ምዕራፍ 17
የመንግሥቱን አገልጋዮች ማሠልጠን
1-3. ኢየሱስ የስብከቱ ሥራ በስፋት እንዲከናወን ሁኔታዎችን ያመቻቸው እንዴት ነው? ይህስ የትኞቹን ጥያቄዎች ያስነሳል?
ኢየሱስ ለሁለት ዓመት ያህል በመላው ገሊላ ሲሰብክ ቆይቷል። (ማቴዎስ 9:35-38ን አንብብ።) ወደተለያዩ ከተሞችና መንደሮች በመሄድ በምኩራቦች አስተምሯል፤ እንዲሁም የመንግሥቱን ምሥራች ሰብኳል። በሚሰብክባቸው ቦታዎች ሁሉ ብዙ ሕዝብ ይከተለው ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ “አዝመራው ብዙ ነው” በማለት ተጨማሪ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ ጠቁሟል።
2 ኢየሱስ የስብከቱ ሥራ በስፋት እንዲከናወን ሁኔታዎችን አመቻችቷል። እንዴት? “የአምላክን መንግሥት እንዲሰብኩ” 12 ሐዋርያቱን በመላክ ነው። (ሉቃስ 9:1, 2) ሐዋርያቱ ይህን ሥራ እንዴት ማከናወን እንደሚችሉ ጥያቄ ተፈጥሮባቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ ሐዋርያቱን ከመላኩ በፊት፣ በሰማይ ያለው አባቱ ለእሱ የሰጠውን ነገር ይኸውም ሥልጠና በመስጠት እንደሚወድዳቸው አሳይቷል።
3 ከዚህ ጋር በተያያዘ በርካታ ጥያቄዎች ወደ አእምሯችን ይመጡ ይሆናል፦ ኢየሱስ ከአባቱ ምን ዓይነት ሥልጠና አግኝቷል? ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የሰጣቸው ምን ዓይነት ሥልጠና ነው? በዛሬው ጊዜስ መሲሐዊው ንጉሥ፣ ተከታዮቹ አገልግሎታቸውን እንዲያከናውኑ የሚያስችላቸው ሥልጠና እየሰጣቸው ነው? ከሆነስ እንዴት?
“የምናገረው ልክ አብ እንዳስተማረኝ” ነው
4. ኢየሱስ ከአባቱ የተማረው መቼና የት ነው?
4 ኢየሱስ፣ አባቱ እንዳስተማረው በግልጽ ተናግሯል። አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ወቅት “እነዚህን ነገሮች የምናገረው ልክ አብ እንዳስተማረኝ [ነው]” ብሏል። (ዮሐ. 8:28) ኢየሱስ ትምህርት ያገኘው መቼና የት ነው? ሥልጠናውን የጀመረው የአምላክ የበኩር ልጅ ሆኖ ከተፈጠረ ብዙም ሳይቆይ መሆን አለበት። (ቆላ. 1:15) ወልድ፣ በሰማይ ካለው አባቱ ጋር ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናት ሲኖር ታላቁን “አስተማሪ” ያዳምጥና የሚያደርገውን ይመለከት ነበር። (ኢሳ. 30:20) በመሆኑም ወልድ ስለ አባቱ ባሕርያት፣ ሥራዎችና ዓላማዎች ከማንም የበለጠ እውቀት ቀስሟል።
5. ወልድ ምድር ላይ ከሚያከናውነው አገልግሎት ጋር በተያያዘ አብ ምን ዓይነት ሥልጠና ሰጥቶታል?
5 ወልድ በምድር ላይ ስለሚያከናውነው አገልግሎት ጊዜው ሲደርስ ይሖዋ አስተምሮታል። በታላቁ አስተማሪና በበኩር ልጁ መካከል ስላለው ግንኙነት የተነገረ አንድ ትንቢት እንመልከት። (ኢሳይያስ 50:4, 5ን አንብብ።) ይሖዋ፣ ልጁን “በየማለዳው” እንደሚያነቃው ትንቢቱ ይገልጻል። ይህ ምሳሌያዊ አገላለጽ፣ ተማሪውን ለማሠልጠን ሲል በማለዳ የሚቀሰቅሰውን አስተማሪ እንድናስብ ያደርገናል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ . . . አገልጋዩን ልክ እንደ አንድ ተማሪ በምሳሌያዊ መንገድ ትምህርት ቤት ወስዶ ምን እና እንዴት እንደሚሰብክ ያስተምረዋል።” ይሖዋ በሰማይ ባለው በዚያ “ትምህርት ቤት” ልጁን ‘ምን እንደሚልና ምን እንደሚናገር’ አስተምሮታል። (ዮሐ. 12:49) በተጨማሪም ወልድ እንዴት ማስተማር እንዳለበት አብ አሠልጥኖታል።a ኢየሱስ ያገኘውን ሥልጠና፣ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት አገልግሎቱን ለማከናወን ብቻ ሳይሆን ተከታዮቹ አገልግሎታቸውን እንዴት እንደሚያከናውኑ ለማሠልጠንም ጭምር ተጠቅሞበታል።
6, 7. (ሀ) ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ምን ዓይነት ሥልጠና ሰጥቷቸዋል? ሥልጠናውስ ምን እንዲያደርጉ አስታጥቋቸዋል? (ለ) ኢየሱስ በዘመናችን ያሉ ተከታዮቹ ምን ዓይነት ሥልጠና እንዲያገኙ አድርጓል?
6 በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው፣ ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የሰጣቸው ሥልጠና ምንድን ነው? በማቴዎስ ምዕራፍ 10 ላይ እንደተገለጸው ለአገልግሎት የሚያስፈልጓቸውን ዝርዝር መመሪያዎች ሰጥቷቸዋል፤ ለምሳሌ፣ የት መስበክ እንዳለባቸው (ቁጥር 5, 6)፣ ምን እንደሚሰብኩ (ቁጥር 7)፣ በይሖዋ የመታመንን አስፈላጊነት (ቁጥር 9, 10)፣ ሰዎችን እንዴት ማነጋገር እንደሚችሉ (ከቁጥር 11-13)፣ ሰዎች ባይቀበሏቸው ምን እንደሚያደርጉ (ቁጥር 14, 15) እንዲሁም ስደት ሲደርስባቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው (ከቁጥር 16-23) አሠልጥኗቸዋል።b ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የሰጣቸው ግልጽ ሥልጠና በመጀመሪያው መቶ ዘመን ምሥራቹን የመስበኩን ሥራ ቅድሚያውን ወስደው እንዲያከናውኑ አስታጥቋቸዋል።
7 ስለ ዘመናችንስ ምን ማለት ይቻላል? የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ፣ ለተከታዮቹ ከሁሉ በላይ ትልቅ ቦታ ያለው ሥራ ሰጥቷቸዋል፤ ሥራው “የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር” መስበክ ነው። (ማቴ. 24:14) ታዲያ ንጉሡ ይህንን በጣም አስፈላጊ ሥራ ማከናወን እንድንችል አሠልጥኖናል? በሚገባ! ንጉሡ ከሰማይ ሆኖ፣ ተከታዮቹ ከጉባኤ ውጭ ላሉ ሰዎች ለመስበክና በጉባኤ ውስጥ ያሏቸውን ለየት ያሉ ኃላፊነቶች ለመወጣት የሚያስችላቸው ሥልጠና እንዲያገኙ አድርጓል።
ወንጌላዊ የሚሆኑ አገልጋዮችን ማሠልጠን
8, 9. (ሀ) የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ዋነኛ ዓላማ ምን ነበር? (ለ) በሳምንቱ መካከል የሚደረገው ስብሰባ በአገልግሎትህ ይበልጥ ውጤታማ እንድትሆን የረዳህ እንዴት ነው?
8 ቀደም ካሉት ዓመታት ጀምሮ የይሖዋ ድርጅት፣ የአምላክን ሕዝቦች ለአገልግሎት ለማሠልጠን በትላልቅ ስብሰባዎች እንዲሁም እንደ አገልግሎት ስብሰባ ባሉ የጉባኤ ስብሰባዎች ሲጠቀም ቆይቷል። ከ1940ዎቹ ዓመታት ወዲህ ግን በዋናው መሥሪያ ቤት ሆነው ሥራውን በኃላፊነት የሚመሩት ወንድሞች የተለያዩ ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም ሥልጠና እንዲሰጥ ዝግጅት ማድረግ ጀመሩ።
9 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት። ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው ይህ ትምህርት ቤት የጀመረው በ1943 ነው። የትምህርት ቤቱ ዓላማ ተማሪዎቹ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ጥሩ ክፍሎችን እንዲያቀርቡ ማሠልጠን ብቻ ነበር? አይደለም። ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የትምህርት ቤቱ ዋነኛ ዓላማ የአምላክ ሕዝቦች የመናገር ስጦታቸውን ይሖዋን በአገልግሎት ለማወደስ እንዲጠቀሙበት ማሠልጠን ነበር። (መዝ. 150:6) በትምህርት ቤቱ የሚካፈሉ ወንድሞችና እህቶች ሁሉ ይበልጥ ውጤታማ የመንግሥቱ አገልጋዮች እንዲሆኑ የሚያስችል ሥልጠና አግኝተዋል። አሁን እንዲህ ዓይነት ሥልጠና የምናገኘው በሳምንቱ መካከል በምናደርገው ስብሰባ አማካኝነት ነው።
10, 11. በአሁኑ ጊዜ በጊልያድ ትምህርት ቤት መካፈል የሚችሉት እነማን ናቸው? የሥልጠናው ዓላማስ ምንድን ነው?
10 ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት። በአሁኑ ጊዜ ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተብሎ የሚጠራው ትምህርት ቤት የተቋቋመው ሰኞ፣ የካቲት 1, 1943 ነው። መጀመሪያ ላይ ትምህርት ቤቱ የተቋቋመበት ዓላማ አቅኚዎችንና ሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሚስዮናዊ ሆነው እንዲያገለግሉ ማሠልጠን ነበር። ከጥቅምት 2011 ወዲህ ግን በትምህርት ቤቱ መሠልጠን የሚችሉት በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሰማሩ ክርስቲያኖች ይኸውም ልዩ አቅኚዎች፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው፣ ቤቴላውያን እንዲሁም በትምህርት ቤቱ ያልተካፈሉ ሚስዮናውያን ብቻ ናቸው።
11 በጊልያድ ትምህርት ቤት የሚሠጠው ሥልጠና ዓላማ ምንድን ነው? በትምህርት ቤቱ አስተማሪ ሆኖ ለረጅም ጊዜ ያገለገለ አንድ ወንድም እንዲህ በማለት መልስ ሰጥቷል፦ “ተማሪዎቹ የአምላክን ቃል ጥልቀት ባለው መንገድ እንዲያጠኑ በማድረግ እምነታቸውን ማጠናከር ብሎም በምድባቸው ላይ የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት የሚያስችሏቸውን መንፈሳዊ ባሕርያት እንዲያዳብሩ መርዳት ነው። በተጨማሪም የሚሰጠው ሥልጠና መሠረታዊ ዓላማ፣ ተማሪዎቹ በወንጌላዊነቱ ሥራ ለመካፈል ይበልጥ ጉጉት እንዲያድርባቸው መርዳት ነው።”—ኤፌ. 4:11
12, 13. በጊልያድ ትምህርት ቤት የሚሰጠው ሥልጠና በዓለም ዙሪያ ከሚከናወነው የስብከት ሥራ ጋር በተያያዘ ምን አስተዋጽኦ አበርክቷል? ምሳሌ ስጥ።
12 በጊልያድ ትምህርት ቤት የሚሰጠው ሥልጠና በዓለም ዙሪያ ከሚከናወነው የስብከት ሥራ ጋር በተያያዘ ምን አስተዋጽኦ አበርክቷል? ከ1943 ጀምሮ ከ8,500 በላይ የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች በዚህ ትምህርት ቤት ሠልጥነዋል፤c እነዚህ ሚስዮናውያንም በዓለም ዙሪያ ከ170 ወደሚበልጡ አገሮች ተልከዋል። ሚስዮናውያኑ በቅንዓት በአገልግሎት በመካፈል ግሩም ምሳሌ የተዉ ከመሆኑም በላይ ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ አሠልጥነዋል፤ በዚህ መንገድ፣ ያገኙትን ሥልጠና ጥሩ አድርገው ተጠቅመውበታል። አብዛኛውን ጊዜ፣ ጥቂት ወይም ምንም የመንግሥቱ አስፋፊዎች በሌሉባቸው አካባቢዎች ሥራው እንዲስፋፋ አድርገዋል።
13 ጃፓንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት፣ በጃፓን በተደራጀ መልክ የሚከናወነው የስብከት እንቅስቃሴ የቆመ ያህል ሆኖ ነበር። በነሐሴ 1949 በአገሪቱ የነበሩት ጃፓናውያን አስፋፊዎች አሥር አይሞሉም። በዚያ ዓመት መጨረሻ አካባቢ ግን በጊልያድ የሠለጠኑ 13 ሚስዮናውያን በጃፓን በስብከቱ ሥራ ተጠምደው ነበር። ከዚያ በኋላም ተጨማሪ ሚስዮናውያን ወደ አገሪቱ ገቡ። መጀመሪያ ላይ መላው ትኩረታቸውን ያደረጉት በትላልቅ ከተሞች ላይ ነበር፤ ውሎ አድሮ ደግሞ ወደ ሌሎች ከተሞች መሄድ ጀመሩ። ሚስዮናውያኑ ተማሪዎቻቸውንም ሆነ ሌሎችን በአቅኚነት አገልግሎት እንዲካፈሉ በጣም ያበረታቷቸው ነበር። ሚስዮናውያኑ በቅንዓት ማገልገላቸው ከፍተኛ ውጤት አስገኝቷል። በአሁኑ ጊዜ በጃፓን ከ216,000 በላይ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ወደ 40 በመቶ የሚሆኑት አቅኚዎች ናቸው!d
14. ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች ምን ያረጋግጣሉ? (“የመንግሥቱን አገልጋዮች የሚያሠለጥኑ ትምህርት ቤቶች” የሚለውን በገጽ 188 ላይ የሚገኝ ሣጥንም ተመልከት።)
14 ሌሎች ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች። የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት፣ ለባለትዳሮች የተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እና ለነጠላ ወንድሞች የተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተማሪዎቹ መንፈሳዊነታቸው እንዲጠነክርና በወንጌላዊነቱ ሥራ ግንባር ቀደም ሆነው በቅንዓት እንዲካፈሉ እየረዷቸው ነው።e እነዚህ ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች በሙሉ፣ ንጉሣችን ተከታዮቹ አገልግሎታቸውን መፈጸም እንዲችሉ ሙሉ በሙሉ እንደሚያስታጥቃቸው ያረጋግጣሉ።—2 ጢሞ. 4:5
ወንድሞች ለየት ያሉ ኃላፊነቶችን እንዲወጡ ማሠልጠን
15. በኃላፊነት ቦታ የሚያገለግሉ ወንዶች በየትኛው አቅጣጫ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ይፈልጋሉ?
15 ኢየሱስ ከአምላክ እንደተማረ የሚገልጸውን የኢሳይያስ ትንቢት አስታውስ። በሰማይ በሚገኘው በዚያ “ትምህርት ቤት” ወልድ “ለደከመው ትክክለኛ ቃል በመናገር እንዴት መልስ መስጠት [እንደሚችል]” ተምሯል። (ኢሳ. 50:4) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት፣ ‘ለደከሙና ሸክም ለከበዳቸው’ ሰዎች እረፍት በመስጠት በሰማይ ያገኘውን ትምህርት ተግባራዊ አድርጓል። (ማቴ. 11:28-30) በኃላፊነት ቦታ የሚያገለግሉ ወንዶች፣ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው የእረፍት ምንጭ መሆን ይፈልጋሉ። በመሆኑም ብቃት ያላቸው ወንድሞች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በማገልገል ረገድ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ለመርዳት ሲባል የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተቋቁመዋል።
16, 17. የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ዓላማ ምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
16 የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት። ይህ ትምህርት ቤት የጀመረው መጋቢት 9, 1959 በሳውዝ ላንሲንግ፣ ኒው ዮርክ ነው። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ አገልጋዮች (በአሁኑ ጊዜ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪዎች ይባላሉ) አንድ ወር በሚፈጀው ኮርስ እንዲካፈሉ ተጋብዘው ነበር። ከጊዜ በኋላ በትምህርት ቤቱ የሚሠጠው ትምህርት ከእንግሊዝኛ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች የተተረጎመ ሲሆን በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ወንድሞች መሰጠት ጀመረ።f
17 የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤትን ዓላማ አስመልክቶ የ1962 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “ብዙዎች ፕሮግራማቸው በጣም በተጣበበበት በዚህ ዓለም በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግል የበላይ ተመልካች የራሱን ሕይወት በተደራጀ መልክ የሚመራ መሆን አለበት፤ እንዲህ ካደረገ በጉባኤው ውስጥ ላሉት ሁሉ ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንዲሁም ለጉባኤው በረከት መሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ጉባኤውን ለመርዳት ሲል የራሱን ቤተሰብ ችላ ማለት አይኖርበትም፤ ከዚህ ይልቅ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ሊሆን ይገባል። በዓለም ዙሪያ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ የጉባኤ አገልጋዮች (የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪዎች) በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት በመካፈል፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ የበላይ ተመልካች ሊያከናውነው እንደሚገባ የሚናገረውን ሥራ ለመፈጸም የሚያስችል ሥልጠና ማግኘት መቻላቸው እንዴት ያለ ግሩም አጋጣሚ ነው!”—1 ጢሞ. 3:1-7፤ ቲቶ 1:5-9
18. ሁሉም የአምላክ ሕዝቦች በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ጥቅም የሚያገኙት እንዴት ነው?
18 የአምላክ ሕዝቦች በሙሉ ከመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ጥቅም እያገኙ ነው። እንዴት? ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች በትምህርት ቤቱ የተማሩትን ተግባራዊ ሲያደርጉ ልክ እንደ ኢየሱስ ለእምነት አጋሮቻቸው የእረፍት ምንጭ ይሆናሉ። አሳቢ የሆነ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ በደግነት ሲያናግርህ፣ ጆሮ ሰጥቶ ሲያዳምጥህ ወይም መጥቶ ሲያበረታታህ ደስ አይልህም? (1 ተሰ. 5:11) ብቃት ያላቸው እንዲህ ያሉ ወንድሞች በእርግጥም ለጉባኤዎቻቸው በረከት ናቸው!
19. የትምህርት ኮሚቴ የትኞቹን ሌሎች ትምህርት ቤቶች በበላይነት ይከታተላል? የእነዚህ ትምህርት ቤቶች ዓላማስ ምንድን ነው?
19 ሌሎች ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች። የበላይ አካሉ የትምህርት ኮሚቴ፣ በድርጅቱ ውስጥ ኃላፊነት ላላቸው ወንድሞች ሥልጠና የሚሰጡ ሌሎች ትምህርት ቤቶችን በበላይነት ይከታተላል። እነዚህ ትምህርት ቤቶች የተዘጋጁት ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ይኸውም የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት ያሏቸውን በርካታ ኃላፊነቶች ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲወጡ ለመርዳት ታስቦ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ሥልጠና፣ ወንድሞች የራሳቸውን መንፈሳዊነት እንዲጠብቁ እንዲሁም ይሖዋ በአደራ የሰጣቸውን ውድ በጎች ሲንከባከቡ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ እንዲያደርጉ ያበረታታቸዋል።—1 ጴጥ. 5:1-3
20. ኢየሱስ እኛን በተመለከተ “ሁሉም ከይሖዋ የተማሩ [ናቸው]” ብሎ መናገር የሚችለው ለምንድን ነው? ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?
20 መሲሐዊው ንጉሥ፣ ተከታዮቹ ጥሩ ሥልጠና እንዲያገኙ እያደረገ እንደሆነ ግልጽ ነው። ሁሉም ሥልጠናዎች የመጡት በተዋረድ ነው፦ ይሖዋ ወልድን አሠልጥኖታል፤ ወልድ ደግሞ ተከታዮቹን አሠልጥኗቸዋል። በመሆኑም ኢየሱስ እኛን በተመለከተ “ሁሉም ከይሖዋ የተማሩ [ናቸው]” ብሎ መናገር ይችላል። (ዮሐ. 6:45፤ ኢሳ. 54:13) ንጉሣችን ከሚያቀርብልን ሥልጠና ሙሉ ጥቅም ለማግኘት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ይህ ሁሉ ሥልጠና የሚሰጥበት ዋነኛ ዓላማ የራሳችንን መንፈሳዊነት ለማጠናከር እንድንችል መሆኑን ምንጊዜም አንዘንጋ፤ ይህም አገልግሎታችንን በተሟላ መንገድ ለማከናወን ያስችለናል።
a ወልድ እንዴት ማስተማር እንዳለበት አብ እንዳሠለጠነው በምን እናውቃለን? እስቲ ይህን አስብ፦ ኢየሱስ በሚያስተምርበት ወቅት በርካታ ምሳሌዎችን መጠቀሙ እሱ ከመወለዱ ከብዙ ዘመናት በፊት የተጻፈ ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል። (መዝ. 78:2፤ ማቴ. 13:34, 35) ከዚህ መመልከት እንደምንችለው ይህንን ትንቢት ያስነገረው ይሖዋ፣ ልጁ በምሳሌዎች ተጠቅሞ እንደሚያስተምር ከረጅም ጊዜ በፊት ያውቅ ነበር። —2 ጢሞ. 3:16, 17
b ከወራት በኋላ ኢየሱስ ‘ሌሎች 70 ሰዎችን በመሾም’ “ሁለት ሁለት አድርጎ” እንዲሰብኩ ላካቸው። ለእነዚህ ሰዎችም ሥልጠና ሰጥቷቸው ነበር።—ሉቃስ 10:1-16
c አንዳንድ ተማሪዎች በጊልያድ ትምህርት ቤት ከአንድ ጊዜ በላይ ተካፍለዋል።
d በጊልያድ የሠለጠኑ ሚስዮናውያን በዓለም ዙሪያ ያከናወኑትን ሥራ በተመለከተ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 23 ተመልከት።
e ለባለትዳሮች በተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እና ለነጠላ ወንድሞች በተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ምትክ የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ተቋቁሟል።
f አሁን በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት የሚካፈሉት ሁሉም ሽማግሌዎች ናቸው፤ ሥልጠናው በየተወሰነ ዓመት የሚሰጥ ሲሆን የሚፈጀው ጊዜም እንደየሁኔታው ይለያያል። ከ1984 ወዲህ የጉባኤ አገልጋዮችም በዚህ ትምህርት ቤት መሠልጠን ጀምረዋል።