ምዕራፍ 7
ለሕይወት የአምላክ ዓይነት አመለካከት አለህ?
“የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነው።”—መዝሙር 36:9
1, 2. (ሀ) ይሖዋ የትኛውን ውድ ስጦታ ሰጥቶናል? (ለ) ይሖዋ ከሁሉ የተሻለውን ሕይወት መምራት እንድንችል ምን ሰጥቶናል?
ይሖዋ ለሁላችንም ግሩም የሆነ ስጦታ ሰጥቶናል። ይህ ስጦታ ሕይወት ነው። (ዘፍጥረት 1:27) ይሖዋ ከሁሉ የተሻለውን ሕይወት እንድንመራ ይፈልጋል። በመሆኑም ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ የሚረዱ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሰጥቶናል። “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር [ለመለየት]” በእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች መጠቀም ይኖርብናል። (ዕብራውያን 5:14) ይህን ስናደርግ ይሖዋ አስተሳሰባችንን እንዲቀርጸው እየፈቀድን ነው። አምላክ የሰጠንን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተላችን የተሻለ ሕይወት ለመምራት ይረዳናል፤ ይህንን ስንመለከት ደግሞ እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑ እንገነዘባለን።
2 በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙን ነገሮች የተወሳሰቡ ሊሆኑ ይችላሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቀጥተኛ ሕግ ያልተሰጠባቸው ሁኔታዎች ብዙ ጊዜ ያጋጥሙናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ዓይነት ሕክምና ያስፈልገን ይሆናል፤ ሕክምናው ደም መውሰድን የሚጨምር ከሆነ በዚህ ረገድ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል። በዚህ ወቅት ይሖዋን የሚያስደስት ውሳኔ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ለሕይወትና ለደም ያለውን አመለካከት የሚያሳዩ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሚገባ ከተረዳን፣ ንጹሕ ሕሊና ይዘን ለመኖር የሚያስችለን ጥሩ ውሳኔ ማድረግ እንችላለን። (ምሳሌ 2:6-11) እስቲ ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።
አምላክ ለሕይወትና ለደም ምን አመለካከት አለው?
3, 4. (ሀ) አምላክ ስለ ደም ያለውን አመለካከት ለሰው ልጆች ያሳወቀው እንዴት ነው? (ለ) ደም ምንን ይወክላል?
3 ደም ቅዱስ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ ምክንያቱም ደም ሕይወትን ያመለክታል። ሕይወት ደግሞ በይሖዋ ፊት ውድ ነው። ቃየን ወንድሙን በገደለው ወቅት ይሖዋ “የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ እየጮኸ ነው” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 4:10) የአቤል ደም ሕይወቱን ያመለክታል፤ ስለሆነም ይሖዋ ስለ አቤል ደም ሲናገር ስለ አቤል ሕይወት መግለጹ ነበር።
4 በኖኅ ዘመን ከደረሰው የጥፋት ውኃ በኋላ ሰዎች ሥጋ መብላት እንደሚችሉ አምላክ ነግሯቸው ነበር። ሆኖም “ሕይወቱ ማለትም ደሙ በውስጡ ያለበትን ሥጋ . . . አትብሉ” የሚል ቀጥተኛ መመሪያ ሰጥቷቸዋል። (ዘፍጥረት 9:4) የኖኅ ዘሮች በሙሉ ይህን ትእዛዝ መከተል አለባቸው፤ ይህ እኛንም ይጨምራል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በይሖዋ ዓይን ደም ሕይወትን ይወክላል። እኛም ለደም ተመሳሳይ አመለካከት ሊኖረን ይገባል።—መዝሙር 36:9
5, 6. የሙሴ ሕግ ይሖዋ ለሕይወትና ለደም ያለውን አመለካከት የሚያሳየው እንዴት ነው?
5 ይሖዋ ለሙሴ በሰጠው ሕግ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ማንኛውም ሰው . . . ምንም ዓይነት ደም ቢበላ፣ ደም በሚበላው ሰው ላይ በእርግጥ ፊቴን አጠቁርበታለሁ፤ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። ምክንያቱም የሥጋ ሕይወት ያለው በደሙ ውስጥ ነው።”—ዘሌዋውያን 17:10, 11
6 የሙሴ ሕግ ማንኛውም ሰው ሥጋ ለመብላት እንስሳ በሚያርድበት ወቅት ደሙን መሬት ላይ ማፍሰስ እንዳለበት ይናገራል። ይህን ማድረጉ የእንስሳውን ሕይወት ለፈጣሪው ለይሖዋ መልሶ እንደሰጠው የሚያሳይ ነው። (ዘዳግም 12:16፤ ሕዝቅኤል 18:4) ሆኖም እስራኤላውያን በእንስሳው ሥጋ ውስጥ አንዲት ጠብታ ደም እንኳ እንዳይቀር የተለየ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ማለት አልነበረም። የእንስሳውን ደም ለማፍሰስ የቻሉትን ያህል ጥረት ካደረጉ በንጹሕ ሕሊና ሥጋውን መብላት ይችላሉ። ለእንስሳው ደም አክብሮት ማሳየታቸው የሕይወት ምንጭ ለሆነው ለይሖዋ አክብሮት እንዳላቸው የሚያሳይ ነው። እስራኤላውያን ለኃጢአታቸው ማስተሰረያ እንዲሆን የእንስሳት መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ሕጉ ያዝዝ ነበር።—ተጨማሪ ሐሳብ 19ን እና 20ን ተመልከት።
7. ዳዊት ለደም አክብሮት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?
7 ዳዊት ከፍልስጤማውያን ጋር እየተዋጋ በነበረበት ወቅት ያደረገው ነገር ለደም አክብሮት እንዳለው ያሳያል። ከዳዊት ጋር የነበሩት ሰዎች ዳዊት ውኃ በጣም እንደጠማው አወቁ፤ በመሆኑም በጠላት ሠራዊት ወደተያዘው አደገኛ ክልል በመግባት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ውኃ አመጡለት። ዳዊት ግን ውኃውን ለመጠጣት ፈቃደኛ አልሆነም፤ ከዚህ ይልቅ “ውኃውን ለይሖዋ አፈሰሰው።” ከዚያም “ይሖዋ ሆይ፣ ይህን ማድረግ ፈጽሞ የማላስበው ነገር ነው! ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው የሄዱትን የእነዚህን ሰዎች ደም ልጠጣ ይገባል?” በማለት ተናገረ። ዳዊት ውኃውን እንደ ሰዎቹ ሕይወት ቆጥሮታል። ሕይወትና ደም በአምላክ ፊት ምን ያህል ውድ እንደሆኑ ተገንዝቦ ነበር።—2 ሳሙኤል 23:15-17
8, 9. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ለደም ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?
8 የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ስላልሆኑ የእንስሳት መሥዋዕት ማቅረብ አይጠበቅባቸውም ነበር። ያም ቢሆን በሕጉ ውስጥ ካሉት መመሪያዎች መካከል የተወሰኑትን መታዘዝ ነበረባቸው። ከእነዚህም መካከል ‘ከደም ስለ መራቅ’ የተሰጠው መመሪያ ይገኝበታል፤ ክርስቲያኖች ለደም ተገቢው አመለካከት እንዳላቸው ማሳየት ይጠበቅባቸው ነበር። ‘ከደም መራቃቸው’ ከፆታ ብልግና ወይም ከጣዖት አምልኮ የመራቅን ያህል አስፈላጊ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29
9 በዛሬው ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ክርስቲያኖች የሕይወት ምንጭ ይሖዋ እንደሆነ እንዲሁም ሕይወት ሁሉ የእሱ መሆኑን እናውቃለን። በተጨማሪም ደም ቅዱስ እንደሆነና ሕይወትን እንደሚያመለክት እንገነዘባለን። በመሆኑም ደምን ለሕክምና መጠቀምን በተመለከተ ማንኛውንም ውሳኔ ስናደርግ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ግምት ውስጥ እናስገባለን።
ደምን ለሕክምና መጠቀም
10, 11. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች ደምን ወይም አራቱን ዋና ዋና የደም ክፍሎች ስለ መውሰድ ምን አመለካከት አላቸው? (ለ) እያንዳንዱ ክርስቲያን ከየትኞቹ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የራሱን ውሳኔ ማድረግ አለበት?
10 የይሖዋ ምሥክሮች ‘ከደም ራቁ’ የሚለው ትእዛዝ ደምን ከመብላት ወይም ከመጠጣት መቆጠብን ብቻ የሚያመለክት እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። ‘ከደም መራቅ’ ሲባል ለሕክምና ደም ከመውሰድ፣ ደም ከመስጠት እንዲሁም የራሳችን ደም ከሰውነታችን ወጥቶ ከቆየ በኋላ እንደገና ወደ ሰውነታችን እንዲገባ ከማድረግ መቆጠብን ይጨምራል። አራቱን ዋና ዋና የደም ክፍሎች ይኸውም ቀይ የደም ሴልን፣ ነጭ የደም ሴልን፣ ፕሌትሌትንና ፕላዝማንም አንወስድም።
11 ከእነዚህ አራት ዋና ዋና የደም ክፍሎች የሚወጡ ንዑሳን ክፍልፋዮችም አሉ። እነዚህን ንዑሳን ክፍልፋዮች መውሰድን በተመለከተ እያንዳንዱ ክርስቲያን የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። በተመሳሳይም የራስን ደም ከሚጠቀሙ የሕክምና ዘዴዎች ጋር በተያያዘ ግለሰቡ የራሱን ውሳኔ ማድረግ አለበት። እያንዳንዱ ክርስቲያን ቀዶ ሕክምና፣ የጤና ምርመራ ወይም ደሙን ቀድቶ ማስቀመጥ የማይጠይቅ ሌላ ዓይነት ሕክምና በሚደረግለት ወቅት የራሱ ደም ጥቅም ላይ ስለሚውልበት መንገድ በግለሰብ ደረጃ ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል።—ተጨማሪ ሐሳብ 21ን ተመልከት።
12. (ሀ) ይሖዋ ለሕሊና በተተዉ ጉዳዮች ረገድ ለምናደርገው ውሳኔ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለምንድን ነው? (ለ) ከሕክምና ጋር በተያያዘ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ ምን ይረዳናል?
12 ይሖዋ ለሕሊና በተተዉ ጉዳዮች ረገድ ለምናደርገው ውሳኔ ትልቅ ቦታ ይሰጣል? አዎ። ለምን? ምክንያቱም ውሳኔያችን በልባችን ውስጥ ምን እንዳለ ያሳያል፤ ይሖዋ ደግሞ ሐሳባችንና አንድን ውሳኔ ለማድረግ የተነሳሳንበት ምክንያት ያሳስበዋል። (ምሳሌ 17:3ን እና 24:12ን አንብብ።) በመሆኑም ከሕክምና ጋር የተያያዘ ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ ይሖዋ እንዲመራን መጸለይ እንዲሁም ስለ ሕክምናው ለማወቅ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። ከዚያም በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናችንን በመጠቀም ውሳኔ እናደርጋለን። ‘አንተ በእኔ ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?’ ብለን ሌሎችን መጠየቅ ተገቢ አይደለም፤ ሌሎችም ቢሆኑ ምን ዓይነት ውሳኔ ማድረግ እንዳለብን ሊነግሩን አይገባም። እያንዳንዱ ክርስቲያን “የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል።”—ገላትያ 6:5፤ ሮም 14:12
የይሖዋ ሕጎች ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳያሉ
13. ይሖዋ ደምን በተመለከተ ከሰጠን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ስለ እሱ ምን እንማራለን?
13 ይሖዋ ማንኛውንም ነገር የሚያዝዘን ለራሳችን ጥቅም ነው፤ ትእዛዛቱ ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳያሉ። (መዝሙር 19:7-11) ይሁንና ይሖዋን የምንታዘዘው ትእዛዛቱ ስለሚጠቅሙን ብቻ አይደለም። ይሖዋን የምንታዘዘው ስለምንወደው ነው። እሱን ስለምንወደው ደም ከመውሰድ እንቆጠባለን። (የሐዋርያት ሥራ 15:20) እንዲህ ማድረጋችን ለጤናችንም ጠቃሚ ነው። በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች ደም መውሰድ አንዳንድ የጤና ችግሮችን ሊያስከትል እንደሚችል ተገንዝበዋል፤ ብዙ ሐኪሞችም ያለደም ቀዶ ሕክምና ማድረግ ለታካሚዎቻቸው ጤንነት የተሻለ እንደሆነ ይስማማሉ። በእርግጥም የይሖዋ ትእዛዛት ጥበብና ፍቅር የሚንጸባረቅባቸው ናቸው።—ኢሳይያስ 55:9ን አንብብ፤ ዮሐንስ 14:21, 23
14, 15. (ሀ) ይሖዋ ሕዝቦቹን ከአደጋ ለመጠበቅ ምን ዓይነት ሕጎች ሰጥቷቸዋል? (ለ) ከእነዚህ ሕጎች በስተ ጀርባ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
14 የአምላክ ሕጎች ምንጊዜም ቢሆን ሕዝቡን የሚጠቅሙ ናቸው። ይሖዋ የጥንቶቹ እስራኤላውያን ከባድ አደጋ እንዳይደርስባቸው ለመከላከል የሚረዱ ሕጎችን አውጥቶ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ቤት የሚሠራ ሰው በጣሪያው ዙሪያ መከታ እንዲያደርግ የሚያዝዝ ሕግ ነበር፤ ይህም አንድ ሰው ከጣሪያው ላይ ወድቆ ጉዳት እንዳይደርስበት ይከላከላል። (ዘዳግም 22:8) እስራኤላውያን ከእንስሶቻቸው ጋር የተያያዘ ሕግም ተሰጥቷቸው ነበር። የመዋጋት አመል ያለበት በሬ ያለው ሰው፣ በሬው ሰዎችን እንዳይወጋ ወይም እንዳይገድል የመጠበቅ ኃላፊነት ነበረበት። (ዘፀአት 21:28, 29) አንድ እስራኤላዊ እነዚህን ሕጎች ሳይታዘዝ በመቅረቱ ምክንያት የሰው ሕይወት ቢጠፋ ተጠያቂ ይሆን ነበር።
15 እነዚህ ሕጎች ሕይወት በይሖዋ ፊት ውድ እንደሆነ ያስገነዝቡናል። ታዲያ ይህን ማወቃችን ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል? እኛም ቤታችን ውስጥ ለአደጋ የሚያጋልጥ ነገር እንዳይኖር በማድረግ፣ መኪናችንን በተገቢው መንገድ በመያዝና በጥንቃቄ በማሽከርከር እንዲሁም ከመጥፎ መዝናኛ በመራቅ ለሕይወት አክብሮት እንዳለን ማሳየት ይኖርብናል። አንዳንድ ሰዎች በተለይ ደግሞ ወጣቶች ምንም ጉዳት እንደማይደርስባቸው ስለሚያስቡ ለአደጋ የሚያጋልጡ ነገሮችን ያደርጋሉ። ይሖዋ ግን እንዲህ እንድናደርግ አይፈልግም። ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ሕይወት አክብሮት እንድናሳይ ይፈልጋል።—መክብብ 11:9, 10
16. አምላክ ለውርጃ ምን አመለካከት አለው?
16 የሁሉም ሰው ሕይወት በይሖዋ ፊት ውድ ነው። በእናቱ ማህፀን ውስጥ ያለ ሕፃን ሕይወትም እንኳ በይሖዋ ዓይን ትልቅ ቦታ አለው። በሙሴ ሕግ መሠረት፣ አንድ ሰው ሳያስበው በእርጉዝ ሴት ላይ ጉዳት ቢያደርስና ሴትየዋ ወይም ልጇ ቢሞቱ ጉዳት ያደረሰውን ግለሰብ ይሖዋ በነፍስ ግድያ ይጠይቀው ነበር። ግለሰቡ ነፍስ ያጠፋው ሳያስበው ቢሆንም የሰው ሕይወት ስለጠፋ ካሳ መከፈል ነበረበት። (ዘፀአት 21:22, 23ን አንብብ።) አምላክ በማህፀን ውስጥ ያለ ሕፃንን ሕይወትም እንኳ እንደ ማንኛውም ሰው ሕይወት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። ከዚህ አንጻር አምላክ ስለ ውርጃ ምን አመለካከት ያለው ይመስልሃል? በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕፃናት በእናታቸው ማህፀን ውስጥ እንደሚገደሉ ሲመለከት አምላክ ምን የሚሰማው ይመስልሃል?
17. ይሖዋን ከማወቋ በፊት ፅንስ ያስወረደችን ሴት የትኛው ሐሳብ ሊያጽናናት ይችላል?
17 አንዲት ሴት፣ ይሖዋ ስለ ውርጃ ያለውን አመለካከት ከማወቋ በፊት ፅንስ አስወርዳ የነበረ ቢሆንስ? የኢየሱስን መሥዋዕት መሠረት በማድረግ ይሖዋ ይቅር እንደሚላት እርግጠኛ መሆን ትችላለች። (ሉቃስ 5:32፤ ኤፌሶን 1:7) ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት ስህተት የሠራች ሴት በድርጊቷ ከልቧ እስከተጸጸተች ድረስ በጥፋተኝነት ስሜት ልትዋጥ አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ መሐሪና ሩኅሩኅ [ነው]። ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ በደላችንን ከእኛ አራቀ” ይላል።—መዝሙር 103:8-14
ጥላቻን አስወግዱ
18. የጥላቻ ስሜትን ለማስወገድ የቻልነውን ያህል ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
18 ከአምላክ ላገኘነው የሕይወት ስጦታ ያለን አክብሮት የሚጀምረው ከአስተሳሰባችን ነው። ለሕይወት ያለን አክብሮት ለሌሎች ሰዎች ከሚኖረን አመለካከት ጋር ግንኙነት አለው። ሐዋርያው ዮሐንስ “ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 3:15) ለምሳሌ፣ አንድ ሰው ብዙም ደስ አይለን ይሆናል፤ ውሎ አድሮ ይህ ስሜት እያደገ ሄዶ ሳይታወቀን ለግለሰቡ ጥላቻ ሊያድርብን ይችላል። ለአንድ ሰው ጥላቻ ካዳበርን ደግሞ ግለሰቡን በንቀት ዓይን ልንመለከተው፣ በሐሰት ልንወነጅለው ይባስ ብሎም እንዲሞት እስከ መመኘት ልንደርስ እንችላለን። ይሖዋ ስለ ሌሎች ምን ስሜት እንዳለን ያውቃል። (ዘሌዋውያን 19:16፤ ዘዳግም 19:18-21፤ ማቴዎስ 5:22) ለአንድ ሰው የጥላቻ ስሜት እንዳለን ካስተዋልን ይህን ለማስወገድ የቻልነውን ያህል ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል።—ያዕቆብ 1:14, 15፤ 4:1-3
19. ለሕይወት አክብሮት እንዳለን ማሳየት የምንችልበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው?
19 ለሕይወት አክብሮት እንዳለን የምናሳይበት ሌላም መንገድ አለ። መዝሙር 11:5 “ይሖዋ . . . ዓመፅን የሚወድን ማንኛውንም ሰው ይጠላል” ይላል። ዓመፅ በሚንጸባረቅባቸው መዝናኛዎች የምንዝናና ከሆነ ይህ ዓመፅን እንደምንወድ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። የዓመፀኝነት መንፈስ የሚንጸባረቅባቸው ቃላት፣ ሐሳቦችና ምስሎች ወደ አእምሯችን ማስገባት እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ከዚህ ይልቅ አእምሯችንን ንጹሕና ሰላማዊ በሆኑ ሐሳቦች መሙላት እንፈልጋለን።—ፊልጵስዩስ 4:8, 9ን አንብብ።
ለሕይወት አክብሮት ከሌላቸው ድርጅቶች ራቁ
20-22. (ሀ) ይሖዋ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለውን ዓለም የሚመለከተው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ ሕዝቦች ‘የዓለም ክፍል እንዳልሆኑ’ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
20 በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም ለሕይወት አክብሮት የለውም፤ በዚህም ምክንያት ይሖዋ ይህን ዓለም የደም ዕዳ እንዳለበት ማለትም በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተጠያቂ እንደሆነ አድርጎ ይመለከተዋል። ባለፉት መቶ ዘመናት የፖለቲካ ኃይሎች፣ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮችን ጨምሮ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆነዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን የፖለቲካ ኃይሎች ወይም መንግሥታት አስፈሪና ጨካኝ እንደሆኑ አራዊት አድርጎ ይገልጻቸዋል። (ዳንኤል 8:3, 4, 20-22፤ ራእይ 13:1, 2, 7, 8) በዛሬው ጊዜ የጦር መሣሪያ ሽያጭ ትልቅ ንግድ ሆኗል። ሰዎች እነዚህን ገዳይ መሣሪያዎች በመሸጥ ከፍተኛ ትርፍ ያጋብሳሉ። በእርግጥም “መላው ዓለም . . . በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው።”—1 ዮሐንስ 5:19
21 እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን “የዓለም ክፍል አይደሉም።” የይሖዋ ሕዝቦች በፖለቲካዊ ጉዳዮችም ሆነ በጦርነት አይካፈሉም። ክርስቲያኖች የሰው ሕይወት አያጠፉም፤ የሰው ሕይወት የሚያጠፉ ድርጅቶችንም አይደግፉም። (ዮሐንስ 15:19፤ 17:16) ክርስቲያኖች ስደት ሲደርስባቸው በምላሹ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ አይሞክሩም። ኢየሱስ ጠላቶቻችንንም ጭምር መውደድ እንዳለብን አስተምሮናል።—ማቴዎስ 5:44፤ ሮም 12:17-21
22 የሃይማኖት ድርጅቶችም በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ተጠያቂ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ ስለምታመለክተው ስለ ታላቂቱ ባቢሎን ሲናገር “በእሷም ውስጥ የነቢያት፣ የቅዱሳንና በምድር ላይ የታረዱ ሰዎች ሁሉ ደም ተገኝቷል” ይላል። ይሖዋ “ሕዝቤ ሆይ . . . ከእሷ ውጡ” በማለት ያዘዘን ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። የይሖዋ አገልጋዮች ከሐሰት ሃይማኖቶች ሙሉ በሙሉ ይርቃሉ።—ራእይ 17:6፤ 18:2, 4, 24
23. ከታላቂቱ ባቢሎን መውጣት ሲባል ምን ማለት ነው?
23 ከታላቂቱ ባቢሎን ‘እንወጣለን’ ሲባል የየትኛውም የሐሰት ሃይማኖት ድርጅት አባል አለመሆናችንን ግልጽ እናደርጋለን ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አባል ከነበርንበት ሃይማኖት መዝገብ ላይ ስማችን እንዲሰረዝ ማድረግ ያስፈልገናል። ይሁንና ይህ ብቻ በቂ አይደለም። የሐሰት ሃይማኖቶች የሚያከናውኗቸውን መጥፎ ድርጊቶች መጥላትና ከእነዚህ መራቅ ይኖርብናል። የሐሰት ሃይማኖቶች የሥነ ምግባር ብልግናን፣ ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ መግባትንና ስግብግብነትን አያወግዙም፤ እንዲያውም ይደግፋሉ። (መዝሙር 97:10ን አንብብ፤ ራእይ 18:7, 9, 11-17) በዚህም የተነሳ ባለፉት ዘመናት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
24, 25. ይሖዋን ማወቃችን ውስጣዊ ሰላምና ጥሩ ሕሊና የሚያስገኝልን እንዴት ነው?
24 ማናችንም ብንሆን ይሖዋን ከማወቃችን በፊት፣ የሰይጣን ዓለም የሚያከናውናቸውን መጥፎ ነገሮች በሆነ መንገድ እንደግፍ ነበር። አሁን ግን ለውጥ አድርገናል። በቤዛው ላይ እምነት አሳድረናል፤ ራሳችንንም ለአምላክ ወስነናል። በመሆኑም ‘ከይሖዋ ዘንድ የመታደስ ዘመን መጥቶልናል።’ አምላክን እያስደሰትን እንደሆነ ስለምናውቅ ውስጣዊ ሰላምና ጥሩ ሕሊና አለን።—የሐዋርያት ሥራ 3:19፤ ኢሳይያስ 1:18
25 በአንድ ወቅት፣ ለሕይወት አክብሮት የማያሳይ ድርጅት አባል የነበርን ቢሆንም እንኳ ይሖዋ በቤዛው አማካኝነት ይቅር ይለናል። ከይሖዋ ያገኘነውን የሕይወት ስጦታ ከልባችን እናደንቃለን። በመሆኑም ሌሎች ስለ ይሖዋ እንዲማሩ፣ ከሰይጣን ዓለም የተለዩ እንዲሆኑና ከአምላክ ጋር የቅርብ ዝምድና እንዲመሠርቱ ለመርዳት የቻልነውን ያህል እንጥራለን፤ ይህን ስናደርግ ከአምላክ ላገኘነው የሕይወት ስጦታ አድናቆት እንዳለን እናሳያለን።—2 ቆሮንቶስ 6:1, 2
ስለ አምላክ መንግሥት ለሌሎች ተናገሩ
26-28. (ሀ) ይሖዋ ለሕዝቅኤል ምን ዓይነት ተልእኮ ሰጥቶት ነበር? (ለ) በዛሬው ጊዜስ ይሖዋ ምን እንድናደርግ ይፈልጋል?
26 ይሖዋ በጥንቷ እስራኤል፣ ለነቢዩ ሕዝቅኤል አንድ ተልእኮ ሰጥቶት ነበር፤ ሕዝቅኤል ኢየሩሳሌም በቅርቡ እንደምትጠፋ ሕዝቡን እንዲያስጠነቅቅ እንዲሁም ከጥፋቱ ለመትረፍ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዲያስተምራቸው ታዝዞ ነበር። ሕዝቅኤል ሕዝቡን ሳያስጠነቅቅ ቀርቶ ቢጠፉ ይህ ነቢይ ለሕዝቡ ሕይወት በይሖዋ ፊት ተጠያቂ ይሆናል። (ሕዝቅኤል 33:7-9) ሕዝቅኤል፣ የተሰጠውን አስፈላጊ መልእክት ለሕዝቡ ለማድረስ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ለሕይወት አክብሮት እንዳለው አሳይቷል።
27 ይሖዋ የሰይጣን ዓለም በቅርቡ እንደሚጠፋ ሰዎችን የማስጠንቀቅ ኃላፊነት ሰጥቶናል፤ በተጨማሪም ሰዎች ከጥፋቱ ተርፈው ወደ አዲሱ ዓለም መግባት እንዲችሉ ስለ እሱ እንድናስተምራቸው አዞናል። (ኢሳይያስ 61:2፤ ማቴዎስ 24:14) ይህን መልእክት ለሰዎች ለማድረስ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። እኛም እንደ ጳውሎስ “ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ [ነኝ]፤ ምክንያቱም የአምላክን ፈቃድ ሁሉ ለእናንተ ከመንገር ወደኋላ አላልኩም” ብለን መናገር እንፈልጋለን።—የሐዋርያት ሥራ 20:26, 27
28 እርግጥ ነው፣ ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር ለሕይወትና ለደም አክብሮት ማሳየታችን ብቻ በቂ አይደለም። በይሖዋ ፊት ምንጊዜም ንጹሕ ሆነን መኖርም ያስፈልገናል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ እንመረምራለን።