በሆንግ ኮንግ እውነተኛውን ሀብት ፈልጎ ማግኘት
ሆንግ ኮንግ ሁሉም ሁኔታዎች ከተመቻቹልህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ገንዘብ ማግኘት የምትችልባት አገር ነች። ባለፉት 40 ዓመታት ወይም ከዚያ ቀደም ባሉት ዓመታት ይህቺ የብሪታንያ ቅኝ ግዛት ጭር ያለች ወደብ ከመሆን ተነስታ በደቡባዊ ምሥራቅ እስያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታላቅ የንግድ መናኸሪያ ተደርጋ እንድትቆጠር የሚያስችል ትልቅ ኢኮኖሚ ገንብታለች።
አነስተኛ የቀረጥ ክፍያ መኖሩም የውጭ አገር ኢንቨስተሮችን ስቧል፤ ይህም ስድስት ሚልዮን በሚሆኑት የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች መካከል የሚታየውን የታታሪነት መንፈስ ያበረታታል። ሌላው ሆንግ ኮንግን አመቺ ወይም ተስማሚ እንድትሆን ያደረጋት ነገር በደቡባዊ ቻይና መግቢያ በር እና በፓስፊክ አካባቢ እንዲሁም ከዚያ ባሻገር ባሉ የእስያ አገሮች መካከል የምትገኝ መሆኗ ነው። በደንብ ተደራጅቶ የተዘረጋው የጅምላና የችርቻሮ ንግድ አውታር ከዘመናዊ የመጓጓዣና የመገናኛ ዘዴዎች ጋር ሆኖ ሆንግ ኮንግ የዓለም አቀፉን የንግድ ፍላጎት በፍጥነት ለማሟላት የምትችል እንድትሆን አድርጓታል።
በኢኮኖሚ ረገድ የተገኘው ስኬታማነት በዓለም ላይ ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ካላቸው አገሮች መካከል አንዷ ሆንግ ኮንግ እንድትሆን አስችሏታል። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ቁሳዊ ብልጽግና ለሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች እርካታንና ዘላቂ ደስታን አስገኝቶላቸዋልን? አላስገኘም። አንዳንዶች ግን ሌላ ዓይነት ሀብት ለማግኘት ፈለጉ፤ ከቁሳዊ ሃብት እጅግ የተሻለውን የሀብት ዓይነትም አገኙ።
መንፈሳዊ ሀብት አገኙ
ዋጋ የማይተመንለትን ሀብት ካገኙት መካከል የሆንግ ኮንግ ተወላጅ የሆነው አልፍሬድ ይገኝበታል። ዋና መሥሪያ ቤቱ በብሪታንያ በሚገኝ በአንድ ዓለም አቀፍ የንግድ ሥራ ድርጅት ውስጥ ዲሬክተር ስለሆነ የተሳካ ቋሚ ሥራ አግኝቶ ነበር። እንደ ብዙዎቹ የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች ሁሉ የእርሱም የሕይወት ግብ ብዙ ገንዘብና የራሱ የሆነ መኖሪያ ቤት ማግኘት፣ በደንብ መመገብና ጥሩ ኑሮ መኖር ነበር። ካለው የሥራ ደረጃና ገቢ የተነሳ ግቦቹ ላይ የደረሰ ይመስላል። ነገር ግን ደስተኛ ነበርን? “ገንዘብ ሊያስገኛቸው የሚችላቸው ነገሮች ውስን የመሆናቸውን ሐቅ ካገኘሁት ልምድ ተምሬአለሁ” በማለት አልፍሬድ በምሬት ተናግሮአል። ከሥራው ቢባረር በባንክ ያስቀመጠው ገንዘብ ለምን ያህል ጊዜ ሊያቆየው እንደሚችል በማሰብ ሳያቋርጥ ይጨነቃል። ይበልጡን ጊዜ በሥራው ላይ ማዋል ሲጀምር በቤተሰቡ ውስጥ ችግሮች መነሳት ጀመሩ። ልጃቸው በድንገት ሲሞት ባለቤቱ ኤሚሊ እጅግ በጣም አዘነች። “እርሱን ለመርዳት አንድ ነገር ማድረግ እችል ዘንድ የት እንዳለ ለማወቅ ፈለግሁ” አለች። ምንም ልታደርግ ባለመቻሏ የመንፈስ ጭንቀት አደረባት።
ጀስቲና አባቷ የሞቱባት ገና በልጅነቷ ነበር። ሆኖም ጠንክራ በመማሯ በሆንግ ኮንግ ከሚገኝ እውቅ ዩንቨርሲቲ ተመረቀች። ይህም የመንግሥት ሥራ እንድትይዝ አስችሏታል። ይህ ዓይነት አጋጣሚ በካንቶኔዝ ቋንቋ ጋም ፋን ዉን ይባላል። ትርጉሙም ወርቃማ የሩዝ ሳህን ማለት ነው። ይህም ጥሩ ክፍያ ያለውና አስተማማኝ ሥራ ማለት ነው። ይህም ሆኖ ጀስቲና ደስተኛ አልነበረችም፤ እርካታም አላገኘችም። ብዙ ጊዜ የሕይወት ዓላማ ምን ይሆን? የወደፊቱ ጊዜስ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን? እያለች ታስባለች። ባለቤቷ ፍራንሲስም ሕይወት ዓላማ የለሽ ሆኖ ይታየው ነበር። ማለቂያ በሌለው ድግግሞሽ እንደሚዘዋወር ከዚህ ግባ የማይባል የአንድ ትልቅ ማሽን ክፍል እንጂ ውጤት ያለው ሥራ እንደሚያከናውን ሰው አድርጎ ራሱን አይቆጥርም።
ከዚያም የአንድ ንግድ ሥራ አስተዳዳሪ ወደ ሆነው ወደ ሪኪ እንምጣ። ምንም እንኳ ብዙ ገንዘብ የሚያገኝ ቢሆንም በሥራ ባልደረቦቹ መካከል የሚታየው እኔ ብቻ ላግኝ የሚለው ፉክክርና በትዳሩ ውስጥ የተነሱት ችግሮች ሕይወትን በሌላ መልኩ እንዲመለከት አደረጉት። ገንዘብ ለእነዚህ ችግሮቹ መፍትሔ ሊያስገኝለት አልቻለም። በባለቤቱ በዌንዲ አመለካከት ዋስትና ያለው ሕይወት ማለት ተስማሚ ሥራና ብዙ ገንዘብ ማግኘት እንዲሁም በፖለቲካ ረገድ በተረጋጋ ኅብረተሰብ ውስጥ መኖር ነው። ይሁን እንጂ ዋስትና ያለው የሚመስለው ኑሮዋ እስከ መቼ ይቀጥል ይሆን? ይህም ይረብሻት ነበር፤ ምክንያቱም ሞት የማይቀርላት ነገር መሆኑ ሕይወቷ ትርጉም የለሽና ዓላማ ቢስ ሆኖ እንዲታያት አድርጓል።
ዴቪድም የሚነግረን የበኩሉ ታሪክ አለው። ዩንቨርሲቲ መማሩ ጥሩ ሥራና አስተማማኝ የኢኮኖሚ ሁኔታ አስገኝቶለታል፤ ይሁን እንጂ ምንም እርካታ አላገኘም። ለምን ይሆን? በዝግመተ ለውጥ እንዲሁም በፍልስፍና ትምህርቶች ውስጥ ሰለተነከረ ሕይወት አሁን ካለበት ሁኔታ አልፎ የማይሄድ መሆኑን በማመኑ ምክንያት ነው። ዴቪድ ወደፊት በተስፋ የሚጠብቀው ምንም ነገር እንደሌለ ተሰማው፤ ቁሳዊ ሀብቱም የከንቱነት ስሜት እንዳይሰማው አልተከላከለ ለትም።
እነዚህ ግለሰቦች የተለያየ የአስተዳደግ ሁኔታ፣ የትምህርትና የኑሮ ደረጃ ቢኖራቸውም ሁሉንም የሚያገናኝ አንድ የጋራ ነገር ነበራቸው። ሁሉም ደስታና እርካታ ያለበት ሕይወት ያስገኛል ብለው ካሰቡት ነገር ላይ ደርሰዋል። ይሁን እንጂ ያለሙት ነገር የሚፈጸምበት ደረጃ ላይ ሲደርሱ ሕይወታቸው ባዶ ሆኖባቸዋል።
በአምላክ ዘንድ ባለ ጠጋ መሆን
የአልፍሬድ፣ የጀስቲናና ከላይ የተጠቀሱት የሌሎቹ ሁኔታ በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ እንደተጠቀሰው ሀብታም ሰው ያለ ነበር። እርሱ ‘ለራሱ ገንዘብ ያከማቸ በአምላክ ዘንድ ግን ባለ ጠጋ’ ያልሆነ ሰው ነበር። (ሉቃስ 12:21) ደስ የሚያሰኘው ነገር ግን እነዚህ ሰዎች የተሻለ ነገር ፈልገው ስላገኙ ሕይወታቸው በእውነተኛው ሀብት በልጽጓል። እውነተኛ ደስታና እርካታ ማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ “ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ” ማድረግ የለባቸውም። (1 ጢሞቴዎስ 6:17) አዎ፤ እነዚህ ግለሰቦች እያንዳንዳቸው እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ማወቃቸውና በእርሱ መታመናቸው በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ አምጥቶላቸዋል። ይህ ሁሉ እንዴት ሊሆን እንደቻለ እስቲ እንመልከት።
አልፍሬድና ኤሚሊ ልጃቸው በድንገት በሞተ ጊዜ በከፍተኛ ኀዘን ተደቆሱ። የነበራቸው ቁሳዊ ሀብት ሁሉ ያደረባቸውን መራራ ኀዘን በጥቂቱም እንኳ ሊያስረሳቸው አልቻለም። ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዱ ነበር፤ ነገር ግን አሁንም የባዶነትና ያለመርካት ስሜት ይሰማቸዋል። በዚህ ጊዜ አንድ የይሖዋ ምስክር ወደ ቤታቸው መጣና “የሰው ልጅ የወደፊት ተስፋ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። አልፍሬድ በቤተ ክርስቲያን ሲነገር በሰማው መሠረት ስለ ገነትና ስለ ሲኦል በመናገር መለሰ። ይሁን እንጂ ‘ሙታን አንዳች እንደማያውቁ’ እንዲሁም በአምላክ ዝክር ውስጥ ያሉት ሙታን በሰው ልጆች የጋራ መቃብር ውስጥ ሆነው ትንሣኤን እንደሚጠብቁ ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳየው። (መክብብ 9:5,10፤ ዮሐንስ 5:28,29) አልፍሬድ ይህን ትክክለኛና ምክንያታዊ ሆኖ አገኘው። አሁን አልፍሬድ ልጁ የሚሠቃይበት ቦታ እንደሌለ አወቀ። ከዚህ ይልቅ ምናልባትም ትንሣኤ አግኝቶ ከቤተሰቦቹ ጋር እንደገና እንዲገናኝ የሚያስችል ተስፋ ኖሮት በሞት ያንቀላፋ መሆኑን ተገነዘበ። እንዴት ያለ መጽናናትና እፎይታ የሚያስገኝ ነው! በመጨረሻም አልፍሬድና ሚስቱ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው ተስማሙና መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው እውነተኛ ሀብት በሚገኝበት መንገድ በጽናት መጓዝ ጀመሩ።
ጀስቲና እርሷ እንደጠበቀችው ከሥራ ባልደረቦቿ መካከል ሰዎችን ለመርዳት የፈቃደኝነት መንፈስ ያላቸው ሰዎችን አላገኘችም ነበር። የካቶሊክ እምነትን አጥብቃ የምትከተል ስለነበረች ቄሱ እንደሌሎቹ ወንዶች ሁሉ እሳቸውም ሲጋራ እንደሚያጨሱና ወደ ዳንስ ቤት እንደሚሄዱ ባወቀች ጊዜ ተበሳጨች። ከዚህ በኋላ ከይሖዋ ምስክሮች ጋር ተገናኘችና ለብዙ ጥያቄዎች አጥጋቢ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ መልስ ማግኘት ጀመረች። ምንም እንኳ ቤተ ክርስቲያን አዘውታሪና ለ10 ዓመታት ያህል ሃይማኖታዊ የጉልበት ሥራዎችን ትሠራ የነበረች ብትሆንም ቄሱ የራሳቸውን አስተያየት ከመናገር በስተቀር ምንም ዕውቀት አልሰጧትም። እርሷም ብትሆን በ16 ዓመታት ውስጥ አንዴም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስን ገልጣ አታውቅም ነበር።
ምስክሮቹ ከጀስቲናና ከባለቤቷ ከፍራንሲስ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በሚያጠኑበት ጊዜ ፍራንሲስ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ባላቸው የእምነትና የተግባር አንድነት ተነካ። ፍራንሲስ አምላክ በእርግጥ ያለ መሆኑን አመነ። ከየአገሩ የተውጣጡ ሕዝቦችን እንዲህ አድርጎ ማንቀሳቀስ የሚችል ህያውና እውነተኛው አምላክ ብቻ ነው ብሎ አሰበ። እነዚህ ባልና ሚስት እውነተኛውን ሀብት በማግኘታቸው ምን ያህል ተደስተው ይሆን!
ሪኪ እና ዌንዲ በከባድ የግል ችግሮች ውስጥ ቀስ በቀስ እየተዋጡ እንደሄዱ ባወቁ ጊዜ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ተሰማቸው። ከዚህ በፊት ሁለቱም ከይሖዋ ምስክሮች ጋር ተገናኝተው ስለነበር እነርሱን እንደገና ፈልገው ለማግኘት በየግላቸው ጥረት ማድረግ ጀመሩ። ከልብ ባደረጉት ጥረት ሪኪ እና ዌንዲ ለችግሮቻቸው ተግባራዊ የሚሆኑ መፍትሔዎችን ብቻ ሳይሆን ‘ከደስተኛው አምላክ’ ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና በመመሥረታቸው እውነተኛ ሀብትንም ጭምር አግኝተዋል። — 1 ጢሞቴዎስ 1:11 አዓት
የይሖዋ ምስክሮች ወደ ቤቱ ሄደው ባነጋገሩት ጊዜ የዴቪድም ሕይወት ተለወጠ። ስህተተኛ መሆናቸውን አጋልጣለሁ ብሎ በማሰብ ተመልሰው እንዲመጡና እንዲያነጋግሩት ተስማማ። ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ ዓይኖቹ ተገለጡለት፤ መጽሐፍ ቅዱስ በሳይንስ፣ በታሪክና በሌሎች መስኮችም ረገድ ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ መሆኑን ማየት ጀመረ። ይህ ሁሉ ዴቪድ መጽሐፍ ቅዱስን ለሕይወቱ እውነተኛ ዓላማ የሚሰጥ የእውነት መጽሐፍ አድርጎ እንዲመለከት ረዳው። እንዴት ያለ አስደሳችና ከፍተኛ ለውጥ ሆነለት!
ሌሎች ብዙ ሰዎች እውነተኛውን ሀብት እንዲያገኙ መርዳት
የሕዝብ ብዛት ባጥለቀለቃት በሆንግ ኮንግ ውስጥ አልፍሬድ፣ ኤሚሊ፣ ጀስቲና፣ ፍራንሲስ እና ከዚህ በፊት የተጠቀሱት ሌሎችም የመጽሐፍ ቅዱስን የእውነት ሀብት ካገኙትና በይሖዋ አምላክ ላይ እምነት ካደረባቸው መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። በ1992 ወደ 2,600 የሚጠጉት የይሖዋ ምስክሮች የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በማነጋገርና ከ3,800 በላይ የሆኑ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በመምራት በጠቅላላው ወደ 900,000 የሚጠጋ ሰዓት በአገልግሎት አሳልፈዋል። ሆኖም የሆንግ ኮንግ ኑሮ ጥድፊያ የበዛበት ነው፤ ሰዎቹም በሥራ የተወጠሩ ናቸው። ስለዚህ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ከቤት ወደ ቤት ከሚያደርጉት ምስክርነት በተጨማሪ በመንገድ ላይ በሚደረግ ምስክርነትም ብዙ የተሳካ ውጤት አግኝተዋል። በተጨማሪም ሥራ ቦታቸው ድረስ በመሄድ የቢሮ ሠራተኞችን፣ ባለሱቆችን፣ ገበሬዎችንና በደቡባዊ ቻይና ከሚገኘው ባህር ዓሣ አጥምደው የሚመለሱትን ሰዎች ያነጋግራሉ።
በእውነትም በሆንግ ኮንግ “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው” ሊባል ይቻላል። (ማቴዎስ 9:37) በአሁኑ ጊዜ ከ2,300 ሰዎች ውስጥ 1ዱ የይሖዋ ምስክር ነው። የመከሩን ሥራ አጣዳፊነት በመገንዘብ እዚያ ካሉት 2,600 የመንግሥት አስፋፊዎች መካከል ወደ 600 የሚጠጉት አቅኚዎች ወይም የምሥራቹ የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች ናቸው። በሌላ ቦታ እንደሚገኙት ሁሉ በሆንግ ኮንግ ያሉት የይሖዋ ምስክሮችም ‘የይሖዋ በረከት ባለ ጠጋ እንደምታደርግ’ ተገንዝበዋል። (ምሳሌ 10:22) ስለዚህ በዚህ በበለጸገ ማኅበረሰብ ውስጥ ሌሎች ብዙ ሰዎችም እውነተኛውን ሀብት እንዲያገኙ ለመርዳት ጠንክረው በመሥራት ላይ ይገኛሉ።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ቻይና
ሆንግ ኮንግ
የደቡባዊ
ቻይና
ባህር