ምዕራፍ 41
ተአምራት የፈጸመው በማን ኃይል ነው?
ማቴዎስ 12:22-32 ማርቆስ 3:19-30 ሉቃስ 8:1-3
ኢየሱስ ሁለተኛ የስብከት ጉዞውን ጀመረ
አጋንንትን አስወጣ፤ ይቅር ስለማይባል ኃጢአት አስጠነቀቀ
ኢየሱስ በፈሪሳዊው ስምዖን ቤት ስለ ኃጢአት ይቅርታ ካስተማረ ብዙም ሳይቆይ በገሊላ ሌላ የስብከት ጉዞ ጀመረ። አገልግሎቱን ከጀመረ ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል፤ አሁን የሚጓዘው ብቻውን አይደለም። አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት እንዲሁም “ከክፉ መናፍስትና ከበሽታ የተፈወሱ አንዳንድ ሴቶች” አብረውት ናቸው። (ሉቃስ 8:2) ከእነዚህም መካከል መግደላዊቷ ማርያም፣ ሶስና እና ባሏ የንጉሥ ሄሮድስ አንቲጳስ ሹም የሆነው ዮሐና ይገኙበታል።
ስለ ኢየሱስ ብዙ ሰዎች እያወቁ ሲሄዱ የሚያከናውነው ሥራ ይበልጥ አነጋጋሪ እየሆነ መጣ። ይህ በግልጽ የታየው ጋኔን የያዘውን አንድ ዓይነ ስውርና ዱዳ ሰው ወደ ኢየሱስ አምጥተውት በተፈወሰ ጊዜ ነው። ሰውየው፣ ጋኔኑ ሲለቅቀው ማየትና መናገር ቻለ። ሕዝቡም በጣም ተደንቀው “ይህ የዳዊት ልጅ ይሆን እንዴ?” ይሉ ጀመር።—ማቴዎስ 12:23
ኢየሱስ ባረፈበት ቤት ዙሪያ በጣም ብዙ ሰዎች ስለተሰበሰቡ እሱና ደቀ መዛሙርቱ እህል እንኳ መቅመስ አልቻሉም። ይሁንና ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት “የዳዊት ልጅ” እንደሆነ ያሰቡት ሁሉም አይደሉም። አንዳንድ ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም ከኢየሩሳሌም ድረስ መጥተዋል፤ የመጡት ግን ከኢየሱስ ለመማር ወይም እሱን ለመደገፍ አይደለም። ‘ብዔልዜቡል እንዳለበትና’ የሚሠራውም ‘ከአጋንንት አለቃ’ ጋር ተባብሮ እንደሆነ ለሕዝቡ መናገር ጀመሩ። (ማርቆስ 3:22) የኢየሱስ ዘመዶችም ስለተፈጠረው ግርግር ሲሰሙ ሊይዙት መጡ። ለምን?
በዚህ ወቅት ወንድሞቹ፣ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ ገና አላመኑም። (ዮሐንስ 7:5) በሕዝብ መካከል እንዲህ ያለ ግርግር እንዲፈጠር ያደረገው ሰው፣ ኢየሱስ እንደሆነ ማመን ከብዷቸዋል፤ ምክንያቱም በናዝሬት አብሯቸው ያደገው ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ የለውም። አስተሳሰቡ እንደተዛባ ስለተሰማቸው “አእምሮውን ስቷል” ብለው አሰቡ።—ማርቆስ 3:21
ሆኖም እውነታው ምን ይጠቁማል? ኢየሱስ ጋኔን የነበረበትን ሰው ስለፈወሰው ግለሰቡ አሁን ማየትና መናገር ችሏል። ይህን ማንም ሊክድ አይችልም። በመሆኑም ጸሐፍትና ፈሪሳውያን በኢየሱስ ላይ የሐሰት ክስ በመሰንዘር እሱን ተቀባይነት ለማሳጣት ሞከሩ። ሕዝቡን “ይህ ሰው በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል ካልሆነ በስተቀር አጋንንትን ሊያስወጣ አይችልም” አሏቸው።—ማቴዎስ 12:24
ጸሐፍትና ፈሪሳውያን የሚያስቡትን ስላወቀ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሁሉ ይጠፋል፤ እንዲሁም እርስ በርሱ የሚከፋፈል ከተማ ወይም ቤት ሁሉ ጸንቶ አይቆምም። በተመሳሳይም ሰይጣን ሰይጣንን የሚያስወጣ ከሆነ እርስ በርሱ ተከፋፍሏል ማለት ነው፤ ይህ ከሆነ ታዲያ መንግሥቱ እንዴት ጸንቶ ሊቆም ይችላል?”—ማቴዎስ 12:25, 26
ኢየሱስ ያነሳው ነጥብ እንዴት ምክንያታዊ ነው! አንዳንድ አይሁዳውያን አጋንንትን እንደሚያስወጡ ፈሪሳውያን ያውቃሉ። (የሐዋርያት ሥራ 19:13) ኢየሱስ “እኔ አጋንንትን የማስወጣው በብዔልዜቡል ከሆነ፣ ልጆቻችሁ የሚያስወጧቸው ታዲያ በማን ነው?” አላቸው። በሌላ አባባል በኢየሱስ ላይ የሰነዘሩት ክስ በእነሱም ላይ ሊሰነዘር ይችላል። ኢየሱስ በመቀጠል “ሆኖም አጋንንትን የማስወጣው በአምላክ መንፈስ ከሆነ የአምላክ መንግሥት ሳታስቡት ደርሶባችኋል ማለት ነው” በማለት ተናገረ።—ማቴዎስ 12:27, 28
ኢየሱስ አጋንንትን ማስወጣቱ በሰይጣን ላይ ያለውን የበላይነት የሚያሳይ ማስረጃ መሆኑን በምሳሌ ለማስረዳት እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው በቅድሚያ ሰውየውን ሳያስር ወደ አንድ ብርቱ ሰው ቤት ገብቶ እንዴት ንብረቱን ሊወስድ ይችላል? ቤቱን መዝረፍ የሚችለው እንዲህ ካደረገ ብቻ ነው። ከእኔ ጎን ያልቆመ ሁሉ ይቃወመኛል፤ ከእኔ ጋር የማይሰበስብም ሁሉ ይበትናል።” (ማቴዎስ 12:29, 30) ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ኢየሱስን እየተቃወሙ እንደሆነ በግልጽ እየታየ ነው፤ ይህ ደግሞ የሰይጣን ወኪሎች መሆናቸውን ያሳያል። ሥራውን በይሖዋ ድጋፍ ከሚያከናውነው ከአምላክ ልጅ፣ ሰዎች እንዲርቁና እንዲበተኑ እያደረጉ ነው።
ኢየሱስ የሰይጣን ወኪሎች ለሆኑት ለእነዚህ ተቃዋሚዎች እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው፦ “የሰው ልጆች ምንም ዓይነት ኃጢአት ቢሠሩ ወይም ምንም ዓይነት የስድብ ቃል ቢናገሩ ሁሉም ይቅር ይባልላቸዋል። ይሁን እንጂ መንፈስ ቅዱስን የሚሳደብ ሁሉ ለዘላለም ይቅር አይባልም፤ ከዚህ ይልቅ ለዘላለም የሚጠየቅበት ኃጢአት ይሆንበታል።” (ማርቆስ 3:28, 29) በአምላክ መንፈስ ድጋፍ እንደተከናወነ በግልጽ የሚታየውን ተአምር፣ ሰይጣን እንደፈጸመው ለተናገሩት ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ይህ ሐሳብ ምን ትርጉም እንዳለው አስበው!