥዎቹ እየተመሩ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ። ክርስቶስ፣ እንዲህ ያለውን ግልጽ ቅዱስ ጽሑፋዊ ተስፋ መረዳት እንዲችሉ የአምላክን ሕዝቦች እንዴት እንደመራቸው ማወቁ የሚያስደስት አይደለም? ይህን ተስፋ በአገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች ማካፈሉ ምንኛ ታላቅ መብት ነው! የእጅግ ብዙ ሕዝብ ቁጥር እያደገ መሄዱን እንዲቀጥል ሁኔታችን የሚፈቅደውን ያህል በአገልግሎቱ በቅንዓት እንካፈል፤ የዚህ ቡድን አባላት ቁጥር በጨመረ መጠን የይሖዋ ስም ይበልጥ ይወደሳል!—ሉቃስ 10:2ን አንብብ።
ለመንግሥቱ ታማኝ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?
20. የሰይጣን ድርጅት የትኞቹን ክፍሎች ያቀፈ ነው? ክርስቲያኖች በዚህ ረገድ ታማኝ መሆናቸውን የሚያሳዩት እንዴት ነው?
20 የአምላክ ሕዝቦች ስለ መንግሥቱ እየተማሩ ሲሄዱ በሰማይ ለሚገኘው ለዚህ መንግሥት ታማኝ መሆን ሲባል ምን ማለት እንደሆነም በደንብ መረዳት ያስፈልጋቸው ነበር። ከዚህ ጋር በተያያዘ በ1922 የወጣ መጠበቂያ ግንብ በአሁኑ ጊዜ ሁለት ድርጅቶች ይኸውም የይሖዋ እና የሰይጣን ድርጅቶች በእንቅስቃሴ ላይ እንዳሉ ገልጾ ነበር፤ የሰይጣን ድርጅት የንግዱን፣ የሃይማኖቱንና የፖለቲካውን ሥርዓት ያቀፈ ነው። በክርስቶስ ለሚመራው የአምላክ መንግሥት ታማኝ የሆኑ ሰዎች፣ ከየትኛውም የሰይጣን ድርጅት ክፍል ጋር አላስፈላጊ ቅርርብ በመፍጠር ታማኝነታቸውን ማላላት የለባቸውም። (2 ቆሮ. 6:17) ታዲያ ይህ ሲባል ምን ማለት ነው?
21. (ሀ) ታማኙ ባሪያ፣ ትላልቅ የንግድ ድርጅቶችን በተመለከተ ለአምላክ ሕዝቦች ምን ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ቆይቷል? (ለ) በ1963 የወጣ መጠበቂያ ግንብ ስለ “ታላቂቱ ባቢሎን” ማንነት ምን ሐሳብ ይዞ ነበር?
21 ታማኙ ባሪያ፣ ትላልቅ የንግድ ድርጅቶች በሙስና የተዘፈቁ እንደሆኑ በሚያቀርበው መንፈሳዊ ምግብ አማካኝነት ያጋለጠ ከመሆኑም ሌላ የአምላክ ሕዝቦች እነዚህ ድርጅቶች በሚያስፋፉት የፍቅረ ነዋይ መንፈስ እንዳይጠመዱ ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል። (ማቴ. 6:24) በተጨማሪም ጽሑፎቻችን፣ የሰይጣን ድርጅት ሃይማኖታዊ ክፍል ማንን እንደሚያመለክት እንዲታወቅ አድርገዋል። በ1963 የወጣ መጠበቂያ ግንብ “ታላቂቱ ባቢሎን” የምታመለክተው ሕዝበ ክርስትናን ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ እንደሆነ በግልጽ አሳይቷል። በመሆኑም በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 10 ላይ በሰፊው እንደምንመለከተው በየትኛውም አገር የሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች ከሐሰት ሃይማኖት ልማዶች ሙሉ በሙሉ በመላቀቅ ‘ከእሷ መውጣት’ ችለዋል።—ራእይ 18:2, 4
22. በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ብዙዎቹ የአምላክ ሕዝቦች በሮም 13:1 ላይ የሚገኘውን መመሪያ የተረዱት እንዴት ነበር?
22 የሰይጣን ድርጅት ክፍል ስለሆነው ፖለቲካዊ ሥርዓትስ ምን ማለት ይቻላል? እውነተኛ ክርስቲያኖች በብሔራት መካከል በሚነሱ ግጭቶችና ጦርነቶች ውስጥ መካፈል ይችላሉ? በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ የክርስቶስ ተከታይ የሆነ ሰው ሌሎችን መግደል እንደሌለበት ተገንዝበው ነበር። (ማቴ. 26:52) ይሁንና ብዙዎች በሮም 13:1 ላይ የሚገኘውን ‘ለበላይ ባለሥልጣናት ተገዙ’ የሚለውን መመሪያ ለመታዘዝ የጦር ሠራዊት አባል መሆን፣ የወታደር የደንብ ልብስ መልበስ አልፎ ተርፎም መሣሪያ መታጠቅ እንደሚኖርባቸው ይሰማቸው ነበር፤ ሆኖም ጠላትን እንዲገድሉ ሲጠየቁ ወደ ሰማይ ይተኩሱ ነበር።
23, 24. በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሮም 13:1ን በተመለከተ ምን ዓይነት ግንዛቤ ነበረን? የክርስቶስ ተከታዮች ምን ዓይነት ትክክለኛ ግንዛቤ አገኙ?
23 በ1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንደጀመረ አካባቢ ገለልተኝነትን በተመለከተ ጥልቀት ያለው ሐሳብ መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጣ። መጠበቂያ ግንቡ ክርስቲያኖች፣ በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያሉት ብሔራት በሚያካሂዷቸው ጦርነቶችና ግጭቶች ውስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ ማድረግ እንደሌለባቸው በግልጽ አብራርቶ ነበር። ይህ እንዴት ያለ ወቅታዊ መመሪያ ነው! በዚህም ምክንያት የክርስቶስ ተከታዮች፣ በዚያ ጦርነት የተካፈሉት ብሔራት ከተሸከሙት ከባድ የደም ዕዳ ነፃ መሆን ችለዋል። ይሁንና ከ1929 ጀምሮ ጽሑፎቻችን በሮም 13:1 ላይ የተጠቀሱት የበላይ ባለሥልጣናት ይሖዋና ኢየሱስ እንጂ ሰብዓዊ ገዢዎች ሊሆኑ እንደማይችሉ ይገልጹ ነበር። በመሆኑም በዚህ ረገድ ትክክለኛ የሆነ ግንዛቤ ያስፈልግ ነበር።
24 በ1962 የክርስቶስ ተከታዮች እንዲህ ያለ ግንዛቤ እንዲያገኙ መንፈስ ቅዱስ ረዳቸው፤ የኅዳር 15 እና የታኅሣሥ 1 መጠበቂያ ግንብ እትሞች ሮም 13:1-7ን በተመለከተ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ትምህርት ይዘው ወጡ። በመጨረሻም የአምላክ ሕዝቦች፣ ኢየሱስ “የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” በማለት በተናገረው ጥቅስ ላይ የሚገኘውን በአንጻራዊ ሁኔታ ስለመገዛት የሚገልጽ መሠረታዊ ሥርዓት መረዳት ቻሉ። (ሉቃስ 20:25) በአሁኑ ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች የበላይ ባለሥልጣናት የተባሉት የዚህ ዓለም ገዥዎች እንደሆኑና ክርስቲያኖች ለእነሱ ሊገዙ እንደሚገባ ተገንዝበዋል። ይሁንና ለእነሱ የሚገዙት በአንጻራዊ ሁኔታ ነው። የዚህ ዓለም ባለሥልጣናት፣ የይሖዋ አምላክን ትእዛዝ እንድንጥስ ሲጠይቁን በጥንት ዘመን እንደነበሩት ሐዋርያት “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል” በማለት እንመልሳለን። (ሥራ 5:29) በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 13 እና 14 ላይ የአምላክ ሕዝቦች የገለልተኝነት አቋም የወሰዱት እንዴት እንደሆነ ይበልጥ ይብራራል።
25. መንፈስ ቅዱስ ስለ አምላክ መንግሥት እንድናውቅ ያበረከተውን አስተዋጽኦ የምታደንቀው ለምንድን ነው?
25 የክርስቶስ ተከታዮች ባለፈው ምዕተ ዓመት ውስጥ ስለ መንግሥቱ ምን ያህል እንደተማሩ እስቲ አስበው። የአምላክ መንግሥት በሰማይ የተቋቋመው መቼ እንደሆነና ይህ መንግሥት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተምረናል። ለአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ስለተዘረጉላቸው ሁለት ተስፋዎች ይኸውም ስለ ሰማያዊውና ስለ ምድራዊው ተስፋ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ አግኝተናል። በተጨማሪም ለዓለም ባለሥልጣናት በአንጻራዊ ሁኔታ እየተገዛን ለአምላክ መንግሥት ታማኝ መሆን የምንችለው እንዴት እንደሆነ አውቀናል። እንግዲያው ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ውድ እውነቶች ምድር ላለው ታማኝ ባሪያው ባያሳውቀውና ለሌሎች እንዲያስተምር ባይረዳው ኖሮ ከእነዚህ እውነቶች መካከል አንዱን እንኳ መረዳት እችል ነበር?’ በእርግጥም ክርስቶስና መንፈስ ቅዱስ እየመሩን በመሆኑ ምንኛ ተባርከናል!
a አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው እዚህ ጥቅስ ላይ “ይመራችኋል” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “መንገድ ማሳየት” የሚል ትርጉም አለው።
b ከዚያ ቀደም ብሎ፣ ይህ ራእይ አረማዊ አምልኮን በሚከተለው የሮም ግዛትና በሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መካከል የሚካሄድ ጦርነትን የሚያመለክት እንደሆነ ይታሰብ ነበር።
c የሰኔ 1880 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ 144,000ዎቹ እስከ 1914 ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ክርስትና እምነት የሚለወጡ የአይሁድ ዝርያ ያላቸው ሰዎች እንደሆኑ የሚገልጽ ሐሳብ ይዞ ነበር። ይሁን እንጂ በ1880 መጨረሻ አካባቢ በአሁኑ ጊዜ ካለን ግንዛቤ ጋር ይበልጥ የሚቀራረብ ሐሳብ ወጣ።