“ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ”
ኢየሱስ ክርስቶስ ከ19 መቶ ዘመናት በፊት እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ጎጂ ከሆኑ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችና ልማዶች እንዲጠበቁ ማስጠንቀቁ ነበር። (ማቴዎስ 16:6, 12) በማርቆስ 8:15 ላይ ያለው ዘገባ “ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” በማለት ቁልጭ አድርጎ ይገልጻል። ሄሮድስ የተጠቀሰው ለምንድን ነው? ከሰዱቃውያን መካከል አንዳንዶቹ የሄሮድስ ተከታዮች የሆኑ አንድ የፖለቲካ ቡድን ስለነበሩ ነው።
እንዲህ ዓይነቱ ልዩ ማስጠንቀቂያ አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው? ፈሪሳውያንም ሆኑ ሰዱቃውያን የኢየሱስ ቀንደኛ ተቃዋሚዎች አልነበሩምን? (ማቴዎስ 16:21፤ ዮሐንስ 11:45–50) አዎን፣ ነበሩ። ሆኖም ከእነርሱ መካከል አንዳንዶቹ ከጊዜ በኋላ ክርስትናን ተቀብለዋል፤ ከዚያም የራሳቸው ሐሳቦች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ተቀባይነት እንዲያገኙ ለማድረግ ሞክረዋል።—ሥራ 15:5
በተጨማሪም ደቀ መዛሙርቱ ራሳቸው ከልጅነት እስከ እውቀት በእነዚህ ሃይማኖታዊ መሪዎች ተጽእኖ ሥር ያደጉ ስለነበሩ እነርሱን ሊመስሉ የሚችሉበት አደገኛ ሁኔታ ነበር። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥረ መሠረት ያላቸው መሆኑ ብቻ የኢየሱስን ትምህርቶች ትርጉም መረዳት እንዳይችሉ እንቅፋት ይሆንባቸው ነበር።
የፈሪሳውያንንና የሰዱቃውያንን ትምህርቶች እጅግ አደገኛ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ነገር ምንድን ነው? በኢየሱስ ዘመን የነበሩትን ሃይማኖታዊ ሁኔታዎች ለአጭር ጊዜ መመልከቱ ፍንጭ ይሰ ጠናል።
ሃይማኖታዊ ክፍፍል
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የነበረውን የአይሁድ ማኅበረሰብ በተመለከተ ታሪክ ጸሐፊው ማክስ ራዲን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የአይሁድ ጉባኤዎች እያንዳንዳቸው በራሳቸው የሚመሩ ነበሩ፤ እንዲያውም ይህ መሆን ያለበት ነገር ነው ይባል ነበር። . . . ብዙውን ጊዜ ለቤተ መቅደሱና ለቅድስቲቱ ከተማ ከፍተኛ ክብር መስጠት እንደሚገባ ይበልጥ ጠበቅ ተደርጎ ሲገለጽ በወቅቱ እናት አገራቸውን እየገዙ የነበሩትን ሰዎች አቃልለው ሊሆን ይችላል።”
በእርግጥም አሳዛኝ መንፈሳዊ ሁኔታ ነበር! ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረጉት አንዳንድ ነገሮች ምን ነበሩ? ሁሉም አይሁዶች ይኖሩ የነበሩት በፍልስጤም ምድር አልነበረም። ካህናት የማኅበረሰቡ መሪዎች ተደርገው የማይታዩበት የግሪክ ባህል ያሳደረው ተጽእኖ ይሖዋ ለክህነት አገልግሎት ላወጣው ሥርዓት ይሰጥ የነበረውን አክብሮት ለማዳከም የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። (ዘጸአት 28:29፤ 40:12–15) የተማሩት ምዕመናንና ጻፎችም ሳይጠቀሱ የሚታለፉ አይ ደሉም።
ፈሪሳውያን
ፈሪሳውያን ወይም ፔሩሺም የሚለው ስም “ራሳቸውን የለዩ” ማለት ሳይሆን አይቀርም። ፈሪሳውያን ራሳቸውን የሙሴ ተከታዮች አድርገው ይቆጥሩ ነበር። የራሳቸው ማኅበር (በዕብራይስጥ ቻቩራህ) አቋቁመው ነበር። አንድ ሰው አባል ሆኖ ተቀባይነት እንዲያገኝ በሦስት አባላት ፊት የሌዋውያንን የመንጻት ሥርዓት ውልፍት ሳይል ለመጠበቅ፣ ከአምሃሬትስ (ካልተማረው ብዙሃን) ጋር የቅርብ ግንኙነት ላለማድረግና አሥራቱን በሚገባ ለመክፈል ቃል ይገባል። ማርቆስ 2:16 ‘ስለ ፈሪሳውያን ጻፎች’ ይናገራል። ከፈሪሳውያን መካከል አንዳንዶቹ የተዋጣላቸው ጻፎችና አስተማሪዎች ነበሩ፤ ሌሎቹ ግን ተራ ምዕመናን ነበሩ።—ማቴዎስ 23:1–7
ፈሪሳውያን አምላክ በማንኛውም ቦታ ይገኛል ብለው ያምኑ ነበር። “አምላክ በየትም ቦታ የሚገኝ ስለሆነ በቤተ መቅደሱ ውስጥም ሆነ ከቤተ መቅደሱ ውጪ ሊመለክ ይችላል፤ እንዲሁም አምላክን መማጸን የሚቻለው በመሥዋዕቶች ብቻ አይደለም” ብለው ያስረዱ ነበር። “በዚህ መንገድ ምኩራቦችን የአምልኮ፣ የማጥኛና የጸሎት ቦታዎች አደረጓቸው፤ እንዲሁም ምኩራብ በሰዎቹ ኑሮ ውስጥ ዋነኛና ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ከቤተ መቅደሱ እኩል የሚታይ ቦታ እንዲሆን አድርገዋል።”—ኢንሳይክሎፔድያ ጁዳይካ
ፈሪሳውያን ለይሖዋ ቤተ መቅደስ አድናቆት ጎድሏቸው ነበር። ይህን ከሚከተሉት የኢየሱስ ቃላት መረዳት ይቻላል፦ “እናንተ፦ ማንም በቤተ መቅደስ የሚምል ምንም የለበትም ማንም በቤተ መቅደስ ወርቅ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል የምትሉ፣ ዕውሮች መሪዎች፣ ወዮላችሁ። እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፣ ማናቸው ይበልጣል? ወርቁ ነውን? ወይስ ወርቁን የቀደሰው ቤተ መቅደስ? ደግማችሁም፦ ማንም በመሠዊያው የሚምል ምንም የለበትም ማንም በላዩ ባለው መባ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል ትላላችሁ። እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፣ ማናቸው ይበልጣል? መባው ነውን? ወይስ መባውን የሚቀድሰው መሠዊያው? እንግዲህ በመሠዊያው የሚምለው በእርሱና በእርሱ ላይ ባለው ሁሉ ይምላል።”—ማቴዎስ 23:16–20
ፈሪሳውያን አስተሳሰባቸው የተዛባ የነበረው ለምንድን ነው? ያላስተዋሏቸው ነገሮች ምን ነበሩ? ኢየሱስ ቀጥሎ የተናገረውን ልብ በል። “በቤተ መቅደስም የሚምለው በእርሱና በእርሱ በሚኖረው ይምላል።” (ማቴዎስ 23:21፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ይህን ጥቅስ በተመለከተ ኢ ፒ ሳንደርስ የተባሉ ምሁር የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥተዋል፦ “ቤተ መቅደሱ ቅዱስ የሆነው ቅዱሱ አምላክ የሚመለክበት ቦታ ስለሆነ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ቅዱሱ አምላክ የሚገኝበትም ቦታ ስለነበረ ነው።” (ጁዳይዝም፦ ፕራክቲስ ኤንድ ቢሊፍ፣ 63 ቢ ሲ ኢ—66 ሲ ኢ) ይሁን እንጂ ይሖዋ በማንኛውም ቦታ ይገኛል ብለው ያስቡ ለነበሩት ሰዎች የይሖዋ በተለየ ሁኔታ መገኘት ምንም ትርጉም አልነበረውም።
በተጨማሪም ፈሪሳውያን የሰው ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለው እምነትና ነፃ ምርጫ አብረው የሚሄዱ ነገሮች ናቸው ብለው ያምኑ ነበር። በሌላ አነጋገር “ማንኛውም ነገር አስቀድሞ የተወሰነ ነው፤ ሆኖም የምርጫ ነጻነት ተሰጥቷል” ማለት ነው። ይሁን እንጂ አዳምና ሔዋን ኃጢአት እንዲሠሩ አስቀድሞ ተወስኖ ነበር፤ እንዲያውም በጣም ትንሽ የጣት መቁሰል እንኳ አስቀድሞ የተወሰነ ነው ብለው ያምኑ ነበር።
ኢየሱስ ለ18 ሰዎች ሞት ምክንያት ስለሆነው የግንብ መፍረስ ሲናገር እነዚህን የመሰሉ የሐሰት አስተሳሰቦችን በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል። “[የአደጋው ሰለባዎች] በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሏችኋልን?” ሲል ጠይቋል። (ሉቃስ 13:4) በአብዛኞቹ አደጋዎች ላይ እንደሚታየው ይህም ፈሪሳውያን እንደሚሉት ዕድል ያመጣው ነገር ሳይሆን “ጊዜና ያልታሰበ አጋጣሚ” የፈጠረው ነገር ነው። (መክብብ 9:11 አዓት) እነዚህን የመሰሉ ብዙ ያውቃሉ የሚባሉት ሰዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ትእዛዞችን የሚመለከቷቸው እንዴት ነበር?
ሃይማኖታዊ ለውጥ አራማጆች ነበሩ
ፈሪሳውያን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትእዛዞች አዳዲስ ከሆኑ ሐሳቦች ጋር በሚስማማ መንገድ በእያንዳንዱ የረቢዎች ትውልድ ትርጉም ሊሰጣቸው ይገባል ይሉ ነበር። በመሆኑም ኢንሳይክሎፔድያ ጁዳይካ “የቶራህን ትምህርቶች ከራሳቸው አዳዲስ ሐሳቦች ጋር ለማስማማት ብዙም አልተቸገሩም፤ ወይም የእነርሱ ሐሳቦች በቶራህ ውስጥ ተጠቅሰው ለማግኘት ብዙም አልተቸገሩም ነበር” ይላል።
ዓመታዊውን የማስተሰርያ ቀን በተመለከተ ከኃጢአት የማንጻቱን ሥልጣን ከሊቀ ካህኑ አንሥተው ለራሱ ለቀኑ አሳልፈው ሰጡ። (ዘሌዋውያን 16:30, 33) በማለፍ በዓል ሥነ ሥርዓት ላይ ከፋሲካው በግ የበለጠ ከወይኑና ካልቦካው ቂጣ በሚካፈሉበት ጊዜ ለሚተረኩት የዘጸአት ዘገባ ትምህርቶች ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡ ነበር።
ከጊዜ በኋላ ፈሪሳውያን በቤተ መቅደሱ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች ሆኑ። ከዚያም በመከር በዓል ወቅት ሌሊት ከሰሊሆም ኩሬ ውኃ ተሸክመው በሰልፍ እንዲመጡ፣ በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ውኃውን በመሠዊያው ላይ እንዲያፈሱ፣ በበዓሉ ማብቂያ ላይ የአኻያ ዛፎችን በመሠዊያው ላይ መቀጥቀጥና በሕጉ ላይ ፈጽሞ ያልተመሠረተ ዘወትር በየዕለቱ የመጸለይ ሥርዓት አወጡ።
“ከሁሉ ደግሞ ለየት የሚለው ፈሪሳውያን ከሰንበት ጋር በተያያዘ ያደረጉት ለውጥ ነው” በማለት ዘ ጁዊሽ ኢንሳይክሎፔድያ ይናገራል። አንዲት ሚስት ሰንበትን መብራት አብርታ መቀበል ይጠበቅባት ነበር። ፈሪሳውያን አንድ የሆነ ሥራ ሕገ–ወጥ የሆነ ነገር የሚያሠራ ሆኖ ከታያቸው እንዳይሠራ ይከለክሉ ነበር። እንዲያውም ሕክምናንም እንኳ እስከ መቆጣጠር ደርሰው ነበር፤ እንዲሁም ኢየሱስ በሰንበት ተአምራዊ ፈውስ በመፈጸሙ ተቆጥተው ነበር። (ማቴዎስ 12:9–14፤ ዮሐንስ 5:1–16) ይሁን እንጂ እነዚህ ሃይማኖታዊ ለውጥ አራማጆች ቅዱስ ጽሑፋዊ ሕግጋትን ለመጠበቅ አጥር ለማበጀት ሲሉ አዳዲስ ወጎችን ማውጣታቸውን አላቆሙም ነበር።
ሕጎችን መሻር
ፈሪሳውያን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሕጎችን የመሰረዝ ወይም የመሻር ሥልጣን አለን ይሉ ነበር። ለዚህም የሚያቀርቡት ምክንያት ታልሙድ ላይ ሰፍሮ በሚገኘው በሚከተለው ደንብ ላይ ተገልጿል፦ “ቶራህ ሙሉ ለሙሉ ከሚረሳ አንዲት ሕግ ብትሻር ይሻላል።” ለዚህ አንዱ ምሳሌ ኢዮቤልዩ እየቀረበ ሲመጣ ለድሀ የሚያበድር አይኖርም በሚል ፍራቻ የኢዮቤልዩ በዓል እንዲቆም መደረጉ ነው።—ዘሌዋውያን ምዕራፍ 25
ሌሎቹ ምሳሌዎች ደግሞ ምንዝር ፈጽማለች ተብላ የተጠረጠረችን አንዲት ሴት ፍርድ ፊት እንድትቀርብ የሚደረግበትን ሁኔታ ማስቀረታቸውና አንድ ገዳዩ ያልታወቀ የነፍስ ግድያ ሲፈጸም የሚከናወነውን የሥርየት ሥርዓት ለተወሰነ ጊዜ ማስቀረታቸው ነው። (ዘኁልቁ 5:11–31፤ ዘዳግም 21:1–9) ብዙም ሳይቆይ ፈሪሳውያን አንድ ሰው የሚያስፈልጓቸው ቁሳዊ ነገሮች ላልተሟሉላቸው ወላጆቹ የሚያስፈልጋቸውን ለማሟላት ያለበትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነት አስቀርተውታል።—ዘጸአት 20:12፤ ማቴዎስ 15:3–6
ኢየሱስ “ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ፣ እርሱም ግብዝነት ነው” ሲል አስጠንቅቋል። (ሉቃስ 12:1) ቲኦክራሲያዊ ያልሆነ አመለካከት ያለው የፈሪሳዊነት መሠረተ ትምህርት እልም ያለ ግብዝነት ነው። ፈጽሞ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ሊሰርጽ አይገባም። ሆኖም የአይሁድ የምርምር ሥነ ጽሑፎች ፈሪሳውያንን ከሰዱቃውያን የተሻሉ እንደሆኑ አድርገው ይገልጿቸዋል። እስቲ አሁን ይህን ይበልጥ ወግ አጥባቂ የሆነ ቡድን እንመልከት።
ሰዱቃውያን
ሰዱቃውያን የሚለው ስም የተወሰደው በሰሎሞን ዘመን ሊቀ ካህን ከነበረው ከሳዶቅ ሳይሆን አይቀርም። (1 ነገሥት 2:35 የአዓት የግርጌ ማስታወሻ) ሰዱቃውያን የቤተ መቅደሱንና የቤተ ክህነቱን ፍላጎቶች የሚወክል ወግ አጥባቂ ቡድን አቋቋሙ። ሥልጣን የሚገኘው በትምህርትና ሃይማኖተኛ በመሆን ነው ከሚሉት ፈሪሳውያን በተለየ መልኩ ሰዱቃውያን ሥልጣናቸው በዘር ሐረጋቸውና ባላቸው ቦታ ላይ የተመሠረተ ነው። ፈሪሳውያን በሕጉ ላይ ያደረጓቸውን ለውጦች ቤተ መቅደሱ እስከጠፋበት እስከ 70 እዘአ ድረስ ይቃወሙ ነበር።
ሰዱቃውያን የሰው ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለውን እምነት ከማጣጣላቸውም በላይ ማንኛውም ትምህርት በአምስቱ የሙሴ መጻሕፍት ላይ በግልጽ እስካልተጠቀሰ ድረስ በአምላክ ቃል ውስጥ በሌላ ቦታ ላይ ቢገለጽም እንኳ አይቀበሉትም ነበር። እንዲያውም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ “መከራከርን በጎ ምግባር እንደሆነ አድርገው ይመለከቱት ነበር።” (ዘ ጂዊሽ ኢንሳይክሎፔድያ) ይህም ትንሣኤን የሚመለከት ጥያቄ በማንሳት ኢየሱስን የተፈታተኑበትን ጊዜ እንድናስታውስ ያደርገናል።
ሰዱቃውያን ሰባት ባሎች ያገባችን አንዲት መበለት ምሳሌ በማቅረብ “በትንሣኤ ቀን ከሰባቱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች?” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል። እርግጥ ሰዱቃውያን የጠቀሷት ይህች መበለት 14ም ሆነ 21 ባሎችን ብታገባ የሚያመጣው ለውጥ የለም። ኢየሱስ “በትንሣኤ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች አያገቡም አይጋቡምም” ሲል ገልጿል።—ማቴዎስ 22:23–30 አዓት
ሰዱቃውያን ከሙሴ በስተቀር በመንፈስ አነሳሽነት የጻፉትን ሌሎቹን ጸሐፊዎች እንደማይቀበሉ ኢየሱስ ያውቅ ስለነበረ ከአምስቱ የሙሴ መጻሕፍት በመጥቀስ ነጥቡን አስረድቷል። እንዲህ አለ፦ “ስለ ሙታን ግን እንዲነሡ እግዚአብሔር፦ እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ እንዳለው በሙሴ መጽሐፍ በቁጥቋጦው ዘንድ የተጻፈውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም።”—ማርቆስ 12:26, 27
የኢየሱስ አሳዳጆች እና ተከታዮቹ
ሰዱቃውያን መሲሑን ከመጠበቅ ይልቅ (ያውም ይመጣል ብለው ካመኑበት ነው) ከሌሎች አገሮች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የአገር ውስጥ ጉዳዮችን የመምራት እምነት ነበራቸው። ከሮም ጋር ስምምነት በማድረግ የቤተ መቅደሱን ሥራ የማካሄድ ኃላፊነት ወስደው ነበር። እነዚህን ሁኔታዎች የሚያደፈርስ ማንኛውም ዓይነት መሲሕ እንዲመጣ አይፈልጉም ነበር። ኢየሱስ ለያዙት ሥልጣን እንቅፋት እንደሚሆን አድርገው በመመልከት እርሱ የሚሞትበትን ዕቅድ ለመሸረብ ከፈሪሳውያን ጋር ግንባር ፈጠሩ።—ማቴዎስ 26:59–66፤ ዮሐንስ 11:45–50
ሰዱቃውያን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የነበራቸው ሰዎች ስለነበሩ ለሮም ታማኝ የመሆን ጥያቄ ያስነሱትና “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ሲሉ የጮኹት እነርሱ መሆናቸው የታወቀ ነው። (ዮሐንስ 19:6, 12–15) ኢየሱስ ከሞተና ከተነሣ በኋላ የክርስትናን ስርጭት ለመግታት በመሞከር ግንባር ቀደም የነበሩት ሰዱቃውያን ነበሩ። (ሥራ 4:1–23፤ 5:17–42፤ 9:14) ቤተ መቅደሱ በ70 እዘአ ከጠፋ በኋላ ይህ ቡድን ደብዛው ጠፋ።
ዘወትር ንቁ የመሆን አስፈላጊነት
የኢየሱስ ማስጠንቀቂያ ተገቢ መሆኑ ተረጋግጧል! አዎን፣ “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ” መጠንቀቅ ያስፈልገናል። አንድ ሰው በዛሬው ጊዜ የዚህን መጥፎ ፍሬ በአይሁድ እምነትም ሆነ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ መመልከት ይችላል።
ይሁን እንጂ ከዚህ በተቃራኒው በዓለም ዙሪያ ከ75,500 በሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ብቃት ያላቸው ሽማግሌዎች ‘ለራሳቸውና ለትምህርታቸው የማያቋርጥ ጥንቃቄ ያደርጋሉ።’ (1 ጢሞቴዎስ 4:16) መላውን መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ እንደሆነ አድርገው በማመን ይቀበሉታል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) አንዳንድ ለውጦችን ከማድረግና የራሳቸውን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ከማራመድ ይልቅ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ያለው አንድ ድርጅት በሚሰጠው አመራር አንድ ሆነው ይሠራሉ። ይህ ድርጅት ይህን መጽሔት መመሪያ የሚሰጥበት ዋነኛ መሣሪያ አድርጎ ይጠቀምበታል።—ማቴዎስ 24:45–47
ይህ ምን ውጤት አስገኝቷል? በዓለም ዙሪያ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ሲረዱ፣ በሕይወታቸው ሲሠሩበትና ይህን ለሌሎች ሲያስተምሩ ከፍተኛ መንፈሳዊ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ይህ እየተከናወነ ያለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ለምን በአቅራቢያህ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ አትሄድም? አለዚያም ለምን ለዚህ መጽሔት አሳታሚዎች አትጽፍም?
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ኢየሱስ የአድማጮቹን ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ ነበር
ኢየሱስ ክርስቶስ የአድማጮቹን ሐሳቦች ግምት ውስጥ በማስገባት በጣም ግልጽ በሆነ መንገድ ያስተምር ነበር። ለምሳሌ ያህል ፈሪሳዊ ለሆነው ለኒቆዲሞስ ስለ ዳግም ‘መወለድ’ በነገረው ጊዜ እንዲህ አድርጎ ነበር። ኒቆዲሞስ “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?” ሲል ጠይቋል። (ዮሐንስ 3:1–5) ፈሪሳውያን ወደ አይሁድ እምነት ለመለወጥ እንደገና መወለድ ያስፈልጋል ብለው ያምኑ ስለነበረና አንድ የረቢዎች አባባል አንድን ወደ አይሁድነት የተለወጠ ሰው “አዲስ ከተወለደ ሕፃን” ጋር ያመሳስለው ስለነበረ ኒቆዲሞስ ግራ የተጋባው ለምን ነበር?
በጆን ላይትፉት የተጻፈው ኤ ኮሜንታሪ ኦን ዘ ኒው ቴስታመንት ፍሮም ዘ ታልሙድ ኤንድ ሂብራይካ የተባለው መጽሐፍ የሚከተለውን ጠለቅ ያለ እውቀት ይሰጣል፦ “አይሁዳውያን አንድ እስራኤላዊ ሊኖረው ስለሚገባው ብቃት ያላቸው የተለመደ አመለካከት . . . ቀደም ሲል በሌሎች ሕዝቦች ላይ የነበረውን ጥላቻ በቀላሉ ከአእምሮ ማስወገድ” በማይችለው በዚህ “ፈሪሳዊ አእምሮ ውስጥ ሥር ሰዶ ነበር።” ስለዚህ ይህ ሰው “‘እስራኤላውያን . . . በመሲሑ መንግሥት ውስጥ ተቀባይነት የማግኘት መብት አላቸው። ታዲያ በዚህ አባባልህ መሠረት ማንኛውም ሰው እንደገና እስራኤላዊ መሆን እንዲችል ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እናቱ ማኅፀን መግባት ያስፈልገዋል ማለትህ ነው?’” ብሎ መጠየቁ ነበር።—ከማቴዎስ 3:9 ጋር አወዳድር።
ምንም እንኳ ኒቆዲሞስ አንድ ሰው እምነቱን ለመለወጥ እንዲችል እንደገና መወለድ አለበት የሚል እምነት የነበረው ቢሆንም ይህ እንደገና ወደ ማኅፀን የመመለስ ሁኔታ ለሥጋዊ እስራኤላውያን ሊሆን የማይችል ነገር እንደሆነ ተሰምቶት ነበር።
በሌላ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ ‘ሥጋውን ስለ መብላትና ደሙን ስለ መጠጣት’ በተናገረ ጊዜ ብዙዎች ተቆጥተው ነበር። (ዮሐንስ 6:48–55) ይሁን እንጂ ላይትፉት “‘መብላትና መጠጣት’ የሚሉትን ቃላት ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ የመጠቀምን ያህል በአይሁድ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተለመደ ነገር አልነበረም” በማለት አመልክተዋል። በተጨማሪም ታልሙድ “መሲሑን መብላት” በማለት እንደሚናገር ጠቅሰዋል።
ስለዚህ የፈሪሳውያንና የሰዱቃውያን አመለካከት በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የአይሁዳውያን አስተሳሰብ ላይ ተጽእኖ አሳድሯል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሁልጊዜ የአድማጮቹን እውቀትና ተሞክሮ ግምት ውስጥ ማስገባቱ ተገቢ ነበር። ይህም ታላቅ አስተማሪ እንዲሆን ካደረጉት ብዙ ነገሮች መካከል አንዱ ነበር።