ለሁሉ የሚሆን ተመጣጣኝ ቤዛ
“የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።”—ማቴዎስ 20:28
1, 2. (ሀ) አምላክ ለሰዎች ከሰጣቸው ሥጦታዎች ሁሉ የሚበልጠው ቤዛው ነው ለማለት የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) ቤዛውን መመርመራችን ምን ጥቅም ያመጣልናል?
ቤዛ አምላክ ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ሥጦታዎች ሁሉ የሚበልጥ ነው። ‘በቤዛ ባገኘነው ነፃነት’አማካኝነት ‘የበደል ሥርየት’ አግኝተናል። (ኤፌሶን 1:7) በሰማይም ሆነ በገነቲቱ ምድር ለምናገኘው የዘላለም ሕይወት ተስፋ መሰረቱ ይኸው ቤዛ ነው። (ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 3:16) በቤዛው ምክንያት ክርስቲያኖች ሁሉ አሁንም እንኳን ቢሆን በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም ለማግኘት ችለዋል።—ራዕይ 7:14, 15
2 ስለዚህ ቤዛው ሊጨበጥ የማይችል ወይም ለመረዳት በጣም የረቀቀ ነገር አይደለም። ቤዛው በመለኮታዊ ሥርዓቶች ላይ ሕጋዊ መሠረት ያለው ስለሆነ ተጨባጭና የተረጋገጡ ጥቅሞችን ሊያስገኝ ይችላል። የዚህን መሠረተ ትምህርት አንዳንድ ገጽታዎች ለመረዳት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። (2 ጴጥሮስ 3:16) ቢሆንም ቤዛው አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ከፍተኛ ፍቅር ስለሚያሳይ ይህንን መሠረተ ትምህርት በጥሞና መመርመር በጣም ይጠቅማል። የቤዛውን ትርጉም መረዳት የማይመረመረውን የአምላክ “ብልጽግና፣ ጥበብና እውቀት” አንዱን ገጽታ መረዳት ማለት ነው።—ሮሜ 5:8፤ 11:33
መልስ የሚገባቸው አከራካሪ ጥያቄዎች
3. ቤዛ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አምላክ የሰው ልጆችን ኃጢአት እንዲሁ ይቅር ሊል የማይችለው ለምንድን ነው?
3 ቤዛ ያስፈለገው ለልጆቹ የሕመም፣ የበሽታ፣ የሐዘንና የሥቃይ ቅርስ ያወረሰው የመጀመሪያው ሰው አዳም ኃጢአት ስለሠራ ነው። (ሮሜ 8:20) የአዳም ተወላጆች በሙሉ አለፍጽምና የወረሱና “የቁጣ ልጆች” በመሆናቸው ሞት የሚገባቸው ናቸው። (ኤፌሶን 2:3፤ ዘዳግም 32:5)አምላክ ከሥርዓት ውጭ በሆነ ስሜት ተሸንፎ የሰው ልጆችን በሙሉ ይቅር ለማለት አይችልም። “የኃጢአት ደመወዝ ሞት መሆኑን የአምላክ ቃል ያረጋግጣል።” (ሮሜ 6:23) አምላክ የሰው ልጆችን ኃጢአተኝነት እንዲሁ ይቅር ቢል የራሱን የጽድቅ ደረጃዎች፣ የራሱን የፍትሕ ሕግ መሻር ይሆንበታል። (ኢዮብ 40:8) የአምላክ ዙፋን ግን “መሠረቱ ጽድቅና ፍርድ ነው።” (መዝሙር 89:14) አምላክ ከጽድቅ አቋሙ ትንሽም ቢሆን ፈቀቅ ቢል ሕገ ወጥነትን ማበረታታትና የጽንፈ ዓለማዊ ልዕልና ደረጃውን ማዳከም ይሆንበታል።—ከመክብብ 8:11 ጋር አወዳድር።
4. የሰይጣን ዐመጽ ምን አከራካሪ ጥያቄዎችን አስነሳ?
4 በተጨማሪም የሠይጣን ዐመጽ ያስነሳውና በሰው ልጅ ላይ ከደረሰው አበሳ የበለጠ አሳሳቢ የሆኑ ሌሎች አከራካሪ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ነበረባቸው። ሠይጣን ይሖዋን ውሸታምና ለፍጥረቶቹ እውቀትና ነፃነት የሚከለክል ጨቋኝ ገዥ ነው ብሎ በመክሰስ በጥሩ ስሙ ላይ ጥቁር ነጥብ ጥሎበት ነበር። (ዘፍጥረት 3:1-5) ከዚህም በላይ አምላክ ምድርን ጻድቅ በሆኑ ሰዎች ለመሙላት የነበረውን ዓላማ ሰይጣን ያከሸፈበት መስሎ ስለታየ አምላክ ዓላማውን ለማስፈጸም የማይችል አስመስሎት ነበር። (ዘፍጥረት 1:28፤ ኢሳይያስ 55:10, 11) በተጨማሪም ሰይጣን የአምላክን ታማኝ አገልጋዮች ለስስት ጥቅማቸው ሲሉ ብቻ ነው የሚያገለግሉት ብሎ እስከመወንጀል ድረስ ተዳፍሮ ነበር። ችግር ቢደርስበት ለአምላክ ታማኝ ሆኖ የሚቆም አንድም አይኖርም ብሎ ፎከረ።—ኢዮብ 1:9-11
5. አምላክ የሰይጣንን የግድድር ጥያቄዎች ችላ ብሎ ለማለፍ ያልቻለው ለምንድን ነው?
5 ይህ ሁሉ ግድድር በቸልታ ሊታለፍ አይችልም። አከራካሪ ጥያቄዎቹ ምላሽ ሳይሰጣቸው ከቀረ ለአምላክ አገዛዝ የሚሰጠው ድጋፍና ትምክህት እየተመናመነ ይሄዳል። (ምሳሌ 14:28) ሕግና ሥርዓት እየጠፋ ከሄደ በጽንፈ ዓለሙ በሙሉ ብጥብጥ አይነግስምን? ስለዚህ አምላክ ለራሱና ለጽድቅ መንገዶቹ ሲል ልዕልናውን ማረጋገጥ ግዴታ ሆነበት። ታማኝ አገልጋዮቹ በማንም ሳይናወጡ ለእርሱ በታማኝነት እንደሚቆሙ እንዲያስመሰክሩ ለመፍቀድ ተገደደ። በዚህ ምክንያት ለታላላቆቹ ጥያቄዎች ቅድሚያ በሚሰጥ መንገድ የኃጢአተኞቹን የሰው ልጆች ችግር መፍታት አስፈለገው። ከዘመናት በኋላ ለእሥራኤላውያን “መተላለፍህን ስለ እኔ ስል የምደመስስ እኔ ነኝ” ብሎአል።—ኢሳይያስ 43:25
ቤዛ፣ መሸፈኛ ነው
6. መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የሰው ልጆችን ያዳነበትን መንገድ ለመግለጽ የተጠቀመባቸው ቃሎች ምንድን ናቸው?
6 መዝሙር 92:5 ላይ “[ይሖዋ (አዓት)] ሆይ፣ ሥራህ እጅግ ትልቅ ነው፣ አሳብህም እጅግ ጥልቅ ነው” የሚል ቃል እናነባለን። ስለዚህ አምላክ ለሰው ልጅ ያደረገውን ነገር ለመረዳትና ለማስተዋል ጥረት ያስፈልገናል ማለት ነው። (ከመዝሙር 36:5, 6 ጋር አወዳድር) መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ድንቅ ሥራዎች ከተለያየ አንጻር በሚገልጹ የተለያዩ ቃላት ወይም ምሳሌዎች በመጠቀም ጉዳዩን እንድናስተውል ስለሚረዳን በጣም ደስ ይለናል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለቤዛው ሲገልጽ መዋጀት፣ መታረቅ፣ ለውጥ፣ መቤዠት፣ ሥርየት በሚሉ ቃላት ይጠቀማል። (መዝሙር 49:8፤ ዳንኤል 9:24፤ ገላትያ 3:13፤ ቆላስይስ 1:20፤ ዕብራውያን 2:17) ጉዳዩን ከሁሉ በተሻለ ሁኔታ የሚገልጸው አነጋገር ግን በማቴዎስ 20:28 ላይ የሚገኘው ቃል ነው፡- “የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።”
7, 8. (ሀ) ቤዛ ተብለው ከተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) ቤዛ ተመጣጣኝነትን የሚጠይቅ መሆኑን በምሳሌ አስረዳ?
7 ቤዛ ምንድን ነው? ሊትሮን የተባለው የግሪክኛ ቃል “መፍታት” የሚል ትርጉም ካለው ግሥ የመጣ ነው። ይህም የጦር እሥረኞችን ለማስፈታት የሚከፈለውን ገንዘብ የሚያመለክት ቃል ነው። በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ግን ቤዛ ተብሎ የተተረጎመው ቃል ኮፈር ሲሆን “መሸፈን” ወይም “ማልበስ” የሚል ትርጉም ካለው ግሥ የተወሰደ ነው። ለምሳሌ አምላክ ኖህን መርከቡን ቅጥራን እንዲያለብሰው (ካፋር) ነግሮት ነበር። (ዘፍጥረት 6:14) ስለዚህ ከዚህ አንጻር ሲታይ ቤዛ መክፈል ወይም ማስተሠረይ ማለት ኃጢአት መሸፈን ማለት ነው።—መዝሙር 65:3
8 የአዲስ ኪዳን መንፈሣዊ መዝገበ ቃላት የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ኮፈር “ሁልጊዜ እኩልነትን” ወይም ተመጣጣኝነት ያመለክታል። ስለዚህ የቃል ኪዳኑ ታቦት ሽፋን (ካፖሬት) ከራሱ ከታቦቱ ጋር በቅርጽ ይተካከል ወይም ይመጣጠን ነበር። በተመሳሳይም ለኃጢአት ሥርየት ለማስገኘት መለኮታዊው ፍትሕ ‘ነፍስ ስለ ነፍስ፣ ዐይን ስለ ዐይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ፣ እጅ ስለ እጅ፣ እግር ስለ እግር’ እንዲሰጥ ይጠይቅ ነበር። (ዘዳግም 19:21) ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ከወንጀሉ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ሌላ ቅጣት በመስጠት ሕጉ የሚጠይቀውን የፍትሕ እርምጃ መፈጸም ይቻል ነበር። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ዘፀአት 21:28-32 አንድ በሬ አንድን ሰው ወግቶ ቢገድለው ስለሚደረገው ነገር ይነግረናል። የበሬው ባለቤት ስለ በሬው ተዋጊነት እያወቀ ተገቢውን ጥንቃቄ ባያደርግ የተገደለውን ሰው ነፍስ በራሱ ነፍስ እንዲከፍል ወይም እንዲሸፍን ይደረጋል። ባለቤቱ ለነፍስ ግድያው ኃላፊ የሆነው በከፊል ብቻ ከሆነስ? በደሉን የሚሸፍንለት ኮፈር ያስፈልገዋል። የተሾሙት ዳኞች የቤዛ ዋጋ የሚሆን መቀጫ ይወስኑበታል።
9. ለቤዛ የሚከፈለው ዋጋ ተመጣጣኝ መሆን እንደሚገባው የሚያሳየን የትኛው የእሥራኤላውያንን በኩራት የተመለከተ ሁኔታ ነው?
9 ከቤዛ ጋር የሚዛመደው ሌላው የዕብራይስጥ ቃል ደግሞ “መዋጀት” የሚል መሠረታዊ ትርጉም ያለው ፓዳህ የተባለው ቃል ነው። ዘኁልቅ 3:39-51 የመዋጂያ ዋጋ ምን ያህል የተስተካከለ መሆን እንደሚገባው በምሳሌ ያስረዳናል። አምላክ በ1513 ከ.ዘ.አ.በ በማለፍ በዓል ዕለት የእሥራኤላውያንን የበኩር ልጆች ከሞት ስላዳናቸው የራሱ ንብረት አድርጎአቸዋል። ስለዚህ እያንዳንዱ የበኩር ልጅ በቤተመቅደሱ እንዲያገለግል ሊጠይቅ ይችል ነበር። ከዚህ ይልቅ ግን አምላክ “ቤዛ” (ፒድዮን፣ ከፓዳህ የተወሰደ ስም በመቀበል “ሌዋውያን በእሥራኤል ልጆች በኩር ሁሉ ፋንታ . . . ለእኔ ይሁኑ” ሲል አዘዘ። ይሁን እንጂ መጠኑ የተስተካከለ መሆን ነበረበት። የሌዊ ነገዶች ሲቆጠሩ 22,000 ወንዶች ሆኑ። ቀጥሎም የእሥራኤል የበኩር ልጆች ተቆጠሩና 22,273 ወንዶች ሆኑ። የ273 በኩራት ብልጫ ስላለ ለእነዚህ ወንዶች የቤተመቅደስ አገልግሎት ሊቀርላቸው የሚችለው ለእያንዳንዱ ወንድ የአምስት ሰቅል ቤዛ ከተከፈለ በኋላ ነበር።
ተመጣጣኝ ቤዛ
10. የእንስሳት መሥዋዕት የሰዎችን ኃጢአት ለመሸፈን በቂ ለመሆን የማይችለው ለምንድን ነው?
10 ከላይ የተመለከትነው ምሳሌ እንደሚያሳየው ቤዛ ለሚተካው ወይም ለሚሸፍነው ነገር በመጠኑ የሚተካከል መሆን አለበት። ከአቤል ጀምሮ የነበሩት የእምነት ሰዎች ያቀረቡአቸው የእንስሳት መሥዋዕቶች የሰዎችን ኃጢአት ሊሸፍኑ አልቻሉም። ምክንያቱም የሰው ልጆች ከእንስሳት የበለጡ ናቸው። (መዝሙር 8:4-8) በዚህም ምክንያት ጳውሎስ “የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና” ብሎ ለመጻፍ ችሎአል። እንደነዚህ ያሉት መሥዋዕቶች ለሚመጣው መሥዋዕት ሰዎችን የሚያዘጋጁ ጥላነት ወይም ምሳሌነት ያላቸው መሥዋዕቶች ብቻ ነበሩ።—ዕብራውያን 10:1-4
11, 12. (ሀ) የሰውን ኃጢአተኛነት ለመሸፈን በሺህ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መሥዋዕት ሆነው መሞት የማያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? (ለ) ‘ተመጣጣኝ ቤዛ’ ሊሆን የሚችለው ማን ብቻ ሆነ? የሞተውስ ለምን ዓላማ ነው?
11 አምላክ በአዳም ላይ የበየነው የሞት ፍርድ የሰውን ዘር በሙሉ የሚኮንን ስለሆነ ይህ ጥላ የተደረገለት ቤዛ ከአዳም ጋር የሚመጣጠን መሆን ይኖርበታል። 1 ቆሮንቶስ 15:22 “ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ” ይናገራል። ስለዚህ ለአዳም ግለሰብ ተወላጆች በሙሉ ምትክ የሚሆኑ በሺህ ሚልዮን የሚቆጠሩ ግለሰቦች መሥዋዕታዊ ሞት መሞት አያስፈልጋቸውም። “ኃጢአት በአንድ ሰው [በአዳም] ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት።” (ሮሜ 5:12) እንግዲህ “ሞት [በአንድ]ሰው በኩል ስለ መጣ” የሰው ዘርም በአንድ ሰው ሊቤዥ ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 15:21
12 ቤዛ ሊሆን የሚችለው ሰው ከአዳም ጋር ሙሉ በሙሉ የሚተካከል ሥጋና ደም የሆነ ፍጹም ሰው መሆን ይኖርበታል። (ሮሜ 5:14) መንፈሳዊ ፍጡር ወይም “ሰውም አምላክም” የሆነ አካል የፍትሕ ሚዛን የሚጠይቀውን ያዛባል። ከአዳም ጋር ሙሉ በሙሉ የሚተካከል “ተመጣጣኝ ቤዛ” ሊያቀርብ የሚችለው የአዳም የሞት ፍርድ የማይመለከተው ፍጹም የሆነ ሰው ብቻ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:6)a ይህ “ኋለኛ አዳም” ሕይወቱን በፈቃዱ በመሰዋት ‘የመጀመሪያውን ሰው የአዳምን’ የኃጢአት ደመወዝ ሊከፍል ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 15:45፤ ሮሜ 6:23
13, 14. (ሀ) አዳምና ሔዋን ከቤዛው ጥቅም ያገኛሉን? አስረዳ። (ለ) ቤዛው የአዳምን ዘሮች የሚጠቅመው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።
13 ይሁን እንጂ አዳምም ሆነ ሔዋን ከቤዛው ምንም ዓይነት ጥቅም አያገኙም። የሙሴ ሕግ የሚከተለውን መሠረታዊ ሥርዓት ይጨምር ነበር፦ “ሞት የተፈረደበትን ነፍሰ ገዳዩንም ለማዳን የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ፤ እርሱ ፈጽሞ ይገደል።” (ዘኁልቅ 35:31) አዳም አልተታለለም፤ ስለዚህ ኃጢአቱ ሆን ብሎ በፈቃደኝነት የፈጸመው ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 2:14) ተወላጆቹ በሙሉ አለፍጽምና ስለወረሱና በዚህም ምክንያት የሞት ፍርድ ስለመጣባቸው ልጆቹን እንደገደላቸው ይቆጠራል። አዳም ፍጹም ሰው ሆኖ ሳለ የአምላክን ሕግ ለመጣስ ሆን ብሎ ስለመረጠ መሞት ይገባው እንደነበረ ግልጽ ነው። ይሖዋ አዳምን የቤዛው ተጠቃሚ ቢያደርገው የራሱን የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓት መጣስ ይሆንበታል። የአዳም ኃጢአት ደመወዝ ቢከፈል ግን በአዳም ተወላጆች ላይ የተበየነው የሞት ፍርድ የሚወገድበትን መንገድ ያሰናዳል። (ሮሜ 5:16) ከሕግ አንጻር ስንመለከተው የኃጢአት የአጥፊነት ኃይል ከሥሩ ይቆረጣል ማለት ነው። ቤዛ የሚሆነው ሰው ‘ለእያንዳንዱ ሰው ሞትን ይቀምሳል።’ ኃጢአት በአዳም ልጆች ላይ ያስከተለውን ጠንቅ በሙሉ ይሸከማል።—ዕብራውያን 2:9፤ 2 ቆሮንቶስ 5:21፤ 1 ጴጥሮስ 2:24
14 ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል በመቶ የሚቆጠሩ ሠራተኞች ያሉት አንድ ትልቅ ፋብሪካ አለ እንበል። የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ አጭበርባሪ ሰው ሆነና ድርጅቱን አከሰረው። ፋብሪካው ተዘጋ። አሁን እነዚያ ሁሉ በመቶ የሚቆጠሩ ሠራተኞች አለሥራ ስለቀሩ ለመኖሪያ ወጪያቸው የሚከፍሉት ገንዘብ አጡ። በዚህ አንድ ሰው ምግባረ ብልሹነት ምክንያት የትዳር ጓደኞቻቸው፣ ልጆቻቸውና ገንዘብ የሚከፍሉአቸው ሰዎች ሁሉ ችግር ላይ ወደቁ! በዚህ ጊዜ አንድ ሀብታም የሆነ በጎ አድራጊ ሰው መጣና የኩባንያውን ዕዳ በሙሉ ከፍሎ ፋብሪካው እንዲከፈት ያደርጋል። የዚህ የፋብሪካው ዕዳ መከፈል ለሠራተኞቹ ሁሉ፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለባለእዳዎቻቸው ሁሉ ሙሉ እፎይታ አመጣላቸው። ይሁን እንጂ የቀድሞው ሥራ አስኪያጅ ከዚህ አዲስ ብልጽግና ሊካፈል ይችላልን? አይችልም፤ ምክንያቱም በወንጀሉ ምክንያት በእሥር ቤት የሚገኝ ስለሆነ ወደ ሥራው ሊመለስ አይችልም! በተመሳሳይም የአዳም ዕዳ መሻሩ በሚልዮን ለሚቆጠሩ ዘሮቹ ጥቅም ያስገኛል፤ ለአዳም ግን ምንም ጥቅም አያመጣለትም።
ቤዛውን የሚከፍለው ማነው?
15. ለሰው ልጆች የሚከፈለውን ቤዛ ሊያስገኝ የሚችለው ማን ብቻ ነው? ለምንስ?
15 መዝሙራዊው “ሰው [የራሱን ወንድም (አዓት)] መቤዠትም ሆነ ለሕይወቱ ቤዛ የሚሆነውን ዋጋ ለእግዚአብሔር መክፈል አይችልም። ለሰው ሕይወት የሚከፈለው ዋጋ እጅግ ብዙ ነው የቱንም ያህል ቢከፈል በቂ አይሆንም” በማለት ሐዘኑን ገልጾአል። አዲሱ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ የቤዛው ዋጋ “ከመክፈል አቅሙ በላይ ነው” ይላል። (መዝሙር 49:7, 8) ታዲያ ቤዛ የሚያስገኝልን ማነው? ‘የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደውን በግ’ ሊሰጠን የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። (ዮሐንስ 1:29) አምላክ የሰው ልጆችን ለማዳን መልአክ አልላከም።’ ‘በተለይ የሚወደውን’ አንድያ ልጁን በመላክ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ መሥዋእትነት ከፈለ።—ምሳሌ 8:30፤ ዮሐንስ 3:16
16. (ሀ) የአምላክ ልጅ ፍጹም ሰው ሆኖ የተወለደው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ከሕግ አንጻር ሲታይ ማን ተብሎ ሊጠራ ይችላል?
16 የአምላክ ልጅ በመለኮታዊው ዝግጅት ውስጥ በፈቃደኝነት በመካፈሉ ከሰማያዊ ፍጥረቱ ተዋርዶ “ራሱን ባዶ አደረገ።” (ፊልጵስዮስ 2:7) ይሖዋ የሰማያዊ በኩር ልጁን የሕይወት ኃይልና ባሕርይ ማርያም ወደተባለች አይሁዳዊት ድንግል ማኅፀን አዛወረ። ለእርስዋም መንፈስ ቅዱስ ጥላ ሆኖላት ስለነበረ በማኅፀንዋ ውስጥ ያድግ የነበረው ሕጻን ቅዱስና ከኃጢአት ሁሉ ፈጽሞ የነጻ ሊሆን ችሎአል። (ሉቃስ 1:35፤ 1 ጴጥሮስ 2:22) ሕጻኑ ሰው ሆኖ በሚኖርበት ጊዜ ኢየሱስ ተብሎ ይጠራል። በሕግ አንጻር ግን ከአዳም ጋር ሙሉ በሙሉ የሚመጣጠን ስለሆነ ‘ኋለኛው አዳም’ ሊባል ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 15:45, 47) በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ራሱን “ዕድፍና ነውር የሌለበት በግ”፣ ለኃጢአተኛው የሰው ልጅ ቤዛ አድርጎ ሊያቀርብ ችሎአል።—1 ጴጥሮስ 1:18, 19
17. (ሀ) ቤዛው የተከፈለው ለማን ነው? ለምንስ? (ለ) ቤዛውን ያዘጋጀውም ሆነ የተቀበለው አምላክ ከሆነ በመሠረቱ ክፍያ ወይም ልዋጭ ለምን አስፈለገ?
17 ይሁን እንጂ ይህ ቤዛ የሚከፈለው ለማን ነው? የሕዝበ ክርስትና የሃይማኖት ሊቃውንት ለብዙ መቶ ዓመታት ቤዛው የተከፈለው ለሰይጣን ዲያብሎስ ነው እያሉ ሲከራከሩ ቆይተዋል። (ሮሜ 7:14፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ሐቁ ግን የሰው ልጅ ለኃጢአት በመሸጡ ምክንያት በሰይጣን ቁጥጥር ሥር መውደቁ ነው። ቢሆንም ለተፈጸመው በደል ቅጣት የሚሰጠው ይሖዋ ነው እንጂ ሰይጣን አይደለም። (1 ተሰሎንቄ 4:6) ስለዚህ መዝሙር 49:7 ግልጽ አድርጎ እንደሚናገረው ቤዛው የሚከፈለው “ለእግዚአብሔር“ ነው። ቤዛውን ያዘጋጀው ይሖዋ ቢሆንም የአምላክ በግ ከተሰዋ በኋላ የቤዛው ዋጋ የሚከፈለው ለአምላክ ነው። (ከዘፍጥረት 22:7, 8, 11-13፤ ዕብራውያን 11:17 ጋር አወዳድር) እንዲህ መደረጉ ቤዛውን ምንም ትርጉም የሌለው፣ ገንዘብ ከአንድ ኪስ አውጥቶ ሌላው ኪስ ውስጥ እንደመጨመር የሚቆጠር የይስሙላ ድርጊት አያደርገውም። የቤዛው ታላቅ ቁምነገር የተመሰረተው በዋጋው መለዋወጥ ላይ ሳይሆን በሕጋዊ ትርጉሙ ላይ ነው። ይሖዋ ከፍተኛ ዋጋ የሚጠይቅበት እንኳን ቢሆን የግድ ቤዛ መከፈል አለበት ማለቱ ለጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ የማያወላውል የጸና አቋም ያለው መሆኑን ያረጋግጣል።—ያዕቆብ 1:17
“ተፈጸመ”
18, 19. ኢየሱስ መከራ እንዲቀበል ያስፈለገው ለምን ነበር?
18 በ33 እዘአ የጸደይ ወራት ቤዛው የሚከፈልበት ጊዜ ደረሰ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ በሐሰት ተከስሶ የፍርደ ገምድልነት ፍርድ ተበየነበትና በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ሞተ። በጣም ከፍተኛ የሆነ ሕመምና ውርደት ስለደረሰበት ለአባቱ “ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ።” (ዕብራውያን 5:7) ኢየሱስ ይህን ሁሉ መከራ መቀበሉ ያስፈልግ ነበርን? አዎ፣ ኢየሱስ እስከ መጨረሻው ድረስ “ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ” ሆኖ መጽናቱ ስለአምላክ አገልጋዮች ንጹሕ አቋም ጠባቂነት ለተነሳው ጥያቄ የማያዳግም ምላሽ ይሰጣል።—ዕብራውያን 7:26
19 በተጨማሪም ክርስቶስ መከራ መቀበሉ የሰው ልጆች ሊቀካህናት በመሆን ለሚፈጽመው ሥራ ፍጹም ብቃት እንዲኖረው አድርጓል። ቀዝቃዛ ስሜት ያለው፣ ከሕዝቡ ራሱን አግልሎ የሚኖር ባለሥልጣን አይሆንም። “እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳ ይችላልና።” (ዕብራውያን 2:10, 18፤ 4:15) ኢየሱስ ሊሞት ሲል በተነፈሰው የመጨረሻ ትንፋሹ በድል አድራጊነት “ተፈጸመ” ሊል ችሎአል። (ዮሐንስ 19:30) የራሱን ንጹሕ አቋም ጠባቂነት ከማረጋገጡም በላይ ለሰው ልጆች መዳኛ የሚሆን ምክንያት አስገኝቶአል። ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋን የበላይ ገዥነት አረጋግጦአል።
20, 21. (ሀ) ኢየሱስ ከሙታን የተነሳው ለምን ነበር? (ለ) ኢየሱስ ‘በመንፈስ ሕያው የሆነው’ ለምን ነበር?
20 ይሁን እንጂ የቤዛው ዋጋ ለኃጢአተኛው የሰው ልጅ ጥቅም ላይ የሚውለው በምን መንገድ ነው? መቼና እንዴትስ? እነዚህ ጉዳዮች በአጋጣሚ ብቻ የሚፈጸሙ አይደሉም። ኢየሱስ ከሞተ በሶስተኛው ቀን ይሖዋ ከሙታን አስነሳው። (ሥራ 3:15፤ 10:40) ይሖዋ ይህን በመቶ በሚቆጠሩ የዐይን ምሥክሮች የተረጋገጠውን ታላቅ ድርጊት በመፈጸሙ ልጁ ለፈጸመው የታማኝነት አገልግሎት የሚገባውን ሽልማት እንዲሰጥ ከማስቻሉም በላይ የአዳኝነት ሥራውን ፍጻሜ ላይ እንዲያደርስ አጋጣሚ ሰጥቶታል።—ሮሜ 1:4፤ 1 ቆሮንቶስ 15:3-8
21 ኢየሱስ ምድራዊ አካሉ በአንድ ተለይቶ ባልተገለጸልን መንገድ ተወገደና “በመንፈስ ሕያው ሆነ።” (1 ጴጥሮስ 3:18፤ መዝሙር 16:10፤ ሥራ 2:27) ከሙታን የተነሳው ኢየሱስ አሁን መንፈሣዊ ፍጡር በመሆኑ በድል አድራጊነት ወደ ሰማይ ሊመለስ ቻለ። በዚህ ጊዜ በሰማይ እንዴት ያለ ደስታና እልልታ እንደሆነ መገመት ይቻላል። (ከኢዮብ 38:7 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ ወደ ሰማይ የተመለሰው ጥሩ አቀባበል እንዲደረግለት ብቻ አልነበረም። መላው የሰው ዘር የቤዛው ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችለውን ሥራ ጨምሮ ሌሎች ተግባሮችን ሊፈጽም ነበር። (ከዮሐንስ 5:17, 20, 21 ጋር አወዳድር።) ይህን ተግባር እንዴት እንደፈጸመና ይህም ለሰው ልጆች ምን ትርጉም እንዳለው በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ይብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a እዚህ ላይ የተጠቀሰው አንቲሊትሮን የተባለው የግሪክኛ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሌላ ሥፍራ አይገኝም። ቃሉ ኢየሱስ በማርቆስ 10:45 ላይ ስለ ቤዛ ሲናገር ከተጠቀመበት ቃል ጋር (ከሊትሮን ጋር) ይዛመዳል። ይሁን እንጂ አዲሱ ኢንተርናሽናል የአዲስ ኪዳን መንፈሣዊ ትምህርት መዝገበ ቃላት ሊትሮን አንድን ነገር የሌላው ነገር ልዋጭ ማድረግን ያጎላል። ስለዚህ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም “ተመጣጣኝ ቤዛ” ብሎ መተርጎሙ ተገቢ ነው።
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ ከሰው ልጅ መዳን ይበልጥ በጣም አሳሳቢ የነበሩት አከራካሪ ጥያቄዎች ምን ነበሩ?
◻ ኃጢአተኞችን መቤዠት ማለት ምን ማለት ነው?
◻ ኢየሱስ ከማን ጋር ተመጣጣኝ መሆን ነበረበት? ለምንስ?
◻ ቤዛውን ያዘጋጀው ማነው? የሚከፈለውስ ለማን ነው?
◻ ክርስቶስ መንፈስ ሆኖ ከሙታን መነሳቱ አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የእንስሳት መስዋዕቶች የሰዎችን ኃጢአት ለመሸፈን በቂ አልነበሩም፤ ወደፊት የሚመጣውን የላቀ መሥዋዕት የሚያመለክቱ ነበሩ