በሰይጣንና በሥራዎቹ ላይ ድል መቀዳጀት
“እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል።”—ያዕቆብ 4:7
1. ‘የኃጥአን እጅ’ በዛሬው ጊዜ ያለውን የሰው ዘር የነካው እንዴት ነው?
ኢዮብ “ምድር በኃጥአን እጅ ተሰጥታለች” ሲል በትክክል ተናግሮ ነበር። (ኢዮብ 9:24) በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታይተው የማያውቁ እጅግ አደገኛ የሆኑ ጊዜያት ተደቅነውብናል። ለምን? ምክንያቱም ይህ ያለንበት ዘመን የሰይጣን አጋንንታዊ ምድራዊ አገዛዝ የ“መጨረሻው ቀን” ስለሆነ ነው። በሰይጣን ገፋፊነት ‘ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ መሄዳቸው’ ምንም አያስደንቅም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 13) ከዚህም በላይ ስደት፣ ግፍ፣ የጭካኔ ድርጊቶች፣ ወንጀሎች፣ የኢኮኖሚ ችግሮች፣ ሥር የሰደዱ በሽታዎች፣ እርጅና የሚያመጣው ሥቃይ፣ የመንፈስ ጭንቀትና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ነገሮች ምሬት እንዲሰማን አድርገውን ሊሆን ይችላል።
2. በዛሬው ጊዜ የሰይጣንን ጥቃቶች መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
2 ቀንደኛው ባላጋራ ሰይጣን ዲያብሎስ በሰው ዘር ላይ በተለይ ደግሞ በእውነተኛ አምላኪዎች ላይ በቀጥታ ያነጣጠረ ጥቃት እየሰነዘረ ነው። ዓላማው ንጹሕ አቋማቸውን ሳያጎድፉ ለመኖር የሚጥሩትን ሁሉ ከአምላክ ዞር በማድረግ ከእሱና ከአጋንንት መላእክት ጋር ወደ ጥፋት አዘቅት እንዲወድቁ ማድረግ ነው። ይሁን እንጂ ንጹሕ አቋማችንን ሳናጎድፍ ከጸናን ዲያብሎስ ከእኛ እንደሚሸሽ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል። ልክ እንደ ኢየሱስ መከራ በምንቀበልባቸው ነገሮች አማካኝነት ለአምላክ ‘መታዘዝን መማር’ እንችላለን፤ እንዲሁም ይገባናል በማንለው ደግነቱ የዘላለም ሕይወትን ማግኘት እንችላለን።—ዕብራውያን 5:7, 8፤ ያዕቆብ 4:7፤ 1 ጴጥሮስ 5:8–10
3, 4. (ሀ) ጳውሎስ የትኞቹን ከውጪ የሚመጡ ፈተናዎች መቋቋም አስፈልጎት ነበር? (ለ) እንደ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ መጠን ጳውሎስ ያሳስበው የነበረው ነገር ምን ነበር?
3 ሐዋርያው ጳውሎስም በብዙ መንገዶች ተፈትኗል። የክርስቶስ አገልጋይ ለመባል የሚያበቁትን ነገሮች ሲገልጽ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እኔ እበልጣለሁ፤ በድካም አብዝቼ፣ በመገረፍ አብዝቼ፣ በመታሰር አትርፌ፣ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ። አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ። ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ። ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ በወንዝ ፍርሃት፣ በወንበዴዎች ፍርሃት፣ በወገኔ በኩል ፍርሃት፣ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፣ በከተማ ፍርሃት፣ በምድረ በዳ ፍርሃት፣ በባሕር ፍርሃት፣ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፤ በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፣ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፣ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ።”
4 “የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፣ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው። የሚደክም ማን ነው፣ እኔም አልደክምምን? የሚሰናከል ማን ነው፣ እኔም አልናደድምን?” (2 ቆሮንቶስ 11:23–29) በዚህ መንገድ ጳውሎስ ከውጪ ስደቶችና ፈተናዎች ሲያጋጥሙት ንጹሕ አቋሙን በማበላሸት አምላክን አልተወም፤ እንዲሁም እንደ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ መጠን በጉባኤው ውስጥ ያሉት ደካማ ወንድሞችና እህቶች ንጹሕ አቋማቸውን ሳያበላሹ ከአምላክ ጋር እንዲጣበቁ በመርዳት እነርሱን የማጠንከሩ ሥራ እጅግ ያሳስበው ነበር። በዛሬው ጊዜ ላሉት ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!
በስደት ጊዜ ንጹሕ አቋምን አለማጉደፍ
5. ለቀጥተኛ ስደት መፍትሔው ምንድን ነው?
5 ሰይጣን ንጹሕ አቋማችንን ለማጉደፍ የሚጠቀምባቸው ዘዴዎች ምንድን ናቸው? ከላይ እንደተጠቆመው ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው እጅግ የከፉ ስልቶች አንዱ ቀጥተኛ ስደት ነው፤ ይሁን እንጂ ለዚህ መልስ አለ። ኤፌሶን 6:10, 11 “በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ። የዲያብሎስን ሽንገላ [ወይም “የተንኮል ድርጊቶች” የአዓት የግርጌ ማስታወሻ] ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ” ሲል ይመክረናል።
6. የይሖዋ ምሥክሮች ከፈተና ‘አሸናፊዎች’ ሆነው እንደወጡ ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው?
6 በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የይሖዋ ምሥክሮች ፈተናዎችን በተደጋጋሚ ጊዜያት መቋቋም አስፈልጓቸዋል። በመሆኑም ከጳውሎስ ጋር “በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን” ማለት እንችላለን። (ሮሜ 8:37) ከ1933 እስከ 1945 በነበረው የናዚ ዘመን በጀርመን፣ በኦስትሪያ፣ በፖላንድና በዩጎዝላቪያ ማጎሪያ ካምፖች፣ በ1945ና በ1989 መካከል በነበሩት ዓመታት በምሥራቅ አውሮፓ በኮሙኒስት ጭቆና ሥርና የአፍሪካንና የላቲን አሜሪካን ክፍሎች በነካው እስከ ቅርብ ጊዜያት በነበረው የስደት ዘመን የይሖዋ ምሥክሮች ንጹሕ አቋማቸውን ሳያጎድፉ እንደኖሩ የሚመሰክረው መዝገብ ይህን ያረጋግጣል።
7. ንጹሕ አቋምን ባለማጉደፍ ረገድ ከኢትዮጵያ ሪፖርት የተደረጉት ስሜት ቀስቃሽ ምሳሌዎች ምንድን ናቸው?
7 በኢትዮጵያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ከ1974 እስከ 1991 በነበሩት ዓመታት ንጹሕ አቋምን ሳያጎድፉ ከአምላክ ጋር ተጣብቆ የመኖር ቀስቃሽ ምሳሌ አሳይተዋል። ወንድሞችን ካሰሩት ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ከነበራቸው ሰዎች አንዱ ለአንድ የታሰረ ወንድም “እንደገና እናንተን ነፃ ከመልቀቅ ስድስት ኪሎ ያሉትን አንበሶች መልቀቅ ይሻላል!” ብሎት ነበር። እነዚህ ጨካኝ አሳዳጆች የይሖዋን አገልጋዮች አሠቃዩአቸው፤ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላም ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሞት ፍርድ በየነባቸው። ማስጠንቀቂያ እንዲሆን የአንድ ወንድም አስከሬን ለሕዝብ እንዲታይ ተደረገ። የተፈረደባቸው የሞት ፍርድ እንደገና እንዲታይላቸው ይግባኝ የጠየቁት ሌሎች ወንድሞች ይበልጥ ለዘብተኛ በሆነ ፍርድ ቤት እንዲለቀቁ ተደርጓል። ከእነዚህ ታማኝ ‘አሸናፊዎች’ መካከል አንዳንዶቹ በ1994 መጀመሪያ ላይ በአዲስ አበባ በተካሄደው “መለኮታዊ ትምህርት” የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም ላይ ክፍል አቅርበዋል።a—ዮሐንስ 16:33፤ ከ1 ቆሮንቶስ 4:9 ጋር አወዳድር።
8. ሰይጣን “ጎሣዊ ምንጠራ” የሚባለውን ነገር እንደ መሣሪያ አድርጎ ለመጠቀም የሞከረው እንዴት ነው?
8 ሰይጣን የእንዲህ ዓይነቶቹን ታማኝነታቸውን ጠብቀው የቆሙ ወንድሞችንና እህቶችን ንጹሕ አቋም ቀጥተኛ በሆነ የግንባር ጥቃት ሊያጎድፈው አልቻለም። ታዲያ ሰይጣን የሚጠቀምባቸው ሌሎች የተንኮል ዘዴዎች ምንድን ናቸው? ራእይ 12:12 ስለ እነዚህ የመጨረሻ ቀናት እንዲህ ይላል፦ “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።” በአምላክ ጎን በታማኝነት የቆመውን ሕዝብ መደምሰስ ስላቃተው በብሽቀት ጠቅላላውን ኅብረተሰብ በጅምላ ለመፍጀት ይሞክራል። ይህንንም የሚያደርገው የይሖዋን ሕዝብ ከቀረው ኅብረተሰብ ጋር ቀላቅሎ ለማጥፋት አልሞ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። በመሆኑም በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ክፍሎች የዘር ምንጠራ የተባለ ዘመቻ ሲካሄድ ቆይቷል። በላይቤሪያ፣ በብሩንዲና በሩዋንዳ አንድን ጎሣ ጨርሶ ለማጥፋት የተቃጣ የመጨፍጨፍ ዘመቻ ተሞክሯል።
9. ብዙውን ጊዜ የሰይጣን ዘዴዎች የማይሠምሩት ለምንድን ነው? ምሳሌዎች ስጥ።
9 ይሁን እንጂ ሰይጣን የሚያመጣው ሥቃይ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ብቸኛ ተስፋቸው የይሖዋ ምሥክሮች በቅንዓት በሚያውጁዋት የአምላክ መንግሥት ላይ የተመካ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ስለሚያደርጋቸው ብዙውን ጊዜ የሰይጣን ዘዴዎች መልሰው ራሱኑ ይመቱታል። (ማቴዎስ 12:21) በእርግጥም ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ወደ መንግሥቲቱ እየጎረፉ ነው! ለምሳሌ ያህል በጦርነት በተበታተኑት በቦስኒያና በሄርዞጎቪና መጋቢት 26, 1994 በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ካለፈው ዓመት የተሰብሳቢዎች ቁጥር በ291 ብልጫ ያላቸው 1,307 ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል። በሳራዬቮ (414)፣ በዜኔትሳ (223)፣ በቱዝላ (339)፣ በባንያ ሉካ (255) እና በሌሎች ከተማዎች ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ተመዝግበዋል። በአጎራባች በምትገኘው በክሮኤሽያ 8,326 የደረሰ አዲስ ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ነበር። በእነዚህ አገሮች የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በአካባቢያቸው እየተካሄደ ያለው ዓመፅ ‘ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ተናገሩ’ የሚለውን ትእዛዝ እንዳያከብሩ አላደረጋቸውም።—1 ቆሮንቶስ 11:26
የጦርነት እሳት በለበለባት በሩዋንዳ
10, 11. (ሀ) የክርስቲያን አገር ተብላ በምትጠራው በሩዋንዳ ምን ተፈጽሟል? (ለ) ታማኝነታቸውን የጠበቁ ሚስዮናውያን ምን አሉ?
10 ሩዋንዳ በ1993 የነበሯት የመንግሥቱ አስፋፊዎች 2,080 ነበሩ፤ በ“መለኮታዊ ትምህርት” የወረዳ ስብሰባ ላይም 4,075 ተሰብሳቢዎች ሲገኙ 230 ተጠምቀዋል። ከእነዚህ መካከል 142ቱ ወዲያውኑ የረዳት አቅኚነት አገልግሎት ቅጽ ሞልተዋል። በ1994 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ 7,655 ሆኖ ነበር፤ በዚህ ደግሞ ሰይጣን እንደማይደሰት ግልጽ ነው! ምንም እንኳ ከሕዝቡ መካከል አብዛኛው ክርስቲያን ነኝ የሚል ቢሆንም በጎሣዎች መካከል የሚደረግ የእርስ በእርስ ፍጅት ተቀሰቀሰ። የቫቲካኑ ሎሰርቫቶሬ ሮማኖ እንደሚከተለው ለማለት ተገዷል፦ “ይህ እልም ያለ ጭፍጨፋ ነው፤ የሚያሳዝነው ደግሞ ካቶሊኮች እንኳ ሳይቀሩ ለዚህ ተጠያቂ መሆናቸው ነው።” በግምት ግማሽ ሚልዮን የሚሆኑ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች እንደ ቅጠል ረግፈዋል፤ ወደ ሁለት ሚልዮን የሚጠጉ ደግሞ ቤት አልባ ሆነዋል ወይም ተፈናቅለዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ሰላማዊ የሆነ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸውን በመጠበቅ አንድ ላይ ለመኖር ጥረት አድርገዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ተገድለዋል። ይሁን እንጂ 65 የመንግሥቱ አስፋፊዎች ባሉበትና 13ቱ በተገደሉበት አንድ ጉባኤ በነሐሴ 1994 የተሰብሳቢዎች ቁጥር ወደ 170 አድጓል። በመጀመሪያ በቦታው ከደረሱት የእርዳታ ዕቃዎች መካከል በሌሎች አገሮች ካሉ ምሥክሮች የተላኩት የእርዳታ ዕቃዎች ይገኙበታል። በሕይወት ለተረፉት ጸሎታችንን እያሰማን ነው።—ሮሜ 12:12፤ 2 ተሰሎንቄ 3:1, 2፤ ዕብራውያን 10:23–25
11 በዚያ ሁሉ ሽብር መሀል በሩዋንዳ የነበሩት ሦስቱ ሚስዮናውያን አምልጠዋል። እንዲህ ሲሉ ጻፉ፦ “በዓለም ዙሪያ የሚገኙት ወንድሞቻችን ተመሳሳይ ሁኔታዎችን ወይም ከዚህም የከፉ ሁኔታዎችን እንዳሳለፉ ተገንዝበናል። ይህም የዚህ ክፉ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ምልክት ክፍል እንደሆነ እናውቃለን። በራስ ላይ ሲደርስ ግን የነገሮችን እውነታና ሕይወት ምን ያህል ውድ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። አንዳንድ ጥቅሶች ለኛ አዲስ ትርጉም ያላቸው ሆነው አግኝተናቸዋል። የቀደሙት ነገሮች ዳግመኛ የማይታወሱበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። እስከዚያው ድረስ በይሖዋ አገልግሎት ተጠምደን መቀጠል እንፈልጋለን።”
ንጹሕ አቋማቸውን ያላጎደፉ ወጣቶች
12, 13. (ሀ) አንዲት ወጣት ንጹሕ አቋምን ባለማጉደፍ ረገድ ምን ዓይነት እርምጃ ወስዳለች? (ለ) በዛሬው ጊዜ ወጣቶቻችን ከየት ማበረታቻ ማግኘት ይችላሉ?
12 ኢየሱስ በእውነት የተነሣ የቤተሰብ አባሎቻቸው ያገለሏቸው ሰዎች “መቶ እጥፍ” ወሮታ እንደሚከፈላቸው አመልክቷል። (ማርቆስ 10:29, 30) ይህ ሁኔታ ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም እንደ ሰማች ለስሙ ከፍተኛ ፍቅር ባደረባት አንዲት በሰሜን አፍሪካ የምትገኝ ኢንቴልያ የምትባል የአሥር ዓመት ልጃገረድ ላይ ደርሷል። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ታጠና ነበር። ምንም እንኳ ብዙውን ጊዜ ወደ ቤቷ ስትመለስ የሚቃወሟት ቤተሰቦቿ እንዳትገባ በር ይዘጉባት የነበረ ቢሆንም በስብሰባዎች ላይ ተገኝታ ለመመለስ 90 ደቂቃ በእግሯ ትጓዝ ነበር። በ13 ዓመቷ ከቤት ወደ ቤት እየሄደች መስበክ ጀመረች። በዚህ ጊዜ የቤተሰቧ ተቃውሞ ይበልጥ ጠነከረ። አንድ ቀን ዘመዶቿ እጆቿንና እግሮቿን አስረው በሚያቃጥል ፀሐይ ላይ ለሰባት ሰዓታት እንድትተኛ አደረጓት። አልፎ አልፎም ቆሻሻ ውኃ ላይዋ ላይ ይደፉባት ነበር። ክፉኛ ደብድበው አንድ ዓይኗን ካጠፉ በኋላ ከቤት አባረሯት። ይሁን እንጂ በአንድ ሆስፒታል ሥራ አገኘችና ከጊዜ በኋላ ነርስ ለመሆን በቃች። በ20 ዓመቷ ተጠመቀችና ወዲያውኑ ረዳት አቅኚ ሆነች። አቋሟን ሳትለውጥ ጸንታ በመቆሟ ቤተሰቦቿ እጅግ በመደነቅ እንደገና ወደ ቤት እንድትመለስ ጥሪ አቀረቡላት። ከእነርሱም መካከል ዘጠኙ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀምረዋል።
13 ኢንቴልያ ከመዝሙር 116 በተለይ ደግሞ ደጋግማ በምታነባቸው ከ1–4 ባሉት ቁጥሮች ይህ ነው የማይባል ማበረታቻ አግኝታለች፦ “እግዚአብሔር የልመናዬን ድምፅ ሰምቶአልና ወደድሁት። ጆሮውን ወደ እኔ አዘንብሎአልና በዘመኔ ሁሉ እጠራዋለሁ። የሞት ጣር ያዘኝ፣ የሲኦልም ሕማም አገኘኝ፤ ጭንቀትንና መከራን አገኘሁ። የእግዚአብሔርንም ስም ጠራሁ፦ አቤቱ፣ ነፍሴን አድናት።” ይሖዋ ለእንዲህ ዓይነት ጸሎቶች መልስ ይሰጣል!
14. ፖላንዳውያን ምሥክሮች ጎልቶ የሚታይ ንጹሕ አቋም ያሳዩት እንዴት ነው?
14 ልክ በኢየሱስ ዘመን እንዳደረገው ሰይጣን ብዙውን ጊዜ የስደትን እሳት ለማቀጣጠል ሃይማኖታዊ አክራሪነትን መሣሪያው አድርጎ ይጠቀማል፤ ሆኖም አልተሳካለትም። በ1994 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው የፖላንድ ወንድሞች ሁኔታ እዚህ ላይ ሊጠቀስ የሚችል ጎላ ያለ አብነት ነው። ሌላው ቀርቶ ወጣቶች እንኳ ንጹሕ አቋማቸውን የማያጎድፉ መሆናቸውን ማስመስከር አስፈልጓቸው ነበር። በ1946 ከእነዚህ መካከል አንዷ “እንደ ካቶሊኮች አማትቢ። አለበለዚያ ጥይት ይጠብቅሻል!” የሚል ዛቻ የደረሰባት የ15 ዓመት ልጃገረድ ነበረች። ንጹሕ አቋሟን አጥብቃ በመያዟ ወደ አንድ ጫካ ተወሰደች፤ በሚዘገንን ሁኔታ አሠቃዩአትና ተኩሰው ገደሏት።—ከማቴዎስ 4:9, 10 ጋር አወ ዳድር።
ሰይጣን የሚጠቀምባቸው ሌሎች የተንኮል ዘዴዎች
15, 16. (ሀ) የሰይጣን አጋንንታዊ መርሆ ምንድን ነው? ሰይጣንን ልንከላከለው የምንችለውስ እንዴት ነው? (ለ) ወጣቶቻችን የሚደናቀፉበት ምንም ምክንያት የሌለው ለምንድን ነው?
15 በእርግጥም የሰይጣን አጋንንታዊ መርሆ “አጥፍተህ ጥፋ” የሚል ነው! ብዙ የጭካኔ መሣሪያዎች በእጁ ይገኛሉ። እንግዲያው ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ማስጠንቀቁ አያስደንቅም፦ “መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፣ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ። ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፣ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ።” (ኤፌሶን 6:12, 13) ፍቅረ ነዋይ፣ ርካሽ የሆነ መዝናኛና ፕሮፓጋንዳ፣ ሰይጣናዊ ሙዚቃ፣ በትምህርት ቤት የሚያጋጥም የእኩዮች ተጽዕኖ፣ አደንዛዥ መድኃኒቶችን አላግባብ መጠቀምና ስካር፤ ከእነዚህ ነገሮች የትኛውም ቢሆን ሕይወታችንን ሊያበላሸው ይችላል። በመሆኑም ሐዋርያው ምክሩን በመቀጠል “በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ” ብሏል።—ኤፌሶን 6:16
16 ሰይጣን ይህን ዓለም ለማጥለቅለቅ እየተጠቀመበት ካለው በጣም እንግዳ የሆነ ሙዚቃ አንጻር ስንመለከተው ይህ በዛሬው ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ ሆኖ እናገኘዋለን። አንዳንድ ጊዜ ከሰይጣናዊ እምነት ጋር ቀጥተኛ ዝምድና አለው። በሳን ዲያጎ (ዩ ኤስ ኤ) ግዛት ከሚገኘው የሕግ አስከባሪ ቢሮ የወጣው አንድ ሪፖርት እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “‘ንጣይሰ’ (Natas) እያሉ አንድ ላይ የሚጮኹ 15,000 ልጆችን ያቀፈ አንድ የሙዚቃ ጓድ የሚያሳየው የሙዚቃ ትርኢት በከተማችን ውስጥ ይገኛል። ይህም ሰይጣን (Satan) የሚለው ቃል ፊደላት ከቀኝ ወደ ግራ ሲነበቡ ነው።” ወጣቶች “ተስፋ ቆርጠው፣ ተበሳጭተውና ብቸኛ ሆነው እየተቅበዘበዙ ስለሆነ” ሰይጣናዊ እምነት ወጣቶች እየተደናቀፉ የሚወድቁበት ጉድጓድ ነው ተብሎ ተገልጿል። እናንተ በክርስቲያን ጉባኤ የምትገኙ ወጣቶች የምትደናቀፉበት ምንም ምክንያት የለም! ይሖዋ የሰይጣን ፍላጻዎች ፈጽሞ ሊበሱ በማይችሉት የብረት ጋሻ ይጋርዳችኋል።—መዝሙር 16:8, 9
17. የመንፈስ ጭንቀትን እንዴት መቋቋም ይቻላል?
17 የሰይጣን የሚንበለበሉ ፍላጻዎች በስሜቶቻችን ላይ ያነጣጠሩ ናቸው። አካላዊ ሕመምን ወይም ከባድ የመንፈስ ጭንቀትን በመሰሉ የኑሮ ግፊቶች አማካኝነት ባላጋራችን አንዳንዶች ምንም ዋጋ እንደሌላቸው ሆኖ እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል። አንድ ሰው በአምላክ አገልግሎት ብዙ ሰዓት ማሳለፍ ስላልቻለ ወይም አንዳንድ የጉባኤ ስብሰባዎች ስለሚያመልጡት ተስፋ ሊቆርጥ ይችላል። ሽማግሌዎችና ሌሎች ደግና እፍቃሪ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች የሚያደርጉት ፍቅራዊ እንክብካቤ አስቸጋሪ የስሜት ቀውሶችን ለመቋቋም ሊረዳ ይችላል። ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን እንደሚወዳቸው ምን ጊዜም አስታውስ። (1 ዮሐንስ 4:16, 19) መዝሙር 55:22 “ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም” ሲል ይገልጻል።
18. አንዳንዶች ከየትኞቹ የሰይጣን ሽንገላዎች ጋር መታገል አስፈልጓቸዋል?
18 የሰይጣን የተንኮል “ሽንገላ” በቅርቡ ደግሞ ሌላ መልክ ይዞ ብቅ ብሏል። በአንዳንድ አገሮች ብዙ ጎልማሶች ልጅ በነበርኩበት ጊዜ በሰይጣናዊ አምልኮ ጭካኔ የተሞላበት የጾታ ብልግና ተፈጽሞብኛል ብለው እንዲረበሹ የሚያደርግ የሚሰቀጥጥ ሐሳብ መጥቶባቸዋል። እነዚህ ሐሳቦች ከየት የመጡ ናቸው? በዓለማውያን ባለሞያዎች ዘንድ ሰፊ ምርምር ቢካሄድም እንኳ የሚሰነዘሩት አመለካከቶች በእጅጉ ይለያያሉ። አንዳንዶች እንዲህ ዓይነቶቹን ሐሳቦች እውነተኛ ትዝታዎች አድርገው ይመለከቷቸዋል፤ ሌሎች እንደ ቅዠቶች አድርገው ይመለከቷቸዋል፤ ምናልባትም አጠያያቂ የሆኑ የአእምሮ ሕክምናዎች የሚፈጥሯቸው ቅዠቶች ሳይሆኑ አይቀሩም ይላሉ፤ ሌሎች ደግሞ በልጅነት ተከስቶ በነበረ አንድ ዓይነት የስሜት ቀውስ ሳቢያ የመጣ እውነትነት ወይም መሠረት የሌላቸውን ነገሮች በሐሳብ የማየትና የመስማት ሁኔታ ነው ብለው ያስባሉ።
19. (ሀ) ኢዮብ የትኞቹን ሐሳቦች መታገል አስፈልጎት ነበር? (ለ) ሽማግሌዎች የኤሊሁን ምሳሌ ሊከተሉ የሚችሉት እንዴት ነው?
19 የአምላክ አገልጋይ የነበረው ኢዮብ ሰይጣን በኤልፋዝና በሶፋር በኩል የሚያሳየውን ‘የሚያስጨንቅ ቅዠት’ መቋቋም አስፈልጎት እንደነበረ ማወቁ ትኩረትን የሚስብ ነገር ነው። (ኢዮብ 4:13–18፤ 20:2, 3 የ1980 ትርጉም) ኢዮብ አእምሮውን ስለነካው “የሚያስደነግጥ” ነገር ‘ትዕግሥት የጎደለው ንግግር’ በመናገሩ ‘በሐዘን’ ተሠቃይቷል። (ኢዮብ 6:2–4፤ 30:15, 16 የ1980 ትርጉም) ኤሊሁ ኢዮብን ጸጥ ብሎ አዳመጠውና ይሖዋ ስለ ነገሮች ያለውን ሁሉንም ነገር ግምት ውስጥ የሚያስገባ አመለካከት እንዲያስተውል ከልቡ ረዳው። ዛሬም በተመሳሳይ የሰውን ችግር የሚረዱ ሽማግሌዎች ተጨማሪ ‘ሸክም’ ባለመጨመር በሐሳብ ለሚሠቃዩ ሰዎች እንደሚያስቡ ያሳያሉ። ከዚህ ይልቅ ልክ እንደ ኤሊሁ በትዕግሥት ያዳምጧቸዋል፤ ከዚያም እፎይታ በሚሰጥ ዘይት ይኸውም በአምላክ ቃል ተጠቅመው ያረጋጓቸዋል። (ኢዮብ 33:1–3, 7፤ ያዕቆብ 5:13–15) ስለዚህ ስሜቱ እውነተኛ በሆነ ተሞክሮም ሆነ በቅዠት የስሜት ቀውስ የተረበሸ ወይም ደግሞ እንደ ኢዮብ ‘በሕልምና በቅዠት የተረበሸ’ ሰው ፈዋሽ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማጽናኛ በጉባኤው ውስጥ ማግኘት ይችላል።—ኢዮብ 7:14 የ1980 ትርጉም፤ ያዕቆብ 4:7
20. የመንፈስ ጭንቀት ያደረባቸው ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ሚዛናቸውን መጠበቅ እንዲችሉ መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው?
20 በአሁኑ ጊዜ አንድ ክርስቲያን ሰይጣን በዚህም ሆነ በዚያ ከእነዚህ አስፈሪ ሐሳቦች በስተጀርባ እንዳለ እርግጠኛ መሆን ይችላል። በጉባኤው ውስጥ ያሉ አንዳንዶች በዚህ መንገድ እየተሠቃዩ ከሆነ እንዲህ ዓይነቶቹን አእምሮ ውስጥ የሚፈጠሩ የሚያስፈሩ ስሜቶች ሰይጣን መንፈሳዊ ሚዛናቸውን እንዲስቱ ለማድረግ የሚያደርሰው ቀጥተኛ ሙከራ እንደሆነ አድርገው መመልከታቸው ጥበብ ነው። እነዚህ ሰዎች ትዕግሥት እያሳየና ችግራቸውን እየተረዳ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የሚሰጥ ሰው ያስፈልጋቸዋል። በጸሎት ወደ ይሖዋ ዞር በማለትና ከመንፈሳዊ እረኝነት በመጠቀም ጭንቀት ውስጥ የወደቁ ሰዎች ከወትሮው ላቅ ያለ ኃይል ማግኘት ይችላሉ። (ኢሳይያስ 32:2፤ 2 ቆሮንቶስ 4:7, 8 አዓት) በዚህ መንገድ በታማኝነት ለመጽናትና አስተሳሰብን የሚበክሉ ክፉ ሐሳቦች የጉባኤውን ሰላም እንዳያደፈርሱ ለመከላከል ይችላሉ። (ያዕቆብ 3:17, 18) አዎን፣ ኢየሱስ “ሂድ፣ አንተ ሰይጣን”! ባለ ጊዜ ያሳየውን ያንኑ መንፈስ በማሳየት ዲያብሎስን መቃወም ይችላሉ።—ማቴዎስ 4:10፤ ያዕቆብ 4:7
21. ቅዱሳን ጽሑፎች ከሰይጣን የተንኮል መንገዶች እንድንጠበቅ የሚያስጠነቅቁን እንዴት ነው?
21 ሐዋርያው ጳውሎስ በ2 ቆሮንቶስ 11:3 ላይ እንዳስጠነቀቀው የሰይጣን ዓላማ በሆነ መንገድ አእምሮአችንን ለመበከል እንደሆነ እናውቃለን፦ “እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፣ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ።” በአሁኑ ጊዜ ያለው የሥጋ ሁሉ ወይም ከአምላክ የራቀው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ የሚታይበት ብልሽት በኖኅ ዘመን የነበሩት ብልሹዎቹና ዓመጸኞቹ “እያነሱ የሚያፈርጡ” ዲቃላዎች ያራምዱት የነበረውን ወራዳ ተግባር ያስታውሰናል። (ዘፍጥረት 6:4, 12, 13 የአዓት የግርጌ ማስታወሻ፤ ሉቃስ 17:26) እንግዲያው ሰይጣን በተለይ በአምላክ ሕዝብ ላይ ብሽቀቱን ለመወጣት ቀድሞ ይጠቀምባቸው ወደነበሩት የተንኮል ድርጊቶችና አታላይ ዘዴዎች መመለሱ አያስደንቅም።—1 ጴጥሮስ 5:8፤ ራእይ 12:17
22. ሰይጣን ከተወገደ በኋላ ምን በረከቶችን መጠበቅ ይቻላል?
22 በመጽሐፍ ቅዱሱ የኢዮብ መጽሐፍ የመደምደሚያ ምዕራፎች ላይ ሰይጣን ጭራሹኑ አልተጠቀሰም። የሰው ልጆች ከአምላክ ጋር በመጣበቅ ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው መቀጠል አይችሉም በማለት ያስነሳው ክፉ ግድድሩ ሐሰት መሆኑ በኢዮብ ንጹሕ አቋም ተረጋግጧል። በተመሳሳይም በቅርቡ ንጹሕ አቋማቸውን ያላጎደፉ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ‘ታላቁን መከራ ሲያልፉ’ ሰይጣን ወደ ጥልቁ ይወረወራል። ታማኙን ኢዮብ ጨምሮ የእምነት ሰዎች የሆኑ ወንዶችና ሴቶች ኢዮብ ካገኘው ወሮታም ይበልጥ ታላቅ የሆኑ ገነታዊ በረከቶችን ለመቋደስ ከእነዚያ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ጋር ይቀላቀላሉ!—ራእይ 7:9–17፤ 20:1–3, 11–13፤ ኢዮብ 14:13
[የግርጌ ማስታወሻ]
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ ኢዮብ፣ ኢየሱስና ጳውሎስ ንጹሕ አቋምን ባለማጉደፍ ረገድ ምን ግሩም ምሳሌዎችን ትተዋል?
◻ ንጹሕ አቋሟቸውን ሳያጎድፉ የሚመላለሱ ሰዎች ሰይጣንን የተቋቋሙት እንዴት ነው?
◻ ወጣቶች የሰይጣንን የተንኮል ዘዴዎች መከላከል የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ የሰይጣንን ሽንገላዎች ለመቋቋም ምን ማድረግ ይቻላል?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ መስዋዕትና ዮዓዳን የተገደለውን አባታቸውን ምሳሌ በመከተል ይሖዋን ሙሉ ጊዜ ያገለግላሉ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢንቴልያ፣ በሰሜን አፍሪካ ውስጥ የምትገኝ ንጹሕ አቋሟን ጠብቃ የምትኖር ወጣት