አዳኝ በሆነው የይሖዋ ክንድ ተማመኑ
“[ይሖዋ ሆይ (አዓት)] . . . ጥዋት ጥዋት ክንድ በመከራም ጊዜ ማዳን ሁነን።”—ኢሳይያስ 33:2
1. ይሖዋ ኃያል ክንድ አለው ለማለት የሚቻለው በምን መንገድ ነው?
ይሖዋ ብርቱ ክንድ አለው። እርግጥ ነው፣ ‘አምላክ መንፈስ’ ስለሆነ ክንዱ የሥጋ ክንድ አይደለም። (ዮሐንስ 4:24) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምሳሌያዊው ክንድ ኃይል የመጠቀም ችሎታን ያመለክታል። ስለዚህ አምላክ ሕዝቡን የሚያድነው በክንዱ ነው። በእርግጥም እርሱ ‘መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፣ ጠቦቶቹንም በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል።’ (ኢሳይያስ 40:11፤ መዝሙር 23:1-4) የይሖዋ ሕዝቦች በእርሱ ፍቅራዊ ክንድ ውስጥ ሲሆኑ ከፍተኛ የመተማመን ስሜት ይሰማቸዋል።—ከዘዳግም 3:24 ጋር አወዳድር
2. እዚህ ላይ ልንመረምራቸው የሚገቡ ምን ጥያቄዎች አሉ?
2 የይሖዋ ክንድ የጥንቶቹንም ሆነ የአሁኖቹን ሕዝቦቹን ያዳነው እንዴት ነው? አምላክ በጉባኤ ደረጃ ምን እርዳታ ሰጥቷቸዋል? ሕዝቦቹስ በመከራቸው ሁሉ በእርሱ የማዳን ክንድ ሊተማመኑ የሚችሉት ለምንድን ነው?
የአምላክ የማዳን ክንድ በተግባር ሲታይ
3. ቅዱሳን ጽሑፎች እስራኤላውያን ከግብፅ ለመዳን ምክንያት የሆናቸው ምን እንደሆነ ነው የሚገልጹት?
3 ከ3,500 ዓመታት በፊት እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ ከማውጣቱ ቀደም ብሎ አምላክ ለነቢዩ ለሙሴ እንዲህ ሲል ነግሮት ነበር፦ “ስለዚህ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፦ እኔ [ይሖዋ (አዓት)] ነኝ፣ ከግብፃውያንም ባርነት አወጣችኋለሁ፣ ከተገዢነታቸውም አድናችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድ በታላቅ ፍርድም እታደጋችኋለሁ።” (ዘፀዓት 6:6) ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው አምላክ እስራኤላውያንን ከግብፅ ያወጣቸው “ከፍ ባለችው ክንዱ” ነበር። (ሥራ 13:17) የቆሬ ልጆች የተስፋይቱ ምድር ድል ሊገኝ የቻለው በአምላክ ኃይል መሆኑን እንዲህ በማለት ገልጸው ነበር፦ “በሰይፋቸው ምድርን አልወረሱም ክንዳቸውም አላዳናቸውም፤ ቀኝህና ክንድህ የፊትህም ብርሃን ነው እንጂ፤ ወድደሃቸዋልና።”—መዝሙር 44:3
4. በአሦር ወረራ ዘመን አዳኝ በሆነው የይሖዋ ክንድ መታመን ዋጋ ያስገኘው እንዴት ነው?
4 እንዲሁም በአሦራውያን የወረራ ዘመን የይሖዋ ክንድ ሕዝቡን ረድቷል። በዚያን ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ “[ይሖዋ ሆይ፣ (አዓት)] ማረን፤ አንተን ተማምነናል፤ ጥዋት ጥዋት ክንድ በመከራም ጊዜ ማዳን ሁነን” በማለት ጸልዮ ነበር። (ኢሳይያስ 33:2) ይህ ጸሎት የአምላክ መልአክ በአሦራውያን ሠፈር ውስጥ 185,000 ወታደሮችን በገደለበትና ንጉሥ ሠናክሬብ ኢየሩሳሌም ተከብባ ከነበረበት ቦታ “አፍሮ” በተመለሰበት ጊዜ መልስ አግኝቷል። (2 ዜና መዋዕል 32:21፤ ኢሳይያስ 37:33-37) አዳኝ በሆነው የይሖዋ ክንድ መተማመን ዋጋ ሳያስገኝ የቀረበት ጊዜ የለም።
5. ኃያሉ የአምላክ ክንድ በአንደኛው የዓለም ጦርነት መጨረሻ ላይ ስደት ለደረሰባቸው ክርስቲያኖች ምን አደረገላቸው?
5 ኃያሉ የአምላክ ክንድ አንደኛው የዓለም ጦርነት ባበቃበት ጊዜ ስደት የደረሰባቸውን ቅቡዓን ክርስቲያኖች አድኗል። በ1918 የአስተዳደር አካሉ ዋና መሥሪያ ቤት በጠላቶቻቸው ጥቃት ደርሶበት ነበር። ታዋቂ የነበሩት ወንድሞችም ታሥረው ነበር። ቅቡዓኑ ዓለማዊ ኃይሎችን በመፍራት ምስክርነት የመስጠት ሥራቸውን አቁመው ነበር። ሆኖም እንደገና ሥራው እንዲጀመርና ከፍርሃት የበድንነትና የርኩሰት ኃጢአት እንዲያነፃቸው ጸሎት አደረጉ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አምላክ ታስረው የነበሩትን ወንድሞች ከቀረበባቸው ክስ ነፃ ሆነው እንዲፈቱ በማድረግ ጸሎታቸውን መለሰላቸው። በ1919 ባደረጉት ትልቅ ስብሰባቸው ላይ በተገለጹት እውነቶች ምክንያትና አንቀሳቃሽ የሆነው የአምላክ መንፈስ በመፍሰሱ ምክንያት ቅቡዓኑ በኢዩኤል 2:28-32 የመጨረሻ ፍጻሜ መሠረት ለይሖዋ ፍርሃት የሌለበት አገልግሎት ለማቅረብ እንደገና ተነቃቁ።—ራእይ 11:7-12
ለጉባኤ የሚሰጥ እርዳታ
6. በጉባኤ ውስጥ የሚነሱትን ፈታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም የሚቻል መሆኑን የምናውቀው እንዴት ነው?
6 አምላክ በአጠቃላይ ድርጅቱን ስለሚደግፍ ክንዱ በድርጅቱ ውስጥ ያሉትን ግለሰቦች ይደግፋል። እርግጥ ሰዎች ሁሉ ፍጽምና የጎደላቸው በመሆናቸው ምክንያት በየትኛውም ጉባኤ ፍጹም የሆነ ሁኔታ አይገኝም። (ሮሜ 5:12) ስለዚህ አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች አንዳንድ ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ፈታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸው ይሆናል። ለምሳሌም ያህል ጋይዮስ በእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ጎብኚ ወንድሞችን በመቀበል “የታመነ ሥራ” ሲሠራ ዲዮጥራጢስ ግን አልተቀበላቸውም፣ እንዲያውም እነርሱን በእንግድነት የሚቀበሉትን ከጉባኤ ሊያስወጣቸው ይሞክር ነበር። (3 ዮሐንስ 5, 9, 10) ይሁን እንጂ ይሖዋ ጋይዮስንና ሌሎች ወንድሞችን የመንግሥቱን የስብከት ሥራ በመደገፍ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በማሳየት እንዲቀጥሉ ረድቷቸዋል። በጸሎት ላይ የተመሠረተ በአምላክ የመመካት መንፈስ ለእምነታችን ፈታኝ ሊሆን የሚችልን ሁኔታ እርሱ እንዲያስተካክል እየጠበቅን መልካም ሥራ መሥራታችንን እንድንቀጥል ሊረዳን ይገባል።
7. በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ የነበሩ ታማኝ ክርስቲያኖች ምን ሁኔታዎች እያሉ ነው ለአምላክ ባደረጉት ውሳኔ ሊጸኑ የቻሉት?
7 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበረው የቆሮንቶስ ጉባኤ አባል ነህ እንበል። በአንድ ወቅት ተፈጥሮ የነበረው መከፋፈል የጉባኤውን አንድነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ አድርሶት ነበር፤ በተጨማሪም የጾታ ብልግና ሲፈጸም ዝም ብሎ ይታይ ስለነበረ የጉባኤው መንፈስ አደጋ ላይ ወድቆ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 1:10, 11፤ 5:1-5) አማኞች በዓለማዊ ፍርድ ቤቶች እርስ በርስ ይካሰሱ ነበር፤ አንዳንዶችም በተለያዩ ምክንያቶች ይጨቃጨቁ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 6:1-8፤ 8:1-13) ምቀኝነት፣ ቅናት፣ ቁጣና ሥርዓት የለሽነት ብዙ ችግር ፈጥረው ነበር። እንዲያውም አንዳንዶች የጳውሎስን ሥልጣን ተጠራጥረውና የንግግር ችሎታውንም አንቋሽሸውበት ነበር። (2 ቆሮንቶስ 10:10) ሆኖም በዚያ ፈታኝ ወቅት የዚያ ጉባኤ አባላት የነበሩ ታማኞች ለአምላክ ባደረጉት ውሳኔ ጸንተው ነበር።
8, 9. በጉባኤ ውስጥ ፈታኝ ሁኔታ ቢያጋጥመን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
8 ፈታኝ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ወደ አምላክ ሕዝቦች መጠጋትና አብሮ መኖር ያስፈልገናል። (ከዮሐንስ 6:66-69 ጋር አወዳድር) ለአንዳንድ ግለሰቦች ከሌሎቹ ይልቅ “አዲሱን ሰውነት”፣ ርህራሄን፣ ደግነትን፣ ትህትናን፣ የዋህነትንና ትዕግስትን ለመልበስ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድባቸው መሆኑን በመገንዘብ እንታገሣቸው። የአምላክ አገልጋዮች የአስተዳደግ ልዩነት ስላላቸው ሁላችንም ፍቅርንና ይቅር ባይነትን ማሳየት ይገባናል።—ቆላስይስ 3:10-14
9 አንድ ወንድም ለብዙ ዓመታት ይሖዋን ካገለገለ በኋላ እንዲህ አለ፦ “ለእኔ በጣም ጠቃሚ ሆኖ ያገኘሁት አንድ ነገር ቢኖር ከሚታየው የይሖዋ ድርጅት ጋር ተቀራርቦ የመሄዱ ጉዳይ ነው። በመጀመሪያ ያጋጠመኝ ተሞክሮ በሰዎች ማስተዋል ላይ መመካት ምን ያህል የማያስተማምን እንደሆነ አስተምሮኛል። አእምሮዬ በዚህ ነጥብ ላይ ቁርጥ አቋም ከወሰደ በኋላ ከታማኙ ድርጅት ጋር ለመቆየት ወሰንኩ። አንድ ሰው የይሖዋን ሞገስና በረከት ለማግኘት የሚችልበት ከዚህ የተሻለ ምን መንገድ ሊኖር ይችላል?” አንተስ በተመሳሳይ ከይሖዋ ደስተኛ ሕዝብ ጋር ሆነህ ይሖዋን የማገልገሉን መብት ታደንቃለህን? (መዝሙር 100:2) እንደዚያ ከሆነ ምንም ነገር ከአምላክ ድርጅት እንዲያወጣህ አትፈቅድም ወይም ክንዱ የሚያፈቅሩትን ሁሉ ከሚያድነው አምላክ ጋር ያለህን ዝምድና ማጥፋት አትፈልግም።
ፈተናዎች ሲያጋጥሙን የምናገኘው እርዳታ
10. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች ፈተናዎችን እንዲቋቋሙ ጸሎት የሚረዳቸው እንዴት ነው? (ለ) ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 10:13 ላይ ምን ማረጋገጫ ሰጥቶናል?
10 ከአምላክ ድርጅት ጋር የምንተባበር ታማኝ ግለሰቦች እንደመሆናችን ፈተና በሚያጋጥመን ጊዜ እርዳታውን እናገኛለን። ለምሳሌም ያህል ፈተና በሚያጋጥመን ጊዜ ፍጹም አቋማችንን ይዘን ለመቆየት ይረዳናል። እርግጥ ኢየሱስ ‘ከክፉው [ከሰይጣን ዲያብሎስ] አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን’ ብሎ ከተናገራቸው ቃላት ጋር የሚስማማ ጸሎት ማቅረብ ይኖርብናል። (ማቴዎስ 6:9-13) በዚህም የእርሱን ትዕዛዝ እንድናፈርስ ፈተና ሲደርስብን እንድንወድቅ እንዳይፈቅድ እንጠይቀዋለን ማለት ነው። በተጨማሪም ፈተናዎችን ለማሸነፍ የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጠን የምናቀርባቸውን ጸሎቶች ይመልሳል። (ያዕቆብ 1:5-8) በተጨማሪም የይሖዋ አገልጋዮች ከእርሱ እርዳታ እንደሚያገኙ እርግጠኞች ሊሆኑ እንደሚችሉ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፣ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።” (1 ቆሮንቶስ 10:13) ይህ ፈተና የሚመጣው ከየት ነው? አምላክስ መውጫውን መንገድ የሚያዘጋጀው እንዴት ነው?
11, 12. እስራኤላውያን በምን ፈተናዎች ተሸነፉ? ከእነርሱስ ተሞክሮ እንዴት ልንጠቀም እንችላለን?
11 ፈተና የሚመጣው ለአምላክ ታማኝ እንዳንሆን ሊገፋፉን ከሚችሉ ሁኔታዎች ነው። ጳውሎስ እንዲህ አለ፦ “እነዚህም [እስራኤላውያን] ክፉ ነገር እንደተመኙ እኛም እንዳንመኝ ይህ ምሳሌ ሆነልን። ሕዝብም ሊበሉ ሊጠጡ ተቀመጡ ሊዘፍኑም ተነሡ ተብሎ እንደተጻፈ ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ። ከእነርሱም አንዳንዶቹ እንደ ሴሰኑ በአንድ ቀንም ሁለት እልፍ ከሦስት ሺህ እንደወደቁ አንሴስን። ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑት በእባቦቹም እንደ ጠፉ [ይሖዋን (አዓት)] አንፈታተን። ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳንጎራጎሩ በሚያጠፋውም እንደ ጠፉ አታንጎራጉሩ።”—1 ቆሮንቶስ 10:6-10
12 እስራኤላውያን ከአምላክ በተአምር የተሰጣቸውን ድርጭት በሚሰበስቡበትና በሚበሉበት ጊዜ በስግብግብነት ፈተና መሸነፋቸው ጎጂ የሆኑ ነገሮችን መመኘታቸው ነበር። (ዘኁልቁ 11:19, 20, 31-35) ከዚያ ቀደም ብሎም ሙሴ አብሯቸው ባለመኖሩ ምክንያት የጥጃ አምልኮ ፈተና ሲደርስባቸው ጣዖት አምላኪዎች ሆነው ነበር። (ዘፀዓት 32:1-6) በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩት ለፈተና በመሸነፋቸውና ከሞዓባውያን ሴቶች ጋር ዝሙት በመፈጸማቸው ጠፍተዋል። (ዘኁልቁ 25:1-9) እስራኤላውያን ለፈተና በመሸነፍ አመጸኞቹ ቆሬ፣ ዳታንና አቤሮን እንዲሁም ተባባሪዎቻቸው በመጥፋታቸው ምክንያት ስላጉረመረሙ 14,700 የሚያክሉ ሰዎች ከአምላክ በተላከ መቅሰፍት ጠፍተዋል። (ዘኁልቁ 16:41-49) ከእነዚህ ፈተናዎች ውስጥ እስራኤላውያን ሊቋቋሙት የማይችሉት ፈተና እንዳልነበረ ብንገነዘብ ከእነዚህ ተሞክሮዎች ትምህርት ልናገኝ እንችላለን። እምነት ቢያሳዩ፣ ለአምላክ ፍቅራዊ እንክብካቤ አመስጋኝ ቢሆኑና የሕጉን ትክክለኛነት ቢያደንቁ ኖሮ ፈተናውን ሊቋቋሙ ይችሉ ነበር። ይህን ቢያደርጉ የይሖዋ ክንድ ሊያድናቸው ይችል ነበር፤ እኛንም ሊያድነን ይችላል።
13, 14. አገልጋዮቹ ፈተና ሲያጋጥማቸው ይሖዋ መውጫውን መንገድ የሚያዘጋጅላቸው እንዴት ነው?
13 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን በሰዎች ላይ የሚደርሰው ፈተና ሁሉ ይደርስብናል። ቢሆንም እርዳታውን ለማግኘት ወደ አምላክ በመጸለይና ፈተናዎችን ለመቋቋም በመጣር ታማኝ ሆነን ለመቀጠል እንችላለን። አምላክ ታማኝ ስለሆነ ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ፈተና እንዲደርስብን አያደርግም። ለይሖዋ ታማኞች ከሆንን ፈቃዱን ማድረግ ፈጽሞ የማይቻል ነገር አይሆንብንም። ፈተናን ለመቋቋም የሚያስችለንን ጥንካሬ በመስጠት መውጫውን መንገድ ያዘጋጅልናል። ለምሳሌም ያህል ስደት ሲደርስብን ከሥቃይና ከሞት ለማምለጥ ስንል እምነታችንን ለመካድ እንፈተን ይሆናል። ሆኖም አዳኝ በሆነው የይሖዋ ክንድ የምንተማመን ከሆነ ፈተናው እምነታችንን ለመጠበቅ በማንችልበት ነጥብ ላይ በፍጹም አያደርሰንም፤ ታማኝነታችንን ለመጠበቅም የሚያስችል በቂ ኃይል ይሰጠናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው፦ “በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም።—2 ቆሮንቶስ 4:8, 9
14 ይሖዋ መንፈሱን እንደ አስታዋሽና እንደ አስተማሪ አድርጎ በመጠቀም ሕዝቡን ያጠነክራል። ይህም ቅዱስ ጽሑፋዊ ነጥቦችን ወደ አእምሮአችን በማምጣት ፈተናን ለመቋቋም እንዴት እንደምንጠቀምባቸው እንድናስተውል ይረዳናል። (ዮሐንስ 14:26) ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች በአንድ ዓይነት ፈተና ውስጥ የሚኖሩትን አከራካሪ ጉዳዮች ስለሚገነዘቡ አንድን የተሳሳተ መንገድ ለመከተል አይታለሉም። አምላክ ለፈተና ሳይሸነፉ እስከ ሞትም እንኳ ድረስ ቢሆን እንዲጸኑ በማስቻል መውጫውን መንገድ አድርጎላቸዋል። (ራእይ 2:10) ይሖዋ በመንፈሱ አገልጋዮቹን ከመርዳቱም በተጨማሪ ድርጅቱን ለመርዳት በመላእክቱ ይጠቀማል።—ዕብራውያን 1:14
በግል ጉዳዮች የሚሰጥ እርዳታ
15. ከሰለሞን መዝሙር ምን በግል የሚጠቅመን እርዳታ ልናገኝ እንችላለን?
15 ከይሖዋ ድርጅት ጋር የተባበሩ ሁሉ በግል ጉዳዮቻቸውም ቢሆን የይሖዋን እርዳታ አግኝተዋል። ለምሳሌም ያህል አንዳንዶች ክርስቲያን የትዳር ጓደኛ ለማግኘት ይፈልጉ ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 7:39) በዚህን ጊዜ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ ቢያጋጥማቸው የእስራኤልን ንጉሥ ሰለሞንን ማስታወሱ ጠቃሚ ይሆናል። ሱናማይቱ ልጃገረድ ዝቅተኛ ደረጃ ያለው አንድ እረኛ በማፍቀርዋ ምክንያት ለጋብቻ እሺ ሊያሰኛት ሳይችል ቀረ። ይህን ጉዳይ በተመለከተ ንጉሡ በጽሑፍ ያስቀመጠው ታሪክ የሰሎሞን ያልተሳካ ፍቅር መዝሙር ተብሎ ሊጠራ ይችላል። ለመፈቀር ያደረግናቸው ጥረቶች በአንዳንድ ሁኔታ ፍሬቢስ ቢሆኑ እናለቅስ ይሆናል። ሰለሞን ግን ይህን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ተቋቁሟል፤ እኛም ለመቋቋም እንችላለን። የአምላክ መንፈስ ራስን መግዛትንና ሌሎች አምላካዊ ባሕርዮችን እንድናሳይ ሊረዳን ይችላል። ቃሉ ማንኛውም ሰው ማንንም ሊያፈቅር ባለመቻሉ ምክንያት የሚያጋጥመውን አሳዛኝ ሁኔታ እንድንቀበል ይረዳናል። (መኃልይ 2:7፤ 3:5) ሆኖም የሰለሞን መዝሙር (መኃልይ) በጥም ሊያፈቅረን የሚችል አማኝ ጓደኛ ለማግኘት እንደሚቻል ያሳያል። ከዚህም በላይ ይህ “የመዝሙሮች መዝሙር” መልካሙ እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ለ“ሙሽራው” ማለትም ለ144,000 ቅቡዓን ተከታዮቹ ባሳየው ፍቅር ተፈጻሚነቱን አግኝቷል።—መኃልይ 1:1፤ ራእይ 14:1-4፤ 21:2, 9፤ ዮሐንስ 10:14
16. የተጋቡ ክርስቲያኖች የሚያጋጥማቸው ‘የሥጋ መከራ’ ምን ነገሮችን ሊጨምር ይችላል?
16 አማኝ የሆነ ሰው ያገቡትም ቢሆኑ “በሥጋቸው መከራ” አለባቸው። (1 ቆሮንቶስ 7:28) ለባል፣ ለሚስትና ለልጆች ከማሰብ ጋር የተያያዙ አስጨናቂ ሁኔታዎች ይኖራሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:32-35) ሕመም ሸክምና ጭንቀትን ሊፈጥር ይችላል። አንድ ክርስቲያን አባት በስደት ወይም በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ለቤተሰቡ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ማቅረብ ሊያስቸግረው ይችላል። ወላጆችና ልጆች በእስር ምክንያት ሊነጣጠሉ ይችላሉ፤ አንዳንዶችም ብዙ ሥቃይ ሊደርስባቸው እንዲያውም ሊገደሉ ይችላሉ። እንደነዚህ ባሉት ሁኔታዎችም ቢሆን አዳኝ በሆነው የይሖዋ ክንድ በእርግጥ የምንታመን ከሆነ እምነታችንን ለማስካድ የሚመጣብንን ፈተና ለመቋቋም እንችላለን።—መዝሙር 145:14
17. አምላክ ይስሐቅና ርብቃ ምን የቤተሰብ ችግር እንዲቋቋሙ ረድቷቸዋል?
17 አንዳንድ ፈተናዎችን ለረጅም ጊዜ መቋቋም ያስፈልገን ይሆናል። ለምሳሌም ያህል አንድ ልጅ የማታምን ሴት በማግባት አምላካዊ የሆኑ ወላጆቹን ሊያሳዝን ይችላል። ይህን የመሰለው ሁኔታ ከጥንት አባቶች አንዱ በሆነው በይስሐቅና በሚስቱ በርብቃ ላይ ደርሷል። 40 ዓመት ዕድሜ የነበረው ኤሳው ሁለት ኬጢያውያን ሴቶችን አግብቶ ነበር፤ “እነርሱም የይስሐቅንና የርብቃን ልብ ያሳዝኑ ነበር።” “ርብቃም ይስሐቅን አለችው፦ ከኬጢ ሴቶች ልጆች የተነሳ ሕይወቴን ጠላሁት፤ ያዕቆብ [ሌላው ወንድ ልጃቸው] ከዚህ አገር ሴቶች ልጆች ሚስትን የሚያገባ ከሆነ በሕይወት መኖር ለምኔ ነው?” (ዘፍጥረት 26:34, 35፤ 27:46) የርብቃ ጻድቅ ነፍስ በዚህ በማያቋርጥ ችግር ተጨንቆ እንደነበር ግልጽ ነው። (ከ2 ጴጥሮስ 2:7, 8 ጋር አወዳድር) ሆኖም የይሖዋ ክንድ ይስሐቅንና ርብቃን ደግፏቸው ስለነበረ ከእርሱ ጋር የነበራቸውን ጠንካራ ዝምድና እንዲጠብቁና ይህንን ፈተና ጸንተው እንዲቋቋሙት አስችሏቸው ነበር።
18. ሲ. ቲ. ራስል በአምላክ እርዳታ የተቋቋመው ምን ግላዊ የሆነን ፈተና ነው?
18 አንድ የተጠመቀ የቤተሰብ አባል በአምላክ አገልግሎት ሲቀዘቅዝ ያሳዝናል። (ከ2 ጢሞቴዎስ 2:15 ጋር አወዳድር) ይሁን እንጂ አንዳንዶች የመጀመሪያ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዝዳንት እንደነበረው እንደ ቻርልስ ቲ. ራስል በመንፈሳዊ የትዳር ጓደኛቸውን ቢያጡም ጸንተዋል። የራስል ሚስት ወደ 18 ዓመታት ከሚጠጋ የትዳር ዘመን በኋላ ከማኅበሩ ጋር የነበራትን ትሥሥር አቋርጣ በ1897 ጥላው ሄደች። በ1903 በፍርድ ቤት ለመለያየት ክስ መሠረተች፤ ይህም በ1908 ተወሰነላት። መጀመሪያ በጻፈላት ደብዳቤው ላይ እንደሚከተለው ብሎ በገለጸ ጊዜ የተሰማው ሐዘን በግልጽ ታይቷል፦ “ስለ አንቺ ወደ ጌታ ከልብ ጸሎት አድርጌአለሁ። . . . ስለ ሐዘኔ በሰፊው በመዘርዘር ሸክም ልጭንብሽ አልፈልግም፣ ወይም ስለ ስሜቴ በመግለጽ እንድታዝኚልኝ ለማድረግ አልሞክርም። በየጊዜው ልብሶችሽንና ሌሎች ዕቃዎችሽን ስመለከት የቀድሞ ባሕሪሽን አስታውሳለሁ፤ የክርስቶስ መንፈስ መግለጫዎች የሆኑት የፍቅር፣ የሐዘኔታ የረዳትነት ጠባይ የሞላብሽ ነበርሽ። . . . እባክሽ አሁን የምነግርሽን ነገር በጸሎት አስቢበት። መራራ ሐዘን የሆኑብኝ የቀረውን የሕይወት ዘመኔን ብቸኛ ሆኜ መኖሬ ሳይሆን የአንቺ መውደቅ ለእኔ እንደሚታየኝ የዘላለም ጥፋት የሚያስከትልብሽ መሆኑ ነው።” ራስል እንዲህ ያለ አሳዛኝ ሁኔታ ቢያጋጥመውም የምድራዊ ሕይወቱን እስከሚጨርስበት ድረስ የአምላክ ድጋፍ አልተለየውም ነበር። (መዝሙር 116:12-15) ምንጊዜም ቢሆን ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ይደግፋል።
ከሁሉም ዓይነት ችግሮች መውጣት
19. አሳዛኝ ችግሮች አልለቀን በሚሉበት ጊዜ ምንን ማስታወስ ይኖርብናል?
19 የይሖዋ ሕዝቦች እርሱ ‘በየዕለቱ ሸክማችንን የሚሸከምልን የማዳን ሥራ የሚሠራ አምላክ’ መሆኑን ያውቃሉ። (መዝሙር 68:19, 20) ስለዚህ እኛም ከምድራዊ ድርጅቱ ጋር የምንተባበር ራሳችንን የወሰንን ግለሰቦች እንደመሆናችን አስጨናቂ የሆኑ ችግሮች ያለማቋረጥ ቢደርሱብን በተስፋ መቁረጥና በሐዘን ስሜት መሸነፍ የለብንም። “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን” መሆኑን አስታውስ። (መዝሙር 46:1) በእርሱ ላይ ያለን ትምክህት ዋጋ ሳያስገኝልን አይቀርም። ዳዊት “[ይሖዋን (አዓት)] ፈለግሁት መለሰልኝም፣ ከመከራዬም ሁሉ አዳነኝ . . . ይህ ችግረኛ ጮኸ፣ [ይሖዋም (አዓት)] ሰማው፣ ከመከራውም አዳነው” ብሏል።—መዝሙር 34:4-6
20. ሊመረመር የሚገባው ምን ጥያቄ ይቀራል?
20 አዎን ሰማያዊው አባታችን ሕዝቡን ከመከራዎች ሁሉ ያድናቸዋል። በጉባኤ ጉዳዮችም ሆነ በግል ጉዳዮች እርዳታውን በመስጠት ምድራዊ ድርጅቱን ይደግፋል። በእርግጥም “[ይሖዋ (አዓት)] ሕዝቡን አይጥልም።” (መዝሙር 94:14) ቀጥለን ግን ይሖዋ ሕዝቡን በግለሰብ ደረጃ የሚረዳባቸውን ሌሎች መንገዶች እንመርምር። ሰማያዊ አባታችን የታመሙትን የአእምሮ ጭንቀት ያጋጠማቸውን፣ ዘመዳቸው በመሞቱ ምክንያት በሐዘን የተጠቁትን፣ ወይም በሠሩት ስህተት በደል ምክንያት የሚተክዙትን አገልጋዮቹን የሚያበረታቸው እንዴት ነው? ወደፊት እንደምንመለከተው በእነዚህም ጉዳዮች ቢሆን በኃያሉ የይሖዋ ክንድ የምንመካበት ምክንያት አለን።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ በቀድሞ ዘመናት የይሖዋ ክንድ መዳን ያስገኘው እንዴት ነበር?
◻ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ባለው ጉባኤ ውስጥ ሕዝቡን የሚረዳው እንዴት ነው?
◻ በግል ጉዳዮች አምላክ ምን እርዳታ ይሰጣል?
◻ አስጨናቂ የሆኑ ችግሮች አልለቀን ቢሉ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ እስራኤላውያንን ‘በተዘረጋች ክንድ’ ከግብጽ አወጣቸው