ከወጣትነቴ ጀምሮ ይሖዋን በትዕግሥት ተጠባብቄያለሁ
በሩዶልፍ ግራይሸን እንደተነገረው
ገና የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ ኀዘን ቤተሰባችንን እንደ መብረቅ መታው። በመጀመሪያ አባቴ ታሰረ። ከዚያም እህቴንና እኔን አስገድደው በመውሰድ ከቤታችን ርቀን ከማናውቃቸው ሰዎች ጋር እንድንኖር አደረጉን። ከጊዜ በኋላ እናቴና እኔ በጌስታፖዎች ተያዝን። እኔ ወደ እስር ቤት እሷ ደግሞ ወደ ማጎሪያ ካምፕ ተወሰድን።
እነዚህ ደረጃ በደረጃ የተፈጸሙ ክስተቶች የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ ምክንያት በወጣትነቴ ከደረሰብኝ አስከፊ ስደት የመጀመሪያዎቹ ብቻ ነበሩ። በአረመኔያዊ ድርጊቱ የሚታወሰው የናዚ ጌስታፖ በኋላም የምሥራቅ ጀርመኑ ሽታዚ ለአምላክ ያለኝን የጸና አቋም እንድለውጥ ለማድረግ ሞክረዋል። ራሴን ለአምላክ ወስኜ ለ50 ዓመታት ያህል ላገለግለው በመቻሌ ልክ እንደ መዝሙራዊው “ከትንሽነቴ ጀምሮ ብዙ ጊዜ ተሰለፉብኝ፤ ነገር ግን አላሸነፉኝም” ብዬ መናገር እችላለሁ። (መዝሙር 129:2) ይሖዋ ታላቅ ባለውለታዬ ነው!
የተወለድኩት ሰኔ 2, 1925 በጀርመን ላይፕሲግ አቅራቢያ በምትገኘው ሉካ ተብላ በምትጠራ አነስተኛ ከተማ ውስጥ ነው። ወላጆቼ ማለትም አልፍሬትና ተሬዛ ከመወለዴ በፊትም በዚያን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እየተባሉ ይጠሩ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች በሚያትሟቸው ጽሑፎች አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለይተው ማወቅ ችለው ነበር። ቤታችን ውስጥ ግድግዳ ላይ ተሰቅለው የነበሩትን የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክቶች የሚያንጸባርቁ ሥዕሎች በየቀኑ እመለከት እንደነበረ አስታውሳለሁ። ከሥዕሎቹ መካከል አንዱ ተኩላና የበግ ጠቦት፣ ነብርና የፍየል ጠቦት፣ እንዲሁም አንበሳና ፍሪዳ በሰላም አንድ ላይ ሆነው አንድ ትንሽ ልጅ ሲመራቸው የሚያሳይ ነበር። (ኢሳይያስ 11:6-9) እንዲህ ዓይነቶቹ ሥዕሎች በውስጤ አንድ የማይፋቅ አሻራ ቀርጸዋል።
ወላጆቼ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም በጉባኤ እንቅስቃሴዎች እንድሳተፍ ያደርጉኝ ነበር። ለምሳሌ ያህል ሂትለር ሥልጣን ከያዘ ከጥቂት ቀናት በኋላ የካቲት 1933 ላይ ስላይዶች፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎችና በቴፕ የተቀረጸ ትረካ ያለው “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለው ፊልም በትንሿ ከተማችን ውስጥ ይታይ ነበር። ገና የሰባት ዓመት ልጅ ሳለሁ በከተማው ውስጥ አንድ ላይ ሆነው በሰልፍ በመጓዝ “ፎቶ ድራማውን” ከሚያስተዋውቁት ወንድሞች ጋር በአንድ አነስተኛ የጭነት መኪና ላይ ከኋላ ተጭኜ መጓዝ በመቻሌ በጣም ተደስቼ ነበር! ገና ትንሽ ልጅ የነበርኩ ቢሆንም ወንድሞች በዚህና በሌሎች አጋጣሚዎችም በመጠቀም የጉባኤው ጠቃሚ አባል እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደርጉ ነበር። ስለዚህ ይሖዋ ከትንሽነቴ ጀምሮ ያስተማረኝ ከመሆኑም በላይ ቃሉ በጎ ተጽእኖ ሊያሳድርብኝ ችሏል።
በይሖዋ መታመንን መማር
የይሖዋ ምሥክሮች ጥብቅ የሆነ ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋም ስላላቸው በናዚ ፖለቲካ ውስጥ ምንም ተሳትፎ አላደረጉም ነበር። በዚህም ምክንያት በ1933 ናዚዎች እንዳንሰብክ፣ እንዳንሰበሰብና አልፎ ተርፎም የራሳችንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች እንዳናነብ የሚያግድ ሕግ አወጡ። መስከረም 1937 አባቴን ጨምሮ በጉባኤያችን የሚገኙ ወንድሞች በሙሉ በጌስታፖዎች ተይዘው ተወሰዱ። ወንድሞች በመታሰራቸው በጣም አዘንኩ። አባቴ አምስት ዓመት እንዲታሰር ተፈረደበት።
ቤት ላለነውም ሁኔታዎቹ በጣም አስቸጋሪ እየሆኑ መጡ። ሆኖም ወዲያውኑ በይሖዋ መታመንን ተማርን። አንድ ቀን ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ስመለስ እናቴ መጠበቂያ ግንብ እያነበበች ነበር። መጽሔቱን አንድ አነስተኛ ኮመዲኖ አናት ላይ አስቀምጣ ቀለል ያለ ምሳ ልትሠራልኝ ተነሳች። ከምሳ በኋላ ዕቃዎቹን እያነሳሳን ሳለ በሩ በኃይል ተንኳኳ። በሩን ያንኳኳው ቤታችን ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ይገኙ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመፈተሽ የመጣ አንድ ፖሊስ ነበር። እኔ በጣም ፈራሁ።
ቀኑ አለወትሮው በጣም ይሞቅ ነበር። ስለዚህ ፖሊሱ በመጀመሪያ የራስ ቁሩን አውልቆ ጠረጴዛ ላይ አስቀመጠው። ከዚያም ፍተሻውን ጀመረ። ጠረጴዛው ሥር አጎንብሶ እየፈለገ ሳለ የራስ ቁሩ ከጠረጴዛው ላይ ተንከባሎ ሊወድቅ ሲል እናቴ ወዲያውኑ አነሳችና ኮመዲኖው ላይ ባለው መጠበቂያ ግንብ ላይ አስቀመጠችው! ፖሊሱ ቤታችንን ከላይ እስከ ታች ቢበረብርም ምንም ጽሑፍ ሊያገኝ አልቻለም። ከራስ ቁሩ ሥር የመመልከት ሐሳብ ፈጽሞ ወደ አእምሮው አልመጣም ነበር። ተመልሶ ሊሄድ ሲል እጁን ወደ ኋላ ሰዶ የራስ ቁሩን እያነሳ ለእናቴ የይቅርታ ቃል አጉተመተመ። እንዴት ያለ እፎይታ እንደተሰማኝ ልነግራችሁ አልችልም!
እንዲህ ዓይነቶቹ ተሞክሮዎች ይበልጥ ከባድ ለሆኑ ፈተናዎች እንድዘጋጅ አደረጉኝ። ለምሳሌ ያህል በትምህርት ቤት ውስጥ ልጆች በወታደራዊ ዲስፕሊን በሚሠለጥኑበትና በናዚ ፍልስፍና እንዲያምኑ በሚደረግበት የሂትለር ወጣቶች ድርጅት ውስጥ እንድገባ ተጽእኖ ይደረግብኝ ነበር። አንዳንድ አስተማሪዎች ተማሪዎቻቸው 100 በመቶ በዚህ ድርጅት ውስጥ እንዲሳተፉ የማድረግ ግብ ነበራቸው። ሄር ሽናይደር የተባለው አስተማሪዬ ዕቅዱ እንደከሸፈበት ሆኖ እንደተሰማው እገምታለሁ፤ ምክንያቱም በትምህርት ቤቱ ውስጥ ያሉት ሌሎች አስተማሪዎች በሙሉ ሲሳካላቸው እሱ ግን በአንድ ተማሪ የተነሣ ተማሪዎቹን መቶ በመቶ ለማሳተፍ የነበረው ግብ ሊሰምርለት አልቻለም። ያ ተማሪ እኔ ነበርኩ።
አንድ ቀን ሄር ሽናይደር “ልጆች፣ ነገ ለሽርሽር ወደ አንድ ቦታ እንሄዳለን” ብሎ ለክፍሉ ተማሪዎች በሙሉ ተናገረ። ሁሉም ደስ አላቸው። ከዚያም “በጎዳናዎች ላይ ስንጓዝ ሁሉም ሰው ጥሩ የሂትለር ልጆች መሆናችሁን እንዲያውቅ የሂትለር ወጣቶች ድርጅት ዩኒፎርማችሁን ለብሳችሁ መምጣት አለባችሁ” ሲል አክሎ ተናገረ። በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ከእኔ በቀር ሁሉም ልጆች ዩኒፎርማቸውን ለብሰው መጡ። አስተማሪው ጠራኝና በክፍላችን ተማሪዎች ፊት አቁሞ “መጀመሪያ ሌሎቹን ልጆች በሙሉ ተመልከትና ከዚያ ራስህን እይ” አለኝ። ከዚያም አክሎ “ወላጆችህ ድሆች ስለሆኑ ዩኒፎርም ሊገዙልህ እንደማይችሉ አውቃለሁ፤ ግን አንድ ነገር ላሳይህ” አለኝ። ወደ ራሱ ዴስክ ወሰደኝና “ይህን አዲስ ዩኒፎርም ልሰጥህ እፈልጋለሁ። አያምርም?” አለኝ።
የናዚን ዩኒፎርም ከመልበስ ሞትን እመርጥ ነበር። አስተማሪዬ ዩኒፎርሙን ለመልበስ እንዳልፈለኩ ሲረዳ ተናደደ፤ የክፍሉ ተማሪዎች በሙሉ አንድ ላይ በመጮኽ አላገጡብኝ። ከዚያ በኋላ እኔን ሰዎች እንዳያዩኝ ዩኒፎርም በለበሱት ተማሪዎች መካከል ሆኜ እንድሄድ በማድረግ ወደ ሽርሽር ይዞን ሄደ። ይሁን እንጂ እኔ ብቻ ከክፍሌ ተማሪዎች የተለየ ልብስ ለብሼ ስለነበረ በከተማው ውስጥ የነበሩ ብዙ ሰዎች ተመለከቱኝ። ወላጆቼና እኔ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆንን ሁሉም ሰው ያውቅ ነበር። ይሖዋ፣ ልጅ በነበርኩበት ጊዜ የሚያስፈልገኝን መንፈሳዊ ጥንካሬ ስለሰጠኝ በጣም አመሰግነዋለሁ።
ስደቱ ተፋፋመ
በ1938 መጀመሪያ ላይ አንድ ቀን እኔና እህቴ ከትምህርት ቤት በአንድ የፖሊስ መኪና ተጭነን 80 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በሽታትሮዳ ከተማ ወደሚገኝ የፀባይ ማረሚያ ትምህርት ቤት ተወሰድን። ወደዚያ የተወሰድነው ለምንድን ነው? ፍርድ ቤቱ እኛን ከወላጆቻችን ተጽእኖ ለማራቅና የናዚ ልጆች አድርጎ ለመለወጥ ወስኖ ስለነበረ ነው። ብዙም ሳይቆይ የትምህርት ቤቱ ፐርሶኔል እኔና እህቴ በክርስቲያናዊ ገለልተኝነታችን ጽኑ አቋም ያለን ብንሆንም እንኳ ሰው አክባሪዎችና ታዛዦች መሆናችንን ተረዳ። ዲሬክተሯ በጣም በመገረሟ እናታችንን በግል ማነጋገር ፈለገች። ወላጆች መጥተው ልጆቻቸውን መጠየቅ የማይፈቀድላቸው ቢሆንም እናታችን መጥታ እንድትጠይቀን ተፈቀደላት። እህቴ፣ እናቴና እኔ አንድ ሙሉ ቀን አንድ ላይ ሆነን እርስ በርሳችን መበረታታት በመቻላችን በጣም ከመደሰታችንም በላይ ይሖዋ ይህን አጋጣሚ ስለሰጠን አመሰገንነው። ይህ ማበረታቻ በጣም ያስፈልገን ነበር።
በፀባይ ማረሚያው ትምህርት ቤት ውስጥ ለአራት ወራት ያህል ቆየን። ከዚያም በፓና ከሚገኝ አንድ ቤተሰብ ጋር እንድንኖር ተደረገ። ከዘመዶቻችን ጋር እንዳያገናኙን መመሪያ ተሰጥቷቸው ነበር። እናቴ እንኳን መጥታ ልትጠይቀን አትችልም ነበር። ሆኖም እኛን ማግኘት የምትችልባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች ተፈጥረው ነበር። እናቴ እነዚህን የማይገኙ አጋጣሚዎች በመጠቀም ይሖዋ ምንም ዓይነት ፈተናዎችና ሁኔታዎች እንዲደርሱብን ቢፈቅድ ምንጊዜም ለእሱ ታማኝ ሆነን ለመቆም የሚያስችል ቆራጥ የሆነ ውሳኔ በውስጣችን ለመትከል የምትችለውን ሁሉ ጥረት አድርጋለች።—1 ቆሮንቶስ 10:13
ደግሞም ፈተናዎቹ መምጣታቸው አልቀረም። ገና የ17 ዓመት ልጅ ሳለሁ ታኅሣሥ 15, 1942 በጌስታፖዎች ተያዝኩና በጌረ በሚገኝ ማቆያ ማዕከል ውስጥ እንድገባ ተደረገ። ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ እናቴም ተያዘችና እኔ ወደነበርኩበት እስር ቤት ገባች። ዕድሜዬ ገና ስላልደረሰ ፍርድ ቤቱ ችሎት ፊት ሊያቀርበኝ አይችልም ነበር። ፍርድ ቤቱ 18 ዓመት እስኪሞላኝ ድረስ እየጠበቀ ስለነበር እናቴና እኔ ተይዘን ለስድስት ወራት ያህል ቆየን። ልክ 18 ዓመት ሲሞላኝ በዚያኑ ዕለት እናቴና እኔ ችሎት ፊት ቀረብን።
እኔ ምን እየተከናወነ እንዳለ እንኳ ሳላውቅ ሁሉ ነገር አልቆ ነበር። እናቴን ዳግመኛ እንደማላያት ፈጽሞ አላወቅኩም ነበር። ለመጨረሻ ጊዜ ያየኋት ፍርድ ቤት ውስጥ በጥቁር አግዳሚ የእንጨት ወንበር ላይ ከጎኔ ተቀምጣ በነበረችበት ጊዜ ነበር። ሁለታችንም ጥፋተኛ ናችሁ ተብሎ ተፈረደብን። እኔ አራት ዓመት እናቴ ደግሞ አንድ ዓመት ተኩል እንድንታሰር ተፈረደብን።
በዚያ ዘመን በእስር ቤቶችና በካምፖች ውስጥ የታሰሩ በሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። እኔ ግን የተላክሁት ከእኔ በቀር ሌላ የይሖዋ ምሥክር ወደሌለበት በሽቶልበርግ ወደሚገኘው እስር ቤት ነበር። ከአንድ ዓመት በላይ ብቻዬን ታሰርኩ፤ ሆኖም ይሖዋ ከእኔ ጋር ነበር። በወጣትነቴ ዘመን ለይሖዋ ያዳበርኩት ፍቅር በመንፈሳዊ ሕያው ሆኜ እንድቀጥል ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
በእስር ቤት ውስጥ ሁለት ዓመት ተኩል ካሳለፍኩ በኋላ ግንቦት 9, 1945 ላይ ጦርነቱ ማክተሙን የሚያበስር ምሥራች ሰማን! በዚያው ቀን ተለቀቅኩ። በእግሬ 110 ኪሎ ሜትር ከተጓዝኩ በኋላ በድካምና በረሃብ የተነሳ ታምሜ እቤት ደረስኩ። እንደገና ጤንነቴን መልሼ ለማግኘት በርካታ ወራት ወስዶብኛል።
እቤት እንደደረስኩ በርካታ አሳዛኝ ዜናዎች ሰማሁ። የመጀመሪያው እናቴን የሚመለከት ነበር። አንድ ዓመት ተኩል ያህል ከታሰረች በኋላ ናዚዎች በይሖዋ ላይ ያላትን እምነት መካዷን የሚገልጽ ሰነድ እንድትፈርም ጠየቋት። ፈቃደኛ አልሆነችም። ስለዚህ ጌስታፖዎች በራቨንስብሩክ ወደሚገኘው የሴቶች ማጎሪያ ካምፕ ወሰዷት። እዚያ ከገባች በኋላ ጦርነቱ ሊያበቃ አካባቢ በተስቦ ሞተች። አንድም ጊዜ ወደ ኋላ ሳትል ለእምነቷ ጠንክራ የተጋደለች በጣም ደፋር ክርስቲያን ነበረች። ይሖዋ በምሕረቱ ያስባት።
ራሱን ለይሖዋ ያልወሰነውን ታላቅ ወንድሜን ቨርነርን በተመለከተ ደግሞ አንድ ሌላ ነገር ሰማሁ። ከጀርመን ጦር ሠራዊት ጎን ተሰልፎ ሲዋጋ ሩስያ ውስጥ ተገደለ። አባቴስ ምን ሆኖ ይሆን? አባቴ ወደ ቤት ተመልሷል፤ የሚያሳዝነው ግን እምነታቸውን መካዳቸውን በሚገልጸው ሰነድ ላይ ከፈረሙት በጣት የሚቆጠሩ ምሥክሮች አንዱ ነበር። ባገኘሁት ጊዜ ፊቱ በኀዘን ተውጦና አእምሮው ተረብሾ ነበር።—2 ጴጥሮስ 2:20
ለአጭር ጊዜ የቆየ ቅንዓት የተሞላበት መንፈሳዊ እንቅስቃሴ
መጋቢት 10, 1946 ከጦርነቱ በኋላ ለእኔ የመጀመሪያ በሆነውና በላይፕሲግ በተካሄደው ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። የጥምቀት ሥነ ሥርዓት በዚያው ዕለት እንደሚከናወን ሲነገር ምንኛ እንደተደሰትኩ ልነግራችሁ አልችልም! ምንም እንኳ ከብዙ ዓመታት በፊት ራሴን ለይሖዋ የወሰንኩ ቢሆንም መጠመቅ የምችልበት አጋጣሚ ሳገኝ ይህ የመጀመሪያዬ ነበር። ያን ዕለት ፈጽሞ አልረሳውም።
ለአንድ ወር ያህል በአቅኚነት ካገለገልኩ በኋላ መጋቢት 1, 1947 ላይ በማግደበርግ ወደሚገኘው ቤቴል ተጠራሁ። የማኅበሩ ቢሮዎች በቦምብ ድብደባ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ነበር። በጥገናው ሥራ የመርዳት ልዩ መብት አገኘሁ! ከዚያ የበጋ ወቅት በኋላ በቪተንበርግ ከተማ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። በጥቂት ወራት ውስጥ ለሌሎች ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች በመስበክ ከ200 ሰዓት በላይ አሳለፍኩ። እንደገና ነፃ በመሆኔና ጦርነት፣ ስደትና እስር ባለመኖሩ በጣም ተደስቼ ነበር!
ይህ ነፃነት በአጭር መቀጨቱ ያሳዝናል። ከጦርነቱ በኋላ ጀርመን ለሁለት ተከፈለችና እኔ ያለሁበት ሥፍራ በኮሙኒስቶች ቁጥጥር ሥር ወደቀ። በመስከረም ወር 1950 ሽታዚ በመባል የሚታወቀው የምሥራቅ ጀርመን ምሥጢራዊ ፖሊስ በዘዴ ወንድሞችን መያዝ ጀመረ። የቀረቡብኝ ክሶች በጣም የሚያስገርሙ ነበሩ። ለአሜሪካ መንግሥት ትሰልላለህ ተብዬ ተከሰስኩ። ከዚያም በብራንደበርግ ወደሚገኘው ከሁሉ ወደከፋው የሽታዚ እስር ቤት ላኩኝ።
ከመንፈሳዊ ወንድሞቼ የተደረገልኝ እርዳታ
በዚያ እስር ቤት ቀን ቀን የሽታዚ ፖሊሶች እንድተኛ አይፈቅዱልኝም ነበር። ሌሊቱን ሙሉ ደግሞ ሲመረምሩኝ ያድራሉ። ለጥቂት ቀናት ያህል በዚህ መንገድ ሲያሰቃዩኝ ከቆዩ በኋላ ሁኔታዎቹ እየተባባሱ ሄዱ። አንድ ቀን ጠዋት ታስሬ ወደነበርኩበት ክፍል በመውሰድ ፋንታ ዩ-ቦት ሴለን (ምድር ቤት ውስጥ የሚገኙ ቦታዎች ስለነበሩ ከባሕር በታች ያሉ ክፍሎች ተብለው ይጠሩ ነበር) ተብለው ከሚጠሩት መጥፎ ክፍሎች ወደ አንዱ ወሰዱኝ። አንድ ያረጀና የዛገ የብረት በር ከፈቱና ወደ ውስጥ እንድገባ አዘዙኝ። አንድ ትልቅ ደፍ ተራምጄ ወደ ውስጥ መግባት ነበረብኝ። እግሬን ወደ ታች ስሰድ ወለሉ በሙሉ በውኃ የተሸነፈ እንደሆነ ተረዳሁ። በሩ ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ድምፅ በማሰማት በኃይል ተወርውሮ ተዘጋ። ብርሃንም ሆነ መስኮት የሚባል ነገር አልነበረም። ድቅድቅ ጨለማ የዋጠው ክፍል ነበር።
ወለሉ ላይ የነበረው ውኃ የተወሰነ ኢንች ያህል ከፍታ ስለነበረው መቀመጥ፣ ጋደም ማለትም ሆነ መተኛት አልችልም ነበር። ቀኑ የዓመት ያህል ረዝሞብኝ ስጠባበቅ ከቆየሁ በኋላ በጣም ኃይለኛ ብርሃን ወዳለበት ቦታ ተወስጄ ተጨማሪም ምርመራ ተደረገብኝ። በድቅድቅ ጨለማ በተዋጠ ስፍራ ሙሉ ቀን ውኃ ውስጥ ከመቆምና እኔ ላይ ባነጣጠሩ ኃይለኛ የባውዛ መብራቶች ሙሉ ሌሊት እየተሠቃዩ ከማሳለፍ የትኛው የከፋ እንደሆነ ለመናገር ያስቸግረኛል።
እንረሽንሃለን እያሉ በተደጋጋሚ ጊዜያት ያስፈራሩኝ ነበር። ለጥቂት ቀናት ሌሊት ሌሊት ሲመረምሩኝ ከቆዩ በኋላ አንድ ቀን ጠዋት ከፍተኛ ሥልጣን ወዳለው የሩስያ ወታደራዊ ሹም ፊት ቀረብኩ። ይህን ያገኘሁትን አጋጣሚ በመጠቀም የጀርመን ሽታዚ ከናዚ ጌስታፖዎች የከፋ ድርጊት እየፈጸሙብኝ እንደሆነ ነገርኩት። የይሖዋ ምሥክሮች በናዚ አገዛዝ ዘመን ገለልተኞች እንደነበሩና አሁንም በኮሙኒስቱ አገዛዝ ወቅት ገለልተኞች እንደሆኑ፣ በተጨማሪም በየትኛውም የዓለም ክፍል ብንገኝ በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ እንደማንገባ ገለጽኩለት። በአንጻሩ ግን በአሁኑ ጊዜ የሽታዚ መኮንኖች ሆነው የሚሠሩት ብዙዎቹ ሰዎች የሂትለር ወጣቶች ድርጅት አባላት እንደነበሩና ምንም ጥፋት ያልሠሩ ንጹሐን ሰዎችን ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ እንዴት ማሠቃየት እንደሚችሉ የተማሩት ከዚያ ሳይሆን እንደማይቀር ነገርኩት። ስናገር ሰውነቴ በቅዝቃዜ፣ በረሃብና በድካም ዝሎ ይንዘፈዘፍ ነበር።
የሩስያው ሹም አለመቆጣቱ የሚያስገርም ነበር። ከዚህ ይልቅ ብርድ ልብስ እላዬ ላይ ደረበልኝና ደግነት በተሞላበት ሁኔታ አነጋገረኝ። እሱ ካነጋገረኝ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ወደተሻለ ክፍል ተዛወርኩ። ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ ጀርመን ፍርድ ቤት ቀረብኩ። ጉዳዬ በቀጠሮ እየታየ በነበረበት ወቅት አንድ የእስር ቤት ክፍል ከሌሎች አምስት ምሥክሮች ጋር የመጋራት መብት በማግኘቴ ተደስቻለሁ። ብዙ አረመኔያዊ ድርጊቶችን ችዬ ካሳለፍኩ በኋላ ከመንፈሳዊ ወንድሞቼ ጋር መገናኘት በመቻሌ መንፈሴ እጅግ ተነቃቅቷል!—መዝሙር 133:1
ፍርድ ቤቱ በስለላ ድርጊት ወንጀለኛ ሆነህ ተገኝተሃል ብሎ ለአራት ዓመት ወኅኒ ቤት እንድወርድ ፈረደብኝ። ይህ ቀለል ያለ ፍርድ ተደርጎ የሚታይ ነበር። አንዳንድ ወንድሞች ከአሥር ዓመታት በላይ እንዲታሠሩ ተፈርዶባቸዋል። ይህ ፍርድ ከተላለፈብኝ በኋላ ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግበት ወኀኒ ቤት ወረድኩ። ጥበቃው በጣም ጥብቅ ስለነበረ አይጥ እንኳን ወደ እስር ቤቱ መግባት ወይም መውጣት የምትችል አይመስልም። ሆኖም በይሖዋ እርዳታ አንዳንድ ደፋር ወንድሞች ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በድብቅ ወደ ወኅኒ ቤቱ ማስገባት ችለው ነበር። እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱሱ መጽሐፍ ለየብቻው የተገነጣጠለ ሲሆን ታስረው የነበሩት ወንድሞች እየተቀባበሉ ያነቡት ነበር።
መጽሐፉን መቀባበል የቻልነው እንዴት ነው? ይህን ማድረጉ በጣም ከባድ ነበር። እርስ በርስ የምንገናኘው በየሁለት ሳምንቱ ገላችንን ወደምንታጠብበት ቦታ ስንወሰድ ብቻ ነበር። አንድ ጊዜ ገላዬን እየታጠብኩ ሳለ አንድ ወንድም ወደ ጆሮዬ ተጠጋና ፎጣው ውስጥ ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ደብቆ እንዳመጣ በሹክሹክታ ነገረኝ። ስለዚህ ገላዬን ታጥቤ ስጨርስ የእኔን ሳይሆን የእሱን ፎጣ መውሰድ ነበረብኝ።
ይህ ወንድም ወደ ጆሮዬ ተጠግቶ ሲያንሾካሹክ ከዘቦቹ አንዱ ተመለከተውና በያዘው ቆመጥ ክፉኛ መታው። ፎጣውን ወዲያውኑ ይዤ ከሌሎቹ እስረኞች ጋር መቀላቀል ነበረብኝ። ደግነቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾቹን ስወስድ አልተያዝኩም። ብያዝ ኖሮ ግን የመንፈሳዊ ምግብ ፕሮግራማችን ይስተጓጎል ነበር። ይህን የመሰሉ ብዙ ተሞክሮዎች አጋጥመውናል። ሁልጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ እናነብ የነበረው ተደብቀንና በሕይወታችን ቆርጠን ነበር። “የማስተዋል ስሜቶቻችሁን ጠብቁ፣ ንቁም” የሚሉት የሐዋርያው ጴጥሮስ ቃላት ለነበርንበት ሁኔታ በጣም ተስማሚ ነበሩ።—1 ጴጥሮስ 5:8 NW
ባለ ሥልጣኖቹ በአንዳንድ ምክንያቶች የተነሣ በየጊዜው ከአንዱ ወኅኒ ቤት ወደ ሌላው ያዛውሩን ነበር። ከአራት ዓመታት በሚበልጡ ጊዜያት ውስጥ ወደ አሥር የተለያዩ ወኅኒ ቤቶች ተዛውሬያለሁ። ሆኖም በሄድኩበት እስር ቤት ሁሉ ወንድሞችን አገኝ ነበር። በየወኅኒ ቤቱ ለማገኛቸው ወንድሞች ሁሉ ጥልቅ ፍቅር አድሮብኝ ነበር፤ በመሆኑም ከእነሱ ተለይቼ ወደ ሌላ ወኅኒ ቤት በተዛወርኩ ቁጥር ልቤ በኀዘን ይዋጥ ነበር።
በመጨረሻ ወደ ላይፕሲግ ከተላኩ በኋላ ከእስር ቤት ተፈታሁ። ነጻ ስለቀቅ ከእስር ቤቱ ያስወጣኝ ዘብ ደህና ሁን አላለኝም፤ ከዚህ ይልቅ “ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደገና እናገኝሃለን” ነበር ያለኝ። ክፋት የተጠናወተው አእምሮው እንደገና እስር ቤት እንድገባ ነበር የተመኘልኝ። ብዙውን ጊዜ፣ በመዝሙር 124:2, 3 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ሐሳብ አስታውሰዋለሁ:- “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን ሰዎች በእኛ ላይ በተነሡ ጊዜ፣ ቁጣቸው በላያችን በነደደ ጊዜ፣ በዚያን ጊዜ ሕያዋን ሳለን በዋጡን ነበር።”
ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ነፃ ያወጣል
አሁን እንደገና ነፃ ሰው ሆንኩ። ከእስር ቤት ስፈታ መንትያ እህቴ የሆነችው ሩትና እህት ሄርታ ሽሌንዞግ በር ላይ ቆመው ተቀበሉኝ። በወኅኒ ቤት ባሳለፍኳቸው በእነዚያ ዓመታት ሁሉ ሄርታ በየወሩ አነስ ያለ የታሸገ ምግብ ትልክልኝ ነበር። እውነቴን ነው የምላችሁ፣ እነዚያን አነስተኛ የታሸጉ ምግቦች ባላገኝ ኖሮ እዚያው ወኅኒ ቤት ውስጥ እሞት ነበር። ይሖዋ በምሕረቱ ያስታውሳት።
ከእስር ከተፈታሁ ጊዜ ጀምሮ ይሖዋ ብዙ የአገልግሎት መብቶችን በመስጠት ባርኮኛል። ጀርመን ውስጥ በግሮኑ ከተማ እንደገና ልዩ አቅኚ ሆኜ ከማገልገሌም በላይ በጀርመን ተራሮች አካባቢ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ሰርቻለሁ። ከጊዜ በኋላ ሚስዮናውያንን በሚያሠለጥነው በጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ለ31ኛው ክፍል እንድመዘገብ ግብዣ ቀረበልኝ። የምረቃው ሥነ ሥርዓት የተካሄደው በ1958 የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ስብሰባ በተደረገበት በያንኪ ስታዲየም ነበር። በዚያ ለተሰበሰቡት ብዙ ወንድሞችና እህቶች ንግግር የማቅረብና አንዳንድ ተሞክሮዎቼን የመናገር ልዩ መብት አግኝቻለሁ።
ከምረቃው በኋላ ሚስዮናዊ ሆኜ ለማገልገል ወደ ቺሊ ተጓዝኩ። እዚያም በቺሊ ደቡባዊ ጠረፍ እንደገና የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ አገልግያለሁ። ቃል በቃል ወደ ምድር ዳርቻ ተልኬ ነበር ብዬ መናገር እችላለሁ። በ1962 ፓትሲ ቦይትናገል የምትባል አሜሪካ ቴክሳስ ውስጥ ከሚገኘው ሳን አንቶኒዮ ከተማ የመጣች አንዲት ደስ የምትል ሚስዮናዊ አገባሁ። ከእሷ ጋር ሆኜ ይሖዋን በማገልገል ብዙ አስደሳች ዓመታት አሳልፌያለሁ።
ከ70 ዓመት በሚበልጠው የሕይወት ዘመኔ ብዙ አስደሳችና ብዙ አሳዛኝ ነገሮች አጋጥመውኛል። መዝሙራዊው “የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፣ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 34:19) በ1963 ገና ቺሊ ውስጥ ሳለን ፓትሲና እኔ በሕፃን ሴት ልጃችን ሞት ከባድ ኀዘን ላይ ወደቅን። ከጊዜ በኋላ ፓትሲ በጣም በመታመሟ ወደ ቴክሳስ ተጓዝን። ገና የ43 ዓመት ሴት ሳለች በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ሞተች። ይሖዋ ውድ ሚስቴን በምሕረቱ እንዲያስታውሳት የዘወትር ጸሎቴ ነው።
አሁን ምንም እንኳ ዕድሜዬ የገፋና ጤናዬ የተጓደለ ቢሆንም ቴክሳስ ውስጥ በሚገኘው የብራዲ ጉባኤ ውስጥ የዘወትር አቅኚና ሽማግሌ ሆኜ የማገልገል መብት አግኝቻለሁ። ባሳለፍኩት ሕይወት ውስጥ የተለያዩ ደንቃራዎች እንዳጋጠሙኝና ወደፊትም ሌሎች ፈተናዎች ሊያጋጥሙኝ እንደሚችሉ እሙን ነው። ይሁን እንጂ እንደ መዝሙራዊው እኔም “አምላኬ፣ ከታናሽነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፤ እስከ ዛሬም ተኣምራትህን እነግራለሁ” ብዬ መናገር እችላለሁ።—መዝሙር 71:17
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
(1) በአሁኑ ጊዜ ሽማግሌና የዘወትር አቅኚ ሆኜ በማገልገል ላይ ነኝ (2) ከፓትሲ ጋር ከሠርጋችን በፊት የተነሳነው ፎቶ (3) በሄር ሽናይደር ክፍል ውስጥ (4) ራቨንስብሩክ ውስጥ የሞተችው እናቴ፣ ተሬዛ