የመተማመን ስሜታችሁን እስከ መጨረሻ አጽንታችሁ ያዙ
በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ውስጥ በበረራ ላይ ያለች አንዲት አነስተኛ አውሮፕላን በዓይነ ሕሊናችሁ ተመልከቱ። የአውሮፕላኗ አብራሪ ጥቅጥቅ ባለ ደመና ስለተሸፈነ መሬቱ አይታየውም፣ የት እንዳለም አያውቅም። ከአውሮፕላኗ የፊት ለፊት መስተዋት ውጭ ያለ ምንም ነገር የማይታየው ቢሆንም ጉዞውን በሰላም እንደሚጨርስ እርግጠኛ ነው። እንዲህ እንዲተማመን ያደረገው ምንድን ነው?
ጥቅጥቅ ባለ ደመና ውስጥም ሆነ በጨለማ ጊዜ ለመጓዝ የሚያስችሉት ትክክለኛ የበረራ መሣሪዎች አሉት። በበረራው ላይ እንዳለ፣ በተለይም ወደ አውሮፕላን ማረፊያው ሲጠጋ በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ የሚተላለፍ አቅጣጫ ጠቋሚ የመብራት ምልክቶችን ከመቀበሉም በተጨማሪ በመሬት ላይ ካሉ የአውሮፕላን ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ጋር በሬዲዮ ይነጋገራል።
እኛም በተመሳሳይ መንገድ የዓለም ሁኔታ በየዕለቱ ይበልጥ እየጨለመ ቢሄድም የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ተማምነን መጠበቅ እንችላለን። ከዚህ ክፉ ሥርዓት ለማለፍ የምናደርገው ጉዞ አንዳንዶች ካሰቡት በላይ ረዝሞ ይሆናል። ይሁን እንጂ በትክክለኛው መንገድና ጊዜ ላይ እንደምንገኝ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። እርግጠኛ ለመሆን የምንችለው ለምንድን ነው? የሰው ዓይን ሊያይ የማይችለውን ነገር ለማወቅ የሚያስችል መመሪያ ስላለን ነው።
የአምላክ ቃል ‘ለመንገዳችን ብርሃን’ ከመሆኑም በላይ ‘የታመነና ተሞክሮ የሌላቸውን ጠቢባን’ የሚያደርግ ነው። (መዝሙር 19:7 አዓት፤ 119:105) አንድ የአውሮፕላን አብራሪ መከተል የሚኖርበትን የበረራ መስመር እንደሚጠቁሙ በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ እንደሚተላለፉ የመብራት ምልክቶች ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስም ለመድረስ ወዳሰብንበት ቦታ አለምንም ሳንካ እንድንደርስ የሚያስችለንን ግልጽ መመሪያ ይሰጣል። ይሁን እንጂ ከመለኮታዊ አመራር እንድንጠቀም ከተፈለገ በዚህ መመሪያ ላይ ሙሉ ትምክህት ሊኖረን ይገባል።
ጳውሎስ ለዕብራውያን በጻፈው ደብዳቤ ላይ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ‘በመጀመሪያ የነበራቸውን የመተማመን ስሜት አጽንተው እንዲይዙ’ መክሯል። (ዕብራውያን 3:14) እምነት ወይም ትምክህት አጽንተን ካልያዝነው ሊናወጥ ይችላል። በዚህም ምክንያት በይሖዋ ላይ ያለንን የመተማመን ስሜት እስከ መጨረሻው አጽንተን ልንይዝ የምንችለው እንዴት ነው? የሚል ጥያቄ ይነሳል።
እምነታችሁ በተግባር ይገለጽ
አንድ አውሮፕላን አብራሪ መሬቱ ሳይታየው በበረራ መሣሪያዎቹና መሬት ላይ በሚገኙ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ብቻ እየተመራ ማብረር ከመጀመሩ በፊት የተሟላ ሥልጠናና በርካታ ሰዓቶች የሚፈጅ የበረራ ልምምድ ማግኘት ያስፈልገዋል። በተመሳሳይም አንድ ክርስቲያን በተለይ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ በይሖዋ አመራር ላይ ያለውን የመተማመን ስሜት ጠብቆ ለመኖር ሳያቋርጥ እምነቱን በተግባር መግለጽ ይኖርበታል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል፦ “ነገር ግን፦ አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ ተብሎ አንደ ተጻፈ ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን፣ እኛ ደግሞ እናምናለን ስለዚህም እንናገራለን።” (2 ቆሮንቶስ 4:13) ስለዚህ ስለ አምላክ የምሥራች በምንናገርበት ጊዜ እምነታችንን በተግባር መግለጻችንና ማጠንከራችን ነው።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለአራት ዓመታት ያህል በማጎሪያ ካምፕ ታስራ የቆየችው ማግዳሌና እንደሚከተለው በማለት የስብከቱ ሥራ ስላለው ጠቀሜታ ገልጻለች፦ “እናቴ ጠንካራ እምነት እንዲኖረን ከፈለግን ስለ ሌሎች ሰዎች መንፈሳዊ ደህንነት ማሰብ እንደሚያስፈልገን አስተምራኝ ነበር። ምን ዓይነት ስሜት ተሰምቶን እንደነበረ የሚያሳይ አንድ አጋጣሚ ትዝ ይለኛል። እኔና እናቴ ከራቨንስብሩክ ማጎሪያ ካምፕ ከተለቀቅን በኋላ ዓርብ ቀን ቤታችን ደረስን። ከሁለት ቀን በኋላ፣ እሁድ ዕለት ማለት ነው፣ ከወንድሞች ጋር ከቤት ወደ ቤት ለመስበክ ተሰማራን። ሌሎች ሰዎች በአምላክ ተስፋዎች ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖራቸው ለመርዳት ጥረት ካደረግን እነዚህ ተስፋዎች ለእኛ ለራሳችን ይበልጥ እውን ሆነው እንደሚታዩን እርግጠኛ ነኝ።”—ከሥራ 5:42 ጋር አወዳድር።
የመተማመን ስሜታችንን እስከ መጨረሻው ድረስ አጽንተን ለመያዝ በሌሎች መስኮችም መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠይቅብናል። የግል ጥናት ሌላው እምነትን የሚያጠነክር ግሩም እንቅስቃሴ ነው። የቤርያን ሰዎች ብንመስልና በየቀኑ ቅዱሳን ጽሑፎችን በትጋት ብንመረምር ‘ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችን ያን ትጋት እስከ መጨረሻ ለማሳየት እንችላለን።’ (ዕብራውያን 6:11፤ ሥራ 17:11) የግል ጥናት ጊዜና ቆራጥነት እንደሚጠይቅ አይካድም። ጳውሎስ ዕብራውያንን ‘ዳተኛ’ ወይም ሰነፍ መሆን አደገኛ እንደሆነ ያስጠነቀቀው ለዚህ ሊሆን ይችላል።—ዕብራውያን 6:12
ዳተኝነት በብዙ የሕይወት መስኮች ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ሰሎሞን “በእጅ መታከት ቤት ያፈስሳል” ብሏል። (መክብብ 10:18) በጊዜው ያልተጠገነ ጣሪያ ውሎ አድሮ ማፍሰሱ አይቀርም። በመንፈሳዊ ሁኔታም እጃችን ከዛለና እምነታችንን ካላጠነከርን የተለያዩ ጥርጣሬዎች ሰርገው ይገቡብናል። በአንጻሩ ደግሞ የአምላክን ቃል አዘውትሮ ማሰላሰልና ማጥናት እምነታችንን ያፋፋዋል፣ ከአደጋም ይጠብቀዋል።—መዝሙር 1:2, 3
ትምክህታችንን በተሞክሮ መገንባት
እርግጥ ነው፣ አንድ አብራሪ የበረራ መሣሪያዎቹ አስተማማኝ መሆናቸውን የሚያውቀው ከተሞክሮውና ከጥናቱ ነው። በተመሳሳይም በይሖዋ ላይ ያለን ትምክህት የሚያድገው በሕይወታችን ውስጥ ይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ እንደሚያደርግልን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ስንመለከት ነው። ኢያሱ ይህን ተመልክቶ ስለነበረ ወገኖቹ ለነበሩት እስራኤላውያን እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እናንተም እግዚአብሔር ስለ እናንተ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ በልባችሁ ሁሉ በነፍሳችሁም ሁሉ እወቁ፣ ሁሉ ደርሶላችኋል። ከእርሱም አንድ ነገር አልቀረም።”—ኢያሱ 23:14
በፊሊፒንስ የምትገኝ ሆሴፊና የምትባል አንዲት ባለ ትዳር እህት ይህንን ከግል ሕይወትዋ ለማወቅ ችላለች። እውነትን ከማወቋ በፊት ሕይወቷ ምን ይመስል እንደነበረ እንዲህ በማለት ትገልጻለች፦ “ባለቤቴ በጣም ይጠጣ ነበር። ሲሰክር በጣም ይቆጣና ይደበድበኛል። በተጨማሪም ደስታ የራቀው ትዳራችን የልጃችንን ሕይወት ማበላሸት ጀምሮ ነበር። እኔና ባለቤቴ የየራሳችን ሥራ የነበረን ከመሆኑም በላይ ጥሩ ገቢ እናገኝ ነበር። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ደመወዛችንን በቁማር እናጠፋዋለን። ባለቤቴ ብዙ ጓደኞች ነበሩት። አብዛኞቹ ግን ወዳጅነቱን የሚፈልጉት መጠጥ እንዲገዛላቸው ብቻ ነበር። እንዲያውም አንዳንዶቹ በእርሱ ለመሳቅ ሲሉ እንዲሰክር ያደርጉት ነበር።
“ይሖዋን ስናውቅና የይሖዋን ምክሮች ልብ ማለት ስንጀምር ግን ሁኔታዎች መለወጥ ጀመሩ። አሁን ባለቤቴ አይጠጣም። ቁማር መጫወት አቁመናል፣ የሚወዱንና የሚረዱን እውነተኛ ጓደኞችም አሉን። ትዳራችን ደስታ የሰፈነበት ሆኗል። ልጃችንም አድጎ ጥሩ ጎረምሳ ሆኗል። አሁን እንደ ቀድሞው ብዙ ሰዓት አንሠራም። ግን ከቀድሞው የበለጠ ገንዘብ አለን። ይሖዋ ልጁን በጣም እንደሚወድ አባት እንደሆነና ሁልጊዜ በትክክለኛው አቅጣጫ እንደሚመራን ከራሳችን ተሞክሮ ተምረናል።”
የአውሮፕላን አብራሪዎች በሬዲዮ ከሚያገኙት መልእክት ወይም የበረራ መቆጣጠሪያ ሰሌዳውን በመመልከት የበረራ መስመራቸውን ማስተካከል እንደሚኖርባቸው የሚገነዘቡባቸው ጊዜያት አሉ። እኛም በተመሳሳይ የይሖዋን መመሪያ በመቀበል አቅጣጫችንን መለወጥ ያስፈልገን ይሆናል። “ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ፦ መንገዱ ይህች ናት፣ በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ።” (ኢሳይያስ 30:21) ከቃሉና ከድርጅቱ ከመንፈሳዊ አደጋዎች እንድንጠነቀቅ የሚያሳስቡ ምክሮች እናገኛለን። ከእነዚህ አደጋዎች አንዱ ባልንጀርነትን የሚመለከት ነው።
ባልንጀሮች ከመንገድ ሊያስወጡን ይችላሉ
አንዲት ትንሽ አውሮፕላን በየጊዜው የበረራ መስመርዋ ካልተስተካከለላት በቀላሉ አቅጣጫዋን ልትስት ትችላለች። ክርስቲያኖችም በተመሳሳይ ውጪያዊ ተጽእኖዎች በተደጋጋሚ ያጋጥሟቸዋል። የምንኖረው ብዙዎች መንፈሳዊ በሆኑ ነገሮች ላይ በሚያሾፉበት፣ ለገንዘብና ለተድላ ብዙ ትኩረት በሚሰጡበት ሥጋዊ ዓለም ውስጥ ነው። መጨረሻው ቀን “አስጨናቂ” እንደሚሆን ጳውሎስ ጢሞቴዎስን አስጠንቅቆት ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ወጣቶች በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘትና ተወዳጆች ለመሆን ስለሚፈልጉ በተለይ ለመጥፎ ባልንጀርነት የተጋለጡ ናቸው።—2 ጢሞቴዎስ 2:22
አሥራ ሰባት ዓመት የሆናት አማንዳ እንዲህ በማለት ትገልጻለች፦ “እምነቴ ለጥቂት ጊዜ በክፍል ጓደኞቼ ምክንያት በመጠኑ ተዳክሞ ነበር። ሃይማኖቴ ነፃነት የሚያሳጣና ምክንያታዊነት የጎደለው እንደሆነ ሁልጊዜ ይናገሩ ስለነበረ ወደኋላ ማለት ጀምሬ ነበር። ይሁን እንጂ ወላጆቼ ክርስቲያናዊ መመሪያዎች ከጉዳት የሚጠብቁ እንጂ የሚጨቁኑ እንዳልሆኑ እንድገነዘብ አስችለውኛል። በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሥርዓቶች ከቀድሞዎቹ የትምህርት ጓደኞቼ የተሻለ የሚያረካ ኑሮ እንድኖር እንዳስቻሉኝ ልገነዘብ ችያለሁ። ከልባቸው በሚያስቡልኝ ወላጆቼና በይሖዋ ላይ መታመን እንደሚኖርብኝ ተምሬያለሁ። በተጨማሪም በአቅኚነት አገልግሎት በመደሰት ላይ ነኝ።”
ወጣቶችም ሆንን ሽማግሌዎች በእምነታችን ላይ የሚሳለቁና የሚያሾፉ ሰዎች ያጋጥሙናል። እነዚህ ሰዎች አዋቂዎችና ሊቃውንት መስለው ሊታዩ ቢችሉም በአምላክ ዓይን ሲታዩ ግን ሥጋውያንና መንፈሳዊነት የጎደላቸው ናቸው። (1 ቆሮንቶስ 2:14) በጳውሎስ ዘመን በቆሮንቶስ ከተማ በዓለም አመለካከት ጠቢባን የሆኑ ተጠራጣሪዎች ነበሩ። የእነዚህ ፈላስፎች ትምህርት አንዳንድ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በትንሣኤ ተስፋ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጡ ሳያደርጋቸው አልቀረም። (1 ቆሮንቶስ 15:12) ሐዋርያው ጳውሎስ “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ሲል አስጠንቅቋል።—1 ቆሮንቶስ 15:33
በአንጻሩ ግን ጥሩ ባልንጀርነት በመንፈሳዊ ያጠነክረናል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የእምነት ኑሮ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ለመወዳጀት የሚያስችል አጋጣሚ እናገኛለን። እውነትን በ1939 ያወቀው ኖርማን አሁንም የሚያገኛቸውን ክርስቲያኖች የሚያጽናና ወንድም ነው። በመንፈሣዊ ነገሮች ላይ ያለው ትኩረት ሳይደበዝዝ የቆየው ለምንድን ነው? “ስብሰባዎችና ከታማኝ ወንድሞች ጋር መቀራረብ በጣም አስፈላጊ ናቸው” ሲል ይመልሳል። “እንዲህ ያለው ባልንጀርነት በአምላክ ድርጅትና በሰይጣን ድርጅት መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ እንድመለከት ረድቶኛል።”
የባለጠግነት አታላይነት
ብራይን የተባለ ብዙ ልምድ ያለው አውሮፕላን አብራሪ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “አንድ አብራሪ የራሱን ግምታዊ አስተሳሰብ በመከተል መሣሪያዎቹ የሚሉትን አላምንም ሊል ይችላል። ብዙ ልምድ ያላቸው የጦር አውሮፕላን አብራሪዎች መሣሪያዎቻቸው የሚነግሯቸውን ከመቀበል ይልቅ በራሳቸው ግምታዊ አስተሳሰብ በመመራታቸው መሬት ላይ ያሉ መብራቶች ከዋክብት መስለዋቸው አውሮፕላናቸውን ገልብጠው እንዳበረሩ ታውቋል።”
በተመሳሳይም የገዛ ራሳችን የራስ ወዳድነት ባሕርይ በመንፈሳዊ ሁኔታ ሊያሳስተን ይችላል። ኢየሱስ ባለጠግነት ‘የማታለል ኃይል’ እንዳለው ተናግሯል። ጳውሎስም ‘ገንዘብን መውደድ ብዙዎችን ከእምነት እንዳስወጣ’ በመግለጽ አስጠንቅቋል።—ማርቆስ 4:19፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:10
ቁሳዊ ሀብት ማካበትን ግብ ማድረግ እንደሚያብለጨልጭ አታላይ መብራት ወደተሳሳተ አቅጣጫ ሊመራን ይችላል። ‘ተስፋ በምናደርገው ነገር ከመደሰት ይልቅ’ ይህ አላፊ ዓለም ይታይልኝ በሚላቸው ነገሮች ልንሳብ እንችላለን። (ዕብራውያን 11:1፤ 1 ዮሐንስ 2:16, 17) የብልጽግና ኑሮ ለመኖር ‘ቆርጠን ከተነሳን’ መንፈሳዊ እድገት ለማግኘት የሚያስችለን ጊዜ እናጣለን።—1 ጢሞቴዎስ 6:9፤ ማቴዎስ 6:24፤ ዕብራውያን 13:5
ፓትሪክ የሚባል ወጣት ባለትዳር እርሱና ሚስቱ የተሻለ ኑሮ ለመኖር ሲሉ መንፈሳዊ ግቦቻቸውን መሥዋዕት አድርገው እንደነበረ ይናገራል። እንዲህ ሲል ያብራራል፦ “በጉባኤያችን ውስጥ ያሉ ትላልቅ ምቹ መኪናዎችና ቆንጆ ቤቶች ያሏቸው ወንድሞች የኑሮ ደረጃ አስተሳሰባችንን ነክቶት ነበር። በመንግሥቱ ተስፋ ላይ ማተኮራችንን ባንተውም እግረ መንገዳችንን የተመቻቸ ኑሮ ብንኖር ክፋት የለውም ብለን አሰብን። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ እውነተኛ ደስታ የሚገኘው ይሖዋን ከማገልገልና መንፈሣዊ ዕድገት በማድረግ እንደሆነ ተገነዘብን። አሁን ቀለል ያለ ኑሮ እንኖራለን። በሥራ የምናሳልፈውን ጊዜ ቀንሰን የዘወትር አቅኚዎች ሆነናል።”
እምነት ተቀባይ በሆነ ልብ ላይ ይመካል
በተጨማሪም በይሖዋ ላይ ያለንን የመተማመን ስሜት በመገንባት ረገድ ተቀባይ የሆነ ልብ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። እርግጥ፣ “እምነት ተስፋ ስለ ምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፣ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ [ወይም “አምነን እንድንቀበል የሚያደርግ” የአዓት የግርጌ ማስታወሻ] ነው።” (ዕብራውያን 11:1) ነገር ግን ተቀባይ የሆነ ልብ ካልኖረን እርግጠኞች ለመሆን አንችልም። (ምሳሌ 18:15፤ ማቴዎስ 5:6) በዚህም ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ ‘እምነትም ለሁሉ አይሆንም’ ሲል አስጠንቅቋል።—2 ተሰሎንቄ 3:2
ታዲያ ልባችን ለምናገኛቸው አሳማኝ ማስረጃዎች ተቀባይ እንዲሆን ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው? አምላካዊ የሆኑ ባሕርያትን፣ እምነት የሚያበለጽጉና የሚቀሰቅሱ ባሕርያትን በመኮትኮት ነው። ጴጥሮስ ‘ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ ላይ በጎነትን፣ እውቀትን፣ ራስን መግዛትን፣ መጽናትን፣ ለአምላክ ማደርን፣ የወንድማማች መዋደድን፣ ፍቅርን ጨምሩ’ ብሏል። (2 ጴጥሮስ 1:5-7፤ ገላትያ 5:22, 23) በአንጻሩ ግን ኑሯችን በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረተ ከሆነ ወይም ይሖዋን የምናገለግለው ለይስሙላ ያህል ብቻ ከሆነ እምነታችን ያድጋል ብለን ልንጠብቅ አንችልም።
ዕዝራ የይሖዋን ቃል ለማንበብና ሥራ ላይ ለማዋል ‘ልቡን አዘጋጅቶ’ ነበር። (ዕዝራ 7:10) ሚክያስም ተቀባይ ልብ ነበረው። “እኔ ግን እግዚአብሔርን እጠባበቃለሁ፣ የሚያድነኝን አምላክ ደጅ እጠናለሁ፣ እርሱም ይሰማኛል” ብሏል።—ሚክያስ 7:7
ቀደም ብላ የተጠቀሰችው ማግዳሊናም ይሖዋን በትዕግሥት ደጅ በመጥናት ላይ ነች። (ዕንባቆም 2:3) እንዲህ ትላለች፦ “አሁን መንፈሳዊውን ገነት አግኝተናል። ሁለተኛ ደረጃ የሆነው ምድራዊ ገነት በቅርቡ ይመጣል። ከዚያ በፊት ግን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከእጅግ ብዙ ሰዎች ጋር በመተባበር ላይ ናቸው። ብዙ ሰዎች ወደ አምላክ ድርጅት ሲጎርፉ መመልከት በጣም ያስደስተኛል።”
የሚያድነንን አምላክ ደጅ መጥናት
የመተማመን ስሜታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ለመያዝ እምነታችንን በሥራ ማሳየትና ከይሖዋና ከይሖዋ ድርጅት የምናገኘውን መመሪያ በጥንቃቄ ማዳመጥ ያስፈልገናል። በዚህ ረገድ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይገባናል። አንድ አብራሪ ከረዥምና አድካሚ ጉዞ በኋላ የደመናውን ቁልል ሰንጥቆ ሲወርድ ልባዊ እርካታ ይሰማዋል። አረንጓዴ የሆነው መሬት እንኳን ደህና መጣህ ብሎ ሲቀበለው ይታየዋል። የአውሮፕላን ማረፊያው ማኮብኮቢያ ሜዳ እጁን ዘርግቶ ይቀበለዋል።
እኛም ተመሳሳይ የሆነ አስደሳች ተሞክሮ ይጠብቀናል። ይህ በድቅድቅ ጨለማ የተዋጠ ክፉ ዓለም ቦታውን ጽድቅ ለሰፈነበት አዲስ ዓለም ይለቃል። መለኮታዊ የሆነ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ይጠብቀናል። “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፣ ተስፋዬን በአንተ ላይ አደርጋለሁ፣ ከልጅነቴ ጀምሮ መታመኛዬ አንተ ነህ። በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በአንተ እደገፋለሁ፣ . . . እኔም ዘወትር አመሰግንሃለሁ” የሚለውን የመዝሙራዊ ቃል ብንፈጽም እዚህ አዲስ ዓለም ለመድረስ እንችላለን።—መዝሙር 71:5, 6 የ1980 ትርጉም