“የይሖዋ እጅ” በሕይወቴ ውስጥ
ሎውረንስ ቶምሶን እንደተናገረው
በ1946 አንድ ምሽት ላይ እኔና አባቴ መኪና ውስጥ ቁጭ ብለን በሰማዩ ላይ የሚብረቀረቁትን የሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ የብርሃን ጮራዎችን እንመለከት ነበር። የይሖዋን ታላቅነትና የእኛን ኢምንትነት አንስተን ተጨዋወትን። የይሖዋ ምስክሮች ሥራ በካናዳ ታግዶ በነበረባቸው ዓመታት ከተደረጉት ነገሮች አንዳንዶቹን አስታውሰን ነበር። ይሖዋ በእነዚያ ዓመታት ሕዝቦቹን እንዴት ይጠብቅና ይመራ እንደነበረ አባቴ የነገረኝ ሁሉ ልቤን በጣም ነክቶታል።
ምንም እንኳ ዕድሜዬ ገና 13 ዓመት ቢሆንም አባቴ የሚናገረውን ቁም ነገር መረዳት እችል ነበር። በተጨማሪም የስብከቱ ሥራ በጣም ሰፊና አጣዳፊ መሆኑ በአእምሮዬ ውስጥ እንዲቀረጹ አድርጓል። አባቴ ዘኁልቁ 11:23ን ጠቅሶ የይሖዋ እጅ አጭር ሆኖ እንደማያውቅ ጠበቅ አድርጎ ነገረኝ። ይሖዋ የሚያደርግልንን ነገር የሚወስንብን እምነታችንና በእርሱ ላይ ያለን ትምክህት ማነሱ ብቻ ነው። ልረሳው የማልችል በጣም ደስ የሚል የአባትና የልጅ ጭውውት ነበር።
በልጅነት ጊዜዬ አስተሳሰቤን በጣም የነካው ሌላ ነገር ደግሞ የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎችን በተለይም በ1939 የታተመውን ሳልቬሽን የተባለውን መጽሐፍ ማጥናቴ ነው። ሥዕላዊ በሆነ መንገድ የቀረበውን የመክፈቻ ምሳሌ አልረሳውም፦ “በታላቅ ፍጥነት በመገስገስ ላይ የሚገኝ አንድ ባቡር በተሳፋሪዎች ታጭቆ በሰዓት 160 ኪሎ ሜትር ይበርራል። አንድን ወንዝ ለማቋረጥ በድልድይ ላይ ማለፍ አለበት። . . . በባቡሩ በስተኋላ ተቀምጠው የነበሩ ሁለት ሰዎች አሻግረው ባቡሩ የሚያልፍበት ድልድይ አንድ ክፍል በእሳት ተያይዞ ወደ ወንዙ ውስጥ ሲወድቅ በፊት ለፊታቸው ይመለከታሉ። አሰቃቂ አደጋ እንደሚያጋጥማቸው ተገነዘቡ። አጣዳፊ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ምንም አያጠራጥርም። የተሳፈሩት መንገደኞች ሕይወት እንዲድን ባቡሩ ልክ በጊዜው መቆም ይችል ይሆንን?”
መጽሐፉ የምሳሌውን ትርጉም ሲያብራራ እንዲህ በማለት ይደመድማል፦ “በተመሳሳይም ዛሬ፣ በምድር ላይ የሚኖሩት መንግሥታትና ሕዝቦች ከድንገተኛ አደጋ ጋር ተፋጥጠዋል። የአርማጌዶን ጥፋት ከፊታቸው እንደተደቀነ አምላክ ባዘዘው መሠረት ማስጠንቀቂያ እየተሰጣቸው ነው። . . . እያንዳንዱ ሰው የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ስለደረሰው ምን ማድረግ እንዳለበት መምረጥ ይኖርበታል።”
ፈጣኑ ባቡር፣ በእሳት የተያያዘው ድልድይና የስብከቱ ሥራ አጣዳፊነት በአእምሮዬ ውስጥ ሊፋቅ በማይችሉበት ሁኔታ ተቀርጸዋል።
የልጅነት ስብከት
በስብከቱ ሥራ መካፈል የጀመርኩበት በ1938 የአምስት ዓመት ልጅ ሳለሁ ነበር። ሁለት አቅኚዎች (የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች) ማለትም ሄንሪ የተባለ ወንድም እና አልስ ትዊድ የተባለች እኅት ይዘውኝ ይወጡና በየቀኑ ከ10 እስከ 12 ሰዓት ከሰዎች ጋር ስንነጋገር እንውል ነበር። በይሖዋ አገልግሎት ሙሉ ቀን ከተሰማራሁባቸው ከእነዚያ ቀኖች ከፍተኛ ደስታ አግኝቻለሁ። ስለዚህ በሚቀጥለው ዓመት አባቴና እናቴ አስፋፊ እንድሆንና የአገልግሎት ሪፖርት እንድመልስ ሲፈቅዱልኝ በጣም ተደሰትኩ።
በዚያ የልጅነት ጊዜ የሐሰት ሃይማኖትን የሚያጋልጡ መፈክሮችንና የአምላክን መንግሥት የሚያስተዋውቁ ትልልቅ ፖስተሮችን ይዘን በከተማው ዋና ዋና መንገዶች በሚደረጉ ሰልፎች እንካፈል ነበር። በተጨማሪም በእጅ በሚያዙ ፎኖግራፎች እየተጠቀምን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መልእክቶችን በየቤቱ በራፍ ላይ ለሰዎች እናሰማ ነበር። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት የነበረውን የጄ ኤፍ ራዘርፎርድን ንግግር እናሰማ ነበር። አንዳንዶቹን ንግግሮች በቃሌ አውቃቸው ነበር። ለምሳሌ፦ “ተደጋግሞ ሲነገር እንደምንሰማው ሃይማኖት ማጭበርበሪያና ማታለያ ነው!” የሚለው ዐረፍተ ነገር አሁንም ጆሮዬ ላይ ይደውላል።
በካናዳ ሥራችን ታገደ
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በናዚ ጀርመንና በሌሎች አገሮች እንደተደረገው የይሖዋ ምስክሮች ሥራ በካናዳ ውስጥም ታገደ። ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እየተጠቀምን አምላክ ያዘዘንን ሥራ በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች መሠረት ማከናወናችንን ቀጠልን። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ሥራ 5:29) ፖሊሶች በድንገት እየመጡ ስብሰባዎቻችንንና ቤቶቻችንን እየፈተሹ የሚፈጥሩብንን ችግር መቋቋም ተማርን። በዳኞች ፊት ቀርቦ በመመስከርና በፍርድ ቤት ለሚቀርቡ መስቀለኛ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ረገድ ጥሩ ልምድ አዳበርን።
ታላቅ ወንድሜ ጂምና እኔ በጉዞ ላይ ባሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ሆነን በየበራፉና በየበረንዳው ላይ ንዑሳን መጻሕፍትን በመወርወር ጥሩ ችሎታ አዳብረን ነበር። ከዚህም በላይ እንደ ሰላዮችና አንዳንዴም እንደ ዘበኛ በመሆን ድንበሩን አቋርጠው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለትልልቅ ስብሰባዎች የሚሄዱትን ወንድሞች ረድተናቸዋል።
ቤታችን በኦንታሪዮ ፖርት አርተር (አሁን ተንደር ቤይ) በሚባለው የከተማው ዳር አካባቢ የሚገኝ ሲሆን በጫካውና በጥሻ የተከበበ አንድ ሄክታር መሬት ያህል ስፋት አለው። ላም፣ ጥጃ፣ አሳማዎችና ዶሮዎች ስለነበሩን የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለምን ሰበካችሁ ተብለው ለእስራት ይታደኑ የነበሩ ወጣት ክርስቲያን አማኞችን ለመደበቅ አስችሎናል።
ማታ ማታ ገለልተኛ በሆነው ግቢያችን ውስጥ ወጣት ክርስቲያኖችን የያዙ ከባድና ቀላል መኪናዎች እንዲሁም ተጎታች ቤቶች ሲገቡና ሲወጡ ያድሩ ነበር። እነዚህን ወጣቶች እያሳደርን፣ እየደበቅን፣ መልካቸውን ለውጠው እንዲወጡ እያደረግንና እየመገብን ወደሚሄዱበት እንሸኛቸው ነበር። አባቴና እናቴ፣ እንዲሁም እነዚያ የጥንት ሠራተኞች በሙሉ ነፍሳቸው ያገለግሉ ስለነበር የወጣትነት ልቤን በይሖዋ አምላክ ፍቅርና አገልግሎት ላይ እንዲያተኩር አድርገው ቀርጸውታል።
በነሐሴ ወር 1941 ራሴን ለይሖዋ ወሰንኩና ጫካ ውስጥ በምትገኝ አንዲት ትንሽ ሐይቅ ውስጥ ተጠመቅሁ፣ ለዚህ ሥነ ሥርዓት በርከት ብለን በሻማ ብርሃን በታገዘች ጠባብ ቤት ውስጥ በሌሊት ተሰብስበን ነበር። እንደተለመደው ፖሊሶች ተጠራጥረው ዙሪያውን በመክበብ በትልልቅ የባውዛ መብራቶች ሐይቁን አንድ በአንድ ቢፈትሹም ሊያገኙን አልቻሉም።
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተለያዩ ዘርፎች
በ1951 ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተመረቅሁ በኋላ 1,600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ኮበርግ፣ ኦንታሪዮ የአቅኚነት አገልግሎት ምድቤን ተቀብዬ ተጓዝኩ። ጉባኤው ትንሽ ነበር፣ አቅኚ ጓደኛም አልነበረኝም። የይሖዋ እጅ አጭር አለመሆኗን በማስታወስ ቤት ተከራይቼ ራሴ ምግቤን እያበሰልኩ ይሖዋን በማገልገል መደሰት ጀመርኩ። በሚቀጥለው ዓመት በቶሮንቶ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ እንዳገለግል ተጠራሁ። በዚህም አገልግሎቴ ለመጪው የመንግሥቱ አገልግሎቴ ሥራዬ ይበልጥ ጥራት የሰጡኝን ብዙ ጠቃሚ ነገሮች ቀስሜአለሁ።
ከአንድ ዓመት በላይ በቶሮንቶ ካገለገልኩ በኋላ እኔና ሉሲ ትሩዶ ተጋባንና በ1954 የክረምት ወራት በኩቤክ ሌቪስ በአቅኚነት እንድናገለግል ተመደብን። አየሩ በጣም ቀዝቃዛ ነው። ረብሻ የሚያስነሱብን ሰዎች ሁኔታና የፖሊሶቹ ፍተሻ ያስፈራል። ፈረንሳይኛ ቋንቋ መማር ቀላል አልነበረም። በዚህ ሁሉ የይሖዋ እጅ አጭር ስላልሆነች በጣም አስፈሪ ወቅቶች ብናሳልፍም ብዙ ጥሩ ውጤቶችን አግኝተናል።
ለምሳሌ፣ በ1955 በአውሮፓ ወደሚደረጉት ትልልቅ ስብሰባዎች የሚሄዱትን ተወካዮች ለማጓጓዝ ማኅበሩ ሊገለገልባቸው ያሰባቸውን (እሮዝ ስታር እሮዝ ኩልም የተባሉትን) መርከቦች እንድንቆጣጠር ተጠይቀን ነበር። የመርከቡ ድርጅት ባለ ሥልጣኖች የማኅበሩን ደንበኝነት ለማግኘት በመጓጓት አልፎ አልፎ ጥሩ አቀባበል ስለሚያደርጉልን በወቅቱ በኩቤክ ከነበረው የአገልግሎት ውጥረት አስደሳች የእፎይታ ጊዜ እናገኝ ነበር።
በ1955 የበልግ ወራት ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተጋበዝኩና በቀዝቃዛው የኦንታሪዮ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኙትን ጉባኤዎች በክረምቱ ወራት ጎበኘናቸው። በሚቀጥለው ዓመት በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት ተካፈልንና ስንጨርስ በደቡብ አሜሪካ በሚገኘው በብራዚል አገር ሚስዮናውያን ሆነን እንድናገለግል ተመደብን።
አዲስ በተመደብንበት አካባቢ በሙሉ ልባችንና ነፍሳችን መሥራት ጀመርን። ብዙም ሳንቆይ በፖርቹጋል ቋንቋ መስበክና ማስተማር ቻልን። በ1957 መጀመሪያ ላይ እንደገና ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። አሁን ግን በጣም ቀዝቃዛ የሆኑት የሰሜን አካባቢዎች ትተን ተቃራኒ የሆነውን እንደ እሳት የሚጠብስ ሙቀት መቋቋም አስፈለገን። ብዙ ጊዜ ጫማዎቻችን ውስጥ የሚገቡትን የሚያቃጥሉ አሸዋዎች ለማውጣትና ሸንኮራ አገዳ ቆርጠን በልተን ኃይላችንን ለማደስ ቆም ማለት ነበረብን። ይህም ሆኖ ብዙ በረከቶችን አግኝተናል።
ራዤንቲ ፈዡ በተባለው ከተማ የፖሊስ አዛዡን አነጋገርኩና ሱቆች በጠቅላላ እንዲዘጉና ሰው ሁሉ ወደ ከተማው አደባባይ እንዲመጣ ትእዛዝ አስተላለፈ። ሰፋፊ ቅጠል ባለው አንድ ባለ አበባ ዛፍ ሥር ተጠልዬ ለከተማው ሕዝብ በሙሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር አደረግሁላቸው። ዛሬ በዚያ ከተማ የምስክሮች ጉባኤ ይገኛል።
ልጆቻችንን በብራዚል ማሳደግ
በ1958 ሉሲ አረገዘችና ጁይዝ ደ ፎራ በተባለ ከተማ መኖሪያችንን አድርገን በልዩ አቅኚነት ማገልገል ጀመርን። በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ሴቶች ልጆቻችን ሱዛን እና ኪም ተወለዱ። በከተማው ውስጥ እንደ ብርቅ ስለታዩ ለአገልግሎቱ ልዩ በረከት ሆነውልኝ ነበር። በሕፃናት ጋሪ አስቀምጠን በኮረኮንች መንገድ ላይ እየገፋን ስንወስዳቸው፣ ሰዎች እነሱን ለማየት ይወጣሉ። በምድር ወገብ አጠገብ በስተደቡብ በሚገኘው በሬሲፍ የመንግሥቱ አስፋፊዎች በብዛት ይፈለጉ ስለነበረ በጣም ሞቃታማ ወደሆነው ወደዚህ ቦታ ተዛወርን።
በ1961 በሳኦ ፖውሎ በተደረገው የማይረሳ ትልቅ ስብሰባ ላይ መገኘት ብቻ ሳይሆን ወደ ስብሰባው ለሚሄዱት ምስክሮች የአውሮፕላን መጓጓዣ በማዘጋጀቱ ሥራ ለመካፈል ችዬ ነበር። 20 ደቂቃ ያህል እንደበረርን በድንገት አውሮፕላኑ በአንፍጫው ለመተከል ወደ መሬት በማሽቆልቆሉ ተሳፋሪዎቹን በግድግዳው ላይ አላተማቸው። የአውሮፕላኑ ውስጠኛ ክፍል በጣም ተጎዳ። ወንበሮቹ ከማሰሪያቸው ተለያይተው ተጨማተሩ። መንገደኞቹም ስለቆሰሉ ብዙ ደም ፈሰሳቸው። ይሁን እንጂ አብራሪው ፓይለት አውሮፕላኑን ከመከስከስ አድኖ በሰላም እንዲያርፍ በማድረጉ በጣም ተደሰትን። ከመካከላችን በሌላ አውሮፕላን ወደ ሳኦ ፓውሎ መጓዝ ያቃተው በጣም የተጎዳ ሰው አልነበረም። ትልቁ ስብሰባ በጣም የሚያንጽ ነበር። ይሁን እንጂ ሁለተኛ በአውሮፕላን አልሄድም ብዬ ወሰንኩ።
ይሁን እንጂ ከስብሰባው ተመልሼ ቤት ስደርስ ሌላ ኃላፊነት ተቀምጦ ጠበቀኝ። በቴረዚና፣ ፒያዩ ግዛት በሚገኝ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ውስጥ ትልቅ ስብሰባ ማዘጋጀት ነበረብኝ። ወደዚያ ቦታ ለመሄድ በአውሮፕላን መጓዝ ነበረብኝ። ብፈራም በይሖዋ ክንድ በመታመን ኃላፊነቱን ተቀበልኩ።
በ1962 ወንዱ ልጃችን ግሬግ በቴሲፍ ተወለደ። አሁን የቤተሰቤ ቁጥር ስለ ጨመረ አቅኚ መሆን ባልችልም በትንሿ ጉባኤ ውስጥ ጥሩ መንፈስ አንዲሰፍን ለማድረግ ችያለሁ። ልጆቹ አገልግሎት እንዲወዱ አድርገናቸው ስለነበር ሁልጊዜ ወደ አገልግሎት ከእኛ ጋር ለመሄድ ይጓጉ ነበር። ሁሉም ከ3 ዓመት ዕድሜያቸው ጀምረው በየበሩ ላይ ጥሩ ምስክርነት ለመስጠት ይችሉ ነበር። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ከመገኘት ወይም በመስክ አገልግሎት ከመካፈል አንድም ቀን ያለመቅረት ልማድ ነበረን። ከቤተሰቡ አባል አንዱ ቢታመም እንኳ አንድ አስታማሚ ከእሱ ጋር ቀርቶ ሌሎቻችን ወደ ስብሰባዎች እንሄዳለን ወይም በመስክ አገልግሎት እንካፈላለን።
ባለፉት ዓመታት ሁሉ ልጆቹ በትምህርት ቤት ስለሚማሯቸው የትምህርት ዓይነቶችና ስለ ወደፊቱ ግባቸው አዘውትረን በመወያየት የወደፊቱን ኑሯቸውን በይሖዋ ድርጅት ውስጥ በሚሰጣቸው ሥራ ላይ እንዲመሠርቱ ረድተናቸዋል። እንደ ቴሌቪዥን ላሉ የሚያዳክሙ ተጽዕኖዎች እንዳይጋለጡ እንጠነቀቅላቸው ነበር። ልጆቹ በአሥራዎቹ ዕድሜያቸው ላይ እስኪደርሱ ድረስ በቤታችን ቴሌቪዥን የሚባል ነገር አልነበረንም። በተጨማሪም አጋጣሚው ቢኖረንም በቁሳዊ ነገሮች እንዲቀናጡ አላደረግንም። ለምሳሌ የገዛንላቸው ሦስቱም በጋራ የሚጠቀሙበት አንድ ብስክሌት ብቻ ነበር።
በተቻለን መጠን የቅርጫት ኳስ እንደመጫወት፣ እንደ ዋና እና ሽርሽር በመሳሰሉት ጨዋታዎች አብረን እንዝናና ነበር። ሽርሽሩ አብዛኛውን ጊዜ በትልልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከመገኘት ወይም በተለያዩ አገሮች የሚገኙትን የቤቴል ቤቶች ከመጎብኘት ጋር የተያያዘ ነበር። እነዚህ ጉዞዎች በነፃነት እንድንነጋገር ይረዱን ስለነበረ እኔና ሉሲ በልጆቻችን ልብ ውስጥ ምን እንዳለ ለማወቅ እንችል ነበር። ይሖዋ እነዚህን አስደሳች ዓመታት ስለሰጠን በጣም እናመሰግነዋለን።
በሐሩሩ አካባቢ ያሳለፍናቸው አሥር ዓመታት ከጊዜ በኋላ በሉሲ ጤንነት ላይ ከባድ ጉዳት አደረሱ። ከዚህም የተነሳ ደቡብ ኩሪቲባ በተባለችው በፓራና ግዛት ወደምትገኘው ነፋሻማ አየር ወዳለባት ከተማ መዛወር ግድ ሆነብን።
ወደ ካናዳ መመለስ
በብራዚል 20 ዓመት ለሚያክል ጊዜ ከቆየን በኋላ በ1977 ሉሲና እኔ ከልጆቻችን ጋር ሆነን በሽተኛ የሆነውን አባቴን ለማስታመም ወደ ካናዳ ተመለስን። ቤተሰባችን ትልቅ የባሕል ለውጥ አጋጠመው! በመንፈሳዊ ግን ምንም የተለወጠ ነገር አላጋጠመንም ምከንያቱም ከተወዳጁ ክርስቲያናዊ የወንድማማች ኅብረት ጋር በመሆን የተለመደውን ሥራችንን መቀጠል ችለናል።
በካናዳ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መላው ቤተሰብ የሚሳተፍበት ሥራ ሆነ። ሴቶቹ ልጆች ተራ በተራ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመሩ። ሁላችንም ቤተሰባችን ለተሰማራበት አገልግሎት አስተዋፅኦ እናደርግ ነበር። ሁላችንም ከትርፍ ጊዜ ሥራ የምናገኘውን ማንኛውም ገቢ የቤትና ተራርቆ የሚገኘውን የአገልግሎት ክልላችንን ለማዳረስ የሚረዱን ሦስት መኪኖች የሚያስፈልጋቸውን ወጪ ለመሸፈን እንጠቀምበታለን። በየሳምንቱ ከቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን በኋላ ስለ ቤተሰባችን ዕቅዶች እንወያያለን። እነዚህ ውይይቶች እያንዳንዳችን ወዴት እየተጓዝን እንዳለንና በሕይወታችን ምን በማድረግ ላይ እንዳለን ለይተን እንድንመለከት ረድተውናል።
ወንዱ ልጃችን ግሬግ እንደ ታላላቅ እኅቶቹ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን የሕይወቱ ግብ አድርጓል። የአምስት ዓመት ልጅ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ ቤቴል ተብሎ በሚጠራው የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ መሥራት እንደሚመኝ ይናገር ነበር። ይህንን ግቡን ፈጽሞ አልረሳውም። ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደተመረቀ እኔና እናቱን “ቤቴል ለመግባት ማመልከት የሚገባኝ ይመስላችኋል?” ብሎ ጠየቀን።
ልጃችን ትቶን በመሄዱ ስሜታችን ቢነካም ያለ ምንም ማወላወል፦ “የይሖዋ ድርጅት ማዕከል እንደ ሆነው እንደ ቤቴል ያለ የይሖዋን እጅ ምንነት የምታደንቅበት ቦታ የለም” በማለት መለስንለት። በሁለት ወር ጊዜ ወስጥ በካናዳ ወደሚገኘው ቤቴል ሄደ። ይህ የሆነው በ1980 ሲሆን እስካሁን ድረስ እዚያው እየገለገለ ነው።
1980ዎቹ ዓመታት ለእኔና ለሉሲ አዳዲስ ችግሮች አምጥተውብናል። መጀመሪያ ሁለታችንም ትዳራችንን በጀመርንበት ጊዜ ወደነበርንበት ሕይወት ተመልሰናል። በዚህ ጊዜ ሱዛን አግብታ ከባሏ ጋር በአቅኚነት ሲያገለግሉ ኪምና ግሬግ ደግሞ በቤቴል እያገለገሉ ነው። ታዲያ አሁን ምን ልናደርግ እንችላለን? ይህ ጥያቄ በ1981 መልስ አገኘ። በካናዳ ውስጥ የ2,000 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ባለው የፖርቹጋል ቋንቋ ተናጋሪ በሆነ ክልል ውስጥ እንድናገለግል ተመደብን። አሁንም በተጓዥ የበላይ ተመልካችንነት ሥራ ላይ ደስ ብሎን ተሰማርተናል።
ኪም አግብታ ጊልያድ ከሠለጠነች በኋላ በአሁኑ ጊዜ ከባሏ ጋር በብራዚል ውስጥ በክልል የበላይ ተመልካችነት ሥራ ላይ ይገኛሉ። ሱዛንና ባሏ አሁንም በካናዳ ውስጥ ሆነው ሁለት ልጆቻቸውን እያሳደጉ ሲሆን የሱዛን ባልም አቅኚ ሆኖ ያገለግላል። በተሰማራንበት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተነሳ ቤተሰባችን በአካል ቢራራቅም በመንፈስና በስሜት ግን በጣም ተቀራርበን እንኖራለን።
ሉሲና እኔ በጸዳችው ምድር ላይ ከቤተሰባችን ጋር አብረን ስንኖር ወለል ብሎ ይታየናል። (2 ጴጥሮስ 3:13) በጥንት ዘመን ይኖር እንደነበረው እንደ ሙሴ በዘኁልቁ 11:23 ላይ ለቀረበው “በውኑ የእግዚአብሔር እጅ አጭር ሆነ? አሁን ቃሌ ይፈጸም ወይስ አይፈጸም እንደሆነ አንተ ታያለህ አለው” የሚለው ጥያቄ እውነት መሆኑን ከራሳችን ተሞክሮ ማወቅ ችለናል። ይሖዋ አገልጋዮቹ ለፈጸሙት የሙሉ ልብ አገልግሎት እነርሱን እንዳይባርክ ሊያግደው የሚችል ምንም ዓይነት ኃይል የለም።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ከሉሲ ጋር