ምዕራፍ 21
“ከተማዋ ‘ይሖዋ በዚያ አለ’ ተብላ ትጠራለች”
ፍሬ ሐሳብ፦ ከተማዋና በመዋጮ የተሰጠው መሬት ያላቸው ትርጉም
1, 2. (ሀ) የተወሰነው የምድሪቱ ክፍል ተለይቶ የተቀመጠው ለምንድን ነው? (በመጽሐፉ ሽፋን ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።) (ለ) ራእዩ ለግዞተኞቹ ምን ዋስትና ይሰጣቸዋል?
ሕዝቅኤል ባየው የመጨረሻ ራእይ ላይ ለአንድ ልዩ ዓላማ ተለይቶ የተቀመጠን መሬት በተመለከተ መግለጫ ተሰጠው። ይህ የምድሪቱ ክፍል ተለይቶ የተቀመጠው ለእስራኤል ነገዶች በርስትነት እንዲሰጥ ሳይሆን ለይሖዋ መዋጮ ሆኖ እንዲሰጥ ነው። በተጨማሪም ሕዝቅኤል አስገራሚ ስያሜ ስለተሰጣት አንዲት ከተማ ተነገረው። ይሄኛው የራእዩ ክፍል ለግዞተኞቹ በጣም አስፈላጊ የሆነ ዋስትና ይሰጣቸዋል፦ ወደሚወዷት የትውልድ አገራቸው ሲመለሱ ይሖዋ ከእነሱ ጋር ይሆናል።
2 ሕዝቅኤል ለይሖዋ በመዋጮ የተሰጠውን መሬት በተመለከተ ዝርዝር መግለጫ አስፍሮልናል። በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው የይሖዋ አምላኪዎች ትልቅ ትርጉም የያዘውን ይህን ዘገባ እስቲ እንመርምር።
‘መዋጮ ሆኖ የተሰጠው ቅዱስ ስፍራና ከተማዋ’
3. መዋጮ ሆኖ የተሰጠው መሬት የትኞቹ አምስት ክፍሎች ነበሩት? እነዚህ ክፍሎች ለምን ዓላማ የሚያገለግሉ ነበሩ? (“መዋጮ አድርጋችሁ ለመስጠት የምትለዩት መሬት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
3 ተለይቶ በተቀመጠው የምድሪቱ ክፍል ውስጥ ከሰሜን እስከ ደቡብ 25,000 ክንድ (13 ኪሎ ሜትር) እንዲሁም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ 25,000 ክንድ ርዝመት ያለው መሬት አለ። አራቱም ጎኖቹ እኩል የሆኑት ይህ አራት ማዕዘን መሬት “በመዋጮ የተሰጠው መሬት በአጠቃላይ” ተብሎ ተገልጿል። መሬቱ ሦስት ቦታ ተከፍሏል። የላይኛው ክፍል ለሌዋውያን፣ መካከለኛው ክፍል ደግሞ ለቤተ መቅደሱና ለካህናቱ የተመደበ ነበር። እነዚህ ሁለት ክፍሎች በጋራ “መዋጮ ሆኖ የተሰጠ ቅዱስ ስፍራ” ተብለው ተጠርተዋል። “የቀረው ቦታ” ማለትም አነስ ያለው የታችኛው የመሬቱ ክፍል ቅዱስ ለሆነ አገልግሎት የተለየ አይደለም። ለከተማዋ የተመደበ ነው።—ሕዝ. 48:15, 20
4. ለይሖዋ መዋጮ ሆኖ ስለሚሰጠው መሬት ከሚገልጸው ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?
4 ለይሖዋ መዋጮ ሆኖ ስለሚሰጠው መሬት ከሚገልጸው ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሖዋ በመጀመሪያ መዋጮ ሆኖ የሚሰጠውን መሬት ከለየ በኋላ ለየነገዶቹ የሚከፋፈለውን መሬት በመመደብ ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባው ለዚህ መንፈሳዊ ማዕከል እንደሆነ አመልክቷል። (ሕዝ. 45:1) መሬቱ በዚህ ቅደም ተከተል መከፋፈሉ፣ በግዞት የነበሩትን እስራኤላውያን በሕይወታቸው ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ መስጠት ያለባቸው ለይሖዋ አምልኮ እንደሆነ አስተምሯቸው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ዛሬም በተመሳሳይ የአምላክን ቃል ማጥናትን፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትንና በስብከቱ ሥራ መካፈልን ለመሳሰሉት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባን እንገነዘባለን። ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን ነገር በማስቀደም ረገድ ይሖዋ የተወውን ምሳሌ የምንከተል ከሆነ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ለእሱ በምናቀርበው አምልኮ ላይ ያተኮረ ይሆናል።
“ከተማዋ በመካከሉ ትሆናለች”
5, 6. (ሀ) የከተማዋ ባለቤት ማን ነው? (ለ) ይህች ከተማ ምን ልታመለክት አትችልም? ለምንስ?
5 ሕዝቅኤል 48:15ን አንብብ። ‘ከተማዋም’ ሆነች በከተማዋ ዙሪያ ያለው መሬት ምን ያመለክታሉ? (ሕዝ. 48:16-18) በራእዩ ላይ ይሖዋ ለሕዝቅኤል “የከተማዋ ርስት” ባለቤት ‘የእስራኤል ቤት ሁሉ’ እንደሚሆን ነግሮታል። (ሕዝ. 45:6, 7) በመሆኑም ከተማዋና በዙሪያዋ ያለው መሬት ‘ለይሖዋ የተለየው’ “መዋጮ ሆኖ የተሰጠ ቅዱስ ስፍራ” ክፍል አይደለም። (ሕዝ. 48:9, 20) ይህን በአእምሯችን ይዘን፣ ስለዚህች ከተማ የተሰጠው መግለጫ ለእኛ ምን ትምህርት እንደያዘ እንመልከት።
6 ሆኖም ስለ ከተማዋ ከተሰጠው መግለጫ ምን ትምህርት እንደምናገኝ ከመመልከታችን በፊት ይህች ከተማ ምን ልታመለክት እንደማትችል ማወቅ ያስፈልገናል። ቤተ መቅደሱ የሚገኝባትን ዳግመኛ የተገነባችውን የኢየሩሳሌም ከተማ ልታመለክት አትችልም። ለምን? ምክንያቱም ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከታት ከተማ በውስጧ ቤተ መቅደስ አይኖራትም። በተጨማሪም ከተማዋ ዳግመኛ በተቋቋመው የእስራኤል ምድር ውስጥ የሚገኝን የትኛውንም ከተማ አታመለክትም። ለምን? ምክንያቱም ከግዞት የተመለሱት እስራኤላውያንም ሆኑ ዘሮቻቸው በራእዩ ውስጥ የተገለጸችውን ዓይነት ከተማ ገንብተው አያውቁም። ከዚህም ሌላ ከተማዋ በሰማይ ላይ ያለችን ከተማ ልታመለክት አትችልም። ለምን? ምክንያቱም ለቅዱስ አምልኮ ብቻ ተለይቶ በተመደበ ቦታ ላይ ከተገነቡ ሕንፃዎች በተለየ መልኩ ይህች ከተማ የተገነባችው ‘ቅዱስ ላልሆነ’ ወይም ተራ ለሆነ አገልግሎት በተመደበ ቦታ ላይ ነው።—ሕዝ. 42:20
7. ሕዝቅኤል በራእይ ያያት ከተማ የምታመለክተው ምንን መሆን አለበት? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
7 ታዲያ ሕዝቅኤል በራእይ ያያት ከተማ ምን ታመለክታለች? ሕዝቅኤል ከተማዋን ያየው ስለ ምድሪቱ ባየው ራእይ ላይ እንደሆነ ልብ በል። (ሕዝ. 40:2፤ 45:1, 6) ምድሪቱ የምታመለክተው ምሳሌያዊ የሆነን “ምድር” እንደሆነ የአምላክ ቃል ይጠቁማል፤ በመሆኑም ከተማዋም የምታመለክተው ምሳሌያዊ የሆነን ከተማ መሆን አለበት። “ከተማ” የሚለው ቃል በአብዛኛው ምን ሐሳብ ያስተላልፋል? ይህ ቃል፣ በርካታ ሰዎች ተደራጅተውና አንድ ዓይነት መዋቅር ፈጥረው አብረው የሚኖሩበትን ቦታ ያመለክታል። በመሆኑም ሕዝቅኤል የተመለከታት አራቱም ጎኗ እኩል የሆነው ከተማ፣ በሚገባ የተደራጀን መስተዳድር የምታመለክት ይመስላል።
8. የዚህ መስተዳድር የግዛት ክልል ምንድን ነው? እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
8 የዚህ መስተዳድር የግዛት ክልል ምንድን ነው? የሕዝቅኤል ራእይ ከተማዋ የምትገኘው በምሳሌያዊው ምድር ውስጥ እንደሆነ ይገልጻል። በመሆኑም ይህ መስተዳድር በዛሬው ጊዜ ሥራውን የሚያከናውነው የአምላክ ሕዝቦች የእንቅስቃሴ ቀጠና በሆነው በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ ነው። ከተማዋ የተገነባችው ቅዱስ ባልሆነ ወይም ለተራ አገልግሎት በሚውል መሬት ላይ መሆኑስ ምን ይጠቁማል? ከተማዋ የምታመለክተው ሰማያዊ የሆነን መስተዳድር ሳይሆን በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ጥቅም ሲባል የተቋቋመውን ምድራዊ መስተዳድር መሆኑን ያስታውሰናል።
9. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ይህ ምድራዊ መስተዳድር እነማንን ያቀፈ ነው? (ለ) ኢየሱስ በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት ምን ያደርጋል?
9 ይህ ምድራዊ መስተዳድር እነማንን ያቀፈ ነው? በሕዝቅኤል ራእይ ላይ፣ በከተማዋ መስተዳድር ውስጥ ግንባር ቀደም ኃላፊነት ያለው ሰው “አለቃው” ተብሎ ተጠርቷል። (ሕዝ. 45:7) “አለቃው” በሕዝቡ መካከል የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግል ቢሆንም ካህን ወይም ሌዋዊ አይደለም። ይህ አለቃ በዛሬው ጊዜ የጉባኤ የበላይ ተመልካቾች ሆነው የሚያገለግሉትን፣ በተለይም ቅቡዓን ያልሆኑትን ሽማግሌዎች ያስታውሰናል። ‘ከሌሎች በጎች’ የተውጣጡት እነዚህ አሳቢ የሆኑ መንፈሳዊ እረኞች በክርስቶስ ሰማያዊ መስተዳድር ሥር የሚሠሩ ትሑት ምድራዊ አገልጋዮች ናቸው። (ዮሐ. 10:16) ኢየሱስ በመጪው የሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት፣ ብቃት ያላቸውን ሽማግሌዎች “በምድር ሁሉ ላይ መኳንንት” አድርጎ ይሾማቸዋል። (መዝ. 45:16) እነሱም በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት በሰማያዊው መንግሥት አመራር ሥር ሆነው የአምላክን ሕዝቦች ያገለግላሉ።
“ይሖዋ በዚያ አለ”
10. የከተማዋ ስም ማን ነው? ይህ ስያሜ ምን ዋስትና ይሰጣል?
10 ሕዝቅኤል 48:35ን አንብብ። የከተማዋ ስም “ይሖዋ በዚያ አለ” የሚል ነው። ይህ ስያሜ ይሖዋ በከተማዋ ውስጥ እንደሚገኝ የሚያሳይ ዋስትና ነው። ይሖዋ በማዕከላዊ ቦታ ላይ የምትገኘውን ይህችን ከተማ ለሕዝቅኤል ሲያሳየው፣ ለግዞተኞቹ ‘ዳግመኛ ከእናንተ ጋር እሆናለሁ!’ የሚል መተማመኛ የሰጣቸው ያህል ነበር። እንዴት ያለ አስደሳች ዋስትና ነው!
11. ሕዝቅኤል ስለ ከተማዋም ሆነ ስለ ከተማዋ ስም ከተመለከተው ራእይ ምን ትምህርት እናገኛለን?
11 ይህ የሕዝቅኤል ትንቢት ምን ትምህርት ይሰጠናል? የከተማዋ ስም ይሖዋ አሁንም ሆነ ለዘላለም፣ ምድር ላይ ካሉት ታማኝ አገልጋዮቹ ጋር እንደሚኖር ማረጋገጫ ይሰጠናል። በተጨማሪም ትልቅ ትርጉም ያዘለው ይህ ስም አንድን ወሳኝ እውነታ አጉልቶ ያሳያል፤ ከተማዋ የተቋቋመችው ለየትኛውም ሰው ሥልጣን ለመስጠት ሳይሆን ፍቅራዊና ምክንያታዊ የሆኑትን የይሖዋ መንገዶች ለማስፈጸም ነው። ለምሳሌ ይሖዋ፣ መስተዳድሩ በሰብዓዊ አመለካከት ላይ ተመሥርቶ ምድሪቱን እንዲያከፋፍል ሥልጣን አልሰጠውም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ፣ ዝቅ ተደርገው የሚታዩትን ጨምሮ ለአገልጋዮቹ በሙሉ የሰጠውን ድርሻ ወይም ቦታ አስተዳዳሪዎቹ እንዲያከብሩ ይፈልጋል።—ሕዝ. 46:18፤ 48:29
12. (ሀ) የዚህች ከተማ አንዱ አስደናቂ ገጽታ ምንድን ነው? ይህስ ምን ያመለክታል? (ለ) ይህ ገጽታ ለክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ምን አስፈላጊ ማሳሰቢያ ያስተላልፋል?
12 “ይሖዋ በዚያ አለ” የተባለችው ከተማ ያላት ሌላ አስደናቂ ገጽታ ምንድን ነው? በጥንት ዘመን የነበሩ ከተሞች ለመከላከያነት የሚያገለግሉ ቅጥሮች የነበሯቸው ሲሆን ቅጥሮቹ ጥቂት በሮች ብቻ ነበሯቸው። ይህች ከተማ ግን 12 በሮች አሏት። (ሕዝ. 48:30-34) በሮቹ ብዙ መሆናቸው (በአራቱም ጎን ሦስት ሦስት በሮች አሉ) የዚህች ከተማ አስተዳዳሪዎች ለአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ተደራሽና በቀላሉ የሚቀረቡ መሆናቸውን ያመለክታል። ከዚህም ሌላ ከተማዋ 12 በሮች ያሏት መሆኑ ለሁሉም፣ ማለትም “ለእስራኤል ቤት ሁሉ” ክፍት መሆኗን ያሳያል። (ሕዝ. 45:6) ወደ ከተማዋ በቀላሉ መግባት የሚቻል መሆኑ ለክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች አንድ አስፈላጊ የሆነ ማሳሰቢያ ያስተላልፋል። ይሖዋ፣ የበላይ ተመልካቾች በመንፈሳዊው ገነት ለሚኖሩ ሁሉ ጊዜ እንዲሰጡና በቀላሉ የሚቀረቡ እንዲሆኑ ይጠብቅባቸዋል።
የአምላክ ሕዝቦች “የአምልኮ ሥርዓት ለመፈጸም” ይመጣሉ፣ ‘ከተማዋንም ያገለግላሉ’
13. ይሖዋ ሕዝቦቹ የሚካፈሉባቸውን የተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች በተመለከተ ምን ገልጿል?
13 እስቲ ወደ ሕዝቅኤል ዘመን መለስ እንበልና ስለ ምድሪቱ አከፋፈል ያየውን ራእይ አስመልክቶ ምን ተጨማሪ ዝርዝር ጉዳዮችን እንደመዘገበ እንመልከት። ይሖዋ ሕዝቦቹ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች እንደሚካፈሉ ተናግሯል። ‘በመቅደሱ የሚያገለግሉት’ ካህናት መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ እንዲሁም ይሖዋን ለማገልገል ወደ እሱ ይቀርባሉ። “በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚያገለግሉት ሌዋውያን” ደግሞ “በውስጡ የሚካሄደውን አገልግሎትና መሠራት ያለበትን ሥራ ሁሉ” ያከናውናሉ። (ሕዝ. 44:14-16፤ 45:4, 5) በተጨማሪም በከተማዋ አቅራቢያ የሚሠሩ ሠራተኞች አሉ። እነዚህ ሠራተኞች እነማን ናቸው?
14. በከተማዋ አቅራቢያ የሚሠሩት ሠራተኞች ምን ያስታውሱናል?
14 በከተማዋ አቅራቢያ የሚሠሩት ሠራተኞች “ከሁሉም የእስራኤል ነገዶች የተውጣጡ ሰዎች” ናቸው። የእነዚህ ሰዎች የሥራ ድርሻ ድጋፍ መስጠት ነው። “ከተማዋን ለሚያገለግሉ ምግብ” የሚሆን እህል የማምረት ሥራ ተሰጥቷቸዋል። (ሕዝ. 48:18, 19) ይህ ዝግጅት እኛ ያለንን የትኛውን አጋጣሚ ያስታውሰናል? በዛሬው ጊዜ በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች የሚሰጡትን አገልግሎት እንዲሁም ‘ከእጅግ ብዙ ሕዝብ’ መካከል ግንባር ቀደም ሆነው አመራር የመስጠት ኃላፊነት ያለባቸው ወንድሞች የሚያከናውኑትን አገልግሎት የመደገፍ አጋጣሚ አላቸው። (ራእይ 7:9, 10) እንዲህ ያለውን ድጋፍ መስጠት የምንችልበት ዋነኛው መንገድ ታማኙ ባሪያ የሚሰጠውን መመሪያ በፈቃደኝነት መቀበል ነው።
15, 16. (ሀ) የሕዝቅኤል ራእይ ምን ሌላ ዝርዝር መረጃ ይዟል? (ለ) እኛስ በተመሳሳይ የትኞቹን ነገሮች የማከናወን አጋጣሚ አለን?
15 በሕዝቅኤል ራእይ ላይ የተጠቀሰው ሌላ ዝርዝር መረጃ ደግሞ አገልግሎታችንን በተመለከተ ጥሩ ትምህርት ይሰጠናል። ይሖዋ ከሌዊ ነገድ ውጭ ያሉት 12 ነገዶች በሁለት ቦታዎች፣ ማለትም በቤተ መቅደሱ ግቢና በከተማዋ የግጦሽ መሬት ላይ የሚያከናውኑት ነገር እንደሚኖር ተናግሯል። በእነዚህ ቦታዎች ላይ የሚያከናውኑት ነገር ምንድን ነው? በቤተ መቅደሱ ግቢ ውስጥ ሁሉም ነገዶች ለይሖዋ መሥዋዕት በማቅረብ “የአምልኮ ሥርዓት” ይፈጽማሉ። (ሕዝ. 46:9, 24) ከዚህም ሌላ የሁሉም ነገዶች አባላት መሬቱን በማረስ ለከተማዋ ድጋፍ ይሰጣሉ። እነዚህ ሠራተኞች ከሚያከናውኑት ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን?
16 በዛሬው ጊዜ የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት በሕዝቅኤል ራእይ ላይ ከተጠቀሱት ነገሮች ጋር የሚመሳሰል ነገር የማከናወን አጋጣሚ አላቸው። አንደኛ፣ የውዳሴ መሥዋዕት በማቅረብ ይሖዋን “በቤተ መቅደሱ” ያመልካሉ። (ራእይ 7:9-15) ይህን የሚያደርጉት በስብከቱ ሥራ በመካፈልና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እምነታቸውን በይፋ በመግለጽ ነው። ተቀዳሚ ኃላፊነታቸው፣ በዚህ መንገድ ለይሖዋ አምልኮ ማቅረብ እንደሆነ ይገነዘባሉ። (1 ዜና 16:29) በተጨማሪም ብዙዎቹ የአምላክ ሕዝቦች በተለያዩ መንገዶች ለአምላክ ድርጅት ድጋፍ ይሰጣሉ። ለምሳሌ የስብሰባ አዳራሾችንና የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎችን በመገንባትና በመጠገን እንዲሁም የይሖዋ ድርጅት በሚያካሂዳቸው ሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶች በመካፈል እርዳታ ያበረክታሉ። ሌሎች ደግሞ የገንዘብ መዋጮ በማድረግ እነዚህን ፕሮጀክቶች ይደግፋሉ። ይህን ሁሉ ሥራ በማከናወን በምሳሌያዊ ሁኔታ መሬቱን የሚያርሱት “ለአምላክ ክብር” ማምጣት ስለሚፈልጉ ነው። (1 ቆሮ. 10:31) ይሖዋ ‘እንዲህ ባሉት መሥዋዕቶች እጅግ እንደሚደሰት’ ስለሚያውቁ ሥራቸውን በቅንዓትና በደስታ ያከናውናሉ። (ዕብ. 13:16) አንተስ በእነዚህ አጋጣሚዎች ሙሉ በሙሉ እየተጠቀምክ ነው?
“አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን”
17. (ሀ) ወደፊት የሕዝቅኤል ራእይ በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው? (ለ) በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት በከተማ ከተመሰለው መስተዳድር ጥቅም የሚያገኙት እነማን ናቸው?
17 ሕዝቅኤል በመዋጮ ስለተሰጠው መሬት ያየው ራእይ ወደፊት በላቀ ሁኔታ ፍጻሜውን ያገኝ ይሆን? አዎ! ሕዝቅኤል “የይሖዋ መቅደስ” የሚገኝበት “መዋጮ ሆኖ የተሰጠ ቅዱስ ስፍራ” የተባለው የመሬቱ ክፍል የሚገኘው በምድሪቱ እምብርት ላይ እንደሆነ መግለጹን ልብ በል። (ሕዝ. 48:10) ይህም ከአርማጌዶን በኋላ በየትኛውም የምድር ክፍል ብንኖር ይሖዋ ከእኛ ጋር እንደሚኖር ዋስትና ይሆነናል። (ራእይ 21:3) በምድር ላይ የአምላክን ሕዝቦች ለማገልገል የሚሾሙትን ሰዎች የሚያመለክተው በከተማ የተመሰለው መስተዳድር፣ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ‘የአዲሱ ምድር’ ማለትም የአዲሱ ኅብረተሰብ አባላት ለሚሆኑ ሁሉ ፍቅራዊ አመራር በመስጠት የግዛት አድማሱን በመላው ምድር ላይ ያስፋፋል።—2 ጴጥ. 3:13
18. (ሀ) በከተማ የተመሰለው መስተዳድር ከአምላክ አገዛዝ ጋር እንደሚስማማ እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) የከተማዋ ስም ምን ያረጋግጥልናል?
18 በከተማ የተመሰለው መስተዳድር ከአምላክ አገዛዝ ጋር ሙሉ በሙሉ እንደሚስማማ እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? የአምላክ ቃል እንደሚያሳየው 12 በሮች ያሏት ምድራዊቷ ከተማ፣ 12 በሮች ያሏት ሰማያዊ ከተማ ነጸብራቅ ነች፤ ይህች ሰማያዊ ከተማ ከክርስቶስ ጋር የሚገዙትን 144,000 ቅቡዓን ያቀፈችው አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ነች። (ራእይ 21:2, 12, 21-27) ይህም ምድራዊው መስተዳድር በሰማይ ያለው የአምላክ መንግሥት ከሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ጋር ሙሉ በሙሉ እንደሚስማማና እነዚህን ውሳኔዎች በጥንቃቄ እንደሚያስፈጽም ያመለክታል። አዎ፣ “ይሖዋ በዚያ አለ” የሚለው የከተማዋ ስም ንጹሕ አምልኮ በገነት ውስጥ ለዘላለም ጸንቶ እንደሚኖር ያረጋግጥልናል። ወደፊት የሚጠብቀን ጊዜ ምንኛ አስደሳች ነው!