ከሁሉ አስቀድመን መንግሥቱን ፈልገናል
በኦሊቭ ስፕሪንጌት እንደተነገረው
እናቴ ጸሎታችንን ከሰማች በኋላ ሻማውን አጥፍታልን ገና መውጣቷ ነበር። ወዲያው ታናሽ ወንድሜ “ኦሊቭ አምላክ እንዴት ይህንን የጡብ ግድግዳ አልፎ ሊያየንና ሊሰማን ይችላል?” ብሎ ጠየቀኝ።
“እማማ ማንኛውንም ነገር አልፎ ማየት ይችላል ብላለች፤ ልባችን ውስጥ ያለውን እንኳ ማየት ይችላል” ብዬ መለስኩለት። እናቴ አምላክን የምትፈራና መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትራ የምታነብ ሴት ነበረች። እኛም ልጆቿ ለአምላክና ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥልቅ አክብሮት እንዲኖረን አድርጋለች።
ወላጆቻችን በእንግሊዝ አገር በኬንት ካንትሪ በምትገኘው በሻታም ከተማ የሚገኝ የአንድ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን አባል ነበሩ። እናቴ አዘውታሪ የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚ ብትሆንም ክርስቲያን ማለት ግን በሳምንት አንድ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ወንበር አሙቆ መመለስ ብቻ እንዳልሆነ ታምን ነበር። አምላክ አንድ እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን ሊኖረው እንደሚገባም እርግጠኛ ነበረች።
ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያለን አድናቆት
በ1918 አምስት ዓመት ገደማ ሲሆነኝ እናቴ በመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ፕሬዚደንት በቻርለስ ቲ ራስል የተጻፈውን የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት (ስተዲስ ኢን ዘ ስክሪፕቸርስ) የተባለውን መጽሐፍ አገኘች። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ዊግሞር በምትባል አንድ ትንሽ አካባቢ ስንኖር ያን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ ከነበሩት የይሖዋ ምስክሮች አንዷ ከእናቴ ጋር ተገናኘች። ዘ ሃርፕ ኦፍ ጎድ (የአምላክ በገና) የተባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ መጽሐፍ አገኘችና ከዚያም ውስጥ ለብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎቿ መልስ ማግኘት ጀመረች። በየሳምንቱ እያንዳንዱ ምዕራፍ ባለው ሐሳብ ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎችን የያዘ ሐምራዊ ቀለም ያለው ካርድ በፖስታ ይላክላት ነበር። ካርዱ የጥያቄዎቹ መልሶች በመጽሐፉ ውስጥ የትኛው ቦታ ላይ እንደሚገኝም ይጠቁም ነበር።
በ1926 ወላጆቼ፣ ታናሽ እኅቴ ቤሪና እኔ የአንግሊካን ቤተክርስቲያን በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ የምታደርገውን ጣልቃ ገብነትና ምክንያታዊ ያልሆኑትን ትምህርቶች በመጥላት ከቤተ ክርስቲያኗ ወጣን። ከእነዚህ ትምህርቶች አንዱ አምላክ ሰዎችን ለዘላለም በሲኦል እሳት ያሠቃያል የሚለው ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከልቧ ትፈልግ የነበረችው እናቴ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ እንዳልሆነ እርግጠኛ ነበረች።
ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የእናቴ ልባዊ ጸሎት መልስ አገኘ። ሚስስ ቻክሰን የምትባል የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ መጥታ አነጋገረችን። ሁለት ሰዓት ለሚያክል ጊዜ ከእናቴና ከእኔ ጋር ጥያቄዎቻችንን ከመጽሐፍ ቅዱስ እየመለሰችልን ተወያየን። ከሌሎቹ ነገሮች በተጨማሪ ጸሎታችን የሚደርሰው የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ወደ ሆነው ወደ ይሖዋ እንጂ ሚስጥራዊ ሥላሴ ወደ ሆነ አምላክ እንዳልሆነ በመማራችን በጣም ተደሰትን። (መዝሙር 83:18፤ ዮሐንስ 20:17) ለእኔ ግን እናቴ ከጠየቀቻቸው ጥያቄዎች ሁሉ የማይረሳኝ “መንግሥስቱን ማስቀደም ማለት ምን ማለት ነው?” የሚለው ነበር።—ማቴዎስ 6:33
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው መልስ ሕይወታችንን በጥልቅ ነካው። ከዛው ሳምንት ጀምረን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ መገኘትና የተማርናቸውንም ነገሮች ለሌሎች ማካፈል ጀመርን። እውነትን እንዳገኘን እርግጠኞች ነበርን። ከጥቂት ወራት በኋላ በ1927 እናቴ ራሷን ለይሖዋ መወሰኗን ለማሳየት ተጠመቀች፤ በ1930 ደግሞ እኔም ተጠመቅሁ።
ወደ አቅኚነት አገልግሎት መግባት
ቤተሰባችን የሚሰበሰበው 25 የሚያህሉ አባላት ባሉበት የጊሊንግሃም ጉባኤ ነበር። ብዙዎቹ አቅኚ ተብለው የሚጠሩ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሲሆኑ ሁሉም የሰማያዊ ተስፋ ያላቸው ነበሩ። (ፊልጵስዩስ 3:14, 20) የነበራቸው ክርስቲያናዊ ቅንዓት ወደ ሌሎች የሚጋባ ነበር። በ1930ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ዕድሜዬ ገና 18 ቢሆንም በቤልጂየም ለአጭር ጊዜ አቅኚ ሆኜ አገልግያለሁ። ይህም በመንግሥቱ አገልግሎት የበለጠ ጊዜ ለማሳለፍ ያለኝን ፍላጎት አጠንክሮልኛል። በዚያ ወቅት ለእያንዳንዱ ቄስ የዓለም ተስፋ የሆነችው መንግሥት (ዘ ኪንግደም ዘ ሆፕ ኦፍ ዘ ወርልድ) የተባለውን ቡክሌት ቅጂ እናሰራጭ ነበር።
አባታችን ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያችንን መቃወም ጀመረ። በ1932 ኮሌጅ ለመግባት ወደ ለንደን የሄድኩበትም አንዱ ምክንያት ይህ ነበር። ከጊዜ በኋላ አስተማሪ ሆኜ ለአራት ዓመታት በሠራሁባቸው ጊዜያት በወቅቱ በለንደን ከነበሩት አራት ጉባኤዎች መካከል አንዱ በነበረው በብላክሄዝ ጉባኤ እሰበሰብ ነበር። ሂትለር በሚያስተዳድራት ጀርመን የነበሩት ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለጦርነት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ እንቢ በማለታቸው ስለሚደርስባቸው እስራትና ስቃይ ሪፖርቶችን መስማት የጀመርነው በዚያ ወቅት ነበር።
ወስጃቸው ለነበሩት መጽሐፎች የነበረብኝን እዳ በ1938 ከፍዬ እንደ ጨረስኩ አቅኚ ለመሆን የነበረኝን ፍላጎት ለማሟላት ስል በዚያው ወር ላይ ሥራዬን ለቀቅሁ። እህቴም ቤሪል በተመሳሳይ ጊዜ የአቅኚነት አገልግሎት ጀመረች። እሷ ትኖር የነበረው ግን በሌላ የአቅኚዎች ቤት ነበር። የመጀመሪያ የአቅኚነት ጓደኛዬ ባሁኑ ወቅት የይሖዋ ምስክሮች የአስተዳደር አካል አባል የሆነውን ጆን ባርን ያገባችው ሚልድሬድ ዊሌት ነበረች። ብዙ ጊዜ ዝናብ የሚዘንብ ቢሆንም በቡድናችን ውስጥ ከሚገኙት ሌሎች ጋር በመሆን ወደምናገለግልበት ክልል በብስክሌት እንሄድና እዛው እንውል ነበር።
አውሮፓ የጦርነት ደመና አጥልቶባት ነበር። የአገሩ ዜጐች የጋዝ መከላከያ ማስኮች የመልበስ ልምምድ ያደርጉ ነበር። በተጨማሪም ጦርነት ቢደረግ ሕፃናትን ወደ እንግሊዝ ገጠሮች ወይም ወደ ትናንሽ መንደሮች ለማሸሽ የሚያስችል ዝግጅት ተጀምሮ ነበር። የነበረኝ ገንዘብ አንድ ጥንድ ጫማ ከመግዛት የሚያልፍ አልነበረም። ከወላጆቼ የገንዘብ ድጋፍ ላገኝ የምችልበት ምንም መንገድ አልነበረም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ‘መንግስቱን ካስቀደማችሁ፤ ሌላው ሁሉ ይጨመርላችኋል’ ብሎ የለምን? (ማቴዎስ 6:33) ይሖዋ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ሁሉ እንደሚያሟላልኝ ሙሉ እምነት ነበረኝ፤ በእነዚህ ሁሉ ዓመታትም የሚያስፈልገኝን አትረፍርፎ ሰጥቶኛል። በጦርነቱ ወቅት ከሚሰጠኝ የምግብ ራሽን በተጨማሪ አንዳንድ ጊዜ የተጫኑ ትላልቅ መኪናዎች በመንገዱ ሲያልፉ የሚያንጠባጥቧቸውን አትክልቶች ለቅሜ እመገብ ነበር። ብዙውን ጊዜም ምግቤን የማገኘው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በፍራፍሬዎችና በአትክልቶች በመለወጥ ነበር።
ታናሽ እህቴ ሶኒያ የተወለደችው በ1928 ነበር። ሕይወቷን ለይሖዋ ስትወስን የሰባት ዓመት ልጅ ነበረች። ሶኒያ በዚያ በትንሽነት እድሜዋ እንኳ ምኞትዋ አቅኚነት እንደሆነ ትናገር ነበር። ወዲያው በ1941 ራሷን መወሰኗን በጥምቀት እንዳሳየች እናቴና እሷ ሳውዝ ዌልስ ወደሚገኘው ወደ ካርፊል በአቅኚነት እንዲያገለግሉ ሲመደቡ ምኞቷ እውን ሆነ።
በጦርነቱ ዓመታት እናከናውነው የነበረው አገልግሎት
በመስከረም 1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲጀምር በብሪታንያ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች በጀርመን የሚኖሩ የእምነት ባልደረቦቻቸው በተሰደዱበት ምክንያት ማለትም በጦርነት ላለመካፈል ገለልተኛ በመሆናቸው ይታሰሩ ነበር። በ1940 እንግሊዝ ከአየር በቦምብ ትደበደብ ጀመር። በየሌሊቱ የሚዘንበው የአየር ድብደባ ጆሮ ሊቀድ የሚደርስ ቢሆንም በይሖዋ እርዳታ ግን ትንሽ እንቅልፍ በመተኛት ለሚቀጥለው ቀን የስብከት ሥራ እንነቃቃ ነበር።
ወደ አገልግሎት ክልላችን ስንሄድ ከፈራረሱ ቤቶች ሌላ የማናገኝበት ጊዜ ነበር። በህዳር ወር ከምንኖርበት ቤት አጠገብ ቦምብ ወድቆ መስኮቶቹን አደቀቃቸው። ከፊት ለፊት የነበረውም ትልቅ በር ተሰባበረ፣ የጭስ ማውጫውም ተደረመሰ። የተቀረውን ሌሊት የአየር ድብደባ መከለያ ባለው ጣቢያ ውስጥ ካሳለፍን በኋላ ተበታትነን በተለያዩ ወንድሞች ቤት መኖር ጀመርን።
ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በታላቋ ለንደን ወዳለችው ክሮይዶን ተመደብኩ። በዚያ ሳለሁ የፖርቶሪኮ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አስተባባሪ ሆኖ ያገለግል የነበረው የራን ፓርኪን እህት አን ፓርኪን የአቅኚነት ጓደኛዬ ነበረች። ከዚያም በፈረስ በሚጎተት የመጫኛ መኪና ውስጥ እየኖርኩ ለስድስት ወራት በአቅኚነት ወዳገለገልኩበት ወደ ሳውዝ ዌልስ ብሪጄን ተዛወርኩ። ላለንበት ቦታ ቅርብ ወደሆነው በፖርት ታልበት ወደሚገኘው ትልቅ ጉባኤ ለመድረስ ስድስት ኪሎሜትር በብስክሌት እንጓዝ ነበር።
በዚህ ወቅት በህሊና ምክንያት በጦርነት አንካፈልም በማለታችን ኮንቺዝ እያሉ በመጥራት ያሾፉብን ነበር። በዚህም ምክንያት የምናድርበት ቤት ለማግኘት እንኳ እንቸገር ነበር። ይሖዋ ግን በገባልን ቃል መሠረት ተንከባክቦናል።
ከጊዜ በኋላ ስምንታችን ልዩ አቅኚዎች ሆነን በሳውዝ ዌልስ የወደብ ከተማ በሆነችው በስዋንሲ ተመደብን። ጦርነቱ እየተስፋፋ ሲሄድ በእኛ ላይ የነበረው ምክንያት የለሽ ጥላቻ እየጨመረ ሄደ። “አይጦች” እና “ፈሪዎች” የሚሉት ቃላት በአቅኚዎች ቤታችን ግድግዳ ላይ ተጽፈው ነበር። ይህን የመሰለ ጥላቻ ሊቀሰቀስ የቻለው የገለልተኝነት አቋማችንን የሚያንቋሽሹ ዘገባዎች በተለያዩ ጋዜጣዎች ላይ በመውጣታቸው ምክንያት ነበር። በመጨረሻ ሰባታችንም አንድ በአንድ ታሠርን። በ1942 በካርዲፍ ወህኒ ቤት ውስጥ ለአንድ ወር ያህል ታስሬአለሁ። እህቴም ቤሪል ትንሽ ቆይት ብሎ ለተወሰነ ጊዜ ወህኒ ቤት ታስራለች። የነበረን ቁሳዊ ንብረት በጣም ጥቂት ቢሆንና የሰዎቹም ፌዝና ነቀፋ ቢያስቸግረንም በመንፈሳዊ ግን ሃብታሞች ነበርን።
በዚሁ ጊዜ እናቴና ሶኒያም በካርፊል እያገለገሉና ተመሳሳይ ተሞክሮዎችን እያሳለፉ ነበር። ሶኒያ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የመራችው ዓርብ ዕለት ማታ ልትጎበኛት ቀጠሮ ለያዘችላት ሴት ነበር። ሶኒያ እናቴ አብራት እንደምትሄድ እርግጠኛ ነበረች፤ እናታችን ግን፦ “እኔ ሌላ ቀጠሮ አለኝ። ቀጠሮውን የያዝሽው አንቺ ስለሆንሽ ብቻሽን ትሄጃለሽ” አለቻት። ሶኒያ ዕድሜዋ 13 አመት ብቻ ቢሆንም ብቻዋን ሄደች፤ ሴትዮዋም ጥሩ መንፈሳዊ ዕድገት አድርጋ ራሷን የወሰነች አገልጋይ ሆነች።
ከጦርነቱ በኋላ የነበረው እንቅስቃሴና የጊልያድ ስልጠና
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1945 ሲያበቃ በዌሊይ ብሪጅ ደርብሻየር በአንድ ራቅ ብሎ በሚገኝ ክልል እያገለገልኩ ነበር። ወላጆቻቸውንና የትዳር ጓደኛቸውን በማጣታቸው እንዲሁም አካላቸው በመቆራረጡ ጨርሰው ተስፋ የቆረጡትን ሰዎች የተኩስ አቁም ስምምነት በተደረገበት ዕለት ጠዋት በመጐብኘት አጽናናናቸው።
ከጥቂት ወራት በኋላ ማህበሩ አረንጓዴይቱ ደሴት ተብላ በምትጠራው አየርላንድ ለመስበክ ፈቃደኛ ለሚሆኑ አቅኚዎች ጥሪ አቀረበ። በዚያን ጊዜ በደሴቲቷ ይኖሩ የነበሩት የይሖዋ ምስክሮች ቁጥር 140 ብቻ ስለነበር አየርላንድ የሚሲዮናዊነት አገልግሎት የሚከናወንበት ክልል ነበረች። በጥቂት ወራት ውስጥ 40 የሚሆኑ ልዩ አቅኚዎች ወደዚያ ሲመደቡ ከእነዚያ መካከል አንዷ እኔ ነበርኩ።
ለተወሰነ ጊዜ በደሴቲቱ ሰሜናዊ ክፍል በኮለሬይንና በኩክስታውን ካገለገልኩ በኋላ ከሌሎች ሦስት አቅኚዎች ጋር በመሆን በምስራቅ የባህር ጠረፍ ወደምትገኘው ድሮግሄዳ ተመደብኩ። የአየርላንድ ሕዝብ ሰው ወዳድና እንግዳ ተቀባይ ቢሆንም የከረረ ሃይማኖታዊ ጥላቻ ነበረው። በዚህ ምክንያት በአንድ ሙሉ ዓመት ውስጥ ለሕዝብ ልናበረክታቸው የቻልናቸው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎች ቁጥር በጣም ጥቂት ነበር። (አንድ መጽሐፍና ጥቂት ቡክሌቶች)
በድሮግሄዳ በቆየንበት ወቅት ከአንዱ እርሻ ወደሌላው በብስክሌት እየሄድኩ እያለሁ በድንገት አንድ ሰው ጥቅጥቅ ካለው የቁጥቋጦ አጥር ውስጥ ፈልፍሎ ወደ መንገዱ ወጣ። መንገዱን ወደ ላይና ወደ ታች ተመለከተና ድምጹን ዝቅ አድርጎ፦ “የይሖዋ ምስክር ነሽ?” ሲል ጠየቀኝ። መሆኔን ከነገርኩት በኋላ እንዲህ በማለት ቀጠለ፦ “ትናንትና ማታ ከእጮኛዬ ጋር ስለ እናንተ ከባድ ክርክር ተከራከርንና ተጣላን። እርሷ ልክ የካቶሊክ ቄሶችና ጋዜጦች እንደሚሉት የይሖዋ ምስክሮች ኮሚኒስቶች ናቸው አለች እኔ ግን በግልጽ ከቤት ወደ ቤት ስለምትሰብኩ ይህ እውነት ሊሆን አይችልም ብዬ ተከራከርኩ።”
የሚያነበው አንድ ቡክሌት ሰጠሁትና በኪሱ ውስጥ ደበቃት፤ “ከእናንተ ጋር ስነጋገር ብታይ ከሥራ እባረራለሁ” ብሎኝ ስለነበር በደንብ ከጨለመ በኋላ ለመገናኘት ቀጠሮ ያዝን። በዚያን ዕለት ምሽት ሁለት ሆነን ሄደን አገኘነውና ብዙ ጥያቄዎቹን መለስንለት። የሰማው ሁሉ እውነት መሆኑን ያመነበት ይመስል ነበር፤ የበለጠ ለመማር በሌላ ምሽት እቤታችን ድረስ እንደሚመጣ ቃል ገባ። ከዚያ በኋላ ግን ፈጽሞ ስላልመጣ በመጀመሪያው ዕለት በዚያ የሚያልፉ ብስክሌተኞች አይተውት ምናልባት ከሥራው ተባርሮ ይሆናል ብለን አሰብን። ይሁን እንጂ ምስክር ሆኖ ይሆን እያልን እናስባለን።
በእንግሊዝ ደቡባዊ ድንበር በምትገኘው በብሪጅተን በ1949 በተደረገው የወረዳ ስብሰባ ከተካፈልን በኋላ ጥቂቶቻችን በኒውዮርክ በሚገኘው የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እንድንካፈል ጥሪ ደረሰን። በሐምሌ 30 1950 በያንኪ ስታዲየም ዓለም አቀፍ ስብሰባ በተደረገበት ጊዜ ከተመረቁት ከ15ኛው ኮርስ ተማሪዎች መካከል 26 የሚያክሉ ከእንግሊዝ አገር የመጡ ተካፍለዋል።
በብራዚል ያከናወንነው አገልግሎት
በሚቀጥለው ዓመት በዓለም ላይ በፍጥነት በማደግ ላይ ከሚገኙት ከተሞች አንዷ በሆነችው የብራዚል ከተማ በሳኦ ፓውሎ ተመደብኩ። በወቅቱ የነበሩት አምስት ጉባኤዎች ብቻ ነበሩ። አሁን ግን ወደ 600 የሚጠጉ ጉባኤዎች ይገኛሉ! በአየርላንድ ካሳለፍነው አገልግሎት እንዴት የተለየ ነበር! በሳኦ ፓውሎ ክልላችን በረጃጅም የብረት አጥሮችና በብረት በተሠሩ በሮች የተከበቡ ትላልቅ ቤቶች ይገኛሉ። የቤቱን ባለቤት ወይም የቤት ሠራተኞቹን የምንጠራው እጃችንን በማጨብጨብ ነበር።
ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ አዳዲስ የአገልግሎት ምድቦች ተሰጥተዋል። በሳኦ ፓውሎ ክፍለ ግዛት ማዕከላዊ ክፍል በ1955 በጁንዲ እና በ1958 በፓይራሲካብ የተቋቋሙትን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች አዳዲስ ጉባኤዎች እንዲቋቋሙ የመርዳት መብት አግኝቼአለሁ። በኋላም በ1960 እህቴ ሶኒያ የሚስዮናዊነት ጓደኛዬ ሆነችና የሪዮ ግራንዴ ዶ ሱል ዋና ከተማ በሆነችው በፖርቶ አሌግሬ ተመደብን። ሶኒያ እንዴት ወደ ብራዚል ልትመጣ ቻለች? ብላችሁ ትገረሙ ይሆናል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሶኒያና እናቴ በእንግሊዝ አብረው በአቅኚነት ማገልገላቸውን ቀጠሉ። ነገር ግን በ1950ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ እናቴ የካንሰር ቀዶ ሕክምና ተደርጎላት ስለነበር የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከመምራትና ደብዳቤ ከመጻፍ ውጭ ከቤት ወደቤት መሄድ እስከማይቻላት ድረስ ታማሚ ሆነች። ሶኒያ ግን እናቴንም እየረዳች በአቅኚነት አገልግሎቷ ቀጠለች። በ1959 ሶኒያ በ33ኛው የጊሊያድ ኮርስ የመካፈል መብት አገኘችና ወደ ብራዚል ተመደበች። እናቴን ግን እስከሞተችበት እስከ 1962 ድረስ ቤሪል ትንከባከባት ነበር። ቤሪል በዚያን ጊዜ ባለትዳር ሆና እሷና ቤተሰቦቿ ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ ነበር።
በብራዚል ሶኒያ እና እኔ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን ወስነው ለጥምቀት እንዲደርሱ ረድተናል። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ብራዚላዊያን ከነበረባቸው ችግር አንዱ ጋብቻቸውን ሕጋዊ ማድረግ ነበር። በብራዚል አገር ሕጋዊ ፍቺ ማግኘት አስቸጋሪ ስለሆነ ሴቶችና ወንዶች በጋብቻ ሳይተሳሰሩ አብረው መኖራቸው የተለመደ ነገር ነበር። በተለይ ይህ የሚሆነው አንዱ ወገን ቀድሞ ከነበረው ሕጋዊ የትዳር ጓደኛው ከተለያየ ነው።
እኔ ያገኘኋት ኢቫ የተባለች አንድ ሴት እንዲህ ባለ ሁኔታ የምትኖር ነበረች። ሕጋዊ የትዳር ጓደኛዋ ጥሏት ጠፍቶ ስለነበር የት እንዳለ ለማወቅ በሬዲዮ ማስታወቂያ አስነገርን። ባሏ የት እንዳለ ከታወቀ በኋላ ሳይጋቡ አብሯት ከሚኖረው ሰው ጋር በሕጋዊ መንገድ ለመጣመር እንዲችሉ ለጋብቻ ነጻ በሚያደርጋት ሰነድ ላይ እንዲፈርምላት የቀድሞ ባሏ ወዳለበት ከተማ አብረን ሄድን። በዳኛው ፊት አቤቱታውን በምታቀርብበት ጊዜ ዳኛው ኢቫንና እኔን ጋብቻዋን ለምን ሕጋዊ ለማድረግ እንደፈለገች ጠየቁን። ዳኛው ምክንያቱን ሲረዱ አድናቆታቸውንና እርካታቸውን ገለጹ።
በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ከጥናቶቼ ከአንዷ ጋር ጉዳይዋን ተከታትሎ የሚያስጨርስላት ጠበቃ ለማነጋገር ሄድን። አሁንም ስለ ጋብቻና ስለ አምላክ የሥነ ምግባር ሕጐች ጥሩ ምስክርነት ለመስጠት ቻልን። በዚህ ጊዜ ፍቺውን ለማስፈጸም የሚጠየቀው ዋጋ በጣም ከፍተኛ ስለነበር እዳውን ለመክፈል ሁለቱም መስራት ነበረባቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይህን የሚያክል ጥረት በማድረጋቸው አልተቆጩም። ሶኒያ እና እኔ በጋብቻቸው ላይ ምስክሮች የመሆን መብት አግኝተናል። በኋላም በአሥራዎቹ እድሜ ውስጥ ያሉት ልጆቻቸው በተገኙበት በቤታቸው የተደረገውን አጭር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር አዳምጠናል።
የበለጸገና ብዙ ፍሬ ያስገኘ ሕይወት
ሶኒያ እና እኔ ሕይወታችንን ለይሖዋ ወስነንና ተጠምቀን ወደ አቅኚነት አገልግሎት ስንገባ ሙሉ ሕይወታችንን በአገልግሎት ለማሳለፍ ወስነን ነበር። ስናረጅ ወይም ስንታመም ወይም የገንዘብ ችግር ሲያጋጥመን ምን እንሆናለን ብለን አስበን አናውቅም። ይሖዋ ቃል እንደገባው ፈጽሞ አልተጣልንም።— ዕብራውያን 13:6
እርግጥ ነው፤ አንዳንድ ጊዜ የገንዘብ ችግር ያጋጥመን ነበር። በአንድ ወቅት እኔና የአገልግሎት ጓደኛዬ አንድ ዓመት በሙሉ ምሳችንን የምንበላው የፐርሰሜሎ ቅጠል ሳንዱች ብቻ ነበር። ቢሆንም ተርበን ወይም የሚያስፈልገንን መሠረታዊ ነገር አጥተን አናውቅም።
ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ጉልበታችንም በዚያው መጠን እየደከመ መጣ። በ1980ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ ሁለታችንም ከባድ የቀዶ ሕክምና ስለተደረገልንና ይህም አገልግሎታችንን በከፍተኛ ሁኔታ ስለገታብን ከባድ ፈተና አጋጠመን። በጥር 1987 በብራዚል በሚገኘው የይሖዋ ምስክሮች ቢሮ ከሚያገለግሉት የቤቴል አባላት መካከል እንድንኖር ተጋበዝን።
ከአንድ ሺህ በላይ አገልጋዮች ያሉበት ይህ ትልቁ ቤተሰባችን ከሳኦፓውሎ 140 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝና ለብራዚል እንዲሁም ለሌሎች የደቡብ አሜሪካ አካባቢዎች የሚሰራጭ ጽሑፍ በሚታተምበት ውብ ሕንፃ ውስጥ ይገኛል። በዚህ ባለንበት ቦታ ለአምላክ ያደሩ አገልጋዮች ፍቅራዊ እንክብካቤ ያደርጉልናል። በ1951 ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ብራዚል ስመጣ የነበሩት የመንግሥቱ መልዕክት ሰባኪዎች 4000 የሚያህሉ ነበሩ፤ አሁን ግን ከ366,000 የሚበልጡ ሰባኪዎች አሉ። ርኅሩኅ የሆነው ሰማያዊ አባታችን ከሁሉ አስቀድመን መንግስቱን በመፈለጋችን ‘ሌላውን ሁሉ’ ጨምሮልናል—ማቴዎስ 6:33
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኦሊቭ ከሚልድሬድ ዊሌት ጋር ከማስታወቂያ ጋሪ አጠገብ፤ በ1939
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኦሊቭ እና ሶኒያ ስፐሪንጌት