የጴጥሮስ መቃብር በቫቲካን ውስጥ ይገኛልን?
“የሐዋርያት ልዑል የተቀበረበት ቦታ ተገኘ።” ሊቀ ጳጳስ ፓየስ 12ኛ ሕዝባቸውን ለማብሰር የተናገሩት ይህ ቃል በቫቲካን ሬዲዮ ተላልፎ ነበር። ጊዜው የ1950 መገባደጃ ነበር፤ በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ሥር ሲደረግ የቆየው አስቸጋሪ ቁፋሮ ገና መጠናቀቁ ነበር። አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ የዚህ አርኪኦሎጂያዊ ምርምር ውጤት ጴጥሮስ በእርግጥ በቫቲካን እንደተቀበረ አረጋግጧል። ይሁን እንጂ በዚህ የተስማሙት ሁሉም አይደሉም።
ካቶሊኮች በቫቲካን ለሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ግምት ይሰጡታል። “ምዕመናን ወደ ሮም የሚጎርፉበት ዋና ዓላማ የጴጥሮስን ተተኪ ለማየትና የእሱን በረከት ለመቀበል ነው፤ ምክንያቱም ለአገር ጎብኚዎች የተዘጋጀው የካቶሊክ መመሪያ መጽሐፍ ጴጥሮስ ወደ ሮም መጥቶ በዚያ ተቀብሯል” በማለት ይገልጻል። ሆኖም ጴጥሮስ በእርግጥ በሮም ተቀብሯልን? መቃብሩ በቫቲካን ይገኛልን? አፅሙስ ተገኝቷልን?
አርኪኦሎጂያዊ ምሥጢር
በ1940 ገደማ ተጀምሮ በግምት እስከ አሥር ዓመት የዘለቀው የከርሰ ምድር ቁፋሮ ብዙ የሚያጨቃጭቅ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል። የከርሰ ምድር ቁፋሮ እንዲያደርጉ በጳጳሱ የተሾሙት አርኪኦሎጂስቶች ያገኙት ነገር ምን ነበር? አንደኛ ብዙ መቃብሮች ያሉበት አንድ የአረማውያን መካነ መቃብር አግኝተዋል። በእነሱም መካከል ይኸውም አሁን ጳጳሱ መሥዋዕት በሚያቀርቡበት መሠውያ ሥር በሁለት ግድግዳዎች መካከል የሚገኝና በቀይ ሲሚንቶ የተለሰነ ሐውልት ወይም ቅርፃ ቅርፅ ማስቀመጫ አንድ አዲኪላ አግኝተዋል። በመጨረሻም በጣም የሚያስገርመው ጥቂት የሰው አፅም ተገኘ። ይህም ከጎንና ከጎን ካሉት ሁለት ግድግዳዎች ከአንዱ ውስጥ የተገኘ ነው ይባላል።
የተለያየ ትርጉም መሰጠት የጀመረው ከዚህ በኋላ ነው። እንደ ብዙዎቹ የካቶሊክ ምሁራን አባባል እነዚህ ግኝቶች ኔሮ ይገዛ በነበረበት ወቅት ምናልባትም በ64 እዘአ በተቀሰቀሰው ስደት ወቅት ጴጥሮስ በሮም ይኖር እንደነበረና እዚያው እያለ ሰማዕት ሆኗል የሚለውን እምነት የሚያረጋግጡ ናቸው። እንዲያውም የአፅም ቅሪቶቹ የሐዋርያው ጴጥሮስ ናቸው፤ ይህንንም በግድግዳው ላይ ተቀርጸው ከተገኙት ጽሑፎች መለየት ይቻላል ተብሏል። ይህ ጽሑፍ በአንድ ሰው ትርጉም መሠረት እንዲህ ይነበባል “ጴጥሮስ እዚህ ነው”። ሊቀ ጳጳስ ጳውሎስ 6ኛ “በሚገባ ልናመልካቸውና ቅዱስ አድርገን ልንይዛቸው ይገባናል” ያሏቸው “የቅዱስ ጴጥሮስ የአፅም ቅሪቶች” መገኘታቸውን በ1968 ሲያስታውቁ ለዚህ መላ ምት ልዩ ግምት መስጠታቸው ነበር።
ይሁን እንጂ ለጽሑፎቹ የተሰጠውን ትርጉም የሚያፈርስ የተቃውሞ ሐሳብ ነበረ። በቫቲካን በተደረገው የከርሰ ምድር ቁፋሮ የተካፈሉት ኢየሱሳዊው የካቶሊክ አርኪዮሎጂስት አንቶንዮ ፈሩዋ ስለ ጉዳዩ የሚያውቁትን ነገር ሁሉ ማለትም ከጴጥሮስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ጥንታዊ ቅርሳ ቅርሶች ተገኝተዋል ከሚለው አባባል ጋር የሚጋጭ ሐሳብ ለማሳተም በተደጋጋሚ ሞክረው ‘እንዳልተፈቀደላቸው’ ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የካቶሊክ ካርዲናል በሆኑት በፖፕዋርድ የተዘጋጀውና በ1991 የታተመው ለአገር ጎብኚዎች የተዘጋጀው የሮም መመሪያ መጽሐፍ “ቀዩ ግድግዳ ከቆመበት መሠረት ሥር በተገኙት የሰው አጥንቶች ላይ የተደረገው ሳይንሳዊ ምርመራ እንደሚያሳየው አጥንቶቹ ከሐዋርያው ጴጥሮስ ጋር ምንም ግንኙነት ያላቸው አይመስልም” ብሏል። በጣም የሚያስገርመው ቀጥሎ በወጣው የመጽሐፉ እትም ላይ ይህ ሐረግ ጠፋና “ጴጥሮስ በቅዱስ ጴጥሮስ ባስሊካ ውስጥ እንዳለ ምንም አያጠራጥርም” በሚል ርዕስ አዲስ መግለጫ ተጨመረ።
ለግኝቶቹ የተሰጠው ትርጉም
ግኝቶቹ በተለያዩ ሰዎች የተለያየ ትርጉም እንደሚሰጣቸው ግልጽ ነው። በጣም የታወቁ የካቶሊክ ታሪክ ጸሐፊዎች “ጴጥሮስ ሰማዕት የሆነውና የተቀበረው በሮም ነው የሚለው አባባል የሚፈጥረውን ታሪካዊ ችግርና አጠያያቂነቱን” ተረድተዋል። የተገኙት ነገሮች በይፋ እንዲታወቅ ያደረጉት ነገር ምንድን ነው?
የካቶሊክን እምነት አቋም ለመደገፍ የሚፈልጉ አንዳንዶች ኤዲኩላ የሚባለው ሐውልት በሦስተኛ መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ይኖር የነበረ ጋየስ የሚባል የአንድ ቄስ “መታሰቢያ” ነው ይላሉ። ጋየስ ‘በቫቲካን ኮረብታ ላይ የጴጥሮስ የመታሰቢያ ሐውልት የሚገኝበትን ቦታ ለመጠቆም’ እችላለሁ ብሏል ሲሉ የአራተኛው መቶ ዘመን የቤተ ክህነት ታሪክ ጸሐፊ የነበሩት የቂሣሪያው ዩሴቢየስ ጽፈዋል። የዚህ እምነት ደጋፊዎች ሐዋርያው ጴጥሮስ “የጋዮስ መታሰቢያ” በመባል ከሚታወቀው ሐውልት ሥር ተቀብሯል ይላሉ። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ የተገደለው እዚያ ቢሆንም እንኳ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ሬሳቸውን ስለሚቀብሩበት ቦታ ይህን ያህል ስለማይጨነቁ የጴጥሮስን አስከሬን ከተቀበረበት የማውጣቱ ጉዳይ በጣም አጠራጣሪ መሆኑን በማስገንዘብ ሌሎች በቁፋሮ የተገኘውን ነገር ፍጹም በተለየ መንገድ ይተረጉሙታል። (በገጽ 29 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።)
የ“ጋየስ የመታሰቢያ ሐውልት” (የተገኘው እሱ ከሆነ ማለት ነው) መቃብር መሆኑን የማይስማሙ ሰዎች አሉ። ወደ ሁለተኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ለጴጥሮስ ክብር የቆመ ሐውልት ሲሆን ከጊዜ በኋላ “የመቃብር ሐውልት እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ጀመር” የሚል አቋም አላቸው። ሆኖም የሃይማኖት ሊቅ የሆኑት ኦስካር ኩልማን “በቫቲካን በተደረገው የከርሰ ምድር ቁፋሮ የጴጥሮስ መቃብር በጭራሽ አልተገኘም” ይላሉ።
ስለተገኘው አፅምስ ምን ለማለት ይቻላል? በእርግጥ አፅሙ ከየት እንደመጣ ማስረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን አሁን የቫቲካን ኮረብታ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ አንድ የአረማውያን መካነ መቃብር ስለነበረ በአካባቢው የብዙ ሰዎች አስከሬን ተቀብሯል። የብዙዎቹም አፅም ተገኝቷል። አንዳንዶች ይህ በድንጋይ ላይ ተቀርጾ የተገኘ ያልተሟላ ጽሑፍ (ምናልባትም በአራተኛው መቶ ዘመን የተቀረጸ ሊሆን ይችላል) ቅርሳ ቅርሶቹ የተገኙበት ቦታ የሐዋርያት መቃብር መሆኑን ይገልጻል፤ ስለዚህ “የጴጥሮስ አፅም አለ ተብሎ የሚገመትበትን” ይበልጥ ሊጠቁም ይችላል ይላሉ። በተጨማሪም ብዙዎች የተቀረጹ ጥንታዊ ጽሑፎችን የሚያጠኑ ሰዎች እንዲያውም የተቀረጹት ጽሑፎች “ጴጥሮስ እዚህ የለም” የሚሉ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል።
‘አስተማማኝ ያልሆነ ወግ’
“ጥንታዊውና ይበልጥ አስተማማኝ የሆነው ምንጭ [ጴጥሮስ] ሰማዕት የሆነበትን ቦታ አይገልጽም፤ ከጊዜ በኋላ በተጻፉትና ብዙም እምነት በማይጣልባቸው ምንጮች መካከል ግን ጴጥሮስ በቫቲካን አካባቢ ሰማዕት እንደሆነ አጠቃላይ ስምምነት አለ” ይላሉ ዲ ደብልዩ ኦክኖር የተባሉት የታሪክ ጸሐፊ። እንግዲያው በቫቲካን ውስጥ የጴጥሮስን መቃብር ለማግኘት የተደረገው ፍለጋ አስተማማኝ ባልሆነ ወግ ላይ የተመሠረተ ነው። ኦክኖር “ለቅርሳ ቅርሶች ትልቅ ግምት እየተሰጠ ሲመጣ ክርስቲያኖች የጴጥሮስ [መታሰቢያ] መቃብሩ ያለበትን ትክክለኛ ቦታ ይጠቁማል ብለው ማመን ጀመሩ” ሲሉ ገልጸዋል።
ይህ ወግ ቅዱስ ጽሑፋዊ ካልሆነው የቅርሳ ቅርስ አምልኮ ጋር ጎን ለጎን እያደገ የመጣ ነው። ከሦስተኛውና ከአራተኛው መቶ ዘመን በኋላ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች “መንፈሳዊ” የበላይነት ለማግኘትና የራሳቸውን ሥልጣን ከፍ ለማድረግ ሲታገሉ ትክክለኛ የሆኑትንም ሆነ የሐሰት ቅርሳ ቅርሶችን ለአምልኮ ሲጠቀሙባቸው ቆይተዋል። ይህንንም ሲያደርጉ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አግኝተዋል። ስለሆነም የጴጥሮስ አፅም ተአምራታዊ ኃይል አለው ብለው የሚያምኑ ምዕመናን የእሱ መቃብር ይገኛል ወደሚባልበት ቦታ ይጎርፋሉ። በስድስተኛው መቶ ዘመን ማለቂያ ገደማ አማኞች በጥንቃቄ የተመዘነ ብትን ጨርቅ አምጥተው “መቃብሩ” ላይ ያስቀምጡ ነበር። አንድ በዚያ ዘመን የተጻፈ ታሪክ እንዲህ ይላል፦ “በአንክሮ የሚጸልየው ሰው እምነት ጽኑ ከሆነ ጨርቁ ከመቃብሩ ላይ በሚነሣበት ጊዜ መለኮታዊ ጸጋ የሞላበት ይሆንና ክብደቱ ከበፊቱ ይጨምራል።” ይህም በዚያን ጊዜ ምን ዓይነት እምነት እንደነበረ ይጠቁማል።
ላለፉት መቶ ዘመናት ሲነገሩ የቆዩት ይህን የመሳሰሉ አፈ ታሪኮችና መሠረተቢስ ወጎች ለቫቲካን ቤተ ክርስቲያን ገናናነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ይሁን እንጂ የተቃውሞ አስተያየቶች መነሣታቸውም አልቀረም። በ12ኛውና በ13ኛው መቶ ዘመን ዋልደንስስ የተባለ አንድ የክርስትና ሃይማኖት ክፍል ይህን ድርጊት ተገቢ አይደለም ሲል አውግዞት ነበር። እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ በመጠቀም ጴጥሮስ በፍጹም ሮም ውስጥ እንዳልነበረ ገልጿል። ከተወሰኑ መቶ ዘመናት በኋላም የፕሮቴስታንት ተሐድሶ ደጋፊዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ተከራከሩ። በ18ኛው መቶ ዘመን የታወቁ ፈላስፎች ወጉ ታሪካዊም ሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የሌለው መሆኑን ተረዱ። የካቶሊክም ሆኑ ሌሎች የታወቁ ምሁራን እስከ ዘመናችን ድረስ ተመሳሳይ አመለካከት እንደያዙ ቆይተዋል።
ጴጥሮስ የሞተው ሮም ውስጥ ነበርን?
ትሑት የገሊላ ዓሣ አስጋሪ የነበረው ጴጥሮስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በነበሩ ሽማግሌዎች ላይ የበላይ የመሆን ምንም ዓይነት ሐሳብ እንዳልነበረው የተረጋገጠ ነው። ከዚህ ይልቅ ራሱን ‘ከእነርሱ ጋር የሚያገለግል ሽማግሌ’ እንደሆነ አድርጎ ጠቅሷል። (1 ጴጥሮስ 5:1–6) የእሱ መቃብር ነው በሚባለው ቦታ የሚካሄደው ደማቅ ሥነ ሥርዓት ከጴጥሮስ የትሕትና ባሕርይ ጋር ይጋጫል። የቫቲካንን የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ የሚጎበኝ ማንኛውም ጎብኚ ይህንን ለማየት ይችላል።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሌሎች የክርስትና ሃይማኖቶች ላይ የበላይነትን ለማግኘት ጴጥሮስ ለተወሰነ ጊዜ በሮም ተቀምጦ ነበር በሚሉ ‘በቅርብ ጊዜ በተገኙና አጠራጣሪ’ በሆኑ ወጎች ለመጠቀም ትሞክራለች። የሚያስገርመው ግን ሌሎች የጥንት ወጎች ጴጥሮስ የተቀበረበት ቦታ የሚገኘው ቫቲካን ውስጥ ሳይሆን ሮም ውስጥ የሆነ ቦታ እንደሆነ ይገምታሉ። ይሁን እንጂ ስለ ጴጥሮስ ያልተበረዘ ያልተከለሰ መረጃ ምንጭ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው በሚገኙት እውነቶች ላይ ለምን አናተኩርም? ጴጥሮስ በኢየሩሳሌም ከሚገኘው የክርስቲያን ጉባኤ የአስተዳደር አካል የተሰጠውን መመሪያ በመታዘዝ ባቢሎንን ጨምሮ በጥንቱ ዓለም ምሥራቃዊ ክፍል ሥራውን እንዳከናወነ የአምላክ ቃል ግልጽ ያደርግልናል።—ገላትያ 2:1–9፤ 1 ጴጥሮስ 5:13፤ ከሥራ 8:14 ጋር አወዳድር።
በ56 እዘአ ገደማ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች ደብዳቤ ሲጽፍ የጴጥሮስን ስም ሳይጠቅስ ወደ 30 ለሚጠጉ የዚያ ጉባኤ አባላት ሰላምታ አቅርቧል። (ሮሜ 1:1, 7፤ 16:3–23) ከዚያም በ60 እና በ65 እዘአ መካከል ጳውሎስ ከሮም ስድስት ደብዳቤዎችን ጽፏል፤ ጴጥሮስ ግን አልተጠቀሰም። ይህም ጴጥሮስ እዚያ እንዳልነበረ የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው።a (ከ2 ጢሞቴዎስ 1:15–17 እና ከ4:11 ጋር አወዳድር) ጳውሎስ በሮም ያከናወነው ሥራ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ መጨረሻ ላይ ተገልጿል። ነገር ግን አሁንም ስለ ጴጥሮስ የተጠቀሰ ምንም ነገር የለም። (ሥራ 28:16, 30, 31) እንግዲያው መጀመሪያ በአእምሮ ውስጥ ከተቀረጹት አመለካከቶች በሙሉ ነፃ በመሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች ላይ የሚደረግ ሚዛናዊ ምርመራ ጴጥሮስ እንዲያውም በሮም አልሰበከም ወደሚለው መደምደሚያ ብቻ ነው ሊመራ የሚችለው።b
የጳጳሱ “የበላይነት” አስተማማኝ ባልሆኑ ወጎችና ተጣምመው በሚጠቀሱ ጥቅሶች ላይ የተመሠረተ ነው። የክርስትና መሠረት ጴጥሮስ ሳይሆን ኢየሱስ ነው። ጳውሎስ ‘ክርስቶስ የጉባኤ ራስ ነው’ ብሏል። (ኤፌሶን 2:20–22፤ 5:23) ይሖዋ እምነት ያላቸውን ሰዎች ሁሉ ለመባረክና ለማዳን የላከው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው።—ዮሐንስ 3:16፤ ሥራ 4:12፤ ሮሜ 15:29፤ በተጨማሪም 1 ጴጥሮስ 2:4–8ን ተመልከት።
እንግዲያው የጴጥሮስ መቃብር በዚያ ይገኛል ብለው ከልብ በማመን ‘የጴጥሮስን ተተኪ ለማግኘት’ ጉዞአቸውን ወደዚያ የሚያደርጉ ሁሉ ‘አስተማማኝ ያልሆኑ ወጎችን’ ከመቀበል ወይም እምነት የሚጣልበትን የአምላክ ቃል ከማመን የትኛውን እንደሚመርጡ ፈታኝ ሁኔታ ገጥሟቸዋል። ክርስቲያኖች እምነታቸው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ስለሚፈልጉ ‘የእምነታቸውን ፍጹም አድራጊ ኢየሱስንና’ እሱ የተወላቸውን ፍጹም ምሳሌ ‘በትኩረት ይመለከታሉ።’—ዕብራውያን 12:2፤ 1 ጴጥሮስ 2:21
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ከ60–61 እዘአ ገደማ ጳውሎስ ለኤፌሶን፣ ለፊልጵስዩስ፣ ለቆላስይስ፣ ለፊልሞናና ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤዎችን ጽፎ ነበር። በ65 እዘአ ደግሞ ሁለተኛ ደብዳቤውን ለጢሞቴዎስ ጻፈ።
b “ጴጥሮስ ሮም ተቀምጦ ያውቃልን?” የሚለው ጥያቄ በኅዳር 1, 1972 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ በገጽ 669–71 ላይ ተብራርቷል።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“የተደረገው የከርሰ ምድር ቁፋሮ ከአዲኪላው (ከመሥዋዕት ማቅረቢያው) ሥር መቃብር እንዳለ የሚጠቁም ምንም ፍንጭ አላስገኘም፤ እንዲያውም የቅዱስ ጴጥሮስ ሬሳ ጴጥሮስን ከገደሉት ሰዎች እጅ ተወስዶ በክርስቲያኖች እንደተቀበረ የሚያሳይ ምንም ማረጋገጫ ሊገኝ አይችልም። የተለመደው አሠራር የአንድ መጻተኛ (ፐርግሪነስ) እና በሕጉ መሠረት እንደ ተራ ወንጀለኛ ተደርጎ የሚታይ ሰው ሬሳ ወደ ታይበር ወንዝ ይጣል ነበር። . . . ከዚህም በላይ በጥንት ጊዜ እንደዚህ እንዳሁኑ አስከሬንን እንደ ቅርስ አድርጎ ጠብቆ የማቆየት ፍላጎት አልነበረም። የዓለም መጨረሻ ቀርቧል የሚለው እምነት እየጠፋ ሲመጣ ሰማዕታትን ማምለክ እየተስፋፋ መጣ። እንግዲያው የቅዱስ ጴጥሮስ ሬሳ ጴጥሮስን ከገደሉት ሰዎች እጅ ተወስዶ አልተቀበረም የሚለው አባባል በእርግጥ ሊሆን የሚችል ነገር ነው።”—በጃስሊን ቶይንቢ እና በጆን ዎርድ ፐርኪንስ የተዘጋጀው ዘ ሽራይን ኦቭ ሴንት ፒተር ኤንድ ዘ ቫቲካን ኤክስካቬሽን