የአልኮል ሱሰኝነትን ታግሎ ማሸነፍ
“በሥራ ጊዜ ከጠዋቱ ወደ አራት ሰዓት ገደማ ስለመጠጥ ማሰብ እጀምራለሁ። በስድስት ሰዓት አንድ ሁለት ብርጭቆ ጠጥቼ ለመምጣት ወጣ እላለሁ። በዘጠኝ ሰዓት ሰውነቴ ይንቀጠቀጣል። ተጨማሪ ለመጠጣት እንድችል የሥራ ሰዓት የሚያልቅበትን ጊዜ በጉጉት እናፍቃለሁ። ብዙ ጊዜ ወደ ቤት ስሄድ እግረ መንገዴን አንድ ሁለት እጠጣለሁ። ወደ አንድ ሰዓት ገደማ እንደገና ጠጣ ጠጣ ይለኛል። ከዚያም ራሴን ስቼ ከወንበር እስክወድቅ ድረስ እጠጣለሁ። ሱሪዬ በሽንት ርሶ እስከጠዋት እተኛለሁ። ይህን ወስዳችሁ በሳምንቱ ሰባት ቀናት አባዙት፤ ይህን ደግሞ በአንድ ዓመት 52 ሳምንታት አባዙት፤ እንደገና ይህን በ29 ዓመት አባዙት።”
ይህ ሰው የአልኮል ሱሰኛ ነው። የአልኮል ሱስ ያለበት እሱ ብቻ አይደለም። በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከዚህ አደገኛ ሁኔታ ጋር ይታገላሉ። ዶክተር ቨርኖን ኢ ጆንሰን በገለጹት መሠረት የአልኮል ሱሰኝነት “የሰውዬውን:- አካላዊ፣ አእምሮአዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና መንፈሳዊ ሁኔታን ይጨምራል” ብለዋል።a
የአልኮል ሱሰኝነትን የሚያክሙ ባለሙያዎች የበሽታ ያክል የሆነ አልኮል ሱሰኝነት ሊድን እንደማይችል ይሁን እንጂ በሕይወት ሙሉ ከአልኮል በመራቅ በቁጥጥር ስር ሊውል የሚችል መሆኑን ይናገራሉ። አልኮል ለሕይወት የግድ አስፈላጊ ነገር ስላልሆነ ይህን እርምጃ እንድንወስድ ብንጠየቅ ምክንያተ ቢስ የሆነ ነገር አይደለም። እንዲያውም አልኮልን አለአግባብ መጠቀም የአምላክን ሞገስ ያሳጣል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) የአልኮል ሱሰኛ ሆኖ የዘላለም ሕይወት ከማጣት አልኮል ቀርቶብን ወደ አምላክ አዲስ ሥርዓት ብንገባ ይሻላል። — ማቴዎስ 5:29, 30
ከአልኮል ሱሰኝነት መላቀቅና ነፃ ሆኖ መኖር ተስፋ የሚያስቆርጥ ተፈታታኝ ትግል ነው። (ከሮሜ 7:21–24 ጋር አወዳድር።) ምን ሊረዳ ይችላል? እስቲ አንዳንድ ቀጥተኛ የሆኑ ምክሮችን እናቅርብ። ይህ ምክር እስከ ጭራሹ አልኮል የማትጠጣ ብትሆን እንኳን ከአልኮል ሱሰኝነት ጋር የሚታገሉ ጓደኞችህን ወይም ዘመዶችህን ለመርዳት የሚያስችልህን እውቀት የሚጨምርልህ ይሆናል።
ራስን በሐቅ መመልከት
አንድ ሰው ሊያሸንፈው የሚገባው አንዱ ትልቁ እንቅፋት የአልኮል ሱሰኛ መሆኑን መካድ ነው። ሐቁን መካድ ራስን መዋሸት ማለት ነው። ለመጠጣት ያለህን ነፃነት ለመጠበቅ ስትል በዓላማ ሰበብ አስባብ ለመፍጠር የሚደረግ ሙከራ ነው። ‘የእኔ የአልኮል ችግር እኮ ይህን ያህል ከባድ አይደለም። ከቤተሰቤም አልተለያየሁም። ሥራዬንም እንደያዝኩ ነኝ’ የሚል ሰበብ ታቀርብ ይሆናል። ልክነህ፣ መዘንጋት የሌለበት ነገር ግን የአልኮል ሱሰኛ ነህ።
ሐቁን መካድ ሊረዱህ የሚፈልጉ ጓደኞችህን እንዳትሰማ ሊያደርግህ ይችላል። ሮበርት የሚስቱ እንጀራ አባት ከባድ የመጠጥ ሱስ እንዳለባቸውና አነጋገራቸውም ያልታረመ መሆን እንደጀመረ ተመለከተ። “ከጥቂት ቀን በኋላ ፊት ለፊት ቀርቤ አነጋገርኳቸውና ለፀባያቸው መለወጥ መጠጥ አስተዋጽዖ እንዳደረገ ይሰማቸው እንደሆነ ጠየቅኋቸው።” ውጤቱስ ምን ሆነ? “‘ምንም ማስረጃ የለህም’ ‘እኔ ምን እንደሚሰማኝ አታውቅም’ የሚሉትን የመሳሰሉ ሐሳቦች በመሰንዘር ፈጽሞ ካዱኝ።”
የአንተ የመጠጥ አወሳሰድ ያሳሰበው የቤተሰብ አባል ወይም ጓደኛ ቀርቦ ቢያነጋግርህ ጨክነህ ሐቁን ተቀበል። (ምሳሌ 8:33) ለአንድ ሳምንት ወይም ለአንድ ወር ወይም ለብዙ ወራት ያለ መጠጥ ለመቆየት ትችላለህን? ካልሆነስ ለምን? የሐሰት ሰበቦችን እያቀረበ እራሱን እንደሚያታልለው ሰው አትሁን። ያዕቆብ እንዲህ ይላል:- “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ራሱን አይቶ ይሄዳልና፣ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል።” (ያዕቆብ 1:22–25)
ማገገም ከጀመርክ በኋላ እንኳን ቢሆን ሐቁን የመካድ ፀባይ እንዳያገረሽብህ መጠንቀቅ አለብህ። ዊልፓወር ኢዝ ኖት ኤነፍ (ውስጣዊ ፈቃድ ብቻውን በቂ አይደለም) የተባለው መጽሐፍ “ከአልኮል የተቆጠበ አዲስ ሰው ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ ለጥቂት ቀን ያህል ማቆም ስለቻለ አሁን ከችግሩ የተላቀቀ መስሎት በስህተት ሊያስብ ይችላል” ሲል ይገልጻል። ይህ ከባድ ሱስ የሚያመጣው አስተሳሰብ ነው። እንዲያውም ለማገርሸት ሲፈልግ ይህ የመጀመሪያው እርምጃ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ሐቁን የመካድ ሁኔታ እንድትቋቋመው ከፈለግህ የአልኮል ሱሰኝነትን ብቻህን ለማሸነፍ አትሞክር።
እርዳታ አግኝ
ሊዮ የተባለ አንድ ሰው የአልኮል ሱሰኝነትን ብቻውን ሊያሸንፈው እንደማይችል በመገንዘብ የአልኮል ሱሰኝነትን በማከም ልዩ ሙያ ካላቸው ሰዎች እርዳታ ፈለገ። ለተወሰነ ጊዜ በጥንቃቄ ሕክምና ከተደረገለት በኋላ ማገገም ጀመረ። ሊዮ ከባለሙያዎች እርዳታ ማግኘቱ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው ቢባል ማጋነን እንዳልሆነ ይሰማዋል።b በአካባቢህ ይህ ዓይነቱ እርዳታ የሚገኝ ከሆነ አንተም በዚህ እርዳታ ለመጠቀም ልትወስን ትችላለህ።
ከበሽታው ለመላቀቅ ሲባል መጠጥ መጠጣትን ጨርሶ ማቆም ብቻ ማለት እንዳልሆነ መገንዘብ አለብህ። ከአልኮል ሱሰኝነት በስተጀርባ ልትጋፈጣቸው የሚገባህ ጠለቅ ያሉ ጉዳዮች አሉ። እነዚህን ችላ ማለት ደግሞ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ዶክተር ቻርሎት ዴቪስ ካስል እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል:- “የችግሩ መንስዔ የሆኑት ዋነኛ ነገሮች ብልሹ ልማድ የሱስ ጥገኝነትና ለሁሉም ነገር ቸልተኛ መሆን በሐኪሞች ዘንድ ተገቢ ትኩረት ባለመሰጠቱ የተነሳ አሥራ አራት ጊዜ ሕክምና ለተደረገላቸው ሰዎች ቃለ ምልልስ አድርጌ ያለሁ።”
ደኒስ ይህ እውነት ሆኖ አግኝቶታል። “እስከ አሁን ድረስ ብዙ ችግሮች ያልተላቀቅሁ የአልኮል ሱሰኛ ነበርኩ። መጠጥ መጠጣትን ማቆም ብቻ አይበቃም። ቀደም ሲል ያሳለፍኩትን ጊዜ መለስ ብዬ መመልከት፣ በልጅነት ጊዜዬ የቀሰምኳቸውን ትምህርቶች መመርመር እነዚህ ነገሮች አሁን እንዴት እየነኩኝ እንዳሉ መረዳትና በፀባዬ በኩል አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ ነበረብኝ” ሲል ጽፏል።
ሊዮም በተመሳሳይ የማገገሙ ሂደት እንዲፋጠን ራሱን ጠለቅ ብሎ መመርመር ነበረበት። “በጣም ቀናተኛና አመፀኛ ሰው ነበርኩ። አንዴ ራሴን የማዋርድና ሌላ ጊዜ ደግሞ ከንቱ የትልቅነት ስሜት የሚሰማኝ ሰው ነበርኩ” ይላል። ሊዮ “ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ” የሚለውን በኤፌሶን 4:22 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሥራ ላይ አዋለ። አዎ ‘የቀድሞ አኗኗርህ’ በአንተነትህ ላይ ኃይለኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ጡብ የሚሰራበትን መሣሪያ ቅርጽ እንደሚይዝ ሁሉ የአንተ ባሕሪይም በከፊል የቀድሞ አኗኗርህን ቅርጽ ይይዛል። መጥፎ ባሕሪይ ሲወገድ ምን ይቀራል? ምናልባትም ለብዙ ዓመታት መጥፎ ቅርጽ ይዞ የነበረው ባሕሪይ ይቀራል። ስለዚህ ከሕመሙ ለማገገም ከቀድሞ የአኗኗር መንገድህ ጋር የሚስማማውን አሮጌውን ሰውነት መለወጥን የሚጨምር መሆን አለበት።
ከአምላክ ጋር ዝምድና መሥርት
የሊዮ ከበሽታው ማገገም ከአምላክ ጋር የግል ዝምድና መመሥረትንም የሚጠይቅ ነበር። “በይሖዋ ላይ መመካት እንዳለብኝ መማሬ ዝንባሌዬን፣ ባሕሪዬንና አመለካከቴን ሙሉ በሙሉ ለውጦታል” በማለት ይናገራል።
ይሁን እንጂ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። ከሰውም ሆነ ከአምላክ ጋር የምናደርገው ግንኙነት ግልጽ፣ ሐቀኛና ታማኝ መሆንን ይጠይቃል። የአልኮል ሱሰኝነት ሸርሽሮ የሚያጠፋቸው እነዚህን ባሕሪያት ነው። እነዚህን ባሕሪያት ኮትኩቶ ማፍራት ይቻላል፤ ነገር ግን ጊዜ ይወስዳል።
የአልኮል ሱሰኛ እንደመሆንህ መጠን ከሌላ ጋር የቅርብ ግንኙነት መመሥረት የሚያስከትለውን ጥሩ ስሜት ላታውቀው ትችላለህ። ምናልባትም ከማንም ጋር የቅርብ ግንኙነት ኖሮህ አያውቅ ይሆናል። ስለዚህ ትዕግሥተኛ ሁን። ወዲያው መጠጥ መጠጣት እንዳቆምክ ከአምላክ ጋር የቅርብ ግንኙነት ለመመሥረት በመጠበቅ ባንዴ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ አትቸኩል። አምላክንና ባሕሪያቱን ለመረዳት ጥረት አድርግ። ምናልባት ስለ ይሖዋና ስለ መንገዶች ጥልቅ የአድናቆት ስሜት የሚገልጹትን የመጽሐፍ ቅዱስ መዝሙሮች በጥንቃቄ በማንበብ ዘወትር አሰላስል።c
“ከወትሮው የበለጠ ኃይል”
በአምላክ እንድትተማመንና እንድትመካ የሚያደርግ ዝምድና በአንተ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ከበሽታው ለመዳን በምታደርገው ጥረት ይሖዋ ይደግፍሃል። (ከመዝሙር 51:10–12፤ 145:14 ጋር አወዳድር።) “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” እንደሚሰጥህ በመተማመን በማንኛውም ጊዜ ልባዊ የሆነ ጸሎት ልታቀርብለት ትችላለህ። — 2 ቆሮንቶስ 4:7፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7
እንዴት ሆነህ እንደተሠራህ ከማንኛውም ሰው ይበልጥ የሚያውቀው ፈጣሪህ ነው። (መዝሙር 103:14) በሰው ጥበብ ላይ የሚመኩ ሰብአዊ መካሪዎች የሚሰጡት ምክር እንኳን ይረዳል። ታዲያ የሰዎች ፈጣሪ በዚህ ውጊያ እንድታሸንፍ የበለጠ ሊረዳህ አይችልምን? (ኢሳይያስ 41:10፤ 48:17, 18) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ፍቅራዊ ድጋፍ ማግኘት የምትችልበትን ዝግጅት አድርጓል።
ድጋፍ ሰጪ የሆነ ሥርዓት
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ በመንፈሳዊ የበሰሉ ሽማግሌዎች ትልቅ የእርዳታ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ። በሕክምና ወይም በሥነ አእምሮ መስኮች ባለሙያ የሆኑ ሽማግሌዎች አይገኙ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ የአምላክን ቃልና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን ያውቃሉ እንዲሁም በእነሱ ይመራሉ። እነሱም “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ በበረሀም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ” ሊሆኑ ይችላሉ። (ኢሳይያስ 32:2) እነሱ በሚሰጡት እርዳታ ሙሉ በሙሉ ተጠቀም።d
እርግጥ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከሌሎች የቤተሰብ አባሎችና ከጓደኞች ጋር በመሆን የራስ ድርጊቶች ከሚያስከትሏቸው ውጤቶች አይከላከሉልህም። ካሚንግ ኦፍ ድሪንክ (ከመጠጥ መላቀቅ) የተባለው ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “የመጠጥ ሱሰኞችን ለማከም ወሳኝ የሆነው ነገር የመጠጥ ጥገኛ መሆን የሚያስከትላቸውን ጉዳቶች የአልኮል ሱሰኞቹ እንዲጋፈጧቸው ማድረግና ለመጥፎ ጸባያቸው ኃላፊነት እንዲወስዱ ማድረግ ነው።” በደግነት ቢይዙህም ችግርህን ፊት ለፊት ይነግሩሃል፤ ከአልኮል ጋር በምታደርገው ውጊያ አሸናፊ እድትሆን በማሰብ እውነታውን እንድትቀበልና የሚያስፈልግህን ሕክምናና ፀባይ በጥብቅ እንድትከተል ያበረታቱሃል።
ከአልኮል ሱሰኝነት መላቀቁ የአንተው ኃላፊነት ነው
ሌሎች የሚሰጡትን ጠቃሚ እርዳታ ማግኘት ብትችልም ማንም ሰው ወይም መንፈስ ከሱሱ እንድትላቀቅ ሊያስገድድህ እንደማይችል ማወቅ ያስፈልግሃል። ነፃ ፈቃድ ያለህ ፍጡር ነህ። ግራም ነፈሰ ቀኝ ከአልኮል ሱሰኝነት መላቀቅ የአንተው ኃላፊነት ነው። (ከዘፍጥረት 4:7፤ ዘዳግም 30:19, 20፤ ፊልጵስዩስ 2:12 ጋር አወዳድር።) ይህን ኃላፊነት ተቀበል፤ ይሖዋም ይረዳሃል። በ1 ቆሮንቶስ 10:13 ላይ “ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፣ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል” የሚል ማረጋገጫ ተሰጥቶናል። እንግዲያው ተጽናና ከአልኮል ሱሰኝነት ጋር በምታደርገው ትግል ልታሸንፍ ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ምንም እንኳን የአልኮል ሱሰኝነትን በወንድ ብንጠቅስም እዚህ ውስጥ ያሉት መሠረታዊ ሥርዓቶች ለሴት የአልኮል ሱሰኞችም እኩል ይሠራሉ።
b እርዳታ መስጠት የሚችሉ ብዙ የሕክምና ማዕከሎች፣ ሆስፒታሎችና ሌሎች የማገገሚያ ፕሮግራሞች አሉ። መጠበቂያ ግንብ ለይቶ የሚደግፈው የሕክምና ዓይነት የለም። አንድ ሰው ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆኑትን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሚያስጥሱ እንቅስቃሴዎች እንዳይካፈል ጥንቃቄ ማደረግ አለበት። ዞሮ ዞሮ እያንዳንዱ ሰው ምን ዓይነት ሕክምና እንደሚያስፈልገው ለራሱ መወሰን አለበት።
c አንዳንዶቹ ምሳሌዎች መዝሙር 8፣ 9፣ 18፣ 19፣ 24፣ 51፣ 55፣ 63፣ 66፣ 73፣ 77፣ 84፣ 86፣ 90፣ 103፣ 130፣ 135፣ 139፣ 145 ናቸው።
d በግንቦት 1, 1983 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 8–11 ላይ ለሽማግሌዎች የሚሆኑ ጠቃሚ መመሪያዎች ወጥተዋል።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአልኮል ሱሰኝነት የሚያፈራው ወራዳ ሁኔታና ጉስቁልና ደርሶብህ ይሆናል። ቢሆንም ተስፋ አትቁረጥ። እርዳታ ማግኘት ትችላለህ።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንድ ቀን ችግሩ ቢያገረሽብህ
ዊልፓወር ኢዝ ኖት ኤነፍ (ውስጣዊ ፈቃድ ብቻውን በቂ አይደለም) የተባለው መጽሐፍ “አንድ ቀን ችግሩ ሊያገረሽብኝ ይችል ይሆናል ብሎ መዘጋጀት ልክ የእሳት ማጥፊያ መሣሪያ አዘጋጅቶ እንደማስቀመጥ ነው። ቃጠሎ ይነሳል ብለህ ትጠብቃለህ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን እሳት ቢነሳ አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነህ ማለት ነው” ይላል። እንግዲያው አንድ ቀን ችግሩ ቢያገረሽብህ:-
□ ወደ ይሖዋ ጸልይ። ችግርህ እንደሚገባውና ሊረዳህ እንደሚፈልግ እርግጠኛ ሁን። — መዝሙር 103:14፤ ኢሳይያስ 41:10
□ ወደ ክርስቲያን ሽማግሌ ቀርበህ ችግርህን አጫውተው። ማናገር ቢያስፈልግህ ማንን ማነጋገር እንደሚኖርብህ በቅድሚያ ወስነህ ቆይ። የተከሰተውን ሁኔታ በሐቅ ተናገር። እንዲሁም የሚሰጥህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በጥንቃቄ አዳምጥ።
□ ተስፋ ከመቁረጥ ራስህን ጠብቅ። ራስህን መጥላት ሙሉ በሙሉ እንዲያገረሽብህ ያደርጋል። ስለዚህ ስህተትህን በተገቢው ሁኔታ ተመልከተው። አንድ ቀን በውጊያው ተሸነፍክ ማለት ደግሞ በጠቅላለው በውጊያው ተሸንፈሃል ማለት አይደለም። አንድ የማራቶን ሯጭ ሲወድቅ ከወደቀበት ተነስቶ ውድድሩን ይቀጥላል እንጂ እንደገና ተመልሶ ሩጫው ወደተጀመረበት መሥመር አይሄድም። አንተም ከበሽታው ለመላቀቅ በምታደርገው ትግል እንደዚሁ አድርግ። አሁንም ከትግሉ ጎዳና አልወጣህም። ከመጠጥ የተቆጠብክባቸው ሳምንታት፣ ወራት ወይም ዓመታት አሁንም አሉ።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጨክነህ ራስህን በሐቅ ብትመለከት እውነቱን ከመካድ ትድናለህ።