“በአፍ እንጂ በእግር አታጉርሱ”
ባሕላዊውን የአፍሪካውያን የቀብር ልማድ ቀረብ ብለን ስንመለከት
“ሙታናቸውን አይቀብሩም!” ይህ በምዕራብ አፍሪካ በሚኖሩ የይሖዋ ምስክሮች ላይ የሚሰነዘር ክስ ነው። ይሁን እንጂ ምስክሮቹ ሙታናቸውን እንደሚቀብሩ የታወቀ ነው።
ሰዎች የይሖዋ ምስክሮች ሙታናቸውን አይቀብሩም የሚሉት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ምስክሮቹ በአካባቢው ከታወቁት የቀብር ልማዶች አብዛኛውን ስለማይከተሉ ነው።
ባሕላዊዎቹ የቀብር ልማዶች
አሊዉ በመካከለኛው ናይጄሪያ ውስጥ በምትገኝ አንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ ይኖራል። እናቱ በሞተችበት ጊዜ የእሷን መሞት ለዘመዶቹ ከነገራቸው በኋላ በቤቷ ውስጥ ቅዱስ ጹሑፋዊ የቀብር ንግግር እንዲሰጥ ዝግጅት አደረገ። በአካባቢው የሚገኘው የይሖዋ ምስክሮች ጉባኤ ሽማግሌ ያቀረበው ንግግር በሙታን ሁኔታና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሰውና ሰዎችን በሚያጽናናው የትንሣኤ ተስፋ ላይ ያተኮረ ነበር። ንግግሩ ከተሰጠ በኋላ የአሊዉ እናት ተቀበረች።
ዘመዶቹ በጣም ተቆጡ። በእነርሱ ልማድ መሠረት አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ባለው ሌሊት ሬሳው እየተጠበቀ ካላደረ በስተቀር ቀብሩ የተሟላ አይደለም። አሊዉ በሚኖርበት አካባቢ ሬሳ ሲጠበቅ የሚታደርበት ሌሊት የለቅሶ ሳይሆን የግብዣ ወቅት ነው። ሬሳው ይታጠባል፣ ነጭ ልብስ ይለብሳል፣ ከዚያም በአልጋ ላይ ይደረጋል። ኀዘንተኞቹ ሙዚቀኞች ይጠራሉ፣ እንደ ቢራና የወይን ጠጅ የመሳሰሉ የአልኮል መጠጦች ይገዙና በሬ ወይም ፍየል ታርዶ ይሠዋል። ከዚያ በኋላ ዘመዶችና ወዳጆች ሌሊቱ እስኪነጋ ድረስ ለመዝፈን፣ ለመጨፈር፣ ለመብላትና ለመጠጣት ይመጣሉ።
በዚህ የግብዣ ወቅት በአስከሬኑ እግር ሥር ምግብ ይቀመጣል። ከሞተው ሰው ላይ ከጠጉሩ፣ ከእጅና ከእግሩ ጥፍሮች ላይ ጥቂት ተቆርጦ ይወሰድና ለ“ዳግማዊ ቀብር” ይቀመጣል። ሁለተኛው የቀብር ሥርዓት ቀናት፣ ሳምንታት ወይም ዓመታትም ቆይቶ ሊደረግ ይችላል።
ሬሳው ሲጠበቅ ባደረበት ሌሊት ቢቀበርም የቀብሩ ሥርዓት ሳምንት ወይም ከዚያ በላይ ሊቆይ ይችላል። ከዚያ በኋላ ዳግማዊው ቀብር ይደረጋል። ከራሱ የተወሰደው ጠጉርና ከእጅና ከእግሩ የተወሰዱት ጥፍሮች በነጭ ጨርቅ ይጠቀለሉና ከ1. 5 እስከ 2 ሜትር የሚደርስ ርዝማኔ ባለው ወፍራም የእንጨት ምሰሶ ላይ ይታሰራሉ። እንጨቱ እየተዘፈነና እየተጨፈረ ወደ መቃብር ቦታው ከተወሰደ በኋላ ሟቹ አጠገብ ይቀበራል። አሁንም እንደገና ብዙ ዘፈን፣ ጭፈራና ግብዣ ይደረጋል። የቀብሩን ሥርዓት ለመደምደም አንድ ጊዜ ወደ ሰማይ ጥይት ይተኮሳል።
አሊዉ እነዚህ ነገሮች እንዲደረጉ ባለመፍቀዱ ሙታንንም ሆነ ለሙታን ክብር የሚደረጉትን ልማዶች ንቋል ተብሎ ተከሰሰ። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምስክር የሆነው አሊዉ ይህን ባሕል ያልተቀበለው ለምን ነበር? እነዚህ ባሕሎች የተመሠረቱበትን ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ሕሊናው ሊቀበልለት ስላልቻለ ነው።
ባሕላዊው የአፍሪካውያን እምነት
በአፍሪካ አሕጉር የሚኖሩ ብዙ ሕዝቦች ሰዎች ሁሉ የመጡት ከመንፈሳዊው ዓለም ስለሆነ ወደዚያው ተመልሰው ይሄዳሉ ብለው ያምናሉ። በናይጄሪያ የሚኖሩ የዮሩባ ብሔር አባላት “መሬት የገበያ ቦታ ስትሆን ሰማይ ግን መኖሪያ ቤታችን ነው” ይላሉ። የኢግቦ ሰዎች ደግሞ “ወደዚህ ዓለም የሚመጣ ማንኛውም ሰው በምድር ላይ ምንም ያህል ዘመን ቢቆይ ቤቱ ወደሆነው ሰማይ መመለሱ አይቀርም” ይላሉ።
ቀደም ብሎ የተጠቀሰውን ልማድ ተመልከት። ሬሳው ሲጠበቅ የሚታደረው ለሟቹ መንፈስ ጥሩ አሸኛኘት ለማድረግ ነው። ነጩ ልብስ ለመንፈሳዊው ዓለም የሚስማማ ልብስ ነው ተብሎ ይታመናል። በአስከሬኑ እግር ሥር ምግብ የሚቀመጠው ደግሞ አስከሬን የሚበላው በእግሩ ነው ተብሎ ስለሚታመን ሲሆን ወደ አያቶቹ አገር ሲጓዝ እንዳይርበው ምግብ ይቀመጥለታል።
ከዚህም በላይ ብዙ ሰዎች የሟቹ መንፈስ ሁለተኛው ቀብር ተደርጐ እስኪለቀቅ ድረስ ወደ አያቶቹ ሳይመለስ እዚሁ በሕያዋኑ መካከል ወዲያና ወዲህ እያለ ይቆያል ብለው ያምናሉ። ሁለተኛው የቀብር ሥርዓት ካልተደረገ መንፈሱ ይቆጣና በሕይወት ያሉትን በበሽታ ወይም በሞት ይቀስፋቸዋል ብለው ይፈራሉ። ጥይት የሚተኮሰው ደግሞ “መንፈሱን ወደ ሰማይ ለመላክ ነው።”
በአፍሪካ ውስጥ የሚከናወነው የቀብር ሥርዓት ከቦታ ወደ ቦታ የሚለያይ ቢሆንም ሰው ከሞተ በኋላ መንፈሱ በሕይወት ይኖራል በሚለው ሐሳብ ላይ የተመሠረተ ነው። የቀብሩ ሥርዓት ዋነኛ ዓላማ መንፈሱ “ወደ ሰማይ እንዲሄድ የተደረገለትን ጥሪ” እንዲቀበል ማገዝ ነው።
እነዚህ እምነቶችና ልማዶች ሕዝበ ክርስትና የሰው ነፍስ አትሞትም ብላ በምታስተምረው ትምህርትና ለ“ቅዱሳን” ክብር በመስጠቷ ሲደገፉ ቆይተዋል። በስዋዚላንድ የሚገኝ አንድ ቄስ ኢየሱስ የመጣው ባሕላዊ እምነቶችን ለማጥፋት ሳይሆን ሊፈጽማቸው ወይም ሊያጸናቸው ነው ሲል የተናገረው ቃል እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችል ነው። ብዙውን ጊዜ የቀብር ሥርዓቶችን የሚመሩት ቄሶች ስለሆኑ ብዙ ሰዎች ይህን ባሕላዊ እምነትና ልማድ መጽሐፍ ቅዱስ የሚደግፈው ይመስላቸዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን እምነቶች ይደግፋቸዋልን? የሙታንን ሁኔታ በተመለከተ መክብብ 3:20 “ሁሉ [ሰዎችና እንስሳት] ወደ አንድ ቦታ ይሄዳል፤ ሁሉ ከአፈር ነው ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳል” በማለት ይናገራል። በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎች “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ . . . ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ጠፍቶአል፣ . . . አንተ በምትሄድበት በሲኦል [በመቃብር] ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና” ይላሉ።—መክብብ 9:5, 6, 10
እነዚህና ሌሎች ጥቅሶች ሙታን ሊያዩን ወይም ሊሰሙን ወይም ሊረዱን ወይም ሊጎዱን እንደማይችሉ ግልጽ ያደርጉልናል። ይህ አባባል ከዚህ በፊት ካስተዋልካቸው ሁኔታዎች ጋር አይስማማምን? ሀብታምና ብዙ ሥልጣን የነበረው አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ቤተሰቡ የቀብሩ ሥርዓት የሚጠይቅባቸውን ነገር ሁሉ ቢያደርጉም በኋላ ግን ብዙ ችግር እንደደረሰባቸው አይተህ ይሆናል። ያ ሰው በመንፈሳዊው ዓለም በሕይወት የሚኖር ከሆነ ቤተሰቡን ለምን አይረዳም? መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ሕይወት እንደሌላቸው፣ ኃይላቸው በሙሉ በሞት እንደተወሰደባቸውና ማንንም ሊረዱ እንደማይችሉ የተናገረው ቃል እውነት ስለሆነ ሊረዳ አልቻለም።—ኢሳይያስ 26:14
የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህ እውነት መሆኑን ያውቅ ነበር። አልዓዛር ከሞተ በኋላ የሆነውን ነገር ተመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ “[ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ] ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ አላቸው። እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ፦ ጌታ ሆይ፣ ተኝቶስ እንደ ሆነ ይድናል አሉት። ኢየሱስ ግን ስለ ሞቱ ተናግሮ ነበር” በማለት ይገልጻል።—ዮሐንስ 11:11–13
ኢየሱስ ሞትን ከእንቅልፍ ማለትም ከዕረፍት ጋር እንዳመሳሰለ አስተውል። ቢታንያ በደረሰ ጊዜ የአልዓዛርን እኅቶች ማርያምንና ማርታን አጽናናቸው። በመንፈሱ አዘነና እንባውን አፈሰሰ። ይሁን እንጂ አልዓዛር ሕያው የሆነና ወደ አያቶቹ አገር ለመሄድ እርዳታ የሚያስፈልገው መንፈስ እንዳለው የሚያመለክት አንድም ቃል አልተናገረም ወይም ምንም ነገር አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ አደርገዋለሁ ብሎ የተናገረውን አደረገ። በትንሣኤ አማካኝነት አልዓዛርን ከሞት እንቅልፍ አስነሣው። ይህም ወደፊት አምላክ በኢየሱስ ተጠቅሞ በመታሰቢያ መቃብር ውስጥ ያሉትን በሙሉ እንደሚያስነሣቸው ያረጋግጣል።—ዮሐንስ 11:17–44፤ 5:28, 29
ከታወቀው ልማድ የተለየ ነገር የሚያደርጉት ለምንድን ነው?
ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆነ እምነት ላይ የተመሠረተ የቀብር ልማድ መፈጸም ምን ስሕተት አለው? አሊዉ እና በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች የይሖዋ ምስክሮች ስሕተት ነው ብለው ያምናሉ። በተሳሳቱና በሐሰት መሠረተ ትምህርቶች ላይ የተመሠረቱ መሆናቸው በግልጽ የሚታወቁትን ልማዶች መደገፍ ስሕተት፣ እንዲያውም ግብዝነት መሆኑን ያውቃሉ። በሃይማኖታዊ ግብዝነታቸው ምክንያት ኢየሱስ እንዳወገዛቸው ጸሐፍትና ፈሪሳውያን መሆን አይፈልጉም።—ማቴዎስ 23:1–36
ሐዋርያው ጳውሎስ የሥራ ባልደረባው የነበረውን ጢሞቴዎስን “መንፈስ ግን በግልጥ፦ በኋለኞቹ ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፣ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል” በማለት አስጠንቅቆታል። (1 ጢሞቴዎስ 4:1, 2) ሙታ ን የሰው ዘሮች በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ይኖራሉ የሚለው አስተሳሰብ የአጋንንት ትምህርት ነውን?
አዎን፣ የአጋንንት ትምህርት ነው። “የሐሰት አባት” የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ሔዋን ለዘላለም በሥጋ እንደምትኖር በማመልከት ፈጽ ሞ እንደማትሞት ነግሯት ነበር። (ዮሐንስ 8:44፤ ዘፍጥረት 3:3, 4) ይህ አባባል ሰው ከሞተ በኋላ ነፍሱ ከሥጋው ተለይታ ትኖራለች ከሚለው አባባል ጋር አንድ አይደለም። ይሁን እንጂ ሰይጣን እና አጋንንቱ ከሞት በኋላ ሕይወት ይኖራል የሚለውን እምነት በማስፋፋት ሰዎችን ከአምላክ ቃል እውነት ለማራቅ ጥረት ያደርጋሉ። የይሖዋ ምስክሮች አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተናገረውን ስለሚያምኑ የሰይጣንን ውሸት በሚደግፉ አመለካከቶችና ልማዶች አይካፈሉም።—2 ቆሮንቶስ 6:14–18
የይሖዋ ምስክሮች ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ከሌለው የቀብር ሥርዓት ስለሚርቁ ከእነሱ የተለየ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ይነቅፏቸዋል። አንዳንድ ምስክሮች የወራሽነት መብት ተነፍጓቸዋል። ሌሎችን ደግሞ ቤተሰቦቻቸው አሠቃይተዋቸዋል። ይሁን እንጂ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደ መሆናቸው መጠን አምላክን በታማኝት መታዘዛቸው በዓለም እንዲጠሉ እንደሚያደርጋቸው ይገነዘባሉ። እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ሐዋርያት ‘ከሰው ይልቅ ለአምላክ ለመታዘዝ’ ቆርጠዋል።—ሥራ 5:29፤ ዮሐንስ 17:14
እውነተኛ ክርስቲያኖች በሞት ያንቀላፉ የሚያፈቅሯቸው ዘመዶቻቸው ትዝታ ከአእምሮአቸው ባይጠፋም በሕይወት ላሉት ፍቅራቸውን ለማሳየት ጥረት ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል አሊዉ አባቱ ከሞቱ በኋላ እናቱን ወደ ቤቱ አምጥቶ እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ ሲመግባቸውና ሲንከባከባቸው ቆይቷል። እንደ አገሩ ልማድ እናቱን ስላልቀበረ እናቱን አይወድም ብለው ሰዎች ቢተቹትም በሕዝቡ መካከል ብዙ ጊዜ የሚነገረውን “ከእግሬ በፊት በአፌ አጉርሱኝ” የሚለውን አባባል ጠቀሰላቸው። በአፍ ማጉረስ ማለትም ሰውየው ወይም ሴትየዋ ገና በሕይወት እያለ ወይም እያለች መንካባከብ ግለሰቡ ከሞተ በኋላ እግሩ ሥር ምግብ ማስቀመጥን ከሚጨምረው ሬሳ ሲጠብቁ ከማደርና ከመሳሰሉት ቀደም ተብሎ ከተጠቀሱት ልማዶች ይበልጥ አስፈላጊ ነው። በእግር ማጉረስ የሞተውን በምንም መንገድ አይጠቅመውም።
አሊዉ ተቺዎቹን ‘ቤተሰባችሁ በእርጅና ዘመናችሁ ቢጦራችሁ ይሻላል ወይስ ከሞታችሁ በኋላ ትልቅ ድግስ ቢያዘጋጅላችሁ?’ ብሎ ጠየቃቸው። ብዙዎቹ በሕይወት እያሉ ቢጦሩ መርጠዋል። በተጨማሪም በሚሞቱበት ጊዜ ክብር ያለው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተና ልከኛ የሆነ የቀብር ሥርዓት እንደሚደረግላቸው በማወቃቸው ደስ ይላቸዋል።
የይሖዋ ምስክሮች ለሚያፈቅሯቸው ሰዎች ለማድረግ የሚጥሩት ይህንን ነው። በአፍ እንጂ በእግር አያጎርሱም።