‘እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ’
“እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ።”—ዘሌዋውያን 19:2
1. በዓለም ዘንድ እንደ ቅዱስ ተደርገው ከሚታዩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እነማን ናቸው?
በአብዛኞቹ የዓለም ታላላቅ ሃይማኖቶች ውስጥ እንደ ቅዱስ ተደርገው የሚታዩ ሰዎች አሉ። የሕንዷ ማዘር ትሬዛ ድሆችን ለመርዳት ያደሩ በመሆናቸው እንደ ቅዱስ ተደርገው ይታያሉ። ጳጳሱ “ቅዱስ አባት” ተብለው ይጠራሉ። የዘመናዊው የካቶሊክ ሃይማኖት እንቅስቃሴ መሥራች የሆነው ኦፐስ ዴ ሆሴ ማሪያ ኤስክሬባ በአንዳንድ ካቶሊኮች ዘንድ “የቅድስና አርዓያ” ተደርጎ ይታያል። የሂንዱ እምነትም የራሱ የሃይማኖት መሪዎች ወይም ቅዱሳን ወንዶች አሉት። ጋንዲ እንደ ቅዱስ ይታዩ ስለነበር ከፍተኛ አክብሮት ተችሯቸዋል። ቡድሂዝም የራሱ ቅዱስ መነኮሳት ሲኖሩት እስልምናም ቅዱስ ነቢያት አሉት። ይሁን እንጂ ቅዱስ መሆን ማለት ምን ማለት ነው?
2, 3. (ሀ) “ቅዱስ” እና “ቅድስና” የሚሉት ቃላት ትርጉም ምንድን ነው? (ለ) መልስ የሚያስፈልጋቸው የትኞቹ ጥያቄዎች ናቸው?
2 “ቅዱስ” ለሚለው ቃል የሚከተሉት ፍቺዎች ተሰጥተውታል፦ “1. . . . ከመለኮታዊ ኃይል ጋር ተዛምዶ ያለው፣ ክቡር። 2. አምልኮ ወይም የላቀ ክብር የሚቀርብለት ወይም ሊቀርብለት የሚገባው . . . 3. ከአንድ ጥብቅ ወይም ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃ ካለው ሃይማኖታዊ ወይም መንፈሳዊ ሥርዓት ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር . . . 4. ለአንድ ሃይማኖታዊ ዓላማ የተወሰነ ወይም የተለየ።” ቅድስና የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ሃይማኖታዊ ንጽሕና፣ ክቡር መሆን” የሚል ትርጉም አለው። ዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል በተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንሳይክሎፔድያ መሠረት “ቆዴሽ የሚለው መሠረታዊው የዕብራይስጥ [ቃል] የተለዩ መሆን፣ ለአንድ ነገር መወሰን፣ ለአምላክ የተቀደሱ መሆን . . . ለአምላክ አገልግሎት የተለዩ መሆን የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል።”a
3 የእስራኤል ብሔር ቅዱስ እንዲሆን ታዝዞ ነበር። የአምላክ ሕግ እንዲህ ይላል፦ “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና፤ ሰውነታችሁን ቀድሱ፣ ቅዱሳን ሁኑ፣ እኔ ቅዱስ ነኝና።” የቅድስና ምንጭ የነበረው ማን ነው? ፍጹማን ያልነበሩት እስራኤላውያን ቅዱስ መሆን የሚችሉት እንዴት ነበር? ይሖዋ ቅዱስ እንዲሆኑ ካቀረበው ጥሪ ዛሬ እኛ ምን ትምህርት እናገኛለን?—ዘሌዋውያን 11:44
እስራኤላውያን ከቅድስና ምንጭ ጋር የተዛመዱት እንዴት ነው?
4. የይሖዋ ቅድስና በእስራኤላውያን አማካኝነት የተገለጠው እንዴት ነው?
4 እስራኤላውያን ለይሖዋ አምላክ ከሚያቀርቡት አምልኮ ጋር ግንኙነት ያለው ማንኛውም ነገር ቅዱስ ተደርጎ መታየትና በዚያ መንገድ መያዝ ነበረበት። ይህ የሆነው ለምን ነበር? ምክንያቱም ይሖዋ ራሱ የቅድስና ምንጭ ስለሆነ ነው። ሙሴ ቅዱስ ስለሆነው የመገናኛ ድንኳን እና ስለ ልብሰ ተክህኖው እንዲሁም ስለ ሌሎች ጌጣጌጦች የተደረገውን ዝግጅት ከተረከ በኋላ እንዲህ በማለት ደምድሟል፦ “ከጥሩ ወርቅ የተቀደሰውን የአክሊል ምልክት ሠሩ፤ በእርሱም እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገው፦ ቅድስና ለእግዚአብሔር [“ለይሖዋ፣” አዓት] የሚል ጻፉበት።” ይህ ከጥሩ ወርቅ የተሠራ አክሊል በሊቀ ካህናቱ ጥምጥም ላይ የሚታሰር ሲሆን ለአንድ ልዩ የሆነ የቅድስና አገልግሎት የተለየ መሆኑን ያመለክት ነበር። እስራኤላውያኑ ይህ የተቀረጸ ምልክት ሲያንጸባርቅ በተመለከቱ ቁጥር ዘወትር የይሖዋን ቅድስና ያስታውሱ ነበር።—ዘጸአት 28:36፤ 29:6፤ 39:30
5. ፍጹማን ያልነበሩት እስራኤላውያን እንደ ቅዱስ ሊታዩ ይችሉ የነበሩት እንዴት ነው?
5 ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ቅዱስ ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነበር? ከይሖዋ ጋር ባላቸው የቅርብ ዝምድናና ለእርሱ በሚያቀርቡት ንጹህ አምልኮ አማካኝነት ብቻ ነበር። እርሱን በቅድስና እንዲሁም በአካላዊና መንፈሳዊ ንጽህና ለማምለክ ስለ ‘ቅዱሱ’ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ያስፈልጋቸው ነበር። (ምሳሌ 2:1-6፤ 9:10) በመሆኑም እስራኤላውያን በትክክለኛ ግፊትና በንጹህ ልብ አምላክን ማምለክ ይጠበቅባቸው ነበር። ማንኛውም ዓይነት የግብዝነት አምልኮ በይሖዋ ፊት አጸያፊ ነበር።—ምሳሌ 21:27
ይሖዋ እስራኤልን የነቀፈበት ምክንያት
6. በሚልክያስ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን የይሖዋን ማዕድ የተመለከቱት እንዴት ነው?
6 እስራኤላውያን እንዲያው ለይስሙላ መናኛና ሰንካላ መሥዋዕቶችን ወደ ቤተ መቅደሱ ያመጡ በነበረበት ጊዜ የግብዝነት አምልኮ በይሖዋ ዘንድ አጸያፊ መሆኑ በግልጽ ታይቷል። ይሖዋ ያቀርቡት የነበረውን መናኛ መሥዋዕት በነቢዩ ሚልክያስ አማካኝነት እንዲህ በማለት ነቅፎታል፦ “በእናንተ ደስ አይለኝም፣ ቁርባንንም ከእጃችሁ አልቀበልም፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። . . . እናንተ ግን፦ የእግዚአብሔር ገበታ ርኩስ ነው፤ ፍሬውና መብሉም የተናቀ ነው በማለታችሁ አስነቀፋችሁት። እናንተ፦ እነሆ፣ ይህ ድካም ነው ብላችሁ ጢቅ አላችሁበት፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ በቅሚያ የያዛችሁትንም አንካሳውንም የታመመውንም አቅርባችኋል፤ እንዲሁ ቁርባንን ታመጣላችሁ፤ በውኑ ከእጃችሁ ይህን ልቀበለውን? ይላል እግዚአብሔር።”—ሚልክያስ 1:10, 12, 13
7. አይሁዳውያን በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ምን ርኩስ ድርጊቶችን ይፈጽሙ ነበር?
7 አምላክ በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ገደማ የአይሁዳውያንን የሐሰት ድርጊቶች ለማውገዝ በሚልክያስ ተጠቅሟል። ካህናቱ መጥፎ ምሳሌ ሆነው ነበር፤ አኗኗራቸውም ጨርሶ ቅዱስ አልነበረም። ሕዝቡም ይህን አመራር በመከተል ሚስቶቻቸውን እስከ መፍታት ድረስ ለመሠረታዊ ሥርዓቶች ግዴለሽ ሆነው ነበር። ሚስቶቻቸውን ይፈቱ የነበረው ጣዖት አምላኪ የሆኑ ቆነጃጅት ለማግባት ብለው ሳይሆን አይቀርም። ሚልክያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሚስትህ ባልንጀራህና የቃል ኪዳንህ ሚስት ሆና ሳለች እርስዋን አታልለሃታልና እግዚአብሔር በአንተና በልጅነት ሚስትህ መካከል ምስክር ስለ ሆነ ነው። . . . ስለዚህ መንፈሳችሁን ጠብቁ፣ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል።b መፋታትን እጠላለሁ፣ ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር።”—ሚልክያስ 2:14-16
8. በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንዶች ዛሬ ስለ ፍቺ ተስፋፍቶ በሚገኘው አመለካከት የተነኩት እንዴት ነው?
8 በዘመናችን በቀላሉ መፋታት በሚቻልባቸው ብዙ አገሮች ውስጥ የፍቺው ቁጥር አሻቅቧል። የክርስቲያን ጉባኤ ሳይቀር በዚህ ተነክቷል። አንዳንዶች ለችግሮቻቸው መፍትሔ ለማግኘትና ትዳራቸውን ለማቃናት የሽማግሌዎችን እርዳታ ከመሻት ይልቅ በችኮላ ትዳራቸውን አፍርሰዋል። በዚህ የተነሣ ብዙውን ጊዜ ልጆች ለከፍተኛ የስሜት ሥቃይ ይዳረጋሉ።—ማቴዎስ 19:8, 9
9, 10. ለይሖዋ የምናቀርበውን አምልኮ መመርመር ያለብን እንዴት ነው?
9 ከላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ በሚልክያስ ዘመን ከነበረው አሳዛኝ መንፈሳዊ ሁኔታ አንጻር የይሁዳን የለበጣ አምልኮ በግልጽ ከመኮነኑም በላይ እርሱ የሚቀበለው ንጹህ አምልኮ ብቻ እንደሆነ አሳይቷል። ይህ ጉዳይ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታና የእውነተኛ ቅድስና ምንጭ ለሆነው አምላክ ለይሖዋ ስለምናቀርበው አምልኮ ጥራት እንድናስብ ሊያደርገን አይገባምን? በእርግጥ ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት እያቀረብን ነውን? መንፈሳዊ ንጽህናችንን እንጠብቃለንን?
10 ይህ ሲባል ፍጹም መሆን አለብን ማለት አይደለም፤ ፍጹም መሆን አንችልም። ወይም ደግሞ ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማወዳደር አለብን ማለትም አይደለም። ነገር ግን እያንዳንዱ ክርስቲያን የግል ሁኔታው በሚፈቅድለት መጠን ለአምላክ ምርጥ የሆነ አምልኮ ማቅረብ ይኖርበታል ማለት ነው። ይህም የአምልኮአችንን ጥራት የሚመለከት ነው። የምናቀርበው አገልግሎት ምርጣችንን ማለትም ቅዱስ አገልግሎት መሆን ይኖርበታል። ይህንን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?—ሉቃስ 16:10፤ ገላትያ 6:3, 4
ንጹህ ልብ ወደ ንጹህ አምልኮ ይመራል
11, 12. ርኩስ ድርጊቶች የሚፈልቁት ከየት ነው?
11 በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ያለው ሁኔታ በሚናገረውና በሚያደርገው ነገር እንደሚገለጥ ኢየሱስ በግልጽ አስተምሯል። ኢየሱስ ራሳቸውን የሚያመጻድቁትን ቅድስና የጎደላቸው ፈሪሳውያን እንደሚከተለው ብሏቸዋል፦ “እናንተ የእፉኝት ልጆች፣ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ለመናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና።” በመቀጠልም ክፉ ድርጊት የሚወጣው በልብ ወይም በውስጥ ሰውነት ካለ ክፉ ሐሳብ እንደሆነ ተናገረ። እንዲህ አለ፦ “ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፣ ሰውንም የሚያረክሰው ያ ነው። ከልብ ክፉ አሳብ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ በውሸት መመስከር፣ ስድብ ይወጣልና። ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው።”—ማቴዎስ 12:34፤ 15:18-20
12 ይህም አንድ ሰው ከመሬት ተነሥቶ ወይም ምንም ዓይነት መሠረት ሳይኖረው ርኩስ ድርጊት እንደማይፈጽም እንድንገነዘብ ይረዳናል። እነዚህ ድርጊቶች በልብ ውስጥ ሲብላሉ የቆዩ ርኩስ ሐሳቦች በሌላ አባባል ስውር የሆኑ ምኞቶችና ቅዠቶች ውጤት ናቸው። ለዚህ ነው ኢየሱስ “አታመንዝር እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል” በማለት የተናገረው። በሌላ አባባል ድርጊቱ ከመፈጸሙ አስቀድሞ ዝሙትና ምንዝር በልቡ ውስጥ ሥር ሰደው ነበር ማለት ነው። እነዚህ ርኩስ ሐሳቦች አጋጣሚው ሲመቻችላቸው ርኩስ ድርጊት ይሆናሉ። ከጊዜ በኋላ በተጨባጭ ከሚታዩት ድርጊቶች መካከል ዝሙት፣ ምንዝር፣ ሰዶማዊነት፣ ሌብነት፣ አምላክን መሳደብና ክህደት ጥቂቶቹ ናቸው።—ማቴዎስ 5:27, 28፤ ገላትያ 5:19-21
13. ርኩስ ሐሳቦች ርኩስ ድርጊቶችን ወደመፈጸም ሊመሩ እንደሚችሉ የሚያሳዩት አንዳንድ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?
13 ይህንን በተለያየ መንገድ በምሳሌ ማስረዳት ይቻላል። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ የቁማር ቤቶች እንደ አሸን መፍላታቸው ቁማር ለመጫወት ያለውን አጋጣሚ ሰፊ አድርጎታል። አንድ ሰው ያለበትን የገንዘብ ችግር ለመወጣት እንደሚያስችለው በማሰብ በዚህ ዘዴ ለመጠቀም ሊፈተን ይችላል። አንዳንድ አታላይ የሆኑ ሐሳቦች አንድ ወንድም የተማራቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ችላ እንዲል ወይም እንዲያቃልል ሊያስቱት ይችላሉ።c በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ክርስቲያን ዕርቃንን የሚያሳዩ ምስሎችን በቴሌቪዥን፣ በቪዲዮ፣ በኮምፒዩተር ወይም በመጻሕፍት ለማየት የተጋለጠ ከሆነ ርኩስ ድርጊት ወደመፈጸም ሊመሩት ይችላሉ። መንፈሳዊ ትጥቁን ካላላ ሳያስበው በሥነ ምግባር ብልግና ይወድቃል። ያም ሆነ ይህ በአብዛኛው ወደ ኃጢአት መንሸራተት የሚጀምረው ከሐሳብ ነው። አዎን፣ ያዕቆብ የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት የሚፈጸሙት እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ነው፦ “እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።”—ያዕቆብ 1:14, 15፤ ኤፌሶን 6:11-18
14. ብዙዎች ከርኩስ ድርጊቶች የተላቀቁት እንዴት ነው?
14 ደስ የሚለው ግን በድካም ምክንያት ኃጢአት የሚፈጽሙ ብዙ ክርስቲያኖች ከልብ ንስሐ ከመግባታቸውም በላይ ሽማግሌዎች እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች በመንፈሳዊ እንዲያገግሙ መርዳት ችለዋል። ንስሐ ባለመግባታቸው ምክንያት የሚወገዱ ብዙዎችም እንኳ ሳይቀሩ የኋላ ኋላ ወደ አእምሮአቸው ተመልሰው እንደገና ከጉባኤው ጋር ይቀላቀላሉ። ርኩስ ሐሳቦች በልባቸው ውስጥ ሥር እንዲሰዱ በመፍቀዳቸው ሰይጣን እንዴት በቀላሉ እንደተቆጣጠራቸውም ይገነዘባሉ።—ገላትያ 6:1፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:24-26፤ 1 ጴጥሮስ 5:8, 9
ድካማችንን ለመቀበል አለማንገራገር
15. (ሀ) ድክመታችንን አምነን መቀበል ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ድክመታችንን አምነን ለመቀበል ምን ሊረዳን ይችላል?
15 የልባችንን ሁኔታ በትክክል ለማወቅ መጣር ይኖርብናል። ድካማችንን አምነን ለመቀበልና ብሎም ለማሸነፍ እንድንችል ጥረት ለማድረግ ፈቃደኞች ነንን? እንዴት ማሻሻል እንደምንችል በሐቀኝነት የሚነግረንን ወዳጅ ለመጠየቅና ምክሩን ለማዳመጥ ፈቃደኞች ነንን? ቅዱሳን ሆነን ለመኖር ድክመቶቻችንን ማሸነፍ ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም ሰይጣን ድካማችንን ያውቃል። እኛን ወደ ኃጢአትና ርኩስ ወደሆኑ ድርጊቶች ለማስገባት መሠሪ በሆኑት ሽንገላዎቹ ይጠቀማል። በተንኮል ድርጊቶቹ አማካኝነት እኛን ከአምላክ ፍቅር በመለየት ቅድስናችንን ሊያረክስና ለይሖዋ አምልኮ ብቁ ሆነን እንዳንገኝ ለማድረግ ይጥራል።—ኤርምያስ 17:9፤ ኤፌሶን 6:11፤ ያዕቆብ 1:19
16. ጳውሎስ ምን ትግል ነበረበት?
16 ሐዋርያው ጳውሎስ የራሱ ፈተናዎች እንደነበሩበት ለሮሜ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ተናግሯል፦ “በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፣ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም። የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም። . . . እንግዲያስ መልካሙን አደርግ ዘንድ ስወድ በእኔ ክፉ እንዲያድርብኝ ሕግን አገኛለሁ። በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፣ ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ።”—ሮሜ 7:18-23
17. ጳውሎስ ከድክመቶቹ ጋር ያደረገውን ትግል በድል አድራጊነት የተወጣው እንዴት ነው?
17 ከጳውሎስ ሁኔታ የምንማረው ዐቢይ ነጥብ ድክመቶቹን አምኖ መቀበሉ ነው። ድክመት ቢኖርበትም እንኳ “በውስጡ [በመንፈሳዊ] ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛል” ማለት ችሎ ነበር። ጳውሎስ መልካም የሆነውን የሚወድና ክፉ የሆነውን የሚጠላ ሰው ነበር። ይሁንና ሁላችንም የምናካሂደው ዓይነት ትግል ማድረግ ነበረበት፤ ይህም ማለት ከሰይጣን፣ ከዓለምና ከሥጋው ጋር መታገል አስፈልጎት ነበር። ታዲያ ከዚህ ዓለምና በውስጡ ከሚንጸባረቀው አስተሳሰብ በመራቅ ቅዱስ ሆነን ለመኖር የምናደርገውን ትግል በድል አድራጊነት መወጣት የምንችለው እንዴት ነው?—2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ኤፌሶን 6:12
ቅዱስ ሆነን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?
18. ቅዱስ ሆነን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?
18 ቅዱስ ሆነን መገኘት የምንችለው ቀላል ሆኖ ያገኘነውን ነገር በማድረግ ወይም ለራሳችን ፍላጎት በመገዛት አይደለም። እንዲህ ዓይነት ሰው ሁልጊዜ ለአድራጎቱ ሰበብ አስባብ የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ጥፋቱን በሌላ ሰው ላይ ለማላከክ ይሞክራል። ምናልባት ላደረግነው ነገር ኃላፊነት መውሰድን መማር ያስፈልገን ይሆናል። አስተዳደጋቸውን ወይም ተፈጥሮአቸውን ሰበብ አድርገው እንደሚያቀርቡ ሰዎች መሆን የለብንም። ቁምነገሩ ያለው በግለሰቡ ልብ ላይ ነው። እርሱ ወይም እርሷ ጽድቅን ያፈቅራሉን? ቅዱስ ሆነው ለመገኘት ይናፍቃሉን? የአምላክን በረከት ለማግኘት ይጓጓሉን? መዝሙራዊው “ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ፤ ሰላምን እሻ ተከተላትም” ባለ ጊዜ የቅድስናን አስፈላጊነት በግልጽ አስቀምጦታል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን። ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ” በማለት ጽፏል።—መዝሙር 34:14፤ 97:10፤ ሮሜ 12:9
19, 20. (ሀ) አእምሮአችንን ማጎልመስ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ውጤታማ የሆነ የግል ጥናት ምን ማድረግን ይጠይቃል?
19 ነገሮችን በይሖዋ ዓይን የምናይ ከሆነና የክርስቶስ አስተሳሰብ ካለን ‘ከበጎ ነገር ጋር መተባበር’ እንችላለን። (1 ቆሮንቶስ 2:16 አዓት) ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? የአምላክን ቃል ዘወትር በማጥናትና በማሰላሰል ነው። ይህ ምክር በጣም ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ ተሰጥቷል! ይሁን እንጂ የሚገባውን ያህል በቁም ነገር አስበንበታልን? ለምሳሌ ያህል ወደ ስብሰባ ከመምጣታችሁ በፊት ይህን መጽሔት ጥቅሶቹን እያወጣችሁ በማንበብ በደንብ ታጠኑታላችሁን? ማጥናት ስንል በእያንዳንዱ አንቀጽ ውስጥ ያሉ ጥቂት ሐረጎችን ማስመር ማለታችን አይደለም። አንድን የጥናት ርዕስ ላይ ላዩን ብቻ ዓይተንና አስምረንበት በ15 ደቂቃ ውስጥ መጨረስ እንችላለን። ይህ ማለት ርዕሱን አጠናነው ማለት ነውን? እንደ እውነቱ ከሆነ እያንዳንዱን ርዕስ ለማጥናትና በውስጡ ያለውን መንፈሳዊ ጥቅም ለመቅሰም አንድ ወይም ሁለት ሰዓት ሊወስድ ይችላል።
20 ምናልባት በየሳምንቱ ለጥቂት ሰዓታት ቴሌቪዥን ከማየት ተቆጥበን የግል ቅድስናችንን ለማጠናከር እንድንችል ራሳችንን መገሰጽ ያስፈልገን ይሆናል። ዘወትር ማጥናታችን ትክክለኛ ውሳኔዎችን ወይም በሌላ አባባል ወደ “ቅዱስ ኑሮ” የሚመሩንን ውሳኔዎች ለማድረግ አእምሮአችንን ስለሚያንቀሳቅስልን በመንፈሳዊ ይገነባናል።—2 ጴጥሮስ 3:11፤ ኤፌሶን 4:23 አዓት፤ 5:15, 16
21. መልስ የሚያስፈልጋቸው የትኞቹ ጥያቄዎች ናቸው?
21 ቀጥሎ የሚነሳው ጥያቄ ደግሞ ይሖዋ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እኛ ክርስቲያኖችም ቅዱስ መሆን የምንችልባቸው ተጨማሪ ዘርፎችና ድርጊቶች የትኞቹ ናቸው? የሚል ይሆናል። የሚቀጥለው ርዕስ ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡንን ጥቂት ነጥቦች ይዞልናል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ይህ ባለ ሁለት ጥራዝ የምርምር ጽሑፍ የተዘጋጀው ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ነው።
b “አያታልል” ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ሰፋ ያለ ግንዛቤ ለማግኘት “አምላክ የሚጠላው ምን ዓይነት ፍቺ ነው?” በሚል ርዕስ በየካቲት 1995 ንቁ! ገጽ 21 ላይ የወጣውን ሐሳብ ተመልከት።
c ቁማር ቅዱስ ያልሆነ ተግባር ነው የተባለበትን ምክንያት በይበልጥ ለመረዳት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን የሚያዚያ 1995 ንቁ! ገጽ 28-29 ተመልከት።
ታስታውሳለህን?
◻ የቅድስና ምንጭ ማን መሆኑ በእስራኤል ብሔር የተገለጠው እንዴት ነው?
◻ የእስራኤላውያን አምልኮ በሚልክያስ ዘመን ረክሶ የነበረው በምን መንገዶች ነው?
◻ ርኩስ ድርጊት የሚጀምረው ከየት ነው?
◻ ቅዱስ ለመሆን ምን መገንዘብ ይኖርብናል?
◻ ቅዱስ ሆነን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?