እንግዳ ስለሆነው የይሖዋ ሥራ ማስጠንቀቃችሁን ቀጥሉ
“ይሖዋ በፓራሲም ተራራ እንደነበረው ዓይነት ይነሣል። በገባዖን ሸለቆ እንደነበረው ዓይነት ይቆጣል።”—ኢሳይያስ 28:21
1, 2. ይሖዋ በዳዊት ዘመን ለሕዝቡ ምን ያልተለመደ ሥራ ፈጽሟል?
እንግዳ ድርጊት! እጅግ በጣም ያልተለመደ ሥራ! ይሖዋ በጥንት ጊዜ በ11ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ለሕዝቡ ያደረገላቸው ያንን ነበር። ይኸው እንግዳ ሥራ በቅርቡ ለሚፈጸም የበለጠ እንግዳ ለሆነ ሥራ ምሳሌ ነበር። ያ የጥንት ድርጊት ምን ነበር? ዳዊት በኢየሩሳሌም ንጉሥ ሆኖ እንደተሾመ ወዲያው ተጐራባች የሆኑት ፍልስጥኤማውያን ጥቃት ሰነዘሩ። ይሖዋ እንግዳ የሆነ ሥራ እንዲፈጽም ያነሣሣው ይህ ነበር። መጀመሪያ ፍልስጤማውያን የራፋይምን ሜዳማ ሸለቆዎች መውረር ጀመሩ። ዳዊት ምን ማድረግ እንዳለበት ይሖዋን ጠየቀ። በእነርሱ ላይ እንዲዘምት ታዘዘ። የይሖዋን ቃል በመታዘዝ ዳዊት ኃይለኛውን የፍልስጤማውያን ሠራዊት በበዓል ፐራሲም በጥሩ ሁኔታ አሸነፈ። ይሁን እንጂ ፍልስጤማውያን ሽንፈትን አልተቀበሉም። ወዲያው በራፋይም ሸለቆ በድጋሚ ለማጥፋትና ለመዝረፍ ተመለሱ። ዳዊትም እንደገና ከይሖዋ መመሪያ እንዲሰጠው ጠየቀ።
2 በዚህ ጊዜ ከሠራዊቱ ጋር ሆኖ ከፍልስጤማውያን ኋላ እንዲሄድ ተነገረው። ይሖዋ እንዲህ አለው፦ “በሾላውም ዛፍ ራስ ውስጥ የሽውሽውታ ድምጽ ስትሰማ በዚያ ጊዜ ይሖዋ የፍልስጤማውያንን ጭፍራ ለመምታት በፊትህ ወጥቶ ይሆናልና በዚያን ጊዜ ቸኩል።” ልክ እንዳለውም ሆነ። ይሖዋ በሾላው ዛፍ ራስ ላይ የሽውሽውታ ድምጽ (ምናልባትም በኃይለኛ ነፋስ አማካኝነት ይሆናል) እስኪያሰማው ድረስ ዳዊት ጠበቀ። ወዲያው ዳዊትና ሠራዊቱ ከተደበቁበት ሥፍራ ዘለው በመውጣት ግራ የተጋቡትን ፍልስጤማውያንን አጠቁ። በታላቅ ግድያም አሸነፋቸው። ፍልስጤማውያን በጦር ሜዳው የተዉአቸው ሃይማኖታዊ ጣዖቶች ተሰብስበው ተቃጠሉ።—2 ሳሙኤል 5:17-25፤ 1 ዜና 14:8-17
3. የይሖዋ እንግዳ አድራጎት በኢሳይያስ ዘመን ይኖሩ ለነበሩት አይሁዳውያን የሚያሳስብ የነበረው ለምንድነው? በአሁኑ ጊዜ ላለችው ሕዝበ ክርስትናስ የሚያሳስብ መሆን ያለበት ለምንድነው?
3 ይህ ይሖዋ ለተቀባው ንጉሡ ሲል በፍልስጤማውያን ላይ የፈጸመው እንግዳ ሥራ፣ ያልተለመደ ድርጊት ነበር። ይህ አስደናቂ ሥራ ልዩ ትኩረት የሚስብ ነው፤ ምክንያቱም ይሖዋ ያንኑ ያህል እንግዳና ኃይለኛ የሆነ ሥራ በይሁዳ መንፈሳዊ ሰካራሞች ላይ እንደሚያደርግ ነቢዩ ኢሳይያስ አስጠንቅቋል። ስለዚህ የኢሳይያስ ዘመን እምነት አጉዳይ የሃይማኖት መሪዎች ልብ ማለት ነበረባቸው። አሁን ያለችው ሕዝበ ክርስትናም ልብ ልትለው ይገባታል፤ ምክንያቱም በይሁዳ ላይ የደረሰው ነገር ለሕዝበ ክርስትና የመጨረሻ ዕጣ ምሳሌ ነው።
“አልጋው በጣም አጭር ሆነ”
4, 5. (ሀ) ኢሳይያስ በዘመኑ የነበሩት ሃይማኖታዊ መሪዎች የነበሩበትን የማይመች ሁኔታ ጉልህ አድርጎ በሥዕላዊ መንገድ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) በአሁኑ ጊዜስ ሕዝበ ክርስትና የማይመች ሁኔታ የደረሰባት ለምንድነው?
4 ኢሳይያስ በመጀመሪያ እነዚያ የጥንት መንፈሳዊ ሰካራሞች የታመኑባቸው ስምምነቶች ማታለያና ሐሰት መሆናቸውን አጋለጠ። ከዚያም በዚያ ሐሰት የተማመኑት ሰዎች ምቾት እንደማይኖራቸው ጉልህ በሆነ ሥዕላዊ መንገድ ገለጸ። እንዲህ አለ፦ “ሰው በእርሱ ላይ ተዘርግቶ ቢተኛ አልጋው አጭር ነው። ሰውም ሰውነቱን መሸፈን ቢወድድ መጐናጸፊያው ጠባብ ነው።” (ኢሳይያስ 28:20) በጣም አጭር በሆነ አልጋ ላይ እግሩን ዘርግቶ የሚተኛ ማንኛውም ሰው እግሩ ከአልጋው ይወጣና ለብርድ ይጋለጣል። በሌላ በኩል አልጋው አጭር በመሆኑ ጉልበቱን ቢሰበስብ መጐናጸፊያው (የሌሊት ልብሱ) በጣም ጠባብ ስለሆነ አብዛኛው ሰውነቱ ለብርድ የተጋለጠ ይሆናል። በዚያም በዚህም ቢል ከፊል ሰውነቱን ብርድ ላይ ይሆናል።
5 በኢሳይያስ ዘመን እምነታቸውን በሐሰት መሸሸጊያ ያደረጉ ሰዎች ሁኔታ በምሳሌያዊ አነጋገር እንደዚያ ነበር። ዛሬም እምነታቸውን በሕዝበ ክርስትና የሐሰት መሸሸጊያ ያደረጉ ሰዎች የማይመች ሁኔታቸው ይኸው ነው። ብርድ ውስጥ እንዳሉ ያህል ነው። ሰላምና የደኅንነት ዋስትና በመፈለግ በዓለማዊ ድርጅቶች ውስጥ ገብቶ ለመጽናናት የሚሞከርበት ጊዜ አይደለም። እየቀረበ ያለው የአምላክ ፍርድ ሥራ ሲያንዣብብ ሕዝበ ክርስትና ከፖለቲካዊ መሪዎች ጋር መጐዳኘቷ የሚያጽናና ሞቅ ያለ ተስፋ አያመጣላትም።
የይሖዋ እንግዳ ሥራ
6. ይሖዋ በይሁዳ ላይ እርምጃ ሊወስድ ተዘጋጅቶ የነበረው እንዴት ነው? በሕዝበ ክርስትና ላይስ እርምጃ የሚወስደው እንዴት ነው?
6 ኢሳይያስ የዘመኑን እምነት አጉዳይዋን ኢየሩሳሌም (እንዲሁም የዘመናዊቷን እምነት አጉዳይዋን ሕዝበ ክርስትና) የማያመች ሁኔታ ጉልህ አድርጎ ከገለጸ በኋላ እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “ይሖዋም ሥራውን ማለት እንግዳ ሥራውን ይሠራ አንድ አድራጎቱንም ማለት ያልታወቀውን (ያልተለመደውን) አድራጎቱን ያደርግ ዘንድ በፐራሲም ተራራ እንደነበረ ይነሣል። በገባዖንም ሸለቆ እንደነበረ ይቆጣል።” (ኢሳይያስ 28:21) አዎን ይሖዋ በበዓል ፐራሲም እንዳደረገው ዓይነት ቶሎ እንደሚነሣ ኢሳይያስ አስጠንቅቋል። ይህን ጊዜ ግን እርምጃ የሚወስደው በእምነት የለሽ ሕዝቦቹ ላይ ነው። የሚሠራውም ልክ በኃይለኛ ጐርፍ እየተናደ ባለ ግድብ ላይ እንደሚፈሰው ዓይነት ነው። ኢየሩሳሌም ከሞት ጋር ገባሁት የምትለው ቃል ኪዳን ባዶና ዋጋ ቢስ መሆኑ ይታያል። በተመሳሳይ መንገድም ይሖዋ በቅርብ ጊዜ በሕዝበ ክርስትና ላይ እርምጃ ይወስዳል። እሷም ከዚህ ዓለም ጋር ያደረገቻቸው የሚያሰክሩ ስምምነቶች ዋጋ የሌላቸው መሆናቸውን ትገነዘባለች። ሰፊው ድርጅቷ ይንኰታኰታል፤ ተከታዮቿም ይበታተናሉ። የሐሰት አማልክቷ በእሳት ይጋያሉ።
7. ይሖዋ ለይሁዳ የነበሩት ዓላማዎች “እንግዳ” እና “ያልታወቀ” (ያልተለመደ) የተባሉት ለምንድነው?
7 ይሖዋ በኢየሩሳሌም ላይ የሚወስደውን እርምጃ ኢሳይያስ እንግዳና ያልተለመደ ሥራ ብሎ የጠራው ለምንድነው? ኢየሩሳሌም የይሖዋ አምልኰ ማዕከልና ይሖዋ የቀባው ንጉሥ ከተማ እንደነበረች ማስታወሱ መልሱን ለማግኘት ይረዳናል። (መዝሙር 132:11-18) እንዲህ በመሆኗም ከዚያ በፊት ፈጽሞ ጠፍታ አታውቅም። ቤተ መቅደሷ ተቃጥሎ አያውቅም። የዳዊት ንጉሣዊ ቤት በኢየሩሳሌም ላይ ከተመሠረተ ጀምሮ ተገልብጦ አያውቅም። እንዲህ ያሉ ነገሮች የማይታሰቡ ነበሩ። ይሖዋ እነዚህን ነገሮች ይፈቅዳል ብሎ ማሰቡ በጣም እንግዳ ነበር።
8. ስለመጪው ያልተለመደ እርምጃው ይሖዋ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር?
8 ይሁን እንጂ ይሖዋ በነቢያቱ አማካኝነት ሰሚውን ክው የሚያደርጉ ነገሮች እንደሚፈጸሙ ተገቢ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (ሚክያስ 3:9-12) ለምሳሌ በ7ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖር የነበረው ነቢዩ ዕንባቆም እንዲህ አለ፦ “እናንተ የምትንቁ ሆይ አንድ ቢተርክላችሁ ስንኳ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እሠራለሁና እዩ ተመልከቱ፤ ተደነቁ። እነሆ የነሱ ያልሆነውን መኖሪያ ይወርሱ ዘንድ በምድር ስፋት ላይ የሚሄዱትን መራሮችንና ፈጣኖችን ሕዝብ ከለዳውያንን አስነሳለሁ። እነሱ የሚያስፈሩና የሚያስደነግጡ ናቸው።”—ዕንባቆም 1:5-7
9. ይሖዋ በኢየሩሳሌም ላይ ማስጠንቀቂያውን የፈጸመው በምን መንገድ ነው?
9 በ607 ከዘአበ ይሖዋ ማስጠንቀቂያውን ፈጸመው። የባቢሎናውያን ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ እንዲመጡ በመፍቀድ ከተማይቱንም ሆነ ቤተመቅደሱን ሲያጠፉ ዝም ብሎ ተመለከተ። (ሰቆቃ 2:7-9) ከዚህም በላይ ኢየሩሳሌም ለሁለተኛ ጊዜ እንድትጠፋ ፈቀደ። ለምን? ከ70 ዓመታት ግዞት በኋላ ንስሐ የገቡ አይሁድ ወደ ትውልድ አገራቸው ተመለሱና በመጨረሻው በኢየሩሳሌም ሌላ ቤተመቅደስ ተሠራ። ሆኖም እንደገና አይሁድ ከይሖዋ ዘወር አሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ጳውሎስ በዘመኑ በነበሩት አይሁዳውያን ላይ የዕንባቆምን ቃላት ጠቀሰና ትንቢቱ ወደፊትም እንደሚፈጸም አስጠነቀቀ። (ሥራ 13:40, 41) ኢየሱስ ራሱም አይሁዳውያን እምነት በማጣታቸው ምክንያት ኢየሩሳሌምና ቤተመቅደሷ እንደሚጠፉ ለይቶ አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 23:37 እስከ 24:2) እነዚያ የአንደኛው መቶ ዘመን አይሁድ ልብ አደረጉን? አላደረጉም። እንደ ቅድመ አያቶቻቸው ሁሉ እነሱም የይሖዋን ማስጠንቀቂያ አሽቀንጥረው ጣሉ። ስለዚህ ይሖዋ እንግዳ ሥራውን ደገመው። ኢየሩሳሌምና ቤተመቅደሷ በሮማውያን ሠራዊት አማካኝነት በ70 እዘአ ጠፉ።
10. ይሖዋ በቅርቡ በሕዝበ ክርስትና ላይ እርምጃ የሚወስደው እንዴት ይሆናል?
10 ታዲያ በዘመናችን ይሖዋ ተመሳሳይ ነገር አይሠራም ብሎ ማንም ሰው እንዴት ሊያስብ ይችላል? ምንም እንኳ ነገሩ ለተጠራጣሪዎች እንግዳና ያልተለመደ ቢመስልም ዓላማውን ከመፈጸም ወደኋላ አይልም። በአሁኑ ጊዜ እርምጃ የሚወሰድባት እንደ ጥንቷ ይሁዳ አምላክን አመልከዋለሁ እያለች ተስፋ እስከማይኖራት ድረስ የተበላሸችው ሕዝበ ክርስትና ናት። ይሖዋ በታላቁ ዳዊት በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በሕዝበ ክርስትና “ፍልስጤማውያን” ላይ ባልጠበቁት ሰዓት ይመጣባቸዋል። የመጨረሻውን የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ሥርዓት ርዝራዥ እንኳን እስከ መጥረግ ድረስ እንግዳ ሥራውን ይፈጽማል።—ማቴዎስ 13:36-43፤ 2 ተሰሎንቄ 1:6-10
ይሖዋ ስለሚወስደው እርምጃ ማስጠንቀቅ
11, 12. የይሖዋ ምሥክሮች ወደፊት ስለሚመጡት የይሖዋ ፍርዶች ያስጠነቀቁት እንዴት ነው?
11 ለብዙ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች ስለ መጪው የይሖዋ የፍርድ ሥራ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። በ607 ከዘአበ፤ እንደገናም በ70 እዘአ የኢየሩሳሌምና የቤተመቅደሷ መጥፋት በሕዝበ ክርስትና ላይ ሊመጡ ላላቸው ነገሮች ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያዎች እንደሆኑ አመልክተዋል። ከዚህም በላይ ሕዝበ ክርስትና በከሃዲነቷ ምክንያት ራሷን የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል እንዳደረገች ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት ከዚህ የሰይጣን ውትብትብ ጥርቅሞሽ ሁሉ ሕዝበ ክርስትና የባሰች ጥፋተኛ ስለሆነች አምላክ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የሚያመጣው ፍርድ በተለይ እሷን ይጐበኛል።—ራእይ 19:1-3
12 የይሖዋ ምሥክሮች ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ የታላቂቱ ባቢሎን ፖለቲካዊ ውሽሞች ዘወር እንደሚሉባት የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ አመልክተዋል። እነዚህን ፖለቲካዊ ኃይሎች አሥር ቀንዶች ባሉት ቀይ አውሬ በመመሰል ራእይ እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃል፦ “ያየሃቸው አሥር ቀንዶችና አውሬው ጋለሞታይቱን [ታላቂቱን ባቢሎን] ይጣላሉ። ባዶዋንና ራቁቷንም ያደርጓታል። ሥጋዋንም ይበላሉ። በእሣትም ያቃጥሏታል።” (ራእይ 17:16) ሃይማኖታዊቷ ሕዝበ ክርስትና ከሌሎች የሐሰት ሃይማኖቶች ሁሉ ጋር ተቃጥላ ትጠፋለች። ይሖዋ በዘመናችን የሚፈጸመው እንግዳ ሥራ ወይም ያልተለመደ ድርጊት ይህ ይሆናል።
13. በአሁኑ ጊዜ ለይሖዋ ማስጠንቀቂያዎች ሰዎች የሚሰጡት ምላሽ ኢሳይያስ ከገጠመው ምላሽ ጋር ተመሳሳይ የሆነው እንዴት ነው?
13 የይሖዋ ምሥክሮች በቅርቡ ስለሚመጣው ስለዚህ ታላቅ መዓት ማስጠንቀቂያ በሚያሰሙበት ጊዜ ብዙውን ጊዜ የማሾፍ ሳቅ ያጋጥማቸዋል። እንዲህ ዓይነቱን ነገር ለመናገር ለመሆኑ እነሱ እነማን ናቸው ብለው ሰዎች ይደነቃሉ። ሕዝበ ክርስትና በጣም ተደላድላ የተቀመጠች፣ ጽኑ ሆና የተመሠረተች ትመስላለች። እንዲያውም አንዳንዶች ሁኔታዋ እየተሻሻለ እንዳለ ይሰማቸዋል። ይጨቁኗት የነበሩ መንግሥታት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታላቅ ነፃነት ፈቅደውላታል። ሆኖም ሕዝበ ክርስትና የሚከተለውን የኢሳይያስን ምክር ልብ ማለት አለባት፦ “አሁንም በምድር ሁሉ ላይ የሚጸናውን የጥፋት ትዕዛዝ ከሠራዊት ጌታ [ከይሖዋ (አዓት)] ዘንድ ሰምቻለሁና እሥራት እንዳይጸናባችሁ አታፊዙ።”—ኢሳይያስ 28:22፤ 2 ጴጥሮስ 3:3, 4
14. የሕዝበ ክርስትና እሥራት ይበልጥ የሚጠነክርባትና የሚጠብቅባት እንዴት ነው?
14 ሕዝበ ክርስትና ለንጉሡና ለመንግሥቱ በአብዛኛው ጠላት ሆና ትቀጥላለች። (2 ተሰሎንቄ 2:3, 4, 8) ይሁን እንጂ በዚያው መጠን እሥራቷ ይበልጥ እየጠነከረባትና እየጠበቀባት ይሄዳል። በሌላ አነጋገር ጥፋቷ ይበልጡኑ እርግጠኛ ይሆናል። ይሖዋ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ በ607 ከዘአበ እንዲጠፉ ከመፍቀድ ውሳኔው ፍንክች እንዳላለ አሁንም ሕዝበ ክርስትና እንድትጠፋ ካደረገው ውሣኔ ፍንክች አይልም።
“ከመካከሏ ውጡ”
15. ቅን ልብ ላላቸው ግለሰቦች ምን ማምለጫ መንገድ ተከፍቷል?
15 አንድ ሰው በሕዝበ ክርስትና ላይ ከሚወርደው ውርጅብኝ ሊያመልጥ የሚችለው እንዴት ነው? በጥንቱ የእሥራኤል ዘመን ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ወደ ንጹሕ አምልኰው እንዲመልሳቸው ይሖዋ ነቢያቱን ይልክ ነበር። ዛሬም ለተመሳሳይ ዓላማ በሚልዮን የሚቆጠሩ ምሥክሮቹን አስነስቷል። እነርሱም በድን የሆነውን የሕዝበ ክርስትናን መንፈሳዊ ሁኔታ ያለ ፍርሐት ያጋልጣሉ። ይህንንም ሲያደርጉ በራእይ ምዕራፍ 8ና 9 ላይ የተጠቀሱት የመላእክት መለከቶች ያሰሙትን መቅሰፍት መሰል ማስታወቂያዎችን በታማኝነት ያስተጋባሉ። ከዚህም በላይ በዮሐንስ ራእይ 18:4 የተመዘገበውን “ሕዝቤ ሆይ . . . ከመቅሰፍቷም እንዳትቀበሉ ከእርሷ ዘንድ ውጡ” የሚለውን ማሳሰቢያ በትጋት ለሕዝብ ያሳውቃሉ። እዚህ ላይ “እሷ” ተብላ የተጠቀሰችው ሕዝበ ክርስትና ዋነኛዋ አባል የሆነችላት ታላቂቱ ባቢሎን ማለትም የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ናት።
16. በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሐሰት ሃይማኖት ያመለጡት በምን መንገድ ነው
16 ከ1919 ጀምሮ በተለይም ከ1922 ወዲህ ለዚያ ማሳሰቢያ ምላሽ የሚሰጡት ቁጥራቸው እየጨመረ የሚመጣ ትሁታን ታላቂቱ ባቢሎንን ለቀው ወጥተዋል። መጀመሪያ ላይ በሺህ ከዚያም በብዙ መቶ ሺህ አሁን ግን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሐሰት ሃይማኖት በተለይም ከሕዝበ ክርስትና ራሳቸውን ለይተው ወደ ንጹሕ አምልኰ ሸሽተዋል። (ኢሳይያስ 2:2-4) ለይሖዋ እንግዳ ሥራ መፈጸም ጊዜው ሲደርስ በታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት ከሚደመደመው ታላቅ መቅሰፍት ለመዳን የሚችሉት ትተዋት በመውጣት ብቻ እንደሆነ ያውቃሉ።
17, 18. ይሖዋ ለሕዝቡ የጌጥ አክሊልና የውበት አበባ ጉንጉን የሆነው እንዴት ነው?
17 ነቢዩ ኢሳይያስ ለንጹሕ አምልኰ ቆራጥ አቋም የሚወስዱትን ሰዎች ደስተኛ ሁኔታ ይገልጽልናል። እንዲህ ይላል፦ “በዚያ ቀን የሠራዊት ጌታ [ይሖዋ (አዓት)] ለቀሩት ሕዝቡ የክብር ዘውድና የጌጥ አክሊል ይሆናል። በፍርድ ወንበር ላይ ለሚቀመጥም የፍርድ መንፈስ ሰልፉን [ከበር] ለሚመልሱም ኃይል ይሆናል።”—ኢሳይያስ 28:5, 6
18 ለእውነት ባላቸው ታማኝነት ምክንያት ይሖዋ ለታማኝና ልባም ባሪያ ቡድን አባሎች የማይሞት የክብር አክሊላቸው ነው። ይህም በተለይ ከ1926 ጀምሮ እውን ሆኗል። በዚያ ዓመት የጥር 1 መጠበቂያ ግንብ “ይሖዋን ማን ያከብረዋል” የሚል ርዕስ ባለው ቀስቃሽ አንቀጹ ላይ የይሖዋን ስም ከፍ የማድረግን አስፈላጊነት አሳስቧል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከዚያ በፊት ተደርጎ በማያውቅ መንገድ ያንን ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳውቀዋል። በ1931 የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን መጠሪያ በመቀበል ከይሖዋ ጋር ይበልጥ የሚያዛምዳቸው ሁኔታ ተፈጠረ። ከዚህም በላይ የሌሎች በጐች ክፍል የሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎች ከሕዝበ ክርስትናና ከቀሪዎቹ የታላቂቱ ባቢሎን ክፍሎች ወጥተው መጥተዋል። እነዚህም ጭምር የአምላክን ስም በደስታ ተቀብለዋል። ውጤቱስ? በ212 አገሮችና ደሴቶች ለሚገኙ ከአራት ሚልዮን በላይ ለሆኑ ሕዝብ ከጥቂት ጊዜያዊ ብሔራዊ ነፃነት ይልቅ ይሖዋ ራሱ የጌጥ አክሊልና የውበት የአበባ ጉንጉን ሆነላቸው። እነዚህ ሰዎች የአንዱን ሕያውና እውነተኛ አምላክ ስም መሸከም እንዴት ያለ ክብር ሆኖላቸዋል!—ራእይ 7:3, 4, 9, 10፤ 15:4
“የይሖዋ መንፈስ ያርፍበታል”
19. በፍርድ ወንበር ላይ የተቀመጠው ማነው? ይሖዋ ለሱ የፍትሕ መንፈስ የሆነለትስ እንዴት ነው?
19 “በፍርድ ወንበር ላይ ለሚቀመጠው” ለኢየሱስ ይሖዋ “የፍርድ (የፍትህ) መንፈስ” ሆኖለታል። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በሚያሰክር የዓለማዊ ኅብረት መንፈስ ሥር ለመውደቅ እምቢ አለ። ዛሬ በዙፋን የተቀመጠ የይሖዋ ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ትክክለኛና የተጣራ ውሣኔ እንዲያደርግ በሚመራው ቅዱስ መንፈስ ተሞልቷል። “የይሖዋ መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኃይል መንፈስ የእውቀትና ይሖዋን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል” የሚለው ትንቢት በኢየሱስ ላይ ተፈጽሟል። (ኢሳይያስ 11:2) በእውነትም ይሖዋ በኢየሱስ አማካኝነት ‘ፍትሕን የመሠረት መለኪያ ጽድቅን ደግሞ ቱንቢ ያደርጋል።’ (ኢሳይያስ 28:17) በመንፈሳዊ ሰካራም የሆኑ ጠላቶች በጥፋት ጎርፍ የሚዋጡ ሲሆን ለይሖዋ ቅዱስ ስምና ለጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነቱ ፍትሕ ይደረጋል።
20, 21. የኢሳይያስ 28:1-22 ቃላት የሚነኩህ በምን መንገድ ነው?
20 እንግዲያውስ ይህ የኢሳይያስ ምዕራፍ 28 ትንቢት በአሁኑ ጊዜ ለእኛ እንዴት ዕፁብ ድንቅ ትርጉም አለው! ከሕዝበ ክርስትና መንፈሳዊ ሰካራሞች ከራቅንና ከንጹሕ አምልኰ ጋር ተጣብቀን ከኖርን ይሖዋ እንግዳ አድራጐቱንና ያልተለመደ ሥራውን በሚሠራበት ጊዜ እንጠበቃለን። ይህን በማወቃችን እንዴት እንደሰታለን! እነዚህ ነገሮች በሚፈጽሙበት ጊዜ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ለታማኝ ሕዝቡና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለልዕልናው መረጋገጥ ሲል እርምጃ እንደወሰደ ማንኛውም ሰው እንዲያውቅ መደረጉን ስናስብ እንዴት ደስ ይለናል!—መዝሙር 83:17, 18
21 እንግዲያውስ እውነተኛ ክርስቲያኖች የሆኑ ሁሉ እንግዳ ስለሆነው የይሖዋ አድራጎት ያለፍርሃት ማስጠንቀቃቸውን ይቀጥሉ። ስላልተለመደ ሥራው መናገራቸውን ይግፉበት። እንዲህ ሲያደርጉም የማይናወጥ ተስፋችን ይሖዋ በዙፋን ላይ ያስቀመጠው ንጉሥ በሚመራው የአምላክ መንግሥት ላይ የጣልን መሆኑን ለሁሉም ያስታውቁ። ቅንዓታቸው፣ ቁርጥ ውሳኔያቸውና ታማኝነታቸው ሁሉን ማድረግ ለሚቻለው አምላካችን ለይሖዋ ዘላለማዊ ምስጋና አስተዋጽኦ የሚያበረክት ይሁን።—መዝሙር 146:1, 2, 10
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ ሕዝበ ክርስትና በማይመች ሁኔታ ላይ የምትገኘው ለምንድነው?
◻ ይሖዋ ለኢየሩሳሌም ምን ዓላማ ነበረው? ይህስ “እንግዳ” እና ያልተለመደ” የሆነው ለምን ነበር?
◻ ሕዝበ ክርስትናን በሚመለከት የይሖዋ ምሥክሮች ምን ማስጠንቀቂያ በጽሑፍ አውጥተዋል? የገጠማቸውስ ምላሽ ምንድነው?
◻ ሰዎች ከሕዝበ ክርስትና ዕጣ ሊያመልጡ የሚችሉት እንዴት ነው?
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በሕዝበ ክርስትና ላይ እንግዳ ሥራውን በድጋሚ ያከናውናል