ምዕራፍ 8
ለስብከት የሚረዱን መሣሪያዎች—ምሥራቹን በዓለም ዙሪያ ለማዳረስ ጽሑፎችን ማዘጋጀት
1, 2. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በሮም ግዛቶች ውስጥ ምሥራቹ በስፋት እንዲሰራጭ አስተዋጽኦ ያደረገው ምንድን ነው? (ለ) በዘመናችን ይሖዋ እየደገፈን እንዳለ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ? (“ከ670 በሚበልጡ ቋንቋዎች የሚሰበክ ምሥራች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
በኢየሩሳሌም ያሉት እንግዶች ጆሯቸውን ማመን አቅቷቸዋል። የገሊላ ሰዎች፣ የባዕድ አገራትን ቋንቋዎች አቀላጥፈው እየተናገሩ ነው፤ የሚናገሩት መልእክትም የሚያዳምጧቸውን ሰዎች ቀልብ የሚስብ ነው። ጊዜው 33 ዓ.ም. ሲሆን የጴንጤቆስጤ በዓል እየተከበረ ነበር። በዚህ ወቅት ደቀ መዛሙርቱ የተለያዩ ቋንቋዎችን የመናገር ስጦታ በተአምር ተሰጣቸው፤ ይህም አምላክ ከእነሱ ጋር መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-8, 12, 15-17ን አንብብ።) በዚያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ምሥራቹን ከተለያየ ቦታ ለመጡ ሰዎች የሰበኩ ሲሆን ከዚያ በኋላም ምሥራቹ በመላው የሮም ግዛት ተዳርሷል።—ቆላ. 1:23
2 እርግጥ ነው፣ ዛሬ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች በተለያዩ ቋንቋዎች የመናገር ተአምራዊ ስጦታ የላቸውም። ያም ቢሆን በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከተሰበከባቸው እጅግ በሚበልጡ ቋንቋዎች ይኸውም ከ670 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች የመንግሥቱን መልእክት እየተረጎሙ ነው። (ሥራ 2:9-11) የአምላክ ሕዝቦች ጽሑፎችን በበርካታ ቋንቋዎች በብዛት በማዘጋጀታቸው በዓለም ላይ የመንግሥቱ መልእክት ያልደረሰበት ቦታ የለም ማለት ይቻላል።a ይህም ቢሆን ይሖዋ የስብከት ሥራችንን ለመምራት በንጉሡ በኢየሱስ ክርስቶስ እየተጠቀመ እንደሆነ የሚያሳይ የማያሻማ ማስረጃ ነው። (ማቴ. 28:19, 20) ባለፈው 100 ዓመት ውስጥ ይህን ሥራ ለማከናወን የተጠቀምንባቸውን አንዳንድ መሣሪያዎች እየተመለከትን ስንሄድ ንጉሡ ለሰዎች በግለሰብ ደረጃ ትኩረት እንድንሰጥ ቀስ በቀስ ያሠለጠነን እንዴት እንደሆነ እንዲሁም የአምላክ ቃል አስተማሪዎች እንድንሆን እንዴት እንዳበረታታን ልብ ለማለት ሞክር።—2 ጢሞ. 2:2
ንጉሡ የእውነትን ዘር እንዲዘሩ አገልጋዮቹን አስታጥቋቸዋል
3. በስብከቱ ሥራችን የተለያዩ መሣሪያዎችን የምንጠቀመው ለምንድን ነው?
3 ኢየሱስ “የመንግሥቱን ቃል” ከዘር፣ የሰዎችን ልብ ደግሞ ከአፈር ጋር አመሳስሎታል። (ማቴ. 13:18, 19) አንድ አትክልተኛ መሬቱን ለማለስለስና ለዘር ለማዘጋጀት የተለያዩ መሣሪያዎችን እንደሚጠቀም ሁሉ የይሖዋ ሕዝቦችም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት እንዲቀበሉ ልባቸውን ለማዘጋጀት የረዱ የተለያዩ መሣሪያዎችን ሲጠቀሙ ቆይተዋል። ከእነዚህ መሣሪያዎች አንዳንዶቹ ያገለገሉት ለተወሰነ ጊዜ ያህል ነበር። እንደ መጻሕፍትና መጽሔቶች ያሉት ሌሎች መሣሪያዎች ግን አሁንም ጠቃሚ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው። ባለፈው ምዕራፍ ላይ ከተመለከትናቸው ዘዴዎች አብዛኞቹ በአንድ ጊዜ ለብዙዎች ለመስበክ የሚያስችሉ ነበሩ፤ ከዚህ በተለየ መልኩ በዚህ ምዕራፍ ላይ የምናያቸው መሣሪያዎች በሙሉ፣ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ አግኝተው እንዲያነጋግሯቸው ረድተዋቸዋል።—ሥራ 5:42፤ 17:2, 3
4, 5. ወንድሞች፣ በሸክላ የተቀዱትን ንግግሮች ለሰዎች የሚያሰሙት እንዴት ነበር? ይህ ዘዴ ምን ይጎድለው ነበር?
4 የተቀዱ ንግግሮች። በ1930ዎቹና በ1940ዎቹ ዓመታት አስፋፊዎች የተቀዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን፣ ይዘውት በሚንቀሳቀሱት የሸክላ ማጫወቻ አማካኝነት ለሰዎች ያሰሙ ነበር። እያንዳንዱ ንግግር አምስት ደቂቃ አይሞላም። የተቀዱት ንግግሮች እንደ “ሥላሴ፣” “መንጽሔ” እና “መንግሥት” የመሳሰሉ አጫጭር ርዕሶች ነበሯቸው። ንግግሮቹን ለሰዎች የሚያሰሙት እንዴት ነበር? በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩትና በ1930 የተጠመቁት ወንድም ክሌይተን ዉድዎርዝ ጁኒየር እንዲህ ብለዋል፦ “በቦርሳ የምትያዝ ትንሽ የሸክላ ማጫወቻ እይዝ ነበር፤ የሸክላ ማጫወቻዋ የምትሠራው ሞላውን በማጠንጠን ሲሆን ሸክላው በአግባቡ እንዲጫወት ማጫወቻውን ዘንግ በሸክላው ጠርዝ ላይ አስተካክዬ ማስቀመጥ ያስፈልገኝ ነበር። ከቤት ወደ ቤት ስሄድ የበሩን ደወል ከመደወሌ በፊት ቦርሳውን ከፍቼ ማጫወቻውን ዘንግ ትክክለኛው ቦታ ላይ አስቀምጠዋለሁ፤ ከዚያም የበሩን ደወል እደውላለሁ። የቤቱ ባለቤት ሲመጣ ‘አንድ ጠቃሚ መልእክት ላሰማዎት እፈልጋለሁ’ እለዋለሁ።” ታዲያ ሰዎች ምን ምላሽ ይሰጡ ነበር? ወንድም ዉድዎርዝ እንዲህ ብለዋል፦ “ብዙውን ጊዜ ሰዎች መልእክቱን ለመስማት ፈቃደኞች ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ግን በሩን ፊታችን ላይ ይዘጉብናል። የሸክላ ማጫወቻ እንደምሸጥ ያሰቡ ሰዎችም አጋጥመውኝ ያውቃሉ።”
5 እስከ 1940 ድረስ ከ90 በላይ የተለያዩ ንግግሮች ተቀድተው የነበረ ሲሆን እነዚህን ንግግሮች በማባዛት ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ቅጂዎች ተዘጋጅተዋል። በወቅቱ በብሪታንያ በአቅኚነት ያገለገለውና ከጊዜ በኋላ የበላይ አካል አባል የነበረው ወንድም ጆን ባር እንዲህ ብሏል፦ “ከ1936 እስከ 1945 ባሉት ዓመታት የሸክላ ማጫወቻ ምንጊዜም ከእጄ አይለይም ነበር። እንዲያውም በዚያ ወቅት የሸክላ ማጫወቻ ካልያዝኩ ምን እንደማደርግ ግራ ይገባኝ ነበር። ከቤት ወደ ቤት በማገለግልበት ወቅት ሰዎች በር ላይ ቆሜ የወንድም ራዘርፎርድን የተቀዳ ንግግር ስሰማ በጣም እበረታታለሁ፤ ወንድም ራዘርፎርድ አጠገቤ ያለ ያህል ይሰማኝ ነበር። እርግጥ ነው፣ በሸክላ ማጫወቻዎች ተጠቅመን መስበክ የአገልግሎታችን አንዱ ገጽታ የሆነውን ነገር ይኸውም ሰዎችን እንድናስተምር የተሰጠንን ተልእኮ ለመፈጸም አያስችለንም፤ በመሆኑም እነዚህን ንግግሮች በማሰማት የሰዎችን ልብ መንካት አንችልም ነበር።”
6, 7. (ሀ) ምሥክርነት መስጫ ካርድ ምን ጥቅም ነበረው? ይህ መሣሪያ ምን የሚጎድሉት ነገሮች ነበሩት? (ለ) ይሖዋ፣ ‘ቃሉን በአፋችን ላይ ያኖረው’ እንዴት ነው?
6 ምሥክርነት መስጫ ካርዶች። አስፋፊዎች ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ፣ ምሥክርነት መስጫ ካርዶችን እንዲጠቀሙ ከ1933 አንስቶ ማበረታቻ ይሰጣቸው ነበር። ምሥክርነት መስጫ ካርድ የሚባለው 7.6 ሴንቲ ሜትር በ12.7 ሴንቲ ሜትር የሆነ ካርድ ነው። ካርዱ ላይ አጠር ያለ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክትና ስለ አንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ የሚገልጽ ሐሳብ የሰፈረ ሲሆን የቤቱ ባለቤት ከፈለገ ጽሑፉን መውሰድ እንደሚችል የሚጠቁም ሐሳብም ይገኛል። አስፋፊው ካርዱን በቀጥታ ለቤቱ ባለቤት ይሰጠውና እንዲያነብበው ይጠይቀዋል። ሊሊያን ካመሩድ “በምሥክርነት መስጫ ካርዶች መስበክ ሲጀመር በጣም ደስ አለኝ” ብላለች፤ ይህች እህት ከጊዜ በኋላ በፖርቶ ሪኮ እና በአርጀንቲና ሚስዮናዊ ሆና አገልግላለች። ሊሊያን በምሥክርነት መስጫ ካርድ መስበክ ያስደስታት የነበረው ለምንድን ነው? “ሰዎችን ጥሩ አድርገን የማነጋገር ችሎታ ያለን ሁላችንም አይደለንም። በመሆኑም ካርዱ ሰዎችን ማነጋገር እንድለምድ ረድቶኛል” ብላለች።
7 በ1918 የተጠመቁት ወንድም ዴቪድ ሩሽ “ምሥክርነት መስጫ ካርዶች ወንድሞችን ረድተዋቸዋል፤ ምክንያቱም አብዛኞቹ ትክክለኛውን ነገር መናገር እንደማይችሉ ይሰማቸው ነበር” ብለዋል። ይሁንና ይህ መሣሪያም ቢሆን የሚጎድሉት ነገሮች ነበሩ። ወንድም ሩሽ እንዲህ ብለዋል፦ “አንዳንድ ጊዜ የምናገኛቸው ሰዎች መናገር እንደማንችል ይሰማቸው ነበር። ደግሞም በአንድ በኩል ሲታይ አብዛኞቻችን መናገር የማንችል ያህል ነበርን። ሆኖም ይሖዋ፣ ሰዎችን ማስተማር እንድንችል እያዘጋጀን ነበር። ብዙም ሳይቆይ፣ ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል በቅዱሳን መጻሕፍት እንድንጠቀም በማስተማር ቃሉን በአፋችን ላይ አኖረው። በ1940ዎቹ ዓመታት የተቋቋመው ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ይህን ለማድረግ አስችሏል።”—ኤርምያስ 1:6-9ን አንብብ።
8. ክርስቶስ እንዲያሠለጥንህ ፈቃደኛ መሆንህን ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?
8 መጻሕፍት። ከ1914 ወዲህ የይሖዋ ሕዝቦች፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳቦችን የሚያብራሩ ከ100 የሚበልጡ መጻሕፍትን አዘጋጅተዋል። ከእነዚህ መጻሕፍት አንዳንዶቹ፣ አስፋፊዎች ውጤታማ አገልጋይ እንዲሆኑ ለማሠልጠን ታስበው የተዘጋጁ ናቸው። በዴንማርክ የሚኖሩትና 70 ለሚያህሉ ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩት እህት አና ላርሰን እንዲህ ብለዋል፦ “ይሖዋ፣ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት እና ከትምህርት ቤቱ ጋር ተያያዥነት ባላቸው መጻሕፍት አማካኝነት ይበልጥ ውጤታማ አስፋፊዎች እንድንሆን ረድቶናል። ከእነዚህ መጻሕፍት የመጀመሪያው በ1945 የወጣው ለመንግሥቱ አስፋፊዎች የተዘጋጀ ቲኦክራሲያዊ ሥልጠና (እንግሊዝኛ) የተባለው እንደነበረ አስታውሳለሁ። ቀጥሎም በ1946 ‘ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ መታጠቅ’ (እንግሊዝኛ) የሚል መጽሐፍ ወጣ። አሁን ደግሞ በ2001 በወጣው በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም በተባለው መጽሐፍ እያሠለጠነን ነው።” ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት እና ከትምህርት ቤቱ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሌሎች መጻሕፍት፣ ይሖዋ “አገልጋዮች እንድንሆን ብቁዎች [ለማድረግ]” በሚሰጠን ሥልጠና ረገድ ቁልፍ ሚና እንደተጫወቱ ምንም ጥርጥር የለውም። (2 ቆሮ. 3:5, 6) አንተስ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተመዝግበሃል? የአገልግሎት ትምህርት ቤት የተባለውን መጽሐፍ በየሳምንቱ ወደ ስብሰባ ይዘህ በመሄድ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ሐሳብ ሲሰጥ እያወጣህ ትከታተላለህ? እንዲህ የምታደርግ ከሆነ የተሻልክ አስተማሪ እንድትሆን ክርስቶስ እንዲያሠለጥንህ ፈቃደኛ ሆነሃል ማለት ነው።—2 ቆሮ. 9:6፤ 2 ጢሞ. 2:15
9, 10. የእውነትን ዘር በመትከሉና በማጠጣቱ ሥራ መጻሕፍት ምን ሚና ተጫውተዋል?
9 በተጨማሪም ይሖዋ፣ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ለማብራራት የሚያስችሉንን መጻሕፍት ድርጅቱ እንዲያዘጋጅልን በማድረግ ረድቶናል። በተለይ ደግሞ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለው መጽሐፍ በጣም ውጤታማ ነበር። መጽሐፉ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው በ1968 ሲሆን ወዲያውኑ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። የኅዳር 1968 የመንግሥት አገልግሎት “እውነት የተባለው መጽሐፍ በጣም ተፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ በመስከረም ወር በብሩክሊን ያለው የማኅበሩ ፋብሪካ የማታ ፈረቃ እንዲሠራ ልዩ ዝግጅት ተደረገ” ብሎ ነበር። ይህ የመንግሥት አገልግሎት አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ታትሞ ከነበረው የእውነት መጽሐፍ ሌላ አንድ ሚሊዮን ተኩል ተጨማሪ ቅጂዎች በነሐሴ ወር አስፈልገው ነበር!” እስከ 1982 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ100 ሚሊዮን የሚበልጡ የዚህ መጽሐፍ ቅጂዎች በ116 ቋንቋዎች ታትመዋል። ከ1968 እስከ 1982 ባሉት 14 ዓመታት ውስጥ የእውነት መጽሐፍ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተጨማሪ የመንግሥቱ አስፋፊዎች እንዲገኙ አስተዋጽኦ አድርጓል።b
10 በ2005 ደግሞ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት የሚረዳ ሌላ መጽሐፍ የወጣ ሲሆን ይህ መጽሐፍ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። እስከ አሁን ድረስ ወደ 200 ሚሊዮን የሚጠጉ ቅጂዎች በ256 ቋንቋዎች ታትመዋል! ታዲያ ምን ውጤት ተገኘ? ከ2005 እስከ 2012 ባሉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ብቻ 1.2 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የምሥራቹ ሰባኪዎች ሆነዋል። በእነዚሁ ዓመታት ውስጥ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ከእኛ ጋር የሚያጠኑት ሰዎች ቁጥር ከ6 ሚሊዮን ተነስቶ ከ8.7 ሚሊዮን በላይ ሆኗል። ይሖዋ፣ የመንግሥቱን እውነት ዘር ለመትከልና ለማጠጣት የምናደርገውን ጥረት እየባረከው እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።—1 ቆሮንቶስ 3:6, 7ን አንብብ።
11, 12. በአንቀጹ ውስጥ ባሉት ጥቅሶች መሠረት መጽሔቶቻችን የሚዘጋጁት የእነማንን ልብ ለመንካት ነው?
11 መጽሔቶች። መጀመሪያ ላይ መጠበቂያ ግንብ በዋነኝነት የሚዘጋጀው ‘ለትንሹ መንጋ’ ማለትም ‘ሰማያዊ ጥሪ’ ላላቸው ክርስቲያኖች ነበር። (ሉቃስ 12:32፤ ዕብ. 3:1) ከጥቅምት 1, 1919 ጀምሮ ደግሞ የይሖዋ ድርጅት፣ ምሥራቹ ለሚሰበክላቸው ሰዎች የሚሆን ሌላ መጽሔት ማዘጋጀት ጀመረ። መጽሔቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችም ሆነ በሌሎች ሰዎች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት በማትረፉ ለበርካታ ዓመታት የዚህ መጽሔት ስርጭት ከመጠበቂያ ግንብ ስርጭት በእጅጉ ይበልጥ ነበር። ይህ መጽሔት መጀመሪያ ላይ ወርቃማው ዘመን ይባል ነበር። በ1937 የመጽሔቱ ስም መጽናኛ ከዚያም በ1946 ንቁ! ተባለ።
12 ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! አቀራረባቸው ተለውጧል፤ እነዚህ መጽሔቶች የሚዘጋጁበት ዓላማ ግን አልተለወጠም፤ ዓላማቸው የአምላክን መንግሥት ማስተዋወቅና ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት እንዲያዳብሩ መርዳት ነው። በአሁኑ ጊዜ መጠበቂያ ግንብ፣ የጥናት እትም እና ለሕዝብ የሚሰራጭ እትም ተብሎ በሁለት መልኩ ይዘጋጃል። የጥናት እትሙ የሚዘጋጀው “ቤተሰቦቹ” ለተባሉት ማለትም ‘ለትንሹ መንጋ’ እና ‘ለሌሎች በጎች’ ነው።c (ማቴ. 24:45፤ ዮሐ. 10:16) ለሕዝብ የሚሰራጨው እትም በዋነኝነት የሚዘጋጀው ለመጽሐፍ ቅዱስ እና ለአምላክ አክብሮት ቢኖራቸውም እውነትን ላላወቁ ሰዎች ነው። (ሥራ 13:16) ንቁ! ደግሞ የሚዘጋጀው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እና ስለ እውነተኛው አምላክ ስለ ይሖዋ ብዙም ለማያውቁ ሰዎች ነው።—ሥራ 17:22, 23
13. ከመጽሔቶቻችን ጋር በተያያዘ አንተን የሚያስገርምህ ምንድን ነው? (“በዓለም ላይ በብዛት የታተሙ ጽሑፎች” በሚለው ሠንጠረዥ ላይ ተወያዩ።)
13 በ2014 መጀመሪያ አካባቢ በየወሩ ከ44 ሚሊዮን በላይ የንቁ! ቅጂዎች እና 46 ሚሊዮን ገደማ መጠበቂያ ግንብ መጽሔቶች ታትመዋል። ንቁ! ወደ 100 በሚጠጉ ቋንቋዎች፣ መጠበቂያ ግንብ ደግሞ ከ200 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል፤ በመሆኑም በብዙ ቋንቋዎች በመተርጎምና በስፋት በመሰራጨት ረገድ በዓለም ላይ ከሚታተሙት መጽሔቶች ሁሉ ቀዳሚውን ቦታ ይዘዋል! ይህ አስገራሚ ነገር ቢሆንም ያን ያህል ሊያስደንቀን አይገባም። ምክንያቱም እነዚህ መጽሔቶች የያዙት መልእክት ኢየሱስ በመላው ምድር እንደሚሰበክ የተናገረለት ምሥራች ነው።—ማቴ. 24:14
14. በየትኛው ሥራ በቅንዓት ስንሳተፍ ቆይተናል? ለምንስ?
14 መጽሐፍ ቅዱስ። ወንድም ራስልና አጋሮቹ ጽሑፎችን ለማተም የሚጠቀሙበት ማኅበር ስም በ1896 እንዲለወጥና መጽሐፍ ቅዱስ (ባይብል) የሚለውን ቃል ያካተተ እንዲሆን አደረጉ፤ በመሆኑም የማኅበሩ ስም ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ የሚል ሆነ። የመንግሥቱን ምሥራች በማሰራጨቱ ሥራ ምንጊዜም ዋነኛ መሣሪያችን ሆኖ የሚያገለግለው መጽሐፍ ቅዱስ በመሆኑ ይህ ለውጥ መደረጉ ተገቢ ነበር። (ሉቃስ 24:27) ከማኅበሩ ሕጋዊ ስም ጋር በሚስማማ መንገድ የአምላክ አገልጋዮች መጽሐፍ ቅዱስን በማሰራጨቱና ሰዎች እንዲያነብቡት በማበረታታቱ ሥራ በቅንዓት ሲሳተፉ ቆይተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ዚ ኢምፋቲክ ዳያግሎት የተባለውን በቤንጃሚን ዊልሰን የተዘጋጀ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በ1926 በራሳችን ማተሚያ አትመናል። ከ1942 ጀምሮ ደግሞ ሙሉውን ኪንግ ጄምስ ቨርዥን መጽሐፍ ቅዱስ በ700,000 ያህል ቅጂዎች አትመን አሰራጭተናል። ከሁለት ዓመት በኋላ፣ አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስ ማተም ጀመርን፤ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ስም 6,823 በሚያህሉ ቦታዎች ላይ ይዟል። እስከ 1950 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ250,000 በላይ የዚህን መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች አሰራጭተናል።
15, 16. (ሀ) አዲስ ዓለም ትርጉምን በተመለከተ የምታደንቀው ነገር ምንድን ነው? (“መጽሐፍ ቅዱስን የመተርጎሙን ሥራ ማፋጠን” በሚለው ሣጥን ላይ ተወያዩ።) (ለ) ይሖዋ፣ ልብህን እንዲነካው እንደምትፈልግ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?
15 በ1950 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ወጣ። በ1961 ደግሞ የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ጥራዝ ወጣ። ይህ ትርጉም፣ የይሖዋን ስም በዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፍ ላይ በነበረባቸው ቦታዎች ሁሉ በማስገባት ለይሖዋ ክብር ሰጥቷል። መለኮታዊው ስም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥም በጥቅሶቹ ላይ 237 ጊዜ ይገኛል። አዲስ ዓለም ትርጉም በተቻለ መጠን ትክክለኛ እና ለማንበብ ቀላል እንዲሆን ለማድረግ ሲባል በተለያዩ ጊዜያት ማስተካከያ የተደረገበት ሲሆን በቅርቡም በ2013 ተሻሽሎ ወጥቷል። እስከ 2013 ድረስ ከ201 ሚሊዮን በላይ የአዲስ ዓለም ትርጉም ቅጂዎች በ121 ቋንቋዎች በሙሉም ሆነ በከፊል ታትመዋል።
16 አንዳንዶች አዲስ ዓለም ትርጉምን በቋንቋቸው ሲያነብቡ ምን ተሰማቸው? በኔፓል የሚኖር አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “ቀደም ሲል የነበረን የኔፓል መጽሐፍ ቅዱስ የቆዩ ቃላትን ስለሚጠቀም ብዙዎች ለመረዳት ይከብዳቸው ነበር። አሁን ግን መጽሐፍ ቅዱስ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን በምንጠቀምበት ቋንቋ ስለተተረጎመ ለመረዳት ቀላል ነው።” በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ የምትኖር አንዲት ሴት ደግሞ በሳንጎ ቋንቋ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ ካነበበች በኋላ “የተተረጎመው ልብ በሚነካ መንገድ ነው” በማለት እንባዋ እየወረደ ተናግራለች። እንደዚህች ሴት ሁሉ፣ እያንዳንዳችን የአምላክን ቃል በየቀኑ በማንበብ ይሖዋ ልባችንን እንዲነካው እንደምንፈልግ ማሳየት እንችላለን።—መዝ. 1:2፤ ማቴ. 22:36, 37
ላገኘናቸው መሣሪያዎችና ሥልጠናዎች አመስጋኝ መሆን
17. የሚሰጠንን ሥልጠናዎችና ያገኘናቸውን መሣሪያዎች እንደምታደንቅ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ምን ውጤት ታገኛለህ?
17 ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ በየጊዜው የሚሰጠንን ሥልጠናዎችና ያገኘናቸውን መሣሪያዎች ታደንቃለህ? የአምላክ ድርጅት የሚያዘጋጃቸውን ጽሑፎች ለማንበብ ጊዜ ትመድባለህ? ሌሎችን ለመርዳትስ ትጠቀምበታለህ? እንዲህ የምታደርግ ከሆነ የእህት ኦፓል ቤትለርን ስሜት እንደምትጋራ ታሳያለህ። ጥቅምት 4, 1914 የተጠመቁት እህት ኦፓል እንዲህ ብለዋል፦ “ባለፉት ዓመታት እኔና ባለቤቴ [ኤድዋርድ] በሸክላ ማጫወቻዎች እንዲሁም በምሥክርነት መስጫ ካርዶች ተጠቅመን ሰብከናል። በመጻሕፍት፣ በቡክሌቶችና በመጽሔቶች በመጠቀም ከቤት ወደ ቤት አገልግለናል። እንዲሁም በዘመቻዎችና በሰልፎች ላይ በመካፈል ትራክቶችን አሰራጭተናል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ተመላልሶ መጠየቅ እንድናደርግ ብሎም ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ቤታቸው ሄደን መጽሐፍ ቅዱስ እንድናስጠና ሥልጠና ተሰጠን። በሥራ የተሞላና አስደሳች ሕይወት አሳልፈናል።” ኢየሱስ፣ የመንግሥቱ ተገዢዎች ዘሩን በመዝራትና በመሰብሰብ ረገድ ብዙ ሥራ እንደሚኖራቸው እንዲሁም በአንድነት እንደሚደሰቱ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። እንደ እህት ኦፓል ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች የዚህን ሐሳብ እውነተኝነት መመሥከር ይችላሉ።—ዮሐንስ 4:35, 36ን አንብብ።
18. ምን ታላቅ መብት አግኝተናል?
18 የንጉሡ አገልጋዮች ያልሆኑ ብዙ ሰዎች፣ የአምላክ ሕዝቦችን “ያልተማሩና ተራ ሰዎች” እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸው ይሆናል። (ሥራ 4:13) ሆኖም እስቲ አስበው! ንጉሡ፣ ተራ የሆኑት አገልጋዮቹ በሕትመት ረገድ ትልቅ ሥራ እንዲያከናውኑ ይኸውም በታሪክ ውስጥ በብዙ ቋንቋዎች በመተርጎምና በስፋት በመሰራጨት ረገድ ተወዳዳሪ የሌላቸውን ጽሑፎች እንዲያዘጋጁ አድርጓቸዋል! ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ በእነዚህ መሣሪያዎች ተጠቅመን ምሥራቹን ከብሔራት ሁሉ ለተውጣጡ ሰዎች እንድናሰራጭ አሠልጥኖናል፤ እንዲሁም ለዚህ ሥራ አነሳስቶናል። የእውነትን ዘር በመዝራትና ደቀ መዛሙርትን በመሰብሰብ ረገድ ከክርስቶስ ጋር መሥራት እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!
a ባለፈው አሥር ዓመት ውስጥ ብቻ የይሖዋ ሕዝቦች ከ20 ቢሊዮን በላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን አዘጋጅተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በዓለም ዙሪያ በኢንተርኔት የሚጠቀሙ ከ2.7 ቢሊዮን የሚበልጡ ሰዎች jw.org የተባለውን ድረ ገጻችንን ማግኘት ይችላሉ።
b የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማስተማር አስፋፊዎችን ከረዷቸው ሌሎች የማስጠኛ መጻሕፍት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ የአምላክ በገና (በ1921 የታተመ፤ እንግሊዝኛ)፣ “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” (በ1946 የታተመ)፣ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ (በ1982 የታተመ) እና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት (በ1995 የታተመ)።
c “ቤተሰቦቹ” የተባሉት እነማን እንደሆኑ አሁን ያለንን ትክክለኛ ግንዛቤ በተመለከተ የሐምሌ 15, 2013 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 23 አንቀጽ 13 ላይ የወጣውን ሐሳብ ተመልከት።