ጥሩና መጥፎ ፍሬዎች
“እግዚአብሔር አሳየኝ፣ እነሆም፣ . . . ሁለት ቅርጫት በለስ ተቀምጠው ነበር። በአንደኛይቱ ቅርጫት አስቀድሞ እንደ ደረሰ በለስ የሚመስል እጅግ መልካም በለስ ነበረባት፤ በሁለተኛይቱ ቅርጫት ከክፋቱ የተነሣ ይበላ ዘንድ የማይቻል እጅግ ክፉ በለስ ነበረባት።”—ኤርምያስ 24:1, 2
1. ይሖዋ ለሕዝቡ ለእስራኤል አዘኔታ ያሳየው እንዴት ነበር? እነሱ ግን ምን ምላሽ ሰጡ?
ዓመቱ 617 ከዘአበ ነበር። ኢየሩሳሌምና ሕዝቦችዋ የሚገባቸውን የይሖዋን ፍርድ ከመቀበላቸው ከአሥር ዓመት በፊት መሆኑ ነው። ኤርምያስ 30 ለሚያክሉ ዓመታት አለምንም ፋታ ሲሰብክ ቆይቷል። ዕዝራ በ2 ዜና መዋዕል 36:15 ላይ በጊዜው ስለነበረው ሁኔታ የሰጠውን ሥዕላዊ መግለጫ ልብ በሉ፦ “የአባቶቻቸውም አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ ማለዳ ተነሥቶ በመልእክተኞቹ እጅ ወደ እነርሱ ይልክ ነበር።” ይህ ሁሉ ጥረት ምን ውጤት አስገኘ? ዕዝራ የነበረውን አሳዛኝ ሁኔታ በቁጥር 16 ላይ እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወጣ ድረስ፣ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፣ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ይሳለቁ፣ ቃሉንም ያቃልሉ፣ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር።”
2, 3. ይሖዋ ለኤርምያስ ያሳየውን አስደናቂ ራእይ ግለጽ።
2 ታዲያ የይሁዳ ብሔር ፈጽሞ መጥፋት ይኖርበታል ማለት ነውን? የዚህን መልስ ለማግኘት ለኤርምያስ የተገለጠለትንና በራሱ ስም በሚጠራው መጽሐፍ በምዕራፍ 24 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን በጣም አስፈላጊ የሆነ ራእይ እንመልከት። አምላክ በዚህ ራእይ ላይ በቃል ኪዳን ሕዝቦቹ ላይ የሚደርሰውን ነገር በምሳሌ ለማሳየት በሁለት ቅርጫቶች ውስጥ ባሉ በለሶች ተጠቅሟል። እነዚህ ሕዝቦች በሁለት የተለያዩ ፍሬዎች ማለትም ጥሩና መጥፎ በሆኑ ፍሬዎች ተመስለዋል።
3 ኤርምያስ ምዕራፍ 24 ቁጥር 1 እና 2 የአምላክ ነቢይ የተመለከተውን ይገልጽልናል፦ “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንን የይሁዳንም አለቆች ጠራቢዎችንና ብረት ሠራተኞችን ከኢየሩሳሌም ማርኮ ወደ ባቢሎን ካፈለሳቸው በኋላ፣ እግዚአብሔር አሳየኝ፣ እነሆም፣ በእግዚአብሔር መቅደስ ፊት ሁለት ቅርጫት በለስ ተቀምጠው ነበር። በአንደኛይቱ ቅርጫት አስቀድሞ እንደ ደረሰ በለስ የሚመስል እጅግ መልካም በለስ ነበረባት፣ በሁለተኛይቱ ቅርጫት ከክፋቱ የተነሣ ይበላ ዘንድ የማይቻል እጅግ ክፉ በለስ ነበረባት።”
በራእይ የታዩት ጥሩ በለሶች
4. የበለሶቹ ራእይ ለታማኝ እስራኤላውያን ምን የሚያጽናና መልእክት ነበረው?
4 ይሖዋ ኤርምያስን ምን እንደተመለከተ ከጠየቀው በኋላ በቁጥር 5 እስከ 7 ላይ እንዲህ አለ፦ “እንደዚህ እንደ መልካሙ በለስ፣ እንዲሁ ከዚህ ስፍራ ወደ ከለዳውያን ምድር የሰደድሁትን የይሁዳን ምርኮ ለበጎነት እመለከተዋለሁ። ዓይኔንም ለበጎነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ ወደዚህችም ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እሠራቸዋለሁ እንጂ አላፈርሳቸውም፤ እተክላቸዋለሁ እንጂ አልነቅላቸውም። እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በፍጹምም ልባቸው ወደ እኔ ይመለሳሉና ሕዝብ ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።”
5, 6. (ሀ) አንዳንድ እስራኤላውያን ወደ ከለዳውያን ምድር ‘ለበጎነት የተላኩት’ እንዴት ነበር? (ለ) ይሖዋ ‘ዓይኑን’ በግዞት በነበሩት ታማኝ እስራኤላውያን ‘ላይ ለበጎነት ያደረገው’ እንዴት ነበር?
5 ስለዚህ ይሖዋ ከተናገረው ከዚህ ቃል መረዳት እንደሚቻለው የይሁዳ ብሔር ፈጽሞ አይጠፋም። ግን የጥሩዎቹ በለሶች ቅርጫት ትርጉም ምንድን ነው?
6 ኢኮንያን ወይም ኢዮአቂን ኢየሩሳሌምን በፈቃዱ ለናቡከደናፆር አሳልፎ በሰጠበት ጊዜ በይሁዳ ላይ ከነገሠ ገና ሦስት ወር ከአሥር ቀኑ ነበር። ከእርሱ ጋር ወደ ግዞት ከተወሰዱት ሰዎች መካከል ዳንኤልና አናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ የተባሉት ሦስቱ ባልንጀሮቹ እንዲሁም ሕዝቅኤል ይገኙ ነበር። የባቢሎን ንጉሥ የእነዚህ ሰዎች ሕይወት እንዲጠበቅ ስላደረገ ይሖዋ ‘ወደ ከለዳውያን ምድር የሰደደውን የይሁዳን ምርኮ ሁሉ ለበጎነት ተመልክቷል’ ሊባል ይቻላል። በተጨማሪም “ዓይኔንም ለበጎነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ” እንዳለ አስተውለሃልን? ይህ ትንቢት የተፈጸመው እንዴት ነበር? ከ80 ዓመት በኋላ፣ በ537 ከዘአበ ይሖዋ ንጉሥ ቂሮስ ከዘሮቻቸው ቀሪዎች ወደ ይሁዳ እንዲመለሱ የሚፈቅድ አዋጅ እንዲያወጣ አደረገው። እነዚህ ታማኝ አይሁዶች የኢየሩሳሌምን ከተማ መልሰው ሠሩ፤ አምላካቸው ይሖዋ የሚመለክበትን አዲስ ቤተ መቅደስ አነጹ፤ በሙሉ ልባቸውም ወደ ይሖዋ ተመለሱ። ስለዚህ በይሖዋ ዓይን እነዚህ ምርኮኞችና ዘሮቻቸው አስቀድሞ እንደ ደረሰ በጣም ጥሩ በለስ ነበሩ ሊባል ይቻላል።
7. ይሖዋ ዓይኑን በዘመናዊው የኤርምያስ ክፍል ላይ ‘ለበጎነት ያደረገው’ መቼና እንዴት ነበር?
7 ባለፈው ርዕስ ላይ የኤርምያስን ትንቢታዊ ቃላት በሚመለከት ትንቢቶቹ ለ20ኛው መቶ ዘመናችን ትርጉም እንዳላቸው ተምረን እንደነበር ታስታውሱ ይሆናል። ምዕራፍ 24ም ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም። በመጀመሪያው ዓለም ጦርነት የጨለማ ዓመታት ራሳቸውን ከወሰኑት የአምላክ አገልጋዮች መካከል ብዙዎቹ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ በታላቂቱ ባቢሎን ተጽዕኖ ሥር ወድቀው ነበር። ይሁን እንጂ ይጠብቃቸው የነበረው ይሖዋ ዓይኑን ‘ለበጎነት እነርሱ ላይ አድርጎ ነበር።’ ስለዚህ ይሖዋ በላያቸው ላይ የተጫነውን የታላቂቱን ባቢሎን ቀንበር በታላቁ ቂሮስ በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ሰበረላቸውና ቀስ በቀስ ወደ መንፈሣዊ ገነት አገባቸው። እነዚህ መንፈሳዊ እስራኤላውያን የአምላክን ጥሪ ተቀብለው በሙሉ ልባቸው ወደ ይሖዋ ተመለሱ። ከዚያም በ1931 የይሖዋ ምስክሮች የሚለውን መጠሪያ ስም በደስታ ተቀበሉ። አሁን በይሖዋ ዓይን እጅግ መልካም በለሶች እንደያዘ ቅርጫት ናቸው ሊባል ይቻላል።
8. የይሖዋ ምስክሮች የመንግሥቱን ምሥራች መልእክት በለስ መሰል ጣፋጭነት ያወጁት በምን መንገድ ነው?
8 የይሖዋ ምስክሮች ከታላቂቱ ባቢሎን አርነት እንዲወጡ ያስቻላቸውንና ይገባናል የማይሉትን የአምላክ ደግነት ዓላማ አልሳቱም። የመንግሥቱን የምሥራች መልእክት በለስ መሰል ጣፋጭነት ሳይሸሽጉ ኢየሱስ በማቴዎስ 24:14 ላይ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል” ሲል በተናገረው መሠረት ለሕዝብ ሁሉ አውጀዋል። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ከ4,700,000 የሚበልጡ መንፈሳዊ እስራኤላውያን ያልሆኑ በግ መሰል ሰዎች ከታላቂቱ ባቢሎን ነፃ ወጥተዋል!
በራእይ የታዩት መጥፎ በለሶች
9. በኤርምያስ ራእይ ውስጥ በታዩት መጥፎ በለሶች የተወከሉት እነማን ነበሩ? የሚደርስባቸውስ ነገር ምን ነበር?
9 ኤርምያስ በራእዩ የተመለከተው የመጥፎ በለሶች ቅርጫትስ? አሁን ኤርምያስ ትኩረቱን በኤርምያስ ምዕራፍ 24 ቁጥር 8 እስከ 10 ላይ በሚገኙት የይሖዋ ቃላት ላይ አደረገ። “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከክፋቱ የተነሣ ይበላ ዘንድ እንደማይቻል እንደ ክፉው በለስ፣ እንዲሁ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን አለቆቹንም በዚህችም አገር የሚቀሩትን የኢየሩሳሌምን ቅሬታ በግብጽም አገር የሚቀመጡትን እጥላቸዋለሁ። በማሳድዳቸውም ስፍራ ሁሉ ለስድብና ለምሳሌ ለማላገጫና ለእርግማን ይሆኑ ዘንድ በምድር መንግሥታት ሁሉ ለመበተን አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። ለእነርሱና ለአባቶቻቸውም ከሰጠኋቸው ምድር እስኪጠፉ ድረስ በመካከላቸው ሰይፍንና ራብን ቸነፈርንም እሰድዳለሁ።”
10. ይሖዋ ሴዴቅያስን እንደ ‘መጥፎ በለስ’ የቆጠረው ለምን ነበር?
10 በእውነትም ሴዴቅያስ በይሖዋ ዓይን ‘ክፉ በለስ’ ሆኗል። ለንጉሥ ናቡከደነፆር በይሖዋ ስም የማለውን መሐላ አፍርሶ ከማመፁም በላይ ይሖዋ በኤርምያስ በኩል የዘረጋለትን ምሕረት በጭራሽ አልቀበልም አለ። እንዲያውም ኤርምያስን እስከማሳሰር ደርሶ ነበር! ዕዝራ የዚህን ንጉሥ ዝንባሌ አጠቃልሎ ሲገልጽ በ2 ዜና መዋዕል 36:12 ላይ “በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ በእግዚአብሔርም . . . ፊት ራሱን አላዋረደም” ማለቱ አያስደንቅም። ሴዴቅያስና በኢየሩሳሌም ቀርተው የነበሩት ሰዎች በይሖዋ ዓይን የተባላሸና የበሰበሰ በለስ እንዳለበት ቅርጫት ነበሩ!
በዘመናችን ያሉ የበሰበሱ ምሳሌያዊ በለሶች
11, 12. ዛሬስ እንደ መጥፎ በለሶች የሚታዩት እነማን ናቸው? ምንስ ይደርስባቸዋል?
11 አሁን ደግሞ በዙሪያችን ያለውን የዛሬውን ዓለም ተመልከቱ። ምሳሌያዊ የሆነ የመጥፎ በለሶች ቅርጫት የምናገኝ ይመስላችኋል? እስቲ የእኛን ዘመን ከኤርምያስ ዘመን ጋር እያወዳደርን ያለውን ሁኔታ እንመልከት። በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመንም ይሖዋ በታላቁ መከራ ስለሚመጣው መዓት ሕዝቦችን ለማስጠንቀቅ በኤርምያስ ክፍል ማለትም በቅቡዓን ቀሪዎች ተጠቅሟል። ብሔራት ለስሙ የሚገባውን ክብር እንዲሰጡ፣ በእውነትና በመንፈስ እንዲያመልኩትና በመግዛት ላይ የሚገኘው ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛው የምድር ገዥ መሆኑን እንዲቀበሉ አጥብቆ ሲመክራቸው ቆይቷል። ታዲያ ለዚህ ምክርና ማስጠንቀቂያ ምን ምላሽ ሰጡ? ከኤርምያስ ዘመን የተለየ አይደለም። ብሔራት በይሖዋ ዓይን ክፉ የሆነውን ማድረጋቸውን ቀጠሉ።
12 ይሁን እንጂ ይህን የዓመፀኝነት ዝንባሌ የሚያስፋፉት እነማን ናቸው? ኤርምያስን መሰል በሆኑት የአምላክ መልእክተኞች ላይ ‘የአምላክ አገልጋዮች እንዲሆኑ ማን ሥልጣን ሰጣቸው?’ እያሉ የሚዘባበቱት እነማን ናቸው? የአምላክን ቃል የሚያቃልሉት እነማን ናቸው? በአብዛኛው በይሖዋ ምስክሮች ላይ ከሚደርሰው ስደት በስተጀርባ ያሉት እነማን ናቸው? መልሱ ለማንም ግልጽ ነው። ሕዝበ ክርስትና፣ በተለይም ቀሳውስት ናቸው! በተጨማሪም ቀደም ብለን የተነጋገርንባቸውን የሕዝበ ክርስትናን የተበላሹና የበሰበሱ ፍሬዎች ተመልከቱ። አዎን፣ ዛሬ በዚህች ምድራችን ላይ በርግጥም የመጥፎ በለሶች ቅርጫት አለ። እንዲያውም ይሖዋ ‘ከክፋቱ የተነሣ ይበላ ዘንድ እንደማይቻል’ በለስ እንደሆኑ ተናግሯል። ‘ይጠፋሉ!’ ሲል ይሖዋ በኤርምያስ በኩል የተናገረው የይሖዋ ቃል እስከ ዘመናችን ድረስ ያስተጋባል። በሕዝበ ክርስትና ላይ የሚወርደው የይሖዋ መዓት ፈውስ የማይገኝለት ይሆናል።
ለኛ ማስጠንቀቂያ የሚሆን ትምህርት
13. በ1 ቆሮንቶስ 10:11 ላይ በሚገኙት የጳውሎስ ቃላት መሠረት ስለ ሁለቱ የበለስ ቅርጫቶች ስለሚገልጸው ራእይ ምን ልንረዳ ይገባናል?
13 በመንፈስ አነሳሽነት የተነገረው የኤርምያስ የማስጠንቀቂያ መልእክት የሚኖረውን ትርጉም በምንመረምርበት ጊዜ በ1 ቆሮንቶስ 10:11 ላይ የሚገኘው “ይህ ሁሉ ነገር የደረሰባቸው ለእኛ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ እንዲሆን ነው፤ የተጻፈውም በዘመናት መጨረሻ ላይ ለምንገኘው ለእኛ ትምህርት እንዲሆነን ነው” የሚለው የሐዋርያው ጳውሎስ ቃል ትዝ ይለናል። (የ1980 ትርጉም) የእነዚህ የሁለቱ የበለስ ቅርጫቶች ራእይ የሚያስተላልፍልንን ማስጠንቀቂያ በግለሰብ ደረጃ ልብ ብለናልን? እስካሁን ሲብራራ የነበረው ለእኛ ማስጠንቀቂያ የሚሆነውን በእስራኤላውያን ላይ የደረሰ ሁኔታ ዋና ዋና ነጥቦች ነው።
14. እስራኤላውያን ይሖዋ ላደረገላቸው እንክብካቤ ምን ምላሽ ሰጡ?
14 በመጨረሻ በ2 ሳሙኤል 7:10 ላይ ይሖዋ ስለ እስራኤል ለንጉሥ ዳዊት የተናገረውን እንዲህ የሚለውን ቃል እናስታውስ፦ “ለሕዝቤም ለእስራኤል ስፍራ አደርግለታለሁ፣ እተክለውማለሁ።” ይሖዋ ሕዝቡን እስራኤልን በብዙ መንገዶች ተንከባክቦታል። እስራኤላውያን በአኗኗራቸው መልካም ፍሬዎችን የሚያፈሩባቸው በቂ ምክንያቶች ነበሯቸው። የሚያስፈልጋቸው የይሖዋን መለኮታዊ ሕግ ማዳመጥና ትዕዛዛቱን መጠበቅ ብቻ ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ያደረጉት በጣም ጥቂቶች ናቸው። አብዛኞቹ አንገተ ደንዳኖችና ከአምላክ መንገድ የራቁ ስለነበሩ መጥፎና የበሰበሰ ፍሬ አፍርተዋል።
15. በዛሬው ጊዜ መንፈሳዊ እስራኤልና በግ መሰል ባልንጀሮቻቸው ይሖዋ ላሳያቸው ርኅራኄ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው?
15 በዘመናችንስ? ይሖዋ ለመንፈሳዊ እስራኤል ቀሪዎች እና በግ መሰል ለሆኑት ባልንጀሮቻቸው ከፍተኛ ርኅራኄ አሳይቷል። በ1919 መንፈሳዊ ነፃነት ካገኙ ወዲህ የአምላክ ዓይን አልተለያቸውም። በኢሳይያስ በኩል አስቀድሞ እንደተናገረው በመላው ጽንፈ ዓለም ከሚገኙት አስተማሪዎች ሁሉ ከሚበልጠው ታላቅ አስተማሪ ከይሖዋ አምላክ መለኮታዊ መመሪያ ይቀበላሉ። (ኢሳይያስ 54:13) ይህ በውድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት የሚተላለፈው መለኮታዊ ትምህርት በመካከላቸው ሰላም እንዲሰፍን ከማድረጉም በላይ ከይሖዋ ጋር በጣም የተቀራረበ ዝምድና እንዲኖራቸው አስችሏል። ይህም ይሖዋን ለማወቅ፣ እርሱን ለማዳመጥና በሕይወታችን ውስጥ ጥሩ ፍሬ፣ ማለትም ይሖዋን የሚያስመሰግን ፍሬ ለማፍራት በሚያስችል ጥሩ መንፈሳዊ አካባቢ እንድንኖር አድርጎናል። ይህ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው!
16. እያንዳንዳችን ስለ ሁለቱ የበለስ ቅርጫቶች የሚገልጸውን ራእይ በግላችን ልንሠራበት የምንችለው እንዴት ነው?
16 ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ የአምላክ የጸጋ ስጦታዎች እያሉ በጥንትዋ ይሁዳ ይኖሩ እንደነበሩት ብዙ ሰዎች ዓመፀኞችና ልበ ደንዳኖች በመሆን በሕይወታቸው ውስጥ መጥፎና የበሰበሰ ፍሬ የሚያፈሩ ሰዎች አሉ። እንዴት የሚያሳዝን ነው! ማናችንም ብንሆን ጥሩና መጥፎ ፍሬዎች በያዙ በእነዚህ ሁለት የበለስ ቅርጫቶች አማካኝነት ያገኘነውን የማስጠንቀቂያ ትምህርት አንዘንጋ። ይሖዋ በከዳተኛይቱ ሕዝበ ክርስትና ላይ የሚያመጣው ተገቢ ፍርድ እየገሰገሰ ሲመጣ “በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔርም እውቀት እያደጋችሁ፣ . . . በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን ምክር ልብ እንበል።—ቆላስይስ 1:10 የ1980 ትርጉም
ክለሳ “መጥፎና ጥሩ ፍሬዎች” እና “ይሖዋ ከብሔራት ጋር ያለው ክርክር” ከሚለው ርዕስ አንቀጽ 1–4
◻ የጥሩዎቹ በለሶች ቅርጫት ምን ያመለክታል?
◻ በራእይ የታየው የመጥፎ በለስ ቅርጫት ግልጽ ሆኖ የታየው እንዴት ነው?
◻ የኤርምያስ መልእክት ምን የማስጠንቀቂያ ትምህርት ይሰጠናል?
◻ 607 ከዘአበን ልዩ ዓመት የሚያደርገው ምንድን ነው? 1914 እዘአንስ?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንደ ጥሩዎቹ በለሶች የሆኑት የአምላክ ሕዝቦች የመንግሥቱን ጣፋጭ ፍሬ አፍርተዋል
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሕዝበ ክርስትና እንደ መጥፎ በለስ ቅርጫት ሆና ተገኝታለች