በኒዩ የሚገኘውን የመንግሥት አዳራሽ ተመልከቱ!
ኒዩ በደቡብ ፓስፊክ ውስጥ ከኒውዚላንድ 2,160 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ ዛጎል በብዛት የሚገኝባት አነስተኛ ደሴት ናት። አንድ የጉዞ ማስተዋወቂያ ብሮሹር እንዳለው ከሆነ ኒዩ የተባለው ስም የመጣው “የኮከነት ዛፎች እዩ” ወይም “ተመልከቱ” ከሚሉት ቃላት ነው። ይህ ብሮሹር እንዲህ ይላል፦ “የመጀመሪያዎቹ ፖሊኔዣውያን ሰፋሪዎች ወደዚህች ደሴት ሲደርሱ በአገሪቱ ውስጥ የበቀሉትን የኮከነት ዛፎች ተመልክተው እነዚህን ቃላት እንደተናገሩ በአፈ ታሪክ ይነገራል።”
በአሁኑ ጊዜ በኒዩ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ለጎብኚዎች “ኢ! ፋል ሂ ካቱ ሃ ሞቶሉ!” ማለትም “የመንግሥት አዳራሻችንን ተመልከቱ” በማለት በኩራት ይናገራሉ። ለዚህ አዳራሽ ይህን ያህል አድናቆት ያደረባቸው ለምንድን ነው? በየትኛውም ቦታ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ለመንግሥት አዳራሾቻቸው በተለይም ራሳቸው ለሠሯቸው አዳራሾች የሚሰጡት ግምት ከፍተኛ ነው። ይሁን እንጂ በተንጣለለው ደቡባዊ ፓስፊክ መካከል ለብቻዋ ተነጥላ በምትገኝ አንዲት ደሴት ላይ የመንግሥት አዳራሽ መሥራት ፈጽሞ የተለየ ጉዳይ ነው። ከዚህም በላይ ኒዩ ያላት የቆዳ ስፋት 260 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ብቻ ሲሆን በመላ ደሴቲቱ ውስጥ የሚኖሩት 2,300 ሰዎች ብቻ ናቸው።
የመንግሥት አዳራሹን ማን ይሠራዋል የሚል ጥያቄ ነበር። ኒዩ በሚገኘው አንድ ጉባኤ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች 32 ብቻ ናቸው። ለሥራው የሚያስፈልጉት እንደ ጭነት መኪናዎች፣ ቡልዶዘሮችና ክሬኖች ያሉት ትላልቅ መሣሪያዎች በሙሉ የመንግሥት ናቸው። ከዚህም በላይ ለሕንፃው መሥሪያ የሚያስፈልጉትን ብረታ ብረቶች፣ የኮንክሪት ብሎኮች፣ ለጣሪያ መሥሪያ የሚያገለግሉ ዕቃዎች፣ የኤሌክትሪክና የቧምቧ ዕቃዎች፣ የድምፅ መሣሪያዎችና ወንበሮች በሙሉ በአምስት ሳምንት አንዴ ብቻ በሚሠራው የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቅሞ ከኒውዚላንድ ማምጣት ሊያስፈልግ ነው። በተጨማሪም የደሴቲቱ አለታማ መሬት የግንባታውን ሥራ አስቸጋሪ የሚያደርገው ሲሆን አዳራሹ የሐሩር ክልል ዓውሎ ነፋሶችን እንዲቋቋም ተደርጎ መሠራት ነበረበት። በእርግጥም ሥራው ለማንኛውም ሰው አዳጋች ነው!
ይሁን እንጂ እዚህ ላይ አንድ ትልቅ ልዩነት አለ። የመንግሥት አዳራሽ የይሖዋ ምሥክሮች በአካባቢያቸው ለሚያቀርቡት እውነተኛ አምልኮ ማዕከል ነው። በተጨማሪም የመንግሥት አዳራሹን ለመሥራት መመሪያና እርዳታ እንዲሰጣቸው ይሖዋ አምላክን ይጠይቃሉ። (መዝሙር 56:11፤ 127:1) በኦክላንድ ውስጥ የሚገኘው የኒዩ ተወላጅ የሆኑ ወንድሞችን ያቀፈው ጉባኤ አባላትን ጨምሮ በኒውዚላንድ የሚገኙ ክርስቲያን ወንድሞች በኒዩ ውስጥ ያለውን አነስተኛ የይሖዋ ምሥክሮች ቡድን ለመርዳትና ለግንባታው ፕሮጄክት የሙሉ ነፍስ ድጋፍ ለመለገስ መጡ።
ሥራውን ለመጀመር መወሰን
በሰኔ 1994 በኒውዚላንድ ውስጥ በሚገኝ ሮቶሩአ በተባለ የመንግሥት አዳራሽ በሚሠራበት ቦታ በኒዩ ሊሠራ በታቀደው የግንባታ ሥራ ለመሳተፍ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ጥሪ ቀረበ። የሚገርመው 200 ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች በዚህ ሥራ ለመሳተፍ ፈቃደኞች መሆናቸውን ገለጹ። ከእነዚህ መካከል አናጺዎች፣ የብረት ሠራተኞች፣ የቧንቧ ሠራተኞች፣ የጣሪያ ሠራተኞች፣ ለሳኞች፣ ቀለም ቀቢዎች፣ የኤሌክትሪክ ሠራተኞች፣ የድምፅ መሣሪያ ቴክኒሻኖች፣ ግንበኞች፣ ሸክላ አንጣፊዎችና የቀን ሠራተኞች የሚገኙበት 80 ሰዎች ተመረጡ።
ወንድሞች ፕላን ካወጡ በኋላ በይሖዋ በመተማመን ሥራውን ተያያዙት። በኒዩ ጉባኤ ውስጥ ካሉት ሁለት ሽማግሌዎች አንዱ የሆነው የአካባቢው ነጋዴ የሚያስፈልጉትን ዕቃዎች ሁሉ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ዝግጅት ማድረግ ጀመረ። የራሳቸውን ወጪዎች ለመሸፈን ፈቃደኛ ለሆኑ ከባሕር ማዶ ለሚመጡት ሠራተኞች ልዩ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያና የመስተንግዶ ዝግጅት ተደረገ። ሕንፃው የሚሠራባቸው ቀናት ተወሰኑ። ፕሮጄክቱ በ20 ቀናት ውስጥ ማለትም ከመጋቢት 4 እስከ መጋቢት 23, 1995 ድረስ ማለቅ ነበረበት። የመንግሥት አዳራሹ መጋቢት 23, 1995 እንዲመረቅ ተወሰነ።
አንዳንድ ነገሮችን ለማዘጋጀት ከአንድ ሳምንት በፊት ከኒውዚላንድ የመጣው የፕሮጄክቱ ዋና አስተባባሪ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ቦታውን ለመጀመሪያ ጊዜ ስመለከተው ከፍተኛ ስጋት አደረብኝ። መሬቱ አለታማ ነው። መሠረት ለመቆፈር ብቻ ሁለት ሳምንት ይፈጃል።” ሆኖም በኋላ ራሱ እንዳመነው በአካባቢው የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች አቅልሎ ተመልክቷቸው ነበር። እንዲህ አለ፦ “የኒዩ ወንድሞች የድንጋዮቹን የተለያዩ ክፍሎች ያውቃሉ። ድንጋዩን የት ቦታ እንደሚመቱትና በትልቁ እንደሚፈረክሱት ያውቃሉ።” መሠረቱ በሁለት ቀናት ውስጥ ተጠናቀቀ!
መጋቢት 4 የኒውዚላንድ የይሖዋ ምሥክሮችን የያዘው የመጀመሪያው ዕቃ የጫነ አውሮፕላን መጣ። የኮንክሪት ሥራው ተጠናቀቀ። ሠራተኞቹ በተከታታይ እንደመጡ የተለያዩ የሥራው ክፍሎች ተጠናቀቁ። ከጠዋቱ 1:00 ሰዓት ሲሆን በዕለት ጥቅሱ ላይ አጭር ውይይት ይደረግና ሥራ ይጀመራል። አንዳንድ ወንድሞች እስከ 36 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሚደርሰው ሙቀት በቀን 12 ሰዓታት ይሠሩ ነበር። በመጨረሻም መጋቢት 23 የመንግሥት አዳራሹ የአትክልት ቦታ በተክሎች እንዲዋብ ተደረገ። ከማንጎ ዛፍ በተሠራ ማራኪ ቅስት ላይ ሕንፃውን ለይቶ የሚያሳውቀው “የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ” የሚለው ጽሑፍ ሰፈረበት።
የትብብርና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ
ፕሮጄክቱ እንዲሳካ በዋንኛነት አስተዋጽኦ ያደረገው የኒዩ ሕዝቦች ትብብር ነው። በአካባቢው የሚገኙ መንደርተኞች በወንድሞች መንፈስ ደስ ከመሰኘታቸው የተነሣ ምግብና ገንዘብ ለግሰዋል። ብዙዎች የአዳራሹን ግንባታ እንደ ራሳቸው ፕሮጄክት አድርገው ተመለክተውታል። የመንግሥት ባለ ሥልጣኖችና ነጋዴዎች ከተጠበቀው በላይ ግልጋሎቶችን አበርክተዋል። አንድ የእንጨት ሥራ ፋብሪካም የሚያስፈልጋቸውን መሣሪያዎች ለግሷቸዋል። የመርከብ ኩባንያው የሚያስፈልጉት ዕቃዎች በተገቢው ጊዜ እንዲደርሱ ለማድረግ መርከቡን በሌላ መንገድ ልኳል።
ቤታቸውንና ንብረታቸውን ያካፈሉት በኒዩ ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩትን የጠንካራ ሠራተኛነትና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ጎብኚዎቹ ከልባቸው አድንቀዋል። አንድ የግንባታው ሠራተኛ “በአካባቢው የሚገኙት እህቶች በጣም ጎበዞች ናቸው” ብሏል። እህቶች በየቀኑ በምሳ ሰዓት ከሚያቀርቡት ትኩስ ምግብ በተጨማሪ ጠዋት ጠዋት በ12:30 ቁርስ ያዘጋጁ ነበር። አንዳንዶቹ ምግብ ለማዘጋጀት ከሌሊቱ 10:30 ከእንቅልፋቸው ይነሡ ነበር። አንድ የግንባታው ሠራተኛ “ከቤታችን ይልቅ እዚህ ኒዩ ውስጥ የተመቸን ይመስለኛል” ብሏል።
መጋቢት 10 የወጣው ኒዩ ስታር የተባለው ጋዜጣ በፊተኛው ገጹ ላይ “በኒዩ የመጀመሪያው የመንግሥት አዳራሽ” በሚል ርዕስ ይህን ድርጊት ከመዘገቡም በላይ ኒውዚላንዳውያንና የኒዩ ተወላጆች አብረው ሲሠሩ የሚያሳይ ፎቶ አውጥቶ ነበር። ጋዜጣው አዳራሹ 280 ስኩየር ሜትር እንደሆነና ከ70 እስከ 100 ሰዎች እንደሚይዝ ገልጿል። ይህ ርዕስ አክሎ ሲናገር “እርግጥ ሥራው በሁለት [ሳምንታት] ውስጥ ሊጠናቀቅ የሚችል ነው። በዚህ ሁኔታ ግን ከዚህ የበለጠ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል። በአሁኑ ወቅት ሥራው ከተጀመረ ገና ሁለት ቀናት ብቻ የሆነው ቢሆንም ከታቀደለት ጊዜ በፊት መሠረቱ የተጣለ ከመሆኑም በላይ የሕንፃው ግድግዳና ጣሪያ ተዋቅሮ ጣሪያው ተመቷል።”
አንድ በአካባቢው የሚገኝ ነጋዴ በኒዩ ደሴት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በሙሉ ይህን ፕሮጄክት ቢመለከቱና ትምህርት ቢቀስሙ ምኞቱ እንደሆነ ገልጿል። ይህ ነጋዴ ሁሉም ሰው በፍቅርና በአንድነት ቢሠራ ምን ሊከናወን እንደሚችል ያሳያል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ብሏል።
በምረቃው ላይ 204 ሰዎች ተገኝተዋል። የኒዩ ወንድሞች፣ እህቶችና ልጆች የመንግሥት አዳራሹ በመሠራቱ ምክንያት የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ ያቀረቡት ሙዚቃና ውዝዋዜ በምረቃው ወቅት ለተገኙት ሁሉ ስሜት ቀስቃሽ ተሞክሮ ሆኖላቸው ነበር። ለግንባታው ሠራተኞችና ይህን ሥራ ለማከናወን እንዲቻል በመንፈሱ አማካኝነት አእምሮአቸውን፣ ልባቸውንና እጆቻቸውን ላንቀሳቀሰው ለይሖዋ ምስጋና ቀረበ።—ኢሳይያስ 40:28–31