የማያዳላውን አምላካችንን እየመሰልከው ነውን?
የማያዳላ ሊኖር ይችላልን? ፈጽሞ የማያዳላ፣ ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻ የሌለበት፣ አንዱን ከሌላው የማያበላልጥ ወይም የዘር መድልዎ የማያደርግ አንድ አካል አለ። ይህ አካል የሰው ልጆች ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው። ሆኖም በ19ኛው መቶ ዘመን የነበረው እንግሊዛዊ ደራሲ ቻርልስ ላምብ ሰዎችን አስመልክቶ ሲጽፍ “በቀላል አነጋገር እኔ ጭፍን ጥላቻ የሞላብኝ ሰው ነኝ፤ አንዱን እወዳለሁ ሌላውን ደግሞ እጠላለሁ” በማለት በግልጽ ተናግሯል።
በሰው ልጆች ግንኙነት ውስጥ አድሎአዊነት በብዛት ይታያል። ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ጠቢቡ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን “ሰው ሰውን የሚገዛው ለጉዳቱ ነው” የሚል አስተያየት ሰንዝሮ ነበር። (መክብብ 8:9 አዓት) የዘር ጥላቻ፣ የብሔር ግጭቶችና በቤተሰብ መካከል የሚፈጠረው ፀብ እየተበራከተ መጥቷል። ታዲያ የሰው ልጆች በራሳቸው ችሎታ አድሎአዊነት የሌለበት ኅብረተሰብ ሊፈጥሩ ይችላሉ ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነውን?
የራሳችንን ዝንባሌዎች ለመቆጣጠርና ማናቸውንም በውስጣችን የተተከሉ መሠረተ ቢስ ጥላቻዎች ለማስወገድ የታሰበበት ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። (ኤፌሶን 4:22-24) ከራሳችን ቤተሰብ፣ ዘርና ብሔር መንጭተው በኅብረተሰባችንና በትምህርቱ ሥርዓት የዳበሩ አመለካከቶች ሳናውቀው ሊዋሃዱን ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ እምብዛም የማይጎዱ የሚመስሉ እነዚህ ዝንባሌዎች በውስጣችን ሥር ሰደው እንድናዳላ የሚያደርጉ አመለካከቶች ያስከትላሉ። ሎርድ ፍራንሲስ ጄፍሪ የተባሉ አንድ የስኮትላንድ ተወላጅ የሆኑ ዳኛና የጽሑፍ አዘጋጅ “ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻን ያህል የሰው ልጅ ሳያውቀው ለረጅም ጊዜ በውስጡ ተደብቆ የሚቆይ ነገር የለም” በማለት ሐቁን ሳይሸሽጉ ተናግረዋል።
ሊናa የአድሎአዊነትን ዝንባሌ ለመዋጋት የታሰበበት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል የሚል እምነት ካላቸው ሰዎች መካከል አንዷ ናት። በአንድ ግለሰብ ውስጥ የተተከለ መሠረተ ቢስ ጥላቻን ማስወገድ “ብዙ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል፤ ምክንያቱም አስተዳደግ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል” ብላለች። በተጨማሪም ሊና የማያቋርጡ ማሳሰቢያዎች እንደሚያስፈልጉ ታምናለች።
ይሖዋ የማያዳላ መሆኑን የሚያሳይ ታሪክ
ይሖዋ አያዳላም፤ በዚህ ረገድ ፍጹም ምሳሌ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ገጾች አንሥቶ ከሰዎች ጋር ባደረጋቸው ግንኙነቶች እንዴት አድሎአዊነት የሌለበት ተግባር እንደፈጸመ እናነባለን። ከእነዚህ ግሩም የሆኑ ምሳሌዎችና ማሳሰቢያዎች ብዙ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን።
ይሖዋ በ36 እዘአ አይሁዳዊው ሐዋርያ ጴጥሮስ ምሥራቹን ለቆርኔሌዎስና ለሌሎች አሕዛብ እንዲናገር ነገሮችን አቅጣጫ በማስያዝ እንደማያዳላ አሳይቷል። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ” ብሏል።—ሥራ 10:34, 35
ይሖዋ ከሰው ልጆች ጋር ባደረጋቸው ግንኙነቶች ሁሉ ምን ጊዜም የማያዳላ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አባቱ ሲናገር “እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፣ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባል” ብሏል። (ማቴዎስ 5:45) ከዚህም በላይ ጴጥሮስ ይሖዋ የማያዳላ አምላክ እንደሆነ ሲገልጽ “ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል” በማለት አወድሶታል።—2 ጴጥሮስ 3:9
በኖኅ ዘመን ‘ይሖዋ የሰው ክፋት በምድር ላይ እንደ በዛ፣ የልቡ ሐሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደሆነ’ ሲመለከት ያን የሰው ልጆች ዓለም ለማጥፋት ወሰነ። (ዘፍጥረት 6:5-7, 11, 12) ሆኖም ኖኅ ከአምላክ በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት በዘመኑ የነበሩ ሰዎች እያዩ መርከብ ሠራ። በተጨማሪም ኖኅ እሱና ልጆቹ መርከብ በሚሠሩበት ወቅት ‘ጽድቅን ይሰብክ’ ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:5) ይሖዋ የዚያን ትውልድ መጥፎ የልብ ዝንባሌ ቢያውቅም ያለ አድልዎ ግልጽ የሆነ መልእክት እንዲነገራቸው አድርጓል። ኖኅ መርከብ እንዲሠራና እንዲሰብክ በማድረግ አእምሯቸውንና ልባቸውን ቀስቅሶ ቀና ምላሽ እንዲሰጡ ለማድረግ ሞክሮ ነበር። ምንም እንኳ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት የሚችሉበት አጋጣሚ የነበራቸው ቢሆንም ‘የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ አላወቁም።’—ማቴዎስ 24:39
ይሖዋ እንደማያዳላ የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የአምላክ አገልጋዮች ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ያለ አድልዎ የመንግሥቱን ምሥራች እንዲያውጁ ያንቀሳቅሳቸዋል። ከዚህም በላይ የይሖዋን የበቀል ቀን ከማሳወቅ ወደ ኋላ አይሉም። በሕዝብ ፊት ያለ አድልዎ የይሖዋን መልእክት ለሰው ሁሉ ይናገራሉ።—ኢሳይያስ 61:1, 2
ይሖዋ የዕብራውያን አባቶች ለሆኑት ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ የገባላቸው ቃል የማያዳላ አምላክ መሆኑን ያረጋግጣል። ‘አሕዛብ ሁሉ ራሳቸውን የሚባርኩበት የተቀባው ዘር’ የሚመጣው በእነሱ የዘር ሐረግ በኩል ነው። (ዘፍጥረት 22:18፤ 26:4፤ 28:14) ይህ ቅቡዕ ክርስቶስ ኢየሱስ ሆነ። በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ አማካኝነት ታዛዥ የሰው ልጆች በሙሉ መዳን የሚችሉበትን መንገድ ይሖዋ አዘጋጅቶላቸዋል። አዎን፣ የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ጥቅሞች ያለ አድልዎ ለሁሉም ሰዎች ቀርበዋል።
በሙሴ ዘመን ከሰለጰዓድ ሴት ልጆች ጋር በተያያዘ ሁኔታም ይሖዋ የማያዳላ መሆኑ እጅግ ትኩረት በሚስብ መንገድ ታይቷል። እነዚህ አምስት ሴቶች በተስፋይቱ ምድር ውስጥ የአባታቸውን ርስት የማግኘት ችግር አጋጥሟቸው ነበር። ይህ የሆነው በእስራኤል ውስጥ ርስት የሚተላለፈው በግለሰቡ ወንድ ልጆች በኩል ስለ ነበር ነው። ሆኖም ሰለጰዓድ ርስቱን የሚረከብ ወንድ ልጅ ሳይወልድ ሞተ። ስለዚህ የሰለጰዓድ አምስት ሴት ልጆች ጉዳዩን አድልዎ በሌለበት መልኩ እንዲመለከትላቸው ለሙሴ ነገሩት፦ “ወንድ ልጅ ባይኖረው የአባታችን ስም ከወገኑ መካከል ለምን ይጠፋል? በአባታችን ወንድሞች መካከል ርስት ስጠን” አሉት። ይሖዋ ልመናቸውን አዳምጦ ሙሴን “ሰው ቢሞት ወንድ ልጅም ባይኖረው፣ ርስቱ ለሴት ልጁ ይለፍ” በማለት አዞታል።—ዘኁልቁ 27:1-11
አድልዎ የሌለበትን ፍቅር የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው! ሴት ልጆቹ ሲያገቡ የአንድ ነገድ ውርሻ ወደ ሌላ ነገድ እንዳይተላለፍ “ከአባታቸው ነገድ ብቻ” እንዲያገቡ ይፈለግባቸው ነበር።—ዘኁልቁ 36:5-12
መስፍንና ነቢይ በነበረው በሳሙኤል ዘመን ይሖዋ የማያዳላ መሆኑን ይበልጥ ግልጽ አድርጎ የሚያሳይ ጠለቅ ያለ ማስተዋል የሚሰጥ ሌላ ነገር ተፈጽሟል። ይሖዋ ሳሙኤልን በይሁዳ ነገድ ውስጥ ከሚገኘው ከቤተ ልሔማዊው ከእሴይ ቤተሰብ አንድ አዲስ ንጉሥ እንዲቀባ አዞት ነበር። ይሁን እንጂ እሴይ ስምንት ልጆች ነበሩት። ለንግሥና የሚቀባው ማን ነው? ሳሙኤል በኤልያብ አካላዊ ቁመና ተማርኮ ነበር። ሆኖም ይሖዋ በውጪያዊ መልክ ተመርቶ አይወስንም። ለሳሙኤል እንዲህ ብሎታል፦ “ፊቱን ወይም የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና፤ . . . ሰው ፊትን ያያል፣ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል።” የእሴይ የመጨረሻ ልጅ የነበረው ዳዊት ተመረጠ።—1 ሳሙኤል 16:1, 6-13
ይሖዋ ካሳየው አድሎአዊነት የሌለበት ባሕርይ መማር
ክርስቲያን ሽማግሌዎች የእምነት ጓደኛቸውን መንፈሳዊ ባሕርያት በመመልከት ይሖዋን ቢመስሉ ጥሩ ነው። የግል ስሜታችን የምንሰጠውን ፍርድ እንዲያጨልምብን በመፍቀድ አንድን ግለሰብ በራሳችን የአቋም ደረጃዎች መለካት ቀላል ነው። አንድ ሽማግሌ “ራሴ በፈጠርኩት መሠረት የሌለው ሐሳብ ሳይሆን ይሖዋን በሚያስደስት መንገድ ከሌሎች ጋር ግንኙነት ለማድረግ ጥረት አደርጋለሁ” በማለት ነጥቡን ገልጿል። የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ ቃሉን መመዘኛ አድርገው ቢጠቀሙበት ምንኛ ጠቃሚ ነው!
ከላይ የተገለጹት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌዎች አሁንም በውስጣችን ሊኖር የሚችለውን የዘር ወይም የብሔር ጥላቻ ለመዋጋት ያስችሉናል። አድልዎ ባለማድረግ ረገድ ይሖዋን በመምሰል ክርስቲያን ጉባኤን ከወገናዊነት ከመነጨ ጥላቻ፣ ከዘር መድልዎና አንዱን ከሌላው አስበልጦ ከማየት መንፈስ እንጠብቃለን።
ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘እግዚአብሔር እንደማያዳላ’ ተገንዝቧል። (ሥራ 10:34) አንዱን ከሌላው አስበልጦ መመልከት የአድሎአዊነት ባሕርይ ከመሆኑም በላይ የፍቅርና የአንድነት መሠረታዊ ሥርዓቶችን ያስጥሳል። ኢየሱስ ድሆችን፣ ደካሞችንና በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎችን ከማስደሰቱም በላይ ሸክማቸውን አቃሎላቸዋል። (ማቴዎስ 11:28-30) በሕዝቡ ላይ እንደ ጌቶች ሆነው ከባድ ደንቦችን ይጭኑባቸው ከነበሩት የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ፈጽሞ የተለየ አቋም ነበረው። (ሉቃስ 11:45, 46) ይህን ማድረግና ለሀብታሞችና ለታዋቂ ሰዎች ማዳላት ከክርስቶስ ትምህርቶች ጋር እንደማይስማማ ግልጽ ነው።—ያዕቆብ 2:1-4, 9
በዛሬው ጊዜ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለክርስቶስ አመራር ራሳቸውን የሚያስገዙ ሲሆን ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ ሕዝቦችን በሙሉ ያለ አድልዎ ይይዟቸዋል። ‘በእነሱ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ሲጠብቁ’ በኢኮኖሚ ደረጃ፣ በባሕርይ ልዩነቶች ወይም በቤተሰብ ትስስሮች ምክንያት ከማዳላት ይቆጠባሉ። (1 ጴጥሮስ 5:2) ክርስቲያን ሽማግሌዎች የማያዳላውን አምላክ በመምሰልና ማዳላትን በተመለከተ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ በመታዘዝ በጉባኤው ውስጥ አድልዎ የሌለበት መንፈስ እንዲስፋፋ ያደርጋሉ።
የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ ጉባኤ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ነው። ይህ ወንድማማችነት በክርስቶስ ኢየሱስ አመራር ሥር ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻና አድልዎ የሌለበት ኅብረተሰብ እውን ሊሆን እንደሚችል የሚያሳይ ሕያው ማስረጃ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ‘ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ለብሰዋል።’ (ኤፌሶን 4:24) አዎን፣ የማያዳላው አምላክ ይሖዋ ካሳየው ፍጹም ምሳሌ በመማር ላይ ናቸው፤ በተጨማሪም ከአድልዎ ነፃ በሆነ አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው።—2 ጴጥሮስ 3:13
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስሟ በሌላ ተተክቷል።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሐዋርያው ጴጥሮስ አምላክ እንደማያዳላ ተገንዝቧል