ልጃችሁ አዳሪ ትምህርት ቤት መግባት ይኖርበታልን?
የምትኖሩት በታዳጊ አገር በምትገኝ አንዲት ትንሽ ከተማ ነው እንበል። አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚማሩ ልጆች ይኖሯችሁና 12 ዓመት ሲሞላቸው ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይዛወራሉ። በአካባቢያችሁ ያለው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደግሞ ከአቅሙ በላይ ብዙ ተማሪዎችን የሚያስተናግድ፣ የውስጥ ድርጅቱ ያልተሟላና ብቃት ያላቸው አስተማሪዎች የሌሉት ይሆናል። አንዳንዴ ደግሞ በአድማ የተነሣ ትምህርት ቤቱ ለሳምንታትና ለወራት የሚዘጋበት ጊዜ ይኖራል።
በዚህ መሃል አንድ ሰው በአንድ ከተማ ስለሚገኝ አዳሪ ትምህርት ቤት የሚገልጽ በጣም ማራኪ የሆነ ብሮሹር ይሰጣችኋል። ብሮሹሩ ላይ ቆንጆ ልብስ የለበሱ ደስተኛ ተማሪዎች የውስጥ ድርጅታቸው በተሟሉ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ ሙከራዎችና ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ሆነው ሲያጠኑ የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ትመለከታላችሁ። ተማሪዎቹ ኮምፒዩተሮችን ይጠቀማሉ፣ ንጹህ በሆኑና በሚያምሩ የመኝታ ክፍሎች ውስጥ ተመችቷቸው ይኖራሉ። ከትምህርት ቤቱ ዓላማዎች አንዱ ተማሪዎች “እንደ አቅማቸው ከፍተኛ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ” እንደሆነ ብሮሹሩ ላይ ታነባላችሁ። በተጨማሪም እንዲህ የሚል ሐሳብ ታያላችሁ:- “ሁሉም ተማሪዎች ጨዋነት፣ ትሕትና፣ ወላጆችንና አረጋውያንን ማክበር፣ ትብብር፣ ታጋሽነት፣ ደግነት፣ ሐቀኝነት፣ ታማኝነት እንዲሁም አንድነት እንዲሰፍን በሚጥር ቤተሰብ ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸውን ዓይነት ባሕርያት እንዲያሳዩ ይጠበቅባቸዋል።”
ፈገግ ብሎ የሚታይ አንድ ወጣት “ወላጆቼ ከሁሉ በተሻለው ትምህርት ቤት ውስጥ እንድገባ በማድረጋቸው ያገኘሁት መብት አቻ የለውም” የሚል አስተያየት ሰጥቷል። አንዲት ልጃገረድ ደግሞ “ትምህርት ቤት አእምሮን የሚያሠራና የሚያስደስት ቦታ ነው። ይህ ትምህርት ቤት ደግሞ ለመማር የሚጋብዝ ነው” ብላለች። ልጃችሁን እዚህ አዳሪ ትምህርት ቤት ታስገባላችሁ?
ትምህርትና መንፈሳዊነት
ለልጆቻቸው የሚያስቡ ወላጆች ሁሉ ልጆቻቸው ለወደፊቱ ጥሩ መሠረት እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ፤ ለዚህ ደግሞ የተሟላና ሚዛናዊ የሆነ ትምህርት መቅሰሙ በጣም አስፈላጊ ነው። ብዙውን ጊዜ ሰብዓዊ ትምህርት ወደፊት ሥራ ማግኘት የሚችሉበትን አጋጣሚ የሚከፍት ከመሆኑም ሌላ ወጣቶች ወደፊት ራሳቸውንና የሚመሠርቱትን ቤተሰብ ለማስተዳደር የሚያስችል ብቃት እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል።
‘አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ ጥሩ ትምህርት የሚሰጥ ከሆነና አንዳንድ ሥነ ምግባራዊ ደንቦች ካሉ ለምን ይህን አጋጣሚ አንጠቀምም?’ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ክርስቲያን ወላጆች ለዚህ ጥያቄ መልስ ከመስጠታቸው በፊት በጸሎት ሊያስቡበት የሚገባ አንድ ጉዳይ አለ፤ ይኸውም የልጆቻቸው መንፈሳዊ ደህንነት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?” ሲል ጠይቋል። (ማርቆስ 8:36) ይህ አንዳችም ጥቅም እንደሌለው የታወቀ ነው። በመሆኑም ክርስቲያን ወላጆች ልጃቸውን አዳሪ ትምህርት ቤት ከማስገባታቸው በፊት በልጃቸው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት መመርመር ይኖርባቸዋል።
የሌሎች ተማሪዎች ተጽእኖ
በአንዳንድ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የትምህርት አሰጣጡ ጥራት በጣም ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በዚያ ትምህርት ቤት የሚማሩት ተማሪዎች አልፎ ተርፎም የአንዳንዶቹ የትምህርት ቤቱ ሠራተኞች የሥነ ምግባር አቋምስ እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ‘የመጨረሻ ቀን’ ስለሚኖሩት ሰዎች ሲናገር እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።”— 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
ይህ በሥነ ምግባራዊና በመንፈሳዊ ነገሮች ረገድ የሚታይ ማሽቆልቆል ምድር አቀፍ በመሆኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተው በመኖር ረገድ ለይሖዋ ምሥክሮች ፈታኝ ሆኗል። በየዕለቱ ወደ ቤታቸው የሚመለሱ ተማሪዎች ከዓለማዊ የክፍል ጓደኞቻቸው ጋር ያላቸው ውስን ቅርርብ እንኳ በመንፈሳዊነታቸው ላይ ጠንካራ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው ተገንዝበዋል። የይሖዋ ምሥክር ልጆች በየዕለቱ ከወላጆቻቸው ድጋፍ፣ ምክርና ማበረታቻ እያገኙም እንኳ ይህን ተጽዕኖ መከላከል ከባድ ትግል የሚጠይቅ ሊሆንባቸው ይችላል።
ታዲያ ከቤታቸው ርቀው በአዳሪ ትምህርት ቤቶች የሚገኙት ልጆች ሁኔታ ምን ይመስል ይሆን? ከአፍቃሪ ወላጆቻቸው ዘወትር ያገኙት ከነበረው መንፈሳዊ ድጋፍ ተለይተው ብቻቸውን ርቀው ይገኛሉ። በየቀኑ 24 ሰዓት ሙሉ ከክፍል ጓደኞቻቸው ስለማይለዩ ብዙሀኑን መስለው እንዲኖሩ የሚገጥማቸው ተጽእኖ በለጋ አእምሮና ልባቸው ላይ የሚያሳድረው ግፊት በቤታቸው ከሚኖሩት ተማሪዎች ይበልጥ ኃይለኛ ነው። “አዳሪ ትምህርት ቤት ያለ ተማሪ ከጠዋት እስከ ማታ የሥነ ምግባር አቋሙ ለአደጋ የተጋለጠ ነው” ሲል አንድ ተማሪ ተናግሯል።
ሐዋርያው ጳውሎስ “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ክርስቲያን ወላጆች ልጃቸው አምላክን ከማያገለግሉ ሰዎች ጋር ሌት ተቀን እየዋለ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ጉዳት አይደርስበትም ብለው በማሰብ ሊሳሳቱ አይገባም። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ አምላካዊ አክብሮት የነበራቸው ልጆች ክርስቲያናዊ ምግባርን አቃልለው ሊያዩ ወይም ለመንፈሳዊ ነገሮች ያላቸው አድናቆት ሊጠፋ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ወላጆች ይህን የልጆቻቸውን ሁኔታ የሚረዱት ልጆቹ ከአዳሪ ትምህርት ቤቱ ከወጡ በኋላ ነው። ከዚህ በኋላ ነገሮችን ለማስተካከል መሞከር ደግሞ ብዙውን ጊዜ የማይታሰብ ነው።
የክሌመንት ተሞክሮ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት ከመግባቴ በፊት ለእውነት ፍቅር ነበረኝ፣ ከወንድሞችም ጋር ወደ መስክ አገልግሎት እሄድ ነበር። በተለይ ደግሞ በቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ላይ መሳተፍ ያስደስተኝ ነበር። ይሁን እንጂ በ14 ዓመቴ ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት ከገባሁ በኋላ እውነትን እርግፍ አድርጌ ተውኩ። በአዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ ባሳለፍኳቸው አምስት ዓመታት በሙሉ ወደ ጉባኤ ስብሰባ ሄጄ አላውቅም። ክፉ ባልንጀሮች ስለነበሩኝ በአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነት፣ ሲጋራ በማጤስና ከልክ በላይ በመጠጣት ተጠመድኩ።”
የአስተማሪዎች ተጽዕኖ
በየትኛውም ትምህርት ቤት ሥልጣናቸውን አላግባብ የሚጠቀሙ በሥነ ምግባር ብልሹ የሆኑ አስተማሪዎች ሊኖሩ ይችላሉ። አንዳንዶቹ ጨካኞችና ርኅራኄ የሌላቸው ናቸው፤ ሌሎቹ ደግሞ ተማሪዎቻቸውን በጾታ ያስነውራሉ። በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደዚህ ያሉ አስተማሪዎች የሚፈጽሙት ድርጊት በአብዛኛው ተሸፋፍኖ ይቀራል።
ይሁን እንጂ አብዛኞቹ አስተማሪዎች ልጆቹ ፍሬያማ የኅብረተሰብ አባላት እንዲሆኑና በዙሪያቸው ካለው ዓለም ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ለማድረግ ከልባቸው ይጥራሉ። ይህም ቢሆን ለይሖዋ ምሥክሮች ልጆች አደጋ አለው። ዓለም ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ነገሮች አብዛኛውን ጊዜ ከክርስቲያን መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር አይስማሙም። አስተማሪዎች ተማሪዎቻቸውን ከዚህ ዓለም ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ቢያበረታቱም ኢየሱስ ተከታዮቹ ‘የዓለም ክፍል እንዳልሆኑ’ ተናግሯል።— ዮሐንስ 17:16
ልጆች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በመከተላቸው ችግሮች ቢነሱስ? ልጆቹ በአቅራቢያቸው በሚገኝ ትምህርት ቤት የሚማሩና እቤታቸው የሚኖሩ ቢሆን ኖሮ ከወላጆቻቸው ጋር ስለጉዳዩ መወያየት ይችሉ ነበር። ወላጆችም ለልጆቻቸው መመሪያ ሊሰጧቸውና አስተማሪውንም ሊያነጋግሩት ይችላሉ። በመሆኑም አብዛኛውን ጊዜ ችግሮችና አለመግባባቶች ወዲያው መፍትሔ ያገኛሉ።
በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ግን ሁኔታው የተለየ ነው። እነዚህ ተማሪዎች ዘወትር በአስተማሪዎቻቸው ቁጥጥር ሥር ናቸው። ልጆች ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ደግፈው ቢቆሙ እንኳ ይህንን የሚያደርጉት የዕለት ተዕለት የወላጆቻቸው እገዛ ሳይታከልበት ነው። አንዳንድ ጊዜ ልጆች እነዚህን በመሰሉ ሁኔታዎች ሥርም ለአምላክ የታመኑ ሆነው ይቆማሉ። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ማድረግ ይሳናቸዋል። አንድ ልጅ ለአስተማሪው ፍላጎት መንበርከኩ አይቀርም።
የተገደበ እንቅስቃሴ
በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተማሪዎች እንደ ልብ መግባት መውጣት የሚችሉ ሲሆን በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ግን የተማሪዎች እንቅስቃሴ የተገደበ ነው። ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች መካከል ብዙዎቹ እሁድ ዕለት ካልሆነ በቀር ተማሪዎች የትምህርት ቤቱን ቅጥር ግቢ ለቀው እንዲወጡ የማይፈቅዱላቸው ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ከነጭራሹ ይህንንም እንኳ አይፈቅዱም። ኤሩ የተባለች አንዲት የ11 ዓመት የአዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ እንዲህ ብላለች:- “የትምህርት ቤቱ ባለ ሥልጣኖች ለስብከት ይቅርና ለጉባኤ ስብሰባዎችም እንኳን እንድንሄድ አይፈቅዱልንም። በትምህርት ቤቱ ውስጥ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚካሄደው ለካቶሊኮችና ለእስላሞች ብቻ ነው። ሁሉም ተማሪ ከሁለት አንዱን መምረጥ አለበት፤ አለዚያ ግን ከተማሪዎችና ከአስተማሪዎች የከረረ ጥላቻ ይገጥመዋል። ከዚህ በተጨማሪ ተማሪዎች ብሔራዊና የቤተ ክርስቲያን መዝሙር እንዲዘምሩ ይገደዳሉ።”
ወላጆች ልጆቻቸውን እንደነዚህ ዓይነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሲያስገቡ ለወጣት ልጆቻቸው የሚያስተላልፉት መልእክት ምንድን ነው? ሰብዓዊ ትምህርት ለአምልኮ ከመሰብሰብ እንዲሁም ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ከመካፈል አልፎ ተርፎም ለአምላክ ንጹሕ አቋምን ከመጠበቅ ይበልጣል የሚል መልእክት ሊሆን ይችላል።— ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20፤ 2 ቆሮንቶስ 6:14-18፤ ዕብራውያን 10:24, 25
በአንዳንድ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የይሖዋ ምሥክር ተማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስን አንድ ላይ ማጥናት ችለዋል፤ ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ ነው። ብሌሲኝ የተባለች አንዲት የ16 ዓመት ወጣት እርሷ ስላለችበት አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲህ ብላለች:- “ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች በየዕለቱ ለመጸለይ ይሰበሰባሉ። እኛ የራሳችንን ጥናት ለማድረግ እንዲፈቀድልን እንጠይቃለን፤ ይሁን እንጂ የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎች ድርጅታችሁ እውቅና የለውም ይሉናል። ከእነርሱ ጋር እንድንጸልይ ሊያስገድዱን ይሞክራሉ። እንቢ ካልን ይቀጡናል። ለአስተማሪዎች መናገር ደግሞ ጉዳዩን ማባባስ ነው። የማያወጡልን የስም ዓይነት የለም፤ ከዚያም የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎች እንዲቀጡን ይደረጋል።”
የተለየ አቋም መያዝ
በአዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ ያሉ ተማሪዎች የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸው በግልጽ መታወቁ ለእነርሱ ጥቅም አለው። የትምህርት ቤቱ ባለ ሥልጣኖች ከምሥክሮቹ እምነት ጋር በሚቃረኑ የሐሰት ሃይማኖት ግዴታዎች ላለመካፈል ፈቃድ ሊሰጧቸው ይችላሉ። ሌሎች ተማሪዎችም በመጥፎ ድርጊቶችና ውይይቶች ውስጥ እነርሱን ለመጨመር ከመሞከር ሊታቀቡ ይችላሉ። ለሌሎች ተማሪዎችና ለአስተማሪዎች የመመሥከር አጋጣሚ ሊከፍትላቸው ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ በክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመሩ ተማሪዎች አንድ ከባድ ጥፋት ቢፈጸም እነርሱ ይሆናሉ ተብለው ካለመጠርጠራቸውም በላይ አንዳንድ ጊዜ የአስተማሪዎችንና የሌሎች ተማሪዎችን አክብሮት ያተርፋሉ።
ይሁን እንጂ ሁልጊዜ ነገሮች እንደዚህ ይቃናሉ ማለት አይደለም። ብዙውን ጊዜ አንድ ወጣት የተለየ አቋም መያዙ በተማሪዎችና በአስተማሪዎችም ዘንድ የጥቃትና የፌዝ ዒላማ ያደርገዋል። ዪንካ የሚባል በአዳሪ ትምህርት ቤት የሚማር አንድ የ15 ዓመት ልጅ እንዲህ ብሏል:- “የይሖዋ ምሥክር መሆናችሁ በትምህርት ቤት ውስጥ ከታወቀ የጥቃት ዒላማ ትሆናላችሁ። መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ አቋማችንን ስለሚያውቁ እኛን የሚይዙበትን ወጥመድ ይዘረጋሉ።”
የወላጅ ኃላፊነት
የትኛውም አስተማሪ፣ ትምህርት ቤት ወይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ልጆች ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ አገልጋዮች እንዲሆኑ ለማድረግ እንደማይጥር የተረጋገጠ ነው። ይህ የእነርሱ ሥራም ሆነ ኃላፊነት አይደለም። የአምላክ ቃል የልጆቻቸውን መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት ያለባቸው ወላጆች ራሳቸው እንደሆኑ ይገልጻል። ጳውሎስ “እናንተም አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቈጡአቸው” ሲል ጽፏል። (ኤፌሶን 6:4) ልጆቻቸው ከእነርሱ ርቀው በወር ከአንድ ወይም ከሁለት ጊዜ በላይ መገናኘት በማይችሉበት አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኙ ከሆነ ወላጆች ይህንን መለኮታዊ ምክር እንዴት ሊሠሩበት ይችላሉ?
የእያንዳንዱ ሰው ሁኔታ በእጅጉ የተለያየ ነው፤ ይሁን እንጂ ክርስቲያን ወላጆች በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው ከሚከተለው ሐሳብ ጋር ለመስማማት መጣር ይኖርባቸዋል:- “ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፣ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።”— 1 ጢሞቴዎስ 5:8
ሌላ አማራጮች ይኖራሉን?
ወላጆች ምርጫው ሁለት ብቻ ይኸውም አዳሪ ትምህርት ቤት ማስገባት አለዚያም የተሟላ የውስጥ ድርጅት በሌለው የአካባቢው ትምህርት ቤት ውስጥ ማስተማር ብቻ ሲሆን ምን ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የገጠማቸው አንዳንዶች ልጆቻቸው በአካባቢው ትምህርት ቤት ከሚያገኙት ትምህርት በተጨማሪ በግል አስተማሪዎችን ቀጥረው ልጆቻቸውን ያስተምራሉ። ሌሎች ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸውን ራሳቸው ለመርዳት ጊዜ መድበዋል።
አንዳንድ ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸው ሁለተኛ ደረጃ ስለሚገቡበት ጊዜ አስቀድመው ጥሩ ዕቅድ በማውጣት ችግሮችን ያስቀራሉ። ትናንሽ ልጆች ካሏችሁ ወይም ልጆች ወልዳችሁ ለማሳደግ ዕቅድ ካላችሁ በአካባቢያችሁ ብቃት ያለው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መኖር አለመኖሩን ልታረጋግጡ ትችላላችሁ። ካልሆነ ትምህርት ቤት ወዳለበት አካባቢ ቀረብ የሚል ቤት ልትቀይሩ ትችላላችሁ።
አንድ ልጅ በውስጡ የይሖዋ ፍቅር እንዲያድርበት ለማድረግ ጥሩ ችሎታ፣ ትዕግሥትና ብዙ ጊዜ እንደሚጠይቅ ወላጆች አሳምረው ያውቃሉ። አንድ ልጅ በቤት ውስጥ እየኖረ እንኳ ይህን ማድረግ አስቸጋሪ ከሆነ ርቆ ሲኖርማ እንዴት ይባስ አስቸጋሪ ይሆናል! ይህ የልጁን የዘላለም ሕይወት የሚነካ ጉዳይ ስለሆነ ወላጆች ልጃቸውን አዳሪ ትምህርት ቤት ማስገባታቸው ሊያስከትለው ከሚችለው አደጋ የሚበልጥ ጥቅም ያለው መሆኑንና አለመሆኑን በቁምነገር በጸሎት ሊያስቡበት ይገባል። አንድ ልጅ በአዳሪ ትምህርት ቤት የሚሰጠውን ትምህርት እንዲያገኝ ሲባል መንፈሳዊ ፍላጎቱን መሠዋት የአርቆ አሳቢነት ጉድለት ይሆናል! ይህ አንዲትን ትንሽ ጌጥ ለማውጣት በእሳት በተያያዘ ቤት ውስጥ ዘሎ ከመግባት ምንም አይለይም፤ ይህ ደግሞ ትርፉ መንደድ ነው።
የአምላክ ቃል “ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጎዳሉ” ይላል። (ምሳሌ 22:3) መጥፎ ሁኔታ ከተፈጠረ በኋላ ችግሩን ለማስተካከል ከመሞከር አስቀድሞ መከላከሉ የተሻለ ነው። ‘ልጃችን አዳሪ ትምህርት ቤት መግባት ይኖርበታልን’ ብላችሁ አስባችሁበት እንደሆነና እንዳልሆነ ራሳችሁን መጠየቃችሁ ብልህነት ነው።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ወጣት ምሥክሮች ስለ አዳሪ ትምህርት ቤት የሰጡት አስተያየት
“አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ ያሉ የይሖዋ ምሥክር ልጆች ከማንኛውም ዓይነት መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ጋር ያላቸው ግንኙነት ይቋረጣል። ክፉ ነገር የማድረግ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያለበትና ጥላቻ የሞላበት ቦታ ነው።”— ከ11 እስከ 14 ዓመት ዕድሜዋ ድረስ በአዳሪ ትምህርት ቤት የቆየችው ሮቲሚ።
“በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው። ስብሰባ ላይ መገኘት እችል የነበረው እሁድ ዕለት ብቻ ነበር፤ ይህንንም ተማሪዎቹ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ ሲሰለፉ ተደብቄ እየወጣሁ ነው። ቤቴ እያለሁ በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች መካፈልና ቅዳሜና እሁድ ወደ አገልግሎት መሄድ እችል ስለነበር ትምህርት ቤት በነበርኩበት ጊዜ ፈጽሞ ደስተኛ ሆኜ አላውቅም። በትምህርት ቤት ያሳለፍኩት ጊዜ የሚያንጽ አልነበረም። ብዙ ነገር አምልጦኛል።”— በትምህርት ቤት ውስጥ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች አልካፈልም በማለቷ ዘወትር አስተማሪዎቿ ይደበድቧት የነበረችው ኤስተር።
“በአዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ ለሌሎች ተማሪዎች መመስከር ቀላል አልነበረም። የተለየ አቋም መያዝም ቀላል አይደለም። ብዙሐኑ የሚያደርጉትን ለመከተል እፈልግ ነበር። ወደ ስብሰባዎች ብሄድና በመስክ አገልግሎት ብካፈል ኖሮ ምናልባት የበለጠ ድፍረት አገኝ ነበር። ግን ይህንን ማድረግ የምችለው በዓመት ሦስት ጊዜ እረፍት ስወጣ ብቻ ነበር። ኩራዛችሁ ጋዝ ካልተሞላ ብርሃኑ እየደበዘዘ ይሄዳል። በትምህርት ቤት ያጋጠመኝ ሁኔታ ከዚህ የተለየ አልነበረም።”— ከ11 እስከ 16 ዓመት ዕድሜዋ በአዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ የተማረችው ላራ።
“አሁን ከአዳሪ ትምህርት ቤት ወጥቻለሁ፤ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት፣ በመስክ አገልግሎት ለመሳተፍና ከሌሎች ቤተሰቡ አባላት ጋር የዕለት ጥቅስ ለማድረግ በመቻሌ ደስተኛ ነኝ። በትምህርት ቤት ውስጥ መቆየት አንዳንድ ጥቅሞች ቢኖሩትም ከይሖዋ ጋር ካለኝ ዝምድና ግን የሚበልጥ ነገር የለም።”— ከአዳሪ ትምህርት ቤት እንዲያስወጣት አባቷን ያሳመነችው ናኦሚ።