“እናንተ ገሮች ሁሉ ይሖዋን ፈልጉ”
“እናንተ የፍርዱን ውሳኔ ጠብቃችሁ የኖራችሁ የምድር ገሮች ሁሉ፣ ይሖዋን ፈልጉ። ጽድቅን ፈልጉ፤ ገርነትን ፈልጉ። ምናልባት በይሖዋ የቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።” — ሶፎንያስ 2:3 አዓት
ነቢዩ ሶፎንያስ እነዚህን ቃሎች የተናገረው ‘በምድር ለሚኖሩ ገሮች’ ነው። እነሱንም “በይሖዋ የቁጣ ቀን” ለመሰወር እንዲችሉ ‘ገርነትን’ እንዲፈልጉ አሳስቧቸዋል። ከጥፋቱ ለመዳን ከሚያስፈልጉት ነገሮች አንዱ ገርነት ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ግን ገርነት ለምን አስፈለገ?
ገርነትን መፈለግ ያለብን ለምንድን ነው?
ገር መሆን ማለት ከእብሪተኝነትና ከትዕቢት ነፃ መሆን፣ የየዋህነት ባሕርይ ማሳየት ማለት ነው። ገርነት እንደ ትሕትናና የዋህነት ከመሰሉት በጎ ባሕርዮች ጋር በጣም የተቀራረበ ዝምድና አለው። ይህም በመሆኑ ገር ሰዎች ትምህርት ተቀባዮችና ለጊዜው የሚያሳዝን ቢመስልም እንኳን ከአምላክ እጅ የሚመጣውን ተግሣጽ ለመቀበል ፈቃደኛ ናቸው። — መዝሙር 25:9፤ ዕብራውያን 12:4–11
ገርነት ከአንድ ሰው የትምህርት ወይም የኑሮ ደረጃ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ላይኖረው ይችላል። ይሁን እንጂ በጣም የተማሩ ወይም በዓለማዊ መንገድ የተሳካላቸው ሰዎች ሁሉንም ነገር የአምልኮ ጉዳዮችን እንኳ ሳይቀር ራሳቸው ለመወሰን ብቃት ያላቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። ይህ አስተሳሰባቸው ሌላ ሰው ስለማንኛውም ጉዳይ እንዲያስተምራቸው ፈቃደኛ እንዳይሆኑ ወይም ምክር እንዳይቀበሉ ወይም በሕይወታቸው ውስጥ አስፈላጊ የሆነ ለውጥ ከማድረግ ወደ ኋላ እንዲሉ ያደርጋቸዋል። በቁሳዊ ነገሮች ሀብታም የሆኑ ሰዎች ያጠራቀሙት ቁሳዊ ሀብት የሕይወታቸው ዋስትና እንደሆነ አድርገው በስሕተት ያስባሉ። ከዚህም የተነሣ ከአምላክ ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኘው መንፈሳዊ ሀብት እንደሚያስፈልጋቸው ሆኖ አይሰማቸውም። — ማቴዎስ 4:4፤ 5:3፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:17
በኢየሱስ ዘመን የነበሩትን ጸሐፍት፣ ፈሪሳውያንና ካህናትን እንውሰድ። በአንድ ወቅት ኢየሱስን ይዘው እንዲያስሩ የተላኩ ሰዎች ባዶ እጃቸውን በተመለሱ ጊዜ ፈሪሳውያን “እናንተ ደግሞ ሳታችሁን? ከአለቆች ወይስ ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን? ነገር ግን ሕግን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው ብለው መለሱላቸው።” (ዮሐንስ 7:45–49) በሌላ አባባል በእነሱ አመለካከት በኢየሱስ የሚያምኑ እውቀት የሌላቸውና ያልተማሩ ብቻ ናቸው።
እንዲህም ሆኖ አንዳንድ ፈሪሳውያን ወደ እውነት ተስበው ኢየሱስንና ክርስቲያኖችን እስከ መደገፍ ደርሰዋል። ከእነዚህም መካከል ኒቆዲሞስና ገማልያል ይገኙበታል። (ዮሐንስ 7:50–52፤ ሥራ 5:34–40) ከኢየሱስ ሞት በኋላ “ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ።” (ሥራ 6:7) በዚህ ረገድ ከሁሉ የሚበልጠው ምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ ነው። ጳውሎስ በገማልያል እግር ሥር ሆኖ የተማረ፣ በኋላም ቀናተኛና የተከበረ የአይሁድ እምነት አስፋፊ የሆነ ሰው ነበር። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ የክርስቶስ ኢየሱስን ጥሪ በትሕትና ተቀብሎ ቀናተኛ ተከታዩ ሆነ። — ሥራ 22:3፤ 26:4, 5፤ ገላትያ 1:14–24፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:12–16
ይህ ሁሉ የሚያስገነዝበን ማንኛውም ሰው ምንም ዓይነት አስተዳደግ ይኑረው ወይም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም ዓይነት ዝንባሌ ያሳይ የሶፎንያስ መልእክት በራሱ ላይ ተፈፃሚነት እንደሚኖረው ነው። አንድ ሰው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘትና በቃሉ ለመመራት ከፈለገ የግዴታ ገር መሆን አለበት።
በጊዜያችን ‘ገርነትን የፈለጉ’ ሰዎች
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች በመቀበል ላይ ናቸው። የይሖዋ ምስክሮች እንደነዚህ ባሉ ምሥራቹን የተቀበሉ ሰዎች ቤት ከአራት ሚልዮን በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እየመሩ ነው። እነዚህ ሰዎች የተለያየ አስተዳደግ ያላቸው፣ ከተለያየ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ደረጃዎች የተውጣጡ ናቸው። ሆኖም ሁሉም ያላቸው አንድ የጋራ ጠባይ በቤታቸው በራፍ ላይም ይሁን በሌላ ቦታ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ያቀረበላቸውን ሰው ለመቀበል ያስቻላቸው ትሕትና ነው። ብዙዎቹ በመንገዳቸው ላይ የሚገጥሟቸውን እንቅፋቶች ለማ ሸነፍ አስፈላጊውን ጥረት ለማድረግ ፈቃደኞች በመሆናቸው መልካም እድገት እያደረጉ ነው። አዎን፣ በዛሬው ጊዜ ‘በምድር ላይ ከሚኖሩት ገሮች መካከል’ ለመሆን ችለዋል።
ለምሳሌ በሜክሲኮ የምትኖረውን የማሪያን ሁኔታ እንውሰድ። በሕግ ትምህርት ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀችና በውርስ ባገኘችው ሀብት ምክንያት በቁሳዊ ረገድ ምንም የማይቸግራት ሴት ነበረች። በዚህ ምክንያት እሷ ራሷ እንደገለጸችው “ዓመፀኛ፣ ባለጌ፣ ያልኩት ይሁን ባይና አምላክ የለም ባይ” ሴት ሆነች። “ገንዘብ የማይፈታው ነገር የለም ብዬ ማሰብ ስለ ጀመርኩ የአምላክ አስፈላጊነት አይታየኝም ነበር። እንዲያውም አምላክ እንዳለ ሆኖ እንኳን አይሰማኝም ነበር” በማለት ማሪያ ታስታውሳለች። “ለእኔ ሃይማኖት ሞኝነትና በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት የሚያስችል ነገር ብቻ ሆኖ ይታየኝ ነበር” ብላለች።
በኋላም የአጎቷ ልጅ የይሖዋ ምስክር ከሆነ በኋላ ያደረገውን ለውጥ ተመለከተች። “በጣም ረብሸኛ ሰው ነበር፤ አሁን ግን በጣም ሰላማዊና ቅን ሰው ሆነ። ዘመዶቻችን ሰባኪና መጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ ሆኗል፣ የማይጠጣውና ሴት ማሳደዱን የተወው ለዚህ ነው ብለው ሲናገሩ ሰማሁ። ስለዚህ በጣም የምፈልገውን ሰላምና ውስጣዊ እርካታ ለማግኘት ያስችለኝ ይሆናል ብዬ ስላሰብኩ እንዲመጣና መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያነብልኝ ጠየቅሁት” ትላለች። ከዚህም የተነሣ ማሪያ የይሖዋ ምስክር ከሆኑ ባልና ሚስት ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ተስማማች።
ልታሸንፋቸው የሚገቡ ብዙ ችግሮች ነበሯት። ለባሏ እንድትገዛ የሚጠይቀውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የራስነት ሥርዓት ለመቀበል በጣም ከብዷት ነበር። ቢሆንም በሕይወቷና በአመለካከቷ ላይ ፈጣን ለውጥ አደረገች። “ወንድሞች የይሖዋን እርዳታ ካመጡልኝ ጊዜ ጀምሮ ደስታ፣ እርካታና የአምላክ በረከት ቤቴን ሞልቶታል” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች። ዛሬ ማሪያ ራስዋን ለአምላክ የወሰነችና የተጠመቀች የይሖዋ ምስክር ሆናለች።
በእውነተኛ አምልኮ ረገድ ገር መሆን ወይም አለመሆን አስፈላጊ አስተዋፅዖ የሚያበረክትበት መስክ አለ። አብዛኛውን ጊዜ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሚስት እውነትን ተቀብላ አምላክን ለማገልገል ፍላጎት ሲኖራት ባልዋ ግን ወደ ኋላ የሚልበት ጊዜ አለ። አንዳንድ ባሎች ሚስቶቻቸው ይሖዋ ለሚባል ሌላ አካል መገዛት የሚኖርባቸው መሆኑን መቀበል በጣም ያስቸግራቸው ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) በሜክሲኮ ውስጥ በኪሁዋሁዋ የምትኖር አንዲት ሴት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላት ጠየቀችና ከጊዜ በኋላ እሷና ሰባት ልጆቿ ወደ እውነት መጡ። መጀመሪያ ላይ ባሏ ይቃወማት ነበር። ምክንያቱም ቤተሰቡ ከቤት ወደ ቤት አየሄደ እንዲሰብክና የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችን እንዲያበረክት አልፈለገም። ክብሩን ዝቅ የሚያደርግበት መስሎ ታየው። ቤተሰቡ ግን አምላክን ለማገልገል ባደረገው ውሳኔ ጸና። ከጊዜ በኋላ ባልየው የአምላክን ዝግጅቶች መቀበል ያለውን ጠቀሜታ መገንዘብ ጀመረ። ይሁን እንጂ ራሱን ለይሖዋ እስከመወሰን ደረጃ ለመድረስ አሥራ አምስት ዓመት ያህል አስፈልጎታል።
በሜክሲኮ አገር የየራሳቸው ቋንቋና ባሕል ያላቸውና ተራርቀው የሚኖሩ ብዙ ማኅበረሰቦች አሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለእነዚህ ሰዎች በመድረሱና አንዳንዶቹም እውነትን በሚያጠኑበት ጊዜ ማንበብና መጻፍ በመማራቸው ምክንያት ባሕላዊ ደረጃቸውን ለማሻሻል ችለዋል። ይሁን እንጂ ሰዎች ብዙ ያልተማሩ ወይም ድሆች መሆናቸው ብቻ በተሻለ ሁኔታ እውነትን እንዲቀበሉ ያደርጋቸዋል ማለት አይቻልም። አንዳንዶች በዘራቸው ስለሚመኩ ወይም የአባቶቻቸውን ወግ በጣም ስለሚያከብሩ እውነትን መቀበል ያስቸግራቸዋል። በሕንዳውያን መንደሮች ውስጥ ከሚኖሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እውነትን ሲቀበሉ የተለያየ ጥቃት የሚፈጸምባቸው በዚህ ምክንያት ነው። ስለዚህ ገርነት የሚገለጽባቸው ብዙ ዓይነት መልኮች አሉ።
በገርነት መቀበል
አንተስ? የአምላክን ቃል እውነት ተቀብለሃልን? ወይስ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን መቀበል ያዳግትሃል? ምናልባት ወደኋላ የሚጎትትህ ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ ራስህን መመርመር ያስፈልግህ ይሆናል። ወደ እውነት ከመጡት ሰዎች አብዛኞቹ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው መሆኑ ቅር አስኝቶህ ይሆን? አስተሳሰብህ በኩራት መንፈስ ተነክቶ ይሆን? ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን ምክር ማሰብ በጣም ይጠቅማል። “ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤ እግዚአብሔርም የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ ነገር የተናቀውንም ነገር ያልሆነውንም ነገር መረጠ፣ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ።” — 1 ቆሮንቶስ 1:27–29
አንድን ውድ ሀብት በተናቀ ሸክላ ዕቃ ውስጥ ስላገኘኸው ብቻ አልፈልገውም ትላለህን? አልፈልገውም እንደማትል የታወቀ ነው! ሆኖም አምላክ ሕይወት አድን የሆነው የእውነት ቃል ወደ እኛ እንዲደርስ የፈለገው በዚህ መንገድ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን” በማለት ገልፆታል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ገርነትና ትሕትና ሀብቱ የሚኖረውን እውነተኛ ጥቅም እንጂ መልእክቱ የተላለፈበትን “ሸክላ” ማለትም መሣሪያ ሆነው መልእክቱን የሚያስተላልፉትን ሰዎች እንዳንመለከት ያደርጉናል። ‘ከይሖዋ የቁጣ ቀን ለመሰወር’ ያለንን አጋጣሚ ከፍ ለማድረግና ‘ምድርን ከሚወርሱት’ ገሮች መካከል ለመሆን እንችላለን። — ሶፎንያስ 2:3፤ ማቴዎስ 5:5