የአንባቢያን ጥያቄዎች
◼ ምሳሌ 27:23 ለመንፈሳዊ እረኞችና ባጠቃላይም ለክርስቲያኖች ምን መሠረታዊ ምክር ይሰጣል?
ይህ ጥቅስ “የበጐችህን መልክ አስተውለህ እወቅ በከብቶችህም ላይ ልብህን አኑር” ይላል። (ምሳሌ 27:23) ይህ ጥቅስ አብዛኛውን ጊዜ የሚያገለግለው መንፈሳዊ እረኞች በጉባኤ ውስጥ የሚገኙትን ክርስቲያኖች ለመርዳት ፍላጎት እንዲያሳዩና ሁኔታዎቻቸውንና ችግሮቻቸውን እንዲያውቁላቸው ለማበረታታት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሽማግሌዎችን እረኞች ጉባኤውን ደግሞ በበግ መንጋ ስለሚመስላቸው እንዲህ ዓይነቱ ማበረታቻ ተገቢ ነው። (ሥራ 20:28, 29፤ 1 ጴጥሮስ 5:2-4) ሆኖም ይህ ጥቅስ ከላይ ላለው ሥርዓት የሚሠራ ቢሆንም በመሠረቱ የሚመለከተው መንፈሳዊ እረኞችን ብቻ አይደለም።
የምሳሌ መጽሐፍ የምክር ቃሎችን በተናጠል የያዙ ብዙ ቁጥሮች አሉት። ምሳሌ 27:23 ግን አንድ አይነት ምክር የሚሰጡ የብዙ ቁጥሮች አንድ ክፍል ብቻ ነው። እንዲህ ይላል፦ “የበጐችህን መልክ አስተውለህ እወቅ። በከብቶችህም ላይ ልብህን አኑር ባለጠግነት ለዘላለም አይኖርምና፣ ዘውድም ለትውልድ ሁሉ አይጸናምና። ደረቅ ሣር ታጭዶ አዲስ ለምለም ሣር ይታያል። ከተራራውም ቡቃያ ይሰበስባል። በጐች ለልብስህ፣ ፍየሎችም የእርሻ ዋጋ ይሆናሉ። ለሲሳይህ ለቤተሰቦችም ሲሳይ ለገረዶችህም ምግብ የፍየል ወተት ይበቃል።”—ምሳሌ 27:23-27
ይህ በመንፈስ የተጻፈ ምንባብ በትጋት፣ በሥራ ወዳድነት፣ ቀልላ በሆነ አኗኗር በመርካትና ሕይወታችን በይሖዋ ላይ የተመካ መሆኑን በመገንዘብ የታገዘን አኗኗር ያጎላል። ይህንንም የሚያደርገው የአንድን እሥራኤላዊ እረኛ ሕይወት ከአሸብራቂው የንግድና በፍጥነት የመበልጸግ ሕይወት ጋር በማነፃፀር ነው።
ብዙዎች እንዳረጋገጡት ከፍተኛ ትርፍ በሚያስገኝ የንግድ እንቅስቃሴ አማካኝነት የተገኘ “ባለጠግነት” ወይም ሀብትና ከሱም ጋር የሚመጣው ክብር (“ዘውድ”) በቀላሉ ሊጠፋ ይችላል። ስለዚህ የጥንት እንስሳትን በመከባከብ ይከተሉት እንደነበረው ዓይነት ቀላል አኗኗር የሚመረጥበት ብዙ ምክንያት አለ። ያ ዓይነት ኑሮ ቀላል ሊባል የሚችለው ጭንቀት የሌለበት በመሆኑ አይደለም። አንድ እረኛ የመንጋውን ሁኔታ ነቅቶ የሚከታተልና ከአደጋ የተጠበቁ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልገው ነበር። (መዝሙር 23:4) ትኩረት ሰጥቶ መንጋውን በሚጠብቅበት ጊዜ የታመመ ወይም የተጐዳ በግ ካገኘ ሕመም የሚያስታግስ ዘይት ይቀባው ነበር። (መዝሙር 23:5፤ ሕዝቅኤል 34:4፤ ዘካርያስ 11:16) አብዛኛውን ጊዜም ልቡን በከብቶቹ ላይ የሚያኖር እረኛ ጥረቱ ውጤት ሊያስገኝና መንጋውም ቀስ በቀስ በቁጥር ሲጨምር ሊያይ ይችል ነበር።
ታታሪና ጠንቃቃ እረኛ ሊመካበት የሚችል የእርዳታ ምንጭ አለው። እርሱም ይሖዋ ነው። እንዴት? በጐቹን ለመመገብ የሚያስችል በቂ ሣር ሊያስገኙ የሚችሉ ወቅቶችንና ዑደቶችን የሚሰጠው አምላክ ነው። (መዝሙር 145:16) ከወቅቶቹ መለዋወጥ ጋር ለምለሙ ሣር ከሜዳው ሲጠፋ ጠንቃቃው እረኛ በጐቹን የሚያሰማራበት ሣር የሞላበት ከፍታ ቦታ ይፈልጋል።
ምሳሌ 27:26, 27 የእንዲህ ዓይነቱ ሥራ ውጤት የሆነውን ምግብና ልብስ ይጠቅሳል። እርግጥ እዚህ ላይ የተገለጸው የቅንጦት ምግብ ወይም በጣም ጣፋጭ ሆኖ የተዘጋጀ ልዩ ልዩ ዓይነት ምግብ አይደለም። ወይም ደግሞ ሠራተኛው የዘመኑን ፋሽን የተከተለ በጣም ውድ የሆነ ልብስ እለብሳለሁ ብሎ ተስፋ እንዲያደርግ አያደርገውም። ይሁን እንጂ ጥረት ለማድረግ ፈቃደኛ ከሆነ እረኛውና ቤተሰቡ ከመንጋው ወተት (በዚያውም ዓይብ) እና ጠንካራ ልብስ ለመሥራት የሚያስችል ሱፍ ሊያገኙ ይችሉ ነበር።
ስለዚህ “የበጐችህን መልክ አስተውለህ እወቅ” የሚለው ምክር በመጀመሪያ ደረጃ የሚሠራው ለመንፈሳዊ የበላይ ተመልካቾች አይደለም። ለሁሉም ክርስቲያኖች የሚሠራ ነው። አምላክ እንደማይተወን በመተማመን በጽናትና በትጋት ሠርተን በምናገኘው ምግብና ልብስ የመርካትን አስፈላጊነት የሚያጎላ ነው። (መዝሙር 37:25፤ 2 ተሰሎንቄ 3:8, 12፤ ዕብራውያን 13:5) ምሳሌ 27:23-27ን በሉቃስ 12:15-21 ላይና በ1 ጢሞቴዎስ 6:6-11 ካለው ምክር ጋር በማወዳደር በዚህ ጉዳይ ላይ የአምላክ ምክር የቱን ያህል የማይለወጥ መሆኑን ለማየት እንችላለን። ስለዚህ እያንዳንዳችን ምሳሌ 27:23-27ን እንደገና በማንበብ ‘ይህን ምክር ልብ በማለት በዕለታዊ ሕይወቴ አውለዋለሁን?’ ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.