በፖርቱጋል ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማሰራጨት
በስተ ሰሜን ከምትገኘው ከካሚኒያ አንስቶ በስተ ደቡብ እስከምትገኘው ቪላ ሪል ደ ሳንቶ አንቶንዮ ድረስ በሺህ የሚቆጠሩ በተለያዩ ሕብረ ቀለማት ያሸበረቁ የዓሣ ማጥመጃ ጀልባዎች 800 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለው በፖርቱጋል የአትላንቲክ ባሕር ጠረፍ ላይ ፈንጠር ፈንጠር ብለው ይታያሉ። ዓሣ አጥማጆች ‘በመርከቦች ወደ ባሕሩ በመሄድ’ ለብዙ መቶ ዘመናት ይህን ሥራ መተዳደሪያቸው ስላደረጉት ዓሣ የፖርቱጋሎች ዋና ምግብ ሆኗል።—መዝሙር 107:23
ባለፉት 70 ዓመታት በፖርቱጋል ውስጥ ሌላ ዓይነት ዓሣ የማጥመድ ተግባር በመካሄድ ላይ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በአሥር ሺዎች ለሚቆጠሩ ምሳሌያዊ ዓሣዎች ምሥራቹን በማዳረሱ ሥራ ተጠምደው ቆይተዋል። (ማቴዎስ 4:19) በግንቦት 1995 የመንግሥቱ አስፋፊዎች ከፍተኛ ቁጥር 44,650 ነበር። ይህም 1 አስፋፊ ለ210 ነዎሪዎች ይደርሳል ማለት ነው። በአንዳንድ ከተሞች 1 አስፋፊ ለ105 ነዎሪዎች ይደርሳል።
ብዙ ሠራተኞች ስላሉ ምሥክርነቱ በሚሰጥባቸው በአብዛኞቹ ቦታዎች የአገልግሎት ክልሎቹ በየሳምንቱ ይሸፈናሉ ማለት ይቻላል። ስለሆነም በፖርቱጋል ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ልዩ ልዩ አቀራረቦች በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋቸውን ለሌሎች ሰዎች ለማካፈል ምን ጊዜም ዝግጁዎች ናቸው። አዎን፣ በማናቸውም መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማሳወቃቸው በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይገነዘባሉ።—1 ቆሮንቶስ 9:20-23
ሃይማኖታዊ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች መርዳት
በ1991 በተደረገ የሕዝብ ቆጠራ መሠረት በፖርቱጋል ከሚገኙት 18 ዓመትና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸው ሰዎች መካከል 70 በመቶው የሮማ ካቶሊክ ተከታዮች እንደሆኑ ይናገራሉ። ሆኖም ሕዝቡ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት አነስተኛ ነው። ዦርናል ደ ኖቲስያስ የተባለው ጋዜጣ “በካቶሊክ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል ከሚታዩት በጣም አሳዛኝ የሆኑ ነገሮች አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መሃይማን መሆናቸው ነው!” ብሏል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? እስፕሪሶ የተባለው የፖርቱጋል ጋዜጣ መልሱን ይጠቁመናል። ጋዜጣው 500 ቀሳውስት በፋቲማ ውስጥ ስላደረጉት ስብሰባ ሲዘግብ እንዲህ ብሏል፦ “ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ቀሳውስት እንደ ተናገሩት ከሆነ ቄሱ የተሰጠውን ‘የአዋጅ ነጋሪነት’ ኃላፊነት ብቻ መወጣት እንዲችል ከኃላፊነቱ ውጪ ከሆኑ በርካታ ሥራዎች ራሱን ነፃ ማድረግ ያስፈልገዋል። . . . አንድ ቄስ ወንጌሉን በመስበኩ ሥራ ሙሉ በሙሉ ከተጠመደ ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል ጊዜ አይኖረውም።”
በአንፃሩ ግን በፖርቱጋል የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በማንኛውም መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማሳወቅ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። በዚህም ምክንያት ብዙ ቅን ካቶሊኮች የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በማግኘት ላይ ናቸው።
ካርሎታ ቀናተኛ የካቶሊክ አማኝና የወጣቶች ሃይማኖታዊ ማኅበር አባል ነበረች። ከዚህም ሌላ አንቶንዮ የተባለ አንድ የይሖዋ ምሥክር በሚሠራበት መዋዕለ ሕፃናት ውስጥ ታስተምር ነበር። አንቶንዮ የዘወትር አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ስለ ሆነ በምሳ ሰዓት አብረውት የሚሠሩትን ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማነጋገር ይጥር ነበር። አንድ ቀን ካርሎታ የሲኦል እሳትንና የማርያም አምልኮን በተመለከተ ጥያቄ አቀረበችለት። አንቶኒዮ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ርዕሰ ጉዳዮች በተመለከተ ምን እንደሚል አሳያት። ከዚያ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይቶች አደረጉ። ካርሎታ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካባቢው በሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በስብሰባ ላይ ስትገኝ በጣም ተገረመች። ሆኖም የስብሰባዎቹ ጊዜያት በአባልነት ትሳተፍበት ከነበረው ሃይማኖታዊ ማኅበር የስብሰባ ፕሮግራም ጋር ተጋጨባት። አንድ ውሳኔ ማድረግ እንደሚኖርባት ተገነዘበች። ምን ታደርግ ይሆን?
ካርሎታ የወጣቶች ሃይማኖታዊ ማኅበሩን አባላት በሙሉ ሰበሰበችና ከማኅበሩ ለመውጣት የወሰነችበትን ምክንያት ከመጽሐፍ ቅዱስ አስረዳቻቸው። በጥሞና ታዳምጣት ከነበረችው ስቴላ የተባለች ወጣት በስተቀር ሁሉም ውሳኔዋን ነቀፉ። በኋላ ካርሎታ ይህችን ወጣት አነጋገረቻት። ስቴላም ስለ ሕይወት አመጣጥና ዓላማ ብዙ ጥያቄዎችን አቀረበች። ካርሎታ ሕይወት እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት?a የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ሰጠቻትና ከእርሷ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረች።
በመካከሉም ካርሎታ ጥሩ መንፈሳዊ እድገት አደረገችና በሰኔ 1991 ተጠመቀች። ከስድስት ወራት በኋላም የዘወትር አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች። በግንቦት 1992 እሷና አንቶኒዮ ከተጋቡ በኋላ የምሥራቹ አገልጋዮች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው ጉባኤ ተዛውረው አንድ ላይ የአቅኚነት አገልግሎታቸውን ቀጠሉ። ስቴላስ? እርሷ ደግሞ በግንቦት 1993 የተጠመቀች ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በዘወትር አቅኚነት በማገልገል ላይ ትገኛለች።
ወጣቱ ፍራንሲስኮ በጣም ሃይማኖተኛ ነበር። እሑድ እሑድ በቅዳሴ ሥርዓት ላይ የሚገኝ ከመሆኑም በተጨማሪ ከሰዓት በኋላ ጸሎት ይደግም ነበር። በቅዳሴ ሥርዓት ወቅት የቄሱ ረዳት ሆኖ በማገልገል የንዋየ ቅዱሳት ግምጃ ቤት ኃላፊ ሆኖ ነበር። እንዲያውም አምላክ አንድ ቀን “ቅዱስ” እንዲያደርገው ጸልዮ ነበር!
ፍራንሲስኮ መጽሐፍ ቅዱስ ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። አንድ ቀን ጓደኛው መጽሐፍ ቅዱስ አዋሰው። አምላክ ይሖዋ የተባለ ስም እንዳለው ሲያውቅ በጣም ገረመው። (ዘጸአት 6:3 የ1879 እትም፤ መዝሙር 83:18 አዓት) አምላክ ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምን የሚከለክል መሆኑን በዘጸአት 20:4, 5 ሲያነብ ይበልጥ ተገረመ! ቤተ ክርስቲያኑ በምስሎች እንደተሞላ ሲመለከት ይህን ግራ የሚያጋባ ነገር እንዲያስተውል ይረዳው ዘንድ ወደ አምላክ ልባዊ ጸሎት አቀረበ። ከብዙ ቀናት በኋላ የቀድሞ የትምህርት ቤት ጓደኛውን አገኘውና የማታውን ትምህርት ለምን እንዳቋረጠ ጠየቀው።
“በአሁኑ ጊዜ ከዚያ የተሻለ ትምህርት ቤት ገብቻለሁ” በማለት ጓደኛው መለሰለት።
“የት ትምህርት ቤት? ምን እየተማርክ ነው?” በማለት ፍራንሲስኮ ጠየቀው። የጓደኛው መልስ በጣም አስገርሞት ነበር።
ጓደኛው “በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ እያጠናሁ ነው። ከእኔ ጋር ለመሄድ ትፈልጋለህ?” አለው።
ፍራንሲስኮ ለመጀመሪያ ጊዜ በስብሰባ ላይ በተገኘበት ወቅት ደስታና ፈገግታ የተሞላበት ፊት፣ ሞቅ ባለ የወዳጅነት መንፈስ እርስ በርሳቸው የሚነጋገሩ ሰዎችና ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ተቀምጠው የሚሰጠውን ትምህርት በጥሞና ሲያደምጡ ሲመለከት ማመን አቃተው።
“እዚህ ቦታ ስገኝ ገና የመጀመሪያ ጊዜዬ ቢሆንም የቤተሰቡ አባል እንደሆንኩ ተሰማኝ!” በማለት ፍራንሲስኮ በአድናቆት ተናገረ። ከዚያ በኋላ ዘወትር በስብሰባ ላይ መገኘት ጀመረ። ፍራንሲስኮ በአሁኑ ወቅት በጉባኤው ሽማግሌ ሆኖ በማገልገል ላይ ሲሆን ከባለቤቱና ከሁለት ልጆቹ ጋር በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙት በመንግሥቱ ታላላቅ ተስፋዎች በመደሰት ላይ ነው።
እውነትን ለዘመዶች መንገር
በሊዝበን አካባቢ ዘወትር አቅኚ ሆና በማገልገል ላይ የምትገኘው ማኑዌላ ዘመዶቿን ጨምሮ ለሁሉም ሰዎች በአሳቢነት መንፈስ በመመሥከሯና በመንፈሰ ጠንካራነቷ ምክንያት መንፈሳዊ ዓሣዎችን በብዛት ለማጥመድ ችላለች። እሷ ካጠመደቻቸው መንፈሳዊ ዓሣዎች መካከል ካራቴና የጦር መሣሪያዎች አጠቃቀም የተማረው ጆዜ ኢድዋርዶ የተባለው ሥጋዊ ወንድሟ ይገኝበታል። በተደጋጋሚ ጊዜያት ሕግ ይጥስ ስለ ነበር በመጨረሻ በ22 ወንጀሎች ተከሰሰና የ20 ዓመት እስራት ተፈረደበት። ኃይለኛ ተደባዳቢ በመሆኑ ምክንያት ሌሎች እስረኞች እንኳ ይፈሩት ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት ክፍል ውስጥ ለብቻው ታስሮ ነበር።
ማኑዌላ ጆዜ ኢድዋርዶን ለሰባት ዓመታት እየተመላለሰች በትዕግሥት ብትጠይቀውም ሁልጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክቷን አይቀበልም ነበር። በመጨረሻ ሕይወት እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? የተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ታትሞ ሲወጣ መጽሐፉን ወሰደ። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረለት። ወዲያውኑ ከፍተኛ የጠባይ ለውጥ ማሳየት ጀመረ። ከአንድ ሳምንት በኋላ ለ200 እስረኞች፣ በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ ለሌሎች 600 እስረኞች ምሥክርነት ሰጠ። እንዲያውም በሌሎቹ የእስር ቤቱ ሕንፃዎች ውስጥ የሚገኙ እስረኞችን ሄዶ እንዲያነጋግር ፈቃድ ተሰጠው። አስደናቂ የባሕሪይ ለውጥ በማሳየቱ ምክንያት እስራቱ ወደ 15 ዓመት ዝቅ እንዲል ተደረገለት። 10 ዓመት ታስሮ ከቆየ በኋላ በአመክሮ ተፈታ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አምስት ዓመታት አልፈዋል። በአሁኑ ጊዜ ጆዜ ኤድዋርዶ የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር ሲሆን በጉባኤው ውስጥ በዲቁና በማገልገል ላይ ነው። በእርግጥም ሁኔታው ‘ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር እንደ ተቀመጠ’ ያህል ነው!—ኢሳይያስ 11:6
ማኑዌላ ለቤተሰቧ ለመመሥከር የምታደርገውን ጥረት ስለገፋችበት ባሏንና ሌሎች አራት የቤተሰቧ አባላት በይሖዋ አገልግሎት እንዲካፈሉ በመርዳት ደስታ አግኝታለች። በአሁኑ ጊዜ ባሏ ዲያቆን ነው።
“በእርግጫና በጥፊ እያልኩ አባርራቸዋለሁ”
ከሊዝበን ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቦታ የምትኖረውን ማርያ ዱ ካርሞን የይሖዋ ምሥክሮች ቤቷ ድረስ መጥተው አነጋገሯት። የነገሯት ነገር ስላስደሰታት አንቶኒዮ የተባለው ባሏን እቤቷ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግ ትችል እንደሆነ ጠየቀችው። “ይህ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው! የይሖዋ ምሥክሮችን ቤታችን ውስጥ ካገኘኋቸው በእርግጫና በጥፊ እያልኩ አባርራቸዋለሁ” ሲል መለሰላት። በነገራችን ላይ አንቶኒዮ የካራቴ አስተማሪ ከመሆኑም በተጨማሪ ሦስተኛ ዲግሪ ብላክ ቤልት ነበረው። ስለዚህ ማርያ ዱ ካርሞ ሌላ ቦታ ለማጥናት ወሰነች።
ከጊዜ በኋላ አንቶኒዮ ለስምንት ቀናት የካራቴ ኮርስ ለመከታተል ወደ እንግሊዝ አገር ለመሄድ ተሰናዳ፤ ማርያ ዱ ካርሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ በጥንቃቄ ሻንጣው ውስጥ ከተተችው።b አንቶኒዮ በጉዞው ወቅት ብዙ ጊዜ ስለ ነበረው መጽሐፉን አነበበው። ወደ ቤቱ በሚመለስበት ወቅት በበረራ ወቅት ከባድ አውሎ ነፋስ አውሮፕላኑን በኃይል አንገጫገጨው። አውሮፕላኑ ለማረፍ እንኳ ተቸግሮ ነበር። አንቶኒዮ በሕይወቱ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ይሖዋ ጸለየ።
አንቶኒዮ ወደ ቤቱ ሲመለስ ባለቤቱን የሚያስጠኗት የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ እንዲገኝ ጋበዙት። በስብሰባው ላይ ለመገኘት ተስማማ። በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ ወዳጃዊ ስሜት ያላቸው እንደሆኑ ተገነዘበ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር ለማድረግ ዝግጅት ተደረገ። ከጥቂት ጊዜ በኋላም አንቶኒዮ አንድ ውሳኔ ማድረግ እንዳለበት ተገነዘበ። በዚህም ምክንያት ካራቴ ማስተማሩን አቆመና ተማሪዎቹን አሁንም ሆነ ለዘላለም ሰላማዊ ሕይወት መኖር የሚቻልበትን መንገድ ማስተማር ጀመረ። በአሁኑ ጊዜ ከእነርሱ መካከል አንዱ የተጠመቀ ክርስቲያን ሆኗል። እርሱም ብላክ ቤልት የነበረው ሰው ነው።
አንቶኒዮ በሚያዝያ 1991 ተጠመቀ። ከተጠመቀ በኋላ በነጋታው የረዳት አቅኚነት አገልግሎት ጀመረ። ከስድስት ወራት በኋላ የዘወትር አቅኚ ሆነ። ብዙም ሳይቆይ 12 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት ጀመረ። በሐምሌ 1993 በጉባኤው ውስጥ ዲያቆን ሆኖ ተሾመ።
በተደጋጋሚ ጊዜያት በተሸፈኑ የአገልግሎት ክልሎች
በአገሪቱ ውስጥ በብዙ ቦታዎች የአገልግሎት ክልሎች በየሳምንቱ ይሸፈናሉ ማለት ይቻላል። ምሥክሮቹ “ዓሣ የማጥመድ” ሥራዎቻቸውን ውጤታማ በሆነ መንገድ የሚያከናውኑት እንዴት ነው?
ዥዋኡ በየቤቱ የሚኖረውን እያንዳንዱን ሰው ለማግኘት ይጥራል። አንዲትን ሴት ሲያነጋግር በቤቱ ውስጥ ሌሎች ሰዎች ይኖሩ እንደሆነ ጠየቃት። ሴትየዋ ባለቤቷና ሁለት ልጆቿ አብረዋት እንደሚኖሩ ገልጻ ሥራ ስላላቸው ቤት ሊገኙ የሚችሉት ማታ ማታ ብቻ እንደሆነና እነርሱን በቀላሉ ማግኘት እንደማይቻል ነገረችው። ስለዚህ ዥዋኡ ምሥክርነት መስጠቱን ቀጠለና በዚያ አካባቢ የሚኖሩትን ሌሎች ሰዎች አነጋገረ። ከአንድ ሰዓት ተኩል በኋላ አንድ ሰው ወደ እርሱ መጣ።
ሰውዬው ዥዋኡን “ከእኔ ጋር ለመነጋገር እንደምትፈልግ ገልጸህ ነበር። እባክህ ምን እንደምትፈልግ ንገረኝ” አለው።
“ይቅርታ አድርግልኝ፣ አላውቅህም፤ ማነህ?” በማለት ዥዋኡን በመገረም መለሰለት።
“አንቶኒዮ እባላለሁ። እዚህ አካባቢ ነው የምኖረው። ሌሎቹን የቤተሰባችንን አባላት ለማነጋገር እንደምትፈልግ ለእናቴ ነግረሃት ነበር። ስለዚህ ምን እንደፈለግህ ለማወቅ መጣሁ።”
ዥዋኡ ለአንቶኒዮ ጥሩ ምሥክርነት ከሰጠው በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረለት። ከሁለተኛው ጥናት በኋላ አንቶኒዮ ጥናቱ በሳምንት ሁለት ጊዜ ሊደረግለት ይችል እንደሆነ ጠየቀ። በአራተኛው ወር በሰፈሩ ውስጥ ከዥዋኡ ጋር ምሥራቹን መስበክ ጀመረ። ከዚያም ከሦስት ወራት በኋላ ተጠመቀ። በቅርቡ ደግሞ እናቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምራለች። በአገልግሎት ወቅት የቤተሰብ አባሎችን በሙሉ ለማነጋገር መሞከር ምን ያህል አስፈላጊ ነው!
እንደነዚህ ያሉ አስደሳች ተሞክሮዎች በፖርቱጋል ባሕር ውስጥ አሁንም ቢሆን ብዙ መንፈሳዊ ዓሣዎችን ማጥመድ እንደሚቻል ያሳያሉ። ይሖዋ እዚያ የሚገኙትን ጠንክረው የሚሠሩ ምሥክሮች በሺህ የሚቆጠሩ እድገት የሚያደርጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በመስጠት ባርኳቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለሁሉም ሰዎች ለማሳወቅ የሚያስችሉ ሌሎች ተጨማሪ መንገዶችን መፈለጋቸውን በመቀጠላቸው ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ክርስቶስ በሁሉም መንገድ ይሰበካል’ በማለት ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች የተናገራቸው ቃላት በአሁኑ ጊዜ በፖርቱጋል በመፈጸም ላይ ናቸው።—ፊልጵስዩስ 1:18
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a መጽሐፉ የታተመው ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ነው።
b መጽሐፉ የታተመው ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ነው።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ስፔይን
ፖርቱጋል
[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በፖርቱጋል የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማሳወቅ በማንኛውም አጋጣሚ ይጠቀማሉ