ጽናት ለክርስቲያኖች እጅግ አስፈላጊ ነው
“በእምነታችሁ [ላይ] . . . መጽናትን . . . ጨምሩ። ” — 2 ጴጥሮስ 1:5, 6
1, 2. ሁላችንም እስከ መጨረሻው መጽናት ያለብን ለምንድን ነው?
አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካችና ባለቤቱ በ90ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ አንድ ክርስቲያን ወንድማቸውን ለመጠየቅ ሄደው ነበር። ይህ ወንድም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ብዙ አሥርተ ዓመታት አሳልፏል። በሚጨዋወቱበት ጊዜ አረጋዊው ወንድም ባለፉት ዓመታት ካገኛቸው መብቶች አንዳንዶቹን እያስታወሰ ነገራቸው። እንባው በጉንጮቹ ላይ ኮለል ብሎ እየወረደ “አሁን ግን ብዙ መሥራት አልችልም” ሲል በሐዘን ተናገረ። ተጓዥ የበላይ ተመልካቹም መጽሐፍ ቅዱሱን ገለጠና ኢየሱስ “እስከ መጨረሻው የሚጸና . . . እርሱ ይድናል” ሲል የተናገረበትን ማቴዎስ 24:13ን አውጥቶ አነበበለት። ከዚያም የበላይ ተመልካቹ ይህን ውድ ወንድማችንን እየተመለከተ “ምንም ያህል ብዙ ወይም ጥቂት ሥራ ብንሠራ ሁላችንም የተሰጠን ትልቁ ተልዕኰ እስከ መጨረሻው ጸንቶ መገኘት ነው” አለው።
2 አዎን፤ እስከዚህ ሥርዓት መጨረሻ ድረስ ወይም እስከ ሕይወታችን ፍጻሜ ድረስ ሁላችንም መጽናት አለብን። ለመዳን የሚያስችለንን የይሖዋን ሞገስ የምናገኝበት ሌላ ምንም መንገድ የለም። የምንገኘው በሕይወት ሩጫ ውስጥ ነው። የሩጫውን የመጨረሻ መስመር እስክናልፍ ድረስም ‘በጽናት መሮጥ’ አለብን። (ዕብራውያን 12:1 አዓት) ሐዋርያው ጴጥሮስ የዚህን ባሕርይ አስፈላጊነት አጥብቆ ሲገልጽ ክርስቲያኖችን “በእምነታችሁ [ላይ] . . . መጽናትን . . . ጨምሩ” ሲል መክሯል። (2 ጴጥሮስ 1:5, 6) ግን መጽናት ማለት ምን ማለት ነው?
መጽናት ማለት ምን ማለት ነው?
3, 4. መጽናት ማለት ምን ማለት ነው?
3 መጽናት ማለት ምን ማለት ነው? “መጽናት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል (ሃይፖሜኖ) ቃል በቃል ሲተረጎም “ባሉበት መቆየት ወይም መቀጠል” ማለት ነው። ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 17 ጊዜ ተጠቅሷል። የመዝገበ ቃላት አዘጋጆች በሆኑት በደብልዩ ባወር፣ በኤፍ ደብልዩ ጊንግሪች እና በኤፍ ዳንከር መሠረት ቃሉ “ከመሸሽ ይልቅ በነበሩበት መቆየት . . .፣ ከአቋም ፍንክች አለማለት፣ ችግሩን መቋቋም” የሚል ትርጉም አለው። “ጽናት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ስም (ሃይፖሜኔ) ከ30 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል። በዊልያም ባርክሌይ የተዘጋጀው ኤ ኒው ቴስታመንት ወርድቡክ የተሰኘው መጽሐፍ ይህንን ቃል አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “ቃሉ አንድን ነገር በትዕግሥት ብቻ ሳይሆን ደስ የሚያሰኝ ተስፋ ይዞ የመቻልን መንፈስ ያመለክታል። . . . አንድ ሰው ፊቱን ነፋስ ወደሚመጣበት አቅጣጫ አዙሮ ሳይንገዳገድ እንዲቆም የሚያስችለው ባሕርይ ነው። ከባዱን መከራ ወደ ክብር ለመለወጥ የሚችል መልካም ባሕርይ ነው፤ ምክንያቱም ከስቃዩ በስተጀርባ ያለውን ግቡን አሻግሮ ይመለከታል።”
4 እንግዲያው ጽናት ከአቋማችን ፍንክች ሳንል እንድንቆምና ዕንቅፋቶች ወይም ችግሮች ቢያጋጥሙንም ተስፋ እንዳንቆርጥ ያደርገናል። (ሮሜ 5:3–5) በጊዜው ካለው ሥቃይ በስተጀርባ ያለውን ግብ ማለትም በሰማይም ሆነ በምድር ላይ ዘላለማዊ ሕይወት የማግኘትን ሽልማት ወይም ስጦታ አሻግሮ ይመለከታል። — ያዕቆብ 1:12
መጽናት ለምን አስፈለገ?
5. (ሀ) ሁሉም ክርስቲያኖች ‘መጽናት የሚያስፈልጋቸው’ ለምንድን ነው? (ለ) የሚደርሱብን ፈተናዎች በምን ሁለት ክፍሎች ሊከፈሉ ይችላሉ?
5 ክርስቲያኖች ስለሆንን ሁላችንም ‘መጽናት ያስፈልገናል።’ (ዕብራውያን 10:36) ለምን? መሠረታዊው ምክንያት “ልዩ ልዩ ፈተና” ስለሚደርስብን ነው። ይህ በያዕቆብ 1:2 ላይ የሚገኘው ጥቅስ በግሪክኛው ቋንቋ አንድ ሰው ዘራፊ ሲያጋጥመው ከሚሰማው ድንገተኛ ወይም የማያስደስት ገጠመኝ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ያመለክታል። (ከሉቃስ 10:30 ጋር አወዳድር።) የሚደርሱብን ፈተናዎች በሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ፤ እነርሱም:- በወረስነው ኃጢአት ምክንያት በሰው ሁሉ ላይ የሚደርሱ መከራዎችና ለአምላክ ያደርን በመሆናችን ምክንያት የሚደርሱብን መከራዎች ናቸው። (1 ቆሮንቶስ 10:13፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:12 አዓት) ከነዚህ ፈተናዎች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
6. አንድ የይሖዋ ምስክር የደረሰበትን የሚያሰቃይ ሕመም በጽናት የተቋቋመው እንዴት ነበር?
6 ከባድ ሕመም። አንዳንድ ክርስቲያኖች እንደ ጢሞቴዎስ ‘በተደጋጋሚ የሚመላለስባቸውን በሽታ’ ችለው ለመኖር ተገደዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:23) በተለይም ሥር የሰደደ፣ ምናልባትም በጣም የሚያሰቃይ በሽታ ሲይዘን በአምላክ እርዳታ መጽናት፣ ከአቋማችን ፍንክች ሳንል መቆምና ክርስቲያናዊ ተስፋችን እንዳይደበዝዝብን መጠበቅ ያስፈልገናል። ፈጥኖ በሚሰራጭ የካንሰርነት ባሕርይ ያለው እጢ ምክንያት ከደረሰበት ሥቃይ ጋር ለረጅም ጊዜ ሲታገል የቆየውን በ50ዎቹ ዓመታት ዕድሜው መጀመሪያ ላይ የሚገኝ የአንድ ምስክር ምሳሌ ተመልከቱ። ሁለት ጊዜ ቀዶ ሕክምና ሲደረግለት ደም ላለመውሰድ ባለው አቋም ጸንቷል። (ሥራ 15:28, 29) ሆኖም እጢው እንደገና በሆዱ ውስጥ ከመውጣቱም በላይ በአከርካሪው አጠገብ ማደግ ጀመረ። እብጠቱ እየጨመረ ሲሄድ ይህ ወንድም ምንም ዓይነት መድኃኒት ሊያስታግሰው የማይችል ከፍተኛ አካላዊ ሥቃይ ደረሰበት። ይሁን እንጂ በጊዜው ከነበረበት ሥቃይ ባሻገር በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚያገኘውን የሕይወት ሽልማት ይመለከት ነበር። ስለዚህም በውስጡ ይንቀለቀል የነበረውን ተስፋ ለዶክተሮች፣ ለነርሶችና ሊጠይቁት ለመጡት ሰዎች ማካፈሉን አላቆመም። ወንድም እስከ መጨረሻው ማለትም እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ጸና። ያለብህ የጤና ችግር ለሕይወትህ የማያሰጋ ሊሆን ወይም ይህ የተወደደ ወንድም የደረሰበትን ያህል የሚያሰቃይ ላይሆን ቢችልም ትልቅ የጽናት ፈተና ሊያመጣብህ ይችላል።
7. ለአንዳንድ መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መጽናት ምን ዓይነት ሥቃይንም ጭምር መቋቋምን ይጨምራል?
7 ስሜታዊ ሥቃይ። አልፎ አልፎ አንዳንድ የይሖዋ ምስክሮች ‘በልብ ሐዘን’ ምክንያት የሚመጣ ‘የመንፈስ መሰበር’ ያጋጥማቸዋል። (ምሳሌ 15:13 አዓት) በዚህ ‘አስጨናቂ ዘመን’ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ማጋጠሙ እንግዳ ነገር አይደለም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ሳይንስ ኒውስ የተባለው መጽሔት በታኅሣሥ 5, 1992 እትሙ እንዲህ በማለት ሪፖርት አድርጓል:- “ከባድ፣ ብዙውን ጊዜም አካልን የሚያደክም የመንፈስ ጭንቀት ከ1915 ወዲህ ባለው ትውልድ ላይ በየዓመቱ እየጨመረ ሄዷል።” ለዚህ ዓይነቱ የመንፈስ ጭንቀት መንስኤ የሚሆኑት ነገሮች ከሥነ አእምሮአዊ ችግሮች አንስቶ አስከፊ እስከሆኑ ገጠመኞች ድረስ የተለያዩ ናቸው። አንዳንድ ክርስቲያኖች በየዕለቱ የሚደርስባቸውን ስሜታዊ ቀውስ ተቋቁመው ለመጽናት ተገደዋል። ሆኖም እጃቸውን አይሰጡም፤ እያነቡም ቢሆን ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ይቆያሉ። — ከመዝሙር 126:5, 6 ጋር አወዳድር።
8. ምን ዓይነት የገንዘብ ችግር ሊያጋጥመን ይችላል?
8 የሚያጋጥሙን የተለያዩ ፈተናዎች ከባድ የኢኮኖሚ ችግርንም የሚጨምሩ ሊሆኑ ይችላሉ። በኒው ጀርሲ ዩ ኤስ ኤ የሚኖር አንድ ወንድም በድንገት ከሥራ ሲወጣ ቤተሰቡን የመመገቡና መኖሪያ ቤቱን የማጣቱ ጉዳይ አሳሰበው። ነገሩ ለምን እንዳሳሰበው ሊገባን ይችላል። ይሁን እንጂ የመንግሥቱ ተስፋ እንዲጨልምበት አልፈቀደም። ሌላ ሥራ እያፈላለገ ይህንን አጋጣሚ ረዳት አቅኚ ሆኖ ለማገልገል ተጠቀመበት። በመጨረሻም ሥራ አገኘ። — ማቴዎስ 6:25–34
9. (ሀ) የምንወደው ሰው መሞት ጽናት ሊጠይቅብን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) የሐዘን እንባ ማንባት ስህተት እንዳልሆነ የሚያሳዩት የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው?
9 የምትወደው ሰው በሞት ተለይቶህ ከሆነ ሊያጽናኑህ የመጡት ሰዎች ሁሉ ወደወትሮው ተግባራቸው ከተመለሱ በኋላ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ጽናት እንዲኖርህ ያስፈልጋል። በተለይ በየዓመቱ ያ የምትወደው ሰው የሞተበት ቀን ሲደርስ ሐዘኑ ይከብድብህ ይሆናል። ይህን ዓይነት ሐዘን ችሎ መጽናት ይገባል ሲባል ግን የሐዘን እንባ ማፍሰስ ስህተት ነው ማለት አይደለም። አንድ የምንወደው ሰው ሲሞት ማዘን ተፈጥሮአዊ ባሕርይ ነው። በትንሣኤ ተስፋ ላይ እምነት እንደሌለን በጭራሽ አያመለክትም። (ዘፍጥረት 23:2፤ ከዕብራውያን 11:19 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ አልዓዛር ከሞተ በኋላ ለማርታ “ወንድምሽ ይነሳል” ብሎ በእርግጠኛነት ቢነግራትም ‘እንባውን አፍስሷል።’ አልዓዛርም ኢየሱስ እንዳለው ተነስቷል! — ዮሐንስ 11:23, 32–35, 41–44
10. የይሖዋ ሕዝቦች ከሌሎች ሰዎች በተለየ መንገድ መጽናት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
10 በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሱት መከራዎች በተጨማሪ የይሖዋ ሕዝቦች በተለየ መንገድ መጽናት ያስፈልጋቸዋል። ኢየሱስ “ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” ሲል አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 24:9) እንዲሁም “እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል” ብሏል። (ዮሐንስ 15:20) ይህ ሁሉ ጥላቻና ስደት የሚደርስብን ለምንድን ነው? የትም ቦታ እንኑር የአምላክ አገልጋዮች በመሆናችን ሰይጣን ለይሖዋ ያለንን የታማኝነት አቋም ሊያበላሽብን ስለሚጥር ነው። (1 ጴጥሮስ 5:8፤ ከራእይ 12:17 ጋር አወዳድር።) ሰይጣን ይህን ዓላማውን ለማሳካት ሲል የስደቱን እሳት እያራገበ ጽናታችን ከባድ ፈተና እንዲደርስበት ያደርጋል።
11, 12. (ሀ) የይሖዋ ምስክሮችና ልጆቻቸው በ1930ዎቹና በ1940ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ምን የጽናት ፈተና አጋጥሟቸው ነበር? (ለ) የይሖዋ ምስክሮች ለብሔራዊ አርማ ሰላምታ የማይሰጡት ለምንድን ነው?
11 ለምሳሌ ያህል በ1930ዎቹና በ1940ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ በዩናይትድ ስቴትስና በካናዳ ይኖሩ የነበሩ የይሖዋ ምስክሮችና ልጆቻቸው በኅሊናቸው ምክንያት ለብሔራዊው አርማ ሰላምታ አንሰጥም ስላሉ ስደት ደርሶባቸው ነበር። ምስክሮቹ የሚኖሩበትን አገር ብሔራዊ አርማ የሚያከብሩ ቢሆንም በአምላክ ሕግ ውስጥ በዘጸአት 20:4, 5 ላይ የተሰጠውን እንዲህ የሚል መሠረታዊ ሥርዓት ይፈጽማሉ:- “በላይ በሰማይ ካለው፣ በታችም በምድር ካለው፣ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፣ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፣ አታምልካቸውምም፤ . . . እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና።” በትምህርት ላይ የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች የሆኑ አንዳንድ ልጆች ይሖዋ አምላክን ብቻ ለማምለክ በመፈለጋቸው ምክንያት ከትምህርት ቤት ተባረዋል። በዚህም ምክንያት ምስክሮቹ ልጆቹን ለማስተማር የመንግሥቱን ትምህርት ቤቶች አቋቁመዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው ጊዜ ያሉ ስለ ጉዳዩ የተረዱ መንግሥታት እንደሚያደርጉት የምስክሮቹን ሃይማኖታዊ አቋም ካወቀላቸው በኋላ እነዚህ ተማሪዎች ወደ ሕዝብ ትምህርት ቤቶች ተመልሰዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ወጣቶች በድፍረት ያሳዩት ጽናት በመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች መሠረት ለመኖር ጥረት በማድረጋቸው የተነሳ መሳቂያና መሳለቂያ ለሆኑት የዘመናችን ክርስቲያን ወጣቶች አብነት ሆኖ ያገለግላል። — 1 ዮሐንስ 5:21
12 በሰው ሁሉ የሚደርሱትም ይሁኑ በክርስቲያናዊ እምነታችን የተነሳ የሚመጡብን የተለያዩ ፈተናዎች መጽናት አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ያሳያሉ። ይሁን እንጂ መጽናት የምንችለው እንዴት ነው?
እስከ መጨረሻው መጽናት የሚቻለው እንዴት ነው?
13. ይሖዋ ጽናትን የሚጨምርልን እንዴት ነው?
13 የአምላክ ሕዝቦች ይሖዋን ከማያመልኩት ሰዎች ይልቅ ለመጽናት በሚያስችል የተሻለ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የተረጋገጠ ነው። እርዳታ ለማግኘት “ጽናት የሚሰጠውን አምላክ” መጠየቅ እንችላለን። (ሮሜ 15:5 አዓት) ይሁን እንጂ ይሖዋ ጽናት የሚሰጠን እንዴት ነው? አንዱ መንገድ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው በሚገኙት የጽናት ምሳሌዎች አማካኝነት ነው። (ሮሜ 15:4) ለጽናት አርዓያ ስለሚሆኑ ስለነዚህ ሰዎች ስናሰላስል ለመጽናት ከመበረታታታችንም በላይ እንዴት መጽናት እንደሚቻልም የበለጠ እንማራለን። በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት የጽናት አርዓያዎች ውስጥ ሁለቱን ማለትም ኢዮብ በድፍረት ያሳየውን ጽናትና የኢየሱስ ክርስቶስን እንከን የለሽ ጽናት እንመልከት። — ዕብራውያን 12:1–3፤ ያዕቆብ 5:11
14, 15. (ሀ) ኢዮብ በጽናት የተቋቋመው ምን ዓይነት መከራዎችን ነው? (ለ) ኢዮብ ያጋጠሙትን ፈተናዎች በጽናት ሊቋቋማቸው የቻለው እንዴት ነው?
14 የኢዮብ ጽናት እንዲፈተን ያደረጉት ሁኔታዎች ምን ነበሩ? ኢዮብ አብዛኛውን ንብረቱን በማጣቱ ምክንያት የኢኮኖሚ ችግር ደረሰበት። (ኢዮብ 1:14–17፤ ከኢዮብ 1:3 ጋር አወዳድር።) አሥሩም ልጆቹ በዐውሎ ንፋስ ሲሞቱበት ከፍተኛ ሐዘን ተሰምቶታል። (ኢዮብ 1:18–21) ከባድና በጣም የሚያሰቃይ በሽታ ይዞት ነበር። (ኢዮብ 2:7, 8፤ 7:4, 5) የገዛ ሚስቱ አምላክን እንዲክድ ትገፋፋው ነበር። (ኢዮብ 2:9) የቅርብ ወዳጆቹ የሚጎዱ፣ ደግነት የጎደላቸውና እውነት ያልሆኑ ነገሮችን ተናገሩት። (ኢዮብ 16:1–3 እና ኢዮብ 42:7ን አወዳድር።) ይህ ሁሉ ቢደርስበትም ኢዮብ ከአቋሙ ፍንክች ሳይል ንጹሕ አቋሙን ጠብቋል። (ኢዮብ 27:5) ኢየሱስ በጽናት የተቋቋማቸው ችግሮች በዛሬው ጊዜ የሚገኙት የይሖዋ ሕዝቦች ከሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች ጋር ተመሳሳይ ናቸው።
15 ኢዮብ በእነዚያ ሁሉ ፈተናዎች ችሎ ሊጸና የቻለው እንዴት ነው? ኢዮብን የረዳው አንዱና ዋነኛው ነገር ተስፋ ነው። “ዛፍ ቢቆረጥ ደግሞ ያቆጠቁጥ ዘንድ፣ ቅርንጫፉም እንዳያልቅ ተስፋ አለው” ሲል ገለጸ። (ኢዮብ 14:7) ኢዮብስ ምን ተስፋ ነበረው? ከጥቂት ቁጥሮች በኋላ እንዲህ ሲል እንደተናገረ እንመለከታለን:- “በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን? . . . በጠራኸኝና በመለስሁልህ ነበር፣ የእጅህንም ሥራ በተመኘኸው ነበር።” (ኢዮብ 14:14, 15) አዎን፤ ኢዮብ በጊዜው ከደረሰበት ሥቃይ ባሻገር የሚኖረውን ሁኔታ ተመልክቷል። መከራው ለዘላለም እንደማይቆይ ያውቅ ነበር። ግፋ ቢል መጽናት የሚኖርበት እስከ ሞት ድረስ ብቻ ነው። ሙታንን ለማስነሳት ፍቅራዊ ምኞት ያለው ይሖዋ ወደ ሕይወት እንደሚመልሰው በተስፋ ይጠባበቅ ነበር። — ሥራ 24:15
16. (ሀ) ከኢዮብ ምሳሌ ስለ ጽናት ምን እንማራለን? (ለ) የመንግሥቱ ተስፋ የቱን ያህል እውን ሊሆንልን ይገባል? ለምንስ?
16 ከኢዮብ ጽናት ምን እንማራለን? እስከ መጨረሻው ለመጽናት ከፈለግን ተስፋችን በፍጹም ሊጨልምብን አይገባም። የመንግሥቱ ተስፋ የተረጋገጠ በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ የሚደርስብን ማንኛውም መከራ ከተስፋችን ጋር ሲነፃፀር ‘በጣም አጭር’ መሆኑንም አስታውስ። (2 ቆሮንቶስ 4:16–18) ውድ ተስፋችን በጽኑ የተመሠረተው ይሖዋ ‘እንባዎችንም ሁሉ [ከዓይኖቻችን] የሚያብስበት፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ የማይሆንበት ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ የማይሆንበት’ ጊዜ በቅርቡ ይመጣል ሲል በገባልን ቃል ላይ ነው። (ራእይ 21:3, 4) ‘የማያሳፍረን’ ይህ ተስፋ አስተሳሰባችንን መጠበቅ ይኖርበታል። (ሮሜ 5:4, 5፤ 1 ተሰሎንቄ 5:8) ይህ ተስፋ አዲሱ ዓለም ውስጥ ገብተን ከበሽታና ከጭንቀት ጋር መታገላችን ቀርቶ በየቀኑ ጠዋት ጠዋት ጥሩ ጤናና ንጹሕ አእምሮ ይዘን ስንነሳ፣ ስለ ከባድ የኢኮኖሚ ችግር መጨነቃችን ቀርቶ የተረጋጋ ኑሮ ስንኖር፣ ለሞቱ ወዳጆቻችን ማልቀስ ቀርቶ ከሞት ሲነሱ እያየን ስንደሰት በእምነት ዓይናችን እስኪታየን ድረስ እውን ሊሆንልን ይገባል። (ዕብራውያን 11:1) ይህ ተስፋ ከሌለን በአሁኑ ጊዜ በሚደርሱብን ፈተናዎች ልንሸነፍና ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። እንዲህ ያለ ተስፋ ስላለን በትግላችን እንድንገፋና እስከ መጨረሻው ድረስ እንድንጸና የሚያስችለን ከፍተኛ ምክንያት አለን።
17. (ሀ) ኢየሱስ በጽናት የተቋቋመው ምን ዓይነት መከራዎችን ነው? (ለ) ኢየሱስ በጽናት የቻለው መከራ ምን ያህል ከባድ እንደነበረ ከምን መረዳት ይቻላል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
17 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን ‘ትኩር ብለን እንድንመለከትና’ ስለ እርሱም ‘እንድናስብ’ አጥብቆ ይመክረናል። ኢየሱስ የጸናባቸው መከራዎች ምንድን ናቸው? ከፈተናዎቹ አንዳንዶቹ በሌሎች ኃጢአትና አለፍጽምና ምክንያት የመጡ ናቸው። ኢየሱስ ችሎ የጸናው ‘ከኀጢአተኞች የደረሰበትን መቃወም’ ብቻ ሳይሆን በደቀ መዛሙርቱ መካከል ማን ታላቅ እንደሚሆን የተነሳውን ተደጋጋሚ ጭቅጭቅና በመካከላቸው የተነሱ ሌሎች ችግሮችን ጭምር ነበር። ከዚህም በላይ በማንም ላይ ደርሶ የማያውቅ የእምነት ፈተናም አጋጥሞታል። ‘በመከራ እንጨት ላይ እስከመሞት ጸንቷል።’ (ዕብራውያን 12:1–3 አዓት፤ ሉቃስ 9:46፤ 22:24) መሰቀሉና የአምላክን ስም እንደተሳደበ ተቆጥሮ በውርደት መገደሉ ያስከተለበትን የአእምሮና የአካል ሥቃይ መገመት እንኳን ያስቸግራል።a
18. ሐዋርያው ጳውሎስ በተናገረው መሠረት ኢየሱስን የረዱት ምን ሁለት ነገሮች ናቸው?
18 ኢየሱስን እስከ መጨረሻው እንዲጸና ያስቻለው ነገር ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስን የረዱትን ሁለት ነገሮች ጠቅሷል። እነርሱም:- ‘ጸሎትና ምልጃ’ እንዲሁም ‘በፊቱ ያለው ደስታ’ ናቸው። ፍጹሙ የአምላክ ልጅ ኢየሱስ እርዳታ ለመጠየቅ አላፈረም። “በብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር” ወደ አምላክ ጸለየ። (ዕብራውያን 5:7፤ 12:2) በተለይ የመጨረሻው ከፍተኛ መከራ የሚደርስበት ጊዜ እየተቃረበ ሲሄድ ጥንካሬ እንዲሰጠው በተደጋጋሚና በጥብቅ መጸለይ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል። (ሉቃስ 22:39–44) ይሖዋ ኢየሱስ ላቀረበው ምልጃ መልስ የሰጠው መከራውን በማስወገድ ሳይሆን መከራውን ለመቋቋም የሚያስችለውን ብርታት በመስጠት ነበር። ኢየሱስ የጸናው ከመከራው እንጨት በስተጀርባ የሚያገኘውን ሽልማት ማለትም ለይሖዋ ስም መቀደስና የሰውን ልጆች ቤተሰብ ከሞት ለመቤዠት አስተዋጽዖ በማድረጉ የሚያገኘውን ደስታ አሻግሮ ስለተመለከተ ነው። — ማቴዎስ 6:9፤ 20:28
19, 20. ጽናት ስለሚያጠቃልላቸው ነገሮች ከእውነታው ያልራቀ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን የኢየሱስ ምሳሌ የረዳን እንዴት ነው?
19 ከኢየሱስ ምሳሌ ጽናት ስለሚያጠቃልላቸው ነገሮች ከእውነታው ያልራቀ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን የሚረዱንን ብዙ ነገሮች እንማራለን። የጽናት ጎዳና ቀላል አይደለም። አንድን ፈተና መቋቋም ከከበደን ኢየሱስም እንዲሁ ተሰምቶት እንደነበረ ማወቃችን ያጽናናናል። እስከ መጨረሻው ለመጽናት ከፈለግን ኃይል እንዲሰጠን ደጋግመን መጸለይ አለብን። ፈተና ሲደርስብን አንዳንድ ጊዜ ለመጸለይ እንኳን የማንበቃ እንደሆንን ሊሰማን ይችላል። ይሖዋ ግን ‘ስለሚያስብልን’ ልባችንን እንድናፈስስለት ይጋብዘናል። (1 ጴጥሮስ 5:7) በተጨማሪም በቃሉ ውስጥ በሰጠን ተስፋ መሠረት በእምነት ለሚለምኑት ‘ከተለመደው በላይ የሆነውን ኃይሉን’ ይሰጣቸዋል። — 2 ቆሮንቶስ 4:7–9 አዓት
20 አንዳንድ ጊዜ እያነባን ለመጽናት እንገደድ ይሆናል። ኢየሱስን ያስደሰተው በመከራ እንጨት ላይ የደረሰበት ሥቃይ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እርሱን ያስደሰተው በፊቱ ያለው ሽልማት ነበር። እኛም ፈተና ሲደርስብን ሁልጊዜ በደስታ እንፈነድቃለን ብለን ካሰብን የማይቻለውን ነገር መጠበቅ ይሆንብናል። (ከዕብራውያን 12:11 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ ሽልማታችንን አሻግረን በመመልከት የሚያጋጥመንን በጣም አስቸጋሪ የሆነ ሁኔታ እንኳን ‘እንደ ሙሉ ደስታ’ ልንቆጥር እንችላለን። (ያዕቆብ 1:2–4፤ ሥራ 5:41) ዋናው ነገር እያነባንም ቢሆን ጸንተን መቆየታችን ነው። ኢየሱስ ያለው ‘ከሁሉ ያነሰ እንባ ያፈሰሰ ይድናል’ ሳይሆን “እስከ መጨረሻው የሚጸና . . . እርሱ ይድናል” ነው። — ማቴዎስ 24:13
21. (ሀ) በ2 ጴጥሮስ 1:5, 6 ላይ በጽናታችን ላይ ምን እንድንጨምር በጥብቅ ተመክረናል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ምን ጥያቄዎች ይመረመራሉ?
21 እንግዲያው ለመዳን መጽናት እጅግ ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ በ2 ጴጥሮስ 1:5, 6 ላይ በጽናታችን ላይ ለአምላክ ያደሩ መሆንን እንድንጨምር በጥብቅ ተመክረናል። ለአምላክ ያደሩ መሆን ምን ማለት ነው? ከጽናት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው? ለአምላክ ያደሩ የመሆንን ባሕርይ ልታገኝ የምትችለውስ እንዴት ነው? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ይመረመራሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኢየሱስ ፍጹም አካሉ በእንጨት ላይ ከተሰቀለ ብዙም ሳይቆይ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ መሞቱ ችሎ የጸናው መከራ የቱን ያህል ከባድ እንደነበረ ያሳያል። ከጎኑ የተሰቀሉትን ክፉ አድራጊዎች ሞት ለማፋጠን ግን እግራቸውን መስበር አስፈልጎ ነበር። (ዮሐንስ 19:31–33) ኢየሱስ ከመሰቀሉ በፊት እንቅልፍ ባይኑ ሳይዞር ባሳለፈው ሌሊት የደረሰበትን ዓይነት አእምሮአዊና አካላዊ ሥቃይ በእነርሱ ላይ አልደረሰም። የደረሰበት ሥቃይ በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ የሚሰቀልበትን የመከራ እንጨት እንኳን መሸከም እስከሚያቅተው ድረስ አድክሞት የነበረ ይመስላል። — ማርቆስ 15:15, 21
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ መጽናት ማለት ምን ማለት ነው?
◻ የይሖዋ ሕዝቦች ከሌሎች ሰዎች በተለየ መንገድ መጽናት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
◻ ኢዮብን እንዲጸና ያስቻለው ነገር ምንድን ነው?
◻ የኢየሱስ ምሳሌ ጽናትን በሚመለከት ከእውነታው ያልራቀ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን የሚረዳን እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋን ብቻ ለማመልክ በመፈለጋቸው ምክንያት ከትምህርት ቤት የተባረሩትን ክርስቲያን ልጆች ለማስተማር የመንግሥቱ ትምህርት ቤቶች ተቋቁመው ነበር
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ አባቱን ለማስከበር ስለቆረጠ መጽናት ይችል ዘንድ ብርታት እንዲሰጠው ጸልዮአል