የእባቡ ዘር፣ እንዴት ተጋለጠ?
“በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ።”—ዘፍጥረት 3:15
1. (ሀ) ይሖዋ ደስተኛ አምላክ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) እርሱ ካለው ደስታ ተካፋይ እንድንሆን ምን ያደረገው ነገር አለ?
ይሖዋ ደስተኛ አምላክ የሆነው አለበቂ ምክንያት አይደለም። ታላቁና ዋነኛው የበጎ ነገሮች ምንጭ ነው። በተጨማሪም ዓላማውን ሊያሰናክል የሚችል አንድም ነገር የለም። (ኢሳይያስ 55:10, 11፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:11 አዓት፤ ያዕቆብ 1:17) አገልጋዮቹ ከደስታው እንዲካፈሉ ስለሚፈልግም ሊያስደስቷቸው የሚችሉ በርካታ ዝግጅቶች አድርጓል። በዚህም ምክንያት የሰው ልጅ ታሪክ እጅግ ጨልሞ ከነበረበት ከኤደን ዓመፅ በኋላ የወደፊቱን ጊዜ ብሩህ አድርገን እንድንጠባበቅ የሚያስችል ዝግጅት አድርጎልናል።—ሮሜ 8:19-21
2. ይሖዋ ኤደን ውስጥ ዓመፅ በፈጸሙት አዳምና ሔዋን ላይ ሲፈርድ ልጆቻቸው ተስፋ እንዲኖራቸው ዝግጅት ያደረገው እንዴት ነበር?
2 ከይሖዋ መንፈሳዊ ልጆች አንዱ አምላክን በመቃወምና ስሙን በማጥፋት ራሱን ሰይጣን ዲያብሎስ አደረገ። የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ፍጡራን የሆኑት አዳምና ሔዋን በእርሱ ቁጥጥር ሥር ወደቁና ይሖዋ በግልጽ ያስቀመጠውን ሕግ ጣሱ። የሚገባቸውን የሞት ፍርድ ተቀበሉ። (ዘፍጥረት 3:1-24) ሆኖም ይሖዋ በእነዚህ ዓመፀኞች ላይ በፈረደበት ጊዜ ከአዳምና ከሔዋን አብራክ የሚወጡ ልጆች ተስፋ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ዝግጅት አድርጓል። በምን መንገድ? ዘፍጥረት 3:15 ላይ እንደተመዘገበው ይሖዋ እንዲህ አለ፦ “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ።” ይህ ትንቢት መላውን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም በቀድሞው ዘመን የተፈጸሙትንና ወደፊት የሚፈጸሙትን ዓለምንም ሆነ የይሖዋ አገልጋዮችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ለመረዳት የሚያስችል ቁልፍ ነው።
የትንቢቱ ትርጉም
3. በዘፍጥረት 3:15 ላይ በተገለጸው መሠረት (ሀ) እባቡ (ለ) “ሴቲቱ” (ሐ) የእባቡ “ዘር” (መ) የሴቲቱ “ዘር” ምን እንደሚያመለክት ግለጽ።
3 የዚህን ትንቢት ትርጉም በተሟላ ሁኔታ ለመረዳት የትንቢቱን የተለያዩ ክፍሎች መርምሩ። በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተጠቀሰው ዝቅተኛ እንስሳ የሆነው ተራ እባብ ሳይሆን በእባቡ የተገለገለው ፍጡር ነው። (ራእይ 12:9) “ሴቲቱ” ደግሞ በምድር ላይ ያሉት በመንፈስ የተቀቡ የይሖዋ አገልጋዮች እናት የሆነችው የይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት እንጂ ሔዋን አይደለችም። (ገላትያ 4:26) የእባቡ “ዘር” ማለትም የሰይጣን ዘር ወይም ልጆቹ ደግሞ አጋንንት፣ የሰይጣንን ባሕርይ የሚያንጸባርቁና ለሴቲቱ “ዘር” የጠላትነት መንፈስ የሚያሳዩ ሰዎች እንዲሁም ሰብዓዊ ድርጅቶች ናቸው። (ዮሐንስ 15:19፤ 17:15) ዋነኛው የሴቲቱ “ዘር” በ29 እዘአ በመንፈስ ቅዱስ የተቀባው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ‘ከመንፈስና ከውኃ ዳግም የተወለዱት’ ከክርስቶስ ጋር የሰማያዊ መንግሥት ወራሾች የሆኑት 144,000 ክርስቲያኖች የዚህ ተስፋ የተሰጠበት ዘር ሁለተኛ ደረጃ ክፍሎች ናቸው። እነዚህ በሴቲቱ ዘር ላይ መጨመር የጀመሩት በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ ነው።—ዮሐንስ 3:3, 5፤ ገላትያ 3:16, 29
4. ዘፍጥረት 3:15 ምድር ከኃጢአትና ከሞት ነፃ በሆኑ ሰዎች የተሞላች ገነት እንደምትሆን የሚናገረው እንዴት ነው?
4 በተንኮል የሰው ልጅ ገነትን እንዲያጣ ያደረገው ፍጡር በኤደን የነበረውን እባብ የመነጋገሪያ መሣሪያ አድርጎ ተጠቅሞበት ነበር። ዘፍጥረት 3:15 ይህን እባብ መሣሪያ አድርጎ የተጠቀመው ፍጡር የሚቀጠቀጥበትን የወደፊት ጊዜ ያመለክታል። ከዚያ በኋላ ሰብዓውያን የአምላክ አገልጋዮች ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ወጥተው በገነት ለመኖር የሚችሉበት በር እንደገና ክፍት ይሆናል። እንዴት ያለ አስደሳች ጊዜ ይሆናል!—ራእይ 20:1-3፤ 21:1-5
5. የዲያብሎስን መንፈሳዊ ልጆች ለይተው የሚያሳውቁ ባሕርያት ምንድን ናቸው?
5 በኤደን ከተፈጸመው ዓመፅ በኋላ የሰይጣን ዲያብሎስን የመሰለ የዓመፅ፣ የውሸት፣ ስም የማጥፋትና ነፍስ የመግደል እንዲሁም የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉና ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎችን የመቃወም ባሕርይ ያላቸው ግለሰቦችና ድርጅቶቸ ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። እነዚህ የዲያብሎስን ዘሮች ማለትም መንፈሳዊ ልጆቹን ለይተው የሚያሳውቁ ባሕርያት ናቸው። ከእነዚህ መካከል ይሖዋ ከእርሱ አምልኮ ይልቅ የአቤልን አምልኮ በተቀበለ ጊዜ ወንድሙን የገደለው ቃየል ይገኝበታል። (1 ዮሐንስ 3:10-12) ስሙ ራሱ ዓመፀኛ እንደነበረ የሚያሳየው ናምሩድ ይሖዋን በመቃወም ኃያል አዳኝና ገዥ ነበረ። (ዘፍጥረት 10:9 አዓት) ከዚህም በተጨማሪ ባቢሎንን ጨምሮ በሐሰት ላይ የተገነቡ ሃይማኖቶችን የሚደግፉና የሚያስፋፉ የጥንት መንግሥታት በየተራ ተነስተዋል። እነዚህ መንግሥታትም የይሖዋ አምላኪዎችን በጭካኔ ጨቁነዋል።—ኤርምያስ 50:29
‘በአንተና በሴቲቱ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ’
6. ሰይጣን ለይሖዋ ሴት ጠላትነት ያሳየው በምን መንገዶች ነው?
6 በዚህ ጊዜ ሁሉ በእባቡና በይሖዋ ሴት መካከል ማለትም በሰይጣን ዲያብሎስና ታማኝ መንፈሳዊ ፍጡራን በሚገኙበት የይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት መካከል ጠላትነት ነበር። የሰይጣን ጠላትነት አምላክን በመስደብና መላእክት ትክክለኛ መኖሪያቸውን እንዲተዉ በመቀስቀስ የይሖዋን ሰማያዊ ድርጅት ለማናጋት በመሞከሩ ታይቷል። (ምሳሌ 27:11፤ ይሁዳ 6) ሰይጣን በአጋንንቱ ተጠቅሞ ለይሖዋ አገልጋዮች አስፈላጊ የሆነ መልእክት ሊያደርሱ የሄዱትን መላእክት ተልእኳቸውን ለማስተጓጎል በመሞከሩ ይህ ጠላትነት ግልጽ ሆኗል። (ዳንኤል 10:13, 14, 20, 21) በተለይ ደግሞ በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ሰይጣን ገና የተወለደውን መሲሐዊ መንግሥት ለማጥፋት ባደረገው ጥረት ይህ ጠላትነት ገሐድ ወጥቷል።—ራእይ 12:1-4
7. ታማኝ የሆኑት የይሖዋ መላእክት ለምሳሌያዊው እባብ ጠላትነት ያሳዩት ለምንድን ነው? ሆኖም ከምን ነገር ታቅበዋል?
7 የታማኝ መላእክት ማኅበር የሆነችውም የይሖዋ ሴት ለምሳሌያዊው እባብ ጠላት ነበረች። ሰይጣን የአምላክን መልካም ስም አጉድፏል። በተጨማሪም መላእክትን ጨምሮ የእያንዳንዱ ማሰብ የሚችል የአምላክ ፍጡር ታማኝነት ጥርጣሬ ውስጥ እንዲወድቅ አድርጓል። ለአምላክ ታዛዥ እንዳይሆኑ ለማድረግ የተቻለውን ያህል ጥሯል። (ራእይ 12:4) ታማኝ መላእክት፣ ኪሩቤሎችና ሱራፌሎች ራሱን ዲያብሎስና ሰይጣን ያደረገውን ይህን ፍጡር መጥላታቸውና እንደ ርኩስ መቁጠራቸው ተገቢ ነው። ሆኖም ይሖዋ በራሱ ጊዜና መንገድ እርምጃ እስኪወስድ ድረስ ዝም ብለው ተጠባብቀዋል።—ከይሁዳ 9 ጋር አወዳድር።
የአምላክ ሴት ዘር የደረሰበት ጥላቻ
8. ሰይጣን የማንን መምጣት ይጠባበቅ ነበር?
8 ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰይጣን ትንቢት የተነገረለትን የሴቲቱን ዘር ማለትም የእባቡን ጭንቅላት እንደሚቀጠቅጥ ይሖዋ የተናገረለትን ዘር በተጠንቀቅ ይጠባበቅ ነበር። ከሰማይ የመጣው መልአክ በቤተ ልሔም የተወለደው ኢየሱስ “መድኃኒት፣ እርሱም ክርስቶስ ጌታ” እንደሆነ ባስታወቀ ጊዜ ሰይጣን ይህ ሕፃን ትንቢት የተነገረለት የሴቲቱ ዘር እንደሚሆን የማያሻማ ማረጋገጫ አገኘ።—ሉቃስ 2:10, 11
9. ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ ሰይጣን አረመኔያዊ ጠላትነት ያሳየው እንዴት ነው?
9 ጭካኔ የተሞላበት የሰይጣን ጠላትነት ብዙም ሳይቆይ አረማዊ ኮከብ ቆጣሪዎች በመጀመሪያ ኢየሩሳሌም ወደነበረው ወደ ንጉሥ ሄሮድስ፣ በኋላ ደግም ሕፃኑን ኢየሱስና እናቱን ማርያምን ወዳገኙበት ቤተ ልሔም ወደሚገኘው ቤት እንዲሄዱ ባነሳሳቸው ጊዜ ግልጽ ሆነ። ከዚህ ጥቂት ቆየት ብሎ ንጉሥ ሄሮድስ በቤተ ልሔምና በአካባቢዋ የነበሩ ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ወንዶች ልጆች በሙሉ እንዲገደሉ አደረገ። ይህን በማድረጉም ሄሮድስ ለዘሩ የከረረ ጥላቻ እንዳለው አሳይቷል። ሄሮድስ መሲሕ የሚሆነውን ሕፃን ሕይወት በአጭሩ ለመቅጨት እየሞከረ እንዳለ አሳምሮ ያውቅ ነበር። (ማቴዎስ 2:1-6, 16) ንጉሥ ሄሮድስ ሕሊና ቢስ፣ ተንኮለኛና ነፍሰ ገዳይ እንደነበረ ታሪክ ይመሰክራል፤ በእርግጥም አንዱ የእባቡ ዘር ነበረ።
10. (ሀ) ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ይሖዋ ተስፋ ስለተደረገበት ዘር ያወጣውን ዓላማ ለማክሸፍ ሰይጣን ራሱ ሙከራ ያደረገው እንዴት ነው? (ለ) ሰይጣን ዓላማውን ለማሳካት በአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች የተጠቀመው እንዴት ነበር?
10 ኢየሱስ በ29 እዘአ በመንፈስ ቅዱስ ከተጠመቀና ይሖዋ ሰማይ ሆኖ ልጁ መሆኑን ከመሰከረለት በኋላ ሰይጣን ኢየሱስን በፈተና ለማንበርከክና በዚህም ይሖዋ ስለ ልጁ ያወጣውን ዓላማ ለማክሸፍ ሞክሯል። (ማቴዎስ 4:1-10) ይህ ሳይሳካለት ሲቀር ደግሞ በሰብዓዊ ወኪሎች በመጠቀም ዓላማውን ለማስፈጸም ሞክሯል። ኢየሱስ ተደማጭነት እንዳያገኝ ለማድረግ ከተጠቀመባቸው ወኪሎቹ መካከል ግብዝ የሆኑ የሃይማኖት መሪዎች ይገኙበታል። እነርሱም ሰይጣን በሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች፣ ማለትም በውሸትና ስም በማጥፋት ተጠቅመዋል። ኢየሱስ ሽባ የነበረውን ሰው “አይዞህ፣ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ” ሲለው ሰውዬው መፈወስ አለመፈወሱን እንኳ ሳይመለከቱ አምላክን ይሳደባል አሉ። (ማቴዎስ 9:2-7) ኢየሱስ በሽተኞችን በሰንበት ቀን በፈወሰ ጊዜ ፈሪሳውያን የሰንበትን ሕግ ይተላለፋል ብለው ካወገዙት በኋላ ሊገድሉት ተማከሩ። (ማቴዎስ 12:9-14፤ ዮሐንስ 5:1-18) ኢየሱስ አጋንንትን ባወጣ ጊዜ ፈሪሳውያን ‘የአጋንንት አለቃ የብዔል ዜቡል’ አጫፋሪ አድርገው ከሰሱት። (ማቴዎስ 12:22-24) አልዓዛር ከሞት ከተነሳ በኋላ ብዙ ሰዎች በኢየሱስ ቢያምኑም የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ግን እንደገና ሊገድሉት ተማከሩ።—ዮሐንስ 11:47-53
11. ኢየሱስ ከመሞቱ ከሦስት ቀን ቀደም ብሎ የእባቡ ዘር መሆናቸውን ያሳዩት እነማን ናቸው? ለምንስ?
11 ኢየሱስ ምን እያሴሩበት እንደነበረ ቢያውቅም ኒሳን 11 ቀን 33 እዘአ በድፍረት ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ ገብቶ በሕዝብ ፊት አወገዛቸው። ጻፎችና ፈሪሳውያን በቡድን ደረጃ ምን ዓይነት ሰዎች መሆናቸውን በማያሻማ ሁኔታ በተደጋጋሚ ግልጽ አድርገዋል። ስለዚህ ኢየሱስ “እናንተ ግብዞች፣ ጻፎችና ፈሪሳውያን፣ መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ፣ ወዮላችሁ። እናንተ አትገቡም የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ” ብሏል። ኢየሱስ “እናንተ እባቦች የእፉኝት ልጆች፣ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?” በማለት የእባቡ ዘር ክፍሎች መሆናቸውን በቀጥታ ተናግሯል። (ማቴዎስ 23:13, 33) አነጋገሩ በዘፍጥረት 3:15 ላይ ያለውን ትንቢት ያንጸባርቃል።
12, 13. (ሀ) የካህናት አለቆችና ጻፎች መንፈሳዊ አባታቸው ማን እንደሆነ ተጨማሪ ማረጋገጫ የሰጡት እንዴት ነው? (ለ) ማን ተባበራቸው? (ሐ) በዘፍጥረት 3:15 ፍጻሜ መሠረት የሴቲቱ ዘር ተረከዙ ላይ የቆሰለው እንዴት ነበር?
12 ታዲያ የኢየሱስን ቃላት ሲሰሙ ልባቸው ተሰብሮ አምላክ ምሕረት እንዲያደርግላቸው ለምነዋልን? ከክፋት ድርጊታቸው ተጸጽተዋልን? አልተጸጸቱም! ማርቆስ 14:1 በማግሥቱ ጠዋት በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰብስበው “የካህናት አለቆችም፣ ጻፎችም እንዴት አድርገው [ኢየሱስን] እንደሚይዙትና እንደሚገድሉት” እንደተማከሩ ይናገራል። ኢየሱስ ቀደም ሲል ነፍሰ ገዳይ እንደሆነ የተናገረለትን የሰይጣንን የነፍሰ ገዳይነት መንፈስ ማንጸባረቅ ቀጠሉ። (ዮሐንስ 8:44) ብዙም ሳይቆይ ከሃዲ እንዲሆን ሰይጣን የገፋፋው አስቆሮቱ ይሁዳ ተባበራቸው። ይሁዳ አንዳች እድፍ የሌለበትን የአምላክ ሴት ዘር ከድቶ የእባቡ ዘር የሆኑትን ተባበራቸው።
13 ኒሳን 14 ማለዳ የአይሁድ ሃይማኖታዊ ሸንጎ አባላት ኢየሱስን አስረው በሮማዊው ገዥ ፊት አቀረቡት። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲሰቀል በግንባር ቀደምትነት የጮሁት የካህናት አለቆች ነበሩ። ጲላጦስ “ንጉሣችሁን ልስቀለውን?” ብሎ ሲጠይቅ “ከቄሣር በቀር ንጉሥ የለንም” ብለው የጮሁት የካህናት አለቆች ነበሩ። (ዮሐንስ 19:6, 15) በእርግጥም በሁሉም መንገዶች የእባቡ ዘር ክፍል መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ሆኖም እንዲህ ያደረጉት እነርሱ ብቻ አልነበሩም። በመንፈስ የተጻፈው መዝገብ ማቴዎስ 27:24, 25 ላይ እንደሚከተለው በማለት ይተርካል፦ “ጲላጦስም . . . ውኃ አንስቶ እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ . . . ሲል በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። ሕዝቡም ሁሉ መልሰው ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን አሉ።” ስለዚህ በዚያ ትውልድ መካከል የነበሩ ብዙ አይሁዳውያን የእባቡ ዘር ክፍል መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ኢየሱስ በዚያው ቀን ተገደለ። ሰይጣን በሚታዩ ዘሮቹ በመጠቀም የአምላክን ሴት ዘር ተረከዙ ላይ አቆሰለው።
14. የሴቲቱ ዘር ተረከዝ መቁሰል ሰይጣን ድል ነሳ ማለት ያልሆነው ለምንድን ነው?
14 ሰይጣን ድል ነሳ ማለት ነውን? በምንም ዓይነት! ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምንና የዓለምን ገዢ ድል አድርጓል። (ዮሐንስ 14:30, 31፤ 16:33) እስከ ሞት ድረስ ለአባቱ ታማኝ ሆኗል። ፍጹም ሰው ሆኖ በመሞቱ አዳም ያሳጣውን የሕይወት መብት ለመዋጀት የሚያስችል ቤዛ ሆኗል። ስለዚህ በዚህ ዝግጅት የሚያምኑና የአምላክን ትእዛዛት የሚጠብቁ ሁሉ የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበትን በር ከፍቷል። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16) ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት አስነስቶ በሰማይ የማይጠፋ ሕይወት ሰጥቶታል። ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ኢየሱስ ሰይጣንን ቀጥቅጦ ከሕልውና ውጭ ያደርገዋል። ይሖዋ በዚህ ታማኝ ዘር አማካኝነት ራሳቸውን ለመባረክ የሚያስፈልገውን እርምጃ ለወሰዱ የምድር ወገኖች በሙሉ ሞገሱን እንደሚዘረጋ በዘፍጥረት 22:16-18 ላይ ተተንብዮአል።
15. (ሀ) ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ሐዋርያቱ የእባቡን ዘር ማጋለጥ የቀጠሉት እንዴት ነው? (ለ) የእባቡ ዘር እስከ ዘመናችን ድረስ እንዴት ያለ ጠላትነት ማሳየቱን ቀጥሏል?
15 ከኢየሱስ ሞት በኋላ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ጌታቸው እንዳደረገው የእባቡን ዘር ማጋለጥ ቀጠሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተነድቶ “እንደ ሰይጣን አሠራር” ስለሚገለጠው “የዓመፅ ሰው” አስጠንቅቋል። (2 ተሰሎንቄ 2:3-10) ይህ የሰዎች ቡድን የሕዝበ ክርስትናን ቀሳውስት እንደሚያመለክት ተረጋግጧል። የእባቡ ዘርም በኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ላይ ከባድ ስደት አምጥቶባቸዋል። በራእይ 12:17 ላይ በተመዘገበው ትንቢት ውስጥ ሰይጣን በአምላክ ሴት ዘር ቀሪዎች ላይ እስከ ዘመናችን ድረስ ጦርነት እንደሚያካሄድ ሐዋርያው ዮሐንስ ተንብዮአል። ይህም በትክክል ተፈጽሟል። የይሖዋ ምሥክሮች በበርካታ አገሮች ለአምላክ መንግሥትና ለጽድቅ መንገዶቹ የጸና አቋም ስለያዙ ታግደዋል፣ ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፣ ወደ ማጎሪያ ካምፖች ተጥለዋል።
በዘመናችን የእባቡን ዘር ማጋለጥ
16. በዘመናችን የሰይጣን ዘር መሆኑ የተጋለጠው ማን ነው? የተጋለጠውስ እንዴት ነው?
16 እውነተኛ ክርስቲያኖች የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል እባቡንና ዘሩን በድፍረት ከማጋለጥ ወደ ኋላ አላሉም። በ1917 በጊዜው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች የሕዝበ ክርስትናን ቀሳውስት ግብዝነት እርቃኑን እንዲቀር ያደረገውን ያለቀለት ምሥጢር የተባለ (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍ አሳተሙ። በመቀጠልም በ1924 ካህናት ተወነጀሉ የሚል መግለጫ አትመው አሰራጩ። በመላው ዓለም ሃምሳ ሚልዮን ቅጂ ተሰራጭቷል። በ1937 በጊዜው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ “ተጋለጠ” እንዲሁም “ሃይማኖትና ክርስትና” የሚሉ ርዕሶች ባሏቸው ንግግሮች የሰይጣንን ዘር እጅጉን አጋልጧል። በሚቀጥለው ዓመት “እውነታዎቹን መቀበል” በሚል ርዕስ በእንግሊዝ ለንደን ውስጥ ንግግር ያቀረበ ሲሆን ንግግሩ ወደ 50 የተለያዩ አገሮች በሬዲዮ ተላልፏል። ከአንድ ወር በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብዛት ያላቸው የሬዲዮ ጣቢያዎች እርስ በርስ ተቀናጅተው “ፋሺዝም ወይም ነፃነት” የተባለውን ንግግር አስተላልፈዋል። እነዚህ ንግግሮች ጠላቶች እና ሃይማኖት የተባሉት (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍትና ተጋለጠ የተባለው (የእንግሊዝኛ) ብሮሹር በሚያስተላልፉት ኃይለኛ ማጋለጫዎች ተደግፈዋል። በአሁኑ ጊዜ በ65 ቋንቋዎች የታተመው ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!a የተባለው መጽሐፍ ከ1920ዎቹ ጀምሮ ከታተሙት ጽሑፎች ጋር በመስማማት ምግባረ ብልሹ የፖለቲካ ገዥዎች እንዲሁም ስግብግብና ሥርዓት የለሽ የሆኑ የንግድ አስተላላፊዎች ጭምር የሚታየው የእባቡ ዘር ዋነኛ ክፍሎች መሆናቸውን አሳውቋል። የፖለቲካ መሪዎች ተገዥዎቻቸውን ለማታለል ብለው ደጋግመው ሲዋሹ፣ ለደም ቅድስና ምንም ዓይነት አክብሮት ሳያሳዩ ሲቀሩና የይሖዋ አገልጋዮችን ሲጨቁኑ (ይህንንም በማድረጋቸው ለአምላክ ሴት ዘር ያላቸውን ጥላቻ ሲገልጹ) የእባቡ ዘር ክፍል መሆናቸውን በተግባር ያሳያሉ። የንግድ አስተላላፊዎችም ከዚህ የተለዩ አይደሉም። ሕሊናቸውን ሳይቆረቁራቸው የገንዘብ ትርፍ ለማግኘት ብለው ከመዋሸታቸውም በተጨማሪ በሽታ እንዲሚያስከትሉ የታወቁ ሸቀጦችን ያመርታሉ እንዲሁም ይሸጣሉ።
17. ዓለምን ትተው ለሚወጡ ታዋቂ ግለሰቦች አሁንም ቢሆን ምን አጋጣሚ አላቸው?
17 በዓለማዊ ሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በንግድ ውስጥ ያሉ ሁሉ የእባቡ ዘር እንደሆኑ ይቀጥላሉ ማለት አይደለም። ከእነዚህ ወንዶችና ሴቶች መካከል አንዳንዶቹ የይሖዋ ምሥክሮችን ማድነቅ ጀምረዋል። ባላቸውም ሥልጣን ተጠቅመው እውነተኛውን አምልኮ ይዘው እንዲቀጥሉ ረድተዋቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶቹ እውነተኛውን አምልኮ መከተል ጀምረዋል። (ከሥራ 13:7, 12፤ 17:32-34 ጋር አወዳድር።) እነዚህን ለመሰሉ ሰዎች ይህ ግብዣ ቀርቦላቸዋል፦ “አሁንም እናንተ ነገሥታት ልብ አድርጉ። እናንተ የምድር ፈራጆችም ተገሠጹ። ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፣ በረዓድም ደስ ይበላችሁ። ተግሣጹን ተቀበሉ፣ ጌታ እንዳይቆጣ፣ እናንተም በመንገድ እንዳትጠፉ። ቁጣው ፈጥና ትነድዳለችና። በእርሱ የታመኑ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው።” (መዝሙር 2:10-12) በእርግጥም የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ሰማያዊው ፈራጅ በሩን ከመዝጋቱ በፊት አሁኑኑ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋቸዋል!
18. ምንም እንኳ የሴቲቱ ዘር ክፍል ባይሆኑም ይሖዋን የሚያመልኩት እነማን ናቸው?
18 የሴቲቱ ዘር ክፍል የሆኑት የሰማያዊው መንግሥት አባሎች ብቻ ናቸው። እነዚህ ቁጥራቸው ጥቂት ነው። (ራእይ 7:4, 9) ሆኖም የይሖዋ አምላኪዎች በመሆናቸው ገነት በምትሆነዋ ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ እጅግ ብዙ ሰዎች፣ አዎን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። የይሖዋን ቅቡዓን አገልጋዮች በቃላቸውም ሆነ በድርጊታቸው “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ” ይሏቸዋል።—ዘካርያስ 8:23
19. (ሀ) ሁሉም ሰዎች ምን ምርጫ ማድረግ ይኖርባቸዋል? (ለ) በተለይ አጋጣሚው ሳይዘጋ ጥበብ የተሞላበት እርምጃ መውሰድ ያለባቸው እነማን ናቸው?
19 አሁን መላው የሰው ልጅ ምርጫውን መወሰን የሚኖርበት ጊዜ ነው። ሰዎች ይሖዋን ለማምለክና ሉዓላዊነቱን ደግፈው ለመቆም ይፈልጋሉ ወይስ ሰይጣንን የሚያስደስቱ ነገሮች በማድረግ ሰይጣን ገዥያቸው እንዲሆን ይፈቅዳሉ? ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጉ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች የመንግሥቱ ወራሾች አባላት ከሆኑበት ከሴቷ ዘር ቀሪዎች ጋር በመተባበር ከይሖዋ ጎን ተሰልፈዋል። ስምንት ሚልዮን የሚያክሉ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ከእነርሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናትና በስብሰባዎቻቸው ላይ በመገኘት ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች እንደነዚህ ላሉት ሰዎች እንዲህ ይላሉ፦ በሩ አሁንም ክፍት ነው! ሳታወላውሉ ከይሖዋ ጎን ቁሙ። ክርስቶስ ኢየሱስ የተስፋው ዘር መሆኑን አምናችሁ ተቀበሉ። ከሚታየው የይሖዋ ድርጅት ጋር በደስታ ተባበሩ። ይሖዋ በንጉሡ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ከሚያመጣቸው በረከቶች ሁሉ ተካፋይ ያድርጋችሁ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መጽሐፉ የታተመው ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ነው።
ታስታውሳለህን?
◻ በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተጠቀሰው እባብ ማነው? ሴቲቱስ?
◻ የእባቡን ዘር ለይተው የሚያሳውቁ ባሕርያት ምንድን ናቸው?
◻ ኢየሱስ የእባቡን ዘር ያጋለጠው እንዴት ነው?
◻ በዘመናችን የእባቡ ዘር ክፍል መሆኑ የተጋለጠው ማን ነው?
◻ ከእባቡ ዘር እንዳንመደብ ምን ፈጣን እርምጃ መውሰድ ይፈለግብናል?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ግብዞቹ የሃይማኖት መሪዎች የእባቡ ዘር ክፍል እንደሆኑ አጋልጧል