ለተሳካ የቤተሰብ ኑሮ ቁልፍ የሆነው ነገር
ባለፈው ዓመት አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንታዊ እጩ “እየተዳከመ የሚሄድ የቤተሰብ ተቋም አለን” ሲሉ አስገንዝበዋል። በእውነቱ ቤተሰብ እስከምን ድረስ እንደተዳከመ መስማቱ ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ዜና ነው። “በዚሁ ወቅት በኢኮኖሚና በኢንዱስትሪ መስኮች ያን ያህል ለውጥ ቢታይ ኖሮ በድንጋጤ ፈዘን እንቀር ነበር” በማለት ፎርቹን የተባለው መጽሔት አትቷል።
የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመከተል የሚጥሩ ቤተሰቦችም እንኳን ብዙ ጊዜ በዚህ ጉዳይ በአሳዛኝ ሁኔታ ይነካሉ። ከጥቂት ዓመታት በፊት ከአሥራዎቹ ዕድሜ በታች የሚገኙ ስድስት ልጆች ያሉት አንድ አባት ልበ ቅን የሆነ አንድ የእምነት ወንድሙ “አራቱን ልጆችህን ለዓለም እንደምታስረክብ ልትጠብቅ ትችላለህ” ሲል ነግሮት ነበር። ይሁን እንጂ ይህ አባት ይህ ነገር በአንዱ ልጁ ላይ እንኳ መድረስ እንደሌለበት ያምን ነበር። እንደዚያ ብሎ የሚያምነው ለምን እንደሆነም አብራርቷል።
“ልጆቻችን በእርግጥ የእኛ አይደሉም። ልጆቻችን እኔና ባለቤቴ ከይሖዋ አምላክ በአደራ የተቀበልናቸው ንብረቶች ወይም ስጦታዎች ናቸው። እኛ በተገቢው መንገድ ካሰለጠንናቸው ‘ከዚያ ፈቀቅ እንደማይሉ’ ይሖዋም ተናግሯል። ስለዚህ ልክ የይሖዋ ንብረቶች እንደሆኑ አድርገን ነው የምንከባከባቸው” ሲል ተናግሯል። — መዝሙር 127:3፤ ምሳሌ 22:6
ይህ አባት ለተሳካ የቤተሰብ ኑሮ ቁልፍ የሆነውን ነገር ለይቶ ገልጿል። ይኸውም ወላጆች የአምላክን ንብረት እንደሚንከባከቡ አድርገው ልጆቻቸውን መንከባከብ ይኖርባቸዋል ማለት ነው። ይህም ሲባል ልጆች በማንኛውም ሁኔታ የእናንተን ግሩም መመሪያ ይከተላሉ ማለት ባይሆንም አምላክ በአደራ የሰጣችሁን ልጆች በእንክብካቤ የማሳደግ ኃላፊነት አለባችሁ።
ከባድ ኃላፊነት
ይህን እንክብካቤ የምታደርጉት ለአምላክ ባላችሁ አክብሮትና ጥልቅ በሆነ አሳቢነት እንጂ በግዴለሽነት ወይም ባወጣው ያውጣው በማለት አይደለም። ከአምላክ ለተቀበላችሁት ንብረት ወይም ስጦታ ለአምላክ መልስ እንደምትሰጡ በመገንዘብ ትጥሩለታላችሁ። የተለያዩ የልጅ አስተዳደግ ዘዴዎችን መሞከር አያስፈልግም። ወላጆች የሚያስፈልጋቸው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የአምላክ መመሪያና ይህንን መመሪያ በጥንቃቄ መከተል ብቻ ነው።
የይሖዋ አምላክ መመ ሪያ እንዲህ ይላል:- “[ቃሌን] ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሣም ተጫወተው። በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው፤ በዓይኖችህም መካከል እንደ ክታብ ይሁንልህ። በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።” በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “እናንተም አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው” በማለት አጥብቆ ያሳስባል። — ዘዳግም 6:7–9፤ ኤፌሶን 6:4
ስለዚህ ልጆችን ማሳደግ በየቀኑ ትኩረትን የሚጠይቅ ነው። ይህም ጊዜያችሁን በተለይም ደግሞ ፍቅራችሁንና ልባዊ አሳቢነታችሁን ምንም ሳትቆጥቡ መስጠት ማለት ነው። እነዚህን መሠረታዊ የሆኑ አስፈላጊ ነገሮች ለልጆቻቸው የሚሰጡ ወላጆች አምላክ በተሳካ የቤተሰብ ሕይወት ለመደሰት አስፈላጊ ነው ያለውን ነገር እያደረጉ ናቸው።
ይህ ከባድ ሸክም ነው ብለህ ታስባለህን? ብዙ ወላጆች እንደዚህ እንደሚሰማቸው በድርጊታቸው ያሳያሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ከአምላክ የተቀበላችኋቸው ስጦታዎች ማለትም ልጆቻችሁ በእርግጥ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸው ናቸው።
ልጆችን እንዴት አድርጎ ማሳደግ ይቻላል?
ልጆችን በማሳደግ በኩል የተሳካላቸውን ሰዎች ምሳሌ መመርመሩ አስተዋይነት ነው። አንድ መጽሔት “አስደናቂ ቤተሰቦች (አሜዚንግ ፋሚሊስ)” በሚለው የመጽሔቱ ዋና ርዕስ ውስጥ ልጆችን በተሳካ ሁኔታ ለማሳደግ አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን አራት ነገሮች ገልጿል። “[1] በምግብ ጊዜ የሚደረግ አእምሮን የሚያመራምር ውይይት፣ [2] ጥሩ የሆኑ መጻሕፍት ማንበብ፣ [3] ጥሩ የፈጠራ ችሎታ ያላቸውንና አርዓያ ሊሆኗቸው የሚገቡትን ሰዎች ማሰብ፣ [4] ተጠብቆ መቆየት የሚገባው የቤተሰቡ ሥርዓት እንዳለ ማወቅ።” — ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ዎርልድ ሪፖርት፣ ታኅሣስ 12, 1988
“በምግብ ጊዜ የሚደረገውን ውይይት” በተመለከተ ወላጆች በቤትም ሲቀመጡ ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ አምላክ እንደሚያዛቸው አስታውስ። ቤተሰብህ በምግብ ጊዜ ዘወትር አብሮ በመብላት በየዕለቱ አንድ ላይ ለመሆንና እርስ በርስ ለመጫወት የሚያስችለው አጋጣሚ ያገኛልን? እነዚህ ጊዜያት ለልጆች አስፈላጊና የማይረሱ ናቸው። የመረጋጋትና የመተማመን ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጓቸዋል። አንድ የስድስት ዓመት ልጅ ምግብ አብረው የሚበሉባቸውን ጊዜያት እንደሚወዳቸው ተናግሯል። ምክንያቱም ሁሉም አንድ ላይ ስላሉ “አንዱ ስለ ሌላው መጨነቅ አያስፈልገውም” ብሏል።
ምግብ አንድ ላይ በምትበሉበት ጊዜ የምታደርጉት ውይይት ምን ዓይነት ነው? ብዙውን ጊዜ “ጥሩ መጻሕፍት” በያዟቸው ነገሮች ላይ ያተኮረ ነውን? ማለትም መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ ለአምላክ ስለምናቀርበው አገልግሎት ወይም ከአምላክ ፍጥረት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሚያብራሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች በያዟቸው ነገሮች ላይ የሚያተኩር ነውን? በምግብ ጊዜ ከሚደረገው ከዚህ ዓይነቱ ውይይት በተጨማሪ ቋሚ በሆነ የጥናት ፕሮግራም አማካኝነት ወላጆች በልጆቻቸው ውስጥ ለይሖዋ የጽድቅ ሕግጋት ፍቅር መኮትኮት ያስፈልጋቸዋል።
ቀደም ሲል የተጠቀሰው የስድስት ልጆች አባት “ዘወትር አብሮ ምግብ መብላት አላስቸገረንም። ይህ የተለመደ ነገር ነበር፤ ይህም እኛን አንድ ለማድረግ አገልግሏል። ይሁን እንጂ ቋሚ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም መያዝ በጣም አስቸጋሪ ነበር” ሲል ገልጿል። ከቀኑ ከባድ ሥራ የተነሳ በጣም ስለሚደክመው አንዳንድ ጊዜ በጥናቱ ወቅት እንቅልፍ ይይዘው ነበር። ይሁን እንጂ ከልጆቹ ጋር ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራቱን በፍጹም አያቋርጥም። ልጆቹን በየግላቸው ያነጋግራቸዋል እንዲሁም የሚናገሩትን ረዘም ላለ ጊዜ ያዳምጣል።
በምግብ ጊዜ በሚደረገው ጠቃሚ ውይይትና ጥሩ የሆኑ መጻሕፍትን በማንበብ ረገድ ምሳሌ ከመሆንህ በተጨማሪ ልጆችህ “ጥሩ የፈጠራ ችሎታ ካሏቸውና አርዓያ ሊሆኗቸው ከሚገቡ ሰዎች” ተፈላጊውን ጥቅም እያገኙ መሆናቸውን ትከታተላለህን? ልጆችህ የተሳካላቸው ጎልማሳ ሰዎች እንዲሆኑ ከተፈለገ እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠውን ታላቅ ሰው የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ ከሚከተሉ ሰዎች ጋር ዘወትር አብረው ጊዜ እንዲያሳልፉ ዝግጅት ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው።
በመጨረሻም “ሊጠበቅ የሚገባውን የቤተሰብ ሥርዓት” በተመለከተስ ምን ማድረግ ይቻላል? ልጆችህ ሊጠብቋቸው የሚገባ የቤተሰብ የአቋም ደረጃዎች እንዳሉ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህም በቤተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸውና የቤተሰቡን ሥርዓት የሚቃወሙ አንድ ዓይነት ባሕርይ፣ አነጋገር፣ አለባበስ፣ ጠባይና የመሳሰሉት ናቸው። የቤተሰቡን ሥርዓት መጣስ ከባድ ነገር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። ልጆቹ ባሳዩት አሳፋሪ ጠባይ ምክንያት ‘በዚያ አገር በሚኖሩ ሰዎች ዘንድ እንደተጠላው’ የጥንቱ የእስራኤላውያን አባት እንደ ያዕቆብ አንተም በጣም ልታዝንባቸው እንደምትችል ማወቅ ይኖርባቸዋል። — ዘፍጥረት 34:30
ልጆቹን እንደ አምላክ ንብረት አድርጎ የተመለከተው የስድስቱ ልጆች አባት በተለይ “የቤተሰብን ሥርዓት” የበለጠ ትኩረት ሰጥቶታል። የቤተሰቡ የአለባበስና የአበጣጠር ሥርዓት ከዓለም መንገዶች መለየቱ ከፈጣሪያችን ከይሖዋ አምላክ መንፈስና መመሪያ ጋር የሚስማማ መሆኑን ዘወትር እያወያየ ያስረዳቸው ነበር። በትክክለኛው መንገድ እንዲሄዱ እነሱን ለማሰልጠን ብዙ ጊዜ፣ ፍቅርና ጥልቅ አሳቢነት ስለተሰጣቸው ስድስቱም ልጆች ‘ከመንገዳቸው ፈቀቅ ባለማለት’ ለጥረቱ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። — ምሳሌ 22:6
በዓለም ዙሪያ በሺህ የሚቆጠሩ እንደዚህ ጠንካራ ቤተሰብ ያሉ ቤተሰቦች አሉ። እነዚህ ፈጣሪን በጣም የሚያስመሰግኑ ናቸው። ራስ ወዳድ ላልሆኑትና አፍቃሪ ለሆኑት ወላጆችም አስደሳች የሆኑ የድካማቸው ዋጋ ናቸው። ወላጆቻቸው ካደረጉላቸው ጥረቶች የተጠቀሙ ልጆች ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ እንዲህ ዓይነቶቹን ወላጆች ያደንቃሉ። እስቲ ቀጥላችሁ አምላካዊ በሆኑ ወላጆች ያደገች የአንዲት ሴት ታሪክ መርምሩ፤ እንዲሁም ከዚህ ታሪክ የሚገኘውን ጠቃሚ ትምህርት ልብ በሉ።