መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ለእውነት የቆሙ ወቅታዊ መጽሔቶች
“የእውነት አምላክ አቤቱ፣ ተቤዥተኸኛልና።”—መዝሙር 31:5
1, 2. (ሀ) አንዲት እኅት በመጠበቂያ ግንብ ላይ ባነበበችው ነገር የተሰማት እንዴት ነበር? (ለ) መጽሔቶቻችንን በተመለከተ ምን ጥያቄዎች ይጠየቃሉ?
“በመጠበቂያ ግንብ ላይ ‘በጭንቀት ጊዜ መጽናኛ ማግኘት ትችላለህ’a በሚል ርዕስ ላወጣችሁት ግሩም የሆነ ትምህርት በጣም አመሰግናችኋለሁ” በማለት አንዲት ክርስቲያን እኅት ጻፈች። “የጠቀሳችኋቸው ነጥቦች በአብዛኛው እኔ እታገልባቸው የነበሩ ስሜቶች ናቸው። ይህን ርዕስ በቀጥታ ለእኔ እንደተጻፈልኝ አድርጌ ተመልክቼዋለሁ። ለመጀመሪያ ጊዜ ሳነበው ዓይኖቼ በእንባ ተሞልተው ነበር። እኔ እንዴት እንደሚሰማኝ የሚያውቅ ሌላ ሰው መኖሩ በጣም ደስ ያሰኛል! ከይሖዋ ምስክሮች አንዷ በመሆኔ በጣም ደስ ብሎኛል። በቅርቡ ገነት በምትሆነዋ ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ፣ በአሁኑም ጊዜ ነፍስን የሚያጽናና ነገር ከሌላ ከየት ማግኘት እችል ነበር! እጅግ በጣም አመሰግናችኋለሁ።”
2 እንደዚህ ተሰምቶህ ያውቃልን? በመጠበቂያ ግንብ ወይም የእርሱ ጓደኛ በሆነው በንቁ! መጽሔት ለአንተ በግልህ እንደተጻፈልህ ያህል ሆኖ የተሰማህን ትምህርት አግኝተህ ታውቃለህን? መጽሔቶቻችን የሰዎችን ልብ እንዲማርኩ የሚያደርጋቸው ነገር ምንድን ነው? እነዚህ መጽሔቶች ከያዙት ሕይወት አድን መልእክት ብዙ ሰዎች እንዲጠቀሙ እንዴት ልንረዳቸው እንችላለን?—1 ጢሞቴዎስ 4:16
የእውነት ጠበቆች የሆኑ መጽሔቶች
3. መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች የብዙዎቹን አንባቢዎች ልብ የነኩት በየትኛው ጥሩ ምክንያት ነው?
3 ይሖዋ “የእውነት አምላክ” ነው። (መዝሙር 31:5) ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስም የእውነት መጽሐፍ ነው። (ዮሐንስ 17:17) ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች ለእውነት አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣሉ። (ከዮሐንስ 4:23, 24 ጋር አወዳድር።) መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! በሚልዮን የሚቆጠሩ አንባቢዎቻቸውን ልብ የማረኩበት አንዱ ምክንያት ለንጹሕ አቋምና ለእውነት የቆሙ መጽሔቶች በመሆናቸው ነው። እንዲያውም መጠበቂያ ግንብ ለመታተም የበቃው ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ታማኝ ደጋፊ ሆኖ እንዲቆም የሚያስገድድ ምክንያት በመፈጠሩ ነው።
4, 5. (ሀ) ሲ ቲ ራስልን መጠበቂያ ግንብ መጽሔትን ወደ ማዘጋጀት ያደረሱት ሁኔታዎች ምን ነበሩ? (ለ) “ታማኝና ልባም ባሪያ” መጠበቂያ ግንብን የሚጠቀምበት እንዴት ነው?
4 በ1876 ቻርልስ ቲ ራስል በሮችስተር ኒው ዮርክ ከሚኖረው ከኔልሰን ኤች ባርበር ጋር በኅብረት መሥራት ጀመረ። ሄራልድ ኦቭ ዘ ሞርኒንግ (የማለዳ አዋጅ ነጋሪ) የተባለው የባርበር ሃይማኖታዊ መጽሔት እንደገና መታተም እንዲጀምር ራስል በገንዘቡ መርዳት ጀመረ። ባርበር ዋና አዘጋጅ ሆኖ ራስል ደግሞ ረዳት አዘጋጅ ሆነ። ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በኋላ ግን በሄራልድ የነሐሴ 1878 እትሙ ላይ ባርበር የክርስቶስ ሞት ከኃጢአት የመቤዠት ችሎታ የለውም የሚል ጽሑፍ አወጣ። 30 ዓመት ገደማ ከባርበር በዕድሜ የሚያንሰው ራስል በሚቀጥለው የመጽሔቱ እትም ላይ “በአምላክ ቃል ውስጥ ከተገለጹት ዋና ዋና ትምህርቶች አንዱ” ብሎ በመጥራት የቤዛውን ዝግጅት የሚደግፍ ርዕስ በማውጣት መልስ ሰጠ። (ማቴዎስ 20:28) ከባርበር ጋር በቅዱስ ጽሑፉ መሠረት ለማወያየትና ለማስረዳት ተደጋጋሚ ጥረት ካደረገ በኋላ ራስል ከሄራልድ ጋር የነበረውን ማንኛውንም ግንኙነት ለማቋረጥ ወሰነ። ከመጽሔቱ የሰኔ 1879 እትም ጀምሮ የራስል ስም በረዳት አዘጋጅነት መጠቀሱ አቆመ። ከአንድ ወር በኋላ የ27 ዓመት ዕድሜ የነበረው ራስል ከመጀመሪያ ጀምሮ እንደ ቤዛ ላሉት ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶች ጠበቃ ሆኖ የቆመ የጽዮን መጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ የተባለውን (አሁን የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ በመባል የሚታወቀውን) መጽሔት ማዘጋጀት ጀመረ።
5 ባለፉት 114 ዓመታት መጠበቂያ ግንብ ጥሩ ችሎታ እንዳለው ጠበቃ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነትና መሠረተ ትምህርት በመደገፍ ተከራክሯል። በዚህ ምክንያት በሚልዮን የሚቆጠሩትን አንባቢዎቹን አመኔታ አትርፏል። አሁንም ቢሆን የቤዛውን ዝግጅት አጥብቆ ይደግፋል። (ለምሳሌ ያህል የየካቲት 15, 1991 እትሙን ተመልከት።) መጠበቂያ ግንብ “ታማኝና ልባም ባሪያ” እና የአስተዳደር አካሉ የተቋቋመውን የይሖዋን መንግሥት ለማስታወቅና “በጊዜው” መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ የሚጠቀሙበት ዋነኛ መሣሪያ ሆኖ ቀጥሏል።—ማቴዎስ 24:14, 45
6, 7. ወርቃማው ዘመን የሚዘጋጅበት ዓላማ ምን እንደሆነ ተገልጾ ነበር? የሚያስብ አእምሮ ያላቸው ሰዎች ለመልእክቱ አዎንታዊ ምላሽ እንደሰጡ የሚያሳየው ምንድን ነው?
6 ስለ ንቁ! መጽሔትስ ምን ለማለት ይቻላል? መታተም ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ ንቁ! የእውነት ጠበቃ ሆኖ ቆይቷል። በመጀመሪያ ወርቃማው ዘመን (ዘ ጎልደን ኤጅ) ተብሎ ይጠራ የነበረው ይህ መጽሔት ለሕዝብ ለማሰራጨት ታስቦ የተዘጋጀ ነበር። የመጽሔቱን ዓላማ አስመልክቶ ጥቅምት 1, 1919 ላይ የወጣው የመጀመሪያ እትም “የመጽሔቱ ዓላማ ከመለኮታዊ ጥበብ አንጻር በዘመናችን የሚከናወኑትን ታላላቅ ድርጊቶች ትርጉም ለማስረዳትና የሚያስብ አእምሮ ላላቸው ሰዎች የሰው ዘር ከፍተኛ በረከቶችን የሚያገኝበት ጊዜ በቅርብ እንደሚመጣ በማያሻማ መንገድ ለማሳመን ነው” በማለት ጠቅሶ ነበር። የሚያስብ አእምሮ ያላቸው ሰዎች ወርቃማው ዘመን ላቀረበላቸው መልእክት አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። እንዲያውም ለበርካታ ዓመታት ስርጭቱ ከመጠበቂያ ግንብ በቁጥር ይበልጥ ነበር።b
7 ይሁን እንጂ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ተወዳጅነትን ያተረፉት የመሠረታዊ ትምህርቶችን እውነት እና የዓለም ሁኔታዎች የደረሱበትን ትንቢታዊ ትርጉም በማብራራታቸው ብቻ አይደለም። በተለይ ባለፉት አሥርና ሃያ ዓመታት መጽሔቶቻችን የሰዎችን ልብ የማረኩበት ሌላም ምክንያት አለ።
የሰዎችን ሕይወት የሚነኩ ወቅታዊ ትምህርቶች
8. ይሁዳ በጉባኤው ውስጥ የተፈጠረውን ተጽእኖ እንዲቋቋሙ አንባቢዎቹን ባሳሰበ ጊዜ ምን የአጻጻፍ ለውጥ አደረገ?
8 ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞተና ከተነሣ ከ30 ዓመታት ገደማ በኋላ ይሁዳ የተባለው አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ አንድ አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጠመው። በክርስቲያኖች መካከል ምግባረ ብልሹ የሆኑና እንስሳዊ ባሕርይ ያላቸው ሰዎች ሰርገው ገብተው ነበር። ይሁዳ ቅቡዓን በጋራ ስለሚካፈሉት መዳን የሚገልጽ መሠረተ ትምህርታዊ የሆነ ጉዳይ ሊጽፍላቸው ፈልጎ ነበር። ከዚህ ይልቅ በመንፈስ ቅዱስ በመመራት አንባቢዎቹ በጉባኤው ውስጥ የሚገኙትንና የሚያበላሽ ተጽእኖ የሚያሳድሩትን መቃወም እንዳለባቸው እያሳሰበ መጻፍ የሚያስፈልግ ሆኖ አገኘው። (ይሁዳ 3, 4, 19–23) ይሁዳ ለሁኔታው የሚስማማ ለውጥ በማድረግ ክርስቲያን ወንድሞቹ የሚያስፈልጋቸውን ወቅታዊ ምክር ሰጣቸው።
9. መጽሔቶቻችን ወቅታዊ የሆነ ርዕስ ይዘው እንዲወጡ ለማድረግ ምን ማድረግ አስፈልጓል?
9 በተመሳሳይም በመጽሔቶቻችን ላይ የሚወጡትን ወቅታዊ ትምህርቶች ማዘጋጀቱ ከባድ ኃላፊነት ነው። ጊዜ ይለወጣል፤ ሰዎችም እንዲሁ ይለወጣሉ። ሰዎች የሚያስፈልጋቸውና የሚያስደስታቸው ነገር ከአሥርና ከሃያ ዓመት በፊት ከነበረው ጋር አንድ አይደለም። አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች በቅርቡ “የይሖዋ ምስክር በሆንኩባቸው በ1950ዎቹ ዓመታት ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ስናስጠናቸው በአብዛኛው እንደ ሥላሴ፣ ሲኦል፣ ነፍስ እና በመሳሰሉ መሠረተ ትምህርቶች ላይ በማተኮር እውነትን እናስተምራቸው ነበር። አሁን ግን በሰዎች ኑሮ ውስጥ ብዙ ችግሮችና እንቅፋቶች ስላሉ እነሱን እንዴት ማሸነፍ እንደሚችሉ ማስተማር ያለብን ይመስለኛል” በማለት የተመለከተውን ተናግሯል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?
10. ከ1914 ጀምሮ የሰው ዘር ሁኔታ እያዘቀጠና እየተበላሸ መምጣቱ ሊያስደንቀን የማይገባው ለምንድን ነው?
10 ስለ “መጨረሻ ቀኖች” መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፣ እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ” በማለት ትንቢት ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 13) ስለዚህ የፍጻሜው ዘመን ከጀመረበት ከ1914 ወዲህ በሰዎች ላይ የሚታየው ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን እያዘቀጠና እየተበላሸ መሄዱ ሊያስገርመን አይገባም። ጥቂት ጊዜ ብቻ የቀረው ሰይጣን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቁጣውን በሰብአዊው ኅብረተሰብ ላይ እያወረደ ነው። (ራእይ 12:9, 12) ከዚህም የተነሣ ሥነ ምግባርንና ቤተሰብን በተመለከተ ሰዎች ያላቸው አስተሳሰብ ከ30 ወይም ከ40 ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲወዳደር በጣም ተለውጧል። ሰዎች በአጠቃላይ ቀደም ካሉት አሥርተ ዓመታት ጋር ሲወዳደሩ ሃይማኖታዊ ዝንባሌ የሌላቸው ሆነዋል። ወንጀል በጣም በመስፋፋቱ ሰዎች ከ20 ወይም ከ30 ዓመት በፊት ተሰምተው የማይታወቁ ጥንቃቄዎችን በማድረግ ላይ ናቸው።—ማቴዎስ 24:12
11. (ሀ) በሰዎች አእምሮ ውስጥ የሚጉላሉት ርዕሰ ጉዳዮች ምን ዓይነት ናቸው? ታማኝና ልባም ባሪያስ ሰዎች ለሚያስፈልጋቸው ነገር ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው? (ለ) የአንተን ሕይወት የነካ በመጠበቂያ ግንብ ወይም በንቁ! መጽሔቶች ላይ የወጣ ርዕስ ካለ አንድ ምሳሌ ጥቀስ።
11 እንግዲያው ስሜትን የሚነኩ፣ የማኅበራዊ እና የቤተሰብ ጉዳዮች አሳሳቢነት በብዙ ሰዎች አእምሮ ውስጥ መጉላላቱ አያስደንቅም። የታማኝና ልባም ባሪያ ቡድን በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ ሰዎች በሚያስፈልጓቸውና ሕይወታቸውን በነኳቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ወቅታዊ ትምህርቶችን አትሞ በማውጣት ድፍረት የሞላበት አዎንታዊ ምላሽ ሰጥቷል። ቀጥሎ አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልከት።
12. (ሀ) በ1980 በመጠበቂያ ግንብ ላይ ነጠላ ወላጆች ስለሚያስተዳድሯቸው ቤተሰቦች ርዕሶች የተዘጋጁት ለምን ነበር? (ለ) ነጠላ ወላጆች ስለሚያስተዳድሯቸው ቤተሰቦች በወጡት ርዕሶች ላይ አንዲት እኅት አድናቆቷን የገለጸችው እንዴት ነበር?
12 የቤተሰብ ችግሮች። ዓለም አቀፉ ሪፖርት ነጠላ ወላጆች የሚያስተዳድሯቸው ቤተሰቦች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ሲያሳይ “አንድ ወላጅ ብቻ የሚያስተዳድራቸው ቤተሰቦች፤ የሚፈጠሩትን ችግሮች እንዴት መቋቋም ይቻላል?” የሚል ርዕስ ያለው አዲስ ትምህርት በመስከረም 15, 1980 መጠበቂያ ግንብ እትም ላይ አዘጋጅቶ አወጣ። ትምህርቶቹ ሁለት ዓላማ ነበራቸው፦ (1) ነጠላ ወላጆች የገጠማቸውን ይህንን ለየት ያለ ችግር መቋቋም እንዲችሉ ለመርዳት (2) ሌሎች ሰዎች ነጠላ ወላጆች የሚያስተዳድሯቸው ቤተሰቦች ምን ችግር እንዳለባቸው ተረድተው የወንድማማች ፍቅራቸውን እንዲያሳዩአቸውና እንዲንከባከቡአቸው ለመርዳት ነበር። (1 ጴጥሮስ 3:8፤ ያዕቆብ 1:27) ብዙ አንባቢዎች ስለ ትምህርቱ የተሰማቸውን አድናቆት ገልጸዋል። “ገና የመጽሔቱን ሽፋን ሳይ ዓይኖቼ በእንባ ተሞሉ። መጽሔቱን ገልጬ በውስጡ የሰፈረውን ትምህርት ሳነብ ይሖዋ እንደዚህ የመሰለውን ትምህርት በወቅቱ በማዘጋጀቱ ልቤ በጥልቅ ምስጋና ተሞላ” በማለት አንዲት ነጠላ ወላጅ ጽፋለች።
13. በ1981 በንቁ! መጽሔት ላይ የመንፈስ ጭንቀትን በተመለከተ ምን ጥልቀት ያለው ትምህርት ቀርቦ ነበር? አንድ አንባቢ ምን ለማለት ችሏል?
13 ስሜታዊ ችግሮች። የመንፈስ ጭንቀትን የሚመለከተው ርዕሰ ጉዳይ ከ1960ዎቹ ዓመታት ጀምሮ በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ ሲወጣ ቆይቷል። (1 ተሰሎንቄ 5:14) “የመንፈስ ጭንቀትን ልታሸንፈው ትችላለህ” በሚለው የመስከረም 8, 1981 ንቁ! መጽሔት በወጣው የሽፋን ርዕስ ሥር በቀረቡት ተከታታይ ክፍሎች በርዕሰ ጉዳዩ ላይ አዲስ የሆነና አዎንታዊ ገጽታ ያለው አመለካከት ቀርቧል። ብዙም ሳይቆይ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የምስጋና ደብዳቤዎች ከዓለም ዙሪያ ጎረፉ። “በልቤ ውስጥ ያለውን ስሜት እንዴት አድርጌ በጽሑፍ ልግለጸው? ዕድሜዬ 24 ዓመት ነው። ባለፉት 10 ዓመታት በተደጋጋሚ የመንፈስ ጭንቀት እየደረሰብኝ ስቸገር ነበር። አሁን ግን ወደ ይሖዋ በይበልጥ የቀረብኩና በእነዚህ ፍቅራዊ ርዕሶች አማካኝነት የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች ለሚያስፈልጋቸው ነገር ምላሽ በመስጠቱ በጣም አመስጋኝ መሆኔን ልገልጽላችሁ ስለፈለግሁ ነው” በማለት አንዲት እኅት ጽፋለች።
14, 15. (ሀ) ሕፃናትን በግብረ ሥጋ የማስነወሩ ርዕሰ ጉዳይ በመጽሔቶቻችን ውስጥ በጥልቀት የተብራራው እንዴት ነበር? (ለ) በአውስትራሊያ አንድን ፈረስ ጋላቢ በጥልቅ የነኩት የትኛው መጽሔት ርዕሶች ናቸው?
14 ማኅበራዊ ችግሮች። መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻው ቀን” “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ . . . ፍቅር የሌላቸው፣ . . . ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ” ይሆናሉ በማለት ትንቢት ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–3) ስለዚህ በዛሬው ጊዜ ሕፃናትን በሩካቤ ሥጋ ማስነወር በጣም የተስፋፋ ልማድ መሆኑ ሊያስደንቀን አይገባም። ርዕሰ ጉዳዩ “በዘመዳቸው ጾታዊ ብልግና ለተፈጸመባቸው የቀረበ እርዳታ” በሚል ርዕስ በጥቅምት 1, 1983 መጠበቂያ ግንብ በግልጽ ተብራርቷል። ከስምንት ዓመት በኋላ የጥቅምት 8, 1991 ንቁ! መጽሔት በሽፋኑ ላይ “በልጅነት ዘመን የደረሰን በጾታ የመነወር ቁስል መፈወስ” የሚል ርዕስ የያዘ ትምህርት የዚህ ድርጊት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ሁኔታው እንዲገባቸውና ተስፋ እንዲኖራቸው ለመርዳት እንዲሁም ሌሎች ነገሩን አውቀውት ጠቃሚ እርዳታ ማበርከት እንዲችሉ በጥንቃቄ ተዘጋጅቶ ወጣ። በዚህ ርዕስ በተከታታይ ስለ ወጡት ትምህርቶች ከአንባቢዎቻችን የመጡልን ደብዳቤዎች ቁጥር በመጽሔቶቻችንን ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማያውቅ ነው። አንዲት አንባቢ እንዲህ ስትል ጻፈች፦ “ከደረሰብኝ ብስጭት እንድላቀቅ ይበልጥ የረዱኝ በርዕሱ ውስጥ የተጠቀሱት የሚያጽናኑ ሐሳቦችና ጥቅሶች ናቸው። ይሖዋ እኔን እንደማልረባ አድርጎ እንደማይቆጥረኝ ማወቄ ከፍተኛ እፎይታ አምጥቶልኛል። በእኔ ላይ ብቻ የደረሰ አለመሆኑን ማወቄም የዚያኑ ያህል አጽናንቶኛል።”
15 በአውስትራሊያ ውስጥ በሜልበርን ከተማ የሚኖር አንድ ፈረስ ጋላቢ ሲድኒ ለሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቢሮ ስልክ ደውሎ በፈረስ ግልቢያ እሽቅድምድም አካባቢ በሚያየው ነገር እንዳልተደሰተ ገለጸ። በመጋቢት 8 ንቁ! መጽሔት ላይ “አስገድዶ ማስነወር—ትልቁ የሴቶች ፍርሃት” የሚለውን ርዕስ እንዳነበበና እንደዚህ ያለ ትልቅ ጥቅም የሚገኝበት መጽሔት መኖሩን ማመን እንዳቃተው ተናገረ። ለ30 ደቂቃ ያህል ጥያቄዎች እየጠየቀ ከተወያየ በኋላ ባገኛቸው መልሶች በጣም ተደሰተ።
16. ለመጽሔቶቻችን ያለህን አድናቆት በምን መንገዶች ልታሳይ ትችላለህ?
16 አንተስ? በመጠበቂያ ግንብ ወይም በንቁ! መጽሔቶች ላይ በወጣ በአንድ ርዕስ ሕይወትህ ተነክቶ ያውቃልን? ከሆነ ለመጽሔቶቻችን ጥልቅ የአድናቆት ስሜት እንዳደረብህ አያጠራጥርም። አድናቆትህን እንዴት ልትገልጸው ትችላለህ? አንተ ራስህ እያንዳንዱን እትም በማንበብ እንደሆነ አያጠራጥርም። እነዚህን ውድ የሆኑ መጽሔቶች ለሌሎች እንዲዳረሱ በሚደረገውም ሥራ የምትችለውን ያህል ልትካፈል ትችላለህ። ይህንን እንዴት ማከናወን ይቻላል?
ለሌሎች አካፍላቸው!
17. የመጽሔት ስርጭት ከፍ እንዲል ጉባኤዎች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
17 በመጀመሪያ ደረጃ እያንዳንዱ ጉባኤ ሊያደርግ የሚችለው ነገር አለ። ኢንፎርማንት (አሁን የመንግሥት አገልግሎታችን የሚባለው) በጥቅምት 1952 እትሙ ላይ “መጽሔቶችን በማሰራጨት ረገድ ይበልጥ ውጤታማ ሆኖ የተገኘው ዘዴ ከቤት ወደ ቤትና ከሱቅ ወደ ሱቅ እየሄዱ ማበርከት ነው። ስለዚህ ማኅበሩ እነዚህ መጽሔት ለማበርከት የሚያስችሉ መንገዶች ቋሚ የሆነ የመጽሔት ማደያ ቀን እንዲኖራቸው ያበረታታል” ብሏል። ምክሩ ዛሬም ቢሆን ሊሠራ የሚችል ነው። ጉባኤዎች መጽሔት በማበርከት ምስክርነት የሚሰጥበትን ቋሚ ቀን ሊመድቡ ይችላሉ። ለብዙዎቹ ጉባኤዎች የቅዳሜን ቀን ለዚህ ሥራ መመደቡ እንደሚስማማቸው ምንም ጥርጥር የለውም። አዎን፣ እያንዳንዱ ጉባኤ በመጽሔት ተጠቅሞ ለመመስከሩ ሥራ የተለዩ ቀኖችን ወይም ምሽቶችን መድቦ ከቤት ወደ ቤት፣ ከሱቅ ወደ ሱቅ፣ ከመንገድ ወደ መንገድ እና ቋሚ የመጽሔት ደንበኞች በማፍራት ሊያገለግል ይችላል። ከዚህም በላይ የመንግሥቱ አስፋፊ የሆንከው አንተስ የመጽሔት ስርጭቱ ሥራ እንዲጨምር ለማድረግ በበኩልህ ምን ልታደርግ ትችላለህ?
18, 19. (ሀ) መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን በንቃት መከታተልህ መጽሔት በማበርከት ሥራ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) መጽሔት በምናበረክትበት ጊዜ አጭርና ቁም ነገሩን የሚገልጽ መግቢያ ቢኖረን ምን ጥቅም አለው? (ሐ) መጽሔቶቹን በሰዎች ቤት ማድረሱ ጥቅም እንዳለው የሚያሳየው ምንድን ነው?
18 የመጀመሪያው እርምጃ “መጠበቂያ ግንብ” እና “ንቁ!” መጽሔቶችን በንቃት መከታተል ነው። ቀደም ብለህ መጽሔቶቹን አንብባቸው። እያንዳንዱን ርዕስ በምታነብበት ጊዜ ‘ይህ ርዕስ ማንን ይማርካል?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። በርዕሱ ላይ ፍላጎት ለማነሣሳት መናገር የምትችላቸውን ጥቂት ቃሎች አስብ። ቋሚ ከሆነው የመጽሔት ማበርከቻ ቀን ሌላ በጉዞ ላይ ሳለህ ወይም ገበያ ስትሄድ፣ ከሥራ ባልደረቦችህ፣ ከጎረቤቶችህ፣ ከትምህርት ቤት ጓደኞችህ ወይም ከአስተማሪዎችህ ጋር ስትነጋገር አጋጣሚውን ተጠቅመህ ለሌሎች ለማካፈል እንድትችል የመጽሔቶቹን ቅጂዎች ይዘህ ለምን አትሄድም?
19 በሁለተኛ ደረጃ የምናቀርብልህ ሐሳብ ቀላል አቀራረብ ይኑርህ የሚለው ነው። የታኅሣሥ 1, 1956 መጠበቂያ ግንብ “መጽሔት በምናበረክትበት ጊዜ አጭርና ፍሬ ነገር ያለው አቀራረብ በጣም ጥሩ ነው። ዓላማችን ብዙ ቅጂዎችን ለማበርከት ነው። እነርሱ ራሳቸው ‘ይናገራሉ’” በማለት ጠቅሶ ነበር። አንዳንድ አስፋፊዎች ከአንድ ርዕስ ውስጥ አንድን ሐሳብ ነጥሎ አውጥቶ በጥቂት ቃሎች በመግለጽ መጽሔቱን ማበርከት ውጤታማ ሆኖ አግኝተውታል። ሰውዬው አንዴ ከተቀበላቸው መጽሔቶቹ ከእርሱ በተጨማሪ ለሌሎችም “ይናገራሉ።” በአየርላንድ የምትገኝ አንዲት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ አባቷ ከአንድ ምስክር የተቀበለውን የመስከረም 1, 1991 የመጠበቂያ ግንብ እትም አነበበች። የሐሳብ ግንኙነት ስለ ማድረግ የሚናገሩት ርዕሶችና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ፍላጎቷን ቀሰቀሱት። መጽሔቱን አንብባ እንደጨረሰች በስልክ ማውጫው ላይ ከሚገኘው የምስክሮቹ አድራሻ ወደ አንዱ ስልክ ደወለች። ወዲያውኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረላትና ወጣቷ ሴት ሐምሌ 1993 በተደረገው “መለኰታዊ ትምህርት” የወረዳ ስብሰባ ላይ ተጠመቀች። መጽሔቶቹ ለሰዎች “መናገር” ወደሚችሉበት ወደየቤቱ እንዲገቡ እንጣር። አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች “መጽሔቶቹን ከመጽሐፍ ቦርሳችሁ ውጭ ያዟቸው” በማለት ሌላ ቀለል ያለ ሐሳብ ያቀርባል። ምናልባት የምትናገረው ነገር እንኳ ባይነካው በመጽሔቱ ሽፋን ላይ የሚታዩት ማራኪ ሥዕሎች መጽሔቱን ወደ ሰዎቹ እጅ እንዲገባ ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል።
20, 21. (ሀ) መጽሔት በማበርከት ሥራ ስትካፈል አቀራረብህን እንደ ሁኔታው መለዋወጥ የምትችለው እንዴት ነው? (ለ) በየወሩ ተጨማሪ መጽሔቶችን ለማበርከት ምን ልታደርግ ትችላለህ?
20 በሦስተኛ ደረጃ የቀረበልህ ሐሳብ አቀራረብህን እንደ ሁኔታው ለውጥ የሚለው ነው። (ከ1 ቆሮንቶስ 9:19–23 ጋር አወዳድር።) አጠር ያሉ ጥቂት መግቢያዎችን አዘጋጅ። ለወንዶች የሚስማማ አንድ ርዕስ፣ ለሴቶች የሚስማማ ሌላ ርዕስ አዘጋጅ። ለወጣቶች ምናልባት “የወጣቶች ጥያቄ . . .” የሚለውን ርዕስ ልትጠቀም ትችል ይሆናል። መጽሔት በማበርከቱ ሥራ ላይ የምትካፈልበትንም ጊዜ እንደ ሁኔታው ለዋውጥ። መጽሔት ከሚበረከትበት ቀን በተጨማሪም በምሽት ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ምስክርነት መስጠቱ መጽሔት ለማበርከት ግሩም አጋጣሚ ሆኖ ታገኘው ይሆናል።
21 በአራተኛ ደረጃ የምንጠቅስልህ ሐሳብ የግል ግብ ይኑርህ የሚል ነው። “መጽሔቶች የሕይወትን መንገድ ያመለክታሉ” የሚለው በመንግሥት አገልግሎታችን የመጋቢት 1984 እትም ላይ የወጣው ተጨማሪ ርዕስ እንደሚከተለው በማለት ገልጿል፦ “አስፋፊዎች እንደ ሁኔታቸው በየወሩ 10 መጽሔቶችን ለማበርከት ግብ ሊያደርጉ ይችላሉ። አቅኚዎች ደግሞ 90 ለማበርከት ጥረት ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ አስፋፊዎች ከእነዚህ የበለጡ መጽሔቶችን ለማበርከት ይችላሉ። እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ለማበርከት ግብ ሊያወጡ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በጤንነት እክል፣ በአገልግሎት ክልል ዓይነት፣ ወይም በሌሎች ጥሩ ምክንያቶች የተነሣ የሌሎች ግብ ከዚህ ዝቅ ይል ይሆናል። ሆኖም ለይሖዋ የሚያቀርቡት አገልግሎታቸው ዋጋው ከሌሎች ያነሰ አይደለም። (ማቴዎስ 13:23፤ ሉቃስ 21:3, 4) ዋናው ነገር የግል ግብ ኖሮን መሥራታችን ነው።”
22. ለእውነት ለቆሙት ወቅታዊ መጽሔቶቻችን የተሰማንን ምስጋና ለይሖዋ በየትኞቹ መንገዶች ለመግለጽ እንችላለን?
22 “የእውነት አምላክ” የሆነው ይሖዋ ታማኝና ልባም ባሪያን እና የአስተዳደር አካሉን እነዚህን ወቅታዊ መጽሔቶች እንዲያዘጋጁንል በማድረጉ ምስጋናችን ምን ያህል ከፍ ያለ ነው! (መዝሙር 31:5) ይሖዋ እስከፈቀደ ድረስ እነዚህ መጽሔቶች ሰዎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ይዘው መውጣታቸውን ይቀጥላሉ። የይሖዋን ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃዎች መደገፋቸውን ይቀጥላሉ። ትክክለኛ መሠረተ ትምህርትን ማስተማራቸውን ፈጽሞ አያቋርጡም። እንደዚሁም የአምላክ መንግሥት መግዛት መጀመሯን በማመልከት ዘመናችንን ተለይቶ እንዲታወቅ የሚያደርጉት ትንቢቶች መፈጸማቸውንና ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄደው እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች በመኖራቸው የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ መፈጸም መጀመሩን ለሰዎች ማስረዳታቸውን ይቀጥላሉ። (ማቴዎስ 6:10፤ ራእይ 11:15) የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች በዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ እንዴት ያሉ ውድ ሀብት ናቸው! የምናገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመን የሰዎችን ሕይወት ለመንካትና የመንግሥቱን እውነት ለማራመድ የሚችሉትን እነዚህን በጣም ውድ መጽሔቶች ገር ልብ ላላቸው ሰዎች እናካፍል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ሐምሌ 15, 1992 ገጽ 19–22
b ለብዙ ዓመታት መጠበቂያ ግንብ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻ የሚዘጋጅ መጽሔት ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ከ1935 ጀምሮ ግን ተስፋቸው በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሆነው “እጅግ ብዙ ሰዎች” መጠበቂያ ግንብ እንዲወስዱና እንዲያነቡት ተደጋጋሚ ማበረታቻ ተሰጠ። (ራእይ 7:9) ከጥቂት ዓመታት በኋላ ማለትም በ1940 መጠበቂያ ግንብ በመንገድ ላይ አዘውትሮ ለሰዎች ይበረከት ጀመር። ከዚያ በኋላ ስርጭቱ በፍጥነት አደገ።
መልስህ ምንድን ነው?
◻ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ለእውነት የቆሙ መጽሔቶች መሆናቸውን የሚያሳየው ምንድን ነው?
◻ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች የሰዎችን ሕይወት የነኩት እንዴት ነው?
◻ የመጽሔት ስርጭት ከፍ እንዲል ጉባኤዎች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
◻ ብዙ መጽሔት እንድታበረክት የትኞቹ ሐሳቦች ሊረዱህ ይችላሉ?
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የሰዎችን ሕይወት የነኩ አንዳንድ ርዕሶች
ባለፉት ዓመታት ብዙ አንባቢዎች ደብዳቤ በመጻፍ በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! ታትመው ለወጡት የተወሰኑ ርዕሶች የተሰማቸውን አድናቆት ገልጸዋል። አንባቢዎቻችንን ከነኳቸው ከብዙዎቹ ርዕሶች ውስጥ ጥቂቶቹን ከዚህ ቀጥሎ ዘርዝረናቸዋል። እነዚህ ወይም ሌሎች ርዕሶች የአንተን ሕይወት ለውጠውታልን?
መጠበቂያ ግንብ
“ስውር ስሕተቶችን ለማሸነፍ የአምላክን እርዳታ ተቀበል” (ሚያዝያ 15, 1985 ወይም በአማርኛው 4–106 ክፍል 4)
“ላረጁ ወላጆች ለአምላክ ያደረን ሰው ጠባይ ማሳየት” (ሰኔ 1, 1987 ወይም በአማርኛው 11–108 ገጽ 15)
“ትምህርትን በዓላማ መከታተል” (ኅዳር 1, 1992)
ንቁ!
“የመንፈስ ጭንቀትን ማሸነፍ ትችላለህ!” (መስከረም 8, 1981 በእንግሊዝኛ)
“የምታፈቅረው ሰው በሚሞትበት ጊዜ . . .” (ሚያዝያ 22, 1985 በእንግሊዝኛ)
“ልጆችህን ጠብቅ!” (ጥቅምት 8, 1993 በእንግሊዝኛ)
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በካናዳ ውስጥ በመጽሔቶች ተጠቅሞ ከቤት ወደ ቤት መስበክ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በማያንማር የሕይወትን መንገድ የሚያመለክቱትን መጽሔቶች ማበርከት