የፍርድ ቀን—የብሩህ ተስፋ ጊዜ ይሆናል!
ስለፍርድ ቀን ማሰብ ራሱ የሚያስፈራህ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ፍርድ ቀን ምን እንደሚል ለምን አትመረምርም? ለምሳሌ አምላክ ፍርዱን በሚያስፈጽምበት ጊዜ ኃጢአተኞች ወደ ሲኦል እሳት ይጣላሉ የሚባለው እውነት ነውን?
ተመዝግቦ በቆየልን ታሪክ መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ መለኰታዊ ፍርድ የተሰጠው ገና የሰው ልጅ ታሪክ በጀመረበት ጊዜ ነበር። አዳምና ሄዋን በምድራዊ ገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ነበራቸው። (ዘፍጥረት 1:26-28፤ 2:7-9, 15-25) ይሁን እንጂ ኃጢአት ሠሩና በአምላክ የቁጣ ፍርድ ሥር ወደቁ። ውጤቱስ ምን ሆነ? አምላክ የሰጣቸውን የሕይወት ስጦታ ወሰደባቸው። በሌላ አነጋገር ሞቱ። አምላክ እንዲህ ብሎ ነግሮአቸዋል፦ “ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፣ አፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህና።” (ዘፍጥረት 3:16-19)
ይህ ከባድ ፍርድ ነበር። ይሁን እንጂ ትክክለኛ ፍርድ ነበር። በቅጣቱ ላይ የሲኦል እሳት ሥቃይ እንዳልተጨመረበት ግልጽ ነበር። አዳምና ሔዋን ሲሞቱ ወደ አፈር (ወደ መሬት) ተመለሱ። መኖር አከተመ። መጽሐፍ ቅዱስ የአዳምም ሆነ የማንኛውም ሌላ ሰው ክፍል የሆነ አንድ ሌላ ነገር ከሞት ተርፎ ለዘላለም ወደሚሰቃይበት ወደ አንድ የስቃይ ቦታ ሄደ ብሎ የሚናገርበት ቦታ የለም። ከዚህ ይልቅ “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና ሙታን ግን አንዳች አያውቁም” የሚል ቃል እናነባለን።—መክብብ 9:5
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ እንደሚል ታውቅ ነበርን? እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የማትሞት ነፍስ” የሚል አነጋገር ፈጽሞ እንደማይገኝ ታውቅ ነበርን? ከዚህ ይልቅ “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች” ይላል። (ሕዝቅኤል 18:4) ይህም “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓት ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማል። (ሮሜ 6:23) ይህ ደንብ ሁላችንንም የሚመለከት ነው። ሁላችንም የኃጢአተኛው የአዳም ዘሮች ነን። ስለዚህ ሁላችንም ኃጢአት ስለሠራን የኃጢአት ደመወዝ የሆነውን ሞትን እንቀበላለን። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለውም፦ “ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።” (ሮሜ 5:12) የፍርድ ቀን አምላክ ከዚህ ሁኔታ እኛን ለማዳን ያዘጋጀው ዝግጅት ዋነኛ ክፍል ነው።
የፍርድ ቀን መሠረት
በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት አምላክ በፍርድ ቀን ለሚሆነው ነገር መሠረት የጣለው ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት ነበር። ይህም ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣ ጊዜና ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ስለኛ በሰጠ ጊዜ ነበር። ኢየሱስ ራሱ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 3:16
በኢየሱስ ካመንን አሁንም እንኳ በመንፈሳዊ መንገድ ከመሥዋዕቱ ጥቅም ለማግኘት እንችላለን። አምላክ ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል። ወደእሱ እንድንቀርብም ይፈቅድልናል። (ዮሐንስ 14:6፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2) ይሁን እንጂ አሁንም ገና ፍጽምና የጎደለን ኃጢአተኞች በመሆናችን እንታመማለን፤ በመጨረሻም እንሞታለን። ኢየሱስ ቃል የገባልንን የዘላለም ሕይወት ገና አላገኘንም። ይህ የዘላለም ሕይወት የሚገኘው በፍርድ ቀን አማካኝነት ነው።
የፍርድ ቀን
ሐዋርያው ዮሐንስ የፍርድን ቀን በራእይ አይቶአል። እንደሚከተለውም ገልጾታል፦ “ታላቅና ነጭ ዙፋንን በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ። ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ። ሥፍራም አልተገኘላቸውም። ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ። መጻሕፍትም ተከፈቱ። ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው። ሙታንም በመጽሐፍት ተጽፎ እንደነበረ እንደሥራቸው መጠን ተከፈሉ።”—ራእይ 20:11, 12
አዎን በዮሐንስ ራእይ መሠረት የፍርድ ቀን የበላይ ዳኛ የሚሆነው አምላክ ራሱ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ሥራ የሚካፈል ሌላ ፈራጅ አለ። ሐዋርያው ጳውሎስ “(አምላክ) ቀን ቀጥሮአልና በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ እንዲፈርድ አለው” በማለት ገልጾታል። (ሥራ 17:31) ያ ሰው ማን ነበር? “ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም” በማለት የተናገረው ኢየሱስ ራሱ ነው። (ዮሐንስ 5:22) ስለዚህ በአምላክ የፍርድ ቀን አምላክ ዳኛ ወይም ፈራጅ አድርጎ የሚሾመው ኢየሱስን ይሆናል።
ይህ ለሰው ልጆች ታላቅ የምሥራች ነው። ኢየሱስ ታላቅ ርኅራኄ የነበረው ሰው እንደነበረ ወንጌሎች ያመለክታሉ። ኢየሱስ ትዕቢተኛ ወይም በግድ ይደረግልኝ ባይ ሳይሆን “የዋህና በልቡ ትሑት” ነው። (ማቴዎስ 11:29፤ 14:14፤ 20:34) በእንዲህ ዓይነቱ ፈራጅ መዳኘት በጣም ደስ የሚል ነገር ነው።
ፍርዱ መቼ ይሆናል?
ታዲያ የፍርድ ቀን መቼ ነው? የራእይ መጽሐፍ “ሰማይና ምድር ሲሸሹ” እንደሚሆን ይናገራል። ይህም የሐዋርያው ጴጥሮስን ቃላት ያስታውሰናል፦ “አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል።” (2 ጴጥሮስ 3:7) ግዑዟ ምድር ልትቃጠል ነውን? አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ ነው። ግዑዟ ምድር ፈጽሞ አትጠፋም። “ምድር . . . ለዘላለም አትወገድም።” (መዝሙር 104:5 ኪንግ ጄምስ ቨርሺን) በጴጥሮስ ቃላት ዙሪያ ያሉት ሐሳቦች የሚጠፋው የአሁኑ አምላካዊ ያልሆነ ዓለማዊ የነገሮች ሥርዓት መሆኑን ያሳያሉ። ፕላኔቷ ምድር ሳትሆን አምላካዊ ያልሆኑ ሰዎች ይጠፋሉ።—ዮሐንስ 12:31፤ 14:30፤ 1 ዮሐንስ 5:19
እነዚህ አምላካዊ ያልሆኑ ሰዎች ይህ መጽሔት አዘውትሮ እንደገለጸው በቅርቡ በሚፈጸመውና መጽሐፍ ቅዱስ አርማጌዶን ብሎ በሚጠራው ጦርነት ይጠፋሉ። (ራእይ 16:14, 16) ከዚያ በኋላ ሰይጣን ራሱ ለሺህ ዓመታት ይታሰርና በሰው ልጆች ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት ይታገዳል። የፍርድ ቀንም የሚቆየው ለዚህ የሺህ ዓመት ርዝመት ላለው ጊዜ ነው። (ራእይ 19:17 እስከ 20:3) አምላካዊ ያልሆኑት ሰዎች በአርማጌዶን ሲጠፉ ታማኞቹስ ምን ይሆናሉ? ከጥፋቱ ተርፈው ወደ ፍርድ ቀን ይገባሉ። እንዲህ እናነባለን፦ “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉ። ኃጥአን ግን ከምድር ይጠፋሉ። ዓመፀኞችም ከእርሷ ይነጠቃሉ።”—ምሳሌ 2:21, 22
መጽሐፍ ቅዱስም ይህን በመደገፍ ከአርማጌዶን በፊት በምድር ላይ ስለሚታዩ “አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ” ስለተውጣጡ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ይናገራል። እነዚህ ሰዎች “ከታላቁ መከራ (ወጥተው) ይመጣሉ።” በሌላ አነጋገር ኖኅ በራሱ ዘመን ከነበረው የዓለም ፍጻሜ እንደዳነ እነሱም ከዚህ አምላካዊ ያልሆነ ዓለም ፍጻሜ ይተርፋሉ። (ራእይ 7:9-17፤ 2 ጴጥሮስ 2:5) ይህ የንቁ ክርስቲያኖች ዓለም አቀፍ የእጅግ ብዙ ሰዎች ጭፍራ ባሁኑ ጊዜም እንዳለ አውቀሃልን? እነዚህ ሰዎች ከታላቁ መከራ ተርፈው በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ ያደርጋሉ። ባሁኑ ጊዜ እነዚህ ሰዎች መኖራቸው ብቻ የፍርድ ቀን ቅርብ መሆኑን የሚያረጋግጥ እርግጠኛ ማስረጃ ነው።
የሚፈረዱት እነማን ይሆናሉ?
ይህ እጅግ ብዙ ሕዝብ በፍርድ ቀን ይፈረዳል። ይሁን እንጂ የሚፈረደው ይህ ሕዝብ ብቻ አይሆንም። የዮሐንስ ትረካ በመቀጠል “ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ። ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ። እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ” ይላል። (ራእይ 20:13) ይህም ሰዎች በሲኦል ለዘላለም እንደማይሠቃዩ የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ ይሆናል። ሲኦል በውስጡ ያሉትን ሙታን የሚሰጥ ከሆነ በዚያ የነበረ ሰው እንዴት ለዘላለም ሊሰቃይ ይችላል? እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱሱ ሲኦል ሙታን ትንሣኤን እየተጠባበቁ ምንም ሳይሰማቸው የሚቆዩበት የሰው ልጆች የጋራ መቃብር ነው። በፍርድ ቀን ሲኦል በውስጡ ያሉትን ሙታን በሙሉ ያስረክባል።—መክብብ 9:10
በፍርድ ቀን ከሙታን የሚነሡት እነማን ይሆናሉ? ሐዋርያው ጳውሎስ “የጻድቃንም ሆነ የዓመፀኞች ትንሣኤ ሙታን ይኖራል” ብሏል። (ሥራ 24:15 ኪንግ ጄምስ ቨርሺን) ስለዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የሆኑት “ጻድቃን” ይነሣሉ። ይሁን እንጂ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሌሎች ሰዎች ማለት “ዓመፀኞችም” ይነሣሉ። ኃጢአታቸው በጣም ከባድ ሆኖ አምላክ ሕይወት እንደማይገባቸው ከፈረደባቸው ሰዎች በስተቀር ትንሣኤው ሞተው እስካሁን በመቃብር ያሉትን ሁሉ እንደሚያጠቃልል ግልጽ ነው።—ማቴዎስ 12:31
ፍርዱ
ታዲያ በሕይወት የሚተርፉት እጅግ ብዙ ሰዎችና ከሙታን የሚነሡት ሰዎች በፍርድ ቀን ምን ይሆናሉ? መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ” ይላል። ይህ የፍርድ ቀን የምርመራ ጊዜ ነው። እንደ ኪንግ ጄምስ ቨርሽን አባባል “በመጻሕፍቱ ተጽፈው በሚገኙት ነገሮች” መሠረት ማለትም በዚያ ጊዜ አምላክ ለሰው ልጆች ከሚያወጣቸው ብቃቶች ጋር ተስማምተው ለመሥራት ወይም ለመኖር ፈቃደኞች የሚሆኑት ሰዎች “በሕይወት መጽሐፍ” ውስጥ ይጻፋሉ። (ራእይ 20:12) የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በሚያስችላቸው መንገድ ላይ ይሆናሉ!
ከዚያም በመጨረሻ ላይ የክርስቶስ መሥዋዕታዊ ሞት አካላዊ ጥቅሞችን ያመጣል! በዚያ ጊዜ በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የሚመዘገቡት ዳግመኛ ወደ ሕመምና ወደ ሞት አይወርዱም። ከዚህ ይልቅ በኢየሱስ ለሚያምኑ ሁሉ ቃል ከተገባላቸው የዘላለም ሕይወት ጋር ቀስ በቀስ ወደ ሰብአዊ ፍጽምና ይታደሳሉ። እንዴት ዓይነት አስደናቂ ተስፋ ነው! ይሁን እንጂ አንዳንዶች “በመጻሕፍቱ ተጽፈው ለሚገኙት ነገሮች” አንታዘዝም እንደሚሉ ግልጽ ነው። ታዲያ ምን ይሆናሉ? የዘላለም ሕይወት አያገኙም። በዚህ ፋንታ ቅዱስ ጽሑፉ “በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ” ይላል።—ራእይ 20:15
ይህ የእሳት ባሕር ሕዝበ ክርስትና የምትናገርለት የሲኦል እሳት ነውን? አይደለም፣ ምክንያቱም በቁጥር አሥራ ሁለት ላይ “ሞትና ሲኦልም ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው” የሚል እናነባለን። (ራእይ 20:14) ሲኦል ወደ እሳት ባሕር ከተጣለ ባሕሩ ሲኦል ራሱ ሊሆን አይችልም። ከዚህም በላይ ሞት ተይዞ ወደ አንድ ቦታ ሊጣል የሚችል ግዑዝ ነገር አይደለም። ስለዚህ የእሳት ባሕሩ ምሳሌያዊ መሆን ይኖርበታል። ታዲያ የምን ምሳሌ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው” ይላል። በተመሳሳይም መጨረሻቸው በዚያ የእሳት ባሕር ውስጥ የሚሆነው ዓመፀኞች ሰዎች ይሞታሉ ወይም ሕልውናቸው ያከትማል። ይህ ግን የትንሣኤ ተስፋ የሌለበት ሁለተኛው ሞት ነው።
የፍርድ ቀን—የተስፋ ዘመን
ስለዚህ ስለ ፍርድ ቀን ስናስብ ልንሸበር ወይም ሊሰቅቀን አይገባም። የፍርድ ቀን የተስፋ ዘመንና አዳም ያጠፋው የዘላለም ሕይወት ለሰው ልጆች የሚመለስበት ጊዜ ነው። የፍርድ ቀን ታማኞች ለመሆናቸው ለተፈረደላቸው ሰዎች የሚያመጣውን በረከቶች አዳምጡ፦ “እነሆ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው። ከእነርሱም ጋር ያድራል። እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ። እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል። እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል። ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም። ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም። የቀድሞው ሥርዓት አልፎአልና።”—ራእይ 21:3, 4
በሺው ዓመት የፍርድ ቀን መጨረሻ ላይ ከሁሉም የምድር ክፍል የተውጣጡ ሰዎች በመጨረሻ ፍጽምና ደረጃ ላይ ይደርሳሉ። ሙሉ በሙሉ “ወደ ሕይወት ይመጣሉ” ወይም “ሕይወት ያገኛሉ።” በዚህም መንገድ የፍርድ ቀን ዓላማ ግቡን ይመታል። (ራእይ 20:5) ከዚያም ሰይጣን ለመጨረሻ ጊዜ ብቻ ወደ ሰው ልጆች እንደሚለቀቅ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ራእይ 20:3, 7-10) በዚህ የመጨረሻ ሰዓት እሱን የሚቋቋሙት ሰዎች “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ። በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ሙሉ ፍጻሜ ያገኛሉ።—መዝሙር 37:29
የፍርድ ቀን እንዴት ያለ አስደናቂ ዝግጅት ነው! አሁንም እንኳ ሳይቀር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት፣ የአምላክን ፈቃድ በመማርና ይህን መለኮታዊ ፈቃድ በሕይወታችን በሥራ በማዋል ለዚያ የፍርድ ቀን ልንዘጋጅ የምንችል መሆኑ በጣም አስደናቂ ነገር ነው! መዝሙራዊው “ሰማያት ደስ ይበላቸው። ምድርም ሐሴትን ታድርግ፤ ባሕርና ሞላዋ ይናወጡ፤ በረሃ በእርሷም ያሉ ሁሉ ሐሴትን ያድርጉ፤ የዱር ዛፎች ሁሉ በዚያን ጊዜ [በይሖዋ (አዓት)] ፊት ደስ ይላቸዋል፤ ይመጣልና፣ በምድር ላይ ሊፈርድ ይመጣልና” በማለት የጻፈው የአምላክን ፍርድ ባሰበ ጊዜ የሚሰማውን ደስታ መግለጹ ነበር።—መዝሙር 96:11-13