‘ልክ እንደታዘዙት አደረጉ’
“ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና”—1 ዮሐንስ 5:3
1. የአምላክ ፍቅር ምን ያህል ጥልቅ ነው?
“እግዚአብሔር ፍቅር ነው።” አምላክን የሚያውቁና ትእዛዛቱን የሚያከብሩ ሁሉ ለዚህ የጠለቀ ፍቅር ከፍተኛ አድናቆት ያድርባቸዋል። “ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።” ውድ በሆነው የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ባሳደርን መጠን ‘በአምላክ ፍቅር ውስጥ መኖራችንን እንቀጥላለን።’ (1 ዮሐንስ 4:8–10, 16) በዚህ መንገድ አሁን የተትረፈረፉ መንፈሳዊ በረከቶች፣ በሚመጣው ሥርዓት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንችላለን።—ዮሐንስ 17:3፤ 1 ዮሐንስ 2:15, 17
2. የአምላክን ትእዛዛት ማክበር አገልጋዮቹን የጠቀማቸው እንዴት ነው?
2 መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ትእዛዛት ያከበሩና በምላሹ እጅግ የተባረኩ በጣም ብዙ ሰዎችን በምሳሌነት ይጠቅሳል። ይህም በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩ ምሥክሮችን ያጠቃልላል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፣ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት፣ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲሆኑ ታመኑ።” (ዕብራውያን 11:13) ከጊዜ በኋላ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች “በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በተገኘው ይገባናል በማንለው ደግነትና እውነት” ተጠቅመዋል። (ዮሐንስ 1:17 አዓት) ይሖዋ ወደ 6,000 የሚጠጉ ዓመታት ባስቆጠረው የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ትእዛዛቱን ያከበሩ ታማኝ ምሥክሮቹን በሙሉ ክሷቸዋል፤ እነዚህ ‘ትእዛዛት ከባዶች’ አይደሉም።—1 ዮሐንስ 5:2, 3
በኖኅ ዘመን
3. ኖኅ ‘ልክ እንደታዘዘው’ ያደረገው በምን በምን መንገድ ነው?
3 መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ፣ በዚህም ዓለምን ኮነነ፣ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ።” ኖኅ ‘የጽድቅ ሰባኪ’ እንደመሆኑ መጠን ከጥፋት ውኃ በፊት ለነበረው ዓመፀኛ ዓለም ስለሚመጣው መለኮታዊ ፍርድ ማስጠንቀቂያ በማሰማት አምላክን ሙሉ በሙሉ ታዟል። (ዕብራውያን 11:7፤ 2 ጴጥሮስ 2:5) መርከቡን ሲሠራ መለኮታዊ ምንጭ ያለውን ንድፍ አንድ በአንድ ተከትሏል። ከዚያም ወደ መርከቡ እንዲያስገባ የተነገረውን እንስሳትና የሚያስፈልገውን ምግብ አስገብቷል። “ኖኅም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ።”—ዘፍጥረት 6:22
4, 5. (ሀ) መጥፎ ተጽዕኖ እስከ ዛሬ ድረስ የሰውን ዘር እየነካ ያለው እንዴት ነው? (ለ) መለኮታዊ መመሪያዎችን በመከተል ረገድ ‘ልክ እንደታዘዝነው’ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
4 ኖኅና ቤተሰቡ ዓመፀኛ የሆኑት መላእክት የሚያደርሱባቸውን መጥፎ ተጽዕኖ መቋቋም ነበረባቸው። እነዚህ የአምላክ ልጆች ሥጋዊ አካል ለብሰው ከሴቶች ጋር መኖር ከመጀመራቸውም በላይ የሰውን ዘር የሚያሠቃዩ ከሰብዓዊ ፍጥረት የተለዩ ዲቃላዎች ወለዱ። “ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ተበላሸች፤ ምድርም ግፍን ተሞላች።” ይሖዋ ያንን ክፉ ትውልድ ጠራርጎ ለማጥፋት የጥፋት ውኃ አወረደ። (ዘፍጥረት 6:4, 11–17፤ 7:1) ከኖኅ ዘመን ወዲህ አጋንንት የሆኑት መላእክት የሰው ዓይነት አካል እንዲለብሱ አልተፈቀደላቸውም። ሆኖም ‘ዓለም በሙሉ ከክፉው ማለትም ከሰይጣን ዲያብሎስ እጅ አልወጣም።’ (1 ዮሐንስ 5:19፤ ራእይ 12:9) ኢየሱስ በኖኅ ዘመን የነበረውን ዓመፀኛ ትውልድ “የመገኘቱ” ምልክት መታየት ከጀመረበት ከ1914 ጀምሮ ከሚኖረው እርሱን ከማይቀበለው የሰው ዘር ትውልድ ጋር አመሳስሎታል።—ማቴዎስ 24:3, 34, 37–39 አዓት ፤ ሉቃስ 17:26, 27
5 ሰይጣን እንደ ኖኅ ዘመን ሁሉ ዛሬም የሰውን ዘርና ፕላኔታችንን ለማጥፋት እየተፍጨረጨረ ነው። (ራእይ 11:15–18) ስለዚህ “የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ” የሚለውን በመንፈስ መሪነት የተሰጠ ትእዛዝ መከተሉ አጣዳፊ ነው። (ኤፌሶን 6:11 የአዓት የግርጌ ማስታወሻ) የአምላክን ቃል በማጥናትና በተግባር በማዋል የሰይጣንን ጥቃት መቋቋም እንችላለን። በተጨማሪም ከቅቡዓን የተውጣጣውን “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንዲሁም በተገቢው መንገድ እንድንመላለስ በትዕግሥት የሚመሩንን አፍቃሪ ሽማግሌዎች የያዘው አሳቢ የይሖዋ ድርጅት አለልን። ዓለም አቀፍ የሆነ የስብከት ሥራ ተሰጥቶናል። (ማቴዎስ 24:14, 45–47) ኖኅ መለኮታዊ መመሪያዎችን በጥንቃቄ እንደታዘዘ ሁሉ እኛም ሁልጊዜ ‘ልክ እንደታዘዝነው’ የምናደርግ እንሁን።
ከሰው ሁሉ እጅግ ትሑት የነበረው ሙሴ
6, 7. (ሀ) ሙሴ ያደረገው ሽልማት የሚያስገኝ ምርጫ ምን ነበር? (ለ) ሙሴ ምን የድፍረት ምሳሌ ትቶልናል?
6 ሌላ የእምነት ሰው እንመልከት፤ ይህ ሰው ሙሴ ነው። ግብጽ ውስጥ በምቾት ተንደላቆ መኖር ይችል ነበር። ቢሆንም “ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ።” የሚያከናውነው ተልዕኮ የተሰጠው የይሖዋ አገልጋይ እንደመሆኑ መጠን ‘ብድራቱን ትኩር ብሎ ከመመልከቱም በላይ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቷል።’—ዕብራውያን 11:23–28
7 በዘኁልቁ 12:3 ላይ “ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ” የሚል እናነባለን። ከዚህ በተቃራኒ ግን የግብጹ ፈርዖን በትዕቢተኝነቱ የሚተካከለው አልነበረም። ይሖዋ በፈርዖን ላይ የምወስደውን እርምጃ ተናገሩ ብሎ ሙሴንና አሮንን ሲያዛቸው ምን ምላሽ ሰጡ? “ሙሴና አሮንም እንዲህ አደረጉ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ” ተብሎ ተነግሮናል። (ዘጸአት 7:4–7) በዛሬው ጊዜ የአምላክን ፍርድ በማወጅ ላይ ለምንገኘው ሰዎች እንዴት ያለ የድፍረት ምሳሌ ነው!
8. እስራኤላውያን ‘ልክ እንደታዘዙት’ ማድረግ የተፈለገባቸው ለምን ነበር? ከዚህ የተነሳ ያገኙት ደስታስ በቅርቡ ከምናገኘው ከየትኛው ደስታ ጋር ይመሳሰላል?
8 እስራኤላውያን ሙሴን በታማኝነት ደግፈውት ነበርን? ይሖዋ ከአሥሩ መቅሰፍቶች ዘጠኙን በግብጽ ላይ ካወረደ በኋላ ስለ ማለፍ በዓል አከባበር ለእስራኤላውያን ዝርዝር መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር። “ሕዝቡም ተጎነበሰ ሰገደም። የእስራኤልም ልጆች ሄዱ፣ እንዲሁም አደረጉ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉ።” (ዘጸአት 12:27, 28) የአምላክ መልአክ ታሪካዊ በሆነው ኒሳን 14, 1513 ከዘአበ እኩለ ሌሊት የእስራኤላውያንን ቤቶች እያለፈ የግብጻውያንን የበኩር ልጆች አንድ በአንድ ገደለ። የእስራኤላውያን የበኩር ልጆች ከሞት የተረፉት ለምን ነበር? በበሮቻቸው መቃን ላይ የተረጨው የማለፍ ጠቦት ደም ከለላ ስለሆነላቸው ነው። እስራኤላውያን ልክ ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዳዘዛቸው አድርገው ነበር። አዎን፣ ‘ልክ እንደታዘዙት አድርገዋል።’ (ዘጸአት 12:50, 51) ይሖዋ ፈርዖንንና ኃያል የጦር ኃይሉን በቀይ ባሕር ሲደመስስ ታዛዥ የሆኑ ሕዝቦቹን በማዳን ሌላ ተአምር ፈጽሟል። እስራኤላውያን እንዴት ተደስተው ይሆን! ዛሬም የይሖዋን ትእዛዛት የሚያከብሩ ብዙ ሰዎች ይሖዋ በአርማጌዶን ከክስ ነፃ ሲሆን በመመልከት ይደሰታሉ።—ዘጸአት 15:1, 2፤ ራእይ 15:3, 4
9. እስራኤላውያን የመገናኛውን ድንኳን በመሥራት ረገድ ‘ልክ እንደታዘዙት’ ማድረጋቸው በጊዜያችን ላሉት ለየትኞቹ መብቶች ጥላ ነው?
9 እስራኤላውያን መዋጮ እንዲሰበስቡና በምድረ በዳ የማደሪያ ድንኳን እንዲሠሩ ይሖዋ ባዘዛቸው ጊዜ ሕዝቡ ሙሉ ድጋፋቸውን ለግሰዋል። ከዚያም ሙሴና ፈቃደኛ ረዳቶቹ ይሖዋ የሰጠውን ንድፍ አንድ በአንድ በመከተል የመገናኛውን ድንኳን ሠሩ። “የመገናኛው ድንኳን የማደሪያው ሥራ ሁሉ ተጨረሰ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ የእስራኤል ልጆች አደረጉ፤ እንዲሁ አደረጉ።” በተመሳሳይም የክህነቱ ሥራ ተመርቆ በተጀመረበት ጊዜ ‘ሙሴ ልክ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አድርጓል።’ (ዘጸአት 39:32፤ 40:16) በአሁኑ ጊዜ የስብከቱን ሥራና የመንግሥቱን እንቅስቃሴዎች ለማስፋፋት የወጡ መርሐ ግብሮችን በሙሉ ልብ የምንደግፍበት አጋጣሚ አለን። ‘ልክ እንደታዘዝነው’ በማድረግ ትብብራችንን ማሳየት እንችላለን።
ደፋርና ጠንካራ የነበረው ኢያሱ
10, 11. (ሀ) ኢያሱ የተሳካለት እንዲሆን ያስቻለው ምንድን ነው? (ለ) በጊዜያችን ያሉትን ፈተናዎች ለመቋቋም የሚያስፈልገንን ጥንካሬ እንዴት ማግኘት እንችላለን?
10 ኢያሱ እስራኤላውያንን ወደ ተስፋዪቱ ምድር የመምራት ተልእኮ ከሙሴ በተቀበለ ጊዜ የነበረው በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የይሖዋ ቃል አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት፣ አንድ ሁለት መዝሙራትና የኢዮብ መጽሐፍ ብቻ ነበር። ተስፋዪቱ ምድር በደረሱ ጊዜ ሕዝቡን እንዲሰበስብና “ይህን ሕግ በእስራኤል ሁሉ ፊት በጆሮው” እንዲያነብ ሙሴ ኢያሱን አዝዞት ነበር። (ዘዳግም 31:10–12) በተጨማሪም ይሖዋ ራሱ ኢያሱን እንዲህ በማለት አዝዞታል፦ “የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፣ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም።”—ኢያሱ 1:8
11 የይሖዋ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ በየዕለቱ ማንበቡ በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ‘የመጨረሻ ቀን’ የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ጥንካሬ እንደሚሰጣቸው ሁሉ ኢያሱ የይሖዋን “መጽሐፍ” በየዕለቱ ማንበቡ ከፊቱ ይጠብቁት የነበሩትን ፈተናዎች ለመወጣት ብቁ አድርጎታል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ዓመፀኛ በሆነ ዓለም የተከበብን እንደመሆናችን መጠን አምላክ እንዲህ በማለት ለኢያሱ የሰጠውን ምክር ልብ እንበል፦ “በምትሄድበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ጽና፣ አይዞህ፤ አትፍራ፣ አትደንግጥ።” (ኢያሱ 1:9) የእስራኤል ነገዶች ከነዓናውያንን አሸንፈው ርስታቸውን በተካፈሉ ጊዜ በጣም ተባርከዋል። ‘የእስራኤል ልጆች ያደረጉት ልክ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ነበር።’ (ኢያሱ 14:5) በዛሬው ጊዜ የአምላክን ቃል በማንበብና በተግባር በማዋል ‘ልክ እንደታዘዝነው’ የምናደርግ ሁሉ ይህንን የመሰለ ሽልማት ይጠብቀናል።
ታማኝና ዓመፀኛ ነገሥታት
12. (ሀ) ለእሥራኤል ነገሥታት ምን ትእዛዝ ተሰጥቶ ነበር? (ለ) ነገሥታቱ አለመታዘዛቸው ምን ነገር አስከትሏል?
12 የእስራኤል ነገሥታት ሁኔታስ እንዴት ነበር? ይሖዋ አንድ ንጉሥ ሲነግሥ የሚከተለውን እንዲያሟላ ይጠይቅበት ነበር፦ “በመንግሥቱም ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ ከሌዋውያን ካህናት ወስዶ ይህን ሕግ ለራሱ በመጽሐፍ ይጻፍ። አምላኩን እግዚአብሔርን መፍራት ይማር ዘንድ፣ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ ይህችንም ሥርዓት ጠብቆ ያደርግ ዘንድ፣ መጽሐፉ ከእርሱ ጋር ይኑር፣ ዕድሜውንም ሁሉ ያንብበው።” (ዘዳግም 17:18, 19) የእስራኤል ነገሥታት ይህንን ትእዛዝ አክብረዋልን? ብዙዎቹ በሚያሳዝን ሁኔታ ይህንን ሳያደርጉ ቀርተዋል፤ ከዚህም የተነሳ በዘዳግም 28:15–68 ላይ የተተነበዩት መርገሞች ደርሰውባቸዋል። በመጨረሻም እስራኤላውያን “ከምድር ዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ” ተበትነዋል።
13. ለይሖዋ ቃል ፍቅር በማሳየት ልክ እንደ ዳዊት ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
13 ነገር ግን የመጀመሪያው ታማኝ የእስራኤል ሰብዓዊ ንጉሥ የነበረው ዳዊት ወደር የሌለው ታማኝነት አሳይቷል። ዳዊት ‘የይሁዳ አንበሳ ደቦል’ እንደሆነ አሳይቷል። ይህም “ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር” የሆነውን ክርስቶስ ኢየሱስን ያመለክታል። (ዘፍጥረት 49:8, 9፤ ራእይ 5:5) ለዳዊት ጥንካሬ ቁልፉ ምን ነበር? በጽሑፍ ለሰፈረው የይሖዋ ቃል ጥልቅ አድናቆት የነበረው ከመሆኑም በላይ ሕይወቱን በዚያ መሠረት ይመራ ነበር። በመዝሙር 19 ላይ በሰፈረው “የዳዊት መዝሙር” ውስጥ “የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው” የሚል እናነባለን። የይሖዋን ማሳሰቢያዎች፣ ሥርዓቶች፣ ትእዛዛትና ፍርድ ከጠቀሰ በኋላ እንዲህ አለ፦ “ከወርቅና ከክቡር ዕንቁ ይልቅ ይወደዳል፤ ከማርና ከማር ወለላም ይጣፍጣል። ባሪያህ ደግሞ ይጠብቀዋል፤ በመጠበቁም እጅግ ይጠቀማል።” (መዝሙር 19:7–11) የይሖዋን ቃል በየዕለቱ ማንበብና ያነበብነውን ማሳላሰል ከዛሬ 3,000 ዓመት በፊት ሽልማት የሚያስገኝ ከሆነ ዛሬ እንዴት አብልጦ ይክስ!—መዝሙር 1:1–3፤ 13:6፤ 119:72, 97, 111
14. የሰሎሞን አካሄድ እውቀት ብቻ በቂ እንዳልሆነ ያሳየው በምን መንገድ ነው?
14 ቢሆንም እውቀት መሰብሰቡ ብቻ በቂ አይደለም። የአምላክ አገልጋዮች ያገኙትን እውቀት አምላክ በሚፈልገው መንገድ በተግባር ላይ በማዋል ሊሠሩበትም ይገባል። አዎን፣ ‘ልክ እንደታዘዙት’ ማድረግ ይፈለግባቸዋል። ይህንንም ‘በእግዚአብሔር መንግሥት ዙፋን ላይ ተቀምጦ በእስራኤል ላይ እንዲነግሥ’ ይሖዋ ከመረጠው ከዳዊት ልጅ ሰሎሞን ማየት ይቻላል። ሰሎሞን ‘በመንፈስ አነሳሽነት’ ለዳዊት የተገለጡለትን የሕንፃ ንድፎች በመጠቀም ቤተ መቅደሱን የመሥራት መብት አግኝቶ ነበር። (1 ዜና መዋዕል 28:5, 11–13) ሰሎሞን ይህንን ከፍተኛ ሥራ ሊያከናውን የቻለው እንዴት ነው? ይሖዋ ሰሎሞን ያቀረበውን ጸሎት በመስማት ጥበብና እውቀት ሰጠው። ሰሎሞን ባገኘው ጥበብ በመጠቀምና የተሰጠውን መለኮታዊ ንድፍ በጥብቅ በመከተል ያንን አስደናቂ ቤት መገንባት ችሏል፤ በኋላም ይህን ቤት የይሖዋ ክብር ሞላው። (2 ዜና መዋዕል 7:2, 3) ከጊዜ በኋላ ግን ሰሎሞን እንደታዘዘው ሳያደርግ ቀረ። በምን ረገድ? የይሖዋ ሕግ በእስራኤል ላይ የሚገዛ ንጉሥ ማድረግ ያለበትን በተመለከተ “ልቡም እንዳይስት ሚስቶችን ለእርሱ አያበዛም” በማለት ይናገር ነበር። (ዘዳግም 17:17) ቢሆንም ሰሎሞን “ወይዛዝር የሆኑ ሰባት መቶ ሚስቶች ሦስት መቶም ቁባቶች ነበሩት፤ ሚስቶቹም . . . ሌሎች አማልክትን ይከተል ዘንድ ልቡን አዘነበሉት።” ሰሎሞን የኋላ ኋላ ‘ልክ እንደታዘዘው’ ከማድረግ ፊቱን አዞረ።—1 ነገሥት 11:3, 4፤ ነህምያ 13:26
15. ኢዮስያስ ‘ልክ እንደታዘዘው’ ያደረገው እንዴት ነበር?
15 ከይሁዳ ነገሥታት መካከል ታዛዥ የነበሩት ጥቂቶቹ ሲሆኑ ከእነርሱም የመጨረሻው ኢዮስያስ ነበር። ኢዮስያስ በ648 ከዘአበ ምድሪቱን ከጣዖት አምልኮ ማጽዳትና የይሖዋን ቤተ መቅደስ ማደስ ጀመረ። ሊቀ ካህናቱ “በሙሴ እጅ የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ” ያገኘው እዚህ ነበር። ኢዮስያስ መጽሐፉ ሲገኝ ምን አደረገ? “ንጉሡም፣ የይሁዳም ሰዎች ሁሉ፣ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩና ካህናቱ፣ ሌዋውያኑም፣ ሕዝቡም ሁሉ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጡ፤ በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ በጆሮአቸው አነበበ። ንጉሡም በስፍራው ቆሞ እግዚአብሔርን ተከትሎ እንዲሄድ፣ ትእዛዙንና ምስክሩን ሥርዓቱንም በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ እንዲጠብቅ፣ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈውን የቃል ኪዳን ቃል እንዲያደርግ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረገ።” (2 ዜና መዋዕል 34:14, 30, 31) አዎን፣ ኢዮስያስ ‘ልክ እንደታዘዘው’ አድርጓል። ይሖዋ በኢዮስያስ የታማኝነት አካሄድ የተነሳ እምነት አልባ በሆነው ይሁዳ ላይ ሊያመጣው የነበረውን ቅጣት ዓመፀኛ የሆኑት የኢዮስያስ ልጆች እስከተነሱበት ጊዜ አራዝሞታል።
የአምላክን ቃል በተግባር ማዋል
16, 17. (ሀ) የኢየሱስን ፈለግ መከተል ያለብን በምን መንገዶች ነው? (ለ) ምሳሌ የሚሆኑልን የትኞቹ ሌሎች ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ናቸው?
16 እስከ ዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የአምላክን ቃል በማሰላሰልና በተግባር በማዋል በኩል ግሩም ምሳሌ የሚሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የአምላክ ቃል ለእርሱ የምግብ ያህል ነበር። (ዮሐንስ 4:34) ያዳምጡት ለነበሩ ሰዎች እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና።” (ዮሐንስ 5:19, 30፤ 7:28፤ 8:28, 42) ኢየሱስ “ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና” በማለት ስለገለጸ ‘ልክ እንደታዘዘው’ አድርጓል። (ዮሐንስ 6:38) እኛም ራሳችንን የወሰንን የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስን ፈለግ በመከተል ‘ልክ እንደታዘዝነው’ እንድናደርግ ተጋብዘናል።—ሉቃስ 9:23፤ 14:27፤ 1 ጴጥሮስ 2:21
17 የአምላክን ፈቃድ መፈጸም በኢየሱስ አእምሮ ውስጥ ምንጊዜም የመጀመሪያ ቦታ ነበረው። የአምላክን ቃል አሳምሮ ያውቅ ስለነበር ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ያለው መልስ ለመስጠት ዝግጁ ነበር። (ማቴዎስ 4:1–11፤ 12:24–31) እኛም ለአምላክ ቃል የማያቋርጥ ትኩረት በመስጠት ‘ፍጹምና ማንኛውንም መልካም ሥራ ለመሥራት ብቁ’ መሆን እንችላለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17 የ1980 ትርጉም) በጥንት ጊዜያትና ከዚያ ወዲህ ባሉት ጊዜያት የኖሩ የእምነት ምሳሌዎችን ከሁሉ በላይ ደግሞ “አብን እንድወድ ዓለም ሊያውቅ፣ አብም እንዳዘዘኝ፣ እንዲሁ አደርጋለሁ” ያለውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ እንከተል። (ዮሐንስ 14:31) ‘ልክ እንደታዘዝነው’ ማድረጋችንን በመቀጠል ለአምላክ ያለንን ፍቅር እናሳይ።—ማርቆስ 12:29–31
18. ‘የቃሉ አድራጊዎች እንድንሆን’ የሚያነሳሳን ምን መሆን አለበት? ቀጥሎ የምናጠናው ምንድን ነው?
18 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይኖሩ የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች ስለተከተሉት የታዛዥነት አካሄድ ስናሰላስል የሰይጣን ክፉ ሥርዓት ማክተሚያ እየተቃረበ ባለበት በአሁኑ ጊዜ አገልግሎታችንን በታማኝነት ለማከናወን አልተበረታታንምን? (ሮሜ 15:4–6) የሚቀጥለው ርዕስ እንደሚያብራራልን ሙሉ በሙሉ ‘ቃሉን የምናደርግ ለመሆን’ መነሳሳት አለብን።—ያዕቆብ 1:22
ታስታውሳለህን?
◻ “የእግዚአብሔር ፍቅር” ለእኛ ምን ትርጉም ሊኖረው ይገባል?
◻ ከኖኅ፣ ከሙሴና ከኢያሱ ምሳሌ ምን እንማራለን?
◻ የእስራኤል ነገሥታት የአምላክን “ቃል” ምን ያህል ታዘዋል?
◻ ኢየሱስ ‘ልክ እንደታዘዘው’ በማድረግ ረገድ ምሳሌያችን የሆነው እንዴት ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኖኅ፣ ሙሴና ኢያሱ ‘ልክ እንደታዘዙት’ አድርገዋል