የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
በብራዚል “ለታሠሩት ” መስበክ
የይሖዋ ሕዝቦች በብራዚል ውስጥ በሐሰት ሃይማኖት ግዞት ለተያዙት ሰዎች የመፈታትን ወንጌል በሚሰብኩበት ጊዜ የይሖዋ መንፈስ በኃይል እየሠራባቸው ነው። (ኢሳይያስ 61:1, 2፤ ሉቃስ 4:18) በ1947 በአገሪቱ በሙሉ 648 ምሥክሮች ብቻ ነበሩ። በ1967 ቁጥሩ ወደ 41,548 ዘለለ። በይሖዋ በረከት በ1991 መጀመሪያ ላይ ቁጥሩ የ302,000 ጣራ ላይ ደረሰ! እውነትም “አምላክ አሳድጎታል።” (1 ቆሮንቶስ 3:7) በ1990 የአገልግሎት ዓመት ብቻ 27,068 ተጠምቀው ነበር።
እንዲህ ባለው ዕድገት ምክንያት በየወሩ አንድ አዲስ ክልል እንዲዋቀር አስፈላጊ ሆኖአል። በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 150 አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች ተመርቀዋል። ከዚህም በላይ ቅርንጫፍ ቢሮው በራሱ ማተሚያዎች መጽሐፍ ቅዱሶችን አሁን እያተመ ባለበት ቦታ የማተሚያ አገልግሎቱን ለማስፋት 200 ሄክታር የሚያክል መሬት ገዝቷል። ስለዚህ የብራዚል ምሥክሮች ከ“ታላቁ መከራ” በፊት ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች “ከታላቂቱ ባቢሎን” እንዲወጡ ለመርዳት በርትተው እየሠሩ ነው።—ራእይ 7:9, 10, 14፤ 18:2, 4
□ አንድ የስምንት ዓመት አስፋፊ ለፖሊስ አዛዡ ሚስት አንድ መጽሐፍ ትቶላት ሄደና ብቻውን ተመላልሶ መጠየቅ አደረገላት። አላማው ሴትየዋ ከታሪኰቹ አንዳንዶቹን እንድታነብና ከእያንዳንዱ ታሪክም የተገነዘበችውን እንድትነግረው ለማድረግ ነበር። ታሪኰቹን ለሱ በምታስረዳበት ጊዜ ራሷም መጽሐፉን ማድነቅ ጀመረችና ከእናቱ ጋር እንዲያስተዋውቃት ጠየቀችው። እሱም አስተዋወቃትና የዘወትር የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረች።
□ በ1984 ማሪያ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያየችው ግብዝነት አሰልችቷት ነበር። እንዲሁም በዓለም ውስጥ ስለሚደርሱት ጥፋቶች ያነበበችው ሁሉ ተስፋ አስቆርጦአት ነበር። ስለዚህ የዱርዬነት ኑሮ መምራት ያዘች። ስትናገርም “ግባችን ማንኛውንም ነገርና ሰው መቃወም ነበር። መልኬ ሆን ተብሎ ሰዎችን እንዲያስደነግጥ ታስቦ እንደማይሆን ሆኖ የተስተካከለና ልብሶቼም ጥቁር ቀለም ያላቸውና ራሴም በከፊል የተላጨ ነበር። ባሌን፣ ልጆቼንና ቤቴን ረሳሁና ከእውነታው ለመሸሽ ማሪዋና ማጨስ ኮኬይን መጠቀም ጀመርኩ። ይሁን እንጂ ይህ የባሰ መጥፎ ስሜት እንዲሰማኝ አደረገ። አለቀስኩ። መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ ሊገባኝ ስላልቻለ አምላክ እንዲረዳኝ ጸለይኩ።
“አንድ ቀን ሁለት ምሥክሮች ወደ ቤቴ መጡና ከአጭር ጊዜ ውይይት በኋላ ሁለት መጽሔቶችን ሰጡኝ። አንዱን መጽሔት ሳገላብጥ ‘ከአምላክ ነፃ መውጣት ለምን አይቻልም?’a የሚል አንቀጽ አገኘሁና አንቀጹ ልቤን ነካው። አምላክ ጸሎቴን እንደመለሰልኝ ተሰማኝና በዚያው ቀን ምሥክሮቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመሩልኝ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጥሩ ለውጦች ማድረግ ጀመርኩ። ባሌና ልጆቼ መጀመሪያ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴን ተቃውመው ነበር። የማደርጋቸውን ለውጦች ሲያዩ ግን ያበረታቱኝ ጀመር። አሁን የተጠመቅሁ የአምላክ አገልጋይ ነኝ።”
በሌላው የምድር ክፍል እንዳሉት የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉ የብራዚል ምሥክሮችም “ለታሠሩት መፈታትን” ለመስበኩ ሥራ ንቁዎች ናቸው። ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሰዎችም ይሖዋን በማገልገል እውነተኛ ነፃነትና ደስታን በማግኘት ምላሽ እየሰጡ ናቸው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የህዳር 1, 1985 መጠበቂያ ግንብ እትም።
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ብራዚል
የሕዝብ ብዛት - 150,367,800
የ1990 ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር - 293,466
ሬሾ፣ 1 አስፋፊ ለ - 512
በ1990 የተጠማቂዎች ቁጥር - 27,068
አማካይ አቅኚ አስፋፊዎች - 30,115
የጉባኤዎች ቁጥር - 4,625
አማካይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች - 341,305
የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች - 790,926