ከፊታችን የተሻለ ጊዜ ይጠብቀናል
“አንድ–ዜሮ–አንድ እናገኛለን” በማለት አንዲት ሴት ተናገረች።
“ለእኔ ሁኔታው ከዚህም ይበልጥ አስከፊ ሆኖብኛል” በማለት ጓደኛዋ መለሰች። “እኔ የማገኘው ዜሮ–ዜሮ–አንድ ብቻ ነው።”
በአንዳንድ የምዕራብ አፍሪካ አገሮች እንዲህ ዓይነቱ አነጋገር ማብራሪያ አያሻውም። በቀን ሦስት ጊዜ (አንድ–አንድ–አንድ) ከመመገብ ይልቅ የዕለት ቀለቡ አንድ–ዜሮ–አንድ የሆነ ሰው በቀን ምግብ መመገብ የሚችለው ሁለት ጊዜ ማለትም ጠዋት አንድ ጊዜ ማታ አንድ ጊዜ ብቻ ነው። የዕለት ቀለቡ ዜሮ–ዜሮ– አንድ የሆነ አንድ ወጣት የራሱን ሁኔታ ሲገልጽ “በቀን አንድ ጊዜ እመገባለሁ። ማቀዝቀዣዬን የምሞላው በውኃ ነው። ማታ ከመተኛቴ በፊት ጋሪ [ካሳቫ] እበላለሁ። ሁኔታውን መቋቋም የቻልኩት በዚህ መንገድ ነው” ብሏል።
በአሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ብዙ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ችግር አለባቸው። የምግብ ዋጋ ይንራል፤ የገንዘብ የመግዛት አቅም ደግሞ ወደ ታች ያሽቆለቁላል።
የምግብ እጥረት እንደሚኖር ተተንብዮአል
ሐዋርያው ዮሐንስ በተመለከታቸው ተከታታይ ራእዮች ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች የሚገጥሟቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች አምላክ ተንብዮአል። ከእነዚህ መካከል የምግብ እጥረት ይገኝበታል። “አየሁም፣ እነሆም፣ ጉራቻ ፈረስ ወጣ፣ በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ” በማለት ዮሐንስ ገልጿል። (ራእይ 6:5) አንድ መጥፎ ሁኔታ እንደሚከሰት የሚጠቁሙት እዚህ ላይ የተጠቀሱት ፈረሱና ጋላቢው ምግብ በመጥፋቱ የተነሳ ምግብ በሚዛን የሚታደልበትን የረሃብ ጊዜ ያመለክታሉ።
ቀጥሎ ሐዋርያው ዮሐንስ “አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፣ . . . ሲል ሰማሁ” በማለት ተናገረ። በዮሐንስ ዘመን አንድ እርቦ ስንዴ የአንድ ወታደር የቀን ቀለብ ሲሆን አንድ ዲናር ደግሞ ለአንድ ሙሉ ቀን ሥራ የሚከፈል ደሞዝ ነበር። በዚህ ምክንያት ሪቻርድ ዌይማውዝ “አንድ ዳቦ በአንድ ሙሉ ቀን ደሞዝ፣ ሦስት የገብስ ቂጣ በአንድ ሙሉ ቀን ደሞዝ” በማለት ጥቅሱን ተርጉመውታል።—ራእይ 6:6
በአሁኑ ጊዜ የአንድ ሙሉ ቀን ደሞዝ ምን ያህል ነው? ስቴት ኦቭ ወርልድ ፖፑሌሽን፣ 1994 የተባለው ሪፖርት “1.1 ቢልዮን የሚያክሉ ማለትም በታዳጊ አገሮች ውስጥ ከሚኖረው ሕዝብ መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች የአንድ ቀን መተዳደሪያቸው 1 የአሜሪካን ዶላር ነው” በማለት ዘግቧል። ስለዚህ በድህነት ቀንበር ውስጥ ለሚኖረው የዓለም ሕዝብ የአንድ ቀን ደሞዝ ቃል በቃል አንድ ዳቦ ቢገዛ ነው።
እርግጥ ነው ይህ በድህነት ተቆራምደው ለሚኖሩ ሰዎች የሚያስደንቅ አይደለም። “ዳቦ!” አለ አንድ ሰው በመደነቅ፤ “ማን ነው ዳቦ የሚበላው? በአሁኑ ጊዜ ዳቦ የቅንጦት ምግብ ሆኗል!”
የሚገርመው ግን የምግብ እጥረት አለመኖሩ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ባለፉት አሥር ዓመታት ከዓለም የሕዝብ ብዛት ጭማሪ በላይ የዓለም የምግብ ምርት 24 በመቶ ከፍ ብሏል። ይሁን እንጂ ይህ የምግብ ጭማሪ የተገኘው በሁሉም አገሮች አይደለም። ለምሳሌ በአፍሪካ የምግብ ምርት 5 በመቶ ወደ ታች ሲያሽቆለቁል የሕዝቡ ብዛት ግን 34 በመቶ አድጓል። ምንም እንኳ በዓለም አቀፍ ዙሪያ ምግብ በብዛት ቢኖርም በብዙ አገሮች የምግብ እጥረት እንዳለ ነው።
የምግብ እጥረት ማለት የዋጋ መጨመር ማለት ነው። ሥራ አጥነት፣ አነስተኛ ደሞዝና የገንዘብ ዋጋ ማጣት በገበያ ላይ የሚገኘውን ምግብ ለመግዛት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማግኘት ይበልጥ አስቸጋሪ እንዲሆን አድርገውታል። የ1994 ሂውማን ዴቨሎፕመንት ሪፖርት “ሰዎች የሚራቡት ምግብ ስለጠፋ ሳይሆን የመግዛት አቅሙ ስለ ሌላቸው ነው” በማለት አትቷል።
ተስፋ ቢስነት፣ ብስጭትና ተስፋ መቁረጥ በመስፋፋት ላይ ናቸው። “ሰዎች፣ ዛሬ ያለው ሁኔታ መጥፎ ነው፤ ነገ ደግሞ የከፋ ይሆናል የሚል ስሜት አላቸው” በማለት በምዕራብ አፍሪካ የሚኖሩት ግሎሪ ተናግረዋል። ሌላዋ ሴት ደግሞ “ሰዎች አንድ መቅሰፍት እየመጣባቸው እንዳለ ሆኖ ይሰማቸዋል። በገበያ ምንም ነገር የማይገኝበት ጊዜ ይመጣል የሚል ፍራቻ አላቸው።”
ይሖዋ የጥንት አገልጋዮቹን ተንከባክቧቸዋል
ይሖዋ ለእርሱ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮችና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ጥንካሬ በመስጠት እንደሚክሳቸው የአምላክ አገልጋዮች ያውቃሉ። እንዲያውም አምላክ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ ለመስጠት በቂ ችሎታ እንዳለው በማመን በእርሱ ላይ ያላቸው ይህ ትምክህት የእምነታቸው ዋነኛ ክፍል ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና” በማለት ጽፏል።—ዕብራውያን 11:6
ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ሁልጊዜ ይንከባከባቸዋል። ሦስት ዓመት ተኩል ድርቅ በነበረበት ጊዜ ይሖዋ ለነቢዩ ኤልያስ የሚያስፈልገውን ምግብ ያቀርብለት ነበር። በመጀመሪያ ቁራዎች እንጀራና ሥጋ እየወሰዱ ኤልያስን እንዲመግቡት አምላክ አዘዘ። (1 ነገሥት 17:2–6) ከዚያም ይሖዋ ኤልያስን ትመግበው የነበረችውን የመበለቲቱን ዱቄትና ዘይት በተአምር እንዳያልቅ አድርጓል። (1 ነገሥት 17:8–16) በዚሁ የረሃብ ወቅት ክፉዋ ንግሥት ኤልዛቤል የከረረ ሃይማኖታዊ ስደት ብታደርስባቸውም ይሖዋ ለነቢያቱ እንጀራና ውኃ የሚያገኙበትን መንገድ አዘጋጅቶ ነበር።—1 ነገሥት 18:13
ከዚያም የባቢሎን ንጉሥ ከሃዲዋን ኢየሩሳሌምን በከበበ ጊዜ ሕዝቡ “እየፈሩም እንጀራን በሚዛን” መብላት ግድ ሆኖባቸዋል። (ሕዝቅኤል 4:16) ሁኔታው በጣም ተስፋ አስቆራጭ በሆነ ጊዜ አንዳንድ ሴቶች የልጆቻቸውን ሥጋ በሉ። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 2:20) ምንም እንኳን ነቢዩ ኤርምያስ በስብከቱ ምክንያት በግዞት ውስጥ ቢከተትም ይሖዋ “እንጀራም ሁሉ ከከተማ እስኪጠፋ ድረስ ዕለት ዕለት አንድ አንድ እንጀራ ከጋጋሪዎች መንገድ [ለኤርምያስ]” እንዲሰጠው አድርጓል።—ኤርምያስ 37:21
እንጀራ ባለቀ ጊዜ ይሖዋ ኤርምያስን ረሳውን? እንዳልረሳው ግልጽ ነው። ምክንያቱም ከተማዋ በባቢሎናውያን እጅ በወደቀች ጊዜ ኤርምያስ ‘ስንቅና ስጦታ ተሰጥቶት እንዲሰናበት ተደርጓል።’—ኤርምያስ 40:5, 6፤ በተጨማሪም መዝሙር 37:25ን ተመልከት።
አምላክ በጊዜአችን ያሉትን አገልጋዮቹን ይረዳቸዋል
ይሖዋ ባለፉት ትውልዶች የነበሩትን አገልጋዮቹን እንደደገፋቸው ሁሉ በጊዜያችንም ያሉትን አገልጋዮቹን በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ በመንከባከብ ይደግፋቸዋል። ለምሳሌ በምዕራብ አፍሪካ የሚኖረውን የላሚቱንዴን ተሞክሮ ተመልከት። እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “በአንድ ወቅት አንድ ትልቅ የዶሮ እርባታ ነበረኝ። አንድ ቀን የታጠቁ ዘራፊዎች ወደ ዶሮ እርባታው መጥተው አብዛኛዎቹን ዶሮዎች፣ መጠባበቂያ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ጀነሬተርና የነበረንን ገንዘብ ዘርፈው ሄዱ። ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የተረፉት ጥቂት ዶሮዎች በበሽታ አለቁ። በዚህ ጊዜ አካሂደው የነበረው የዶሮ እርባታ ንግድ አከተመለት። ለሁለት ዓመታት ሥራ ለማግኘት ላይ ታች ብልም ሊሳካልኝ አልቻለም። ሁኔታዎች ሁሉ አስቸጋሪ ሆኑ። ይሖዋ ግን ረድቶኛል።
“እነዚህን አስቸጋሪ ጊዜያት እንድቋቋም የረዳኝ ነገር ይሖዋ አመለካከታችንን ለማስተካከል አንዳንድ ነገሮች እንዲደርሱብን እንደሚፈቅድ መገንዘቤ ነበር። ባለቤቴና እኔ ቋሚ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልማዳችንን ከማከናወን ወደ ኋላ አላልንም። ይህም ትልቅ እርዳታ አበርክቶልናል። በተጨማሪም ጸሎት ትልቅ የጥንካሬ ምንጭ ሆኖልን ነበር። አንዳንድ ጊዜ ጸልይ፣ ጸልይ አይለኝም። እንደምንም ብዬ በምጸልይበት ጊዜ ግን ጥሩ ስሜት ይሰማኝ ነበር።
“በእነዚያ አስቸጋሪ ጊዜያት በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የማሰላሰልን ዋጋማነት ተገንዝቤ ነበር። ይሖዋ እረኛችን እንደሆነ የሚገልጸውን መዝሙር 23ን በጣም አሰላስልበት ነገር። ሌላው ብርታት የሰጠኝ ጥቅስ ‘አእምሮን ሁሉ ስለሚያልፈው የአምላክ ሰላም’ የሚጠቅሰው ፊልጵስዩስ 4:6, 7 ነበር። ሌላው ጥንካሬ የሰጠኝ ‘እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት’ የሚለው 1 ጴጥሮስ 5:6, 7 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ነበር። እነዚህ ሁሉ ጥቅሶች በእነዚያ አስቸጋሪ ጊዜያት ረድተውኛል። በምታሰላስሉበት ጊዜ በአእምሯችሁ ውስጥ የነበሩትን ጭንቀት የሚፈጥሩ ሐሳቦች ልታስወግዷቸው ትችላላችሁ።
“አሁን ሥራ አግኝቻለሁ። ይሁን እንጂ ሐቁን ለመናገር አሁንም ቢሆን ያለው ሁኔታ ቀላል አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ በ2 ጢሞቴዎስ 3:1–5 ላይ አስቀድሞ እንደተናገረው ‘አስጨናቂ በሆነው የመጨረሻ ዘመን’ ውስጥ እንኖራለን። ቅዱስ ጽሑፉ የሚናገረውን መለወጥ አንችልም። ስለዚህ ኑሮ ቀላል ይሆናል ብዬ አልጠብቅም። ቢሆንም ችግሮችን ለመቋቋም የይሖዋ መንፈስ እየረዳኝ እንዳለ ይሰማኛል።”
ምንም እንኳ የምንኖረው አስጨናቂ በሆነ ዘመን ውስጥ ቢሆንም በይሖዋ እና ንጉሥ በሆነው ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የታመኑ የጠበቁት ነገር ሳይፈጸም ቀርቶ ለብስጭት አይዳረጉም። (ሮሜ 10:11) ኢየሱስ ራሱ እንዲህ በማለት ማረጋገጫ ሰጥቶናል፦ “ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፣ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፣ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? ስለ ልብስስ ስለ ምን ትጨነቃላችሁ?”—ማቴዎስ 6:25–28
እነዚህ ያለጥርጥር በዚህ አስጨናቂ ዘመን ልባችንን እንድንመረምር የሚያደርጉ ጥያቄዎች ናቸው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በእነዚህ የማጽናኛ ቃላት ንግግሩን ይቀጥላል፦ “የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም። እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፣ እናንተ እምነት የጎደላችሁ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።”—ማቴዎስ 6:28–33
ከፊታችን የተሻለ ጊዜ ይጠብቀናል
እያዘቀጠ ያለው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታ በብዙ የዓለም ክፍሎች ይበልጥ እየተባባሰ እንደሚሄድ ያሉት ሁኔታዎች ይጠቁማሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁኔታዎች ጊዜያዊ እንደሆኑ የአምላክ አገልጋዮች ያውቃሉ። የንጉሥ ሰሎሞን አስደሳች ግዛት ከሰሎሞን ለሚበልጠውና በመላው ምድር ላይ በጽድቅ ለሚገዛው ንጉሥ ጥላ ነው። (ማቴዎስ 12:42) ይህም ንጉሥ “የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።—ራእይ 19:16
በንጉሥ ሰሎሞን ግዛት የመጀመሪያውን ፍጻሜ ያገኘው መዝሙር 72 እጹብ ድንቅ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን አገዛዝ ይገልጻል። በመዝሙር 72 ላይ ወደፊት በክርስቶስ ግዛት ሥር ምድር የሚኖራትን ሁኔታ በማስመልከት የተተነበዩትን አንዳንድ አስደናቂ ነገሮች ተመልከት።
በዓለም ዙሪያ ሰላም ይሰፍናል፦ “በዘመኑም ጽድቅ ያብባል፣ ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ ሰላም ብዙ ነው። ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፣ ከወንዝም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይገዛል።”—መዝሙር 72:7, 8
ለችግረኞች ማሰብ፦ “ወደ እርሱ የሚጮኹትን ድኾች ነፃ ያወጣል፤ ችግረኞችንና የተናቁትን ሰዎች ይታደጋል። ለድኾችና ለደካሞች ይራራል፤ በችግር ላይ ያሉትን ሰዎች ከሞት ያድናል። የእነርሱ ሕይወት በእርሱ ዘንድ ውድ ስለሆነ፣ ከጭቆናና ከዐመፅ ይታደጋቸዋል።”—መዝሙር 72:12–14 የ1980 ትርጉም
የተትረፈረፈ ምግብ፦ “በምድሩ ላይ በቂ እህል ይኑር፤ ተራራዎች በሰብል ይሸፈኑ።”—መዝሙር 72:16 የ1980 ትርጉም
ምድር በይሖዋ ክብር ትሞላለች፦ “ይህን ሁሉ ተአምራት የሚያደርግ እርሱ ብቻ ስለሆነ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን። ስሙ ለዘላለም የተመሰገነ ይሁን፤ ክብሩ በምድር ሁሉ ይሙላ።”—መዝሙር 72:18, 19 የ1980 ትርጉም
አዎን፣ ከፊታችን የተሻለ ጊዜ እንደሚጠብቀን የተረጋገጠ ነው።