የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ትንንሽ ልጆች በአፍሪካ ምሥራቹን ያውጃሉ
ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አንድ አፍሪካዊ ሰው ኢየሩሳሌምን ጎብኝቶ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ስሙ ማን እንደሆነ አይገልጽም። “ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋ ሁሉ የሠለጠነ” ሰው እንደሆነ ብቻ ነው የሚታወቀው። ይህ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አንድ መልአክ ክርስቲያኑን ወንጌላዊ ፊልጶስን “ስለ ኢየሱስ ወንጌልን” እንዲሰብክለት ወደዚህ ሰው ስለመራው ነው። ይህ ኢትዮጵያዊ ሰው በታሪክ ተመዝግቦ የሚገኘው የመጀመሪያው አፍሪካዊ የክርስቲያን ጉባኤ አባል ነው።—ሥራ 8:26–39
በአፍሪካ በአሁኑ ጊዜ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን ምሥራች ለሰዎች ለማካፈል እያንዳንዱን አጋጣሚ ይጠቀማሉ። በአፍሪካ የሚገኙ ትንንሽ ልጆች እንኳን ሳይቀሩ ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው የሚከተሉት ተሞክሮዎች ያሳያሉ።
◻ በኬንያ ናይሮቢ የሚኖሩት ሳንዲ እና ፕሪያ የተባሉት ሁለት የ11 ዓመት ልጃገረዶች ጎረቤታሞች ነበሩ። አብረው ይጫወታሉ፤ እንዲሁም የተረት መጽሐፎችን ይዋዋሳሉ። የፕሪያ ወላጆች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። አሁን ፕሪያ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የታተመውን በተለይም ከሁሉ አብልጣ የወደደችውን ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥ የተባለውን መጽሐፍ ጨምሮ ቀደም ሲል ካሏት መጻሕፍት በተጨማሪ ሌሎች አዳዲስ መጻሕፍት አገኘች። ታላቁ አስተማሪ የተባለውን መጽሐፍ ለጓደኛዋ አሳየቻትና ሁለቱም ልጆች በቋሚነት መጽሐፉን ማጥናት ጀመሩ።
ይሁን እንጂ የሳንዲ እናት ዩና በአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ትሰበሰብ ስለነበረ ልጅዋ የይሖዋ ምሥክሮችን መጻሕፍት እንድታነብ አልፈለገችም። የእናትየው ተቃውሞ ቢኖርም ጥናቱ ቀጠለ። አንድ ቀን ሳንዲ የሚያደርጉትን ውይይት አንዴ ብቻ እንድታዳምጥ እናቷን ለመነቻት። በዚያን ቀን ልጆቹ ያነቡት የነበረው ምዕራፍ “የልደት በዓላቸውን ያከበሩ ሁለት ሰዎች” የሚለውን ርዕስ ነበር። ዩና በሰማችው ነገር በጣም ተነካች። ወዲያው ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችን ይዛ ወደ ፕሪያ እናት ሄደች።
የፕሪያ እናት ለዩና መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠናት አንድ ምሥክር አዘጋጀችላት። ወዲያው ዩና ራሷ የሥራ ባልደረባዋ ለሆነችው ለዶሊ የተማረችውን አካፈለቻት። በዚህ ጊዜ ውስጥ የ11 ዓመቷ ፕሪያ እድገት ማድረጓን ቀጠለችና በይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለይሖዋ ራሷን መወሰኗን በውኃ ጥምቀት ለማሳየት ቆረጠች። በዚህ ትልቅ ስብሰባ ላይ ዩና እና ዶሊም በመጠመቃቸው ፕሪያ በጣም ተደስታለች!
◻ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ እውቅና ያላገኘባቸው አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች አሉ። እንዲህ ካሉት አገሮች መካከል በአንዷ የሚኖሩ ሰዎች በአጠቃላይ ሲታዩ ለምሥክሮቹ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎችና እምነቶች ግዴለሾች ናቸው። በዚህ አገር ባለ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚማር አንድ የሰባት ዓመት ልጅና የስድስት ዓመት ወንድሙ የይሖዋ ምሥክር ልጆች ሲሆኑ ሃይማኖታዊ ጸሎት በሚቀርብበት ወቅት ክፍሉን ለቅቀው እንዲወጡ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ነበር።
አንድ ቀን አንድ አዲስ አስተማሪ ከሌሎች ልጆች ጋር አብረው እንዲጸልዩ ነገራቸው። ትልቁ ልጅ እምቢ ስላለ አስተማሪው ገረፈው። ታናሽ ወንድሙ የሆነው የስድስት ዓመቱ ሻድራክ የትምህርት ቤቱን ዲሬክተር ለማነጋገር ወደ ቢሮው ሄደ። የትምህርት ቤቱ ዲሬክተርና አዲሱ አስተማሪ ከሌሎቹ ልጆች ጋር አብሮ መጸለይ ለምን እንዳልፈለገ ጠየቁት። ወላጆቹ እንዳይገርፉት ፈርቶ እንደሆነም ጠየቁት። በጣም ግሩም በሆነ አረብኛ “አይደለም። እኔ የማመልከው አምላክ የሥርዓት አምላክ እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም። በቤት የይሖዋ ምሥክር በትምህርት ቤት ደግሞ የሌላ ሃይማኖት አባል መሆን አልችልም!” ሲል መለሰ። በመጨረሻም ፈቃድ ተሰጠው።
በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው ኢትዮጵያዊ ሰው ከተጠመቀ በኋላ “ደስ ብሎት መንገዱን” ቀጠለ። (ሥራ 8:39) በተመሳሳይም በአሁኑ ጊዜ በጣም ሰፊ በሆነው የአፍሪካ አህጉር የሚገኙ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ‘ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን ምሥራች የማወጅ’ መብት በማግኘታቸው ደስተኞች ናቸው።—ሥራ 8:35